‘በልጅነት ሚስትህ ደስ ይበልህ’
“በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። . . . ልጄ ሆይ፤ በአመንዝራ ሴት ፍቅር ለምን ትሰክራለህ?”—ምሳሌ 5:18, 20
1, 2. በባልና ሚስት መካከል ያለው ፍቅር የተባረከ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾታ ግንኙነት በግልጽ ይናገራል። ምሳሌ 5:18, 19 እንዲህ ይላል:- “ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤ ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።”
2 እዚህ ላይ “ምንጭ” የሚለው ቃል በጾታ ግንኙነት የሚገኘውን እርካታ ያመለክታል። በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚኖረው ፍቅርና የሚያገኙት እርካታ የአምላክ ስጦታ በመሆኑ ይህ ምንጭ የተባረከ እንደሆነ ተገልጿል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ቅርርብ ሊኖር የሚገባው በጋብቻ ውስጥ ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረውና የምሳሌን መጽሐፍ የጻፈው ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፤ በአመንዝራ ሴት ፍቅር ለምን ትሰክራለህ? የሌላዪቱንስ ሴት ብብት ስለ ምን ታቅፋለህ?” በማለት ጠይቋል።—ምሳሌ 5:20
3. (ሀ) በርካታ ጋብቻዎች ምን አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሟቸዋል? (ለ) አምላክ ምንዝርን እንዴት ይመለከተዋል?
3 አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ አንዳቸው ሌላውን ለማፍቀርና ታማኝ ሆነው ለመኖር በሠርጋቸው ዕለት ቃል ይገባሉ። ያም ሆኖ ግን በርካታ ትዳሮች በምንዝር ምክንያት ይፈርሳሉ። እንዲያውም ከ20 በላይ የሚሆኑ ጥናቶችን የተመለከቱ አንዲት ተመራማሪ “25 በመቶ የሚሆኑት ሚስቶችና 44 በመቶ የሚሆኑት ባሎች ከጋብቻቸው ውጭ የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ምንዝር በአምላክ ፊት ከባድ ኃጢአት መሆኑ የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም። በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮች በጋብቻ ውስጥ ታማኝነታቸውን ላለማጉደል መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ‘ጋብቻ እንዲከበርና መኝታውም ንጹሕ’ እንዲሆን ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?—ዕብራውያን 13:4
ተንኰለኛው ልብ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
4. አንድ ያገባ ክርስቲያን ሳይታወቀው ከጋብቻው ውጭ የፍቅር ግንኙነት እንዲመሠርት ሊያደርጉት የሚችሉ ምን ሁኔታዎች አሉ?
4 በሥነ ምግባር በዘቀጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙዎች “ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም።” (2 ጴጥሮስ 2:14) እንደዚህ ያሉት ሰዎች ሆን ብለው ከትዳራቸው ውጭ የፍቅር ግንኙነት ይጀምራሉ። በአንዳንድ አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከቤታቸው ውጭ መሥራት መጀመራቸው ከተቃራኒ ጾታ ጋር አብሮ የመዋል አጋጣሚ እንዲኖር አድርጓል፤ ይህም በሥራ ቦታ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። ከዚህም በላይ በጣም ዓይናፋር የሆኑ ሰዎች እንኳ በኢንተርኔት ቻት ሩም አማካኝነት በቀላሉ የፍቅር ግንኙነት መመሥረት ችለዋል። በርካታ ያገቡ ሰዎች ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እየገቡ እንዳሉ ሳይገነዘቡት እንዲህ ባለው ወጥመድ ይወድቃሉ።
5, 6. አንዲት ክርስቲያን አደገኛ በሆነ ወጥመድ ውስጥ የገባችው እንዴት ነው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
5 ሜሪ የተባለች (እውነተኛ ስሟ አይደለም) አንዲት ክርስቲያን የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም ሊያደርሳት ይችል በነበረ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንደገባች እንመልከት። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቷ ለቤተሰቡ እምብዛም ፍቅር አያሳይም ነበር። ሜሪ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የባለቤቷ የሥራ ባልደረባ ከሆነ ሰው ጋር እንደተዋወቀች ታስታውሳለች። ሰውየው ጨዋ ከመሆኑም በላይ ስለ ሜሪ ሃይማኖት ማወቅ እንደሚፈልግ ቆየት ብሎ ገለጸላት። ሜሪ “በጣም ጥሩ ሰው ነው፤ ባሕርይውም ከባለቤቴ ፈጽሞ የተለየ ነው” በማለት ትናገራለች። ብዙም ሳይቆይ ሜሪና የባለቤቷ የሥራ ባልደረባ ተዋደዱ። ሜሪ “ምንዝር አልፈጸምኩም፤ ደግሞም ሰውየው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ይፈልጋል። ምናልባትም ልረዳው እችል ይሆናል” ብላ ታስብ ነበር።
6 ደግነቱ ግን፣ ሜሪ ከሰውየው ጋር የጀመረችው የፍቅር ግንኙነት ወደ ምንዝር ከማምራቱ በፊት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ተገነዘበች። (ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 4:19) ሕሊናዋ መሥራት በመጀመሩ አካሄዷን አስተካከለች። የሜሪ ተሞክሮ፣ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ” መሆኑን ያሳያል። (ኤርምያስ 17:9) መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 4:23) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
‘አስተዋይ ሰው መጠጊያ ይሻል’
7. በጋብቻው ውስጥ ችግሮች ያጋጠሙትን ሰው በምትረዱበት ወቅት የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መከተል ጥበቃ ይሆናል?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ “ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) እንዲሁም ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። ከልክ በላይ በራስ በመተማመን ‘ምንም አልሆንም’ ብሎ ከማሰብ ይልቅ አንዳንድ ሁኔታዎች እንዴት ወደ ችግር ሊመሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ ማሰቡ ጥበብ ነው። ለአብነት ያህል፣ በጋብቻው ውስጥ ከባድ ችግሮች ላጋጠሙት ተቃራኒ ጾታ ያለው ሰው ምስጢረኛ ከመሆን ተቆጠቡ። (ምሳሌ 11:14) ግለሰቡ በጋብቻው ውስጥ ያጋጠመውን ችግር ከትዳር ጓደኛው፣ ጋብቻው እንዲሰምር ከሚፈልግ ተመሳሳይ ጾታ ካለው የጎለመሰ ክርስቲያን አሊያም ከሽማግሌዎች ጋር ቢወያይበት የተሻለ እንደሚሆን ንገሩት። (ቲቶ 2:3, 4) በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። አንድ ሽማግሌ ከአንዲት ክርስቲያን ጋር በግል መወያየት ካስፈለገው ይህን የሚያደርገው እንደ መንግሥት አዳራሽ ባለ ብዙ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ነው።
8. በሥራ ቦታ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል?
8 በሥራ ቦታም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የፍቅር ግንኙነት ወደ መመሥረት ሊያደርሱ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። ለምሳሌ፣ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ከሥራ ሰዓት ውጭ ተቀራርቦ መሥራት ለፈተና ሊዳርግ ይችላል። ያገባችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከትዳር ጓደኛችሁ ውጭ ከማንም ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈቃደኛ አለመሆናችሁን በንግግራችሁም ሆነ በአኳኋናችሁ በግልጽ ማሳየት ይኖርባችኋል። ለአምላክ ያደራችሁ ሰዎች ስለሆናችሁ ሌሎችን በማሽኮርመምም ሆነ ተገቢ ባልሆነ አለባበስና አጋጌጥ አላስፈላጊ ትኩረት መሳብ እንደማትፈልጉ ጥያቄ የለውም። (1 ጢሞቴዎስ 4:8 NW፤ 6:11 NW፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4) የትዳር ጓደኛችሁንና የልጆቻችሁን ፎቶግራፍ በሥራ ቦታችሁ ማስቀመጣችሁ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጧቸው ሰዎች መኖራቸውን እናንተም ሆናችሁ ሌሎች እንድታስታውሱ ይረዳችኋል። ሌሎች ሰዎች እናንተን በፍቅር ለመማረክ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉበት የሚያበረታታ አዝማሚያ ላለማሳየትና ሌላው ቀርቶ ድርጊታቸውን በዝምታ ላለማለፍም ጭምር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።—ኢዮብ 31:1
“ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ”
9. አንድን አዲስ የፍቅር ግንኙነት ማራኪ የሚያደርገው የየትኞቹ ሁኔታዎች መገጣጠም ሊሆን ይችላል?
9 ልብን ለመጠበቅ ከአደገኛ ሁኔታዎች መራቅ ብቻ በቂ አይደለም። ያገቡ ሰዎች ከጋብቻቸው ውጭ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት መፈለጋቸው አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት ለትዳር ጓደኛቸው ፍላጎት ትኩረት እንዳልሰጡ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። አንዲት ሚስት ሁልጊዜ ችላ ትባል ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ባል ዘወትር ትችት ይሰነዘርበት ይሆናል። በዚህ መሃል በሥራ ቦታ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚያገኟቸው ሌሎች ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸው የጎደሏቸውን ባሕርያት ሲያንጸባርቁ ይመለከታሉ። ብዙም ሳይቆይ ቅርርብ ይፈጠርና አዲሱ ግንኙነት ለማቆም አስቸጋሪ እስከሚሆን ድረስ በጣም ማራኪ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች አንድ ላይ ሲገጣጠሙ የሚያስከትሉት ስውር አደጋ “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል።—ያዕቆብ 1:14
10. ባልና ሚስቶች ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚችሉት እንዴት ነው?
10 ባልና ሚስቶች የሚወዳቸው፣ ጓደኛ የሚሆናቸው አሊያም ችግር ሲገጥማቸው የሚደግፋቸው ሰው ለማግኘት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከሌላ ሰው ጋር ለመቀራረብ ከመሞከር ይልቅ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ፍቅራቸውን ለማጠናከር መጣር ይኖርባቸዋል። እንግዲያው አብራችሁ ጊዜ በማሳለፍ እርስ በርስ ተቀራረቡ። መጀመሪያ እንድትፋቀሩ ባደረጓችሁ ነገሮች ላይ አሰላስሉ። የትዳር ጓደኛችሁ ለሆነው ሰው የነበራችሁን የፍቅር ስሜት እንደገና ለማደስ ጥረት አድርጉ። አብራችሁ ያሳለፋችኋቸውን አስደሳች ጊዜያት መለስ ብላችሁ አስቡ። ስለ ጉዳዩ ወደ አምላክ ጸልዩ። መዝሙራዊው ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ይሖዋን ተማጽኖታል። (መዝሙር 51:10) ‘አምላክ ከፀሓይ በታች በሰጠህ የሕይወት ዘመን ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ’ የሚለውን ጥቅስ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።—መክብብ 9:9
11. እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል የጋብቻን ጥምረት በማጠናከር ረገድ ምን ሚና ይጫወታሉ?
11 የጋብቻን ጥምረት በማጠናከር ረገድ እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል ያላቸው ጠቃሚ ድርሻም ችላ ሊባል አይገባም። ምሳሌ 24:3, 4 “ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል፤ በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ ክፍሎቹ ይሞላሉ” ይላል። አንድን ደስተኛ ቤተሰብ ከሚሞሉት ውድ ነገሮች መካከል እንደ ፍቅር፣ ታማኝነት፣ አምላካዊ ፍርሃትና እምነት ያሉት ባሕርያት ይገኙበታል። እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር አምላክን ማወቅ ያስፈልጋል። እንግዲያው ያገቡ ሰዎች የአምላክን ቃል በቁም ነገር ማጥናት ይኖርባቸዋል። ጥበብና ማስተዋልስ ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው? በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ጥበብ ማለትም ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀትን ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ አስፈላጊ ነው። አስተዋይ የሆነ ሰው የትዳር ጓደኛውን ሐሳብና ስሜት መረዳት ይችላል። (ምሳሌ 20:5) ይሖዋ፣ በሰሎሞን በኩል “ልጄ ሆይ፤ ጥበቤን ልብ በል፤ የማስተዋል ቃሌንም በጥሞና አድምጥ” ብሏል።—ምሳሌ 5:1
‘በመከራ’ ወቅት
12. ያገቡ ሰዎች ችግሮች ቢያጋጥሟቸው አስገራሚ የማይሆነው ለምንድን ነው?
12 ፍጹም የሆነ ትዳር የለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችና ሚስቶች “በሥጋቸው ላይ መከራ” እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:28 የ1954 ትርጉም) ጭንቀት፣ ሕመም፣ ስደትና ሌሎች ሁኔታዎች በትዳር ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ። ሆኖም ችግሮች ሲፈጠሩ፣ ይሖዋን ለማስደሰት የሚጥሩ ታማኝ የትዳር ጓደኛሞች እንደሚያደርጉት አብራችሁ መፍትሔ መፈለግ ይኖርባችኋል።
13. ባልና ሚስት በየትኞቹ አቅጣጫዎች ራሳቸውን መመርመር ይችላሉ?
13 በጋብቻው ውስጥ ውጥረት የሰፈነው የትዳር ጓደኛሞቹ አንዳቸው ሌላውን በሚይዙበት መንገድ የተነሳ ቢሆንስ? መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ደግነት በጎደለው መንገድ መነጋገር አመል ሆኖባቸው ይሆናል። (ምሳሌ 12:18) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ይህ ዓይነቱ ልማድ በትዳር ውስጥ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ “ከጨቅጫቃና ከቍጡ ሚስት ጋር ከመኖር፣ በምድር በዳ መኖር ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 21:19) በእንደዚህ ዓይነት ትዳር ውስጥ ያለሽ ሚስት ከሆንሽ ‘ባለቤቴ አብሮኝ መሆን እንዲያስጠላው የሚያደርግ ባሕርይ አለኝ?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ። መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች “ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” የሚል ምክር ይዟል። (ቈላስይስ 3:19) ስለዚህ ባል ከሆንክ ‘ፍቅሬን የማልገልጽላት በመሆኔ ምክንያት ባለቤቴ ወደ ሌሎች ለመሄድ እንድትፈተን አደርጋታለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በእርግጥ የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም የሚያበቃ ምንም ሰበብ ሊኖር አይችልም። ያም ቢሆን ግን እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል መሆኑ ችግሮችን በግልጽ ለመወያየት የሚያነሳሳ ጥሩ ምክንያት ነው።
14, 15. ከጋብቻ ውጭ ግንኙነት መመሥረት በትዳር ውስጥ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት የማይረዳው ለምንድን ነው?
14 የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር በመቀራረብ መጽናኛ ለማግኘት መሞከር በጋብቻ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ አይሆንም። እንዲህ ያለው ግንኙነት ወዴት ሊያመራ ይችላል? ከበፊቱ የተሻለ አዲስ ትዳር ለመመሥረት ያስችላል? አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል። እንዲያውም ‘ይህ ሰው የትዳር ጓደኛዬ እንዲኖረው የምፈልጋቸው ባሕርያት አሉት’ ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ምክንያት ከእውነታው የራቀ ነው፤ የትዳር ጓደኛውን የሚተው ወይም እናንተ እንዲህ እንድታደርጉ የሚያበረታታ ማንኛውም ግለሰብ ቅዱስ ለሆነው የጋብቻ ጥምረት አክብሮት ይጎድለዋል። በመሆኑም ከእንዲህ ዓይነቱ ሰው ጋር የሚመሠረተው ግንኙነት የተሻለ ጋብቻ ያስገኛል ብሎ ማሰቡ ሞኝነት ነው።
15 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሜሪ አካሄዷ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በጥሞና አሰበችበት፤ የምትወስደው እርምጃ እሷም ሆነች ሌላው ግለሰብ የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ሊያደርግ እንደሚችልም አስተዋለች። (ገላትያ 6:7) እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ለባለቤቴ የሥራ ባልደረባ ያለኝን ስሜት መመርመር ስጀምር፣ ይህ ሰው የእውነትን እውቀት የመቀበል አዝማሚያ ቢኖረው እንኳ የእኔ አድራጎት እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ተገነዘብኩ። ኃጢአት መፈጸም በድርጊቱ የተካፈሉትን ሰዎች የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ሌሎችን ያሰናክላል!”—2 ቆሮንቶስ 6:3
ከሁሉ የላቀው ምክንያት
16. የሥነ ምግባር ብልግና የሚያስከትላቸው አንዳንድ መዘዞች ምንድን ናቸው?
16 መጽሐፍ ቅዱስ “የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤ አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤ በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመራለች፤ ሁለት አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 5:3, 4) የሥነ ምግባር ብልግና ሥቃይና ይባስ ብሎም ሞት ሊያስከትል ይችላል። እንዲህ ያለው ድርጊት ለሕሊና ሥቃይና በጾታ ብልግና ለሚተላለፉ በሽታዎች የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ ታማኝ የሆነውን ግለሰብ ስሜት ይጎዳል። ይህን ማሰባችን በጋብቻ ውስጥ ታማኝነትን ወደ ማጉደል የሚመራ አካሄድ እንዳንከተል ምክንያት ይሆነናል።
17. በጋብቻ ውስጥ ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ሊያነሳሳን የሚገባው ጠንካራ ምክንያት ምንድን ነው?
17 በጋብቻ ውስጥ ታማኝነትን ማጉደል ስሕተት የሆነበት ዋነኛው ምክንያት፣ የጋብቻ መሥራች የሆነውና የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ችሎታ የሰጠን ይሖዋ እንዲህ ያለውን ድርጊት ስለሚጠላው ነው። ይሖዋ፣ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት “ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ . . . በአመንዝራዎች . . . ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሚልክያስ 3:5) ምሳሌ 5:21 “የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ ነውና፤ እርሱ መሄጃውን ሁሉ ይመረምራል” ይላል። በእርግጥም “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።” (ዕብራውያን 4:13) እንግዲያው ታማኝነትን ማጉደል ምንም ያህል በምስጢር ቢፈጸም እንዲሁም የሚያስከትለው አካላዊም ሆነ ማኅበራዊ መዘዝ የቱንም ያህል ትንሽ ቢመስል እንዲህ ያለው ድርጊት ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል፤ ለትዳራችን ምንጊዜም ታማኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው።
18, 19. ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት ጋር በተያያዘ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 የያዕቆብ ልጅ የሆነው የዮሴፍ ምሳሌ፣ ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ጥሩ ግንኙነት እንዳይበላሽ ያለን ፍላጎት እንዲህ ያለውን ድርጊት ከመፈጸም እንድንቆጠብ ሊያደርገን እንደሚችል ያሳያል። ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ በነበረው በጲጥፋራ ዘንድ ሞገስ ያገኘው ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤት ውስጥ የተከበረ ቦታ ተሰጥቶት ነበር። ዮሴፍ “ጥሩ ቊመና ያለውና መልከ መልካም” ስለነበር የጲጥፋራ ሚስት ዓይኗን ጣለችበት። ዮሴፍን በመማረክ ከእርሷ ጋር የጾታ ብልግና እንዲፈጽም ለማድረግ በየዕለቱ ብትጥርም ሊሳካላት አልቻለም። ዮሴፍ በማባበያዎቿ እንዳይሸነፍ የረዳው ምን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ ‘ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት [ሰጠኝ፣] . . . እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?’”—ዘፍጥረት 39:1-12
19 ዮሴፍ ያላገባ ቢሆንም ከሌላ ሰው ሚስት ጋር የጾታ ብልግና ለመፈጸም አሻፈረኝ በማለት የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ጠብቋል። ምሳሌ 5:15 “ከገዛ ማጠራቀሚያህ ውሃ፣ ከገዛ ጕድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ” ይላል። አስባችሁበት ባይሆንም እንኳ ከትዳራችሁ ውጭ የፍቅር ግንኙነት ከመመሥረት ራቁ። በጋብቻችሁ ውስጥ ፍቅራችሁን ለማጠናከር ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ችግር ቢፈጠር ለመፍታት ጠንክራችሁ ሥሩ። ምንጊዜም ቢሆን ‘በልጅነት ሚስትህ ደስ ይበልህ’ የሚለውን ምክር ተግባራዊ አድርጉ።—ምሳሌ 5:18
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• አንድ ክርስቲያን ሳያስበው በፍቅር ግንኙነት ሊጠመድ የሚችለው እንዴት ነው?
• አንድ ግለሰብ የትዳር ጓደኛው ካልሆነ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ከመመሥረት ለመቆጠብ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይችላል?
• የተጋቡ ሰዎች ችግር ሲያጋጥማቸው ምን ማድረግ አለባቸው?
• በትዳር ውስጥ ታማኝነትን ለመጠበቅ ጠንካራ ምክንያት ሊሆን የሚገባው ምንድን ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሥራ ቦታ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ አሳዛኝ ነው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በዕውቀትም ክፍሎቹ ውብ በሆነ ንብረት ይሞላሉ’