ክርስቲያኖች ትዳራቸውን የሰመረ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
“ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ . . . ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌ. 5:33
1. ጋብቻ ብዙውን ጊዜ ጅምሩ አስደሳች ቢሆንም ባለትዳሮች ምን እንደሚያጋጥማቸው ሊጠብቁ ይችላሉ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
አንዲት ሙሽራ በሠርጓ ዕለት አምራና ደምቃ ከሙሽራው ጋር በምትገናኝበት ጊዜ ሁለቱም የሚሰማቸውን ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ተጋቢዎቹ፣ በመጠናናት ባሳለፉት ጊዜ ፍቅራቸው እያደገ በመምጣቱ አሁን አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ሆነው ለመኖር ቃል ሊገቡ ተዘጋጅተዋል። እርግጥ ነው፣ ሁለት ሰዎች ጎጆ ወጥተው አብረው መኖር ሲጀምሩ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። ጋብቻን ያቋቋመው አፍቃሪ አምላክ፣ ሁሉም ባለትዳሮች በትዳር ሕይወታቸው ደስተኛ እንዲሆኑና ጋብቻቸው እንዲሰምር ስለሚፈልግ ማግባት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲመሩበት ሲል በቃሉ ውስጥ ጥበብ ያዘለ ምክር አስፍሯል። (ምሳሌ 18:22) ያም ቢሆን ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ፍጹም ያልሆኑ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በግልጽ ይናገራሉ። (1 ቆሮ. 7:28) እንዲህ ያለውን መከራ ለመቀነስ ምን ማድረግ ይቻላል? ክርስቲያኖች ትዳራቸው እንዲሰምር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
2. የትዳር ጓደኛሞች የትኞቹን የፍቅር ዓይነቶች ማንጸባረቅ ያስፈልጋቸዋል?
2 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ሊያሳዩአቸው የሚገቡ የተለያዩ የፍቅር ዓይነቶች አሉ። ለምሳሌ፣ አንዳቸው ሌላውን መውደድ (በግሪክኛ ፊሊያ) ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚኖረውን ዓይነት ፍቅር (ኤሮስ) ማሳየታቸው ደስታ ያስገኝላቸዋል። ልጆች ከወለዱ ደግሞ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚኖረውን ፍቅር (ስቶርጌ) ማንጸባረቃቸው አስፈላጊ ነው። ይሁንና ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራው ፍቅር (አጋፔ) ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ዓይነቱን ፍቅር በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌ. 5:33
በትዳር ውስጥ የባልና የሚስት ድርሻ
3. ባልና ሚስት ምን ያህል ጠንካራ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል?
3 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ራሱን ለጉባኤው አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:25) የኢየሱስ ተከታዮች እሱን መምሰል ከፈለጉ፣ እሱ እንደወደዳቸው እርስ በርሳቸው መዋደድ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን እና 15:12, 13ን አንብብ።) በመሆኑም ክርስቲያን ባለትዳሮች፣ አስፈላጊ ከሆነ አንዳቸው ለሌላው ሕይወታቸውን እንኳ ለመስጠት የሚያነሳሳ ጠንካራ ፍቅር ማዳበር ይኖርባቸዋል። በባልና ሚስት መካከል ከባድ አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ ግን እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት ይከብዳቸው ይሆናል። ይሁንና አጋፔ የተባለው ፍቅር “ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” በእርግጥም “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” (1 ቆሮ. 13:7, 8) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ባልና ሚስት፣ የትዳር ጓደኛቸውን ለማፍቀርና አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን ቃል እንደገቡ ማስታወሳቸው የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ችግር ላቅ ካሉት የይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመፍታት ተባብረው እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል።
4, 5. (ሀ) አንድ ባል የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ምን ኃላፊነት አለበት? (ለ) አንዲት ሚስት ስለ ራስነት ሥልጣን ምን አመለካከት ሊኖራት ይገባል? (ሐ) አንድ ባልና ሚስት ምን ዓይነት የአመለካከት ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል?
4 ጳውሎስ እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ያለበትን ኃላፊነት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ አካሉ ለሆነውና አዳኙ ለሆነለት ጉባኤ ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው።” (ኤፌ. 5:22, 23) ባል የሚስቱ ራስ መሆኑ፣ ሚስት የባሏ የበታች እንድትሆን አያደርጋትም። እንዲያውም አምላክ ለሚስት ያሰበውን ድርሻ ለመወጣት ያስችላታል፤ አምላክ ሴትን ሲፈጥር “[አዳም] ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም። ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 2:18) ‘የጉባኤ ራስ’ የሆነው ክርስቶስ ፍቅር እንደሚያሳይ ሁሉ አንድ ክርስቲያን ባልም የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር ሊጠቀምበት ይገባል። ባል እንዲህ ሲያደርግ ሚስቱ ከስጋት ነፃ ትሆናለች፤ እንዲሁም ባሏን ማክበር፣ እሱን መደገፍና ለእሱ መገዛት ያስደስታታል።
5 ካቲ፣[1] ትዳር ከመሠረተች በኋላ ማስተካከያ ማድረግ እንዳስፈለጋት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ከማግባቴ በፊት የሌላ ሰው እገዛ ሳያስፈልገኝ ሁሉን ነገር በራሴ እወስን ነበር። ትዳር ከመሠረትኩ በኋላ ግን አንዳንድ ውሳኔዎችን ባለቤቴ እንዲያደርግ መጠበቅ እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ በአመለካከቴ ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጎኛል። ይህን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ሆኖልኛል ማለት አይደለም፤ ይሁንና ነገሮችን በይሖዋ መንገድ ማከናወናችን እርስ በርስ ይበልጥ እንድንቀራረብ ረድቶናል።” ባለቤቷ ፍሬድ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ውሳኔ ማድረግ ለእኔ ምንጊዜም ከባድ ነበር። ካገባሁ በኋላ ደግሞ ሁለት ሰዎችን ግምት ውስጥ አስገብቶ መወሰን ነገሩን ይበልጥ ያከብደዋል። ሆኖም ይሖዋ እንዲረዳኝ በጸሎት መጠየቄና የባለቤቴን ሐሳብ ማዳመጤ ይህ ኃላፊነት እየቀለለኝ እንዲሄድ አድርጓል። ከባለቤቴ ጋር ተቀናጅተን እንደምንሠራ ይሰማኛል!”
6. በትዳር ውስጥ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
6 ጠንካራ ትዳር፣ አንዳቸው የሌላውን ስህተት በትዕግሥት የሚያልፉ ባልና ሚስት ጥምረት ነው። እንዲህ ያሉ ባልና ሚስት ‘እርስ በርስ ይቻቻላሉ፤ እንዲሁም በነፃ ይቅር ይባባላሉ።’ እርግጥ ነው፣ ሁለቱም ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ባልና ሚስት ከስህተታቸው መማር፣ የትዳር ጓደኛቸውን ይቅር ማለት እንዲሁም “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነውን ፍቅር ማሳየት ይችላሉ። (ቆላ. 3:13, 14) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4, 5) አለመግባባቶች በተቻለ ፍጥነት መፈታት አለባቸው። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት በመካከላቸው ለተፈጠረው ለማንኛውም ቅራኔ፣ ጀምበር ሳትጠልቅ እልባት ማበጀት ይኖርባቸዋል። (ኤፌ. 4:26, 27) “ስላስከፋሁህ ይቅርታ አድርግልኝ” ብሎ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ትሕትና እና ድፍረት ይጠይቃል፤ ይሁንና የትዳር ጓደኛሞች እንዲህ ማድረጋቸው ችግሮችን በመፍታት ብሎም በመካከላቸው ያለውን ጥምረት በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
አሳቢነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው
7, 8. (ሀ) በትዳር ውስጥ የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል? (ለ) የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት ማሳየት ያለባቸው ለምንድን ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባለትዳሮች ለትዳር ጓደኛቸው የሚገባውን ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 7:3-5ን አንብብ።) ባለትዳሮች በፍቅር ተነሳስተው አንዳቸው ለሌላው ስሜትና ፍላጎት አሳቢነት ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ባል ለሚስቱ አሳቢነት የማያሳያት ከሆነ ሚስቱ በፆታ ግንኙነት መደሰት አስቸጋሪ ሊሆንባት ይችላል። ባሎች ሚስቶቻቸውን “በእውቀት” እንዲይዟቸው ተመክረዋል። (1 ጴጥ. 3:7) የፆታ ግንኙነት አንደኛው ወገን ሳይፈልግ ወይም ተገዶ የሚደረግ ነገር መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ደስ እያላቸው ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወንዱ ከሴቷ ይልቅ ቶሎ ስሜቱ ሊነሳሳ ቢችልም የእሷም ስሜት እስኪነሳሳ ድረስ ጊዜ መስጠት ይኖርበታል።
8 መጽሐፍ ቅዱስ በባልና ሚስት መካከል ከሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ የፍቅር መግለጫዎች ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚገባ ወይም እስከ ምን ድረስ መሄድ እንደሚቻል ዝርዝር መመሪያ ባይሰጥም አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎችን ይጠቅሳል። (መኃ. 1:2፤ 2:6) ክርስቲያን ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት ማሳየት አለባቸው።
9. የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ማንኛውም ሰው የፆታ ስሜት እንዲያድርብን መፍቀድ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
9 ለአምላክና ለሌሎች ጥልቅ ፍቅር ካለን ማንኛውም ሰው ወይም ነገር በትዳራችን ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም። አንዳንድ ባለትዳሮች የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን (ፖርኖግራፊ) የማየት ወይም የማንበብ ልማድ ስለተጠናወታቸው፣ በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ከመፈጠራቸውም አልፎ ትዳራቸው እስከ መፍረስ ደርሷል። ፖርኖግራፊ የማየት ጉጉትም ሆነ ከትዳር ጓደኛችን ውጭ በማንኛውም መንገድ የፆታ ስሜትን የማርካት ፍላጎት እንዲያድርብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። የትዳር ጓደኛችን ያልሆነን ሰው እያሽኮረመምን እንዳለን የሚያስመስል ነገር ማድረግ እንኳ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ስለሆነ ልንርቀው ይገባል። አምላክ የምናስበውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንደሚያውቅ ማስታወሳችን፣ እሱን የሚያሳዝን ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ያስችለናል።—ማቴዎስ 5:27, 28ን እና ዕብራውያን 4:13ን አንብብ።
በትዳር ውስጥ ችግሮች ሲፈጠሩ
10, 11. (ሀ) ፍቺ ምን ያህል ተስፋፍቷል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛ ጋር ስለ መለያየት ምን ይላል? (ሐ) የትዳር ጓደኛሞች ለመለያየት እንዳይቸኩሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
10 አንድ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ እልባት ያላገኘ ከባድ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ከሁለት አንዳቸው አሊያም ሁለቱም ለመለያየት ወይም ለመፋታት ሊያስቡ ይችላሉ። በአንዳንድ አገሮች ትዳር ከሚመሠርቱት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ይፋታሉ። ይህ ችግር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያን ያህል ጎልቶ የሚታይ ባይሆንም በክርስቲያኖች ትዳር ውስጥ የሚፈጠሩት ችግሮች እየጨመሩ መምጣታቸው አሳሳቢ ነው።
11 መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መመሪያ ይሰጣል፦ “ሚስት ከባሏ አትለያይ። ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።” (1 ቆሮ. 7:10, 11) ባለትዳሮች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር መለያየትን እንደ ቀላል ነገር ሊያዩት አይገባም። በትዳር ውስጥ ከባድ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ መለያየት መፍትሔ ቢመስልም እንዲህ ማድረጉ በአብዛኛው ተጨማሪ ችግሮች ያስከትላል። ይሖዋ፣ ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር እንደሚጣበቅ ተናግሯል፤ ኢየሱስም ይህን ሐሳብ በድጋሚ ከተናገረ በኋላ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:3-6፤ ዘፍ. 2:24) ይህ ጥቅስ ባልና ሚስት ራሳቸውም ቢሆኑ ‘አምላክ ያጣመረውን መለያየት’ እንደሌለባቸው ያጎላል። በይሖዋ ፊት ጋብቻ የዕድሜ ልክ ጥምረት ነው። (1 ቆሮ. 7:39) ማናችንም ብንሆን በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን፤ ባለትዳሮች ይህን ማስታወሳቸው፣ ችግሮች ተባብሰው ከባድ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ዛሬ ነገ ሳይሉ መፍትሔ ለማግኘት ከልባቸው ጥረት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
12. አንድ ሰው ከትዳር ጓደኛው ጋር ለመለያየት እንዲያስብ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
12 በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች መንስኤው የትዳር ጓደኛሞች ከእውነታው የራቁ ነገሮችን መጠበቃቸው ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ትዳሩ አስደሳች እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ ይህ እውን ሳይሆን ሲቀር እርካታ ሊያጣ፣ እንደተታለለ ሊሰማው አልፎ ተርፎም በምሬት ሊዋጥ ይችላል። ባልና ሚስት ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ተመሳሳይ አለመሆኑ ወይም በመካከላቸው የአስተዳደግ ልዩነት መኖሩ ችግሮች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከገንዘብ፣ ከአማቶች ወይም ከልጅ አስተዳደግ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ይሁንና አብዛኞቹ ክርስቲያን ባለትዳሮች የአምላክን መመሪያ ስለሚከተሉ፣ ለእነዚህ ችግሮች ሁለቱንም ወገኖች የሚያስማሙ መፍትሔዎችን ማግኘት ችለዋል፤ ይህም የሚያስመሰግናቸው ነው።
13. ለመለያየት እንደ በቂ ምክንያት ሊታዩ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
13 እርግጥ ነው፣ ለመለያየት የሚያበቁ በጣም ከባድ ሁኔታዎች የሚፈጠሩበት ጊዜ ይኖራል። አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ከባድ አካላዊ ጥቃት የሚያደርስባቸው በመሆኑ እንዲሁም መንፈሳዊነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በመፈጠሩ የተነሳ ለመለያየት በቂ ምክንያት እንዳላቸው ተሰምቷቸዋል። በትዳራቸው ውስጥ ከባድ ችግር ያጋጠማቸው ባለትዳሮች፣ ሽማግሌዎች እንዲረዷቸው መጠየቅ አለባቸው። ተሞክሮ ያላቸው እነዚህ ወንድሞች፣ ባለትዳሮች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ። በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ስንጥር፣ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ለማዋልና የመንፈስ ፍሬ ለማፍራት እንዲረዳን መጸለይም ይኖርብናል።—ገላ. 5:22, 23[2]
14. የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ላላቸው ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል?
14 አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ይኖራቸው ይሆናል። ሁኔታው እንዲህ ቢሆንም እንኳ አብረው መኖራቸው የተሻለ የሚሆንባቸው ምክንያቶች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:12-14ን አንብብ።) የይሖዋ አምላኪ ያልሆነው የትዳር ጓደኛ ቢገነዘበውም ባይገነዘበውም፣ አማኝ በሆነው የትዳር ጓደኛው የተነሳ “ተቀድሷል።” ልጆቻቸውም ቢሆኑ “ቅዱሳን” እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን መለኮታዊ ጥበቃ ያገኛሉ። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ?” (1 ቆሮ. 7:16) በሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ማለት ይቻላል ለትዳር ጓደኛቸው ‘መዳን’ ምክንያት የሆኑ ክርስቲያን ባለትዳሮች አሉ።
15, 16. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋይ ያልሆነ ባል ላላቸው ክርስቲያን ሚስቶች ምን ምክር ይሰጣል? (ለ) “አማኝ ያልሆነው ወገን ለመለየት ከመረጠ” አንድ ክርስቲያን ምን ያደርጋል?
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ምክር ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው።” አንዲት ሚስት “በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ” ማንጸባረቅ ይጠበቅባታል፤ ስለ እምነቷ አዘውትራ ከመናገር ይበልጥ ባሏን ወደ እውነተኛው አምልኮ የሚስበው ይህ ምግባሯ ሊሆን ይችላል።—1 ጴጥ. 3:1-4
16 ይሁንና አማኝ ያልሆነው የትዳር ጓደኛ ለመለያየት ቢወስንስ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አማኝ ያልሆነው ወገን ለመለየት ከመረጠ ይለይ፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምንም ዓይነት ግዴታ የለባቸውም፤ አምላክ የጠራችሁ ለሰላም ነውና።” (1 ቆሮ. 7:15) ይህ ሲባል ግን አማኝ የሆነው ወገን፣ እንደገና እንዲያገባ ቅዱስ ጽሑፉ ይፈቅድለታል ማለት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን የሆነው ባለትዳር፣ የማያምነው ወገን አብሮት እንዲኖር ለማስገደድ መሞከር አለበት ማለትም አይደለም። መለያየታቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሰላም እንዲሰፍን ሊያደርግ ይችላል። ለመለያየት የወሰነው የትዳር ጓደኛ፣ ከጊዜ በኋላ ተመልሶ በትዳራቸው ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ፈቃደኛ ሊሆን አልፎ ተርፎም የአምላክ አገልጋይ ሊሆን ይችላል።
ባለትዳሮች ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
17. ያገቡ ክርስቲያኖች ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
17 የምንኖረው ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ እየተገባደዱ ባሉበት ጊዜ ላይ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በማለት ገልጾታል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ያም ቢሆን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ጠንካሮች መሆናችን የዚህን ዓለም መጥፎ ተጽዕኖ እንድናሸንፍ ኃይል ይሰጠናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የቀረው ጊዜ አጭር [ነው]። . . . ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ . . . በዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ።” (1 ቆሮ. 7:29-31) ጳውሎስ ይህን ሲል ያገቡ ክርስቲያኖች፣ ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ቸል እንዲሉ መምከሩ አይደለም። ሆኖም የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ነው።—ማቴ. 6:33
18. ክርስቲያኖች ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበትና ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው?
18 የምንኖረው በጣም ተፈታታኝ በሆነ ዘመን ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ትዳሮች ሲፈርሱ እንመለከታለን፤ ያም ቢሆን ትዳራችን ደስታ የሰፈነበትና ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። በእርግጥም ከይሖዋና ከሕዝቡ ጋር ተቀራርበው የሚኖሩ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ተግባራዊ የሚያደርጉ እንዲሁም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራቸው የሚፈቅዱ ያገቡ ክርስቲያኖች “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ።—ማር. 10:9
^ [1] (አንቀጽ 5) ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ [2] (አንቀጽ 13) ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቺና ስለ መለያየት ምን ይላል?” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።