በአምላክ መንፈስ መመራት ያለብን ለምንድን ነው?
“አንተ አምላኬ ነህና፣ . . . መልካሙ መንፈስህም፣ በቀናችው መንገድ ይምራኝ።”—መዝ. 143:10
1. በዓይን የማይታይ ኃይል አንድን ሰው ሊመራው እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
የምትጓዝበትን አቅጣጫ ለማወቅ ኮምፓስ ተጠቅመህ ታውቃለህ? ኮምፓስ፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚያመለክት ባለ ማግኔት ቀስት ያለው ውስብስብ ያልሆነ መሣሪያ ነው። በኮምፓስ ውስጥ ያለው ቀስት ወደ ሰሜን ዋልታ የሚያመለክተው በዓይን በማይታይ የምድር መግነጢሳዊ ኃይል ምክንያት ነው። ለብዙ መቶ ዓመታት አገር አሳሾችና ሌሎች ተጓዦች በየብስም ሆነ በባሕር በሚጓዙበት ጊዜ አቅጣጫቸውን ለማወቅ በኮምፓስ ሲጠቀሙ ቆይተዋል።
2, 3. (ሀ) ይሖዋ ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት ምን ዓይነት ኃይል ተጠቅሟል? (ለ) በዓይን የማይታየው የአምላክ ኃይል በዛሬው ጊዜ ሕይወታችንን ሊመራልን እንደሚችል መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
2 ሕይወታችንን ለመምራት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ በዓይን የማይታይ ሌላ ኃይል አለ። ይህ ኃይል ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ስለዚህ ኃይል ተገልጿል። የዘፍጥረት መጽሐፍ ይሖዋ ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት ስላከናወነው ነገር ሲገልጽ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። ይሖዋ እነዚህን አካላት ለመፍጠር ከፍተኛ ኃይል ተጠቅሟል፤ ምክንያቱም ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ በመቀጠል “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር” ይላል። (ዘፍ. 1:1, 2) አምላክ የፍጥረት ሥራዎችን ባከናወነበት ወቅት የተጠቀመበት በሥራ ላይ የነበረው ይህ ኃይል መንፈስ ቅዱስ ነው። ይሖዋ እኛን ወደ ሕልውና ለማምጣትም ሆነ ሁሉንም ሥራዎቹን ለማከናወን በዚህ መንፈስ ተጠቅሟል።—ኢዮብ 33:4፤ መዝ. 104:30
3 በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል ሕልውና እንዲኖረን ከማድረግ ባሻገር በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል? የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “መንፈስ . . . ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” በማለት መናገሩ ይህን መጠበቅ እንደምንችል ያሳያል። (ዮሐ. 16:13) ለመሆኑ የዚህን መንፈስ ምንነት መረዳት ያለብን እንዴት ነው? በዚህ መንፈስ ለመመራት መፈለግ ያለብንስ ለምንድን ነው?
የመንፈስ ቅዱስ ምንነት
4, 5. (ሀ) በሥላሴ የሚያምኑ ሰዎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ምን የተሳሳተ እምነት አላቸው? (ለ) መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
4 በአገልግሎት ላይ የምታገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው ሳታስተውል አልቀረህም። በሥላሴ የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ አካል አለው እንዲሁም ከአብ ጋር እኩል ነው የሚል አመለካከት አላቸው። (1 ቆሮ. 8:6) ይሁንና የሥላሴ መሠረት ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን።
5 ታዲያ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው? ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዘፍጥረት 1:2 የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ ይላል፦ “ሩአህ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል ‘መንፈስ’ ተብሎ ከመተርጎሙም በተጨማሪ ‘ነፋስ’ ተብሎ ተተርጉሟል፤ በሌላ አባባል በዓይን የማይታይ በሥራ ላይ ያለ ኃይልን ያመለክታል።” (በባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም [እንግሊዝኛ] ላይ ከዘፍጥረት 3:8 እና ዘፍጥረት 8:1 የግርጌ ማስታወሻዎች ጋር አወዳድር።) ነፋስ የማይታይ ቢሆንም አንዳንድ ነገሮች እንደሚያንቀሳቅስ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም በዓይን የማይታይና አካል የሌለው ቢሆንም የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን ይችላል። ይህ መንፈስ ከአምላክ የሚመነጭ ኃይል ሲሆን በሰዎች ወይም በነገሮች ላይ በማደር የአምላክን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ያደርጋል። ታዲያ እንዲህ ያለው ኃይል ቅዱስ ከሆነው ምንጭ ማለትም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ እንደሚወጣ ማመን ያን ያህል ሊከብደን ይገባል? በፍጹም!—ኢሳይያስ 40:12, 13ን አንብብ።
6. ዳዊት ለይሖዋ ምን አስፈላጊ ልመና አቅርቧል?
6 ይሖዋ ዛሬም መንፈስ ቅዱሱን ተጠቅሞ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ እኛን ሊመራን ይችላል? ይሖዋ ለመዝሙራዊው ዳዊት “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (መዝ. 32:8) ዳዊትስ፣ በአምላክ መንፈስ መመራት ይፈልግ ነበር? “አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ፤ መልካሙ መንፈስህም፣ በቀናችው መንገድ ይምራኝ” በማለት ይሖዋን መማጸኑ ይህን ያሳያል። (መዝ. 143:10) እኛም በአምላክ መንፈስ ለመመራት ተመሳሳይ ፍላጎትና የፈቃደኝነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል። ለምን? እስቲ አራት ምክንያቶችን እንመርመር።
ራሳችንን በራሳችን የመምራት ችሎታ የለንም
7, 8. (ሀ) ያለ አምላክ እርዳታ ራሳችንን በራሳችን መምራት የማንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይህን ክፉ ሥርዓት በራሳችን መንገድ ለማለፍ መዳዳት የሌለብን ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
7 በአምላክ መንፈስ ለመመራት የምንፈልግበት የመጀመሪያው ምክንያት ራሳችንን በራሳችን የመምራት ችሎታ የሌለን መሆኑ ነው። “መምራት” ሲባል “አቅጣጫን ማሳየት ወይም የትኛውን መንገድ ተከትሎ መሄድ እንደሚገባ ማመልከት” ማለት ነው። ይሖዋ፣ እንኳንስ ፍጽምና ጎድሎን ይቅርና መጀመሪያ ሲፈጥረንም ይህን ችሎታ አልሰጠንም። የይሖዋ ነቢይ የሆነው ኤርምያስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤር. 10:23) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኤርምያስ ራሳችንን በራሳችን የመምራት ችሎታ የሌለን ለምን እንደሆነ አምላክ ሲናገር ሰምቷል። ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን የሚወክለውን ምሳሌያዊ ልብ አስመልክቶ ሲናገር “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” ብሏል።—ኤር. 17:9፤ ማቴ. 15:19
8 ምንም ዓይነት የጉዞ ልምድ የሌለው አንድ ሰው፣ ጥሩ መንገድ መሪም ሆነ ኮምፓስ ሳይዝ ከዚህ በፊት ሄዶበት በማያውቅ ምድረ በዳ ውስጥ መጓዝ ቢጀምር አደገኛ አይሆንም? ይህ ሰው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ሕይወትን ማቆየት እንደሚቻልም ሆነ ወዳሰበው ቦታ በሰላም መድረስ የሚቻልበትን ዘዴ ካላወቀ ሕይወቱ አደጋ ላይ ይወድቃል። በተመሳሳይም በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ትክክለኛውን መንገድ አምላክ እንዲያሳየው ከመፍቀድ ይልቅ አካሄዱን በራሱ መምራት እንደሚችል የሚያስብ ሰው ሕይወቱን አደጋ ላይ እየጣለ ነው። ይህን ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ ለማለፍ ያለን ብቸኛው አማራጭ ልክ እንደ ዳዊት “እግሮ[ቼ] እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና” የሚል ልመና ለይሖዋ ማቅረብ ነው። (መዝ. 17:5 የ1954 ትርጉም፤ 23:3) አምላክ እንዲህ ዓይነቱን አመራር ሊሰጠን የሚችለው እንዴት ነው?
9. በገጽ 17 ላይ የሚገኘው ፎቶግራፍ እንደሚጠቁመው የአምላክ መንፈስ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ሊመራን የሚችለው እንዴት ነው?
9 ትሑቶችና በይሖዋ የምንታመን ከሆንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት አካሄዳችንን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ይመራልናል። ይህ መንፈስ የሚረዳን እንዴት ነው? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።” (ዮሐ. 14:26) ክርስቶስ የተናገራቸውን ነገሮች ጨምሮ የአምላክን ቃል በጸሎት በመታገዝ አዘውትረን የምናጠና ከሆነ መንፈስ ቅዱስ፣ ጥልቅ ስለሆነው የይሖዋ ጥበብ ያለንን ግንዛቤ ያሳድግልናል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን መመሪያ በጥብቅ እንድንከተል ያስችለናል። (1 ቆሮ. 2:10) በተጨማሪም ሕይወት ለማግኘት በምናደርገው ጉዞ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን መንፈስ ቅዱስ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይጠቁመናል። ከዚህ ቀደም የተማርናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድናስታውስ ይረዳናል፤ እንዲሁም ቀጣዩን አካሄዳችንን ለመምራት እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ያስገነዝበናል።
ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ ይመራ ነበር
10, 11. የአምላክ አንድያ ልጅ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ይጠብቅ ነበር? መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና ተጫውቷል?
10 በአምላክ መንፈስ ለመመራት የምንፈልግበት ሁለተኛው ምክንያት አምላክ የራሱን ልጅ በዚህ መንፈስ የመራው መሆኑ ነው። የአምላክ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስለ እሱ የተነገረውን የሚከተለውን ትንቢት ያውቀው ነበር፦ “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” (ኢሳ. 11:2) ኢየሱስ ፈተናዎች በሞሉበት በዚህ ምድር ላይ በሚኖርበት ወቅት የአምላክን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት ምን ያህል ይጓጓ እንደነበር ገምት!
11 ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። የሉቃስ ወንጌል ኢየሱስ እንደተጠመቀ የተከሰተውን ነገር ሲገልጽ “ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ከተመለሰ በኋላ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው” ይላል። (ሉቃስ 4:1) ኢየሱስ በምድረ በዳ ሆኖ በሚጾምበት፣ በሚጸልይበትና በሚያሰላስልበት ወቅት ይሖዋ፣ ወደፊት ስለሚያጋጥመው ነገር መመሪያ ሰጥቶትና አንዳንድ ነገሮችን ገልጾለት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክ መንፈስ በኢየሱስ አእምሮና ልብ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮ ስለነበር አስተሳሰቡና እርምጃው የሚመራው በዚህ መንፈስ ነበር። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ የሚያጋጥመውን እያንዳንዱን ነገር እንዴት መወጣት እንዳለበት ያውቅ ነበር፤ ከዚህም ባሻገር ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ልክ አባቱ እንደሚፈልገው ነበር።
12. መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን አምላክን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ መመራት ያለውን ጥቅም በሕይወቱ ስላየ ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለያቸውና በዚህ መንፈስ መመራታቸው አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ገልጾላቸዋል። (ሉቃስ 11:9-13ን አንብብ።) እኛስ በአምላክ መንፈስ መመራታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የአምላክ መንፈስ አስተሳሰባችንን በመለወጥ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንድንይዝ ስለሚረዳን ነው። (ሮም 12:2፤ 1 ቆሮ. 2:16) የአምላክ መንፈስ ሕይወታችንን እንዲመራው በመፍቀድ እንደ ክርስቶስ ማሰብና የእሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን።—1 ጴጥ. 2:21
የዓለም መንፈስ አቅጣጫችንን ሊያስተን ይችላል
13. የዓለም መንፈስ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ተጽዕኖስ ያሳድራል?
13 የአምላክ መንፈስ እንዲመራን የምንፈልግበት ሦስተኛው ምክንያት በመንፈስ ቅዱስ የማንመራ ከሆነ በዛሬው ጊዜ፣ በብዙ ሰዎች ላይ እየሠራ ያለው የዓለም መንፈስ በቀላሉ አቅጣጫችንን ሊያስተን የሚችል መሆኑ ነው። ይህ ዓለም፣ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ከሚያፈራው ፍሬ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ መንገድ እንድንከተል የሚያነሳሳ የራሱ የሆነ ኃይል አለው። የዓለም መንፈስ ሰዎች የክርስቶስን አስተሳሰብ እንዲይዙ ከማድረግ ይልቅ አመለካከታቸውና ድርጊታቸው የዚህ ዓለም ገዥ የሆነውን የሰይጣንን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ያደርጋል። (ኤፌሶን 2:1-3ን እና ቲቶ 3:3ን አንብብ።) አንድ ሰው ለዓለም መንፈስ ከተሸነፈና የሥጋ ሥራዎችን መፈጸም ከጀመረ አሳዛኝ ውጤት ሊያስከትልበት ይኸውም የአምላክን መንግሥት ከመውረስ ሊያግደው ይችላል።—ገላ. 5:19-21
14, 15. የዓለምን መንፈስ በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ የዓለምን መንፈስ መቋቋም እንድንችል አስታጥቆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክፉው ቀን በሚመጣበት ጊዜ መቋቋም እንድትችሉ ከጌታና ከታላቅ ብርታቱ ኃይል ማግኘታችሁን ቀጥሉ’ ብሏል። (ኤፌ. 6:10, 13) ሰይጣን እኛን ለማሳሳት የሚያደርገውን ጥረት መቋቋም እንድንችል ይሖዋ በመንፈሱ ይደግፈናል። (ራእይ 12:9) የዓለም መንፈስ ኃይለኛ ከመሆኑም ባሻገር ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን አንችልም። ያም ሆኖ ይህ መንፈስ እንዳይበክለን መከላከል እንችላለን። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ከዓለም መንፈስ እጅግ የላቀ ስለሆነ እርዳታ ሊያደርግልን ይችላል።
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ ክርስትናን ስለካዱ ሰዎች ሲናገር “ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል” ብሏል። (2 ጴጥ. 2:15) ‘የተቀበልነው ከአምላክ የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ ባለመሆኑ’ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (1 ቆሮ. 2:12) ይህ መንፈስ እንዲመራን የምንፈቅድ እንዲሁም ይሖዋ ትክክለኛውን ጎዳና ተከትለን እንድንጓዝ እኛን ለመርዳት ሲል ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ የምንጠቀም ከሆነ ሰይጣን የሚያስፋፋውን የዚህን ክፉ ዓለም መንፈስ በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን።—ገላ. 5:16
መንፈስ ቅዱስ ጥሩ ፍሬ ያፈራል
16. መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ምን ፍሬ ሊያፈራ ይችላል?
16 የአምላክ መንፈስ እንዲመራን የምንፈልግበት አራተኛው ምክንያት ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ በሚመሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ይህ መንፈስ መልካም ፍሬ የሚያፈራ መሆኑ ነው። (ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ።) ይበልጥ አፍቃሪ፣ ደስተኛና ሰላማዊ መሆን የማይፈልግ ከእኛ መካከል ማን አለ? ትዕግሥት፣ ደግነትና ጥሩነት በዝቶ እንዲትረፈረፍልን የማንፈልግ ማናችን ነን? ከመካከላችን እምነትን ገርነትንና ራስን መግዛትን ይበልጥ በማዳበሩ የማይጠቀም ማን ነው? የአምላክ መንፈስ እኛንም ሆነ አብረውን የሚኖሩና የሚያገለግሉ ሰዎችን የሚጠቅሙ ግሩም ባሕርያትን እንድናፈራ ያስችለናል። የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት ምንጊዜም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ይህን ፍሬ ማፍራት የሚያስፈልገን እስከምን ድረስ እንደሆነ እንዲሁም የማፍራት አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ ገደብ አልተቀመጠም።
17. የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ይበልጥ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
17 አነጋገራችንም ሆነ ድርጊታችን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራንና የመንፈስ ፍሬን እያፈራን መሆናችንን የሚያሳይ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ራሳችንን መመርመራችን ጥበብ ነው። (2 ቆሮ. 13:5ሀ፤ ገላ. 5:25) ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል የተወሰኑትን የበለጠ ማዳበር እንዳለብን ከተሰማን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ጥረት በማድረግ እነዚህን ባሕርያት ማፍራት እንችላለን። እንግዲያው በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ከፈለግን እያንዳንዱ የመንፈስ ፍሬ ገጽታ የተጠቀሱባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና እነዚህ ባሕርያት የተብራሩባቸውን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ማጥናት ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን እነዚህን ባሕርያት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች እንድናስተውል ይረዳናል፤ ከዚያም ባሕርያቱን በሕይወታችን ውስጥ የበለጠ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።a የአምላክ መንፈስ በእኛም ሆነ በክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ሕይወት ውስጥ በሚሠራበት ወቅት የሚያስገኘውን ውጤት ስንመለከት በዚህ መንፈስ መመራት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታየናል።
በአምላክ መንፈስ ለመመራት ፈቃደኛ ናችሁ?
18. ለአምላክ መንፈስ በመታዘዝ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ፣ ምድርን ጨምሮ አጽናፈ ዓለም በሚፈጠርበት ጊዜ “ዋና ባለሙያ” ሆኖ ከአምላክ ጋር የሠራ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች አቅጣጫን ለማወቅ ስለሚጠቀሙበት የምድር መግነጢሳዊ ኃይል በሚገባ ያውቃል። (ምሳሌ 8:30፤ ዮሐ. 1:3) ሆኖም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አቅጣጫን ለማወቅ በዚህ ኃይል ተጠቅሞ እንደነበር የሚጠቁም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ ምድር ላይ ሰው ሆኖ ሲመላለስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያለውን ከፍተኛ ኃይል በሕይወቱ እንደተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ይፈልግ ነበር፤ በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ አንድ ነገር እንዲያደርግ ሲገፋፋው ፈቃደኛ በመሆን ይህ መንፈስ ከሚሰጠው አመራር ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስድ ነበር። (ማር. 1:12, 13፤ ሉቃስ 4:14) አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ?
19. መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን እንዲመራልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 ዛሬም፣ በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች አእምሮና ልብ ውስጥ በመሥራት ለተግባር እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል፤ እንዲሁም ይመራቸዋል። የአምላክ መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዲሠራና በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመራህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህና በመንፈሱ ለመመራት የሚያስችል የፈቃደኝነት መንፈስ በውስጥህ እንዲያሳድር ያለማቋረጥ ጸልይ። (ኤፌሶን 3:14-16ን አንብብ።) እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ የሥራ ውጤት የሆነውንና በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያዘሉ መመሪያዎች በሥራ ላይ አውል፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ልባዊ ጥረት አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ፣ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በተሻለው ጎዳና ላይ ሊመራህ እንደሚችል እምነት እንዳለህ ታሳያለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እያንዳንዱ የመንፈስ ፍሬ ገጽታ፣ የተብራራባቸውን ጽሑፎች ለማግኘት ከመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ላይ “ፍሩቴጅ ኦቭ ጎድስ ስፒሪት” በሚለው ርዕስ ሥር “ሊስት ባይ አስፔክት” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።
ዋና ዋና ነጥቦቹን አስተውለሃል?
• መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
• በአምላክ መንፈስ ለመመራት የምንፈልግባቸው አራት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
• መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠን አመራር ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በእኛ በኩል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንፈስ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንፈስ በሰዎች አእምሮና ልብ ውስጥ በመሥራት ለተግባር እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል፤ እንዲሁም ይመራቸዋል