ከአምላክ ላገኛችሁት የጋብቻ ስጦታ ልባዊ አድናቆት አላችሁ?
“ይሖዋ በምታገቡት ባል ቤት እረፍት በመስጠት ይባርካችሁ።”—ሩት 1:9 NW
የጥያቄዎቹን መልስ ለማግኘት ሞክር፦
በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ከእሱ ላገኙት የጋብቻ ስጦታ አድናቆት ነበራቸው የምንለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ የትዳር ጓደኛ ምርጫችን ያሳስበዋል የምንለው ለምንድን ነው?
ጋብቻን አስመልክቶ ከተሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች የትኛውን በሕይወትህ ተግባራዊ ለማድረግ አስበሃል?
1. አዳም ሚስት ሲያገኝ ምን እንደተሰማው ግለጽ።
“እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።” (ዘፍ. 2:23) የመጀመሪያው ሰው አዳም፣ ሚስት በማግኘቱ በጣም ተደስቶ ነበር! በወቅቱ የተሰማውን ስሜት በግጥም መግለጹ ምንም አያስደንቅም! ይሖዋ በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ከጣለበት በኋላ ከጎድን አጥንቶቹ አንዱን ወስዶ ውብ የሆነች ሴት ፈጠረለት። በኋላም አዳም ይህችን ሴት ሔዋን ብሎ ጠራት። ከዚያም አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን በጋብቻ አጣመራቸው። ይሖዋ፣ ሔዋንን ለመፍጠር የአዳምን የጎድን አጥንት ስለተጠቀመ አዳምና ሔዋን በአሁኑ ጊዜ ካሉ ከማንኛውም ባልና ሚስት የበለጠ ቅርበት ነበራቸው።
2. በወንዶችና በሴቶች መካከል የመሳሳብ ስሜት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ ወደር በማይገኝለት ጥበቡ ተጠቅሞ ሰዎች ለተቃራኒ ፆታ የፍቅር ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል፤ እንዲህ ያለው ፍቅር በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መሳሳብ እንዲኖር ያደርጋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ወንድና ሴት ሲጋቡ የፆታ ስሜታቸው እንደሚረካ ብሎም ፍቅራቸው ዘላቂ እንደሚሆን ይጠብቃሉ።” በይሖዋ ሕዝቦች መካከልም እንዲህ የመሰለ የፍቅር ግንኙነት የሚመሠርቱ በርካታ ወንዶችና ሴቶች አሉ።
ለጋብቻ ስጦታ አመስጋኝ ነበሩ
3. ይስሐቅ ሚስት ያገኘው እንዴት ነው?
3 ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሆነው አብርሃም ለጋብቻ ዝግጅት ከፍተኛ አክብሮት ነበረው። በመሆኑም በዕድሜ የገፋው አገልጋዩን ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት ወደ መስጴጦምያ ልኮት ነበር። ይህ አገልጋይ ጉዳዩን አስመልክቶ መጸለዩ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ምክንያቱም አገልጋዩ ፈሪሃ አምላክ ያላትን ርብቃን ያገኘ ሲሆን እሷም ለይስሐቅ ጥሩ ሚስት ሆናለታለች፤ እንዲሁም ይሖዋ፣ የአብርሃምን ዘር ጠብቆ ለማቆየት ባደረገው ዝግጅት የራሷን ሚና ተጫውታለች። (ዘፍ. 22:18፤ 24:12-14, 67) ይሁንና ይህ ታሪክ አንድ ሰው ሳይጠየቅ (ምናልባትም በቅን ልቦና ተነሳስቶ ሊሆን ይችላል) ትዳር ፈላጊዎችን የማገናኘት መብት ይሰጠዋል ማለት አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ራሳቸው ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የትዳር ጓደኛ ይመርጥልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። ሆኖም አንድ ክርስቲያን ማግባት የሚፈልግ ከሆነ አምላክን በጸሎት በመጠየቅና በመንፈሱ በመመራት በዚህም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ረገድ የይሖዋን አመራር ማግኘት ይችላል።—ገላ. 5:18, 25
4, 5. ሱላማጢሷና እረኛው አንዳቸው ለሌላው የፍቅር ስሜት እንደነበራቸው በምን እርግጠኛ መሆን እንችላለን?
4 በጥንቷ እስራኤል ትኖር የነበረችው ውብ የሆነችው ሱላማጢሷ ልጃገረድ በርካታ ሚስቶች ላሉት ለንጉሥ ሰለሞን ሚስት እንድትሆነው ሰዎች እንዳይገፋፏት ፈልጋ ነበር። በመሆኑም “እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፤ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት አማጥናችኋለሁ” አለቻቸው። (ማሕ. 8:4) ሱላማጢሷ ከአንድ እረኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀምራ ነበር። ይህች ወጣት ራሷን ዝቅ በማድረግ “እኔ የሳሮን ጽጌረዳ፣ የሸለቆም አበባ ነኝ” ስትል እረኛው ቀበል አድርጎ “በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ፣ ውዴም በቈነጃጅት መካከል እንዲሁ ናት” በማለት አሞግሷታል። (ማሕ. 2:1, 2) በእርግጥም እነዚህ ወጣቶች ከልብ ይዋደዱ ነበር።
5 ሱላማጢሷና እረኛው ከምንም በላይ ለአምላክ ፍቅር ስለነበራቸው የጋብቻ ጥምረታቸው ጠንካራ እንደሚሆን አያጠራጥርም። እንዲያውም ሱላማጢሷ በጣም ለምትወደው ለዚህ እረኛ እንዲህ ብላዋለች፦ “እንደ ማህተም በልብህ፣ እንደ ማህተም በክንድህ አስቀምጠኝ፤ ምክንያቱም ፍቅር እንደ ሞት የበረታ ነው፣ እንደ ሲኦልም የማይበገር ነው፤ ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። የፍቅር ወላፈን የእሳት ወላፈን ነው፣ የያህም ነበልባል ነው [ምክንያቱም የፍቅር ምንጭ እሱ ነው]። የውኃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋው አይችልም፣ ወንዞችም ጠራርገው ሊወስዱት አይችሉም። አንድ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ በመስጠት ፍቅርን ለመግዛት ቢሞክር ሰዎች ሀብቱን ይንቁበታል።” (ማሕ. 8:6, 7 NW) ታዲያ አሁን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነትንና ፍቅርን በማሳየት ረገድ ከትዳር ጓደኛቸው ከዚህ ያነሰ ነገር ሊጠብቁ ይገባል?
የምናደርገው ምርጫ አምላክን ያሳስበዋል
6, 7. ይሖዋ የትዳር ጓደኛ ምርጫችን እንደሚያሳስበው እንዴት እናውቃለን?
6 ይሖዋ የትዳር ጓደኛ ምርጫህ ያሳስበዋል። የከነዓንን ነዋሪዎች በተመለከተ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው።” (ዘዳ. 7:3, 4) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ካህኑ ዕዝራ “እናንተ ታማኞች አልነበራችሁም፤ በእስራኤል በደል ላይ በደል በመጨመር ባዕዳን ሴቶችን አገባችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዕዝራ 10:10) ሐዋርያው ጳውሎስም ለእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንዲት ሚስት ባሏ በሕይወት ባለበት ዘመን ሁሉ የታሰረች ናት። ባሏ በሞት ካንቀላፋ ግን በጌታ ብቻ ይሁን እንጂ የፈለገችውን ለማግባት ነፃ ናት።”—1 ቆሮ. 7:39
7 ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ክርስቲያን የማያምን ሰው ቢያገባ ድርጊቱ አምላክን ላለመታዘዝ እንደመረጠ ያሳያል። በዕዝራ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ‘ባዕዳን ሴቶችን በማግባት’ ታማኝ አለመሆናቸውን አሳይተዋል፤ በመሆኑም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በግልጽ የተቀመጡትን መመሪያዎች ማለሳለስ ተገቢ አይደለም። (ዕዝራ 10:10፤ 2 ቆሮ. 6:14, 15) አንድ ክርስቲያን የማያምን ሰው ቢያገባ በጉባኤ ውስጥ ምሳሌ አይሆንም፤ እንዲሁም ከአምላክ ላገኘው የጋብቻ ስጦታ ልባዊ አድናቆት እንደሌለው ያሳያል። አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ እንዲህ ያለ ጥምረት ውስጥ ቢገባ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ መብቶች ሊያጣ ይችላል። ከዚህም ሌላ ይህ ግለሰብ ጸሎቱ ላይ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ሕግህን የጣስኩት ሆን ብዬ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ግን እባክህ ባርከኝ’ በማለት ሆን ብሎ መበደሉን እያመነ የይሖዋን በረከት ለማግኘት መጠበቁ ተገቢ አይሆንም።
የሰማዩ አባታችን የሚበጀንን ያውቃል
8. ይሖዋ ትዳርን አስመልክቶ የሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያለብን ለምን እንደሆነ ግለጽ።
8 አንድን ማሽን የፈለሰፈ ሰው ዕቃው እንዴት እንደሚሠራ በሚገባ ያውቃል። ስለ ዕቃው አጠቃቀም በተለይ ደግሞ ዕቃው መገጣጠም የሚያስፈልገው ከሆነ ይህን በተመለከተ ከማንም በተሻለ ዝርዝር መረጃ መስጠት የሚችለው ይህ ሰው ነው። ሆኖም መመሪያውን ችላ ብለን ዕቃውን በራሳችን መንገድ ገጣጥመን ለመጠቀም ብንሞክርስ? ዕቃው ሊበላሽ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው እኛም ደስተኛ ትዳር የመመሥረት ምኞታችንን ለማሳካት ከፈለግን የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ የሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
9. ይሖዋ፣ ስለ ብቸኝነት ስሜት እንዲሁም በትዳር ውስጥ ሊገኝ ስለሚችለው ደስታ በሚገባ ያውቃል የምንለው ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ ስለ ሰው ልጆች ተፈጥሮም ሆነ ስለ ትዳር ሁሉንም ነገር ያውቃል። ሰዎች ‘ተባዝተው ምድርን እንዲሞሏት’ ስለፈለገ የፆታ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል። (ዘፍ. 1:28) አምላክ የብቸኝነትን ስሜት ይረዳል፤ ምክንያቱም የመጀመሪያዋን ሴት ከመፍጠሩ በፊት “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” ብሏል። (ዘፍ. 2:18) በተጨማሪም ይሖዋ በጋብቻ ውስጥ ሊገኝ ስለሚችለው ደስታ በሚገባ ያውቃል።—ምሳሌ 5:15-18ን አንብብ።
10. ክርስቲያን ባለትዳሮች የፍቅር ስሜትን ከመግለጽ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል?
10 ሰዎች ከአዳም ኃጢአትንና አለፍጽምናን በመውረሳቸው ፍጹም የሆነ ትዳር ሊመሠርቱ አይችሉም። ሆኖም የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ቃል የሚታዘዙ ከሆነ በጋብቻ ጥምረታቸው እውነተኛ ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። በትዳር ውስጥ የፆታ ስሜትን ከማርካት ጋር በተያያዘ ጳውሎስ የሰጠውን ግልጽ ምክር እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል። (1 ቆሮንቶስ 7:1-5ን አንብብ።) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አንድ ባልና ሚስት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያለባቸው ልጅ ለመውለድ ሲያስቡ ብቻ እንደሆነ አይናገሩም። ከፆታ ስሜት ጋር በተያያዘ ፍቅራቸውን መግለጻቸው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ፍላጎታቸውን በተገቢው መንገድ ለማርካት ያስችላቸዋል። ሆኖም ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ መንገድ የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት አምላክን አያስደስትም። ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስቶች በትዳር ሕይወታቸው ትልቅ ቦታ ሊሰጡት ከሚገባው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንዳቸው ለሌላው ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት ፍቅራቸውን መግለጽ ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋን የሚያሳዝን ማንኛውም ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ ይገባቸዋል።
11. ሩት ነገሮችን በይሖዋ መንገድ በማከናወኗ የተባረከችው እንዴት ነው?
11 የትዳር ሕይወት ደስታና እርካታ የሚያመጣ እንጂ አሰልቺ ሊሆን አይገባውም። በተለይ የክርስቲያኖች ቤት የሰላምና የእረፍት ቦታ መሆን ይኖርበታል። እስቲ ከ3,000 ዓመታት በፊት የተፈጸመን አንድ ሁኔታ እንመልከት፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸው አረጋዊቷ ኑኃሚን እንዲሁም ምራቶቿ ዖርፋና ሩት ከሞዓብ ወደ ይሁዳ እየተጓዙ ነው። በመንገድ ላይ ሳሉም ኑኃሚን፣ ምራቶቿ ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱ ለመነቻቸው። ሞዓባዊቷ ሩት ግን ለእውነተኛው አምላክ ታማኝ ስለነበረች ከኑኃሚን ለመለየት ፈቃደኛ አልሆነችም፤ በዚህም የተነሳ ቦዔዝ “በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ” በማለት ባርኳታል። (ሩት 1:9፤ 2:12) ሩት ለጋብቻ ዝግጅት ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራት የይሖዋ እውነተኛ አምላኪ የሆነውንና በዕድሜ የገፋውን ቦዔዝን ለማግባት ፈቃደኛ ሆናለች። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት ተነስታ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት እንደሆነች ስታውቅ ምን ያህል ትደሰት ይሆን! (ማቴ. 1:1, 5, 6፤ ሉቃስ 3:23, 32) በእርግጥም ሩት ነገሮችን በይሖዋ መንገድ በማከናወኗ ተባርካለች!
ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ የሚረዳ ጥሩ ምክር
12. አንድ ሰው ትዳርን በተመለከተ ጥሩ ምክር ማግኘት የሚችለው ከየት ነው?
12 የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ ምን ነገሮችን ማወቅ እንዳለብን ነግሮናል። ማንም ሰው የእሱን ያህል ሊያውቅ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ምንጊዜም ትክክል ነው፤ አንድ ሰው ትዳርን በተመለከተ ጥሩ ምክር ለማግኘት ከፈለገ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩትን መመሪያዎች መከተል ይኖርበታል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።” (ኤፌ. 5:33) የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮችን መረዳት አይከብዳቸውም። ጥያቄው ‘የይሖዋን ቃል በተግባር ያውላሉ?’ የሚለው ነው። ለጋብቻ ስጦታ ልባዊ አድናቆት ካላቸው ይህን ማድረግ አያቅታቸውም።a
13. በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አለማድረግ ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?
13 አንድ ክርስቲያን ባል፣ ሚስቱን በፍቅር ሊይዛት ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ እናንተም ከእነሱ ጋር የሕይወትን ጸጋ ወራሾች ስለሆናችሁ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእናንተ ይበልጥ ተሰባሪ ዕቃ ለሆኑት ለሴቶች ክብር በመስጠት ልክ እንደዚሁ ከእነሱ ጋር በእውቀት መኖራችሁን ቀጥሉ።” (1 ጴጥ. 3:7) አንድ ባል፣ የይሖዋን ምክር ተግባራዊ የማያደርግ ከሆነ ጸሎቱ ሊታገድ ይችላል። በተጨማሪም የሁለቱም መንፈሳዊነት መጎዳቱ አይቀርም፤ እንዲሁም ግንኙነታቸው ውጥረት የሰፈነበትና ጭቅጭቅ የበዛበት ሊሆን አልፎ ተርፎም አንዱ ሌላውን በጥሩ ሁኔታ እንዳይዝ ሊያደርግ ይችላል።
14. አፍቃሪ የሆነች ሚስት በቤተሰቧ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ትችላለች?
14 በይሖዋ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ሚስት ቤቷን የተረጋጋና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ትችላለች። እርግጥ ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ባል ሚስቱን መውደዱና እሷን በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ መንከባከቡ የሚጠበቅ ነገር ነው። ያም ሆኖ አንዲት ሚስት የባሏን ፍቅር ለማግኘት ከፈለገች እንዲወዳት የሚያደርጉ ባሕርያትን ማፍራት ይኖርባታል። ምሳሌ 14:1 “ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች” ይላል። ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነች ሚስት ቤተሰቧ ስኬታማና ደስተኛ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። በተጨማሪም ከአምላክ ላገኘችው የጋብቻ ስጦታ ልባዊ አድናቆት እንዳላት ታሳያለች።
15. ኤፌሶን 5:22-25 ምን ጠቃሚ ምክር ይዟል?
15 ባሎችና ሚስቶች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ኢየሱስ ጉባኤውን የያዘበትን መንገድ ምሳሌ አድርገው የሚከተሉ ከሆነ ከአምላክ ላገኙት የጋብቻ ስጦታ አመስጋኝ እንደሆኑ ያሳያሉ። (ኤፌሶን 5:22-25ን አንብብ።) ባለትዳሮች ከልብ የሚዋደዱ እንዲሁም ኩራት፣ ኩርፊያና ሌሎች ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ባሕርያት ትዳራቸውን እንዲያደፈርሱባቸው የማይፈቅዱ ከሆነ በእርግጥም ብዙ በረከት ያጭዳሉ።
ማንም አይለያያቸው
16. አንዳንድ ክርስቲያኖች በነጠላነት የሚቀጥሉት ለምንድን ነው?
16 ብዙ ሰዎች አንድ ቀን እንደሚያገቡ ያስባሉ፤ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ደግሞ እነሱም ሆነ ይሖዋ የሚደሰቱበት ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ባለማግኘታቸው ነጠላ ሆነው እየኖሩ ነው። ሌሎች ደግሞ ነጠላነትን ከይሖዋ እንዳገኙት ስጦታ አድርገው ተመልክተውታል፤ ይህም በትዳር ጉዳይ ሐሳባቸው ሳይከፋፈል ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል አስችሏቸዋል። እርግጥ ነው፣ ነጠላነት ስጦታ የሚሆንላቸው የይሖዋን መመሪያ እስከተከተሉ ድረስ ነው።—ማቴ. 19:10-12፤ 1 ቆሮ. 7:1, 6, 7, 17
17. (ሀ) ኢየሱስ ትዳርን አስመልክቶ የሰጠውን የትኛውን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) አንድ ክርስቲያን የሌላውን ሰው የትዳር ጓደኛ መመኘት ከጀመረ በአፋጣኝ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል?
17 ነጠላም ሆንን ያገባን፣ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን መመሪያ ልብ ማለታችን ተገቢ ነው፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማቴ. 19:4-6) የሌላውን ሰው የትዳር ጓደኛ መመኘት ኃጢአት ነው። (ዘዳ. 5:21) አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ምኞት በአእምሮው ማስተናገድ ጀምሮ ከሆነ ይህን ርኩስ ሐሳብ ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፤ ይህ ግለሰብ የራስ ወዳድነት ምኞት በውስጡ እንዲያቆጠቁጥ በመፍቀዱ የተነሳ እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ማለት የለበትም። (ማቴ. 5:27-30) እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ማስወገዳችንና ተንኮለኛው ልባችን ላለው የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ፊት አለመስጠታችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ኤር. 17:9
18. ከአምላክ ላገኘነው የጋብቻ ስጦታ ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርብን ይገባል?
18 ስለ ይሖዋም ሆነ እሱ ስለሰጠው የጋብቻ ስጦታ እምብዛም እውቀት የሌላቸው ወይም ጨርሶ የማያውቁ ሰዎችም እንኳ ለትዳር ዝግጅት በተወሰነ መጠን አድናቆት አላቸው። ታዲያ ‘ደስተኛ ለሆነው አምላክ’ ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ባደረገልን ዝግጅቶች ሁሉ ይበልጥ ልንደሰት እንዲሁም ለጋብቻ ስጦታ ከሌሎች በተሻለ አድናቆት እንዳለን ልናሳይ አይገባም?—1 ጢሞ. 1:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ትዳርን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና 11 ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጥሩ ትዳር ይሖዋን የሚያስከብር ከመሆኑም ሌላ ለመላው ቤተሰብ ከፍተኛ ደስታ ያመጣል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት ከአምላክ ላገኘችው የጋብቻ ስጦታ አድናቆት እንዳላት አሳይታለች
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከይሖዋ ያገኘኸውን የጋብቻ ስጦታ ከልብ እንደምታደንቅ ታሳያለህ?