ይሖዋ “በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” ሰዎችን ይወዳል
“በጥሩ አፈር ላይ የወደቁት . . . በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”—ሉቃስ 8:15
1, 2. (ሀ) ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ በታማኝነት የሚሰብኩ ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ የሚሆኑን ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ “በገዛ አገሩ” መስበክን በተመለከተ ምን ብሏል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
ሰርዦ እና ኦሊንዳ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አቅኚዎች ናቸው። እነዚህ ባልና ሚስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እግራቸውን ስለሚያማቸው እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ ያስቸግራቸዋል። ያም ቢሆን በየዕለቱ ጠዋት ተነስተው በእግራቸው በመጓዝ ብዙዎች ወደሚመላለሱበት አንድ አደባባይ ልክ አንድ ሰዓት ላይ ይደርሳሉ፤ ይህ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የቆየ ልማዳቸው ነው። አውቶቡስ ፌርማታ አጠገብ ሆነው ለአላፊ አግዳሚው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ያበረክታሉ። በዚያ የሚያልፉት አብዛኞቹ ሰዎች ዞር ብለው እንኳ አያዩአቸውም፤ ባልና ሚስቱ ግን ምንጊዜም ከቦታቸው አይጠፉም፤ ደግሞም ፊታቸው ላይ ፈገግታ ይነበባል። ሰርዦና ኦሊንዳ፣ እኩለ ቀን ሲሆን እያዘገሙ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። በማግስቱም አንድ ሰዓት ላይ እዚያው አደባባይ ይገኛሉ። እነዚህ ታማኝ ባልና ሚስት ከዓመት እስከ ዓመት በሳምንት ስድስት ቀን በዚያ አደባባይ የመንግሥቱን ምሥራች ይሰብካሉ።
2 እንደ ሰርዦና ኦሊንዳ ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ታማኝ ወንድሞችና እህቶችም በጉባኤያቸው ክልል ውስጥ ያሉት ሰዎች ምሥራቹን ባይቀበሉም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲሰብኩ ቆይተዋል። እናንተም እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟችሁ ከሆነ ጽናታችሁን ከልብ እንደምናደንቅ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።a ይሖዋን በጽናት ማገልገላችሁ ለብዙዎች ሌላው ቀርቶ ተሞክሮ ላላቸው የእምነት ባልንጀሮቻችሁ እንኳ የብርታት ምንጭ ነው። ለአብነት ያህል፣ አንዳንድ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሰጧቸውን አስተያየቶች እንመልከት፦ “እንዲህ ካሉ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር በአገልግሎት ስካፈል ምሳሌነታቸው ብርታት ይሰጠኛል።” “ታማኝነታቸው በአገልግሎቴ እንድጸና ብሎም በድፍረት እንዳገለግል ያበረታታኛል።” “አርዓያነታቸው በጣም ያስደንቀኛል።”
3. የትኞቹን ሦስት ጥያቄዎች እንመለከታለን? ለምንስ?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመለከታለን፦ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል? ፍሬ ማፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? በጽናት ፍሬ ማፍራታችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን ኢየሱስ እንድናከናውነው በሰጠን የስብከት ሥራ እስከ መጨረሻው ለመጽናት ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።
ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?
4. (ሀ) አብዛኞቹ አይሁዳውያን ምሥራቹን ባለመቀበላቸው ጳውሎስ ምን ተሰምቶታል? (ለ) ጳውሎስ እንዲህ የተሰማው ለምንድን ነው?
4 የምትሰብኩት አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ መሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ከሆነባችሁ ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማውን ስሜት መረዳት ላይከብዳችሁ ይችላል። ጳውሎስ ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት ባከናወነው አገልግሎት በርካታ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ረድቷል። (ሥራ 14:21፤ 2 ቆሮ. 3:2, 3) ሆኖም ብዙ አይሁዳውያን እውነተኛውን አምልኮ እንዲቀበሉ ለመርዳት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። አብዛኞቹ፣ ጳውሎስን ለመስማት አሻፈረን ብለዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ስደት አድርሰውበታል። (ሥራ 14:19፤ 17:1, 4, 5, 13) ታዲያ ይህ በጳውሎስ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮበታል? “የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ . . . ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ሮም 9:1-3) ጳውሎስ እንዲህ የተሰማው ለምንድን ነው? ለስብከቱ ሥራ እና ለሰዎች ፍቅር ስለነበረው ነው። ለአይሁዳውያን የሰበከው ከልብ ስለሚያስብላቸው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ፣ አይሁዳውያን የአምላክን ምሕረት ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ሲመለከት በጣም አዝኗል።
5. (ሀ) ለሰዎች ለመስበክ የሚያነሳሳን ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ብንቆርጥ የሚያስገርም ያልሆነው ለምንድን ነው?
5 እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ለሰዎች የምንሰብከው ከልባችን ስለምናስብላቸው ነው። (ማቴ. 22:39፤ 1 ቆሮ. 11:1) ይሖዋን ለማምለክ የመረጡ ሰዎች በሕይወታቸው ምን ያህል እንደሚባረኩ ከራሳችን ተሞክሮ ተመልክተናል። በክልላችን ውስጥ ስላሉት ሰዎች ስናስብ ‘ምን እንደቀረባቸው ቢያውቁ ኖሮ!’ የሚል ስሜት ይፈጠርብን ይሆናል። ስለሆነም ስለ ይሖዋና ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ እንዲማሩ ማበረታታታችንን አናቋርጥም። ለሰዎች ስንሰብክ ‘ግሩም የሆነ ስጦታ ይዘንላችሁ መጥተናል። እባካችሁ ተቀበሉን’ የምንላቸው ያህል ነው። ሰዎቹ ስጦታውን ለመቀበል አሻፈረን ሲሉ ‘በልባችን ውስጥ ሥቃይ’ ቢሰማን አያስገርምም። እንዲህ የሚሰማን መሆኑ፣ እምነት እንደጎደለን የሚያሳይ ሳይሆን የስብከቱን ሥራ እንደምንወደው የሚጠቁም ነው። በመሆኑም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በሥራው እንጸናለን። ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች ኤሌና የተባለች እህት የተናገረችው ሐሳብ የብዙዎቻችንን ስሜት የሚገልጽ ነው፤ ኤሌና “የስብከቱ ሥራ ተፈታታኝ እንደሆነ ይሰማኛል። ያም ቢሆን ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ እወደዋለሁ” ብላለች።
ፍሬ ማፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?
6. የትኛውን ጥያቄ እንመለከታለን? የጥያቄውን መልስ ለማግኘት ምን ይረዳናል?
6 የምንሰብክበት ክልል የትም ይሁን የት በአገልግሎታችን ፍሬያማ መሆን እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው? ለዚህ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ኢየሱስ ‘ፍሬ የማፍራትን’ አስፈላጊነት የገለጸባቸውን ሁለት ምሳሌዎች እንመርምር። (ማቴ. 13:23) የመጀመሪያው ምሳሌ ስለ ወይን ተክል የሚናገር ነው።
7. (ሀ) “አትክልተኛው፣” “የወይኑ ተክል” እንዲሁም “ቅርንጫፎቹ” እነማንን ያመለክታሉ? (ለ) የየትኛውን ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል?
7 ዮሐንስ 15:1-5, 8ን አንብብ። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብታሳዩ በዚህ አባቴ ይከበራል” እንዳላቸው ልብ እንበል። በምሳሌው ላይ “አትክልተኛው” ይሖዋን፣ “እውነተኛው የወይን ተክል” ኢየሱስን እንዲሁም “ቅርንጫፎቹ”b ደቀ መዛሙርቱን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። ታዲያ የክርስቶስ ተከታዮች ማፍራት ያለባቸው ፍሬ ምንድን ነው? ኢየሱስ ይህ ፍሬ ምን እንደሆነ በቀጥታ አልተናገረም፤ ሆኖም የፍሬውን ምንነት ለማወቅ የሚረዳ ጠቃሚ ፍንጭ ሰጥቶናል።
8. (ሀ) በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ፍሬ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ሊያመለክት አይችልም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ነገር በተመለከተ እርግጠኞች መሆን የምንችልበት ሐቅ የትኛው ነው?
8 ኢየሱስ “በእኔ ላይ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ [አባቴ] ቆርጦ ይጥለዋል” ብሏል። በሌላ አባባል ይሖዋ እንደ አገልጋዮቹ አድርጎ የሚመለከተን ፍሬ የምናፈራ ከሆነ ብቻ ነው። (ማቴ. 13:23፤ 21:43) ስለሆነም በዚህ ምሳሌ ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን ማፍራት እንዳለበት የተጠቀሰው ፍሬ፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማስገኘትን የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። (ማቴ. 28:19) ይህ ባይሆን ኖሮ አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ የሚያገለግሉ ታማኝ ክርስቲያኖች፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማስገኘት ባለመቻላቸው ምክንያት በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሱት ፍሬ የማያፈሩ ቅርንጫፎች ይቆጠሩ ነበር። ይሁንና ይህ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው! ለምን? ምክንያቱም ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ማስገደድ አንችልም። ይህ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር ነው፤ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ደግሞ ከአቅማችን በላይ የሆነውን ነገር ባለማድረጋችን ምክንያት አገልጋዮቹ ለመሆን ብቁ እንዳልሆንን አድርጎ ይመለከተናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ማድረግ የማንችለውን ነገር አይጠብቅብንም።—ዘዳ. 30:11-14
9. (ሀ) ፍሬ ማፍራት የምንችለው የትኛውን ሥራ በማከናወን ነው? (ለ) የትኛውን ምሳሌ እንመለከታለን? ለምንስ?
9 ለመሆኑ ልናፈራው የሚገባው ፍሬ ምንድን ነው? ፍሬው፣ ሁላችንም ልናከናውን የምንችለውን ሥራ የሚያመለክት መሆን አለበት። ታዲያ ‘ፍሬ እንደማፍራት’ ሊቆጠር የሚችለው ሥራ የትኛው ነው? የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው።c (ማቴ. 24:14) ኢየሱስ ስለ አንድ ዘሪ የተናገረው ምሳሌ ይህን ያረጋግጣል። እስቲ ይህን ምሳሌ ደግሞ እንመልከት።
10. (ሀ) በዚህ ምሳሌ ላይ ዘሩ እና አፈሩ ምን ያመለክታሉ? (ለ) የስንዴ ቡቃያ አድጎ ፍሬ አፈራ የሚባለው መቼ ነው?
10 ሉቃስ 8:5-8, 11-15ን አንብብ። ስለ ዘሪው በሚናገረው ምሳሌ ላይ ዘሩ የሚያመለክተው ‘የአምላክን ቃል’ ወይም የመንግሥቱን መልእክት ነው። አፈሩ ደግሞ የሰዎችን ምሳሌያዊ ልብ ያመለክታል። ጥሩ አፈር ላይ የወደቀው ዘር ሥር ሰድዶ በቀለ፤ እድገት እያደረገም ሄደ። ከዚያም ‘100 እጥፍ አፈራ።’ የተዘራው ዘር ስንዴ ነው እንበል፤ የስንዴ ቡቃያ አድጎ ፍሬ አፈራ የሚባለው ሌሎች ቡቃያዎች ሲያወጣ ሳይሆን ዛላው ፍሬ ወይም ዘር ሲይዝ ነው። እርግጥ እነዚህ አዳዲስ የስንዴ ዘሮች ውሎ አድሮ አዳዲስ ቡቃያዎች ሊያወጡ ይችላሉ። በዚህ ምሳሌ ላይ አንዱ ዘር መቶ ዘሮችን አስገኝቷል። ታዲያ ይህ ምሳሌ ከአገልግሎታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
11. (ሀ) ስለ ዘሪው የሚናገረው ምሳሌ ከአገልግሎታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ለ) አዲስ የመንግሥቱን ዘር ማፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?
11 ክርስቲያን ወላጆቻችን ወይም ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲነግሩን በጥሩ አፈር ላይ ዘር የዘሩ ያህል ነው። ደግሞም በዘር የተመሰለውን የመንግሥቱን መልእክት በመቀበላችን በጣም እንደተደሰቱ ጥያቄ የለውም። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ጥሩ አፈር፣ ዘሩ ተመችቶት እንዲያድግ እንዳስቻለ ሁሉ እኛም መልእክቱን ተቀብለን በልባችን ውስጥ አኖርነው። እንዲህ በማድረጋችን፣ በዘር የተመሰለው የመንግሥቱ መልእክት በልባችን ውስጥ ሥር ሰድዶ በማደግ በምሳሌያዊ አነጋገር ቡቃያ ሆነ፤ ውሎ አድሮም ቡቃያው ፍሬ ለማፍራት ደረሰ። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የስንዴ ቡቃያ አድጎ ፍሬ አፈራ የሚባለው ሌሎች ቡቃያዎችን ሲያወጣ ሳይሆን አዲስ ዘር ሲይዝ ነው፤ በተመሳሳይ እኛም ፍሬ አፈራን የሚባለው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስናስገኝ ሳይሆን አዳዲስ የመንግሥቱን ዘሮች ስናፈራ ነው።d ለመሆኑ አዲስ የመንግሥቱን ዘር ማፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በተናገርን ቁጥር በልባችን ውስጥ ያለውን ዘር እየዘራነው ወይም እያሰራጨነው ነው ሊባል ይችላል። (ሉቃስ 6:45፤ 8:1) በመሆኑም የመንግሥቱን መልእክት ማወጃችንን እስከቀጠልን ድረስ ‘በጽናት ፍሬ እያፈራን’ እንዳለ ከዚህ ምሳሌ እንማራለን።
12. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ወይን ተክሉና ስለ ዘሪው ከተናገራቸው ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ይፈጥርብሃል?
12 ኢየሱስ ስለ ወይን ተክሉና ስለ ዘሪው ከተናገራቸው ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? እነዚህ ምሳሌዎች፣ ፍሬ ማፍራት አለማፍራታችን የተመካው በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ለምሥራቹ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ሳይሆን በምናሳየው ታማኝነት ላይ እንደሆነ ያስተምሩናል። ጳውሎስም “እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል” በማለት መናገሩ ይህን ሐቅ ያጎላል። (1 ቆሮ. 3:8) ለአንድ ሰው የሚሰጠው ወሮታ የሚመካው፣ ሥራው በሚያስገኘው ውጤት ላይ ሳይሆን በሥራው ላይ ነው። ለ20 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ማቲልዳ “ይሖዋ ወሮታ የሚሰጠን ለጥረታችን መሆኑን ማወቄ ያስደስተኛል” ብላለች።
በጽናት ፍሬ ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?
13, 14. በሮም 10:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ የመንግሥቱን ምሥራች ላልተቀበሉት ሰዎች መስበኩን እንዲቀጥል ያነሳሱት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
13 በጽናት ፍሬ ማፍራታችንን እንድንቀጥል ምን ይረዳናል? ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ አይሁዳውያን የመንግሥቱን ምሥራች አለመቀበላቸው ለጳውሎስ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበት ነበር። ያም ቢሆን ለእነሱ መስበኩን አላቆመም። ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለእነዚህ አይሁዳውያን ያለውን ስሜት ሲገልጽ ምን እንዳለ እንመልከት፦ “ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው። ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም።” (ሮም 10:1, 2) ለመሆኑ ጳውሎስ ለእነሱ መስበኩን እንዲቀጥል ያነሳሱት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
14 ጳውሎስ ለአይሁዳውያን ለመስበክ ያነሳሳው የመጀመሪያው ነገር ‘የልቡ ምኞት’ እንደሆነ ገልጿል። አይሁዳውያን እንዲድኑ ከልቡ ይጓጓ ነበር። (ሮም 11:13, 14) በሁለተኛ ደረጃ ጳውሎስ “ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ” እንደሚያቀርብ ተናግሯል። ሐዋርያው ቢያንስ አንዳንድ አይሁዳውያን የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ይሖዋን ተማጽኗል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አይሁዳውያን “ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው” ገልጿል። እነዚህ ሰዎች መልካም ጎን እንዳላቸውና አምላክን ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አስተውሏል። ጳውሎስ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ካደረጉ ቀናተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን እንደሚችሉ ያውቅ ነበር፤ የራሱ ተሞክሮም ለዚህ ምሥክር ይሆናል።
15. የጳውሎስን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
15 እኛስ የጳውሎስን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን የማግኘት ልባዊ ምኞት ለማዳበር እንጥራለን። ሁለተኛ፣ ይሖዋ ቀና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ልብ እንዲከፍት በጸሎት እንማጸነዋለን። (ሥራ 13:48፤ 16:14) ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች ሲልቫና የምትባል እህት “በክልሌ ውስጥ አንድን ቤት ከማንኳኳቴ በፊት አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” ብላለች። በተጨማሪም አምላክ በመላእክቱ ተጠቅሞ ቅን ልብ ወዳላቸው ሰዎች እንዲመራን እንጸልያለን። (ማቴ. 10:11-13፤ ራእይ 14:6) ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ከመላእክት ጋር አብሮ መሥራት በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፤ ምክንያቱም መላእክት፣ በምንሰብክላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ያውቃሉ።” ሦስተኛ ደግሞ የምንሰብክላቸውን ሰዎች መልካም ጎን ለማየት ብሎም የይሖዋ አገልጋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሰብ እንጥራለን። ከተጠመቀ ከ50 ዓመት በላይ የሆነው ካርል የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንድ ሰው ቅን ልብ እንዳለው የሚጠቁሙ ትናንሽ ነገሮችን ለምሳሌ ፊቱ ላይ ፈገግታ የሚነበብ መሆኑን፣ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየቱን አሊያም ጥሩ ጥያቄዎችን የሚያነሳ መሆኑን ለማስተዋል እሞክራለሁ።” በእርግጥም እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በጽናት ፍሬ ማፍራት እንችላለን።
“እጅህ ሥራ አይፍታ”
16, 17. (ሀ) በመክብብ 11:6 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ዘር የመዝራቱ ሥራችን በሚመለከቱን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።
16 የምንሰብከው መልእክት ወደ ሰዎች ልብ ጠልቆ እንዳልገባ ቢሰማንም እንኳ ዘር የመዝራቱ ሥራችን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልለን መመልከት የለብንም። (መክብብ 11:6ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች የምንናገረውን መልእክት አያዳምጡም፤ ያም ሆኖ ሁኔታችንን ማየታቸው አይቀርም። ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበሳችንን፣ ትሕትናችንን እንዲሁም ሞቅ ያለ ፈገግታችንን ያስተውላሉ። ምግባራችን፣ አንዳንዶች ስለ እኛ ያላቸው አሉታዊ አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን ውሎ አድሮ እንዲገነዘቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሰርዦ እና ኦሊንዳ ይህ እውነት መሆኑን ተመልክተዋል።
17 ሰርዦ እንዲህ ብሏል፦ “በሕመም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደዚያ አደባባይ አልሄድንም ነበር። በኋላ ላይ ተመልሰን ስንሄድ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ‘ምነው ጠፋችሁ? ናፍቃችሁን ነበር’ አሉን።” ኦሊንዳም ፊቷ በፈገግታ ተሞልቶ እንዲህ ትላለች፦ “የአውቶቡስ ሾፌሮች ሲያልፉ እጃቸውን እያውለበለቡ ሰላም ያሉን ሲሆን አንዳንዶቹም ከመኪናቸው ሆነው ‘በርቱ!’ ይሉን ነበር። መጽሔት እንድንሰጣቸው የጠየቁንም አሉ።” እንዲያውም አንድ ሰው፣ ባልና ሚስቱ ወደሚሰብኩበት ቦታ በመምጣት እቅፍ አበባ ካበረከተላቸው በኋላ የሚያከናውኑትን ሥራ እንደሚያደንቅ ገለጸላቸው።
18. ‘በጽናት ፍሬ ለማፍራት’ የቆረጥከው ለምንድን ነው?
18 በእርግጥም የመንግሥቱን ዘር ከመዝራት ‘እጃችን ሥራ እስካልፈታ’ ድረስ ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክርነት’ በመስጠቱ ሥራ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት እንችላለን። (ማቴ. 24:14) ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ እንደምናገኝ ማወቃችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል፤ ምክንያቱም ይሖዋ “በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” ሰዎችን ሁሉ ይወዳል።
a ኢየሱስም እንኳ “በገዛ አገሩ” መስበክ ተፈታታኝ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች በዘገባቸው ላይ ይህን ሐሳብ አስፍረውታል።—ማቴ. 13:57፤ ማር. 6:4፤ ሉቃስ 4:24፤ ዮሐ. 4:44
b በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ቅርንጫፎች የሚያመለክቱት ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ቢሆንም ከምሳሌው ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።
c ‘ፍሬ ማፍራት’ የሚለው አገላለጽ “የመንፈስ ፍሬ” ማፍራትንም ያመለክታል፤ ይሁንና በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ትኩረት የምናደርገው ‘የከንፈራችንን ፍሬ’ በማፍራት ወይም የስብከቱን ሥራ በማከናወን ላይ ነው።—ገላ. 5:22, 23፤ ዕብ. 13:15
d ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ ለማስተማር ሲል ዘር መዝራትንና ሰብል ማጨድን እንደ ምሳሌ የተጠቀመባቸው ጊዜያትም አሉ።—ማቴ. 9:37፤ ዮሐ. 4:35-38