በሥራችሁ እርካታ አግኙ
1. ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ሊያቀዘቅዘው የሚችለው ምንድን ነው?
1 ሰዎች የተፈጠሩት ‘በሥራቸው እርካታ’ እንዲያገኙ ተደርገው ነው። (መክ. 2:24) ይሁንና በአገልግሎታችን መልካም ውጤት ካላገኘን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ ቅንዓታችንም ሊቀዘቅዝ ይችላል። በዚህ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?
2. በአገልግሎታችን ላይ ሰዎች ስለሚሰጡት ምላሽ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
2 ምክንያታዊ ሁኑ፦ ለኢየሱስ ስብከት ጥሩ ምላሽ የሰጡት ጥቂቶች ቢሆኑም በአገልግሎቱ ውጤታማ እንደነበር አትዘንጉ። (ዮሐ. 17:4) ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ አብዛኞቹ ሰዎች በዘር ለተመሰለው የመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ እንደማይሰጡ አስቀድሞ ገልጿል። (ማቴ. 13:3-8, 18-22) ያም ቢሆን ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጋችን ብዙ ውጤት ማስገኘቱ አይቀርም።
3. ለስብከቱ ሥራችን በጎ ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ ‘ፍሬ ማፍራት’ የምንችለው እንዴት ነው?
3 ብዙ ፍሬ ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ መሠረት መልእክቱን የሚቀበሉ ሰዎች ‘ፍሬ ያፈራሉ።’ (ማቴ. 13:23) አንድ የስንዴ ቡቃያ የሚጎመራው ከሥሩ ሌሎች ትናንሽ ቡቃያዎችን በማውጣት ሳይሆን ዛላው ፍሬ ሲይዝ ነው። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ስኬታማ ለመሆን የግድ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት አይጠበቅበትም፤ ከዚህ ይልቅ የመንግሥቱን ዘር በብዙ እጥፍ ማፍራት በሌላ አባባል ስለ መንግሥቱ በተደጋጋሚ መናገር ይኖርበታል። የሰዎች ምላሽ ምንም ይሁን ምን ይህን በማድረጋችን እውነተኛ ‘እርካታ’ እናገኛለን። በዚህ መንገድ ፍሬ በማፍራት የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። (ኢሳ. 43:10-12፤ ማቴ. 6:9) በተጨማሪም ከአምላክ ጋር አብረን የመሥራት መብት በማግኘታችን እንደሰታለን። (1 ቆሮ. 3:9) እንዲህ ያለው “የከንፈር ፍሬ” ይሖዋን ያስደስተዋል።—ዕብ. 13:15, 16
4. አገልግሎታችን እኛ ሳናውቀው እንዴት ያለ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
4 በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለጊዜው ለእኛ ባይታየንም እንኳ በትጋት መስበካችን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። ኢየሱስ ሲሰብክ ከሰሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የእሱ ደቀ መዛሙርት የሆኑት ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። በተመሳሳይም በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የዘራነው የመንግሥቱ ዘር ወዲያውኑ ማደግ ላይጀምር ይችላል፤ በኋላ ላይ ግን እኛ ባናውቅም ግለሰቡ ወደ እውነት ይመጣ ይሆናል። በእርግጥም አገልግሎታችን ትልቅ ሥራ ያከናውናል። በመሆኑም ‘ብዙ ፍሬ በማፍራት’ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናሳይ።—ዮሐ. 15:8