በመታሰቢያው በዓል ላይ ጥሩ አቀባበል አድርጉላቸው
1 ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙት 3 ሰዎች መካከል የምሥራቹ አስፋፊ 1 ሰው ብቻ ነበር። በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ መሆኑ አይቀርም። አንዳንዶች በዚያ የተገኙት ዘመዳቸው ወይም አንድ በሌላ ከተማ የሚኖር የሚያውቁት ሰው ነግሯቸው አለበለዚያም የጉባኤው አስፋፊዎች ጋብዘዋቸው ይሆናል። በዚያ የሚገኙት ሌሎች ደግሞ የተጠመቁ ቢሆኑም እንኳ በአገልግሎት ቀዝቅዘው የቆዩ ናቸው። ኢየሱስ “ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ሲል ለሰጠው ትዕዛዝ አክብሮት ለሚያሳዩ ሰዎች ሁሉ ልባዊ አቀባበል እናደርግላቸዋለን። — 1 ቆሮ. 11:24፤ ሮሜ 15:7
2 የተመደቡ አስተናጋጆች ሁሉንም ሰው በተለይም አዲስ ሰው ከሆነ ወደ መንግሥት አዳራሹ እንደ ደረሰ ተቀብለው ለማስተናገድ ንቁ መሆን አለባቸው። ይሁን እንጂ ሁላችንም በመታሰቢያው በዓል ላይ እንግዳ ተቀባዮች መሆን እንችላን። (ሮሜ 12:13) ግን እንዴት?
3 በዚያ ምሽት አንዳንድ አስፋፊዎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎቸን በመኪና በማመላለስ በሥራ በጣም መያዛቸው አይቀርም። ሌሎች ደግሞ ቀደም ብለው በመገኘት በራሳቸው ትራንስፖርት የመጡትን እንግዶች ማስተናገድ ይችላሉ። አንድ እንግዳ ወደ አዳራሹ ሲገባ ሞቅ ያለ ሰላምታ ስጡት። ከዚያ ወዲያው ውይይት ክፈቱ። በጉባኤው ውስጥ የሚያውቀው ሰው እንዳለ ጠይቁት። የሚያውቀው ሰው ካለ ያ ሰው እስኪመጣ ድረስ በደንብ ተንከባከቡት። (ከሉቃስ 10:35 ጋር አወዳድሩ።) በግል የሚያውቀው ማንም ሰው ከሌለ በስብሰባው ወቅት ከእናንተ ጋር እንዲቀመጥ ለምን አትጋብዙትም? በፕሮግራሙ ወቅት ቂጣውና ወይኑ ምን እንደሚደረግ አስረዱት። ተናጋሪው የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶች ለማውጣትም የእናንተ እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል።
4 የመታሰቢያው በዓል ሲያበቃ በዚያ በመገኘቱ እንደ ተደሰታችሁ ግለጹለት። ሥራችንን በተመለከተ ልትመልሱለት የምትችሉት ጥያቄ ይኖረው ይሆናል። በግል ቀርባችሁ ያሳያችሁት ፍቅር እዚያው መንግሥት አዳራሹ ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ ተገናኝታችሁ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ላይ ውይይት ወደ ማድረግ ሊመራ ይችል ይሆናል። ይህንን የሚያስመሰግን እርምጃ የወሰዱ ንቁ ወንድሞች በጣም ጥሩ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አግኝተዋል። ከመንግሥት አዳራሹ ከመውጣቱ በፊት ከሌሎች ጋር አስተዋውቁትና ሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲመጣ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቡለት።
5 በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የማይገኙትን ወይም ለተወሰነ ጊዜ በአገልግሎታቸው ቀዝቅዘው የነበሩትን ውድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መቀበል እንዴት የሚያስደስት ነው! ለምን ጠፋህ ብላችሁ ከመጠየቅ ይልቅ በዚያ ስለተገኘ የተሰማችሁን ደስታ ግለጹለት። ምናልባት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ንግግር የሚሰሙት አንድ ነገር ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና መለስ ብለው እንዲያስቡበት ሊያደርጋቸው ይችል ይሆናል። ያደረጋችሁላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልና ያሳያችኋቸው እውነተኛ አሳቢነት ልባቸውን ሊነካው ይችላል። ዳግመኛ እነርሱን ለማየት እንደምትጓጉም አሳውቋቸው። — ሮሜ 1:11, 12
6 ሚያዝያ 10 ቀን በአብዛኞቹ ጉባኤዎች “እውነተኛው ሃይማኖት ለሰብአዊው ኀብረተሰብ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያሟላል” የሚል ርዕስ ያለው ልዩ የሕዝብ ንግግር ይሰጣል። በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሁሉ ንግግሩን እንዲያዳምጡ ጋብዟቸው፤ በስብሰባው ላይ ለመገኘት እንዲችሉም ድጋፍ አድርጉላቸው። በእነዚህ ልዩ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግላቸውና በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን የሞቀ የወንድማማች መንፈስ ማየት እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን። — መዝ. 133:1