ምን አማራጮች እንዳሉህ ታውቃለህ?
በዓለም ላይ፣ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ የሕክምና ማዕከሎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ያለ ደም የሚሰጡ የሕክምና ዓይነቶችን በተመለከተ ስላሉት አማራጮች በሚገባ ታውቃለህ? ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ እንድትችል ስለ እነዚህ ጉዳዮች በደንብ ማወቅ ያስፈልግሃል። በመጀመሪያ ደም አልወስድም—የሕክምናው መስክ መፍትሔ አስገኝቷል የተባለውን ፊልም ተመልከት፤ ከዚያም ከታች የቀረቡትን ጥያቄዎች በመጠቀም ከፊልሙ ምን እውቀት እንዳገኘህ በጸሎት አስብበት።—ማሳሰቢያ፦ ቪዲዮው ቀዶ ሕክምና ሲደረግ የሚያሳዩ ክፍሎች ስላሉት ወላጆች ትናንሽ ልጆቻቸው ፊልሙን ሊያዩት ይገባ እንደሆነና እንዳልሆነ አመዛዝነው መወሰን ይኖርባቸዋል።
(1) የይሖዋ ምሥክሮች ደም የማይወስዱበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (2) በሕክምና ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ምንድን ነው? (3) ታካሚዎች ምን መሠረታዊ መብት አላቸው? (4) አንድ ሰው በደም ምትክ የሚሰጥ ሕክምናን መምረጡ አስተዋይ እንዲሁም ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (5) ከባድ የሆነ የደም መፍሰስ ሲያጋጥም ሐኪሞች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ሁለት ተቀዳሚ ተግባራት የትኞቹ ናቸው? (6) በደም ምትክ የሚሠራባቸውን የሕክምና ዘዴዎች በተመለከተ አራቱ መሠረታዊ ደንቦች ምንድን ናቸው? (7) ዶክተሮች (ሀ) ብዙ ደም እንዳይፈስ (ለ) ቀይ የደም ሴሎች እንዳይባክኑ (ሐ) ሰውነት ደም እንዲያመርት (መ) የፈሰሰው ደም እንዲተካ የሚያደርጉት በምን መንገድ ነው? (8) (ሀ) ሄሞዳይሉሽን (ለ) ሴል ሳልቬጅ የሚባሉት የሕክምና ዓይነቶች አሠራራቸው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (9) ማንኛውንም በደም ምትክ የሚሰጥ ሕክምና በሚመለከት ማወቅ ያለባችሁ ነገር ምንድን ነው? (10) ያለ ደም ከባድ የሆኑና የተወሳሰቡ ቀዶ ሕክምናዎችን ማድረግ ይቻላል? (11) በሕክምናው መስክ ምን አበረታች እድገት እየተገኘ ነው?
በፊልሙ ላይ የቀረቡትን አንዳንድ የሕክምና አማራጮች መቀበልም ሆነ አለመቀበል እያንዳንዱ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው ተጠቅሞ የሚያደርገው የግል ውሳኔ ነው። ልጆችህን ጨምሮ አንተ ራስህ ምን ዓይነት ሕክምና እንደምትቀበል ወስነሃል? የሕክምና መመሪያ ካርድህንስ ሞልተሃል? በዚህ ጉዳይ ላይ የተሟላ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 15, 2004 እና በጥቅምት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” በጥንቃቄ ከልስ። ከዚያም በኅዳር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ በወጣው “የደም ክፍልፋዮችንና የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በተመለከተ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብኛል?” በሚለው ርዕስ ሥር በሚገኙት ቅጾች ላይ የምትቀበላቸውንና የማትቀበላቸውን የሕክምና አማራጮች አስመልክቶ ያደረግከውን የግል ውሳኔ አስፍር። በመጨረሻም ያደረግካቸውን ምርጫዎች የሕክምና መመሪያ ካርድህ ላይ በጥንቃቄ ገልብጥ። የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎች እንዲሆኑ የመረጥካቸው ሰዎችና የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የቤተሰብህ አባላት ያደረግከውን ውሳኔ በሚገባ እንዲያውቁት ማድረግ ይኖርብሃል።