እንግዳ ተቀባይ በመሆን ለሌሎች “ጥሩ ነገር” አካፍሉ (ማቴ. 12:35ሀ)
ሁላችንም “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” በማዳበር ለሌሎች “ጥሩ ነገር” ማካፈል እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። (ሮም 12:13) ሽማግሌዎች ከሌላ ጉባኤ የሚመጡ ተናጋሪዎች ተገቢውን መስተንግዶ እንዲያገኙና የጉዞ ወጪያቸው እንዲሸፈን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ይሁንና አቅማችን ውስን በመሆኑ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ከማሳየት ወደኋላ ልንል እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ሌሎችን ቤታችን መጋበዝ ያስጨንቀን ይሆናል። ኢየሱስ ለማርታ የሰጣትን ምክር ልብ ማለታችን እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ለማሸነፍ ይረዳናል። (ሉቃስ 10:39-42) እንግዳ በምንቀበልበት ጊዜ ‘የተሻለው ነገር’ ድል ያለ ግብዣ ማድረጋችን ወይም ቤታችን ያማረ መሆኑ ሳይሆን አብሮ ጊዜ ማሳለፍና እርስ በርስ መበረታታት እንደሆነ ኢየሱስ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህን ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ሁላችንም የአምላክ ቃል በሚያዘው መሠረት ለሌሎች “ጥሩ ነገር” ማካፈል እንችላለን።—3 ዮሐ. 5-8