የጥናት ርዕስ 45
በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ አምልኮ የማቅረብ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው
‘ሰማይንና ምድርን የሠራውን አምልኩ።’—ራእይ 14:7
መዝሙር 93 ለስብሰባ ስንገናኝ በረከትህ አይለየን
ማስተዋወቂያa
1. አንድ መልአክ ምን እያለ ነው? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
አንድ መልአክ ቢያነጋግርህ የሚለውን ለመስማት ፈቃደኛ ትሆናለህ? በአሁኑ ወቅት አንድ መልአክ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እየተናገረ ነው። መልእክቱ ምንድን ነው? “አምላክን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ . . . ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ” የሚል ነው። (ራእይ 14:6, 7) ሁሉም ሰው ሊያመልከው የሚገባው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ ነው። ይሖዋ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እሱን የማምለክ ውድ መብት ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን!
2. የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? (“ምን አይደለም?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
2 ለመሆኑ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? ይህን ቤተ መቅደስ በተመለከተ ማብራሪያ ማግኘት የምንችለውስ ከየት ነው? መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በእውን ያለ ሕንፃ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ እንድንችል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።b
3-4. ጳውሎስ በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን ዕብራውያን ክርስቲያኖች አስመልክቶ ያሳሰበው ነገር ምን ነበር? የረዳቸውስ እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈላቸው ለምንድን ነው? በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ሳይሆን አይቀርም። አንደኛ፣ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ስለፈለገ ነው። ብዙዎቹ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት የአይሁድ እምነት ተከታዮች ነበሩ። ክርስቲያን በመሆናቸው የተነሳ የቀድሞ የሃይማኖት መሪዎቻቸው አፊዘውባቸው ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያኖች አምልኮ የሚያቀርቡበት የሚያስደምም ቤተ መቅደስ፣ ለአምላክ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ እንዲሁም የሚያገለግሏቸው ካህናት አልነበሯቸውም። ይህ ሁኔታ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ተስፋ ሊያስቆርጣቸውና እምነታቸውን ሊያዳክመው ይችላል። (ዕብ. 2:1፤ 3:12, 14) ምናልባትም አንዳንዶቹ ወደ አይሁድ እምነት ለመመለስ ተፈትነው ሊሆን ይችላል።
4 ሁለተኛ፣ ጳውሎስ እነዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን “ጠንካራ ምግብ” ማለትም አዳዲስ ወይም ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለመረዳት ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 5:11-14) አንዳንዶቹ ያኔም የሙሴን ሕግ መከተላቸውን አላቆሙ ይሆናል። ይሁንና ጳውሎስ በሕጉ መሠረት የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደማይችሉ አብራርቶላቸዋል። በዚህም የተነሳ ሕጉ “ተሽሯል።” በመሆኑም ጳውሎስ ጥልቀት ያላቸውን አንዳንድ እውነቶች አስተማራቸው። የእምነት አጋሮቹ ‘ወደ አምላክ እንዲቀርቡ’ ሊረዳቸው የሚችል በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ “የተሻለ ተስፋ” እንዳላቸው አስታውሷቸዋል።—ዕብ. 7:18, 19
5. የዕብራውያን መጽሐፍን በመመርመር ስለ ምን መማር ይኖርብናል? ለምንስ?
5 ጳውሎስ የክርስቲያኖች የአምልኮ ሥርዓት ቀደም ሲል በሕጉ ሥር ያቀርቡ ከነበረው አምልኮ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ ለዕብራውያን ወንድሞቹ አብራርቶላቸዋል። በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩት የአምልኮ ዝግጅቶች “ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤ እውነተኛው ነገር ግን የክርስቶስ ነው።” (ቆላ. 2:17) የአንድ ነገር ጥላ የሚያሳየው የእውነተኛውን ነገር መሠረታዊ ቅርጽ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥንት የነበረው የአይሁዳውያን የአምልኮ ሥርዓት ወደፊት ለሚመጣው የተሻለ ነገር ጥላ ብቻ ነበር። ይሖዋ ለኃጢአታችን ይቅርታ አግኝተን ለእሱ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ እንድንችል ስላደረገልን ዝግጅት በሚገባ መረዳት ይኖርብናል። በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ማብራሪያ መሠረት አድርገን ‘ጥላውን’ (የጥንቱን የአይሁዳውያን የአምልኮ ሥርዓት) ‘ከእውነተኛው ነገር’ (ከክርስቲያኖች የአምልኮ ሥርዓት) ጋር እናወዳድር። እንዲህ ማድረጋችን ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስና ይህ ቤተ መቅደስ ለእኛ ስላለው ትርጉም ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።
የማደሪያው ድንኳን
6. የማደሪያው ድንኳን ጥቅም ላይ የዋለው በምን መንገድ ነው?
6 ጥላው። ጳውሎስ ማብራሪያውን የሰጠው ሙሴ በ1512 ዓ.ዓ. የተከለውን የማደሪያ ድንኳን መሠረት አድርጎ ነው። (“ጥላው—እውነተኛው ነገር” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።) እስራኤላውያን መጀመሪያ ላይ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ይህን የማደሪያ ድንኳን ተሸክመውት ይሄዱ ነበር። ይህን የማደሪያ ድንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤተ መቅደስ እስከተገነባበት ጊዜ ድረስ ለ500 ዓመት ያህል ተጠቅመውበታል። (ዘፀ. 25:8, 9፤ ዘኁ. 9:22) “የመገናኛ ድንኳኑ” እስራኤላውያን ወደ አምላክ መቅረብ እንዲሁም መሥዋዕትና አምልኮ ማቅረብ የሚችሉበት ማዕከላዊ ቦታ ነበር። (ዘፀ. 29:43-46) ይሁንና የማደሪያ ድንኳኑ ወደፊት በክርስትና ዘመን ለሚመጣው የላቀ ነገር ጥላ ሆኖ አገልግሏል።
7. መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ወደ ሕልውና የመጣው መቼ ነው?
7 እውነተኛው ነገር። የጥንቱ የማደሪያ ድንኳን ‘ለሰማያዊ ነገሮች ጥላ’ የነበረ ሲሆን ታላቁን የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ያመለክታል። ጳውሎስ “ይህ ድንኳን ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ” እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 8:5፤ 9:9) በመሆኑም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ተመሥርቷል ማለት ነው። ወደ ሕልውና የመጣው በ29 ዓ.ም. ነው። በዚያ ዓመት ኢየሱስ ተጠመቀ፤ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ፤ እንዲሁም በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ “ታላቅ ሊቀ ካህናት” ሆኖ ማገልገል ጀመረ።c—ዕብ. 4:14፤ ሥራ 10:37, 38
ሊቀ ካህናቱ
8-9. በዕብራውያን 7:23-27 መሠረት በእስራኤል ሊቃነ ካህናትና በታላቁ ሊቀ ካህናት በኢየሱስ መካከል ምን ትልቅ ልዩነት አለ?
8 ጥላው። ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ በአምላክ ፊት የመቅረብ ሥልጣን ነበረው። የእስራኤል የመጀመሪያ ሊቀ ካህናት የነበረውን አሮንን የሾመው ይሖዋ ሲሆን የተሾመውም የማደሪያ ድንኳኑ በተመረቀበት ወቅት ነው። ይሁንና ጳውሎስ እንደገለጸው “ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው።”d (ዕብራውያን 7:23-27ን አንብብ።) ደግሞም እነዚያ ሊቃነ ካህናት ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ስለነበሩ ለራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው። በእስራኤል በነበሩት ሊቃነ ካህናትና በታላቁ ሊቀ ካህናት በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት ይህ ነው።
9 እውነተኛው ነገር። ሊቀ ካህናታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የእውነተኛው ድንኳን አገልጋይ ነው፤ ይህም ድንኳን በሰው ሳይሆን በይሖዋ የተተከለ ነው።” (ዕብ. 8:1, 2) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም” ብሏል። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘ያልረከሰና ከኃጢአተኞች የተለየ’ እንደሆነ እንዲሁም ከእስራኤል ሊቃነ ካህናት በተለየ መልኩ ለራሱ ኃጢአት ‘በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ እንደማያስፈልገው’ ገልጿል። አሁን ደግሞ በአይሁድ እምነትና በክርስትና ውስጥ ባሉት መሠዊያዎችና መሥዋዕቶች መካከል ያለውን ልዩነት እንመልከት።
መሠዊያዎቹና መሥዋዕቶቹ
10. በመዳቡ መሠዊያ ላይ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ምን ያመለክታሉ?
10 ጥላው። በማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት የመዳብ መሠዊያ ነበር። (ዘፀ. 27:1, 2፤ 40:29) ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች የሕዝቡን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ሊያስተሰርዩ አልቻሉም። (ዕብ. 10:1-4) በማደሪያ ድንኳኑ በየጊዜው ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ለሚያወጣው መሥዋዕት ጥላ ሆነው አገልግለዋል።
11. ኢየሱስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት መሠዊያ ምንድን ነው? (ዕብራውያን 10:5-7, 10)
11 እውነተኛው ነገር። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ወደ ምድር የላከው ሰብዓዊ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ መሆኑን ያውቅ ነበር። (ማቴ. 20:28) በመሆኑም በተጠመቀበት ወቅት ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቀረበ። (ዮሐ. 6:38፤ ገላ. 1:4) ኢየሱስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው የአምላክን “ፈቃድ” በሚያመለክተው ምሳሌያዊ መሠዊያ ላይ ነው፤ የአምላክ ፈቃድ ልጁ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ነበር። ኢየሱስ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን ኃጢአት ለማስተሰረይ ወይም ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ሕይወቱን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። (ዕብራውያን 10:5-7, 10ን አንብብ።) ቀጥሎ ደግሞ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ያሉት ነገሮች ምን እንደሚያመለክቱ እንመርምር።
ቅድስቱ እና ቅድስተ ቅዱሳኑ
12. ወደ ቅድስቱ እና ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚችሉት እነማን ነበሩ?
12 ጥላው። የማደሪያ ድንኳኑም ሆነ ከጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም የተገነቡት ቤተ መቅደሶች መሠረታዊ ንድፋቸው ተመሳሳይ ነበር። ከውስጥ ሁለት ክፍሎች አሏቸው—‘ቅድስቱ’ እና ‘ቅድስተ ቅዱሳኑ።’ በመካከላቸው ደግሞ ጥልፍ የተጠለፈበት መጋረጃ አለ። (ዕብ. 9:2-5፤ ዘፀ. 26:31-33) ቅድስቱ ውስጥ የወርቅ መቅረዝ፣ የዕጣን መሠዊያ እንዲሁም የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ ነበር። ወደ ቅድስቱ ገብተው ቅዱስ አገልግሎት ማከናወን የሚፈቀድላቸው “ቅቡዕ የሆኑት ካህናት” ብቻ ነበሩ። (ዘኁ. 3:3, 7, 10) ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ደግሞ የይሖዋን መገኘት የሚወክለው ከወርቅ የተሠራው የቃል ኪዳኑ ታቦት ይገኛል። (ዘፀ. 25:21, 22) መጋረጃውን አልፎ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚፈቀድለት ሊቀ ካህናቱ ብቻ ሲሆን የሚገባውም በዓመታዊው የስርየት ቀን ላይ ነው። (ዘሌ. 16:2, 17) በየዓመቱ የራሱንም ሆነ የመላውን ብሔር ኃጢአት ለማስተሰረይ የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ እነዚህ የማደሪያ ድንኳኑ ገጽታዎች ያላቸውን እውነተኛ ትርጉም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ግልጽ አደረገ።—ዕብ. 9:6-8e
13. የማደሪያ ድንኳኑ ቅድስት እና ቅድስተ ቅዱሳን ምን ያመለክታሉ?
13 እውነተኛው ነገር። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል፤ እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና አላቸው። እነዚህ 144,000 ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 1:6፤ 14:1) ቅድስት የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና ምድር ላይ ሳሉ ያሉበትን ሁኔታ ማለትም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን ያመለክታል። (ሮም 8:15-17) ቅድስተ ቅዱሳን የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ደግሞ ይሖዋ የሚኖርበትን ሰማይን ያመለክታል። ቅድስቱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን የሚለየው “መጋረጃ” ኢየሱስ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ወደ ሰማይ እንዳይገባ ያገደውን ሥጋዊ አካሉን ያመለክታል። ኢየሱስ ሰብዓዊ አካሉን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። እነሱም ቢሆኑ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመቀበል ሥጋዊ አካላቸውን መተው ይጠበቅባቸዋል። (ዕብ. 10:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:50) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ገባ፤ ውሎ አድሮ ደግሞ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደዚያ ይገባሉ።
14. በዕብራውያን 9:12, 24-26 መሠረት ይሖዋ ያደረገው የመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት ያቋቋመው የንጹሕ አምልኮ ዝግጅት የላቀ መሆኑን እዚህ ላይ በግልጽ ማየት እንችላለን። በእስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት፣ መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትን እንስሳት ደም ይዞ በሰው እጅ ወደተሠራው ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ከየትኛውም ቦታ ይበልጥ ቅዱስ ወደሆነው ወደ ሰማይ በመግባት በይሖዋ ፊት ቀርቧል። በዚያም የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ በአምላክ ፊት አቀረበ፤ ይህን ያደረገው ለእኛ ሲል “ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ኃጢአትን ለማስወገድ” ነው። (ዕብራውያን 9:12, 24-26ን አንብብ።) ኃጢአትን ለዘላለም ማስወገድ የሚችለው ብቸኛው መሥዋዕት የኢየሱስ መሥዋዕት ነው። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ፣ ሁላችንም ይሖዋን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ማምለክ እንችላለን።
ግቢዎቹ
15. በማደሪያ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ የሚያገለግሉት እነማን ነበሩ?
15 ጥላው። የማደሪያ ድንኳኑ፣ ካህናቱ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት በአጥር የተከለለ አንድ ግቢ ነበረው። የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት ትልቁ የመዳብ መሠዊያ የሚገኘው በግቢው ውስጥ ነበር። ካህናቱ ቅዱስ የሆኑ ሥራዎቻቸውን ከማከናወናቸው በፊት ለመታጠብ የሚጠቀሙበት ከመዳብ የተሠራው የውኃ ገንዳም የሚገኘው እዚያው ነው። (ዘፀ. 30:17-20፤ 40:6-8) ከጊዜ በኋላ የተገነቡት ቤተ መቅደሶች ግን ካህናት ያልሆኑ ሰዎች መጥተው ይሖዋን ማምለክ የሚችሉበት ውጨኛ ግቢም ነበራቸው።
16. በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ ግቢና ውጨኛ ግቢ ውስጥ የሚያገለግሉት እነማን ናቸው?
16 እውነተኛው ነገር። በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሰማይ ላይ ከኢየሱስ ጋር ካህናት ሆነው ማገልገል ከመጀመራቸው በፊት በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ ግቢ ውስጥ በታማኝነት ያገለግላሉ። ትልቅ የውኃ ገንዳ መኖሩ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያስታውሳቸዋል፤ እርግጥ ይህ ማሳሰቢያ ለሁሉም ክርስቲያኖች አስፈላጊ ነው። ይሁንና የኢየሱስን ቅቡዓን ወንድሞች በታማኝነት የሚደግፉት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አምልኮ የሚያቀርቡት የት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ‘በአምላክ ዙፋን ፊት ሆነው በቤተ መቅደሱ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ’ ተመልክቷል፤ እጅግ ብዙ ሕዝብ ይህን የሚያደርጉት በምድር ላይ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውጨኛ ግቢ ውስጥ ሆነው ነው። (ራእይ 7:9, 13-15) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ቦታ ያለን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!
ይሖዋን የማምለክ መብታችን
17. ለይሖዋ ምን ዓይነት መሥዋዕት የማቅረብ መብት አለን?
17 በዛሬው ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ተጠቅመው ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማራመድ ለይሖዋ መሥዋዕት የማቅረብ መብት አላቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንደነገራቸው “የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ” ማቅረብ እንችላለን፤ “ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት የከንፈራችን ፍሬ ነው።” (ዕብ. 13:15) ካሉን ነገሮች መካከል ምርጡን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን በማቅረብ እሱን የማምለክ መብታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን።
18. በዕብራውያን 10:22-25 መሠረት የትኞቹን ነገሮች ፈጽሞ ችላ ልንል አይገባም? ልንረሳው የማይገባው ነገርስ ምንድን ነው?
18 ዕብራውያን 10:22-25ን አንብብ። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ አካባቢ ፈጽሞ ችላ ልንላቸው የማይገቡ የተለያዩ የአምልኳችንን ገጽታዎች ጠቅሷል። ከእነዚህ መካከል ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ፣ ተስፋችንን በይፋ ማወጅ፣ በጉባኤ ደረጃ አንድ ላይ መሰብሰብ እንዲሁም “[የይሖዋ ቀን] እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ መበረታታት ይገኙበታል። በራእይ መጽሐፍ መደምደሚያ አካባቢ የይሖዋ መልአክ ሁለት ጊዜ “ለአምላክ ስገድ!” ብሏል፤ ይህም ይሖዋን የማምለክን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ራእይ 19:10፤ 22:9) ታላቁን የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ያገኘነውን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነት እንዲሁም ያለንን ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን የማምለክ ውድ መብት ፈጽሞ ልንረሳው አይገባም!
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ
a በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች አንዱ ስለ ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚገልጸው ነው። ይህ ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? ይህ የጥናት ርዕስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዕብራውያን መጽሐፍ ስለዚህ ቤተ መቅደስ በሚሰጠው ማብራሪያ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ጥናት፣ ይሖዋን የማምለክ መብትህን ይበልጥ ከፍ አድርገህ እንድትመለከተው እንደሚያነሳሳህ ተስፋ እናደርጋለን።
b የዕብራውያን መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት የዕብራውያን መጽሐፍ ማስተዋወቂያ የተባለውን ቪዲዮ ከjw.org ላይ ተመልከት።
c በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ኢየሱስን ሊቀ ካህናት ብሎ የሚጠራው የዕብራውያን መጽሐፍ ብቻ ነው።
d አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ እስራኤል ውስጥ ወደ 84 የሚደርሱ ሊቃነ ካህናት የነበሩ ይመስላል።
g በሐምሌ 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምን ትርጉም እንዳለው መንፈስ የገለጠው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።