ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
2 በተጨማሪም፣ እናንተ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት ሙታን የነበራችሁ ቢሆንም አምላክ ሕያው አድርጓችኋል፤+ 2 በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ሥርዓት* ተከትላችሁ፣+ የአየሩ ሥልጣን ገዢ+ በሚፈልገው መንገድ ትመላለሱ ነበር፤ ይህም አየር በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ ነው።+ 3 አዎ፣ እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንንና የሐሳባችንን ፈቃድ እየፈጸምን+ ከሥጋችን ፍላጎት ጋር ተስማምተን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤+ እንደ ሌሎቹ ሁሉ እኛም በተፈጥሯችን የቁጣ ልጆች ነበርን።+ 4 ሆኖም አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው፤+ እኛን ከወደደበት ታላቅ ፍቅሩ የተነሳ+ 5 በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜም እንኳ ሕያዋን አድርጎ ከክርስቶስ ጋር አንድ አደረገን፤+ እንደ እውነቱ ከሆነ የዳናችሁት በጸጋ ነው። 6 ደግሞም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ስላለን ከእሱ ጋር አስነሳን፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን፤+ 7 ይህን ያደረገው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላለን ለእኛ በቸርነቱ* የገለጠውን ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና በመጪዎቹ ሥርዓቶች* ያሳይ ዘንድ ነው።
8 እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት በዚህ ጸጋ ነው፤+ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት አይደለም፤ ይልቁንም የአምላክ ስጦታ ነው። 9 ማንም ሰው የሚኩራራበት ምክንያት እንዳይኖር ይህ በሥራ የሚገኝ አይደለም።+ 10 እኛ የአምላክ የእጁ ሥራዎች ነን፤ ደግሞም አምላክ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለን አንድነት+ የፈጠረን፣+ እኛ እንድንሠራቸው አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ ነው።
11 ስለዚህ በሰው እጅ በሥጋ “የተገረዙት፣” በአንድ ወቅት በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁትን እናንተን “ያልተገረዙ” ይሏችሁ እንደነበር አስታውሱ። 12 በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ብሔር ተገልላችሁና ለተስፋው ቃል ኪዳኖች+ ባዕዳን ሆናችሁ በዓለም ውስጥ ያለተስፋና ያለአምላክ እንዲሁም ያለክርስቶስ ትኖሩ እንደነበረ አስታውሱ።+ 13 ሆኖም እናንተ በአንድ ወቅት ርቃችሁ የነበራችሁ አሁን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላችሁ ሆናችኋል፤ እንዲሁም በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። 14 ሁለቱን ወገኖች አንድ ያደረገውና+ ይለያያቸው የነበረውን በመካከል ያለ ግድግዳ ያፈረሰው+ እሱ ሰላም አምጥቶልናልና።+ 15 ሁለቱን ወገኖች ከራሱ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ አንድ አዲስ ሰው መፍጠርና+ ሰላም ማስፈን ይችል ዘንድ በሥጋው አማካኝነት ጠላትነትን ይኸውም ትእዛዛትንና ድንጋጌዎችን የያዘውን ሕግ አስወገደ፤ 16 እንዲሁም ይህን ያደረገው በመከራው እንጨት*+ ሁለቱን ወገኖች አንድ አካል አድርጎ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ ለማስታረቅ ነው፤ ምክንያቱም በገዛ አካሉ ጠላትነትን አስወግዷል።+ 17 እሱም መጥቶ ከአምላክ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሆነ ወደ እሱ ቀርበው ለነበሩት የሰላምን ምሥራች አወጀ፤ 18 ምክንያቱም እኛ፣ የሁለቱም ወገን ሕዝቦች በእሱ አማካኝነት በአንድ መንፈስ ወደ አብ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።
19 ስለዚህ እናንተ ከዚህ በኋላ እንግዶችና ባዕዳን አይደላችሁም፤+ ከዚህ ይልቅ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና+ የአምላክ ቤተሰብ አባላት ናችሁ፤+ 20 እንዲሁም በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ተገንብታችኋል፤+ ዋናው የመሠረት ድንጋይ* ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው።+ 21 ሕንጻው በሙሉ ከክርስቶስ ጋር አንድ ላይ በመሆን ልዩ ልዩ ክፍሎቹ ስምም ሆነው እየተገጣጠሙ+ የይሖዋ* ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን በማደግ ላይ ነው።+ 22 እናንተም ከእሱ ጋር ባላችሁ አንድነት አምላክ በመንፈስ የሚኖርበት ቦታ ለመሆን አንድ ላይ እየተገነባችሁ ነው።+