የጥናት ርዕስ 45
መዝሙር 138 ሽበት ያለው ውበት
ታማኝ ሰዎች ከተናገሯቸው የስንብት ቃላት ተማሩ
“በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣ ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?”—ኢዮብ 12:12
ዓላማ
ይሖዋ አምላክን መታዘዝ በአሁኑ ጊዜ በረከት ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።
1. ከአረጋውያን መማር ያለብን ለምንድን ነው?
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ስናደርግ ምክር ያስፈልገናል። ከጉባኤ ሽማግሌዎችና ከሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ምክር ማግኘት እንችላለን። ዕድሜያቸው ከእኛ በጣም የሚበልጥ ከሆነ ምክራቸው ዘመን ያለፈበት እንደሆነ ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋ ከአረጋውያን እንድንማር ይፈልጋል። ከእኛ የበለጠ ረጅም ዕድሜ ስለኖሩ ተሞክሮ፣ ማስተዋልና ጥበብ ማካበት ችለዋል።—ኢዮብ 12:12
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማበረታታትና ለመምራት ታማኝ አረጋውያንን ተጠቅሟል። ሙሴን፣ ዳዊትንና ሐዋርያው ዮሐንስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ሰዎች የኖሩት በተለያየ ዘመን ነው፤ የነበሩበት ሁኔታም ቢሆን በእጅጉ ይለያያል። የሕይወታቸው ማብቂያ ሲቃረብ ለወጣቶች ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጥተዋል። ሦስቱም ታማኝ አረጋውያን አምላክን መታዘዝ ያለውን ጥቅም ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች የተናገሯቸው ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት እስከ ዘመናችን ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርጓል። ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን የእነሱን ምክር መመርመራችን ይጠቅመናል። (ሮም 15:4፤ 2 ጢሞ. 3:16) እነዚህ ሦስት አረጋውያን የተናገሯቸውን የስንብት ቃላት እንዲሁም ከተናገሩት ሐሳብ የምናገኘውን ትምህርት በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
‘ረጅም ዕድሜ ትኖራለህ’
3. ሙሴ በየትኞቹ መንገዶች አገልግሏል?
3 ሙሴ ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ ሰው ነበር። ነቢይ፣ ፈራጅ፣ የጦር አዛዥና ታሪክ ጸሐፊ ሆኖ አገልግሏል። ሙሴ ብዙ የሕይወት ተሞክሮ ነበረው። የእስራኤል ብሔርን እየመራ ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷል፤ እንዲሁም ይሖዋ የፈጸማቸውን በርካታ ተአምራት በዓይኑ ተመልክቷል። የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አምስት መጻሕፍት፣ መዝሙር 90ን ምናልባት ደግሞ መዝሙር 91ንም ጭምር እንዲጽፍ ይሖዋ ተጠቅሞበታል። የኢዮብ መጽሐፍንም የጻፈው እሱ ሳይሆን አይቀርም።
4. ሙሴ ማበረታቻ የሰጠው ለማን ነው? ለምንስ?
4 ሙሴ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የ120 ዓመት አረጋዊ ሳለ መላውን የእስራኤል ማኅበረሰብ በመሰብሰብ ያዩአቸውንና ያሳለፏቸውን አንዳንድ ነገሮች አስታወሳቸው። ከአድማጮቹ መካከል አንዳንዶቹ በወጣትነታቸው ይሖዋ የፈጸማቸውን በርካታ ተአምራት እንዲሁም በግብፅ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ተመልክተዋል። (ዘፀ. 7:3, 4) ቀይ ባሕር ሲከፈል በመካከሉ ተራምደው አልፈዋል፤ የፈርዖን ሠራዊት ሲጠፋም አይተዋል። (ዘፀ. 14:29-31) በምድረ በዳ የይሖዋን ጥበቃና እንክብካቤ አጣጥመዋል። (ዘዳ. 8:3, 4) አሁን ብሔሩ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ ተቃርቧል። ሙሴ ይህን የመጨረሻ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሕዝቡን አበረታታ።a
5. በዘዳግም 30:19, 20 ላይ የሚገኙት የሙሴ የስንብት ቃላት ለእስራኤላውያን ምን ዋስትና ይሰጣሉ?
5 ሙሴ ምን ብሏል? (ዘዳግም 30:19, 20ን አንብብ።) እስራኤላውያን ከፊታቸው ግሩም ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። በይሖዋ እርዳታ ተስፋይቱ ምድር ውስጥ ረጅም ዘመን መኖር ይችላሉ። ደግሞም ምድሪቱ እጅግ ውብና ፍሬያማ ነበረች። ሙሴ ስለ ተስፋይቱ ምድር ሲናገር እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንተ ያልገነባሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞች፣ አንተ ባልደከምክባቸው የተለያዩ መልካም ነገሮች የተሞሉ ቤቶችን፣ አንተ ያልቦረቦርካቸውን የውኃ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም አንተ ያልተከልካቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች [ታገኛለህ]።”—ዘዳ. 6:10, 11
6. አምላክ ሌሎች ብሔራት እስራኤላውያንን ድል እንዲያደርጉ የፈቀደው ለምንድን ነው?
6 ሙሴ ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያም ሰጥቷቸዋል። በዚያች ፍሬያማ ምድር ውስጥ መኖራቸውን መቀጠል ከፈለጉ የይሖዋን ትእዛዛት መከተል ነበረባቸው። ሙሴ የይሖዋን ቃል በመስማትና “ከእሱ ጋር በመጣበቅ” ‘ሕይወትን እንዲመርጡ’ አበረታቷቸዋል። ሆኖም እስራኤላውያን ይሖዋን አልታዘዙም። በመሆኑም አምላክ በአሦራውያን፣ በኋላም በባቢሎናውያን ድል እንዲደረጉና በግዞት እንዲወሰዱ ፈቀደ።—2 ነገ. 17:6-8, 13, 14፤ 2 ዜና 36:15-17, 20
7. ሙሴ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 ምን ትምህርት እናገኛለን? ታዛዥነት ሕይወት ያስገኛል። በተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ እኛም አምላክ ቃል ወደገባው አዲስ ዓለም ልንገባ በጣም ተቃርበናል። ያኔ ምድር ገነት ትሆናለች። (ኢሳ. 35:1፤ ሉቃስ 23:43) ዲያብሎስና አጋንንቱ አይኖሩም። (ራእይ 20:2, 3) ሰዎችን ከይሖዋ የሚያርቅ የሐሰት ሃይማኖት አይኖርም። (ራእይ 17:16) ዜጎቻቸውን የሚጨቁኑ ሰብዓዊ መንግሥታት አይኖሩም። (ራእይ 19:19, 20) በገነት ውስጥ ለዓመፀኞች ቦታ የለም። (መዝ. 37:10, 11) በሁሉም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ስለሚያከብሩ አንድነትና ሰላም ይሰፍናል። ሁሉም ሰዎች እርስ በርስ ይዋደዳሉ እንዲሁም ይተማመናሉ። (ኢሳ. 11:9) እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! ግን ይህ ብቻ አይደለም። ይሖዋን ከታዘዝን በገነት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም መኖር እንችላለን።—መዝ. 37:29፤ ዮሐ. 3:16
8. የዘላለም ሕይወት ተስፋ አንድን ሚስዮናዊ የረዳው እንዴት ነው? (ይሁዳ 20, 21)
8 አምላክ የሰጠንን የዘላለም ሕይወት ተስፋ በአእምሯችን አቅርበን ከተመለከትን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ከእሱ ጋር ለመጣበቅ እንነሳሳለን። (ይሁዳ 20, 21ን አንብብ።) ይህ ተስፋ ከግል ድክመቶቻችን ጋር ለመታገልም ብርታት ይሰጠናል። አፍሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በሚስዮናዊነት ያገለገለ አንድ ወንድም ሥር ከሰደደ የሥጋ ድክመት ጋር መታገል አስፈልጎታል። እንዲህ ብሏል፦ “ለዘላለም የመኖር ተስፋዬ አደጋ ላይ እንደወደቀ መገንዘቤ ችግሩን ለመዋጋት ይበልጥ ቁርጠኛ እንድሆንና ወደ ይሖዋ ልባዊ ምልጃ እንዳቀርብ አነሳስቶኛል። በእሱ እርዳታ ድክመቴን ማሸነፍ ችያለሁ።”
“ይሳካልሃል”
9. ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ የትኞቹን ፈተናዎች አሳልፏል?
9 ዳዊት በጣም ጥሩ ንጉሥ ነበር። በተጨማሪም ሙዚቀኛ፣ ገጣሚ፣ ተዋጊና ነቢይ ነበር። ዳዊት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል። ንጉሥ ሳኦል ስለቀናበት ለተወሰኑ ዓመታት ያህል በስደት ለመኖር ተገዷል። ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላም ልጁ አቢሴሎም ዙፋኑን ለመንጠቅ በሞከረበት ወቅት ሕይወቱን ለማትረፍ በድጋሚ መሸሽ አስፈልጎታል። ዳዊት ብዙ መከራዎችን ያሳለፈና አንዳንድ ኃጢአቶችን የሠራ ቢሆንም እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” በማለት ገልጾታል። በመሆኑም የዳዊትን ምክር መስማታችን ተገቢ ነው!—ሥራ 13:22፤ 1 ነገ. 15:5
10. ዳዊት አልጋ ወራሹ ለሆነው ለልጁ ለሰለሞን ምክር የሰጠው ለምንድን ነው?
10 ዳዊት አልጋ ወራሹ ለሆነው ለልጁ ለሰለሞን ምን ምክር እንደሰጠው እንመልከት። ወጣቱ ሰለሞን እውነተኛውን አምልኮ እንዲያስፋፋ እንዲሁም አምላክን የሚያስከብር ቤተ መቅደስ እንዲገነባ ይሖዋ መርጦት ነበር። (1 ዜና 22:5) ሰለሞን ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል። ታዲያ ዳዊት ምን ምክር ይሰጠው ይሆን? እስቲ እንመልከት።
11. በ1 ነገሥት 2:2, 3 መሠረት ዳዊት ለሰለሞን ምን ምክር ሰጥቶታል? ዳዊት የተናገራቸው ቃላት እውነት ሆነው የተገኙትስ እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ዳዊት ምን ብሏል? (1 ነገሥት 2:2, 3ን አንብብ።) ይሖዋን ከታዘዘ በሕይወቱ ስኬታማ እንደሚሆን ለልጁ ነግሮታል። ደግሞም ሰለሞን ለበርካታ ዓመታት ስኬታማ ሕይወት መርቷል። (1 ዜና 29:23-25) ዕጹብ ድንቅ የሆነውን ቤተ መቅደስ ገንብቷል፤ እንዲሁም የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ጽፏል። በጥበቡና በብልጽግናው ዝና አትርፏል። (1 ነገ. 4:34) ሆኖም ዳዊት እንደተናገረው ሰለሞን ስኬታማ የሚሆነው ይሖዋ አምላክን እስከታዘዘ ድረስ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው፣ ሰለሞን በሸመገለ ጊዜ ሌሎች አማልክትን ማምለክ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሞገሱን ወሰደበት፤ ሰለሞንም ሕዝቡን በጽድቅና በፍትሕ ለማስተዳደር የሚያስችለውን ጥበብ አጣ።—1 ነገ. 11:9, 10፤ 12:4
12. ዳዊት ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን?
12 ምን ትምህርት እናገኛለን? ታዛዥነት ስኬት ያስገኛል። (መዝ. 1:1-3) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እንደ ሰለሞን ሀብትና ክብር እንደሚሰጠን ቃል አልገባልንም። ሆኖም አምላክን ከታዘዝን ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። (ምሳሌ 2:6, 7፤ ያዕ. 1:5) እሱ የሰጠን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ ሥራ፣ ትምህርት፣ መዝናኛና ገንዘብ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ይረዱናል። አምላካዊ ጥበብን በሥራ ላይ ማዋላችን ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብን ይጠብቀናል። (ምሳሌ 2:10, 11) ጥሩ ወዳጆች እናገኛለን። አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት መመሥረትም እንችላለን።
13. ካርመን ስኬታማ ሕይወት መምራት የቻለችው እንዴት ነው?
13 በሞዛምቢክ የምትኖረው ካርመን ለስኬት ቁልፉ ከፍተኛ ትምህርት እንደሆነ ታስብ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ገብታ የሥነ ሕንፃ ትምህርት መከታተል ጀመረች። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ትምህርቱን በጣም እወደው ነበር። ሆኖም ጊዜዬንና ጉልበቴን በሙሉ ወሰደብኝ። ከጠዋቱ 1:30 አንስቶ እስከ ምሽቱ 12:00 ድረስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበርኩ። ስብሰባ መገኘት ከባድ ሆነብኝ፤ መንፈሳዊነቴም መጎዳት ጀመረ። ሁለት ጌቶችን ለማገልገል እየሞከርኩ እንዳለሁ ተገነዘብኩ።” (ማቴ. 6:24) ካርመን ያለችበትን ሁኔታ በተመለከተ ጸለየች፤ እንዲሁም በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አደረገች። እንዲህ ብላለች፦ “ከጎለመሱ ወንድሞችና ከእናቴ ጥሩ ምክር ካገኘሁ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቁሜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ። እንዲህ ማድረጌ በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዳደርግ ረድቶኛል። ደግሞም በውሳኔዬ አልቆጭም።”
14. ሙሴም ሆነ ዳዊት የሰጡት ምክር መሠረታዊ ሐሳቡ ምንድን ነው?
14 ሙሴና ዳዊት ይሖዋን ይወዱት ነበር። እሱን መታዘዝ ያለውን ጥቅምም በደንብ ተገንዝበዋል። በመሆኑም ሌሎች የእነሱን ምሳሌ በመከተል ከአምላካቸው ከይሖዋ ጋር እንዲጣበቁ ምክር ሰጥተዋል። በተጨማሪም ሁለቱም ይሖዋን የሚተዉ ሰዎች የእሱን ሞገስም ሆነ ቃል የገባላቸውን በረከት እንደሚያጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። እነሱ የሰጡት ምክር ለእኛም ይጠቅመናል። ከእነሱ ዘመን በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የኖረ ሌላ የይሖዋ አገልጋይም ለአምላክ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።
“የበለጠ ደስታ የለኝም”
15. ሐዋርያው ዮሐንስ በሕይወት ዘመኑ ምን ተመልክቷል?
15 ዮሐንስ ኢየሱስ የሚወደው ሐዋርያ ነበር። (ማቴ. 10:2፤ ዮሐ. 19:26) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አብሮት ተጉዟል፤ የፈጸማቸውን ተአምራት ተመልክቷል፤ እንዲሁም በአስቸጋሪ ወቅት ለእሱ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ኢየሱስ ሲሰቀል ተመልክቷል፤ ከሞት ከተነሳ በኋላም አግኝቶታል። በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና ሲስፋፋ አይቷል፤ ጥቂት ታማኝ ሰዎችን ያቀፈ ቡድን ከመሆን ተነስቶ “[ምሥራቹ] ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል” የሚባልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ለማየት በቅቷል።—ቆላ. 1:23
16. ዮሐንስ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች እነማን ተጠቅመዋል?
16 ዮሐንስ በረጅም የሕይወት ዘመኑ ማብቂያ አካባቢ በመንፈስ መሪነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የመጻፍ መብት አግኝቷል። ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለትን’ አስደናቂ ራእይ ዘግቧል። (ራእይ 1:1) ዮሐንስ በስሙ የተጠራውን ወንጌል ጽፏል። በተጨማሪም በመንፈስ መሪነት ሦስት ደብዳቤዎችን ጽፏል። ዮሐንስ ሦስተኛውን ደብዳቤ የጻፈው ጋይዮስ ለተባለ ታማኝ ክርስቲያን ነው፤ ዮሐንስ ጋይዮስን እንደ መንፈሳዊ ልጁ አድርጎ ይመለከተው ነበር። (3 ዮሐ. 1) በወቅቱ ዮሐንስ እንደ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ የሚመለከታቸው በርካታ ክርስቲያኖች እንደሚኖሩ ምንም ጥያቄ የለውም። ይህ ታማኝ አረጋዊ የጻፈው ደብዳቤ እስከ ዘመናችን ድረስ ሁሉንም የኢየሱስ ተከታዮች እያበረታታ ነው።
17. በ3 ዮሐንስ 4 መሠረት ዮሐንስን በጣም ያስደሰተው ምንድን ነው?
17 ዮሐንስ ምን ብሎ ጽፏል? (3 ዮሐንስ 4ን አንብብ።) ዮሐንስ በደብዳቤው ላይ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ አምላክን መታዘዛቸው ምን ያህል እንዳስደሰተው ጽፏል። ዮሐንስ ሦስተኛውን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስፋፉና ክፍፍል የሚፈጥሩ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ‘በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን’ ቀጥለዋል። ይሖዋን ይታዘዙ እንዲሁም ‘በትእዛዛቱ መሠረት ይመላለሱ’ ነበር። (2 ዮሐ. 4, 6) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ዮሐንስን ብቻ ሳይሆን ይሖዋንም አስደስተውታል።—ምሳሌ 27:11
18. ዮሐንስ ከጻፋቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 ምን ትምህርት እናገኛለን? ታማኝነት ደስታ ያስገኛል። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋን እያስደሰትን እንዳለ ማወቃችን ያስደስተናል። ይሖዋ የዓለምን ፈተናዎች አሸንፈን ቃሉን ስንታዘዝ ይደሰታል። (ምሳሌ 23:15) መላእክትም ይህን ሲያዩ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:10) በተጨማሪም ሌሎች የተለያዩ ፈተናዎችንና መከራዎችን አሸንፈው ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ ስንመለከት እኛም እንደሰታለን። (2 ተሰ. 1:4) ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ደግሞ፣ ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥም እንኳ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንዳስመሠከርን ማወቃችን ጥልቅ እርካታ ያስገኝልናል።
19. ሬቸል የተባለች እህት ለሌሎች እውነትን ማስተማርን በተመለከተ ምን ብላለች? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
19 በተለይ ለሌሎች እውነትን ስናስተምር በጣም እንደሰታለን። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የምትኖረው ሬቸል ስለምናገለግለው አስደናቂ አምላክ ሌሎችን ማስተማር በቃላት ሊገለጽ የማይችል መብት እንደሆነ ይሰማታል። ስለ መንፈሳዊ ልጆቿ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የማስተምራቸው ሰዎች ለይሖዋ ፍቅር ሲያዳብሩ፣ በእሱ ሙሉ በሙሉ ሲታመኑ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያዎችን ሲያደርጉ ስመለከት የሚሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ይህን ስመለከት እነሱን ለማስተማር ያደረግኩት ጥረትም ሆነ የከፈልኩት ማንኛውም መሥዋዕት አይቆጨኝም።”
ታማኝ ሰዎች ከተናገሯቸው የስንብት ቃላት ተማሩ
20. ከሙሴ፣ ከዳዊትና ከዮሐንስ ጋር የምንመሳሰለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
20 ሙሴ፣ ዳዊትና ዮሐንስ የኖሩበት ዘመንም ሆነ የነበሩበት ሁኔታ ከእኛ በእጅጉ የተለየ ነው። ይሁንና ከእነሱ ጋር የሚያመሳስለን ብዙ ነገር አለ። እኛም እንደ እነሱ እውነተኛውን አምላክ እናገለግላለን። እንደ እነሱ ሁሉ እኛም ወደ ይሖዋ እንጸልያለን፤ በእሱ እንታመናለን፤ እንዲሁም ከእሱ መመሪያ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። በተጨማሪም በጥንት ዘመን እንደኖሩት እንደ እነዚህ ሰዎች ሁሉ እኛም፣ ይሖዋ የሚታዘዙትን ሰዎች አትረፍርፎ እንደሚባርክ እርግጠኞች ነን።
21. ሙሴ፣ ዳዊትና ዮሐንስ የሰጡትን ምክር ከተከተልን ምን በረከት እናገኛለን?
21 እንግዲያው ይሖዋን በመታዘዝ እነዚህ ታማኝ አረጋውያን የሰጡትን ምክር እንከተል። እንዲህ ካደረግን፣ በምናደርገው ነገር ሁሉ እውነተኛ ስኬት እናገኛለን። ‘ረጅም ዕድሜ እንኖራለን’፤ እንዲያውም የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (ዘዳ. 30:20) በተጨማሪም ከምንጠብቀውም ሆነ ከምናስበው እጅግ አብልጦ ቃሉን የሚፈጽመውን አፍቃሪውን አባታችንን ማስደሰት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን።—ኤፌ. 3:20
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
a ይሖዋ በቀይ ባሕር የፈጸመውን ተአምር ያዩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር አልገቡም። (ዘኁ. 14:22, 23) ይሖዋ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት እስራኤላውያን በምድረ በዳ እንደሚሞቱ ተናግሮ ነበር። (ዘኁ. 14:29) ሆኖም ኢያሱ፣ ካሌብ፣ ከወጣቱ ትውልድ መካከል ብዙዎቹ እንዲሁም አብዛኞቹ ሌዋውያን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ዮርዳኖስ ወንዝን ተሻግረው ወደ ከነአን ምድር ገብተዋል።—ዘዳ. 1:24-40
b የሥዕሉ መግለጫ፦ በስተ ግራ፦ ዳዊት በሕይወቱ ማብቂያ ላይ ለልጁ ለሰለሞን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ሲሰጠው። በስተ ቀኝ፦ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎች ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ሲቀስሙ