ሁለተኛ ሳሙኤል
2 ከዚህ በኋላ ዳዊት “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዱ ልውጣ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም “ውጣ” አለው። ዳዊትም “ወዴት ብሄድ ይሻላል?” አለ። እሱም “ወደ ኬብሮን”+ አለው። 2 በመሆኑም ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ማለትም ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል+ ጋር ወደዚያ ወጣ። 3 በተጨማሪም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች+ እያንዳንዳቸውን ከነቤተሰባቸው ይዞ ወጣ፤ እነሱም በኬብሮን ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ መኖር ጀመሩ። 4 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች መጥተው በዚያ ዳዊትን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።+
ለዳዊትም “ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስጊልያድ ሰዎች ናቸው” ብለው ነገሩት። 5 በመሆኑም ዳዊት ወደ ኢያቢስጊልያድ ሰዎች መልእክተኞችን በመላክ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር ለእሱ ታማኝ ፍቅር ስላሳያችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ።+ 6 ይሖዋ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ያሳያችሁ። እኔም ይህን ስላደረጋችሁ ደግነት አደርግላችኋለሁ።+ 7 እንግዲህ አሁን ጌታችሁ ሳኦል ስለሞተና የይሁዳም ቤት እኔን በላያቸው ንጉሥ አድርገው ስለቀቡኝ እጆቻችሁን አበርቱ፤ ደፋሮችም ሁኑ።”
8 የሳኦል ሠራዊት አለቃ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር+ ግን የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን+ ወስዶ ወደ ማሃናይም+ አሻገረው፤ 9 እሱንም በጊልያድ፣+ በአሱራውያን፣ በኢይዝራኤል፣+ በኤፍሬምና+ በቢንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው። 10 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር፤ እሱም ለሁለት ዓመት ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ደገፈ።+ 11 ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ በይሁዳ ቤት ላይ የገዛበት ጊዜ* ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበር።+
12 ከጊዜ በኋላ የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ አገልጋዮች ከማሃናይም+ ወደ ገባኦን+ ወጡ። 13 የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብና+ የዳዊት አገልጋዮችም ወጥተው በገባኦን ኩሬ አጠገብ አገኟቸው፤ አንደኛው ቡድን ከኩሬው በዚህኛው በኩል ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከኩሬው በዚያኛው በኩል ተቀመጠ። 14 በመጨረሻም አበኔር ኢዮዓብን “እስቲ ወጣቶቹ ይነሱና በፊታችን ይፋለሙ”* አለው። ኢዮዓብም “እሺ ይነሱ” አለ። 15 በመሆኑም ተነሱ፤ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ 12 ቢንያማውያን፣ ከዳዊት አገልጋዮችም 12 ሰዎች ተቆጥረው ተሻገሩ። 16 ከዚያም አንዱ የሌላውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በባላጋራው ጎን እየሻጠ ሁሉም ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህ በገባኦን የሚገኘው ያ ቦታ ሄልቃትሃጽጹሪም ተባለ።
17 በዚያን ዕለት የተነሳው ውጊያ እጅግ ከባድ ነበር፤ በመጨረሻም አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት አገልጋዮች ፊት ተሸነፉ። 18 ሦስቱ የጽሩያ+ ልጆች ኢዮዓብ፣+ አቢሳ+ እና አሳሄል+ እዚያ ነበሩ፤ አሳሄል በመስክ ላይ እንዳለች የሜዳ ፍየል ፈጣን ሯጭ ነበር። 19 አሳሄልም አበኔርን ማሳደዱን ተያያዘው፤ እሱን ከማሳደድ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አላለም። 20 አበኔርም ወደ ኋላ ዞር ብሎ ተመለከተና “አሳሄል፣ አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለው። 21 ከዚያም አበኔር “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ብለህ ከወጣቶቹ መካከል አንዱን ያዝና ያለውን ነጥቀህ ለራስህ ውሰድ” አለው። አሳሄል ግን እሱን ማሳደዱን መተው አልፈለገም። 22 በመሆኑም አበኔር አሳሄልን እንደገና “እኔን ማሳደድህን ተው። እኔስ ለምን ልግደልህ? የወንድምህን የኢዮዓብንስ ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። 23 እሱ ግን ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም፤ በመሆኑም አበኔር በጦሩ የኋላ ጫፍ ሆዱን ወጋው፤+ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ እሱም እዚያው ወድቆ ወዲያውኑ ሞተ። በዚያ የሚያልፍ ሰው ሁሉ አሳሄል ወድቆ የሞተበት ስፍራ ሲደርስ ቆም ይል ነበር።
24 ከዚያም ኢዮዓብና አቢሳ አበኔርን ማሳደድ ጀመሩ። ወደ ገባኦን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ላይ ከጊያህ ፊት ለፊት ያለው የአማ ኮረብታ ጋ ሲደርሱ ፀሐይ ጠለቀች። 25 ቢንያማውያንም በአበኔር ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እነሱም ግንባር በመፍጠር በአንድ ኮረብታ አናት ላይ ቆሙ። 26 ከዚያም አበኔር ኢዮዓብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰይፍ ያለገደብ ሰው መብላት አለበት? ውጤቱስ መራራ እንደሚሆን አንተ ራስህ ሳታውቀው ቀርተህ ነው? ሰዎቹ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲመለሱ የማትነግራቸው እስከ መቼ ነው?” 27 በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ “ሕያው በሆነው በእውነተኛው አምላክ እምላለሁ፣ አንተ ይህን ባትናገር ኖሮ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዳቸውን አያቆሙም ነበር” አለ። 28 ኢዮዓብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእሱ ሰዎችም እስራኤልን ማሳደዳቸውን ተዉ፤ ውጊያውም አቆመ።
29 ከዚያም አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ በአረባ+ ሲጓዙ አደሩ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ሸለቆውን* ሁሉ አቋርጠው በመጨረሻ ማሃናይም+ደረሱ። 30 ኢዮዓብም አበኔርን ከማሳደድ ተመልሶ ሕዝቡን በሙሉ አንድ ላይ ሰበሰበ። ከዳዊትም አገልጋዮች መካከል ከአሳሄል በተጨማሪ 19 ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። 31 የዳዊት አገልጋዮች ግን ቢንያማውያንንና የአበኔርን ሰዎች ድል ያደረጓቸው ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ መካከል 360 ሰዎችን ገድለው ነበር። 32 እነሱም አሳሄልን+ ወስደው በቤተልሔም+ በሚገኘው በአባቱ የመቃብር ቦታ ቀበሩት። ከዚያም ኢዮዓብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግሱ አድረው ንጋት ላይ ኬብሮን+ ደረሱ።