የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የምትመርጠው የሕክምና ዓይነት ለውጥ ያመጣልን?
ሕመም፣ በሽታና የመቁሰል አደጋ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሱ የተለመዱ ችግሮች ናቸው። ብዙ ሰዎች እነዚህ የጤና እክሎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ በሕክምና እፎይታ ለማግኘት ይጥራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ያለው ጥረት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመገንዘብ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም” ሲል ተናግሯል።—ሉቃስ 5:31
እነዚህን ቃላት የመዘገበው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ሉቃስ ራሱ ሐኪም ነበር። (ቆላስይስ 4:14) ሉቃስ ከጳውሎስ ጋር በተጓዘባቸው ጊዜያት በሕክምና ሙያው ሐዋርያው ጳውሎስን ሳይረዳው አልቀረም። ይሁንና በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረውን ሕክምና አስመልክቶ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡት መመሪያ ይኖራልን? የምትመርጠው የሕክምና ዓይነትስ ለውጥ ያመጣልን?
ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የሚወስደውን የሕክምና ዓይነት በተመለከተ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ዘዳግም 18:10-12 እንደ ምዋርትና ጥንቆላ ያሉት ነገሮች በይሖዋ ዘንድ ‘የተጠሉ’ መሆናቸውን ይገልጻል። ጳውሎስ እንድንርቀው ያስጠነቀቀን “መናፍስታዊ ተግባር” እነዚህን የተከለከሉ ድርጊቶች አጠቃልሎ የሚይዝ ነው። (ገላትያ 5:19-21 NW ) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር ግንኙነት ካላቸው የምርመራ ወይም የሕክምና ዓይነቶች ይርቃሉ።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ለሕይወትና ለደም ቅድስና ምን ያህል የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 9:3, 4) የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን ትእዛዝ ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ ያደረጉ በመሆናቸው ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ከሚያስጥስ የሕክምና ዓይነት ይርቃሉ። (ሥራ 15:28, 29) ይህ ማለት ግን ሁሉንም ዓይነት ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆኑም ማለት አይደለም። ይልቁንም ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን ዓይነት ሕክምና ለማግኘት ይጥራሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ ከሆነው ሃይማኖታዊ አቋማቸው ጋር የሚጣጣም ሕክምና ያደርጉላቸው ዘንድ የጤና ባለሙያዎችን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አይሉም።
አካሄድህን ተመልከት
ንጉሥ ሰሎሞን “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ሲል አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 14:15) አንድ ሰው አንድን ሕክምና በተመለከተ የሚያደርገው ውሳኔ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በቀጥታ በማይጋጭበትም ጊዜ እንኳ ‘አካሄዱን መመልከት’ ይኖርበታል። ሁሉም ዓይነት ሕክምና ጠቃሚ ነው ማለት አይቻልም። ኢየሱስ ‘ሕመምተኞች ባለ መድኃኒት ያስፈልጋቸዋል’ ብሎ ሲናገር በዘመኑ የነበሩት ሁሉም የሕክምና ዓይነቶች ተቀባይነት አላቸው ማለቱ አልነበረም። አንዳንዶቹ የሕክምና ልማዶች ምንም ጉዳት የሌላቸው ሌሎቹ ደግሞ ጭራሽ የተሳሳቱ እንደሆኑ ያውቅ ነበር።a
ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንዶቹ ሕክምናዎች ምንም ፋይዳ የሌላቸው ምናልባትም ማታለያ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። በጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ውሳኔ ማድረግ አለመቻል አንድን ግለሰብ አላስፈላጊ ለሆኑ አደጋዎች ሊያጋልጠው ይችላል። ለአንድ ሰው ጥሩ ሆኖ የተገኘው ሕክምና ለሌላው ሰው ምንም ላይፈይድ አልፎ ተርፎም ጎጂ ሊሆን እንደሚችል መታወቅ አለበት። ብልህ የሆነ ሰው የሚወስደውን የሕክምና ዓይነት በተመለከተ ምርጫ ማድረግ ሲያስፈልገው ‘የተነገረውን ሁሉ ከማመን ይልቅ’ በቅን ልቦና የሚመክሩትን ወዳጆቹን ቃል ጨምሮ አማራጮቹን ሁሉ በጥንቃቄ ያመዛዝናል። በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማድረግ ይችል ዘንድ አስተማማኝ መረጃ በማፈላለግ “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዳለው ያሳያል።—ቲቶ 2:12 NW
ከእውነታው አትራቅ፤ ምክንያታዊ ሁን
አንድ ሰው ስለ ጤናው ማሰቡ ተገቢ ነው። ለአካላዊ ደህንነታችን ሚዛናዊ የሆነ ትኩረት መስጠቱ ለሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለንና መለኮታዊ ምንጭ ያለው መሆኑንም እንደምንገነዘብ ያሳያል። (መዝሙር 36:9) ክርስቲያኖች ተገቢ የሆነ ሕክምና ለማግኘት የሚጥሩ ቢሆንም ጤንነትን አስመልክቶ ሚዛናቸውን ጠብቀው መገኘት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል መጠነኛ ጤንነት ያለው ሰው ከልክ በላይ ስለ ጤናውና ስለ አካል ብቃቱ የሚጨነቅ ከሆነ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች’ ሳያስተውል ሊቀር ይችላል።—ፊልጵስዩስ 1:9-11፤ 2:3, 4
በኢየሱስ ዘመን በሕመም ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት ያደረባትን ሥር የሰደደ በሽታ ለመታከም ባለ መድኃኒቶች ዘንድ እየተመላለሰች ‘ገንዘብዋን ሁሉ ከስራ’ ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ጤንነቷ እየከፋ ሄደ እንጂ አልተሻላትም። ይህ ራሱ ተስፋ አስቆርጧት መሆን አለበት። (ማቴዎስ 5:25, 26) እፎይታ ለማግኘት የምትችለውን ሁሉ ብታደርግም ያገኘችው መፍትሄ አልነበረም። ከዚህች ሴት ተሞክሮ መረዳት እንደምንችለው በዘመኑ የነበረው የሕክምና ሳይንስ አቅም ውስን ነበር። ዛሬም ቢሆን የሕክምናው ምርምርና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ መሻሻል ቢያሳይም የብዙ ሰዎች ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። በመሆኑም የሕክምናው ሳይንስ ሊያደርግ ይችላል ብለን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት መያዙ አስፈላጊ ነው። በዚህ ሥርዓት ፍጹም ጤና ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። አምላክ ‘አሕዛብን የሚፈውስበት’ ጊዜ ገና ወደፊት የሚመጣ መሆኑን ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። (ራእይ 22:1, 2) በመሆኑም ሕክምናን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 4:5 NW
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የምናደርገው ምርጫ ለውጥ ያመጣል። ከዚህ የተነሣ የምንወስደውን የሕክምና ዓይነት በተመለከተ ምርጫ ለማድረግ ስንገደድ ምርጫችን ጥሩ ጤንነት ለማግኘት እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለንን ጤናማ ዝምድና ጠብቀን ለመቆየት የምንፈልግ መሆናችንን የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባል። እንደዚያ ስናደርግ በመጪው ክብራማ አዲስ ዓለም ውስጥ “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” የሚለው ይሖዋ የሰጠው ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ ለማየት በትምክህት ልንጠባበቅ እንችላለን።—ኢሳይያስ 33:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የዳየስኮረዲዝ የሕክምና ኢንሳይክለፒዲያ ውስጥ ለወይቦ (jaundice) ፍቱን መድኃኒት ሆኖ የቀረበው ከፍየል በጠጥ ጋር የተበጠበጠ ወይን መጠጣት ነው። እርግጥ ዛሬ እንዲህ ያለው መድኃኒት የበሽተኛውን ጣር ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ተገንዝበናል።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰር ሉክ ፋይልድስ በ1981 የተዘጋጀው “ዘ ዶክተር”
[ምንጭ]
Tate Gallery, London/Art Resource, NY