ምዕራፍ 40
ይቅርታ ስለ ማግኘት የተሰጠ ትምህርት
ኃጢአተኛ የሆነች አንዲት ሴት የኢየሱስን እግር ዘይት ቀባች
ባለዕዳ መሆንን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ይቅርታ ስለ ማግኘት አስተማረ
ሰዎች ለኢየሱስ ትምህርትና ለድርጊቶቹ የሚሰጡት ምላሽ በልባቸው ሁኔታ ላይ የተመካ ነው። ኢየሱስ በገሊላ በአንድ ቤት እያለ የተከናወነው ነገር ይህን በግልጽ አሳይቷል። ስምዖን የተባለ አንድ ፈሪሳዊ፣ እነዚህን አስደናቂ ሥራዎች እያከናወነ ያለውን ሰው ይበልጥ ቀረብ ብሎ ለማወቅ ፈልጎ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስን ቤቱ ጋበዘው። ኢየሱስ በሌሎች አጋጣሚዎች ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች ከእነሱ ጋር እንዲበላ ያቀረቡለትን ግብዣ እንደተቀበለ ሁሉ ይህንንም ግብዣ የተቀበለው በዚያ የሚገኙትን ሰዎች ለማስተማር የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርጎ ስለተመለከተው ሳይሆን አይቀርም።
ሆኖም ኢየሱስ ወደ ስምዖን ቤት ሲገባ፣ ብዙውን ጊዜ ለእንግዶች የሚደረገው ወዳጃዊ አቀባበል አልተደረገለትም። አቧራማ በሆኑት የፓለስቲና መንገዶች ላይ ክፍት ጫማ አድርገው የሚጓዙ ሰዎች የሚሞቃቸው ከመሆኑም ሌላ እግራቸው ይቆሽሻል፤ በመሆኑም እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሰው የእንግዶቹን እግር በቀዝቃዛ ውኃ ማጠቡ የተለመደ ነው። ለኢየሱስ ግን እንዲህ አልተደረገለትም። በተጨማሪም እንደ ባሕሉ፣ እንኳን ደህና መጣህ ብሎ የሳመው አልነበረም። የእንግዳን ፀጉር ዘይት መቀባት ሌላው የእንግዳ ተቀባይነትና የደግነት መገለጫ ነው። ለኢየሱስ ይህም አልተደረገለትም። ታዲያ ስምዖን፣ ኢየሱስን ጥሩ አድርጎ ተቀብሎታል ሊባል ይችላል?
እንግዶቹ በማዕድ ዙሪያ ቀርበው መመገብ ጀመሩ። እየተመገቡ ሳለ አንዲት ያልተጋበዘች ሴት ቀስ ብላ ወደ ክፍሉ ገባች። ሴትየዋ “በከተማው ውስጥ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ” ናት። (ሉቃስ 7:37) ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሙሉ ኃጢአተኞች እንደሆኑ የታወቀ ነው፤ ይህች ሴት ግን ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት የምትመራ ምናልባትም ዝሙት አዳሪ ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ “ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” ሲል ያቀረበውን ጥሪ ጨምሮ ያስተማረውን ትምህርት ሳትሰማ አልቀረችም። (ማቴዎስ 11:28, 29) ባየችውና በሰማችው ነገር ልቧ በመነካቱ ኢየሱስን ፈልጋ አገኘችው።
ሴትየዋ ከበስተ ኋላ ወደ ማዕዱ መጣችና ከኢየሱስ እግር አጠገብ ተንበረከከች። ከዚያም እንባዋን እግሩ ላይ እያፈሰሰች በፀጉሯ ታብሰው ጀመር። በተጨማሪም እግሩን እየሳመች ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት አውጥታ ቀባችው። ስምዖን ያየው ነገር ደስ ስላላለው “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ ቢሆን ኖሮ የምትነካው ማን መሆኗንና ምን ዓይነት ሴት እንደሆነች ይኸውም ኃጢአተኛ መሆኗን ባወቀ ነበር” ብሎ በልቡ አሰበ።—ሉቃስ 7:39
ኢየሱስ፣ ስምዖን ምን እያሰበ እንዳለ ስለገባው “ስምዖን፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እሱም “መምህር፣ እሺ ንገረኝ” አለ። ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ 500 ሌላው ደግሞ 50 ዲናር ተበድረው ነበር። ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው ዕዳቸውን ሙሉ በሙሉ ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ ሰዎች አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?” ስምዖንም መልሶ “ብዙ ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” አለው፤ ምናልባትም ይህን የተናገረው፣ ምሳሌው ትኩረቱን እንዳልሳበው በሚያሳይ መንገድ ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 7:40-43
ኢየሱስ በስምዖን ሐሳብ ተስማማ። ከዚያም ወደ ሴቲቱ እየተመለከተ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያታለህ? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ይሁንና አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም። ይህች ሴት ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ አበሰች። አንተ አልሳምከኝም፤ ይህች ሴት ግን ከገባሁበት ሰዓት አንስቶ እግሬን መሳሟን አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ ይህች ሴት ግን እግሬን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ቀባች።” ኢየሱስ፣ ሴትየዋ ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗሯ ከልቧ መጸጸቷን እያሳየች መሆኑን ማስተዋል ችሏል። በመሆኑም እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “እልሃለሁ፣ ኃጢአቷ ብዙ ቢሆንም ይቅር ተብሎላታል፤ ምክንያቱም ታላቅ ፍቅር አሳይታለች። በትንሹ ይቅር የተባለ ግን የሚያሳየውም ፍቅር አነስተኛ ነው።”—ሉቃስ 7:44-47
ኢየሱስ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራት ተቀባይነት እንዳለው እየገለጸ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽሙም በድርጊታቸው እንዳዘኑ የሚያሳዩና እረፍት ለማግኘት ወደ ክርስቶስ ዞር የሚሉ ሰዎችን በርኅራኄ በመቀበል ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው መጠቆሙ ነው። ኢየሱስ “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል። . . . እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” ሲላት ሴትየዋ ምን ያህል እፎይታ ተሰምቷት ይሆን!—ሉቃስ 7:48, 50