መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
በ60ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዲት ሴት ጣዖት ማምለካቸውን የተዉት ለምን ነበር? የሺንቶ ካህን የሆነ አንድ ሰው በሺንቶ ቤተ መቅደስ የነበረውን ሥራ ትቶ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆን የገፋፋው ምንድን ነው? ገና እንደተወለደች በጉዲፈቻ የተሰጠች አንዲት ሴት እንደተጣለች ሆኖ የሚሰማትን ስሜት መቋቋም የቻለችው እንዴት ነበር? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።
‘የጣዖታት ባሪያ ከመሆን ተገላግያለሁ።’—አባ ዳንሶ
የትውልድ ዘመን፦ 1938
የትውልድ አገር፦ ቤኒን
የኋላ ታሪክ፦ ጣዖት አምላኪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በአንድ ሐይቅ አጠገብ፣ ረግረጋማ በሆነ አካባቢ በምትገኘው ሶቻሁዊ የምትባል መንደር ነው። የመንደሯ ነዋሪዎች ዓሣ በማጥመድ እንዲሁም የቀንድ ከብቶች፣ ፍየሎች፣ በጎች፣ አሳማዎችና ወፎች በማርባት ይተዳደራሉ። በአካባቢው መንገድ ስለሌለ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር የሚጠቀሙት በጀልባዎችና በታንኳዎች ነው። ብዙ ሰው ቤቱን የሚሠራው በእንጨትና በሣር ሲሆን አንዳንዶች ግን በጡብ ይሠራሉ። አብዛኛው ሰው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ይመራል። እንደዚያም ሆኖ ወንጀል በከተሞች ውስጥ የሚታየውን ያህል አልተስፋፋም።
ልጅ ሳለሁ አባቴ እኔንና ታላቅ እህቴን በባሕላዊ እምነት ኮትኩቶ ለማሳደግ ሲል አስማታዊ ኃይል አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ቅርጻ ቅርጾች ወደሚገኙበት ገዳም ላከን። ሳድግ በሩባ ባሕል እንደ አምላክ ተደርጎ የሚታሰበውን ዱዱዋን (ኦዱዱዋን) የራሴ አምላክ አድርጌ ተቀበልኩ። ለዚህ አምላክ ቤት ከሠራሁለት በኋላ ስኳር ድንች፣ የዘንባባ ዘይት፣ ቀንድ አውጣ፣ ዶሮ፣ ርግብና ሌሎች የተለያዩ እንስሳትን ዘወትር መሥዋዕት አድርጌ አቀርብለት ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ስለነበሩ ገንዘቤ በሙሉ የሚያልቀው በዚህ ነበር ማለት ይቻላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ተማርኩ። በተጨማሪም እሱን ለማምለክ በጣዖት መጠቀማችን እንደማያስደስተው አወቅሁ። (ዘፀአት 20:4, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ገባኝ። ስለዚህ የነበሩኝን ምስሎች በሙሉ በመጣል ቤቴን ከጣዖት አምልኮ ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር አጸዳሁ። ጠንቋይ ጋር መሄድ አቆምኩ፤ እንዲሁም በአካባቢው በሚደረጉ ሃይማኖታዊ ልማዶችና ከባዕድ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ መካፈል ተውኩ።
በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኝ ለእንደ እኔ ዓይነት ሴት እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ጓደኞቼ፣ ዘመዶቼና ጎረቤቶቼ ይቃወሙኝ እንዲሁም ያሾፉብኝ ነበር። ይሁን እንጂ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። በምሳሌ 18:10 ላይ የሚገኘው “[የይሖዋ] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” የሚለው ሐሳብ በእጅጉ አጽናንቶኛል።
ሌላው የረዳኝ ነገር የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ ነው። በስብሰባዎቹ ላይ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማየት የቻልኩ ከመሆኑም በላይ እነዚህ ሰዎች ላቅ ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚጥሩ መሆናቸው አስደነቀኝ። በዚያ ያየሁት ነገር እውነተኛውን ሃይማኖት እየተከተሉ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ እንዳምን አደረገኝ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ከልጆቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንዳሻሽል ረድቶኛል። በተጨማሪም ከባድ ሸክም ከጫንቃዬ ላይ የወረደልኝ ያህል ሆኖ ይሰማኛል። ገንዘቤን በሙሉ ምንም ለማይጠቅሙኝ በድን ጣዖታት ሳፈስ ኖሬያለሁ። አሁን ግን ለችግሮቻችን በሙሉ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣውን ይሖዋን እያመለክሁ ነው። (ራእይ 21:3, 4) የጣዖታት ባሪያ ከመሆን ተገላግዬ የይሖዋ ባሪያ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ! ወደ ይሖዋ መቅረቤ እውነተኛ የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገ ከመሆኑም በላይ አስተማማኝ ተገን አግኝቻለሁ።
“ከልጅነቴ ጀምሮ አምላክን ስፈልግ ኖሬያለሁ።”—ሺንጂ ሳቶ
የትውልድ ዘመን፦ 1951
የትውልድ አገር፦ ጃፓን
የኋላ ታሪክ፦ የሺንቶ ካህን
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት ፉኩኦካ በሚባለው የጃፓን ክፍለ ግዛት ውስጥ በምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ወላጆቼ በጣም ሃይማኖተኛ ሰዎች ነበሩ፤ እኔንም ከልጅነቴ ጀምሮ ለሺንቶ አማልክት አምልኮታዊ ፍርሃት እንዲኖረኝ አድርገው አሳድገውኛል። ከፍ እያልኩ ስሄድ መዳን የማግኘት ጉዳይ ብዙ ጊዜ ያሳስበኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን የመርዳት ከፍተኛ ምኞት ነበረኝ። የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ አስተማሪያችን በክፍል ውስጥ ያለነውን ልጆች ስናድግ ምን መሆን እንደምንፈልግ ጠይቆን የነበረበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። የክፍል ጓደኞቼ ሳይንቲስት መሆንን የመሳሰሉ ትልልቅ ሕልሞች ነበሯቸው። እኔ ግን ምኞቴ አምላክን ማገልገል እንደሆነ ተናገርኩ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ሳቁ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ የሃይማኖት አስተማሪዎች ወደሚሠለጥኑበት ትምህርት ቤት ገባሁ። በሥልጠናው ወቅት ትርፍ ጊዜውን ጥቁር ሽፋን ያለው መጽሐፍ በማንበብ የሚያሳልፍ አንድ የሺንቶ ካህን አግኝቼ ነበር። አንድ ቀን “ሳቶ፣ ይህ መጽሐፍ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ሽፋኑን ልብ ብዬ አይቼው ስለነበር “መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት መለስኩለት። እሱም “የሺንቶ ካህን መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ይህን መጽሐፍ ማንበብ ይኖርበታል” አለ።
እኔም ወዲያውኑ ሄጄ መጽሐፍ ቅዱስ ገዛሁ። መጽሐፍ ቅዱሱን በመጻሕፍት መደርደሪያዬ ላይ በግልጽ በሚታይ ቦታ አስቀመጥኩት፤ በጥንቃቄም ይዤው ነበር። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤት ሕይወት ጊዜዬን በጣም ስላጣበበብኝ መጽሐፉን ለማንበብ ጊዜ አላገኘሁም ነበር። ትምህርቴን ስጨርስ በአንድ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሺንቶ ካህን ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚህ መልኩ የልጅነት ሕልሜ እውን ሆነ።
ይሁን እንጂ የሺንቶ ካህን መሆን የጠበቅኩትን ያህል እንዳልሆነ ወዲያውኑ ተገነዘብኩ። አብዛኞቹ ካህናት ለሌሎች እምብዛም ፍቅር ወይም አሳቢነት አልነበራቸውም። ብዙዎቹም እምነት የላቸውም። ሌላው ቀርቶ አለቆቼ ከሆኑት ካህናት አንዱ “እዚህ ቦታ እንዲሳካልህ የምትፈልግ ከሆነ ማውራት ያለብህ ፍልስፍናን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ብቻ ነው። ስለ እምነት ማውራት ፈጽሞ የተከለከለ ነው” ብሎኝ ነበር።
እንዲህ ያሉት አስተያየቶች በሺንቶ ሃይማኖት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብኝ አድርገውኛል። ምንም እንኳ በቤተ መቅደሱ ማገልገሌን ብቀጥልም ሌሎች ሃይማኖቶችንም መመርመር ጀመርኩ። ሆኖም ከአንዳቸውም ቢሆን የተሻለ ነገር አላገኘሁም። ብዙ ሃይማኖቶችን በመረመርኩ መጠን የባሰ ተስፋ እየቆረጥኩ ሄድኩ። እውነተኛ ሃይማኖት እንደሌለ ተሰማኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1988 አንድ የቡድሃ ሃይማኖት ተከታይ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳነብ አበረታታኝ። ይህ ሁኔታ ከዓመታት በፊት እንዲህ እንዳደርግ አበረታቶኝ የነበረውን የሺንቶ ቄስ አስታወሰኝ። እኔም ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ወሰንኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከጀመርኩ በኋላ የማነበው ነገር ይመስጠኝ ጀመር። አንዳንድ ጊዜ ሌሊቱን በሙሉ ሳነብ አድሬ መንጋቱን የማውቀው በመስኮቱ በኩል የፀሐይ ብርሃን ሲገባ ነበር።
የማነበው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ወደሆነው አምላክ እንድጸልይ ገፋፋኝ። ከዚያም በማቴዎስ 6:9-13 ላይ የሠፈረውን የናሙና ጸሎት መጸለይ ጀመርኩ። ይህን ጸሎት በየሁለት ሰዓት ልዩነት እጸልይ የነበረ ሲሆን እንዲህ የማደርገው በሺንቶ ቤተ መቅደስ አገልግሎቴን በማከናውንበት ጊዜም ጭምር ነበር።
ያነበብኳቸው ነገሮች ብዙ ጥያቄዎች ፈጠሩብኝ። በወቅቱ ትዳር መሥርቼ ነበር፤ ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች ባለቤቴን አነጋግረዋት ስለነበረ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምሩ አውቄ ነበር። ከዚያም አንዲት የይሖዋ ምሥክር አግኝቼ የጥያቄ መዓት አዥጎደጎድኩባት። ለእያንዳንዱ ጥያቄዬ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ስትሰጠኝ ተደነቅሁ። እሷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ዝግጅት አደረገችልኝ።
ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ምንም እንኳ በወቅቱ ባልገነዘበውም በስብሰባው ላይ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት በጥሩ ሁኔታ ያልተቀበልኳቸው የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነሱ ግን ሞቅ ባለ መንፈስ የተቀበሉኝ ሲሆን እንግድነት እንዳይሰማኝም አድርገው ነበር።
በስብሰባ ላይ ባሎች ለቤተሰባቸው አባላት ፍቅርና አክብሮት እንዲያሳዩ አምላክ እንደሚጠብቅባቸው ተማርኩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሙሉ ትኩረቴ ያረፈው በክህነት ሥራዬ ላይ ብቻ ስለነበር ሚስቴንና ሁለቱን ልጆቻችንን ችላ ብያቸው ነበር። በሺንቶ ቤተ መቅደስ ለማምለክ የሚመጡ ሰዎች ሊነግሩኝ የፈለጉትን ነገር ሁሉ በትኩረት አዳምጥ እንደነበር፣ ባለቤቴ ልትናገር የፈለገችውን ግን አንድ ጊዜም እንኳ አዳምጫት እንደማላውቅ ተገነዘብኩ።
በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ ወደ ራሱ ስለሳበኝ ስለ ይሖዋ ብዙ ነገሮች ተማርኩ። በተለይ በሮም 10:13 ላይ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” እንደሚለው ያሉት ጥቅሶች ልቤን ነክተውት ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ አምላክን ስፈልግ ኖሬያለሁ፤ ይኸው አሁን በመጨረሻ አገኘሁት።
ውሎ አድሮ በሺንቶ ቤተ መቅደስ ማገልገል ለእኔ እንደማይሆን ይሰማኝ ጀመር። መጀመሪያ ላይ ‘የሺንቶን ሃይማኖት ብተው ሌሎች ምን ይሰማቸው ይሆን?’ የሚለው ነገር አስጨንቆኝ ነበር። ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ ያለው በሌላ እምነት ውስጥ ከሆነ የሺንቶን ሃይማኖት ትቼ እንደምሄድ ሁልጊዜ ለራሴ እነግረው ነበር። ስለዚህ በ1989 የጸደይ ወራት ሕሊናዬ የሚነግረኝን ለመከተል ወሰንኩ። ቤተ መቅደሱን ትቼ በመውጣት በይሖዋ እቅፍ ውስጥ ገባሁ።
ቤተ መቅደሱን መልቀቅ ለእኔ ቀላል አልነበረም። አለቆቼ የተቆጡ ከመሆኑም በላይ በሥራዬ እንድቀጥል ጫና ሊያደርጉብኝ ሞከሩ። ከሁሉም የሚከብደው ግን ይህን ውሳኔዬን ለወላጆቼ ማሳወቁ ነበር። ይህን ለመንገር ወደ ወላጆቼ ቤት እየሄድኩ ሳለ በከፍተኛ ጭንቀት ከመዋጤ የተነሳ ደረቴ ላይ ይወጋኝ እንዲሁም ጉልበቶቼ ይብረከረኩ ነበር! ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠኝ ለመጸለይ በተደጋጋሚ እቆም ነበር።
ወላጆቼ ቤት ስደርስ መጀመሪያ ላይ ስለ ጉዳዩ ማንሳት እንኳ በጣም አስፈርቶኝ ነበር። ስለ ጉዳዩ ምንም ሳላነሳ ሰዓታት አለፉ። በመጨረሻም ከብዙ ጸሎት በኋላ ሁሉንም ነገር ፍርጥርጥ አድርጌ ለአባቴ ነገርኩት። እውነተኛውን አምላክ እንዳገኘሁትና እሱን ለማገልገል ስል የሺንቶን ሃይማኖት እንደተውኩ ነገርኩት። አባቴ ስለ ጉዳዩ ሲሰማ ክው ብሎ ቀረ፤ እንዲሁም አዘነ። ሌሎች ዘመዶቼም ቤት መጥተው ሐሳቤን ሊያስለውጡኝ ሞከሩ። እርግጥ ቤተሰቦቼን ማስቀየም አልፈልግም፤ ይሁን እንጂ ይሖዋን ማገልገል ላደርገው የሚገባ ትክክለኛ ነገር እንደሆነ ተገንዝቤ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ቤተሰቦቼ ውሳኔዬን አክብረውልኛል።
ቤተ መቅደሱን በአካል ትቶ መሄድ አንድ ነገር ሲሆን በአእምሮ ትቶ መውጣት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። ካህን ሆኜ ያሳለፍኩት ሕይወት በውስጤ ተቀርጾ ነበር። ይህን ሕይወት ለመርሳት ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፤ ይሁን እንጂ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የቀድሞ ሕይወቴን የሚያስታውሱኝ ነገሮች አላጣም ነበር።
ሁለት ነገሮችን ማድረጌ ከእነዚህ ተጽዕኖዎች እንድላቀቅ ረድቶኛል። አንደኛ፣ በቤቴ ውስጥ ከቀድሞው ሃይማኖቴ ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር ለማግኘት በጥንቃቄ ፈለግኩ። ከዚያም ያገኘኋቸውን ነገሮች በሙሉ ማለትም መጻሕፍትን፣ ፎቶግራፎችን አልፎ ተርፎም ውድ የሆኑ ማስታወሻዎችን እንኳ ሳይቀር አቃጠልኩ። ሁለተኛ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመቀራረብ የቻልኩትን ያህል ብዙ ጥረት አደረግኩ። ከእነሱ ጋር የመሠረትኩት ወዳጅነትና ያደረጉልኝ ድጋፍ በእጅጉ ረድቶኛል። በዚህ መንገድ የቀድሞ ትዝታዎቼ ቀስ በቀስ ከአእምሮዬ እየተነኑ ወጡ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ባለቤቴንና ልጆቼን ችላ እላቸው ስለነበር ከፍተኛ በሆነ የብቸኝነት ስሜት ተውጠው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች እንዲያደርጉ በሚያስተምረው መሠረት ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ስጀምር ይበልጥ እየተቀራረብን ሄድን። ከጊዜ በኋላ ባለቤቴም የይሖዋ አገልጋይ ሆነች። በአሁኑ ጊዜ ወንድ ልጃችንን እንዲሁም ሴት ልጃችንንና ባለቤቷን ጨምሮ ሁላችንም በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነናል።
በልጅነቴ አምላክን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት የነበረኝን ምኞት መለስ ብዬ ሳስብ ስፈልገው የነበረውን ነገር ሁሉ፣ እንዲያውም ከተመኘሁት በላይ እንዳገኘሁ ይሰማኛል። ለይሖዋ ያለኝን አመስጋኝነት በቃላት ልገልጸው አልችልም።
“ሁልጊዜ አንድ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር።”—ሊኔት ሃውቲንግ
የትውልድ ዘመን፦ 1958
የትውልድ አገር፦ ደቡብ አፍሪካ
የኋላ ታሪክ፦ እንደተጣለች ሆና ይሰማት የነበረች ሴት
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩባትና እምብዛም ወንጀል በሌለባት ጀርሚስተን በምትባል የማዕድን ማውጫ ከተማ ነው። ወላጆቼ ሊንከባከቡኝ እንደማይችሉ ስለተሰማቸው በጉዲፈቻ ሊሰጡኝ ወሰኑ። ገና የ14 ቀን ጨቅላ ሳለሁ አፍቃሪ ለሆኑ ባልና ሚስት በማደጎ ልጅነት ተሰጠሁ፤ እነሱም ለእኔ እንደ እናትና አባት ሆኑልኝ። እንደዚያም ሆኖ የኋላ ታሪኬን ሳውቅ እንደተጣልኩ ሆኖ ከሚሰማኝ ስሜት ጋር መታገል ጀመርኩ። አሳዳጊ ወላጆቼም ቢሆኑ እውነተኛ ወላጆቼ እንዳልሆኑና የሚሰማኝን ስሜት በትክክል ሊረዱልኝ እንደማይችሉ ማሰብ ጀመርኩ።
አሥራ ስድስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ መጠጥ በገፍ ወደሚቀርብባቸው ቡና ቤቶች ከጓደኞቼ ጋር መሄድ ጀመርኩ፤ እዚያም እንጨፍር የነበረ ከመሆኑም በላይ ዘፋኞች ከመድረክ ሲዘፍኑ እናይ ነበር። በ17 ዓመቴ ሲጋራ ማጨስ ጀመርኩ። በሲጋራ ማስታወቂያዎች ላይ ፎቶግራፋቸው እንደሚታየው ቀጫጭን ሴቶች መሆን እፈልግ ነበር። በ19 ዓመቴ በጆሀንስበርግ ከተማ መሥራት የጀመርኩ ሲሆን በዚያም ብዙ ሳልቆይ ከአጉል ጓደኞች ጋር ገጠምኩ። ወዲያውኑም ጸያፍ ቃላት መጠቀም፣ በጣም ብዙ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ከመጠን በላይ መጠጣት ጀመርኩ።
እንደዚያም ሆኖ በአካላዊ እንቅስቃሴ ረገድ ንቁ ነበርኩ። አዘውትሬ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አደርግ፣ የሴቶች እግር ኳስ እጫወት እንዲሁም ሌሎች ስፖርቶችን እሠራ ነበር። በተጨማሪም በሥራዬ ትጉህ ስለነበርኩ በኮምፒውተር ኢንዱስትሪ ታዋቂ መሆን ችዬ ነበር። በመሆኑም በኢኮኖሚ ረገድ ጥሩ ደረጃ ላይ ደረስኩ፤ እንዲሁም ብዙ ሰዎች የተሳካልኝ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኝ ጀመር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ፍጹም ደስታ የራቀኝ ሰው ነበርኩ፤ ያጣሁት ነገር እንዳለ የሚሰማኝ ከመሆኑም ሌላ በሕይወቴ ተስፋ ቆርጬ ነበር። በውስጤ ሁልጊዜ አንድ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ይሖዋ የፍቅር አምላክ እንደሆነ ተማርኩ። በተጨማሪም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ በመስጠት ይህን ፍቅሩን እንደገለጸልን አወቅኩ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እርምጃችንን ለማቅናት ሲል ለእያንዳንዳችን የጻፈው ደብዳቤ ነው ማለት ይቻላል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ከይሖዋ ፍቅራዊ አመራር ለመጠቀም ከፈለግሁ በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ትልልቅ ለውጦችን ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።
ለውጥ ማድረግ ካስፈለጉኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ ከጓደኛ ጋር በተያያዘ የነበረኝ ሁኔታ ነው። በምሳሌ 13:20 ላይ የሚገኘውን “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” የሚለውን ሐሳብ በቁም ነገር አሰብኩበት። ይህ መመሪያ የቀድሞ ጓደኞቼን ትቼ ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አዳዲስ ጓደኞችን እንዳፈራ አነሳሳኝ።
ከምንም ነገር በላይ ተፈታታኝ የሆነብኝ ግን ሲጋራ ማጨሴን ማቆም ነበር፤ ምክንያቱም ኃይለኛ ሱስ ነበረብኝ። ይህን መሰናክል ቀስ በቀስ እያሸነፍኩ ስሄድ ደግሞ ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ ገጠመኝ። ሲጋራ ማጨሴን ሳቆም 13.6 ኪሎ ጨመርኩ! ይህ ደግሞ ለራሴ የነበረኝን ጥሩ ግምት እንዳጣ አደረገኝ፤ ይህን ክብደት ለመቀነስ ወደ አሥር ዓመት ገደማ ፈጅቶብኛል። ያም ሆኖ ሲጋራ ማጨሴን ማቆም ላደርገው የሚገባ ትክክለኛ ነገር እንደሆነ አውቅ ነበር። አዘውትሬ ወደ ይሖዋ እጸልይ የነበረ ሲሆን እሱም ይህን ሱስ ለማሸነፍ የሚያስችል ኃይል ሰጥቶኛል።
ያገኘሁት ጥቅም፦ አሁን ጥሩ ጤንነት አለኝ። በሕይወቴም እውነተኛ እርካታ አግኝቻለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዓለማዊ ሥራ፣ ዝና እና ሀብት ያስገኛሉ የሚባለውን የማይጨበጥ ደስታ አላሳድድም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማካፈል ደስታ እያገኘሁ ነው። በመሆኑም ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼ መካከል ሦስቱ በአሁኑ ጊዜ ከእኔና ከባለቤቴ ጋር ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ለአሳዳጊ ወላጆቼ መጽሐፍ ቅዱስ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚኖር የሚገልጸውን ተስፋ ከመሞታቸው በፊት ነግሬያቸው ነበር።
ወደ ይሖዋ መቅረቤ እንደተጣልኩ ሆኖ የሚሰማኝን ስሜት ለመቋቋም ረድቶኛል። ይሖዋ የእኔ የምላቸው የእምነት አጋሮች ወደተሰበሰቡበት ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ውስጥ አምጥቶኛል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ብዙ እናቶች፣ አባቶች፣ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ።—ማርቆስ 10:29, 30
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ክርስቲያናዊ ፍቅር ማየት ችያለሁ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ ወቅት አምልኮ አቀርብበት የነበረው የሺንቶ ቤተ መቅደስ