የጥናት ርዕስ 12
ፍጥረትን በማየት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ተማሩ
“የማይታዩት ባሕርያቱ . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”—ሮም 1:20
መዝሙር 6 ሰማያት የአምላክን ክብር ይናገራሉ
ማስተዋወቂያa
1. ኢዮብ ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ የቻለበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
ኢዮብ በሕይወቱ ሁሉ ካደረጋቸው ውይይቶች መካከል በተለይ አንዱን ፈጽሞ እንደማይረሳው መገመት እንችላለን፤ ይህም ከይሖዋ አምላክ ጋር ያደረገው ውይይት ነው። በዚህ ውይይት ላይ ይሖዋ ለኢዮብ አንዳንድ አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎቹን እንዲመለከት ነግሮታል፤ ይህም ኢዮብ፣ ይሖዋ ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ እንዲያይና ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማቅረብ ችሎታ እንዳለው እንዲተማመን ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለእንስሳት የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያቀርብላቸው ለኢዮብ በማስታወስ እሱንም እንደሚንከባከበው አረጋግጦለታል። (ኢዮብ 38:39-41፤ 39:1, 5, 13-16) ኢዮብ አንዳንድ የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት ስለ አምላኩ ባሕርይ ብዙ ትምህርት ማግኘት ችሏል።
2. የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በደንብ እንዳንመለከት እንቅፋት የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል?
2 እኛም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች በመመርመር ስለ አምላካችን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ሆኖም እንዲህ ማድረግ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። የምንኖረው ከተማ ውስጥ ከሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተፈጥሮን የምናይበት አጋጣሚ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ተፈጥሮን ማየት የሚቻልበት አካባቢ ብንኖርም እንኳ ቆም ብለን በደንብ ለመመልከት ጊዜ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። እንግዲያው ተፈጥሮን ለመመልከት ጊዜ መመደባችንና ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ይሖዋና ኢየሱስ የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅመው ምን እንዳስተማሩና ከተፈጥሮ ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማግኘት ምን ማድረግ እንደምንችል እንመረምራለን።
ፍጥረትን በትኩረት መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?
3. ይሖዋ አዳም ፍጥረታትን በማየት እንዲደሰት እንደፈለገ የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 ይሖዋ የመጀመሪያው ሰው ፍጥረትን በማየት እንዲደሰት ይፈልግ ነበር። አምላክ አዳምን ከፈጠረው በኋላ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ እንዲኖር ያደረገው ሲሆን ገነትን የማልማትና የማስፋፋት ሥራ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 2:8, 9, 15) አዳም ዘሮች ሲበቅሉና አበቦች ሲያብቡ ሲመለከት ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን። አዳም ኤደን ገነትን የመንከባከብ ልዩ መብት አግኝቶ ነበር! በተጨማሪም ይሖዋ ለእንስሳት ስም የማውጣቱን ኃላፊነት ለአዳም ሰጥቶታል። (ዘፍ. 2:19, 20) ይሖዋ ለእያንዳንዱ እንስሳ እሱ ራሱ ስም ማውጣት ይችል ነበር፤ እሱ ግን ይህን ኃላፊነት ለአዳም ሰጠው። አዳም ስም ከማውጣቱ በፊት እንስሳቱን በትኩረት በመመልከት ባሕርያቸውን እንዳጠና ምንም ጥርጥር የለውም። አዳም በዚህ ሥራ በጣም እንደተደሰተ መገመት እንችላለን። የአባቱን ጥበብና የፈጠራ ችሎታ ይበልጥ የሚያስተውልበት አጋጣሚ እንደሰጠው ግልጽ ነው።
4. (ሀ) ፍጥረትን ለመመርመር የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) አንተ በግልህ በጣም የምታደንቀው የፍጥረት ሥራ ምንድን ነው?
4 ፍጥረትን እንድንመረምር የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት ይሖዋ እንዲህ እንድናደርግ የሚፈልግ መሆኑ ነው። “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ” በማለት ጋብዞናል። ከዚያም “እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። መልሱ ግልጽ ነው። (ኢሳ. 40:26) ይሖዋ ሰማያትን ብቻ ሳይሆን ምድርንና ባሕርንም ጭምር አስደናቂ በሆኑ የፍጥረት ሥራዎቹ ሞልቷል፤ እኛም ከእነዚህ የፍጥረት ሥራዎቹ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (መዝ. 104:24, 25) እስቲ አምላክ እኛን የፈጠረበትን መንገድ እንኳ ለማሰብ ሞክሩ። በተፈጥሮ ላይ የምናያቸውን የሚያማምሩ ነገሮች የማድነቅ ችሎታ በውስጣችን አኑሯል። በተጨማሪም በአምስቱ የስሜት ሕዋሶቻችን ማለትም በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰስ፣ በመቅመስና በማሽተት ችሎታችን ተጠቅመን የተለያዩ ፍጥረታቱን ማድነቅ እንድንችል አድርጎ ፈጥሮናል።
5. ሮም 1:20 ላይ እንደተገለጸው የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በትኩረት መመልከታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
5 መጽሐፍ ቅዱስ ፍጥረትን ለመመርመር የሚያነሳሳንን ሌላ አስፈላጊ ምክንያት ይጠቅሳል። ፍጥረት ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያስተምረናል። (ሮም 1:20ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ በፍጥረት ሥራዎች ላይ በግልጽ የሚታየውን ንድፍ ለማሰብ ሞክሩ። የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቅ አይደለም? የምንመገባቸውን የተለያዩ ዓይነት ምግቦችም ለማሰብ ሞክሩ። ይህ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በግልጽ የሚያሳይ ነው። የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በማየት ባሕርያቱን ስናስተውል እሱን በደንብ ልናውቀውና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ልንነሳሳ እንችላለን። ከዚህ በመቀጠል ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅሞ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ትምህርቶችን ያስተማረባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።
አምላክ የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅሞ ስለ ራሱ ያስተምረናል
6. ወደ ሌላ አካባቢ የሚፈልሱትን ወፎች በመመልከት ምን ትምህርት እናገኛለን?
6 ይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ አለው። እስራኤላውያን በየዓመቱ ከየካቲት መጨረሻ አንስቶ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ራዛዎች ወደ ሰሜን ሲፈልሱ የማየት አጋጣሚ ነበራቸው። አምላክ “በሰማይ የምትበረው ራዛ . . . ወቅቷን ታውቃለች” በማለት ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል። (ኤር. 8:7) ይሖዋ ለእነዚህ ወፎች የሚፈልሱበት ጊዜ እንደመደበላቸው ሁሉ ፍርዱን የሚያስፈጽምበትንም ጊዜ መድቧል። በዛሬው ጊዜ የሚፈልሱ ወፎችን ስንመለከት ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም ለማጥፋት ‘የወሰነው ጊዜ’ እንዳለ መተማመን እንችላለን።—ዕን. 2:3
7. ወፎች የሚበርሩበትን መንገድ በመመልከት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (ኢሳይያስ 40:31)
7 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣል። ይሖዋ ሕዝቡ በሚደክሙበት ወይም ተስፋ በሚቆርጡበት ጊዜ ብርታት በመስጠት “እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ [እንዲወጡ]” እንደሚያደርግ በኢሳይያስ አማካኝነት ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 40:31ን አንብብ።) እስራኤላውያን ንስሮች ያለምንም ድካም ወደ ላይ ወጥተው ሲበርሩ በተደጋጋሚ ያዩ ነበር፤ ንስሮቹ እንዲህ የሚያደርጉት ወደ ላይ የሚወጣውን የአየር ሞገድ በመከተል ነው። ይህ ይሖዋ ለእነዚህ ወፎች ኃይል እንደሰጣቸው ሁሉ ለአገልጋዮቹም ኃይል እንደሚሰጥ እንድናስታውስ የሚያደርግ ጠንካራ ማስረጃ ነው! ትላልቅ ወፎች ክንፋቸውን እምብዛም ማርገብገብ ሳያስፈልጋቸው ሰማይ ላይ ወደ ላይ ወጥተው ሲንሳፈፉ ስታዩ ይሖዋ ለእናንተም ከችግሮቻችሁ በላይ እንድትንሳፈፉ የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጣችሁ አስታውሱ።
8. ኢዮብ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች በመመርመር ምን ትምህርት አግኝቷል? እኛስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
8 ይሖዋ እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው። ይሖዋ፣ ኢዮብ በእሱ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጠናክር ረድቶታል። (ኢዮብ 32:2፤ 40:6-8) ከኢዮብ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ከዋክብትን፣ ደመናትንና መብረቅን ጨምሮ የተለያዩ ፍጥረታትን ጠቅሶለታል። ይሖዋ እንደ ዱር በሬና ፈረስ ስላሉ እንስሳትም ተናግሯል። (ኢዮብ 38:32-35፤ 39:9, 19, 20) እነዚህ የፍጥረት ሥራዎች አምላክ ያለውን አስደናቂ ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍቅሩንና ወደር የለሽ ጥበቡንም ያሳያሉ። ይህ ውይይት ኢዮብ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ከምንጊዜውም ይበልጥ እንዲያጠናክር ረድቶታል። (ኢዮብ 42:1-6) እኛም ፍጥረትን በትኩረት መመልከታችን ይሖዋ ገደብ የሌለው ጥበብ እንዳለውና ከእኛ ይበልጥ እጅግ ኃያል እንደሆነ እንድናስታውስ ይረዳናል። አሁን ያሉብንን ችግሮች ሁሉ ማስወገድም ይችላል፤ ደግሞም እንዲህ ያደርጋል። ይህን መገንዘባችን በእሱ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል።
ኢየሱስ የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅሞ ስለ አባቱ አስተምሮናል
9-10. ፀሐይና ዝናብ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምሩናል?
9 ኢየሱስ ስለ ፍጥረት ጠንቅቆ ያውቃል። አባቱ ጽንፈ ዓለምን ሲፈጥር “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ አብሮት ሠርቷል። (ምሳሌ 8:30) በኋላ ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ስለ አባቱ ለማስተማር ፍጥረትን ተጠቅሟል። እስቲ ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ ጥቂቶቹን እንመልከት።
10 ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ብዙዎች እምብዛም ትኩረት ስለማይሰጧቸው ሁለት የፍጥረት ሥራዎች ተናግሯል፤ እነሱም ፀሐይና ዝናብ ናቸው። ሁለቱም ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ናቸው። ይሖዋ እሱን የማያገለግሉ ሰዎች ፀሐይና ዝናብ እንዳያገኙ መከልከል ይችል ነበር። እሱ ግን በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም ሰዎች ፀሐይንና ዝናብን ሰጥቷል። (ማቴ. 5:43-45) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ በመጠቀም ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር እንድናሳይ እንደሚፈልግ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። ፀሐይ ስትጠልቅ ያለውን ማራኪ እይታም ሆነ መንፈስን የሚያድስ ዝናብ ስንመለከት ይሖዋ ስላሳየው ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍቅር ማሰብ እንችላለን። እሱ የተወልን ምሳሌ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች በመስበክ ተመሳሳይ ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል።
11. የሰማይ ወፎችን መመልከታችን የሚያበረታታን እንዴት ነው?
11 ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ያሟላልናል። ኢየሱስ በዚያው የተራራ ስብከት ላይ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል።” ኢየሱስ “ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” በማለት በጠየቀበት ወቅት አድማጮቹ ወፎች ሲበርሩ እየተመለከቱ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:26) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ በመጠቀም ይሖዋ ቁሳዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟላልን ፍቅራዊ ማረጋገጫ ሰጥቶናል! (ማቴ. 6:31, 32) ከፍጥረት የሚገኘው ይህ ትምህርት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ያበረታታል። በስፔን ያለች አንዲት ወጣት አቅኚ የምትኖርበት አመቺ ቦታ ማግኘት ባለመቻሏ ተስፋ ቆርጣ ነበር። ሆኖም ወፎች ጥሬና ፍራፍሬ እየለቀሙ ሲበሉ ስታይ በጣም ተበረታታች። እንዲህ ብላለች፦ “እነዚያን ወፎች ሳይ ይሖዋ እነሱን እንደሚንከባከባቸው ሁሉ እኔንም እንደሚንከባከበኝ አሰብኩ።” ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እህት የምትኖርበት ቤት አገኘች።
12. ማቴዎስ 10:29-31 ላይ እንደተጠቀሰው ድንቢጦች ስለ ይሖዋ ምን ያስተምሩናል?
12 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ ይመለከተናል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለስብከት ከመላኩ በፊት ተቃውሞን እንዳይፈሩ አዘጋጅቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:29-31ን አንብብ።) እንዲህ ያደረገው በእስራኤል ውስጥ ካሉ በጣም የተለመዱ ወፎች መካከል አንዷ የሆነችውን ድንቢጥን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ነው። ድንቢጦች በኢየሱስ ዘመን በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ወፎች ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ “ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። አክሎም “እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ” ብሏቸዋል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል፤ ስለዚህ ስደትን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የለም። ደቀ መዛሙርቱ በከተማዎችና በመንደሮች ውስጥ እየሰበኩ ባሉበት ወቅት ድንቢጦችን ሲያዩ ኢየሱስ የነገራቸውን ነገር አስታውሰው መሆን አለበት። ትናንሽ ወፎችን ስትመለከቱ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታችሁ አስታውሱ፤ ምክንያቱም እናንተም “ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።” በይሖዋ እርዳታ ተቃውሞን በድፍረት መጋፈጥ ትችላላችሁ።—መዝ. 118:6
ከፍጥረት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
13. ከፍጥረት ትምህርት ለማግኘት ምን ይረዳናል?
13 ከፍጥረት ስለ ይሖዋ ሌሎች ብዙ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። እንዴት? በቅድሚያ ፍጥረትን በትኩረት የምንመለከትበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ከዚያም ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምረን ማሰብ ይኖርብናል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ ሁሌም ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ጄራልዲን የተባለች በካሜሩን የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ያደግኩት ከተማ ውስጥ ነው፤ ስለዚህ ፍጥረትን ለመመልከት የታሰበበት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተገንዝቤአለሁ።” አልፎንሶ የተባለ ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ብቻዬን ሆኜ የይሖዋን ፍጥረታት የምመለከትበትና አንድ የፍጥረት ሥራ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምረኝ የማሰላስልበት ጊዜ መመደብ እንደሚያስፈልገኝ አስተውያለሁ።”
14. ዳዊት በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ሲያሰላስል ምን ተምሯል?
14 ዳዊት በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በጥልቀት ያሰላስል ነበር። እንዲህ በማለት ለይሖዋ ተናግሯል፦ “የጣቶችህን ሥራ ሰማያትን፣ አንተ የሠራሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን ስመለከት፣ ታስበው ዘንድ ሟች ሰው ምንድን ነው?” (መዝ. 8:3, 4) አዎ፣ ዳዊት የምሽቱን ሰማይ ቀና ብሎ ሲመለከት በጽንፈ ዓለም አስደናቂነት ብቻ ተደምሞ አላቆመም። ከዋክብት ስለ አምላክ በሚያስተምሩት ትምህርትም ላይ አሰላስሏል። ይሖዋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ተምሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ዳዊት በእናቱ ማህፀን ውስጥ ስላደገበት መንገድ አሰላስሏል። በእነዚህ አስደናቂ ነገሮች ላይ ማሰላሰሉ ለይሖዋ ጥበብ ያለውን አድናቆት አሳድጎለታል።—መዝ. 139:14-17
15. የይሖዋን ባሕርያት እንድታዩ የረዷችሁን የፍጥረት ሥራዎች ጥቀሱ። (መዝሙር 148:7-10)
15 እናንተም ልክ እንደ ዳዊት ልታሰላስሉባቸው የምትችሏቸውን የፍጥረት ሥራዎች በአቅራቢያችሁ ማግኘት ትችላላችሁ። ዙሪያችሁን ብትመለከቱ የይሖዋን በርካታ ባሕርያት ማስተዋል ትችላላችሁ። ለምሳሌ የፀሐይ ሙቀት ሰውነታችሁ ላይ ሲያርፍ የይሖዋን ኃይል አስቡ። (ኤር. 31:35) አንዲት ወፍ ጎጆዋን ስትሠራ ስትመለከቱ የአምላክን ጥበብ አድንቁ። አንዲት ቡችላ ጭራዋን ለመያዝ እየሞከረች ስትጫወት ይሖዋ ደስተኛ አምላክ እንደሆነ አስቡ። አንዲት እናት ልጇን ስታጫውት ስታዩ ደግሞ ይሖዋን ለፍቅሩ አመስግኑት። ስለ ይሖዋ የምንማርባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን፤ ምክንያቱም ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከቅርብ እስከ ሩቅ ያሉት ፍጥረታቱ ሁሉ እሱን ያወድሱታል።—መዝሙር 148:7-10ን አንብብ።
16. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
16 አምላካችን በጥበቡ፣ በአሳቢነቱ፣ በፈጠራ ችሎታውና በኃይሉ ተወዳዳሪ የለውም። የፍጥረት ሥራዎችን በትኩረት የምንመለከት ከሆነ እነዚህን ጨምሮ በርካታ ባሕርያቱን በግልጽ ማየት እንችላለን። እንግዲያው ሁላችንም የፍጥረት ሥራዎችን የምንመለከትበትና እነዚህ የፍጥረት ሥራዎች ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሩን የምናሰላስልበት ቋሚ ጊዜ እንመድብ። እንዲህ ካደረግን ወደ ፈጣሪያችን ከምንጊዜውም ይበልጥ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:8) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ወላጆች ፍጥረትን ተጠቅመው ልጆቻቸው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
መዝሙር 5 የአምላክ ድንቅ ሥራዎች
a የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች በጣም አስደናቂ ናቸው። እጅግ ከፍተኛ ኃይል ካላት ፀሐይ አንስቶ ለስላሳ እስከሆኑት አበቦች ድረስ ሥራዎቹ ያስደምሙናል። ፍጥረታትን በማየት የምናገኘው ትምህርት ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ እንድናውቅም ይረዳናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ፍጥረትን በደንብ ለመመልከት ጊዜ መመደብ ያለብን ለምን እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን ወደ አምላካችን ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።