መለኮታዊ ትምህርትና የአጋንንት ትምህርት የሚያደርጉት ውጊያ
“በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:1
1. ክርስቲያኖች በየትኛው ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ?
ዕድሜህን በሙሉ ጦርነት በሚደረግበት አካባቢ ብታሳልፍ ምን ይሰማሃል? የጠመንጃ ተኩስ እየሰማህ ብትተኛና ጠዋት ስትነሣ ደግሞ የመድፍ ድምፅ ብትሰማ እንዴት ይሰማሃል? በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች እንደዚህ ባለው ሁኔታ የሚኖሩ ሰዎች አሉ፤ ሁኔታው ያሳዝናል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ደግሞ ሁሉም ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ለ6,000 ዓመታት ያህል ሲካሄድ በቆየና በዘመናችን ደግሞ በጣም በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ይኖራሉ። ለረጅም ዓመታት የቆየው ይህ ጦርነት ምንድን ነው? በእውነትና በውሸት፣ በመለኮታዊ ትምህርትና በአጋንንት ትምህርት መካከል የሚደረግ ውጊያ ነው። ይህ ጦርነት፣ ቢያንስ ከአንደኛው ተዋጊ አንጻር ሲታይ፣ በጭካኔውና በገዳይነቱ በሰው ታሪክ ውስጥ ከተነሡት ግጭቶች ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
2. (ሀ) በጳውሎስ አባባል መሠረት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑት የትኞቹ ሁለት ወገኖች ናቸው? (ለ) ጳውሎስ “ሃይማኖት” ወይም እምነት ሲል ምን ማለቱ ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ “መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል” በማለት በሁለቱ ወገኖች መካከል ስላለው ግጭት ጠቅሷል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) የአጋንንት ትምህርት ይበልጥ የሚያይለው “በኋለኞቹ ዘመናት” መሆኑን ልብ በል። ከጳውሎስ ዘመን አንጻር ሲታይ ይህ እኛ የምንኖርበት ዘመን የኋለኛው ዘመን ነው። እንዲሁም ከአጋንንት ትምህርት ጋር የሚቃረነው “ሃይማኖት” ወይም እምነት መሆኑን ልብ በል። እዚህ ላይ “ሃይማኖት” ወይም እምነት ተብሎ የተጠቀሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙትና በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት በተነገሩት የአምላክ ቃላት ላይ የተመሠረተውን ትምህርት ያመለክታል። እንደዚህ ያለው እምነት ሕይወት ያስገኛል። አንድን ክርስቲያን የአምላክን ፈቃድ እንዴት እንደሚያደርግ ያስተምረዋል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት ነው።—ዮሐንስ 3:16፤ 6:40
3. (ሀ) በእውነትና በውሸት መካከል በሚደረገው ጦርነት በተሸናፊዎቹ ላይ ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) ከአጋንንት ትምህርቶች በስተጀርባ ያለው ማን ነው?
3 ከዚህ እምነት የሚወጣ ማንኛውም ሰው የዘላለም ሕይወት አያገኝም። በጦርነቱ ተሸናፊ ይሆናል። በአጋንንት ትምህርት ለመታለል ፈቃደኛ መሆን ይህን የመሰለ ውድቀት ያስከትላል። (ማቴዎስ 24:24) በግለሰብ ደረጃ የዚህ ጦርነት ተሸናፊዎች ከመሆን እንዴት ልንርቅ እንችላለን? “የአጋንንት አለቃ” የሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ ዓላማ ማስፈጸሚያ የሆኑትን እነዚህ የውሸት ትምህርቶች በመቃወም ነው። (ማቴዎስ 12:24) ሰይጣን ራሱ “የሐሰት አባት” እንደመሆኑ መጠን የሰይጣን ትምህርቶች ሐሰት እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል። (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን እንዴት ባለ ዘዴ ተጠቅሞ በውሸት እንዳሳታቸው ተመልከት።
የአጋንንት ትምህርቶች ተጋለጡ
4, 5. ሰይጣን ለሔዋን ምን ውሸት ነገራት? ይህስ ክፉ የነበረው ለምን ነበር?
4 የተፈጸሙት ሁኔታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘፍጥረት 3:1–5 ላይ ተመዝግበዋል። ሰይጣን እባብን በመጠቀም ሔዋን ወደተባለችው ሴት ቀረብ ብሎ “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” በማለት ጠየቃት። ጥያቄው ምንም ጉዳት ያዘለ አይመስልም። ነገር ግን ይህን ጥያቄ ደግመን እንመልከት። ሰይጣን “በውኑ እግዚአብሔር . . . አዟልን?” ሲል ‘አምላክ እንዲህ ያለውን ነገር ለምን ያዛል?’ ማለቱ ነበር።
5 ሔዋን በየዋህነት አምላክ ይህን የመሰለ ትእዛዝ እንደሰጠ ገለጸች። መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ ከበሉ እንደሚሞቱ አዳም ነግሯት ስለነበረ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን መለኮታዊ ትምህርት ታውቃለች። (ዘፍጥረት 2:16, 17) የሰይጣን ጥያቄ ፍላጐቷን ስለቀሰቀሰው ሊናገር የፈለገውን ዋና ነጥብ አዳመጠች። “እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም።” እንዴት ያለ ክፉ ንግግር ነው! ሰይጣን የእውነትና የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለሰብአዊ ልጆቹ ዋሽቷል ብሎ ከሰሰው።—መዝሙር 31:5፤ 1 ዮሐንስ 4:16፤ ራእይ 4:11
6. ሰይጣን የይሖዋን መልካምነትና የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት የተገዳደረው እንዴት ነበር?
6 ነገር ግን ሰይጣን የተናገረው ይህን ብቻ አልነበረም። በመቀጠል “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” አለ። በሰይጣን አባባል ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የተትረፈረፈ ዝግጅት ያደረገላቸው ይሖዋ አምላክ በጣም ጥሩ የሆነ ነገር ከልክሏቸዋል። እንደ አማልክት እንዳይሆኑ ሊከለክላቸው ፈልጓል። ከዚህም የተነሣ ሰይጣን የአምላክን ጥሩነት ተገዳድሯል። እንዲሁም የራስን ፍላጐት ማሳደድና ሆን ብሎ የአምላክን ሕግ መጣስ ጠቃሚ ነው የሚል ትምህርት አስፋፍቷል። አምላክ ሰይጣን በራሱ ፍጥረት ላይ ያለውን ሉዓላዊ ገዥነት በመገዳደር ሰው በሚያደርገው ነገር ላይ ገደብ የማበጀት መብት የለውም ብሏል።
7. የአጋንንት ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው መቼ ነበር? የአጋንንት ትምህርቶች በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ የሆኑት እንዴት ነው?
7 የአጋንንት ትምህርት መሰማት የጀመረው በእነዚህ የሰይጣን ቃላት ነው። ዛሬም ቢሆን እነዚህ ክፉ ትምህርቶች ከሰይጣን አነጋገር ጋር የሚመሳሰሉ አምላክ የለሽ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያስፋፋሉ። በአሁኑ ጊዜ የሌሎች ዓመፀኛ መናፍስትን ድጋፍ ያገኘው ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ እንዳደረገው አምላክ የሰዎችን አካሄድ የሚገዙ ደንቦችን ለማውጣት ያለውን መብት አሁንም መገዳደሩን አላቆመም። አሁንም እንኳ ቢሆን የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት ይገዳደራል፤ ሰዎችም ሰማያዊ አባታቸውን እንዳይታዘዙ ለማድረግ ይሞክራል።—1 ዮሐንስ 3:8, 10
8. አዳምና ሔዋን በኤደን ምን አጡ? ነገር ግን ይሖዋ እውነተኛ መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነበር?
8 በመለኮታዊ ትምህርትና በአጋንንት ትምህርት መካከል በሚደረገው ውጊያ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ግጭት ወቅት አዳምና ሔዋን የተሳሳተ ውሳኔ በማድረጋቸው ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:19) ጊዜ እያለፈ ሲሄድና ሰውነታቸውም እያረጀ ሲመጣ በኤደን ውስጥ ማን ውሸት ተናግሮ እንደነበረና ማን ደግሞ እውነት ተናግሮ እንደነበረ በግልጽ ተረጋገጠላቸው። ይሁን እንጂ በአካላዊ ሁኔታ ከመሞታቸው በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የሕይወታቸው ምንጭ ከሆነው ፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸው ዝምድና ሲቋረጥ በእውነትና በውሸት መካከል በሚደረገው ውጊያ የመጀመሪያዎቹ የጦር ጉዳተኞች ወይም ተገዳዮች ሆኑ። ይህም የሆነው በመንፈሳዊ ሁኔታ በሞቱ ጊዜ ነው።—መዝሙር 36:9፤ ከኤፌሶን 2:1 ጋር አወዳድር።
በዛሬው ጊዜ ያለው የአጋንንት ትምህርት
9. ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ የአጋንንት ትምህርቶች ምን ያህል ተሳክተውላቸው ነበር?
9 በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ በ1914 ወደ ጀመረው “የጌታ ቀን” በመንፈስ ተወስዶ ነበር። (ራእይ 1:10) በዚያን ጊዜ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባረሩና ወደ ምድር አካባቢ መጡ። ይህም ለታላቁ ፈጣሪያችን ተቃዋሚ ትልቅ ሽንፈት ነበር። በይሖዋ አገልጋዮች ላይ በሚያቀርበው የማያቋርጥ ክስ አማካኝነት የሚያሰማው ድምፅ በሰማይ ላይ ከዚህ በኋላ አልተሰማም። (ራእይ 12:10) ይሁንና ከኤደን ገነት ጀምሮ የአጋንንት ትምህርቶች በምድር ላይ ምን ያህል ተስፋፍተዋል? የተጻፈው መዝገብ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ” ይላል። (ራእይ 12:9) ዓለም በሙሉ በሰይጣን ውሸት ተጠምዷል። ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” መባሉ አያስደንቅም!—ዮሐንስ 12:31፤ 16:11
10, 11. በዛሬው ጊዜ ሰይጣንና አጋንንቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙት በምን መንገዶች ነው?
10 ሰይጣን ከሰማይ ከተባረረ በኋላ መሸነፉን አምኖ ተቀብሏልን? በጭራሽ! መለኮታዊ ትምህርትንና ከዚህ ትምህርት ጋር የተጣበቁትን ሰዎች መዋጋቱን ለመቀጠል ቆርጦ ተነሣስቷል። ከሰማይ ከተጣለ በኋላ ሰይጣን ጦርነቱን በመቀጠል “ዘንዶውም [ሰይጣን] በሴቲቱ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።”—ራእይ 12:17
11 ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች መዋጋት ብቻ ሳይሆን ዓለምን በፕሮፓጋንዳው በማጥለቅለቅ በሰው ልጆች ላይ ያለውን የበላይነት ለማጠናከር መሞከሩን ቀጥሏል። በጌታ ቀን ስለሚሆኑት ነገሮች ከሚገልጹት ራእዮች በአንዱ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ሰይጣንን፣ ምድራዊ የፖለቲካ ድርጅቱንና በዘመናችን የሚገኘውን የዓለም ኃያል መንግሥት የሚወክሉትን ሦስት አውሬዎች ተመልክቷል። ከእነዚህ ከሦስቱ አፍ እንቁራሪቶች ወጡ። እነዚህ እንቁራሪቶች ምንን ያመለክታሉ? ዮሐንስ “ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፣ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ” በማለት ጽፏል። (ራእይ 16:14) በግልጽ እንደሚታየው የአጋንንት ትምህርቶች በምድር ላይ ተሰራጭተዋል። ሰይጣንና አጋንንቱ አሁንም ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር እየተዋጉ ሲሆን በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ውጊያቸውን እንዲያቆሙ እስከሚገደዱበት ድረስ ጦርነታቸውን ይገፉበታል።—ራእይ 20:2
የአጋንንትን ትምህርቶች ለይቶ ማወቅ
12. (ሀ) የአጋንንትን ትምህርቶች መቋቋም የሚቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን በአምላክ አገልጋዮች ላይ ያለውን ዓላማ ለማሳካት የሚሞክረው እንዴት ነው?
12 አምላክን የሚፈሩ ሰዎች የአጋንንትን ትምህርቶች መቋቋም ይችላሉን? አዎን፣ በሁለት ምክንያቶች የተነሣ መቋቋም ይችላሉ። አንደኛው ምክንያት መለኮታዊ ትምህርት ይበልጥ ኃይለኛ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህን ትምህርቶች ለመቋቋም እንችል ዘንድ ይሖዋ የሰይጣንን የውጊያ ስልቶች ስላጋለጣቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእሱን አሳብ አንስተውምና” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ስደት መሆኑን እናውቃለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ከዚህ ይበልጥ መሠሪ በሆነ መንገድ ደግሞ አምላክን የሚያገለግሉትን ሰዎች አእምሮና ልብ ለመማረክ ይሞክራል። ሔዋንን አሳታትና መጥፎ ምኞት በልቧ ውስጥ አስቀመጠ። ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ይሞክራል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች “ነገር ግን እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” በማለት ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) የሰው ዘሮችን አስተሳሰብ በአጠቃላይ እንዴት እንዳበላሸው ተመልከት።
13. ከኤደን ጀምሮ ሰይጣን ለሰው ልጆች ምን ውሸት ሲነግራቸው ቆይቷል?
13 ሰይጣን ይሖዋን ሐሰተኛ ነው ብሎ በሔዋን ፊት ከሰሰው። በተጨማሪም ፈጣሪያቸውን ካልታዘዙ ሰዎች አማልክት ይሆናሉ በማለት ነገራት። የሰው ልጆች የወደቁበት ዛሬ የምናየው የኃጢአተኝነት ሁኔታ ውሸታሙ ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አለመሆኑን አረጋግጧል። ዛሬ እንደምናየው ሰዎች አማልክት አይደሉም! ይሁን እንጂ ሰይጣን በዚያ የመጀመሪያ ውሸት ላይ ሌሎች ተመሳሳይ ውሸቶች መናገሩን ቀጠለ። የሰው ነፍስ የማትሞት ናት የሚል ሐሳብ አመነጨ። በዚህ ሁኔታ በሌላ መንገድ አማልክት መሆን ይቻላል የሚል ማራኪ ሐሳብ ለሰው ልጆች አቀረበ። ከዚያም በዚህ የሐሰት መሠረተ ትምህርት ላይ በመመሥረት የእሳታማ ሲኦልን፣ የመንጽሔን፣ የመናፍስትነትንና የአያቶችን አምልኮ ትምህርቶች አስፋፋ። እነዚህ ውሸቶች አሁንም በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ባሪያ አድርገው ይዘዋል።—ዘዳግም 18:9–13
14, 15. ስለ ሞትና ሰው ስላለው የወደፊት ተስፋ እውነተኛው ነገር ምንድን ነው?
14 ይሖዋ ለአዳም የነገረው ነገር እውነት እንደነበረ ግልጽ ነው። አዳም በአምላክ ላይ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ሞቷል። (ዘፍጥረት 5:5) አዳምና ዝርያዎቹ በሞቱ ጊዜ በድን፣ የማይሰሙና የማይንቀሳቀሱ ነፍሶች ሆኑ። (ዘፍጥረት 2:7፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ከአዳም ኃጢአትን በመውረሳቸው ምክንያት ሰብአዊ ነፍሶች ሁሉ ይሞታሉ። (ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ በኤደን ይሖዋ የዲያብሎስን ሥራ ተዋግቶ የሚያሸንፍ ዘር እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠ። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ዘር የአምላክ የራሱ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ሆኖ ሞተ። የተሠዋው ሕይወቱ የሰውን ዘር ከሟችነት ሁኔታቸው ሊያድናቸው የሚችል ቤዛ ሆነላቸው። በታዛዥነት በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ አዳም ያጠፋውን የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ አላቸው።—ዮሐንስ 3:36፤ ሮሜ 6:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6
15 የሰው ልጆች እውነተኛ ተስፋ ቤዛው እንጂ ነፍስ አትሞትም የሚል የማይጨበጥ ሐሳብ አይደለም። ይህ መለኮታዊ ትምህርት ነው። እውነት ነው። የይሖዋ ፍቅርና ጥበብ በአስደናቂ መንገድ የታየበት ዝግጅት ነው። (ዮሐንስ 3:16) ይህንን እውነት በመማራችንና በዚህ ረገድ ከአጋንንት ትምህርቶች ነፃ በመውጣታችን ምን ያህል አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!—ዮሐንስ 8:32
16. ሰዎች የራሳቸውን ጥበብ ሲከተሉ የኋላ ኋላ የሚከተሉት ውጤቶች ምንድን ናቸው?
16 ሰይጣን በኤደን ገነት በተናገረው ውሸት አዳምንና ሔዋንን አምላክ ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩና በራሳቸው ጥበብ ተማምነው እንዲመሩ አበረታታቸው። ዛሬ፣ የዚህን ውጤት በወንጀሉ፣ በኢኮኖሚው ድቀት፣ በጦርነቶችና በዓለም ላይ በሚገኘው ከፍተኛ መበላለጥ እያየነው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና” ማለቱ አያስደንቅም። (1 ቆሮንቶስ 3:19) ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ሰዎች የይሖዋን ትምህርቶች ከመስማት ይልቅ እየተሠቃዩ መኖርን በሞኝነት ይመርጣሉ። (መዝሙር 14:1–3፤ 107:17) መለኮታዊ ትምህርትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ግን በዚህ ወጥመድ ከመያዝ ይድናሉ።
17. ሰይጣን ያስፋፋው “በውሸት እውቀት የተባለው” ምንድን ነው? ፍሬዎቹስ ምንድን ናቸው?
17 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፣ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፣ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) ይህ እውቀት የአጋንንት እውቀት ነው። በጳውሎስ ዘመን ይህ እውቀት በጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች ያስፋፉት የነበረውን የክህደት ትምህርት ያመለክታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:16–18) ከጊዜ በኋላ በውሸት እውቀት የተባሉ እንደ ግኖስቲሲዝምና የግሪክ ፍልስፍና የመሳሰሉ ትምህርቶች ጉባኤውን በከሉት። በዛሬው ዓለም ውስጥ አምላክ የለም ባይነት፣ ስለ አምላክ መኖር ሊታወቅ አይችልም ባይነት፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና መጽሐፍ ቅዱስን መተቸት በዘመናችን የሚገኙ ከሀዲዎች የሚያስፋፉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ሐሳብ በውሸት እውቀት የተባሉ ናቸው። በውሸት እውቀት የተባሉት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ያፈሯቸው ፍሬዎች በሥነ ምግባር ውድቀት፣ በጣም ተስፋፍቶ በሚገኘው ለሥልጣን አክብሮት ባለማሳየት፣ በማጭበርበርና የሰይጣንን የነገሮች ሥርዓት ለይተው በሚያሳውቁት የራስ ወዳድነት ድርጊቶች አማካኝነት ይታያሉ።
ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር መጣበቅ
18. መለኮታዊውን ትምህርት በዘመናችን የሚከተሉት እነማን ናቸው?
18 ምንም እንኳ ሰይጣን ከኤደን ጀምሮ ምድርን በአጋንንት ትምህርቶች ቢያጥለቀልቃትም መለኮታዊውን ትምህርት ለማግኘት ፍለጋ ያደረጉ ጥቂት ሰዎች ምንጊዜም አልታጡም። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሆነዋል። ይህም ቁጥር በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የመንገሥ እርግጠኛ ተስፋ ያላቸውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎችና የዚህን መንግሥት ምድራዊ ግዛት የመውረስ ተስፋ ያላቸው ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑትን እጅግ ብዙ ሰዎችን ይጨምራል። (ማቴዎስ 25:34፤ ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:3, 9) ዛሬ እነዚህ ሰዎች “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” የሚሉት የኢሳይያስ ቃላት በሚሠሩበት አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ በአንድነት ተሰብስበዋል።—ኢሳይያስ 54:13
19. ከይሖዋ መማር ምን ነገሮችን ይጨምራል?
19 ምንም እንኳ እውነተኛውን መሠረተ ትምህርት ማወቁ አስፈላጊ ቢሆንም ከይሖዋ የተማሩ መሆን ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። ይሖዋ እንዴት መኖር እንደሚገባን፣ መለኮታዊውን ትምህርት እንዴት በግል ሕይወታችን ላይ ልንሠራበት እንደምንችል ያስተምረናል። ለምሳሌ ያህል የራስ ወዳድነት፣ የብልግናና በራስ አሳብ የመመራት መንፈስ በዙሪያችን ባለው ዓለም ላይ በጣም አይለው ይገኛሉ። እነዚህ ባሕርያት እንዳይጋቡብን እንከላከላለን። ሀብት የማሳደዱ ከንቱ ልፋት ወደ ሞት የሚያመራ መሆኑን እናውቃለን። (ያዕቆብ 5:1–3) “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” በሚሉት የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት የተገለጸውን መለኮታዊ ትምህርት ምንጊዜም አንረሳም።—1 ዮሐንስ 2:15
20, 21. (ሀ) ሰይጣን ሰዎችን ለማሳወር በሚያደርጋቸው ጥረቶች በምን ይጠቀማል? (ለ) ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር ለሚጣበቁ ሁሉ ምን በረከቶች ይመጡላቸዋል?
20 የአጋንንት ትምህርቶች በሰለባዎቻቸው ላይ የሚያስከትሉት ጠንቆች ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ [ሰይጣን] የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” በማለት ከጻፋቸው ቃላት መረዳት ይቻላል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን እውነተኛ ክርስቲያኖችንም ቢሆን በዚህ መንገድ ለማሳወር ይፈልጋል። በዔደን እባብን በመጠቀም ከአምላክ አገልጋዮች መካከል አንዷን አስቷል። ዛሬ፣ ዓመፅ ወይም ብልግና የተሞሉ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ይጠቀማል። የሬድዮ፣ የሥነ ጽሑፍና የሙዚቃ ዝግጅቶችን ለክፉ ይጠቀምባቸዋል። ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች በጣም ኃይለኛው መጥፎ ባልንጀርነት ነው። (ምሳሌ 4:14፤ 28:7፤ 29:3) ምንጊዜም ቢሆን እነዚህ ነገሮች ምን እንደሆኑ አስታውሱ። የአጋንንት ትምህርቶችና መሣሪያዎቻቸው ናቸው።
21 ሰይጣን በዔደን የተናገራቸው ቃላት ውሸት መሆናቸውን አትርሳ፤ ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ግን እውነት መሆናቸው ተረጋግጧል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁኔታው እንደዚያው ሆኖ ቀጥሏል። ሰይጣን ሁልጊዜ ውሸታምነቱ እየተረጋገጠበት ሲሆን መለኮታዊ ትምህርት ግን ምንጊዜም እውነት ሆኖ ቀጥሏል። (ሮሜ 3:4) ከአምላክ ቃል ጋር ከተጣበቅን በእውነትና በውሸት መካከል በሚደረገው ጦርነት ከአሸናፊው ወገን እንቆማለን። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) እንግዲያው ሁሉንም ዓይነት የአጋንንት ትምህርቶች ላለመቀበል የቆረጥን እንሁን! በዚህ መንገድ በእውነትና በውሸት መካከል የሚደረገው ጦርነት እስኪያበቃ ድረስ እንጸናለን። እውነት ያሸንፋል። በዚያን ጊዜ ሰይጣን አይኖርም። መለኮታዊ ትምህርት ብቻ በምድር ሁሉ ላይ ድምፁ ይሰማል።—ኢሳይያስ 11:9
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ አጋንንታዊ ትምህርት መጀመሪያ የተሰማው መቼ ነበር?
◻ በሰይጣንና በአጋንንቱ የተሰራጩት አንዳንድ ውሸቶች ምንድን ናቸው?
◻ ዛሬ ሰይጣን ከልክ በላይ የሚሯሯጠው በምን መንገዶች ነው?
◻ ሰይጣን የአጋንንት ትምህርቶችን ለማስፋፋት በምን ይጠቀማል?
◻ ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር የሚጣበቁ ምን በረከቶችን ያገኛሉ?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጋንንታዊ ትምህርት በመጀመሪያ የተሰማው በኤደን ገነት ውስጥ ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ቤዛውና ስለ መንግሥቱ የቀረበው መለኮታዊ ትምህርት ለሰው ልጆች ብቸኛ የሆነውን ተስፋ ይሰጣል