መለኮታዊ ትምህርት ድል ያደርጋል
“ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” —ኢሳይያስ 30:20, 21
1. የይሖዋ ትምህርት መለኮታዊ ትምህርት ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ ከማንም የበለጠ የጥሩ ትምህርት ምንጭ ነው። እርሱ የሚናገረውን፣ በተለይ በቅዱስ ቃሉ አማካኝነት የሚያስተምረንን ብንሰማ ታላቅ አስተማሪያችን ይሆንልናል። (ኢሳይያስ 30:20) በተጨማሪም የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “መለኮት” ሲል ይጠራዋል። (መዝሙር 50:1) ስለዚህ የይሖዋ ትምህርት መለኮታዊ ትምህርት ነው ማለት ነው።
2. አምላክ ብቻ ጥበበኛ ነው መባሉ እውነት የሆነው በምን መንገድ ነው?
2 ዓለም የሚኩራራባቸው ብዙ የትምህርት ተቋሞች አሉ። ይሁን እንጂ ከአንዳቸውም ቢሆን መለኮታዊ ትምህርት አይገኝም። እንዲያውም ባለፉት ዘመናት በሙሉ የተካበተው ዓለማዊ ጥበብ ዳርቻ በሌለው የይሖዋ ጥበብ ላይ ከተመሠረተው መለኮታዊ ትምህርት ጋር ሲወዳደር ከቅንጣት የሚቆጠር አይደለም። ሮሜ 16:27 አምላክ ብቻ ጠቢብ እንደሆነ ይናገራል። ይህም የሆነው ፍጹምና የተሟላ ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ስለሆነ ነው።
3. ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ አስተማሪ የሆነው ለምንድን ነው?
3 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የጥበብ ሁሉ መስፈሪያ ነው። ከእርሱ ጋር የሚተካከል ታላቅ አስተማሪ በምድር ላይ ተነስቶ አያውቅም። ይህም የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ለብዙ ዘመናት በሰማያት ሆኖ ከይሖዋ ሲማር ቆይቷል። እንዲያውም መለኮታዊ ትምህርት መሰጠት የጀመረው አምላክ የመጀመሪያ ፍጥረቱ የሆነውን ይህን አንድያ ልጁን ማስተማር በጀመረ ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ‘አባቴ እንዳስተማረኝ እናገራለሁ’ ብሎአል። (ዮሐንስ 8:28፤ ምሳሌ 8:22, 30) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት የክርስቶስ ቃላት ስለ መለኮታዊ ትምህርት ያለንን ዕውቀት ይጨምሩልናል። ቅቡዓን የኢየሱስ ተከታዮችም እርሱ ያስተማራቸውን ለሌሎች ሲያስተምሩ “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ” በጉባኤው በኩል እንዲታወቅ ፈቃዱ የሆነውን ታላቅ መምህር መምሰላቸው ነበር።—ኤፌሶን 3:10, 11፤ 5:1፤ ሉቃስ 6:40
ጥበብን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
4. የሰው አእምሮ ስላለው ችሎታ ምን ተብሏል?
4 እውነተኛ ጥበብ ለማግኘት አምላክ በሰጠን የማሰብ ችሎታ በትጋት መጠቀም ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ እውነተኛ ጥበብ ለማግኘት የተቻለው የሰው አእምሮ ከፍተኛ የሆነ እምቅ ችሎታ ስላለው ነው። ዘ ኢንክሬዲብል ማሽን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እጅግ በጣም የተራቀቀ ነው ብለን የምናስበው ኮምፒውተር እንኳን የሰው ልጅ አእምሮ ካለው ወሰን የለሽ ውስብስብነትና ሊፈጽም ከሚችላቸው የተለያዩ ተግባራት ጋር ሲወዳደር በጣም መናኛ ነው። የሰው አእምሮ ይህን የመሰለ ባሕርይ ሊኖረው የቻለው በጣም የረቀቀና በተወሰነ መጠን የተከፋፈለ የኤሌክትሮኬሚካል መልእክቶች ቅንብር ስላለው ነው። . . . በማንኛውም ቅጽበት በአእምሮአችሁ ውስጥ የሚመላለሱት በሚልዮን የሚቆጠሩ መልእክቶች ሊሸከሙ የሚችሏቸው መረጃዎች መጠን በጣም ከፍተኛ ነው። ስለ ሰውነታችሁ ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ አካባቢ የሚገልጹ መረጃዎችን ያቀብላሉ። በእግራችሁ ጣት አካባቢ የሚሰማችሁ የመቆርቆር ስሜት መኖሩን፣ ወይም የቡና መዓዛ መኖሩን ወይም ወዳጃችሁ የሚያስቅ ነገር መናገሩን የሚገልጽ ዜና ያመጡላችኋል። ሌሎች መልእክቶች ደግሞ መረጃዎችን አጠናቅረውና አመዛዝነው የተለያዩ ስሜቶችን፣ ትውስታዎችን፣ ሐሳቦችን ወይም ወደ ውሳኔ የሚያደርሱ እቅዶችን ይቀሰቅሳሉ። ከአእምሮአችሁ የሚወጡ መልእክቶች ወዲያው በቅጽበት ሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች አንድ ዓይነት ድርጊት እንዲፈጽሙ ይነግሯቸዋል። የእግራችሁን ጣት እንድታንቀሳቅሱ፣ ቡናውን እንድትጠጡ፣ እንድትስቁ ወይም ቀልዱን በቀልድ እንድትመልሱ ያደርጓችኋል። “ይህ ሁሉ በመከናወን ላይ እያለ አእምሮአችሁ አተነፋፈሳችሁን፣ የደማችሁን ኬሚካላዊ ውህደት፣ የሰውነታችሁን ሙቀትና ሌሎች ከራሳችሁ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አስፈላጊ ክንውኖችን ይቆጣጠራል። ሰውነታችሁ በአካባቢያችሁ በሚፈጸሙ ለውጦች ምክንያት ተግባሩን ሳያጓድል ሚዛኑን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችሉትን ትዕዛዞች ያስተላልፋል። በተጨማሪም ወደፊት ለሚነሱ ችግሮችና ተግባሮች እንዲዘጋጅ ያደርጋል።”—ገጽ 326
5. በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ጥበብ ምንድን ነው?
5 የሰው አእምሮ በጣም አስደናቂ ችሎታ እንዳለው አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ አእምሯችንን በከፍተኛ ደረጃ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? በጣም ጥልቅ በሆነ የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የሳይንስ ወይም የሥነ ሃይማኖት ጥናት በመመሰጥ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ አእምሮአችንን የምንጠቀመው መለኮታዊ ትምህርት ለመቀበል መሆን ይኖርበታል። እውነተኛ ጥበብ የሚያስገኝልን ይህ መለኮታዊ ትምህርት ነው። ይሁን እንጂ እውነተኛ ጥበብ ምንድን ነው? ጥበብ የተባለው ቃል ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሰጡት ትርጉም መሠረት አጽንኦት የሚሰጠው በትክክለኛ ዕውቀትና ማስተዋል ላይ የተመሠረተ የማመዛዘንና የመወሰን ችሎታ ነው። ጥበብ በዕውቀትና በማስተዋል ተጠቅመን ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ እንድንፈታ፣ ከአደገኛ ሁኔታዎች እንድንጠበቅ፣ ሌሎችን እንድንመክር፣ ግቦቻችን ላይ እንድንደርስ ያስችለናል። ጥበብ እንደ ድንቁርና እና እንደ ሞኝነት ያሉት መጥፎ ባሕርያት ተቃራኒ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል።—ዘዳግም 32:6፤ ምሳሌ 11:29፤ መክብብ 6:8
ታላቁ የይሖዋ ማስተማሪያ መጽሐፍ
6. እውነተኛ ጥበብ ለማሳየት ከፈለግን በምን ነገር መጠቀም ይኖርብናል?
6 በአካባቢያችን በጣም ብዙ ዓለማዊ ጥበብ አለ። (1 ቆሮንቶስ 3:18, 19) ይህ ዓለም በትምህርት ቤቶችና በሚልዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍትን በያዙ ቤተ መጻሕፍት የተሞላ ነው። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ብዙዎቹ ለቋንቋ፣ ለሒሳብ፣ ለሳይንስና ለሌሎች የዕውቀት መስኮች ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ታላቁ መምህር ከእነዚህ መጻሕፍት በሙሉ ታላቅ ብልጫ ያለው የማስተማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅቶልናል። እርሱም በመንፈስ የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይህ መጽሐፍ ከታሪክ፣ ከጂኦግራፊና ከሥነ ዕፀዋት ጋር ስለሚዛመዱ ነገሮች በሚያነሳበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች በሚተነብይበት ጊዜም ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ደስታ የሚገኝበትና ፍሬያማ የሆነ ኑሮ እንድንኖር ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ በዓለማዊ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በመጽሐፎቻቸው መጠቀም እንደሚኖርባቸው ሁሉ እኛም ‘ከይሖዋ የተማርን ሰዎች ሆነን’ በእውነተኛ ጥበብ ለመመላለስ ከፈለግን ከታላቁ የአምላክ መጽሐፍ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ይኖርብናል።—ዮሐንስ 6:45
7. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የአእምሮ ዕውቀት ብቻ ቢኖረን በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?
7 ይሁን እንጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የአእምሮ ዕውቀት ማግኘት እውነተኛ ጥበብ ከማግኘትና ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር ተስማምቶ ከመኖር ጋር አንድ አይደለም። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት በ17ኛው መቶ ዘመን እዘአ አንድ ቆርነሊየስ ቫን ደር ስቲን የተባለ ካቶሊክ ኢየሱሳዊ ሚስዮን ለመሆን ፈልጎ ቁመቱ በጣም አጭር በመሆኑ ሳይፈቀድለት ቀረ። ማንፍረት ባርተል ጀስዊትስ፣ ሂስትሪ ኤንድ ለጀንድ ኦቭ ዘ ሶሳይቲ ኦቭ ጂሰስ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፦ “ኮሚቴው ቫን ደር ስቲን መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በቃል ቢያጠና ማሟላት የሚኖርበትን የቁመት ብቃት እንደሚያነሳለት ነገረው። ቫን ደር ስቲን ይህን አዳጋች ጥያቄ ባይፈጽም ኖሮ ይህን ታሪክ መተረክ አስፈላጊ አይሆንም ነበር።” መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በቃል ለማጥናት ምን ያህል ከፍተኛ ጥረት ጠይቆበት እንደነበረ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል በትክክል መረዳት በቃል ከማጥናት መብለጡ አያጠያይቅም።
8. ከመለኮታዊ ትምህርት እንድንጠቀምና እውነተኛ ጥበብን እንድናሳይ ምን ሊረዳን ይችላል?
8 እውነተኛውን ጥበብና ከመለኮታዊ ትምህርት የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ትክክለኛውን የቅዱሳን ጽሑፎች ዕውቀት ማግኘት ይኖርብናል። በተጨማሪም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል መመራት ይኖርብናል። ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ ማለትም ጥልቅ የሆኑትን እውነቶች እንድንማር የሚያስችለን ይህ መንፈስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:10) እንግዲያው ይሖዋ የሚያስተምርበትን ታላቁን መጽሐፍ በትጋት እናጥና። በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲመራን እንጸልይ። በምሳሌ 2:1–6 ላይ ከተገለጸው ምክር ጋር በመስማማት ለጥበብ ትኩረት እንስጥ፣ ልባችን ወደ ማስተዋል እንዲያዘነብል እናድርግ፣ ማስተዋልንም እንጥራ። ይህንንም ስናደርግ የተደበቀ ሀብት እንደሚፈልግ ሰው ትጋት ያስፈልገናል። ‘ይሖዋን ስለ መፍራት ልንረዳና የአምላክን ዕውቀት ልናገኝ’ የምንችለው ይህን ካደረግን ብቻ ነው። በመለኮታዊ ትምህርት እንዴት እንደምንጠቀምና መለኮታዊው ትምህርት እንዴት ድል እንደሚነሳ ብንማር ከአምላክ ለሚገኘው ጥበብ ያለን አድናቆት ከፍ ይላል።
እየጨመረ የሚሄድ ዕውቀት
9, 10. በዘፍጥረት 3:15 ላይ እንደተመዘገበው አምላክ ምን ብሎ ነበር? የእነዚህ ቃላት ትክክለኛ ትርጉምስ ምንድን ነው?
9 መለኮታዊው ትምህርት የይሖዋ ሕዝቦች እየጨመረ የሚሄድ የቅዱሳን ጽሑፎች ዕውቀት እንዲያገኙ በማድረግ ድል ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል በኤደን ገነት በእባብ አማካኝነት የተናገረው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነና እርሱም የተከለከለውን ፍሬ መብላት የሞት ቅጣት ያስከትላል ብሎ አምላክ የተናገረው ውሸቱን ነው በማለት ይሖዋን እንደ ወነጀለ ተምረናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አምላክን ትዕዛዝ መጣስ በሰው ልጅ ላይ ሞት እንዳስከተለ ተመልክተናል። (ዘፍጥረት 3:1–6፤ ሮሜ 5:12) ሆኖም አምላክ ለሰይጣን “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ። እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” በማለት ለሰው ልጅ ተስፋ ሰጥቷል።—ዘፍጥረት 3:15
10 በእነዚህ ቃላት ውስጥ እያደር የሚገለጥ ምሥጢር ተካትቷል። ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት የእርሱ ልዕልና ንጉሣዊ አገዛዝ የመቀበል ሕጋዊ መብት በተሰጠው በአብርሃምና በዳዊት ዘር አማካኝነት መረጋገጡ እንደሆነ ሕዝቦቹን አስተምሯል። (ዘፍጥረት 22:15–18፤ 2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ ሕዝቅኤል 21:25–27) በተጨማሪም የሴቲቱ ማለትም የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ዋነኛ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ታላቁ አስተማሪያችን አስተምሮናል። (ገላትያ 3:16) ሰይጣን የተለያየ ፈተና ቢያመጣበትም ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ፣ ማለትም የዘሩ ተረከዝ እስከ ቆሰለበት ጊዜ ድረስ ታማኝነቱን ጠብቋል። በተጨማሪም ከሰው ልጆች የተውጣጡ 144,000 ተባባሪ ወራሾች ከክርስቶስ ጋር ሆነው “የቀደመውን እባብ” የሰይጣን ዲያብሎስን ጭንቅላት እንደሚቀጠቅጡ ተምረናል። (ራዕይ 14:1–4፤ 20:2፤ ሮሜ 16:20፤ ገላትያ 3:29፤ ኤፌሶን 3:4–6) ከአምላክ ቃል ላገኘናቸው ለእነዚህ ዕውቀቶች ከፍተኛ አድናቆት አለን።
ወደ አምላክ አስደናቂ ብርሃን መምጣት
11. መለኮታዊ ትምህርት ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ብርሃን በማምጣት ድል ያደርጋል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
11 መለኮታዊ ትምህርት ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ብርሃን በማምጣት ድል ያደርጋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1 ጴጥሮስ 2:9 ላይ የተገለጸው ተስፋ ተፈጽሞላቸዋል። “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከአምላክ የሚገኘው ብርሃን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” በርቶላቸዋል። (ራዕይ 7:9፤ ሉቃስ 23:43) አምላክ ለሕዝቡ በሚሰጠው ትምህርት ረገድ ምሳሌ 4:18 እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።” ተማሪዎች ሰዋስው፣ ታሪክ ወይም ሌላ ትምህርት በሚያጠኑበት ጊዜ ከመምህራቸው በሚያገኙት ጥሩ እርዳታ እየታገዙ በዕውቀት እንደሚያድጉ ሁሉ እኛም በዚህ እያደገና እየጨመረ በመጣው የትምህርት ሂደት ስለ መለኮታዊው ትምህርት ያለን ግንዛቤ የተጣራ ሆኖአል።
12, 13. መለኮታዊ ትምህርት የይሖዋን ሕዝቦች የጠበቀው ከየትኞቹ አደገኛ መሠረተ ትምህርቶች ነው?
12 ሌላው የመለኮታዊ ትምህርት ድል አድራጊነት ትምህርቱን በትሕትና የሚቀበሉትን ሰዎች ‘ከአጋንንት ትምህርት’ መጠበቁ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ሕዝበ ክርስትናን ከዚህ አንጻር እንመልከት። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አለቃ የነበሩት ጆን ሄንሪ ኒውማን በ1878 እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር፦ “የቤተ ክርስቲያን ገዥዎች ክርስትና ራሱን በክፋት ከመበከል ሊጠብቅና አጋንንታዊ የሆኑ የአምልኮ መሣሪያዎችን የወንጌላዊ አገልግሎት መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀም የሚያስችል ኃይል እንዳለው በማመን አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ነባራዊውን የብዙሐን ልማድና የምሁራን መደብ ፍልስፍና ለመቅዳትና ለመቀበል ዝግጁ ሆነዋል።” በተጨማሪም ኒውማን እንደ ጠበል፣ ልብሰ ተክህኖና ምስል የመሰሉት የአምልኮ መገልገያዎች “የቤተ ክርስቲያንን ተቀባይነት ያገኙና የቅድስና ክብር የተሰጣቸው ከአረማውያን የተወረሱ ናቸው” ብለዋል። መለኮታዊ ትምህርት፣ እንዲህ ካለው ክህደት ስለሚጠብቀንና በማንኛውም ዓይነት አጋንንታዊ አምልኮ ላይ የበላይነት ስላለው የአምላክ ሕዝቦች በጣም አመስጋኞች ናቸው።—ሥራ 19:20
13 መለኮታዊ ትምህርት ሃይማኖታዊ ስህተቶችን በማንኛውም መንገድ ድል ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ከአምላክ የተማርን በመሆናችን ይሖዋ የሁሉ የበላይ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነና መንፈስ ቅዱስ አንቀሳቃሽ የአምላክ ኃይል እንደሆነ እናምናለን እንጂ እንደ ሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች በሥላሴ አናምንም። ሲኦል የሰው ልጆች የጋራ መቃብር እንደሆነ ስለምንገነዘብ የሲኦል እሳትን አንፈራም። የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሰው ነፍስ የማትሞትና ዘላለማዊት ናት ቢሉም ሙታን አንዳች ነገር የማይሰማቸው እንደሆኑ እናውቃለን። በመለኮታዊ ትምህርት አማካኝነት ያወቅናቸውን ሌሎች ብዙ እውነቶች መዘርዘር እንችላለን። የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን እሥራት ነጻ መሆን ምንኛ ታላቅ በረከት ነው!—ዮሐንስ 8:31, 32፤ ራእይ 18:2, 4, 5
14. የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ብርሃን መመላለሳቸውን መቀጠል የሚችሉት ለምንድን ነው?
14 መለኮታዊ ትምህርት ሐሰተኛ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ድል ስለሚያደርግ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ብርሃን እየተመላለሱ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። ከዚህም የተነሣ “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” የሚለውን ቃል ከኋላቸው ይሰማሉ። (ኢሳይያስ 30:21) የአምላክ ትምህርት አገልጋዮቹን በተሳሳተ መንገድ ከማሰብ ይጠብቃቸዋል። “ሐሰተኛ ሐዋርያት” በጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር ማድረግ በጀመሩ ጊዜ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “የጦር መሣሪያዎቻችንም ምሽግ ለማፍረስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው እንጂ እንደ ዓለም የጦር መሣሪያዎች አይደሉም። በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ አሳብ እናፈርሳለን። አእምሮን ሁሉ እየማረክንም ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።” (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5፤ 11:13–15 የ1980 ትርጉም።) መለኮታዊውን ትምህርት የሚጻረሩ አስተሳሰቦች በጉባኤ ውስጥ በየዋህነት በሚሰጡ ትምህርቶችና በውጭ ላሉት ሰዎች በምናደርገው የስብከት ሥራ ይገለበጣሉ። —2 ጢሞቴዎስ 2:24–26
በእውነትና በመንፈስ ማምለክ
15, 16. ይሖዋን በመንፈስና በእውነት ማምለክ ምን ማለት ነው?
15 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ወደፊት እየገፋ በሄደ መጠን መለኮታዊው ትምህርት ቅን ሰዎች አምላክን ‘በመንፈስና በእውነት’ የሚያመልኩበትን መንገድ በማሳየት ድል ያደርጋል። ኢየሱስ በሲካር ከተማ አጠገብ ይገኝ በነበረው በያዕቆብ ጉድጓድ ላገኛት ሳምራዊት ሴት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ውሃ ሊሰጥ እንደሚችል ተናግሮ ነበር። ቀጥሎም ስለ ሳምራውያን ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “እናንተ ለማታውቁት አምላክ ትሰግዳላችሁ። . . . ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለእግዚአብሔር አብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እንዲያውም አሁን መጥቶአል። እግዚአብሔር አብም የሚፈልገው እንደዚህ የሚሰግዱለትን ነው።” (ዮሐንስ 4:7, 15, 21–23 የ1980 ትርጉም) ከዚያም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ገልጦ ተናገረ።
16 ይሁን እንጂ አምላክን በመንፈስ የምናመልከው እንዴት ነው? ልባችን በአምላክ ቃል ትክክለኛ ዕውቀት ላይ በተመሠረተ የአምላክ ፍቅር ተሞልቶ ንጹሕ አምልኮ በማቅረብ ነው። ሃይማኖታዊ ውሸቶችን በማስወገድና በታላቁ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠውን መለኮታዊ ፈቃድ በመፈጸም በእውነት ልናመልከው እንችላለን።
የሚያጋጥሙትን መከራዎችና ይህንን ዓለም ድል ያደርጋል
17. መለኮታዊ ትምህርት የይሖዋ አገልጋዮች መከራዎችንና ፈተናዎችን እንዲያሸንፉ እንደረዳቸው እንዴት ታረጋግጣለህ?
17 የአምላክ ሕዝቦች መከራና ስደት በሚደርስባቸው ጊዜም መለኮታዊው ትምህርት ድል አድራጊ መሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጧል። የሚከተለውን እንመልከት፦ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመስከረም ወር 1939 በፈነዳ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ታላቁን መጽሐፍ በተለየ ሁኔታ ማስተዋል አስፈልጓቸው ነበር። በዚህ ረገድ መለኮታዊው ትምህርት ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት የሚሰጠውን ዕውቀት ያብራራውና በህዳር 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው ጽሑፍ ከፍተኛ እርዳታ አበርክቷል። (ዮሐንስ 17:16) በተመሳሳይም በ1960ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ለመንግሥታዊ “የበላይ ባለ ሥልጣናት” በተወሰነ መጠን መገዛት አስፈላጊ ስለመሆኑ ያብራሩ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የአምላክ አገልጋዮች ማኅበረሰባዊ ዓመፆች እየተሰፋፉ በሄዱባቸው ዓመታት ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ አስችለዋቸዋል።—ሮሜ 13:1–7፤ ሥራ 5:29
18. በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች ወራዳ መዝናኛዎችን እንዴት ይመለከቷቸው ነበር? በዛሬው ጊዜ መለኮታዊ ትምህርት በዚህ ረገድ ምን እርዳታ አበርክቷል?
18 በተጨማሪም መለኮታዊ ትምህርት ወራዳ የሆኑ መዝናኛዎችን የመሰሉ መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈልግ የሚያባብለንን ፈተና ድል እንድንነሳ ይረዳናል። በሁለተኛውና ሦስተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን ነን ባዮች የተናገሩትን ልብ እንበል። ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ከሰርከስ ማሳያዎች እብደት፣ ከቲያትር ቤቶች ሐፍረተቢስነት፣ ከስፖርት መመልከቻዎች አረመኔነት ጋር የንግግር፣ የማየትም ሆነ የመስማት ተካፋይነት እንዲኖረን አንፈልግም።” ሌላው የዚያ ዘመን ጸሐፊ ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ጠይቋል፦ “አንድ ታማኝ ክርስቲያን ስለ ክፋት ከማሰብ እንኳን የሚርቅ ከሆነ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ምን ዓይነት ተካፋይነት ሊኖረው ይችላል? እንዴት ሴሰኝነትን በሚያሳዩ ነገሮች ሊደሰት ይችላል?” እነዚህ ጸሐፊዎች በሕይወት የኖሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሞተው ካለቁ በኋላ ቢሆንም ወራዳ የሆኑ መዝናኛዎችን አውግዘዋል። ዛሬም ቢሆን መለኮታዊው ጥበብ ብልግና፣ ሥነ ምግባራዊ ነውርና ዓመጽ ከሚታይባቸው የመዝናኛ ዓይነቶች እንድንርቅ የሚያስችለንን ጥበብ ይሰጠናል።
19. መለኮታዊ ትምህርት ዓለምን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
19 ከመለኮታዊ ትምህርት ጋር መስማማት ዓለምን ድል እንድናደርግ ያስችለናል። አዎ፣ የታላቁን መምህራችንን ትምህርት ሥራ ላይ ማዋል በሰይጣን ሥልጣን ሥር ከሚገኘው ከዚህ ዓለም የሚመጣውን ክፉ ተጽዕኖ እንድናሸንፍ ያስችለናል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ኤፌሶን 2:1–3 እንደዚህ አየር ሥልጣን ገዥ በምንመላለስበት ጊዜ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን የነበርን ብንሆንም አምላክ ሕያው አድርጎናል ይላል። መለኮታዊ ትምህርት ዓለማዊ ፍላጎቶችንና የእኛም ሆነ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ የሚወጣውን መንፈስ ድል እንድናደርግ ስለሚያስችለን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።
20. ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
20 ከዚህ ሁሉ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው መለኮታዊ ትምህርት በብዙ መንገዶች ድል ያደርጋል። እንዲያውም የሚያስገኛቸውን ድሎች በሙሉ መዘርዘር አይቻልም። በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ይነካል። ይሁን እንጂ ለአንተ በግልህ ምን እያደረገልህ ነው? መለኮታዊ ትምህርት ሕይወትህን እንዴት እየለወጠው ነው?
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
◻ እውነተኛ ጥበብ እንዴት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?
◻ አምላክ ዘፍጥረት 3:15ን በተመለከተ ምን እየጨመረ የሚሄድ ዕውቀት ገልጿል?
◻ መለኮታዊ ትምህርት በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ድል ያደረገው እንዴት ነው?
◻ አምላክን በመንፈስና በእውነት ማምለክ ምን ማለት ነው?
◻ መለኮታዊ ትምህርት የይሖዋ አገልጋዮች ያጋጠማቸውን መከራና ይህንን ዓለም እንዲያሸንፉ የረዳቸው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ማለትም የዘሩ ተረከዝ እስከ ቆሰለበት ጊዜ ድረስ ታማኝነቱን ጠብቋል