የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥር 2020
ከጥር 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 1-2
“ይሖዋ በምድር ላይ ሕያዋን ፍጥረታትን ፈጠረ”
(ዘፍጥረት 1:3, 4) አምላክም “ብርሃን ይሁን” አለ። ብርሃንም ሆነ። 4 ከዚህ በኋላ አምላክ ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ አምላክም ብርሃኑን ከጨለማው ለየ።
(ዘፍጥረት 1:6) ከዚያም አምላክ “በውኃዎቹ መካከል ጠፈር ይሁን፣ ውኃዎቹም ከውኃዎቹ ይከፈሉ” አለ።
(ዘፍጥረት 1:9) በመቀጠልም አምላክ “ከሰማያት በታች ያሉት ውኃዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰብሰቡና ደረቁ መሬት ይገለጥ” አለ። እንዳለውም ሆነ።
(ዘፍጥረት 1:11) ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ። እንዳለውም ሆነ።
it-1 527-528
ፍጥረት
አምላክ በአንደኛው ቀን ላይ “ብርሃን ይሁን” ሲል የብርሃኑ ምንጭ ከምድር ላይ ባይታይም ጨረሩ ደመናትን አልፎ ወደ ምድር መጥቶ መሆን አለበት። ይህ ቀስ በቀስ የተከናወነ ሂደት ይመስላል፤ ጄ ዋትስ የተባሉት ተርጓሚ ዘፍጥረት 1:3ን “ቀስ በቀስ ብርሃን ሆነ” በማለት መተርጎማቸው ይህን ይጠቁማል። (ኤ ዲስቲንክቲቭ ትራንስሌሽን ኦቭ ጀነሲስ) አምላክ ብርሃኑንና ጨለማውን በመለየት ብርሃኑን ‘ቀን’ ጨለማውን ደግሞ ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው። ይህም ምድር በራሷ ምሕዋር ላይ እየተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያ ትዞር እንደነበርና በዚህም ምክንያት በምሥራቃዊና በምዕራባዊ ንፍቀ ክበቦቿ ላይ ብርሃንና ጨለማ ይፈራረቅ እንደነበር ያሳያል።—ዘፍ 1:3, 4
በሁለተኛው ቀን ላይ አምላክ ‘ውኃዎቹን ከውኃዎቹ’ በመክፈል ጠፈርን ፈጠረ። የተወሰነው የውኃው ክፍል ምድር ላይ የቀረ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ደግሞ ከምድር ገጽ በጣም ከፍ እንዲል ተደረገ፤ በዚህ መንገድ በሁለቱ ውኃዎች መካከል ጠፈር ሊኖር ቻለ። አምላክ ጠፈሩን ‘ሰማይ’ ብሎ ጠራው። ሆኖም ይህ አገላለጽ የተሠራበት ከምድር አንጻር እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ጥቅሱ ከጠፈሩ በላይ ያሉት ውኃዎች ከዋክብትን ወይም ሌሎች የሰማይ አካላትን እንደሸፈኑ አይናገርም።—ዘፍ 1:6-8፤ ጠፈር የሚለውን ተመልከት።
በሦስተኛው ቀን ላይ የአምላክ ኃይል በምድር ላይ ያሉት ውኃዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡና ደረቁ መሬት እንዲገለጥ አደረገ፤ ከዚያም አምላክ ደረቁን መሬት የብስ አለው። አምላክ በዝግመተ ለውጥ ወይም በአጋጣሚ ሳይሆን ለቁስ አካላት ሕልውና በመስጠት ሣሮችን፣ ተክሎችንና ፍሬ የሚሰጡ ዛፎችን የፈጠረውም በዚሁ ቀን ነው። እነዚህ ሦስት ዋና ዋና ቡድኖች እያንዳንዳቸው “እንደየወገናቸው” የመባዛት ችሎታ ተሰጥቷቸዋል።—ዘፍ 1:9-13
(ዘፍጥረት 1:14) አምላክም እንዲህ አለ፦ “ቀኑና ሌሊቱ እንዲለይ በሰማያት ጠፈር ላይ ብርሃን ሰጪ አካላት ይኑሩ፤ እነሱም ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ።
(ዘፍጥረት 1:20) ከዚያም አምላክ “ውኃዎቹ በሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታት ይሞሉ፤ እንዲሁም የሚበርሩ ፍጥረታት ከምድር በላይ በሰማያት ጠፈር ላይ ይብረሩ” አለ።
(ዘፍጥረት 1:24) ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደየወገናቸው እንዲሁም የቤት እንስሳትን፣ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው ታውጣ” አለ። እንዳለውም ሆነ።
(ዘፍጥረት 1:27) አምላክም ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በአምላክ መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
it-1 528 አን. 5-8
ፍጥረት
በተጨማሪም በዘፍጥረት 1:16 ላይ “ፈጠረ” የሚል ትርጉም ያለው ባራ የሚለው የዕብራይስጥ ግስ ያልገባ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ከዚህ ይልቅ እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው “ሠራ” የሚል ትርጉም ያለው አሳህ የሚለው የዕብራይስጥ ግስ ነው። ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት በዘፍጥረት 1:1 ላይ በተጠቀሰው “ሰማያት” ውስጥ ስለሚካተቱ እነዚህ ነገሮች የተፈጠሩት በአራተኛው ቀን ሳይሆን ከዚያ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። አምላክ በአራተኛው ቀን ላይ እነዚህን ሰማያዊ አካላት ‘የሠራው’ ከምድርና ከበላይዋ ካለው ጠፈር ጋር በተያያዘ አዲስ ዓይነት ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ነው። “አምላክ በምድር ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ አስቀመጣቸው” የሚለው አገላለጽ እነዚህ አካላት ጠፈር ላይ ያሉ ያህል ከምድር ላይ መታየት እንደጀመሩ የሚጠቁም ነው። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ የብርሃን አካላት “ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ”፤ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ጠቋሚ በመሆን የሰው ልጆችን አገልግለዋል።—ዘፍ 1:14
የመጀመሪያዎቹ ሰው ያልሆኑ ሕያዋን ነፍሳት በምድር ላይ የተፈጠሩት በአምስተኛው ቀን ላይ ነው። አምላክ አንዱ ፍጡር በዝግመተ ለውጥ ወደ ሌሎች ፍጡራን እንዲቀየር አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ እንደሚለው የሚርመሰመሱ ወይም እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሕያዋን ነፍሳትን በአንድ ጊዜ ፈጥሯል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክም ግዙፍ የባሕር ፍጥረታትን እንዲሁም በውኃዎቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና የሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ እንደየወገናቸው ብሎም ክንፍ ያለውን እያንዳንዱን የሚበር ፍጥረት እንደየወገኑ ፈጠረ።” አምላክ በፈጠረው ነገር ደስ ስለተሰኘ ፍጥረታቱን “ብዙ ተባዙ” በማለት ባረካቸው፤ ደግሞም የተለያየ ዝርያ ያላቸው እነዚህ ፍጥረታት “እንደየወገናቸው” የመራባት ችሎታ ስለተሰጣቸው መባዛት ይችላሉ።—ዘፍ 1:20-23
በስድስተኛው ቀን ላይ አምላክ “በምድር ላይ ያሉ የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳትን እንደየወገናቸው እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ ፍጥረታትን ሁሉ እንደየወገናቸው ሠራ።” ይህ ሥራውም እንደ ሌሎቹ የፍጥረት ሥራዎቹ ሁሉ መልካም ነበር።—ዘፍ 1:24, 25
በስድስተኛው የፍጥረት ቀን መገባደጃ አካባቢ አምላክ ከእንስሳት የላቀ ከመላእክት ግን ያነሰ ፈጽሞ የተለየ ፍጡር ፈጠረ። ይህ ፍጡር በአምላክ መልክና አምሳያ የተፈጠረው ሰው ነው። ዘፍጥረት 1:27 የሰው ዘርን አስመልክቶ “[አምላክ] ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በማለት ጠቅለል አድርጎ ቢናገርም በዘፍጥረት 2:7-9 ላይ ያለው ተመሳሳይ ዘገባ ይሖዋ አምላክ ሰውን ከምድር አፈር እንደሠራውና በአፍንጫው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ እንዳለበት ከዚያም ሰውየው ሕያው ነፍስ እንደሆነ ይናገራል፤ ይህ ፍጡር ምግብና ገነት የሆነች መኖሪያ ተዘጋጅቶለት ነበር። ይሖዋ የምድርን ንጥረ ነገሮች ተጠቅሞ ሰውየውን የፈጠረ ሲሆን ሴቲቱን ለመፍጠር ደግሞ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዷን ተጠቅሟል። (ዘፍ 2:18-25) ሴቲቱ ስትፈጠር ሰው የተሟላ ‘ወገን’ ሆነ።—ዘፍ 5:1, 2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 1:1) በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።
ሳይንስ በሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
የምድርና የጽንፈ ዓለም ዕድሜ
የሳይንስ ሊቃውንት ምድር የ4 ቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳላትና ጽንፈ ዓለም ደግሞ ወደ ሕልውና የመጣው ከ13 እስከ 14 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እንደሆነ ይገምታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጽንፈ ዓለም የተፈጠረበትን ጊዜ አይናገርም። እንዲሁም ምድር የተፈጠረችው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነ አይናገርም። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ራሱ “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) ይህ ጠቅለል ያለ አነጋገር የሳይንስ ሊቃውንት በትክክለኛ ሳይንሳዊ ሕግጋት ላይ ተመርኩዘው የግዑዙን ዓለም ዕድሜ ማስላት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።
(ዘፍጥረት 1:26) ከዚያም አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ፤ እሱም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማያት ላይ በሚበርሩ ፍጥረታት፣ በቤት እንስሳትና በምድር ሁሉ እንዲሁም በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑረው” አለ።
it-2 52
ኢየሱስ ክርስቶስ
ረዳት ፈጣሪ አይደለም። ወልድ ከአብ ጋር በፍጥረት ሥራ መካፈሉ ረዳት ፈጣሪ አያሰኘውም። የፍጥረት ሥራው የተከናወነው ከአምላክ በተገኘ ኃይል ማለትም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (ዘፍ 1:2፤ መዝ 33:6) ደግሞም ይሖዋ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሚታዩትም ሆኑ የማይታዩት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ሕይወት ያገኙት ከእሱ ነው። (መዝ 36:9) እንግዲያው ወልድ ረዳት ፈጣሪ ሳይሆን ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ሥራውን ለማከናወን የተጠቀመበት ወኪል ወይም መሣሪያ ነው። ኢየሱስ ራሱም ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነ ተናግሯል፤ ቅዱሳን መጻሕፍትም ይህንኑ ሐሳብ ይደግፋሉ።—ማቴ 19:4-6፤ ፍጥረት የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 1:1-19) በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። 2 ምድርም ቅርጽ አልባና ባድማ ነበረች፤ ጥልቁም ውኃ በጨለማ ተሸፍኖ ነበር፤ የአምላክም ኃይል በውኃው ላይ ይንቀሳቀስ ነበር። 3 አምላክም “ብርሃን ይሁን” አለ። ብርሃንም ሆነ። 4 ከዚህ በኋላ አምላክ ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ አምላክም ብርሃኑን ከጨለማው ለየ። 5 አምላክም ብርሃኑን ‘ቀን’ ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ግን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን። 6 ከዚያም አምላክ “በውኃዎቹ መካከል ጠፈር ይሁን፣ ውኃዎቹም ከውኃዎቹ ይከፈሉ” አለ። 7 ከዚያም አምላክ ጠፈርን ሠራ፤ ከጠፈሩ በታች ያሉትንም ውኃዎች ከጠፈሩ በላይ ካሉት ውኃዎች ለየ። እንዳለውም ሆነ። 8 አምላክ ጠፈሩን ‘ሰማይ’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን። 9 በመቀጠልም አምላክ “ከሰማያት በታች ያሉት ውኃዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰብሰቡና ደረቁ መሬት ይገለጥ” አለ። እንዳለውም ሆነ። 10 አምላክ ደረቁን መሬት ‘የብስ’ ብሎ ጠራው፤ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ውኃዎች ግን ‘ባሕር’ ብሎ ጠራቸው። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 11 ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ። እንዳለውም ሆነ። 12 ምድርም ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ማብቀል ጀመረች። ከዚያም አምላክ ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 13 መሸ፣ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን። 14 አምላክም እንዲህ አለ፦ “ቀኑና ሌሊቱ እንዲለይ በሰማያት ጠፈር ላይ ብርሃን ሰጪ አካላት ይኑሩ፤ እነሱም ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ። 15 በምድርም ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ ያሉ ብርሃን ሰጪ አካላት ሆነው ያገለግላሉ።” እንዳለውም ሆነ። 16 አምላክም ሁለቱን ታላላቅ ብርሃን ሰጪ አካላት ሠራ፤ ታላቁ ብርሃን ሰጪ አካል በቀን እንዲያይል፣ ታናሹ ብርሃን ሰጪ አካል ደግሞ በሌሊት እንዲያይል አደረገ፤ ከዋክብትንም ሠራ። 17 በዚህ መንገድ አምላክ በምድር ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ አስቀመጣቸው፤ 18 በተጨማሪም በቀንና በሌሊት እንዲያይሉ እንዲሁም ብርሃኑን ከጨለማው እንዲለዩ አደረገ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 19 መሸ፣ ነጋም፤ አራተኛ ቀን።
ከጥር 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 3-5
“የመጀመሪያው ውሸት ያስከተለው አስከፊ መዘዝ”
(ዘፍጥረት 3:1-5) እባብም ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት። 2 በዚህ ጊዜ ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን። 3 ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” 4 በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። 5 አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።”
የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!
9 ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በማታለል በሰማዩ አባቷ በይሖዋ ላይ እንድታምፅ አደረጋት። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ፤ ራእይ 12:9) ሰይጣን የአምላክ ሰብዓዊ ልጆች “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ” መብላት የማይችሉ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ጥያቄ አነሳ። ሰይጣን ‘የምትፈልጉትን ነገር ማድረግ አትችሉም ማለት ነው?’ ያለ ያህል ነበር። ከዚያም “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” በማለት ዓይን ያወጣ ውሸት ተናገረ። ቀጥሎም “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡ . . . ስለሚያውቅ ነው” በማለት ሔዋን አምላክን መታዘዝ እንደማያስፈልጋት ሊያሳምናት ሞከረ። ሰይጣን እንዲህ ሲል፣ ይሖዋ ከፍሬው እንዳይበሉ ያዘዛቸው ልዩ እውቀት እንዳያገኙ ብሎ እንደሆነ አድርጎ መናገሩ ነበር። በተጨማሪም ፍሬውን ቢበሉ “መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ” እንደሚሆኑ በመግለጽ የሐሰት ተስፋ ሰጣቸው።
(ዘፍጥረት 3:6) በዚህም የተነሳ ሴቲቱ ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች፤ ዛፉ ለዓይን የሚማርክ ነበር። ስለሆነም ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች። ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።
ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት መማር እንችላለን
ሔዋን ኃጢአት ከመሥራት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራትም ማለት ነውን? በፍጹም! ራስህን በእሷ ቦታ አስቀምጠህ ሁኔታውን ለማየት ሞክር። እባቡ የነገራት ነገር አምላክና አዳም ከነገሯት ፍጹም ተቃራኒ ነበር። አንድ የማታውቀው ግለሰብ፣ የምትወድደውንና የምታምነውን ሰው በእምነት ማጉደል ቢወነጅለው ምን ይሰማሃል? ሔዋን የሰማችውን ነገር በመጸየፍና ቁጣዋን በመግለጽ አልፎ ተርፎም ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆን የተለየ ምላሽ መስጠት ነበረባት። ደግሞስ እባቡ ማንሆነና ነው የአምላክን ጽድቅና ባልዋ የነገራትን ነገር አጠያያቂ የሚያደርገው? ሔዋን ለራስነት መሠረታዊ ሥርዓት አክብሮት በማሳየት ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከማድረጓ በፊት ምክር መጠየቅ ነበረባት። እኛም አምላክ ካወጣው መመሪያ ጋር የሚቃረን መረጃ ከደረሰን እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አለብን። ሆኖም ሔዋን መልካሙንና ክፉውን ራስዋ ለመወሰን በመፈለጓ ፈታኙ የነገራትን ቃል አመነች። በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ባውጠነጠነች መጠን የዚያኑ ያህል ማራኪ ሆኖ ታያት። መጥፎውን ምኞት ከአእምሮዋ ከማውጣት አሊያም ከቤተሰቧ ራስ ጋር በጉዳዩ ላይ ከመወያየት ይልቅ ጉዳዩን በአእምሮዋ በማጉላላቷ ትልቅ ስህተት ላይ ወደቀች!—1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ያዕቆብ 1:14, 15
አዳም የሚስቱን ቃል ሰማ
ሔዋን ብዙም ሳይቆይ አዳም በኃጢአቷ እንዲተባበራት አግባባችው። አዳም በቀላሉ እጅ መስጠቱን በተመለከተ ምን ማለት እንችላለን? (ዘፍጥረት 3:6, 17) አዳም ለማን ታማኝ እንደሚሆን ግራ ተጋብቶ ነበር። ተወዳጅ የትዳር ጓደኛው የሆነችውን ሔዋንን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለሰጠው ለፈጣሪው ይታዘዝ ይሆን? አዳም በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ለማወቅ ከአምላክ መመሪያ ይጠይቅ ይሆን? ወይስ ከሚስቱ ጋር በኃጢአቷ ለመተባበር ይወስናል? አዳም ሚስቱ የተከለከለውን ፍሬ በመብላት ለማግኘት የተመኘችው ነገር ሊሆን የማይችል ነገር መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የተታለለም አዳም አይደለም፣ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች።” (1 ጢሞቴዎስ 2:14) በመሆኑም አዳም ሆነ ብሎ ይሖዋን ለመቃወም መረጠ። ከሚስቱ የሚለያይ መሆኑ ያሳደረበት ስጋት አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ባለው ችሎታ ላይ ካለው እምነት የላቀ እንደነበር ግልጽ ነው።
(ዘፍጥረት 3:15-19) በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።” 16 ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል፤ ምኞትሽ ሁሉ ባልሽ ይሆናል፤ እሱ ደግሞ ይገዛሻል።” 17 አዳምንም እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ስለሰማህና ‘ከእሱ አትብላ’ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ ወስደህ ስለበላህ በአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የምድርን ፍሬ በሥቃይ ትበላለህ። 18 ምድርም እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ አንተም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል ትበላለህ። 19 ከመሬት ስለተገኘህ ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ ላብህን እያንጠፈጠፍክ ምግብ ትበላለህ። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።”
አምላክ በእርግጥ ለሴቶች ያስብላቸዋል?
አምላክ ሴቶችን ረግሟቸዋል?
አልረገማቸውም። አምላክ የረገመው ‘ዲያብሎስ ተብሎ የሚጠራውን የመጀመሪያውን እባብ’ እንጂ ሴቶችን አይደለም። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:14) አምላክ፣ አዳም በሚስቱ ላይ “የበላይ” እንደሚሆን ሲናገር ወንዶች ሴቶችን እንዲጨቁኑ መፍቀዱ አልነበረም። (ዘፍጥረት 3:16) ከዚህ ይልቅ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት መሥራታቸው የሚያስከትለውን አሳዛኝ መዘዝ መተንበዩ ነበር።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
3:17—ምድር የተረገመችው እንዴት ነበር? እርግማኑ የቆየውስ ለምን ያህል ጊዜ ነው? ምድር መረገሟ ከዚያ በኋላ ለማልማት አስቸጋሪ እንደምትሆን ያመለክታል። ምድር ከተረገመች በኋላ እሾህና አሜከላ የምታበቅል መሆኗ ለአዳም ዘሮች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ አስከትሎባቸው ስለነበር የኖኅ አባት ላሜህ ‘እግዚአብሔር በረገማት ምድር ልፋታችንና የጉልበታችን ድካም’ በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 5:29 አ.መ.ት) ከጥፋት ውኃው በኋላ ይሖዋ ኖኅና ልጆቹን የባረካቸው ከመሆኑም በላይ ምድር በሰው ዘር እንድትሞላ ያለውን ዓላማ ገልጾላቸዋል። (ዘፍጥረት 9:1) በመሆኑም አምላክ በምድር ላይ የተናገረው እርግማን የተነሳ ይመስላል።—ዘፍጥረት 13:10
it-2 186
ምጥ
ልጅ ከመውለድ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሥቃይ። የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን ኃጢአት ከሠራች በኋላ አምላክ ይህ ድርጊቷ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ ምን መዘዝ እንደሚያስከትልባት ነግሯታል። ታዛዥ ሆና ብትቀጥል ኖሮ የአምላክ በረከት ስለማይለያት ልጅ መውለድ አንዳች ሐዘን ያልታከለበት አስደሳች ነገር ይሆንላት ነበር፤ ምክንያቱም “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም።” (ምሳሌ 10:22) አሁን ግን የሰው ልጆች አካል ፍጹም በሆነ መንገድ ስለማይሠራ በጥቅሉ ሲታይ ልጅ መውለድ ሥቃይ የሚያስከትል ነገር ሆኗል። በመሆኑም አምላክ እንዲህ ብሏል (ደግሞም አምላክ፣ እንዲሆኑ የፈቀዳቸውን ነገሮች እሱ እንዳደረጋቸው አድርጎ የተናገረባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ)፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል።”—ዘፍ 3:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 4:23, 24) ከዚያም ላሜህ ለሚስቶቹ ለአዳና ለጺላ የሚከተለውን ተቀኘ፦ “እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤ የምላችሁንም አዳምጡ፦ አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣ አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት። 24 ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት የሚደርስበት ከሆነ ላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።”
it-2 192 አን. 5
ላሜህ
ላሜህ ለሚስቶቹ የገጠመው ግጥም (ዘፍ 4:23, 24) በዚያን ጊዜ የነበረውን የዓመፅ መንፈስ ያንጸባርቃል። ግጥሙ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤ የምላችሁንም አዳምጡ፦ አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣ አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት። ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት የሚደርስበት ከሆነ ላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።” ላሜህ፣ ነፍስ ያጠፋው እንደ ቃየን ሆን ብሎ እንዳልሆነ በመግለጽ የመከላከያ ሐሳብ እያቀረበ ያለ ይመስላል። ላሜህ፣ ሰውየው ስለመታውና ስላቆሰለው ራሱን ለመከላከል ሲል እንደገደለው ተናግሯል። በመሆኑም ግጥሙ የሟቹን ደም ለመበቀል የሚፈልግ ሰው ጥቃት እንዳያደርስበት የቀረበ ልመና ነው።
(ዘፍጥረት 4:26) ሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያን ዘመን ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ።
it-1 338 አን. 2
ስድብ
ከጥፋት ውሃ በፊት በነበረው የሄኖስ ዘመን የተጀመረው “የይሖዋን ስም መጥራት” ትክክለኛና ቀና ባሕርይ ያለው ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ከዚያ በፊት አቤል አምላክን በመለኮታዊ ስሙ ሲጠራ እንደቆየ ጥርጥር የለውም። (ዘፍ 4:26፤ ዕብ 11:4) አንዳንድ ምሁራን እንደሚያምኑት እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአምላክን ስም መጥራት፣ የይሖዋን ስም ለሰዎች ወይም ለጣዖታት በመስጠት የአምላክን ስም ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን የሚያመለክት ከሆነ ድርጊቱ ስድብ ይሆናል።—ሄኖስ የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 4:17–5:8) ከዚህ በኋላ ቃየን ከሚስቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች፤ ሄኖክንም ወለደች። ከዚያም ቃየን ከተማ መገንባት ጀመረ፤ ከተማዋንም በልጁ በሄኖክ ስም ሰየማት። 18 ከጊዜ በኋላም ሄኖክ ኢራድን ወለደ። ኢራድም መሁያኤልን ወለደ፤ መሁያኤልም መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤል ደግሞ ላሜህን ወለደ። 19 ላሜህም ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የመጀመሪያዋ ስም አዳ ሲሆን የሁለተኛዋ ስም ደግሞ ጺላ ነበር። 20 አዳ ያባልን ወለደች። ያባል በድንኳን የሚኖሩና ከብት የሚያረቡ ሰዎች አባት ነበር። 21 የወንድሙ ስም ዩባል ነበር። እሱም የበገና ደርዳሪዎችና የእምቢልታ ነፊዎች አባት ነበር። 22 ጺላ ደግሞ ቱባልቃይንን ወለደች፤ እሱም መዳብና ብረት እየቀጠቀጠ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይሠራ ነበር። የቱባልቃይን እህት ናዕማ ትባል ነበር። 23 ከዚያም ላሜህ ለሚስቶቹ ለአዳና ለጺላ የሚከተለውን ተቀኘ፦ “እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤ የምላችሁንም አዳምጡ፦ አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣ አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት። 24 ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት የሚደርስበት ከሆነ ላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።” 25 አዳም ከሚስቱ ጋር በድጋሚ የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም “ቃየን አቤልን ስለገደለው በእሱ ፋንታ አምላክ ሌላ ዘር ተክቶልኛል” በማለት ሴት አለችው። 26 ሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያን ዘመን ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ።
5 የአዳምን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ይህ ነው። አምላክ አዳምን በፈጠረበት ቀን፣ በአምላክ አምሳል ሠራው። 2 ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። በተፈጠሩበትም ቀን ባረካቸው፤ እንዲሁም ሰው ብሎ ጠራቸው። 3 አዳም 130 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም እሱን የሚመስል ወንድ ልጅ በራሱ አምሳያ ወለደ፤ ስሙንም ሴት አለው። 4 አዳም ሴትን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 5 ስለዚህ አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ። 6 ሴት 105 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሄኖስን ወለደ። 7 ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ 807 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 8 ስለዚህ ሴት በአጠቃላይ 912 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ከጥር 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 6-8
“ልክ እንደዚሁ አደረገ”
(ዘፍጥረት 6:9) የኖኅ ታሪክ ይህ ነው። ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።
(ዘፍጥረት 6:13) ከዚህ በኋላ አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ስለሆነም እነሱን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።”
ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉትን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ተከተሉ
4 ኖኅ ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች። የኖኅ ቅድመ አያት በሆነው በሄኖክ ዘመን የነበሩት ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ነበሩ። ሌላው ቀርቶ በይሖዋ ላይ “ክፉ ቃል” ይናገሩ ነበር። (ይሁዳ 14, 15) ዓመፅ ከዕለት ወደ ዕለት እየተስፋፋ ነበር። እንዲያውም በኖኅ ዘመን ምድር “በዓመፅ ተሞልታ ነበር።” ክፉ መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር በመምጣት የሰውን ሴቶች ልጆች ያገቡ ሲሆን ጨካኝ የሆኑ የሰውና የመላእክት ዲቃላዎችን ወለዱ። (ዘፍ. 6:2-4, 11, 12) ኖኅ ግን በዘመኑ ካሉት ሰዎች የተለየ አቋም ነበረው። “በይሖዋ ፊት ሞገስ [ያገኘ]” ከመሆኑም ሌላ “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።”—ዘፍ. 6:8, 9
(ዘፍጥረት 6:14-16) አንተ ከጎፈር እንጨት ለራስህ መርከብ ሥራ። በመርከቡም ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ፤ እንዲሁም መርከቡን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን ለቅልቀው። 15 መርከቡንም የምትሠራው እንደሚከተለው ነው፦ የመርከቡ ርዝመት 300 ክንድ፣ ወርዱ 50 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 30 ክንድ ይሁን። 16 በመርከቡም ላይ ከጣሪያው ሥር አንድ ክንድ ቁመት ያለው ብርሃን ማስገቢያ የሚሆን መስኮት ሥራ፤ የመርከቡንም በር በጎኑ በኩል አድርግ፤ መርከቡም ምድር ቤት እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ይኑረው።
“ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር”
የመርከቡ ሥራ በርካታ አሥርተ ዓመታትን ምናልባትም ከ40 እስከ 50 ዓመት የሚፈጅ ነበር። ሥራው ዛፍ መቁረጥን እንዲሁም ግንዱን ማጓጓዝን፣ መሰንጠቅን፣ መጥረብንና ማገጣጠምን ይጠይቃል። መርከቡ ባለ ሁለት ፎቅ ወይም ደርብ ሲሆን በርካታ ክፍሎች እንዲሁም በጎን በኩል በር ያስፈልገው ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው መርከቡ ጣሪያው ሥር መስኮቶች ያሉት ሲሆን ውኃ በቀላሉ እንዲወርድ ለማስቻል ጣሪያው አሞራ ክንፍ ተደርጎ የተሠራ ነው።—ዘፍጥረት 6:14-16
(ዘፍጥረት 6:22) ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ።
ሩጫውን በጽናት ሩጡ
13 እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ጸንተው ውድድሩን ለማጠናቀቅ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ጳውሎስ ስለ ኖኅ የጻፈውን ሐሳብ ልብ በል። (ዕብራውያን 11:7ን አንብብ።) ‘ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ የሚያጠፋው የጥፋት ውሃ’ ኖኅ ከዚያ ቀድሞ ‘ያላየው’ ነገር ነበር። (ዘፍ. 6:17) የጥፋት ውሃው ከዚያ በፊት ፈጽሞ ታይቶ የማያውቅ እንግዳ ነገር ነበር። ያም ሆኖ ኖኅ እንዲህ ያለው ነገር የማይመስል እንዲያውም ጨርሶ ሊሆን የማይችል እንደሆነ አድርጎ አላሰበም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ እንደሚፈጽም እምነት ነበረው። ኖኅ እንዲሠራ የተጠየቀው ነገር በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ልክ አምላክ ‘እንዳዘዘው አድርጓል።’ (ዘፍ. 6:22) ኖኅ መርከብ መሥራት፣ እንስሳቱን መሰብሰብ፣ ለሰዎችና ለእንስሳት የሚሆን ምግብ በመርከቡ ውስጥ ማከማቸት፣ የማስጠንቀቂያ መልእክት መስበክ እንዲሁም የቤተሰቡን መንፈሳዊነት መጠበቅ እንደነበረበት ስናስብ ሁሉን ነገር ልክ አምላክ ‘እንዳዘዘው ማድረግ’ ቀላል እንዳልነበረ መረዳት አያዳግትም። ያም ሆኖ ኖኅ እምነትና ጽናት ማሳየቱ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት ለማትረፍና በረከት ለማግኘት አስችሎታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 7:2) ከአንተም ጋር ንጹሕ ከሆነው ከእያንዳንዱ እንስሳ ሰባት ሰባት ትወስዳለህ፤ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ ንጹሕ ካልሆነው ከእያንዳንዱ እንስሳ ደግሞ ሁለት ሁለት ውሰድ፤ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
7:2—ንጹህ የሆኑና ያልሆኑ እንስሳትን ለመለየት የተሠራበት መሥፈርት ምንድን ነው? ንጹህ በሆኑና ባልሆኑ እንስሳት መካከል ልዩነት የተደረገው በአምልኮ ለመሥዋዕትነት ለሚቀርቡ እንስሳት እንጂ የሚበሉትንና የማይበሉትን እንስሳት ለመለየት አይደለም። ከጥፋት ውኃው በፊት ሰዎች የእንስሳት ሥጋ አይበሉም ነበር። ከምግብ ጋር በተያያዘ “ንጹህ” እና “ርኩስ” የሚለው ልዩነት የመጣው የሙሴ ሕግ ከተሰጠ በኋላ ሲሆን ሕጉ ሲወገድ ይህ ትእዛዝም ቀርቷል። (የሐዋርያት ሥራ 10:9-16፤ ኤፌሶን 2:15) ኖኅ ለይሖዋ አምልኮ ተስማሚ የሚሆኑትን እንስሳት ያውቅ የነበረ ይመስላል። ልክ ከመርከቡ እንደወጣ “ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፣ ከንጹህም እንስሳ ሁሉ ከንጹሃን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፣ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።”—ዘፍጥረት 8:20
(ዘፍጥረት 7:11) ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር ከወሩም በ17ኛው ቀን፣ በዚያ ቀን፣ ተንጣሎ የሚገኘው ጥልቅ ውኃ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማያት የውኃ በሮችም ተከፈቱ።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
7:11—ዓለምን ያጥለቀለቀው ውኃ ከየት መጣ? በምድር ዙሪያ ያለው “ጠፈር” በተፈጠረበት በሁለተኛው የፍጥረት “ቀን” ውኃ “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ” ይገኝ ነበር። (ዘፍጥረት 1:6, 7) “ከጠፈር በታች” ያለው ውኃ በምድር ላይ የነበረው ነው። “ከጠፈር በላይ” የሆነው ውኃ ከምድር በላይ የተንጠለጠለ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት አዘል አየር ሲሆን ይህም ‘ታላቅ ቀላይ’ ተብሏል። በኖኅ ዘመን ይህ ውኃ በምድር ላይ ዘነበ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 6:1-16) ሰዎች በምድር ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ሴቶች ልጆችን ወለዱ፤ 2 የእውነተኛው አምላክ ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ። በመሆኑም የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። 3 ከዚያም ይሖዋ “ሰው ሥጋ ስለሆነ መንፈሴ ሰውን ለዘላለም አይታገሥም። በመሆኑም ዘመኑ 120 ዓመት ይሆናል” አለ። 4 በዚያ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ኔፍሊም በምድር ላይ ነበሩ። በዚያ ጊዜም የእውነተኛው አምላክ ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ግንኙነት ፈጸሙ፤ ሴቶቹም ወንዶች ልጆችን ወለዱላቸው። እነሱም በጥንት ዘመን በኃያልነታቸው ዝና ያተረፉ ሰዎች ነበሩ። 5 በዚህም የተነሳ ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ እንደሆነ ተመለከተ። 6 ይሖዋም ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም አዘነ። 7 በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “የፈጠርኳቸውን ሰዎች ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ ሰውን ጨምሮ የቤት እንስሳትን እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትን አጠፋለሁ፤ ምክንያቱም እነሱን በመፍጠሬ ተጸጽቻለሁ።” 8 ኖኅ ግን በይሖዋ ፊት ሞገስ አገኘ። 9 የኖኅ ታሪክ ይህ ነው። ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር። 10 ኖኅ ከጊዜ በኋላ ሴም፣ ካምና ያፌት የተባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11 ይሁንና ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። 12 አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤ ሰው ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር። 13 ከዚህ በኋላ አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ስለሆነም እነሱን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። 14 አንተ ከጎፈር እንጨት ለራስህ መርከብ ሥራ። በመርከቡም ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ፤ እንዲሁም መርከቡን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን ለቅልቀው። 15 መርከቡንም የምትሠራው እንደሚከተለው ነው፦ የመርከቡ ርዝመት 300 ክንድ፣ ወርዱ 50 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 30 ክንድ ይሁን። 16 በመርከቡም ላይ ከጣሪያው ሥር አንድ ክንድ ቁመት ያለው ብርሃን ማስገቢያ የሚሆን መስኮት ሥራ፤ የመርከቡንም በር በጎኑ በኩል አድርግ፤ መርከቡም ምድር ቤት እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ይኑረው።
ከጥር 27–የካቲት 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 9-11
“ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋ . . . ትጠቀም ነበር”
(ዘፍጥረት 11:1-4) በዚህ ጊዜ፣ ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ቃላት ትጠቀም ነበር። 2 ወደ ምሥራቅ ሲጓዙም በሰናኦር ምድር ወደሚገኝ አንድ ሸለቋማ ሜዳ ደረሱ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ። 3 እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ በእሳትም እንተኩሰው” ይባባሉ ጀመር። በመሆኑም በድንጋይ ፋንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ። 4 ከዚያም “ኑ! በመላው ምድር ላይ እንዳንበተን ከተማና ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንገንባ፤ ስማችንንም እናስጠራ” ተባባሉ።
it-1 239
ታላቂቱ ባቢሎን
የጥንቷ ባቢሎን ገጽታዎች። በሰናኦር ሜዳ የምትገኘው የባቢሎን ከተማ የተመሠረተችው የባቤልን ግንብ ለመገንባት ሙከራ በተደረገበት ጊዜ ነው። (ዘፍ 11:2-9) በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ግንቡንና ከተማዋን ለመገንባት የተነሳሱበት ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ስም ለማስከበር ሳይሆን የራሳቸውን ‘ስም ለማስጠራት’ ነበር። በጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሾች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሜሶጶጣሚያ ባሉ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በቁፋሮ የተገኙት የዚጉራት ግንቦች የቀድሞው ግንብ፣ ንድፉ ወይም ቅርጹ ምንም ይሁን ምን፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ እንደነበር የሚያረጋግጡ ይመስላል። ይሖዋ አምላክ የቤተ መቅደሱን ግንባታ በማክሸፍ አፋጣኝ እርምጃ መውሰዱ ግንባታው ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ተያያዥነት እንዳለው በግልጽ ያሳያል። ለከተማዋ የተሰጣት ባቤል የሚለው የዕብራይስጥ ስም “ዝብርቅ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በሱሜሪያ ቋንቋ (ካዲንጊራ) እና በአካድ ቋንቋ (ባቢሉ) የተሰጧት ስሞች ግን ሁለቱም “የአምላክ በር” የሚል ትርጉም አላቸው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ቀሪዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ስሙ ከያዘው ኩነኔ አዘል ትርጉም ለመሸሽ ሲሉ ቃሉን ትንሽ ለወጥ አድርገውት ነበር፤ ሆኖም አዲሱ ወይም የቀድሞውን ተክቶ የመጣው ስምም ቢሆን ከተማዋን ከሃይማኖት ጋር ያያይዛት ነበር።
it-2 202 አን. 2
ቋንቋ
የዘፍጥረት ዘገባ ከጥፋት ውኃው በኋላ ከኖሩት ሰዎች መካከል የተወሰኑት አንድ ላይ በማበር አምላክ ለኖኅና ለልጆቹ የገለጠውን ፈቃድ የሚቃወም ዕቅድ እንዳወጡ ይናገራል። (ዘፍ 9:1) ወደተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ‘ምድርን ከመሙላት’ ይልቅ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ በሜሶጶጣሚያ በሚገኝ ሰናኦር ሜዳ ተብሎ የሚታወቅ ቦታ ላይ ብቻ ተወስኖ በአንድ አካባቢ እንዲኖር ፈልገው ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው በዚህ ሥፍራ ሃይማኖታዊ አገልግሎት የሚሰጥ ግንብ ገንብተው ቦታውን ሃይማኖታዊ ማዕከል ማድረግም አስበው ነበር።—ዘፍ 11:2-4
(ዘፍጥረት 11:6-8) ይሖዋም እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ ናቸው፤ ይኸው አሁን ደግሞ ይህን መሥራት ጀምረዋል። በዚህ ከቀጠሉ ያሰቡትን ሁሉ ከማከናወን የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም። 7 ና! እንውረድና በቋንቋ እርስ በርስ እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እናዘበራርቅ።” 8 በመሆኑም ይሖዋ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አደረገ፤ እነሱም ቀስ በቀስ ከተማዋን መገንባታቸውን አቆሙ።
it-2 202 አን. 3
ቋንቋ
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የጋራ መግባቢያ ቋንቋቸውን በማዘበራረቅ ትዕቢት የተንጸባረቀበት ዕቅዳቸውን አከሸፈባቸው። እርስ በርስ መግባባት አለመቻላቸው በአንድነት መሥራት እንዲያቅታቸው ያደረገ ሲሆን ይህም በመላዋ ምድር እንዲበታተኑ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ቋንቋቸው መዘበራረቁ ወደፊት አምላክን ተቃውመው በተቃራኒ አቅጣጫ ለመሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ሊገታው ወይም ወደኋላ ሊያስቀረው ይችላል፤ ምክንያቱም ሰዎች በቋንቋ መግባባት አለመቻላቸው፣ የጠነሰሱትን አንድ ዓይነት ሴራ ዳር ለማድረስ አእምሯዊም ሆነ አካላዊ ችሎታቸውን ማቀናጀት ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም የቋንቋ ቡድኖቹ ከአምላክ ያገኙትን ሳይሆን በተሞክሮ ወይም በምርምር የደረሱበትን እውቀት አንድ ላይ አጣምረው ጥቅም ላይ ማዋል እንዳይችሉ እንቅፋት ይፈጥራል። (ከመክ 7:29 እና ዘዳ 32:5 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም የቋንቋ መዘበራረቅ ትልቅ ክፍፍል የፈጠረ ቢሆንም ሰዎች ጎጂና አደገኛ የሆኑ ግቦችን ዳር ማድረስ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው በማድረግ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል። (ዘፍ 11:5-9፤ ከኢሳ 8:9, 10 ጋር አወዳድር።) አምላክ በባቤል የተደረገውን ሙከራ በቸልታ ቢያልፈው ኖሮ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚፈጠር ለመረዳት የሰው ዘር፣ ያካበተውን እውቀት ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀሙ በዘመናችን የተከሰቱትን ችግሮች ማሰቡ ብቻ በቂ ነው።
(ዘፍጥረት 11:9) የከተማዋ ስም ባቤል የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በዚያ የምድርን ሁሉ ቋንቋ አዘበራርቋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሰዎቹ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አድርጓል።
it-2 472
ብሔራት
የሰው ዘር በቋንቋ ከተከፋፈለ በኋላ እያንዳንዱ የቋንቋ ቡድን የራሱን ሃይማኖት፣ የራሱን ባሕል፣ የራሱን ሥነ ጥበብና የራሱን ልማድ በማዳበር፣ ነገሮችን በራሱ መንገድ ማከናወን ጀመረ። (ዘሌ 18:3) ከአምላክ የራቁት እነዚህ ቡድኖች በየፊናቸው ጣዖታትን ሠርተው አፈ ታሪክ የወለዳቸውን አማልክታቸውን ማምለክ ጀመሩ።—ዘዳ 12:30፤ 2ነገ 17:29, 33
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 9:20-22) ኖኅም ገበሬ ሆነ፤ የወይን እርሻም አለማ። 21 አንድ ቀን ኖኅ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ራቁቱን ሆነ። 22 የከነአን አባት ካምም የአባቱን እርቃን አየ፤ ውጭ ላሉት ሁለት ወንድሞቹም ነገራቸው።
(ዘፍጥረት 9:24, 25) ኖኅ ከወይን ጠጅ ስካሩ ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ፤ 25 እንዲህም አለ፦ “ከነአን የተረገመ ይሁን። ለወንድሞቹም የባሪያ ባሪያ ይሁን።”
it-1 1023 አን. 4
ካም
ድርጊቱን የፈጸመው ከነአን ቢሆንም አባቱ ካም እርማት ሳይሰጠው ቀርቶ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ኖኅ በካም ልብ ውስጥ ያለው መጥፎ ዝንባሌ (ምናልባትም በልጁ በከነአን ውስጥ ከወዲሁ መታየት ጀምሮ ይሆናል) ወደ ከነአን ዘሮች እንደሚተላለፍ በመንፈስ ተመርቶ እየተነበየ ሊሆን ይችላል። የሴም ዘሮች የሆኑት እስራኤላውያን ከነአናውያንን ድል ባደረጓቸው ጊዜ ይህ እርግማን በከፊል ፍጻሜውን አግኝቷል። ከጥፋት የተረፉት ሰዎች (ለምሳሌ፣ ገባኦናውያን [ኢያሱ 9]) የእስራኤላውያን ባሪያዎች ሆነዋል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ፣ የካም ልጅ የሆነው የከነአን ዝርያዎች የያፌት ዘር በሆኑት በሜዶ ፋርስ፣ በግሪክና በሮም የዓለም ኃያላን መንግሥታት ቁጥጥር ሥር ሲውሉ እርግማኑ ተጨማሪ ፍጻሜውን አግኝቷል።
(ዘፍጥረት 10:9, 10) እሱም ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ። በዚህም የተነሳ “እንደ ናምሩድ ያለ ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” ይባል ነበር። 10 የግዛቱ መጀመሪያም በሰናኦር ምድር የሚገኙት ባቤል፣ ኤሬክ፣ አካድ እና ካልኔ ነበሩ።
it-2 503
ናምሩድ
የናምሩድ መንግሥት ግዛት ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ ከተሞች መካከል በሰናኦር ምድር ያሉት ባቤል፣ ኤሬክ፣ አካድና ካልኔ ይገኙበታል። (ዘፍ 10:10) በመሆኑም ባቤልንና ግንቧን የመገንባቱ ሥራ የተጀመረው በእሱ አመራር ሥር ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሐሳብ የጥንቶቹ አይሁዳውያን ከነበራቸው አመለካከት ጋር ይስማማል። ጆሴፈስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ናምሩድ] ቀስ በቀስ አምባገነናዊ የአገዛዝ ሥርዓት መከተል ጀመረ፤ ሰዎች አምላክን እንዳይፈሩ ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በቋሚነት በእሱ ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ማድረግ እንደሆነ ያምን ነበር። አምላክ ምድርን ዳግመኛ በውኃ የሚያጥለቀልቃት ከሆነ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ይዝት ነበር፤ ውኃው ሊደርስበት የማይችል ከፍ ያለ ግንብ በመገንባት በአያቶቻቸው ላይ የደረሰውን ጥፋት እንደሚበቀል ይናገር ነበር። ሰዎቹም ለአምላክ መገዛትን እንደ ባርነት በመቁጠር [የናምሩድን] ምክር በደስታ ተቀበሉት፤ በመሆኑም ግንቡን መገንባት ጀመሩ፤ . . . ግንቡም ፍጹም ባልተጠበቀ ፍጥነት እያደገ ሄደ።”—ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ I, 114, 115 (iv, 2, 3)
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 10:6-32) የካም ወንዶች ልጆች ኩሽ፣ ሚጽራይም፣ ፑጥ እና ከነአን ነበሩ። 7 የኩሽ ወንዶች ልጆች ሴባ፣ ሃዊላ፣ ሳብታ፣ ራአማ እና ሳብተካ ነበሩ። የራአማ ወንዶች ልጆች ሳባ እና ዴዳን ነበሩ። 8 ኩሽ ናምሩድን ወለደ። እሱም በምድር ላይ የመጀመሪያው ኃያል ሰው ነበር። 9 እሱም ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ። በዚህም የተነሳ “እንደ ናምሩድ ያለ ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” ይባል ነበር። 10 የግዛቱ መጀመሪያም በሰናኦር ምድር የሚገኙት ባቤል፣ ኤሬክ፣ አካድ እና ካልኔ ነበሩ። 11 ከዚያ ምድር ተነስቶም ወደ አሦር በመሄድ ነነዌን፣ ረሆቦትኢርን እና ካላህን ቆረቆረ፤ 12 እንዲሁም በነነዌና በካላህ መካከል የምትገኘውን ረሰንን ቆረቆረ፤ እሷም ታላቋ ከተማ ናት። 13 ሚጽራይም ሉድን፣ አናሚምን፣ ለሃቢምን፣ ናፊቱሂምን፣ 14 ጳትሩሲምን፣ ካስሉሂምን (ፍልስጤማውያን የተገኙት ከእሱ ነው) እንዲሁም ካፍቶሪምን ወለደ። 15 ከነአን የበኩር ልጁን ሲዶናን፣ ሄትን 16 እንዲሁም ኢያቡሳዊውን፣ አሞራዊውን፣ ገርጌሻዊውን፣ 17 ሂዋዊውን፣ አርቃዊውን፣ ሲናዊውን፣ 18 አርዋዳዊውን፣ ጸማራዊውን እና ሃማታዊውን ወለደ። ከዚያ በኋላ የከነአናውያን ቤተሰቦች ተበተኑ። 19 በመሆኑም የከነአናውያን ወሰን ከሲዶና አንስቶ በጋዛ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጌራራ እንዲሁም እስከ ሰዶም፣ ገሞራ፣ አድማህ እና በላሻ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጸቦይም ድረስ ያለው ነበር። 20 የካም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ። 21 የኤቤር ወንዶች ልጆች ሁሉ ቅድመ አያትና የታላቅየው የያፌት ወንድም የሆነው ሴምም ልጆች ወለደ። 22 የሴም ወንዶች ልጆች ኤላም፣ አሹር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ እና አራም ነበሩ። 23 የአራም ወንዶች ልጆች ዑጽ፣ ሁል፣ ጌተር እና ማሽ ነበሩ። 24 አርፋክስድ ሴሎምን ወለደ፤ ሴሎምም ኤቤርን ወለደ። 25 ኤቤር ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። የአንደኛው ስም ፋሌቅ ነበር፤ ምክንያቱም በእሱ የሕይወት ዘመን ምድር ተከፋፍላ ነበር። የወንድሙ ስም ደግሞ ዮቅጣን ነበር። 26 ዮቅጣን አልሞዳድን፣ ሸሌፍን፣ ሃጻርማዌትን፣ ያራህን፣ 27 ሃዶራምን፣ ዑዛልን፣ ዲቅላን፣ 28 ኦባልን፣ አቢማዔልን፣ ሳባን፣ 29 ኦፊርን፣ ሃዊላን እና ዮባብን ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ወንዶች ልጆች ነበሩ። 30 መኖሪያ ስፍራቸውም ከሜሻ አንስቶ እስከ ሰፋር ይኸውም እስከ ምሥራቅ ተራራማ አካባቢ ድረስ ይዘልቃል። 31 የሴም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ። 32 የኖኅ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች እንደየዘር ሐረጋቸው በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውኃው በኋላ ብሔራት ሁሉ በምድር ላይ የተሰራጩት ከእነዚህ ነበር።