ዘፍጥረት
3 እባብም+ ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ* ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?”+ ሲል ጠየቃት። 2 በዚህ ጊዜ ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን።+ 3 ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ+ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” 4 በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።+ 5 አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ+ ስለሚያውቅ ነው።”
6 በዚህም የተነሳ ሴቲቱ ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች፤ ዛፉ ለዓይን የሚማርክ ነበር። ስለሆነም ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች።+ ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።+ 7 ከዚያም የሁለቱም ዓይኖች ተገለጡ፤ ራቁታቸውን መሆናቸውንም አስተዋሉ። በመሆኑም የበለስ ቅጠል በመስፋት የሚያሸርጡት ነገር ለራሳቸው ሠሩ።+
8 በኋላም ሰውየውና ሚስቱ ቀኑ ነፋሻማ በሆነበት ጊዜ ላይ ይሖዋ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ሲሄድ ድምፁን ሰሙ፤ እነሱም በአትክልቱ ስፍራ ባሉት ዛፎች መካከል በመግባት ከይሖዋ አምላክ ፊት ተደበቁ። 9 ይሖዋ አምላክም ሰውየውን በተደጋጋሚ በመጣራት “የት ነህ?” አለው። 10 በመጨረሻም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ድምፅህን ሰማሁ፤ ሆኖም ራቁቴን ስለነበርኩ ፈራሁ፤ ስለሆነም ተደበቅኩ” አለ። 11 እሱም “ራቁትህን+ እንደሆንክ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ በላህ?” አለው። 12 ሰውየውም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ይህች ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። 13 ከዚያም ይሖዋ አምላክ ሴቲቱን “ለመሆኑ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው?” አላት። ሴቲቱም “እባቡ አታለለኝና በላሁ”+ ስትል መለሰች።
14 ከዚያም ይሖዋ አምላክ እባቡን+ እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ ከቤት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ከዱር እንስሳት ሁሉ የተረገምክ ትሆናለህ። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በሆድህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፤ እንዲሁም አፈር ትበላለህ። 15 በአንተና+ በሴቲቱ+ መካከል እንዲሁም በዘርህና+ በዘሯ+ መካከል ጠላትነት+ እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤*+ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”*+
16 ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል፤ ምኞትሽ ሁሉ ባልሽ ይሆናል፤ እሱ ደግሞ ይገዛሻል።”
17 አዳምንም* እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ስለሰማህና ‘ከእሱ አትብላ’ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ ወስደህ ስለበላህ በአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን።+ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የምድርን ፍሬ በሥቃይ ትበላለህ።+ 18 ምድርም እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ አንተም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል ትበላለህ። 19 ከመሬት ስለተገኘህ+ ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ ላብህን እያንጠፈጠፍክ ምግብ ትበላለህ። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።”+
20 ከዚህ በኋላ አዳም ሚስቱን ሔዋን* ብሎ ጠራት፤ ምክንያቱም እሷ የሕያዋን ሁሉ እናት ትሆናለች።+ 21 ይሖዋ አምላክም ረጅም ልብስ ከቆዳ ሠርቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።+ 22 ከዚያም ይሖዋ አምላክ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ሰውየው መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል።+ አሁን ደግሞ እጁን በመዘርጋት ከሕይወት ዛፍ+ ፍሬ ወስዶ እንዳይበላና ለዘላለም እንዳይኖር . . .” 23 ይህን ካለ በኋላም የተገኘበትን መሬት እንዲያርስ፣+ ይሖዋ አምላክ አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ+ አባረረው። 24 ሰውየውንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ በኤደን የአትክልት ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤልና+ ያለማቋረጥ የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።