በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ማቅረብ
በታሪክ ሂደት በአንድ ወቅት ወደ ኤደን ገነት በሚወስደው በስተ ምሥራቅ ባለው መግቢያ ላይ አንድ አስደናቂ ሁኔታ ይታይ ነበር።a በዚህ ቦታ ኃያላን ኪሩቤሎች ቆመው ይጠብቃሉ። አስፈሪ ገጽታቸው ማንም ሰው በዚያች አካባቢ ዝር ማለት እንደማይችል ይጠቁማል። እንደ ኪሩቤሉ ሁሉ በምሽት በአካባቢው ባሉት ዛፎች ላይ ከፍተኛ ነፀብራቅ የሚፈጥረውና እንደ እሳት የሚንበለበለው የሚሽከረከር ሰይፍም አንድም ሰው ወደዚያ ድርሽ እንዳይል የሚያስጠነቅቅ ነበር። (ዘፍጥረት 3:24) ዕይታው ዓይን የሚማርክ ቢሆንም እንኳ ማንኛውም ተመልካች ወደዚያ መቅረብ አይችልም።
ቃየንና አቤል በተደጋጋሚ ወደዚህ ቦታ ሳይሄዱ አይቀሩም። ከአትክልት ሥፍራው ውጭ የተወለዱት ቃየንና አቤል በአንድ ወቅት ወላጆቻቸው በቂ ውኃ በሚያገኘውና ለምለም በሆነው እንዲሁም የተትረፈረፉ ፍራፍሬዎችና ዕጽዋት በሞሉበት ገነት ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ሁኔታ መኖር ምን ይመስል እንደነበር ከመገመት በቀር ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም። በወቅቱ የሚታየው የኤደን ክልል ዳዋ የበላው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
አዳምና ሔዋን የአትክልት ቦታው እንደዚያ ዳዋ በልቶት የቀረበትንና እነሱ ከዚያ የተባረሩበትን ምክንያት ለልጆቻቸው እንደነገሯቸው የተረጋገጠ ነው። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6, 23) ቃየንና አቤል ይህን ሲሰሙ ምንኛ ተቆጭተው ይሆን! የአትክልት ቦታውን ከውጭ ሆነው ማየት ቢችሉም ወደ ውስጥ መግባት ግን አይችሉም። ቃየንና አቤል ለገነት በጣም ቅርብ ቢሆኑም ወደዚያ መቅረብ እንኳ አይችሉም ነበር። ቃየንና አቤል አለፍጽምና በክሏቸዋል፤ ግን ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም።
በወላጆቻቸው መካከል የነበረው ግንኙነት ሁኔታዎችን ከማባባስ በስተቀር ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ እሙን ነው። አምላክ በሔዋን ላይ ፍርድ ሲያስተላልፍ “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ብሏል። (ዘፍጥረት 3:16) በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት አዳም ምናልባትም በፊት ያደርግ እንደነበረው ሚስቱን አጋሩና ረዳቱ አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ ገዥዋ እንደሆነ አሳይቶ መሆን አለበት። ሔዋን ደግሞ ራሷን ከልክ በላይ የእሱ ጥገኛ አድርጋ ሳትመለከት አትቀርም። እንዲያውም አንድ የትንታኔ መጽሐፍ የእርሷን ‘ፈቃድ’ (በእንግሊዝኛ “ክሬቪንግ”) “የበሽታ ያክል አስከፊ የሆነ ምኞት” በማለት እስከ መግለጽ ደርሷል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓይነቱ የጋብቻ ዝምድና ልጆቹ ለወላጆቻቸው በሚኖራቸው አክብሮት ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እንዳሳደረ የሚገልጸው ነገር የለም። ሆኖም አዳምና ሔዋን ለልጆቻቸው መጥፎ አርአያ መተዋቸው ግልጽ ነው።
የተለያዩ ጎዳናዎች መምረጥ
ውሎ አድሮ አቤል እረኛ ሲሆን ቃየን ደግሞ በእርሻ ሥራ ተሰማራ። (ዘፍጥረት 4:2) አቤል መንጋውን በሚጠብቅበት ወቅት ወላጆቹ ከኤደን ከመባረራቸው በፊት “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” ተብሎ በተነገረው ልዩ ትንቢት ላይ የሚያሰላስልበት ሰፊ ጊዜ እንዳገኘ አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 3:15) አቤል ‘አምላክ እባቡን ስለሚቀጠቅጠው ዘር የሰጠው ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ይሆን? እንዲሁም ይህ ዘር ሰኮናው ላይ የሚነከሰውስ እንዴት ነው?’ ብሎ ሳያስብ አይቀርም።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቃየንና አቤል በጉልምስና ዕድሜያቸው ሳይሆን አይቀርም ለይሖዋ መሥዋዕት አቀረቡ። አቤል እረኛ እንደመሆኑ መጠን “ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ” መሥዋዕት ማቅረቡ አያስደንቅም። በአንጻሩ ደግሞ ቃየን “ከምድር ፍሬ” አቀረበ። ይሖዋ የአቤልን መሥዋዕት ሲቀበል “ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም።” (ዘፍጥረት 4:3-5) ለምን?
አንዳንዶች የአቤል መሥዋዕት “ከበጎቹ በኩራት” የቀረበ ሲሆን የቃየን ግን እንደነገሩ “ከምድር ፍሬ” በመቅረቡ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ዘገባው ይሖዋ “ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ” በደስታ ሲመለከት “ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ” ግን በደስታ አለመመልከቱን ስለሚገልጽ ችግሩ ያለው ቃየን ባቀረበው ነገር ጥራት ላይ አልነበረም። ስለዚህ ይሖዋ በአንደኛ ደረጃ የተመለከተው የአምላኪውን የልብ ዝንባሌ ነበር። እንዲህ ሲያደርግ የተመለከተው ነገር ምን ነበር? ዕብራውያን 11:4 አቤል መሥዋዕቱን ያቀረበው “በእምነት” መሆኑን ይናገራል። ስለዚህ ቃየን የአቤል መሥዋዕት ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው እምነት ይጎድለው እንደነበር ግልጽ ነው።
በዚህ ረገድ የአቤል መሥዋዕት ደም ማፍሰስን ማካተቱ ትኩረት የሚስብ ነው። አምላክ ተረከዙ ላይ ስለሚነከሰው ዘር ከገባው ቃል በመነሳት ጉዳዩ አንድ ሕይወት መሥዋዕት እንዲሆን ይጠይቃል የሚል ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ሳያደርሰው አይቀርም። ስለዚህ የአቤል መሥዋዕት ለዕርቅ የቀረበ ልመና ሊሆን ይችላል። እንዲሁም መሥዋዕቱ አምላክ በወሰነው ጊዜ ለኃጢአት ማስተሰሪያ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛ እንደሚያቀርብ እምነት እንዳለው ያሳያል።
በአንፃሩ ደግሞ ቃየን ስለሚያቀርበው መሥዋዕት ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ እንዲሁ ለታይታ ያደረገው ይመስላል። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ “እርሱ መሥዋዕቱን ያቀረበው እንዲያው ለይሉኝታ ሲል ብቻ ነው ለማለት ይቻላል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። “ያቀረበው መሥዋዕት በእርሱና በፈጣሪው መካከል ያለውን ዝምድና የሚያሻክር ነገር መኖሩንና ለኃጢአት ንስሐ የመግባትንም ሆነ የስርየትን አስፈላጊነት አለመገንዘቡን በግልጽ ያሳይ ነበር።”
ከዚህ በተጨማሪም ቃየን በኩር እንደመሆኑ መጠን እባቡን ማለትም ሰይጣንን የሚያጠፋው ተስፋ የተደረገበት ዘር እርሱ እንደሆነ አድርጎ በትዕቢት ሳያስብ አይቀርም። ሔዋንም ሳትቀር ለበኩር ልጅዋ ይህ ዓይነቱን ጉጉት የታከለበት ምኞት አሳድራ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 4:1) እርግጥ ነው፣ ቃየንም ሆነ ሔዋን እንዲህ ዓይነት ምኞት ከነበራቸው በጣም ተሳስተዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የአቤልን መሥዋዕት መቀበሉን ያሳየው እንዴት እንደሆነ አይገልጽልንም። አንዳንዶች ከሰማይ የወረደ እሳት መሥዋዕቱን እንደበላው ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ ቃየን መሥዋዕቱ ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲገነዘብ ‘እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።’ (ዘፍጥረት 4:5) ቃየን ወደ ጥፋት እያመራ ነበር።
የይሖዋ ምክርና ቃየን የሰጠው ምላሽ
ቃየን ስሜቱን እንዲመረምር ይሖዋ ሊረዳው ሞክሯል። “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?” ሲል ጠየቀው። ቃየን የቀረበለት ጥያቄ ስሜቱንና ግፊቱን እንዲመረምር በቂ አጋጣሚ ሰጥቶታል። በመቀጠልም ይሖዋ “መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” አለው።—ዘፍጥረት 4:6, 7 (በገጽ 23 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
ቃየን የተነገረውን አልሰማም። ከዚህ ይልቅ አቤልን ወደ ሜዳ ይዞት ሄደና ገደለው። ከዚያም ይሖዋ ቃየንን አቤል የት እንዳለ ሲጠይቀው “አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” ሲል በቁጣ በመመለስ በፈጸመው ኃጢአት ላይ ውሸት አከለበት።—ዘፍጥረት 4:8, 9
ቃየን አቤልን ከመግደሉ በፊትም ሆነ ከገደለው በኋላ ‘መልካም ለማድረግ’ ፈቃደኛ አልሆነም። በእርሱ ላይ ኃጢአት እንዲነግሥ መረጠ። በዚህ ምክንያት ቃየን ሰብዓዊው ቤተሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ተባረረ። በአቤል ሞት ምክንያት ማንም ሰው ቃየንን እንዳይበቀለው “ምልክት” ተደረገ፤ ይህ ምልክት የተባለው ነገር ቃየን አንዳይገደል የሚደነግግ ሕግ ሊሆን ይችላል።—ዘፍጥረት 4:15
ከጊዜ በኋላ ቃየን ከተማ ቆረቆረና በልጁ ስም ሰየማት። የእርሱ ዝርያዎች በዓመፅ ድርጊታቸው የታወቁ መሆናቸው አያስገርምም። በመጨረሻም በኖኅ ዘመን የመጣው የጥፋት ውኃ ክፉ ሰዎችን በሙሉ ጠራርጎ ሲያጠፋ የቃየን የዘር ሐረግ ተደመሰሰ።—ዘፍጥረት 4:17-24፤ 7:21-24
ስለ ቃየንና አቤል የሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ለመዝናናት እንድናነበው ተብሎ የቆየ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘገባው የተጻፈው “ለትምህርታችን” ስለሆነ “ለትምህርትና ለተግሣጽ . . . ይጠቅማል።” (ሮሜ 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
የምናገኘው ትምህርት
ቃየንና አቤል እንዳደረጉት ዛሬ ክርስቲያኖች ቃል በቃል የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሳይሆን “ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” ለአምላክ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል። (ዕብራውያን 13:15) ይህ ጥቅስ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እየሰበኩ ባሉበት በዚህ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። (ማቴዎስ 24:14) አንተም በዚህ ሥራ ተሳትፎ እያደረግህ ነው? ከሆነ ‘እግዚአብሔር ያደረግከውን ሥራ ለስሙም ያሳየኸውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳልሆነ’ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።—ዕብራውያን 6:10
ቃየንና አቤል ያቀረቡት መሥዋዕት የተመዘነው እንዲሁ ከውጭ በሚታየው ነገር እንዳልሆነ ሁሉ አንተም የምታቀርበው መሥዋዕት የሚመዘነው ከውጭ በሚታየው ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል በአገልግሎት በምታሳልፈው የሰዓት መጠን ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ይሖዋ ውስጥን ይመረምራል። ኤርምያስ 17:10 እንደሚገልጸው እርሱ ‘ልብን ይመረምራል’ አልፎ ተርፎም ‘ኩላሊትን ይፈትናል።’ ይህም ማለት አንድ ሰው ያለውን ውስጣዊ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ግፊት ያያል ማለት ነው። ስለዚህ አንገብጋቢው ጉዳይ ብዛቱ ሳይሆን ውስጣዊ ግፊቱ ነው። በእርግጥም፣ ብዙም ሆነ ጥቂት አንድ መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ዋጋ የሚኖረው በፍቅር ከተሞላ ልብ የቀረበ ሲሆን ነው።—ማርቆስ 12:41-44ን ከ14:3-9 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ቃየን በሙሉ ልብ ያላቀረበውን መሥዋዕት እንዳልተቀበለ ሁሉ ሰንካላ መሥዋዕቶችን እንደማይቀበል ማወቅ ይኖርብናል። (ሚልክያስ 1:8, 13) ይሖዋ ምርጥህን እንድትሰጠው ማለትም በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ ሐሳብህና ኃይልህ እንድታገለግለው ይጠብቅብሃል። (ማርቆስ 12:30) እንዲህ እያደረግህ ነው? ከሆነ ባቀረብከው መሥዋዕት እርካታ የምታገኝበት በቂ ምክንያት አለህ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል።”—ገላትያ 6:4
ቃየንና አቤል ተመሳሳይ አስተዳደግ ነበራቸው። ሆኖም ጊዜና አጋጣሚ እያንዳንዳቸው የየግላቸውን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። የቃየን አስተሳሰብ ደረጃ በደረጃ በቅናት፣ በጠበኝነትና በግልፍተኝነት እየተመረዘ ሄደ።
በአንፃሩ ደግሞ አቤል በአምላክ ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቆጥሯል። (ማቴዎስ 23:35) አቤል ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም አምላክን ለማስደሰት የነበረው ጽኑ አቋም በቤተሰቡ ውስጥ ከነበሩት ምስጋና ቢሶች ማለትም ከአዳም፣ ከሔዋንና ከቃየን ልዩ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አቤል ቢሞትም “እስከ አሁን ይናገራል” ሲል ይገልጽልናል። አምላክን በታማኝነት ማገልገሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ቋሚ የታሪክ መዝገብ ክፍል ነው። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ማቅረባችንን በመቀጠል አቤል የተወልንን ምሳሌ የምንከተል እንሁን።—ዕብራውያን 11:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶች የኤደን የአትክልት ስፍራ በዛሬዋ ቱርክ በምሥራቅ ክልል ባለው ተራራማ ቦታ ላይ ይገኝ እንደነበር ይገምታሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ክርስቲያን መካሪዎች ሊከተሉት የሚገባ አርአያ
“ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?” ይሖዋ እነዚህን ጥያቄዎች በመጠየቅ ቃየን ጉዳዩን እንዲያስብበት በደግነት ሊረዳው ሞክሯል። ቃየን የመምረጥ ነፃነት ያለው ፍጡር ስለሆነ ይሖዋ አካሄዱን እንዲለውጥ አላስገደደውም። (ከዘዳግም 30:19 ጋር አወዳድር።) የሆነ ሆኖ ይሖዋ፣ ቃየን የተከተለው አጓጉል አካሄድ ሊያስከትልበት የሚችለውን መዘዝ ከመንገር ወደኋላ አላለም። ቃየንን “መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው” ሲል አስጠንቅቆታል።—ዘፍጥረት 4:6, 7
ይሖዋ ይህን የመሰለ ጠንካራ ተግሣጽ ቢሰጠውም እንኳ ቃየንን ‘ምንም ተስፋ እንደሌለው’ አድርጎ እንዳልተመለከተው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ቃየን አካሄዱን ካስተካከለ የሚያገኛቸውን በረከቶች ከመንገሩም በላይ ከፈለገ ይህን ችግር ማሸነፍ እንደሚችል ያለውን ትምክህት ገልጿል። ይሖዋ “መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን?” ሲል ነግሮታል። በተጨማሪም ወደ ግድያ ሊያመራው የሚችለውን ቁጣ በተመለከተ “አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” ብሎታል።
በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች የይሖዋን አርዓያ መኮረጅ ይኖርባቸዋል። በ2 ጢሞቴዎስ 4:2 ላይ እንደተጠቀሰው አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች አንድ ስሕተት የፈጸመ ክርስቲያን መጥፎ አካሄዱ ሊያስከትልበት የሚችለውን መዘዝ ፊት ለፊት በመንገር ‘መዝለፍና መገሠጽ’ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች ‘መምከርም’ አለባቸው። ፓራካሌኦ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ማጽናናት” ማለት ነው። “ፍቅራዊ ተግሳጹ የሚያቆስል፣ የሌላውን አመለካከት የሚያወግዝ ወይም ክፉኛ ለመተቸት የታቀደ አይደለም” ሲል ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ገልጿል። “ሌላ የቃሉ ትርጉም ማጽናናት የሚል መሆኑ ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተላልፋል።”
ፓራክሌቶስ የሚለው ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነው የግሪክኛ ቃል ከሕግ ጋር በተያያዘ ጉዳይ እርዳታ የሚሰጥን ወይም ጥብቅና የሚቆምን ሰው ሊያመለክት መቻሉ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ነው። ስለዚህ ሽማግሌዎች ተግሣጽ ለሚያስፈልገው ግለሰብ ቀጥተኛ የሆነ ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜም የግለሰቡ ባላንጣዎች ሳይሆኑ ረዳቶች መሆናቸውን ማስታወስ አለባቸው። ይሖዋ እንዳደረገው ሁሉ ሽማግሌዎች አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ምክር የሚሰጠው ሰው ችግሩን ሊያሸንፍ እንደሚችል ትምክህት ማሳየት ይኖርባቸዋል።—ከገላትያ 6:1 ጋር አወዳድር።
የሆነ ሆኖ ፍቅራዊ ተግሣጹን በተግባር ማዋል አለማዋል ለግለሰቡ የተተወ መሆኑ የታወቀ ነው። (ገላትያ 6:5፤ ፊልጵስዩስ 2:12) ቃየን በቀጥታ ከፈጣሪው የመጣለትን ተግሳጽ ችላ ለማለት እንደመረጠ ሁሉ ምክር ሰጪዎች አንዳንዶች የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ እንደማይቀበሉ ይመለከቱ ይሆናል። ሆኖም ሽማግሌዎች ይሖዋ ለክርስቲያን መካሪዎች የተወላቸውን ፍጹም አርአያ ሲከተሉ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ሁሉ እንዳደረጉ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ።