በሸክላ ዕቃ ውስጥ ያለን ውድ ሀብት
“ከወትሮው የበለጠ ኃይል ያገኘነው ከአምላክ እንጂ ከራሳችን እንዳልሆነ እንዲታወቅ ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።”—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW
1. የኢየሱስ ምሳሌ ሊያበረታታን የሚገባው እንዴት ነው?
ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ በይሖዋ እየተቀረጸ በነበረበት ጊዜ የሰው ልጅ ያለበትን ድካም በራሱ ላይ ከደረሰው ሁኔታ መመልከት ችሏል። የጸና አቋም በመጠበቅ ረገድ የተወው ምሳሌ ምንኛ ሊያበረታታን ይገባል! ሐዋርያው እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።” (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ በዚህ መንገድ ለመቀረጽ ፈቃደኛ በመሆኑ ዓለምን ድል አድርጓል። ሐዋርያቱም ድል አድራጊዎች እንዲሆኑ አደፋፍሯቸዋል። (ሥራ 4:13, 31፤ 9:27, 28፤ 14:3፤ 19:8) በተጨማሪም ለመጨረሻ ጊዜ በሰጣቸው ንግግሩ መደምደሚያ ላይ በእጅጉ አበረታቷቸዋል! እንዲህ አለ:- “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33
2. ከዓለም ዕውርነት በተለየ መልኩ ምን ዓይነት ብርሃን አለን?
2 በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ያመጣውን ዕውርነት ‘ከክብራማው ምሥራች ብርሃን’ ጋር ካነጻጸረ በኋላ ውድ ስለሆነው አገልግሎታችን እንዲህ ብሏል:- “የኃይሉ ታላቅነት [“ከወትሮው የበለጠ ኃይል ያገኘነው፣” NW] ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ [“ውድ ሀብት፣” NW] በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቈርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም።” (2 ቆሮንቶስ 4:4, 7–9) ደካማ ‘የሸክላ ዕቃዎች’ ብንሆንም እንኳ አምላክ በመንፈሱ ስለቀረጸን የሰይጣንን ዓለም ሙሉ በሙሉ ድል ማድረግ እንችላለን።—ሮሜ 8:35–39፤ 1 ቆሮንቶስ 15:57
የጥንቱን የእስራኤል ሕዝብ መቅረጽ
3. ኢሳይያስ የአይሁድ ሕዝብ የተቀረጸበትን ሁኔታ የገለጸው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ብሔራትንም ይቀርጻል። ለምሳሌ ያህል የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ይሖዋ እንዲቀርጸው ፈቃደኛ በነበረበት ጊዜ በልጽጓል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የአምላክን ሕግ መጣስ ልማዳቸው አደረጉት። በዚህም የተነሳ የእስራኤል ሠሪ ‘ወዮታ’ አመጣባቸው። (ኢሳይያስ 45:9) በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢሳይያስ እስራኤላውያን ስለፈጸሙት ከባድ ኃጢአት እንዲህ በማለት ለይሖዋ ተናግሮ ነበር:- “አቤቱ፣ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፣ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። . . . ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል።” (ኢሳይያስ 64:8–11) እስራኤላውያን ከጥፋት በቀር ለሌላ ለምንም የማያገለግል ዕቃ ሆነዋል።
4. ኤርምያስ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ምን ነገር አድርጓል?
4 ይህ ከሆነ ከአንድ መቶ ዘመን በኋላ የፍርዱ ቀን እየቀረበ ሲሄድ ይሖዋ ኤርምያስን ገምቦ ይዞ ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሄኖም ሸለቆ እንዲሄድ በመንገር እንዲህ ሲል አዘዘው:- “ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፣ እንዲህም ትላቸዋለህ:- የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- የሸክላ ሠሪው ዕቃ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፣ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ።”—ኤርምያስ 19:10, 11
5. ይሖዋ በእስራኤል ላይ ያመጣው ፍርድ ምን ያህል ስፋት ነበረው?
5 በ607 ከዘአበ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ከነቤተ መቅደሷ በማውደም በሕይወት የተረፉትን አይሁዶች ወደ ባቢሎን አጋዘ። ሆኖም ለ70 ዓመታት በግዞት ከቆዩ በኋላ ንስሐ የገቡ አይሁዶች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ዳግመኛ ለመገንባት ወደ አገራቸው መመለስ ችለዋል። (ኤርምያስ 25:11) ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ሕዝቡ ዳግመኛ ታላቁን ሸክላ ሠሪ በመተው የራሱን የአምላክን ልጅ በመግደል ከሁሉ የከፋ ወንጀል እስከመፈጸም ደረሱ። በ70 እዘአ አምላክ የሮማውን የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ፍርድ አስፈጻሚ አድርጎ በመጠቀም የአይሁድን የነገሮች ሥርዓት ጠራርጎ አጠፋ፣ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷንም ጨርሶ አወደመ። የእስራኤል ሕዝብ በይሖዋ እጅ ‘እንደተቀደሰና እንደተዋበ’ ዕቃ የሚቀረጽበት ጊዜ ለአንዴና ለመጨረሻ አከተመ።a
መንፈሳዊ ብሔር መቅረጽ
6, 7. (ሀ) ጳውሎስ መንፈሳዊው እስራኤል የሚቀረጽበትን ሁኔታ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የ“ምሕረት ዕቃዎች” ጠቅላላ ቁጥር ስንት ነው? ይህስ ቁጥር የሚሟላው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስን የተቀበሉ አይሁዶች የአንድ አዲስ ብሔር ማለትም የመንፈሳዊ የ“እግዚአብሔር እስራኤል” መሥራች አባላት ሆነው ተቀርጸዋል። (ገላትያ 6:16) ከዚህ አኳያ ሲታይ የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ተስማሚ ናቸው:- “ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? ነገር ግን እግዚአብሔር ቊጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፣ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፣ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ፣ እንዴት ነው?”—ሮሜ 9:21–23
7 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ እነዚህ የ“ምሕረት ዕቃዎች” 144,000 እንደሚሆኑ ገለጸ። (ራእይ 7:4፤ 14:1) ሥጋዊ እስራኤላውያን ቁጥሩን ሊያሟሉ ባለመቻላቸው ይሖዋ ምሕረቱን ለሌሎች ብሔራት ሕዝቦች ዘረጋ። (ሮሜ 11:25, 26) አፍላ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በፍጥነት እያደገ ሄደ። በ30 ዓመት ውስጥ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰበከ። (ቆላስይስ 1:23) በመሆኑም በትክክለኛ የበላይ አመራር ሥር ሆነው የሚንቀሳቀሱ ተራርቀው የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች ማቋቋም አስፈልጎ ነበር።
8. የመጀመሪያው የአስተዳደር አካል አባላት እነማን ነበሩ? ይህ አካል ያደገውስ እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ 12ቱ ሐዋርያት የመጀመሪያው የአስተዳደር አካል እንዲሆኑ በማዘጋጀት እነሱንም ሆነ ሌሎችን ለአገልግሎት አሰልጥኗል። (ሉቃስ 8:1፤ 9:1, 2፤ 10:1, 2) በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ ተቋቋመ፤ ከጊዜ በኋላ የአስተዳደር አካሉ ሰፍቶ ‘ሐዋርያትንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች’ ያቀፈ ሆነ። የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ሐዋርያ ባይሆንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለገለ ይመስላል። (ሥራ 12:17፤ 15:2, 6, 13፤ 21:18) ታሪክ ጸሐፊው ዩሲቢየስ እንዳለው ከሆነ ስደቱ ይበልጥ በሐዋርያት ላይ በማነጣጠሩ ወደ ሌሎች ክልሎች ተበታትነው ነበር። የአስተዳደር አካሉ መዋቅርም ከሁኔታው ጋር በሚስማማ መንገድ ተስተካክሏል።
9. ኢየሱስ ምን አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል?
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ‘ጠላት ማለትም ዲያብሎስ’ ስንዴ መሰል በሆኑት የ“መንግሥተ ሰማያት” ወራሾች መካከል ‘እንክርዳድ መዝራት’ ጀመረ። ኢየሱስ ይህ አሳዛኝ ክስተት እስከ “ዓለም መጨረሻ” እንዲቆይ የሚፈቀድለት መሆኑን አስቀድሞ ተናግሯል። ከዚያ በኋላ ‘ጻድቃን ዳግመኛ በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።’ (ማቴዎስ 13:24, 25, 37–43) ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
በዛሬው ጊዜ የአምላክን እስራኤል መቅረጽ
10, 11. (ሀ) በዘመናችን የአምላክ እስራኤልን የመቅረጹ ሥራ የተጀመረው እንዴት ነው? (ለ) በሕዝበ ክርስትናና ቅን የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች መካከል ምን ልዩነት ነበረ?
10 በ1870 ቻርልስ ቴዝ ራስል በዩ ኤስ ኤ ፔንሲልቫንያ ፒትስበርግ ውስጥ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋመ። በ1879 በዛሬው ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀውን መጽሔት በየወሩ ማተም ጀመረ። በወቅቱ ይጠሩበት በነበረው መጠሪያ መሠረት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብዙም ሳይቆይ ሕዝበ ክርስትና ነፍስ አትሞትም፣ እሳታማ ሲኦል፣ መንጽሔ፣ ሥላሴና የሕፃናት ጥምቀትን የመሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ የአረማውያን ትምህርቶች እንደተቀበለች ተገነዘቡ።
11 ከዚህም በላይ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወዳዶች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መቤዠትና ከሞት ተነሥቶ በአምላክ መንግሥት ሥር ሰላማዊ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖርን የመሳሰሉ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን መልሰው ማስተማር ጀመሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑ የሚረጋገጥበት ጊዜ መቅረቡን አጽንኦት ሰጥተው መግለጽ ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚከተለው የጌታ ጸሎት መልስ የሚያገኝበት ጊዜ መቃረቡን አምነው ነበር:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) ሰላም ወዳድ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያኖች ማኅበር እንዲሆኑ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እየተቀረጹ ነበር።
12. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ወቅት ለይተው ማወቅ የቻሉት እንዴት ነው?
12 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በዳንኤል ምዕራፍ 4 እና በሌሎች ትንቢቶች ላይ ያደረጉት ጥልቅ ምርምር ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ጊዜ መቅረቡን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ በ1914 እንደሚያበቁ ተገነዘቡ። (ሉቃስ 21:24፤ ሕዝቅኤል 21:26, 27) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቡድኖችን (ከጊዜ በኋላ ጉባኤዎች ተብለው የተጠሩትን) በማቋቋም እንቅስቃሴያቸውን በፍጥነት እያሰፉ ሄዱ። በዚህ በያዝነው መቶ ዘመን መባቻ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ሥራቸውን ወደ አውሮፓና ወደ አውስትራሊያ አስፋፉ። ጥሩ ድርጅት ማዋቀሩ አስፈላጊ ሆነ።
13. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ሕጋዊ ዕውቅና አገኙ? የማኅበሩ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንትስ ምን ታላቅ አገልግሎት አከናውኗል?
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤቱን በፔንሲልቫንያ ፒትስበርግ ውስጥ በማድረግ በ1884 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሕጋዊ ኮርፖሬሽን ሆኖ ተቋቋመ። ዲሬክተሮቹ ዓለም አቀፋዊውን የአምላክ መንግሥት የስብከት ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠር ማዕከላዊ የአስተዳደር አካል ሆነው ማገልገል ጀመሩ። የማኅበሩ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የሆነው ቻርልስ ቲ ራስል የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በሚል ርዕስ ስድስት ጥራዞች ያሉት መጽሐፍ ከማዘጋጀቱም በላይ ብዙ ቦታዎችን የሸፈነ የስብከት ጉዞ አድርጓል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምሩን ከመጀመሩ በፊት ያከማቸውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ለዓለም አቀፉ የመንግሥቱ ሥራ አበርክቷል። በ1916 ታላቁ ጦርነት አውሮፓን እየናጣት በነበረበት ወቅት እጅግ ተዳክሞ የነበረው ወንድም ራስል በስብከት ጉዞ ላይ እንዳለ አረፈ። ያለው ነገር ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰጠውን ምሥክርነት ለማስፋፋት እንዲውል አድርጓል።
14. ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ‘መልካሙን ገድል የተጋደለው’ እንዴት ነው? (2 ጢሞቴዎስ 4:7)
14 በሚዙሪ ለጥቂት ጊዜ ዳኛ ሆኖ የሠራው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በምትኩ ፕሬዚዳንት ሆነ። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በድፍረት ጥብቅና በመቆሙ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ‘በሕግ ላይ ዓመፅ በመሥራት’ ከፖለቲከኞች ጋር ጥምረት ፈጠሩ። ሰኔ 21, 1918 ወንድም ራዘርፎርድና ሌሎች በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከ10 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ተደራራቢ ፍርድ ተበይኖባቸው ወኅኒ ወረዱ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የደረሰባቸውን ጥቃት መቋቋም ችለዋል። (መዝሙር 94:20፤ ፊልጵስዩስ 1:7) ይግባኝ በመጠየቅ መጋቢት 26, 1919 ተለቀቁ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሣሣት ሞክረዋል በሚል ተሰንዝሮባቸው ከነበረው የሐሰት ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኑ።b ይህ የደረሰባቸው ሁኔታ ቆራጥ የእውነት ጠበቆች እንዲሆኑ አድርጎ ቀርጿቸዋል። ታላቂቱ ባቢሎን ብትቃወማቸው እንኳ በይሖዋ እርዳታ ምሥራቹን ለማወጅ በሚደረገው መንፈሳዊ ውጊያ ድል ለማድረግ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመዋል። ይህ ውጊያ አሁን እስካለንበት እስከ 1999 ዓመት ድረስ ቀጥሏል።—ከማቴዎስ ምዕራፍ 23 እና ከዮሐንስ 8:38–47 ጋር አወዳድር።
15. በይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ 1931 ታላቅ ግምት የሚሰጠው ዓመት የሆነው ለምንድን ነው?
15 በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት ቅቡዓን የአምላክ እስራኤል በታላቁ ሸክላ ሠሪ አመራር መቀረጻቸውን ቀጠሉ። ከቅዱሳን ጽሑፎች የፈነጠቀው ትንቢታዊ ብርሃን ለይሖዋ ክብር እንዲሰጡና በኢየሱስ መሲሐዊ መንግሥት ላይ እንዲያተኩሩ አደረጋቸው። በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲስ ስም በመቀበላቸው ተደሰቱ።—ኢሳይያስ 43:10–12፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14
16. እና በገጽ 19 ላይ ያለው ሣጥን። የ144,000 ጠቅላላ ቁጥር የሞላው መቼ ነው? ለዚህስ ምን ማስረጃ አለ?
16 በ1930ዎቹ ዓመታት “የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም” የተባሉት 144,000ዎች ቁጥራቸው እንደሞላ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ታዩ። (ራእይ 17:14፤ በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲሁም ሕዝበ ክርስትና ታላቅ ክህደት ባስፋፋችባቸው በጨለማዎቹ ዘመናት ከነበሩት “አረሞች” መካከል ምን ያህል ቅቡዓን እንደተሰበሰቡ አናውቅም። ሆኖም በ1935 ከፍተኛው የአስፋፊዎች ቁጥር 56,153 ደርሶ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ 52,465 የሚሆኑ ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን በመካፈል ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል። ታዲያ ገና የሚሰበሰቡት ብዙዎቹ ሰዎች ዕጣቸው ምንድን ነው?
“እነሆ! እጅግ ብዙ ሰዎች”
17. በ1935 ምን ታሪካዊ ሁኔታ ተከናውኗል?
17 ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 3, 1935 በዩ ኤስ ኤ ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ “ታላቅ ሕዝብ” በሚል ርዕስ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ንግግር አደረገ። ‘ማንም ሰው ሊቆጥረው የማይችለው’ ይህ ቡድን የ144,000 መንፈሳዊ እስራኤል መታተም ሲያበቃ ወደ መድረክ ብቅ የሚል ነው። እነዚህም ሰዎች “በበጉ ደም” ማለትም በኢየሱስ ደም የመቤዠት ኃይል የሚያምኑ ከመሆናቸውም በላይ ይሖዋ ለአምልኮ ባቋቋመው የቤተ መቅደስ ዝግጅት ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ። በቡድን ደረጃ ‘ታላቁን መከራ በሕይወት በማለፍ’ ‘ሞት የማይኖርበትን’ ምድራዊ ገነት ይወርሳሉ። ከዚህ የአውራጃ ስብሰባ በፊት ለተወሰኑ ዓመታት ይህ ቡድን የኢዮናዳብ ክፍል በመባል ይጠራ ነበር።—ራእይ 7:9–17፤ 21:4፤ ኤርምያስ 35:10
18. በምን መንገዶች ነው 1938 ወሳኝ ዓመት የሆነው?
18 በ1938 ሁለቱ ክፍሎች ማንነታቸው በደንብ ተለይቶ ታወቀ። የመጋቢት 15 እና የሚያዝያ 1, 1938 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች “መንጋው” በሚል ጭብጥ በሁለት የጥናት ርዕስ ባቀረቡት ማብራሪያ ቅቡዓን ቀሪዎችና ባልንጀሮቻቸው የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ያላቸውን ቦታ ግልጽ አድርገዋል። ከዚያም የሰኔ 1 እና የሰኔ 15 እትሞች በኢሳይያስ 60:17 ላይ በተመሠረተው “ድርጅት” በሚለው ጭብጥ የጥናት ርዕሶችን ይዘው ወጡ። ሁሉም ጉባኤዎች አገልጋይ ለመሾም የአስተዳደር አካሉን እንዲጠይቁ ተደረገ። በዚህ መንገድ የተሻሻለና አምላክ ያቋቋመው ቲኦክራሲያዊ አሠራር ተጀመረ። ጉባኤዎቹም እንደተባለው አደረጉ።
19. እና የግርጌ ማስታወሻ። ለ“ሌሎች በጎች” የቀረበው አጠቃላይ ጥሪ በአሁኑ ጊዜ ከ60 ዓመት በላይ እንደሆነው የሚያረጋግጡት የትኞቹ እውነታዎች ናቸው?
19 በ1939 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ቁጥር ጥቂት ነው፤ ወደፊትም ቢሆን አይጨምርም። እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የጽዮን ማለትም የአምላክ ድርጅት ዘሮች ‘ቀሪዎች’ ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 12:17) አሁን ጌታ ‘ታላቅ ሕዝብ’ የሚሆኑትን ‘ሌሎች በጎች’ ወደ ራሱ እየሰበሰበ ነው። (ዮሐንስ 10:16) አሁን እየተሰበሰቡ ያሉት ከቀሪዎቹ ጋር የሚሠሩ የቀሪዎቹ ባልንጀሮች ናቸው። ከአሁን በኋላ የ‘ሌሎች በጎች’ አባሎች ‘ታላቁ ሕዝብ’ እስከሚሰበሰብ ድረስ በቁጥር እየጨመሩ ይሄዳሉ።” ቅቡዓን ክርስቲያኖች እጅግ ብዙ ሰዎችን የመሰብሰቡን ሥራ ማካሄድ በሚችሉበት ሁኔታ ተቀርጸዋል። እነዚህኛዎቹም መቀረጽ አለባቸው።c
20. ከ1942 ወዲህ ምን ድርጅታዊ ለውጦች ተደርገዋል?
20 በጥር 1942 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት ጆሴፍ ራዘርፎርድ ሞተና በናታን ኖር ተተካ። ሦስተኛው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋሙና ሚስዮናውያን የሚሰለጥኑበትን የጊልያድ ትምህርት ቤት በመመሥረቱ ጥሩ ትዝታ ጥሎ አልፏል። በ1944 በተካሄደው የማኅበሩ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የማኅበሩ አባል መሆን የሚቻለው በቁሳዊ መዋጮ መሆኑ ቀርቶ በመንፈሳዊነት ይሆን ዘንድ የማኅበሩ ቻርተር ማሻሻያ እየተደረገበት መሆኑን አሳወቀ። በቀጣዮቹ 30 ዓመታት የመስኩ ሠራተኞች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ156,299 ወደ 2,179,256 አደገ። ከ1971–75 ተጨማሪ ድርጅታዊ ለውጦች ማድረግ አስፈልጎ ነበር። ምድር አቀፉን የመንግሥቱን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠረው ፕሬዚዳንቱ ብቻ መሆኑ ቀረ። አባላቱ በየተራ ሊቀ መንበር እየሆኑ የሚሠሩበት የአስተዳደር አካል አድጎ 18 ቅቡዓን አባላትን ያቀፈ ሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚሆኑት ምድራዊ ሕይወታቸውን አጠናቅቀዋል።
21. የታናሹን መንጋ አባላት ለመንግሥቱ ብቁ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?
21 የቀሩት የታናሹ መንጋ አባላት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ባሳለፏቸው ፈተናዎች ሲቀረጹ ቆይተዋል። ‘መንፈሱ በማያሻማ መንገድ ስለመሰከረላቸው’ ከፍተኛ ድፍረት አሳይተዋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በአሥራ ሁለቱም በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።”—ሮሜ 8:16, 17፤ ሉቃስ 12:32፤ 22:28–30
22, 23. ታናሹ መንጋና ሌሎች በጎች እየተቀረጹ ያሉት እንዴት ነው?
22 በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ ቀሪዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑ የጎለመሱ ወንድሞች በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን ሁሉንም ጉባኤዎች ማለት ይቻላል በበላይነት እንዲመሩ ሲደረግ ቆይቷል። ከቅቡዓን ምሥክሮች መካከል የመጨረሻዎቹ ምድራዊ ሕይወታቸውን በሚያጠናቅቁበት ጊዜ ደግሞ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑት መሳፍንታዊ ሳሪም በምድር ላይ የአለቃው ክፍል ሆነው አስተዳደራዊ ተግባሮቻቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ሥልጠና ያገኙ ይሆናሉ።—ሕዝቅኤል 44:3፤ ኢሳይያስ 32:1
23 ታናሹ መንጋም ሆነ ሌሎች በጎች ለክብራማ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች መሆን በሚችሉበት መንገድ መቀረጻቸውን ይቀጥላሉ። (ዮሐንስ 10:14–16) ተስፋችን የተመሠረተው ‘በአዲሱ ሰማይ’ ላይም ሆነ ‘በአዲሱ ምድር’ ለሚከተለው የይሖዋ ጥሪ በሙሉ ልባችን ምላሽ እንስጥ:- “በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ [ሰማያዊቷን] ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።” (ኢሳይያስ 65:17, 18) እኛ ደካማ የሆንነው ሰዎች ‘ከወትሮው በላቀ ኃይል’ ማለትም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ኃይል በመቀረጽ ዘወትር በትሕትና እናገልግል!—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW፤ ዮሐንስ 16:13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የጥንቷ እስራኤል ጥላ የሆነችላት ከዳተኛዋ ሕዝበ ክርስትና የዚሁ ዓይነት የይሖዋ ፍርድ ማስጠንቀቂያ ይድረሳት።—1 ጴጥሮስ 4:17, 18
b የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን በዋስ የመፈታት መብት ነፍገዋቸው የነበሩት የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ማንተን የተባሉ ዳኛ ከጊዜ በኋላ ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተከስሰው ወኅኒ ወርደዋል።
c በ1938 በዓለም ዙሪያ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች 73,420 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 39,225ቱ ማለትም 53 በመቶ የሚሆኑት ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ ተካፍለዋል። በ1998 የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 13,896,312 የደረሰ ሲሆን ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት 8,756 ብቻ ነበሩ፤ ይህም በአማካይ በ10 ጉባኤዎች ከ1 ያነሰ ተካፋይ ነበረ ማለት ነው።
[ታስታውሳለህን?]
◻ ኢየሱስ አባቱ እንዲቀርጸው ራሱን በፈቃደኝነት በማቅረብ ምሳሌ የሆነን እንዴት ነው?
◻ በጥንቱ እስራኤል ምን የመቅረጽ ሥራ ተከናውኖ ነበር?
◻ “የአምላክ እስራኤል” እስካሁን ድረስ እየተቀረጸ ያለው እንዴት ነው?
◻ “ሌሎች በጎች” ሲቀረጹ የቆዩት ለምን ዓላማ ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተካሄደ ተጨማሪ የመቅረጽ ሥራ
ከግሪክ አቴንስ ከተማ የወጣው የአሶሲየትድ ፕሬስ ሪፖርት በቅርቡ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ሆነው የተሾሙትን ሰው በተመለከተ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሰላም መልእክተኛ ይሆናሉ ተብሎ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ በይበልጥ ለውጊያ እየተዘጋጀ ያለ ጄኔራል ነው የሚመስሉት።
“ሊቀ ጳጳስ ክሪስቶዱሎስ በቅርቡ ከግሪክ ጦር ሠራዊት ቀን ጋር በአንድነት በሚከበረው ድንግል ማርያም ያረገችበት ቀን ክብረ በዓል ላይ ‘አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደማችንን ለማፍሰስና መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች ነን። ቤተ ክርስቲያናችን ለሰላም ትጸልያለች . . . ሁኔታው አስገዳጅ በሚሆንበት ጊዜ ግን ቅዱሶቹን የጦር መሣሪያዎች እንባርካለን’ ብለዋል።”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ከእንግዲህ የሚጨመር አይኖርም!”
በ1970 በተካሄደ በአንድ የጊልያድ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበረው ፍሬድሪክ ፍራንዝ ሁሉም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የሌሎች በጎች አባላት የሆኑት ተማሪዎች የቅቡዓን ቀሪዎች አባል ነኝ ሊል የሚችል ሰው ሊያጠምቁ ስለሚችሉበት አጋጣሚ ተናግሮ ነበር። ይህ ሊያጋጥም ይችላል? ወንድም ፍራንዝ መጥምቁ ዮሐንስ የሌሎች በጎች ክፍል ቢሆንም ኢየሱስንና አንዳንድ ሐዋርያትን እንዳጠመቀ ገልጿል። ከዚያም አሁንም ተጨማሪ ቀሪዎችን ለመሰብሰብ ጥሪ ይቀርብ እንደሆነና እንዳልሆነ ከጠየቀ በኋላ “ከእንግዲህ የሚጨመር አይኖርም!” ብሏል። “ይህ ጥሪ ከብዙ ጊዜ በፊት ከ1931–35 ባሉት ዓመታት አብቅቷል! ከእንግዲህ የሚጨመር አይኖርም። ታዲያ ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን ጠጅ የሚካፈሉት ጥቂት አዳዲስ ተባባሪዎች እነማን ናቸው? የቀሪዎቹ ክፍል አባላት ከሆኑ ተተኪዎች ናቸው ማለት ነው። በቀሪዎቹ ቁጥር ላይ የሚጨመሩ ሳይሆኑ ከእምነት ጎዳና በወጡት የሚተኩ ናቸው።”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውድ የሆነውን የአገልግሎት መብታችንን እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን!
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንቱ እስራኤል ከመጣል በቀር ለሌላ ለምንም የማያገለግል ዕቃ ሆኗል