ጋብቻ
ፍቺ:- ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በሰፈረው ሥርዓትና ደንብ መሠረት ባልና ሚስት ሆነው በአንድነት ለመኖር የሚመሠርቱት ውህደት ነው። ጋብቻ መለኮታዊ ተቋም ነው። በትዳር ጓደኞች መካከል የፍቅር መንፈስ ስለሚኖርና አንዱ የትዳር ጓደኛ ለሌላው አሳቢነት ለማሳየት ቃል የገባ ስለሆነ ጋብቻ በባልና በሚስት መካከል መተማመን ያለበትና የተቀራረበ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል። ይሖዋ ጋብቻን ያቋቋመው የወንድ ማሟያ የምትሆን የቅርብ ጓደኛ ለማስገኘት ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ዝግጅት አማካኝነት ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች እንዲወለዱ ሲል ነው። በሚቻልበት ቦታ ሁሉ የክርስቲያን ጉባኤ የሚቀበለው ማንኛውም ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ እንዲሆን ይፈለጋል።
ከአገሩ ሕግ ጋር የሚስማማ ጋብቻ መመሥረት አስፈላጊ ነውን?
ቲቶ 3:1:- “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ . . . እንዲሆኑ አሳስባቸው።” (ሰዎች እነዚህን መመሪያዎች ሲያከብሩ የተጋቢዎቹ ስም ከነቀፋ ይጠበቃል። የሚወለዱትም ልጆች ሕጋዊ ጋብቻ ከሌላቸው ወላጆች በሚወለዱ ልጆች ላይ ከሚደርሰው ነቀፋ ይድናሉ። በተጨማሪም ጋብቻን ሕግ በሚጠይቀው መንገድ ማስመዝገብ ከትዳር ጓደኛሞች አንዱ በሞት በሚለይበት ጊዜ የቤተሰቡን የንብረት ባለቤትነት መብት ለማስጠበቅ ይጠቅማል።)
ዕብ. 13:4:- “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።” (በሕጋዊ መንገድ መጋባቱ ጋብቻው “ክቡር” እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። ለ“ሴሰኝነት” እና ለ“ምንዝር” በምንሰጠው ትርጉም ላይ በቲቶ 3:1 ላይ የተጠቀሰውን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።)
1 ጴጥ. 2:12–15:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፣ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፣ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። በጎ እያደረጋችሁ፣ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።”
አዳምና ሔዋን አብረው መኖር ሲጀምሩ “ሕጋዊ ሥርዓት” ተፈጽሞ ነበረን?
ዘፍ. 2:22–24:- “እግዚብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ:- ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (አዳምንና ሔዋንን አንድ ላይ እንዲኖሩ ያደረገው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ አምላክ ራሱ እንደሆነ ልብ በል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ስለ ሕጋዊ ባለ ሥልጣን ሳይጨነቁ አብረው ለመኖር አልወሰኑም። የጋብቻ አንድነት ዘላቂ መሆን እንዳለበት አምላክ ጠበቅ አድርጎ የተናገረውንም ልብ በል።)
ዘፍ. 1:28:- “እግዚአብሔርም [አዳምንና ሔዋንን] ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (እዚህ ላይ የመጨረሻው ከፍተኛ ሕጋዊ ባለ ሥልጣን ጋብቻውን ባርኮታል። ሩካቤ ሥጋ እንዲፈጽሙ የተፈቀደላቸው ሲሆን ለሕይወታቸውም ትርጉም የሚሰጥ ሥራ ሰጣቸው።)
አንድ ሰው የአካባቢው ሕግ የሚፈቅድለት ከሆነ ከአንድ ሚስት በላይ ሊኖረው ይችላልን?
1 ጢሞ. 3:2, 12:- “ኤጲስ ቆጶስ [“የበላይ ተመልካች” አዓት ] . . . የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል [መሆን ይገባዋል።] . . . ዲያቆናት እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ።” (እነዚህ ወንዶች ኃላፊነት የተሰጣቸው ብቻ ሳይሆኑ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደ መልካም ምሳሌ አድርገው የሚከተሏቸው ጭምር ናቸው።)
1 ቆሮ. 7:2:- “ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ሚስት ትኑረው፣ እያንዳንዲቱም ደግሞ ለራሷ ባል ይኑራት።” (ማንኛቸውም ቢሆኑ ከአንድ በላይ ማግባት አልተፈቀደላቸውም።)
አብርሃም፣ ያዕቆብ እና ሰሎሞን እያንዳንዳቸው ከአንድ በላይ ሚስት እንዲኖራቸው አምላክ ለምን ፈቀደ?
ብዙ ሚስት የማግባትን ሥርዓት ያቋቋመው አምላክ አልነበረም። አምላክ ለአዳም የሰጠው አንዲት ሚስት ብቻ ነበር። ከጊዜ በኋላ የቃየን ተወላጅ የነበረው ላሜህ ሁለት ሚስቶች አገባ። (ዘፍ. 4:19) ውሎ አድሮ ሌሎችም የእርሱን ምሳሌ ተከተሉ፣ አንዳንዶችም ገረዶቻቸውን ቁባት አደረጉ። አምላክ ይህን አድራጎት ዝም ብሎ ተመልክቶታል። እንዲያውም እንዲህ ባለ ግንኙነት ለተሳሰሩ ሴቶች ተገቢ አያያዝ እንዲደረግላቸው የሚያዙ ደንቦች በሙሴ ሕግ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል። ይህን ያደረገው ግን የክርስቲያን ጉባኤ እስከሚቋቋም ድረስ ነበር። ከዚያ በኋላ አገልጋዮቹ እርሱ ራሱ በኤደን ውስጥ አቋቁሞት ወደነበረው ሥርዓት እንዲመለሱ አድርጓል።
አብርሃም ሦራን (ሣራን) ሚስት አድርጎ ወሰዳት። ሦራ ዕድሜዋ 75 ዓመት በሆነ ጊዜ ከዚያ በኋላ ልጅ እንደማትወልድ አስባ በገረድዋ በኩል ሕጋዊ ልጅ ለማግኘት ባልዋ ከገረድዋ ጋር ግንኙነት እንዲያደርግ ራሷ ጠየቀችው። አብርሃምም እንዳለችው አደረገ። ይሁን እንጂ በዚህ ሳቢያ በቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል። (ዘፍ. 16:1–4) ይሖዋ ለአብርሃም “ዘር” እንደሚሰጠው የገባውን ቃል ኪዳን ሣራ በተአምር እንድትፀንስ በማድረግ ፈጽሞአል። (ዘፍ. 18:9–14) ሣራ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ አብርሃም ሌላ ሚስት አላገባም።—ዘፍ. 23:2፤ 25:1
ያዕቆብ ከአንድ ሚስት በላይ ያገባው አማቱ ስላታለለው ነበር። ሚስት ለመፈለግ ወደ ፓዳንኤራም (ሜሶጶጣሚያ) በሄደ ጊዜ ከአንድ በላይ የማግባት ፍላጎት በሐሳቡ ውስጥ አልነበረም። በያዕቆብ ሚስቶች መካከል ደስታቸውን የሚያጠፋ ምቀኝነት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል።—ዘፍ. 29:18–30:24
ሰሎሞን ብዙ ሚስቶችና ቁባቶች እንደነበሩት የታወቀ ነው። ነገር ግን ይህን በማድረጉ ንጉሡ “ልቡ እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያበዛም ” የሚለውን የይሖዋን ግልጽ ትእዛዝ እንደጣሰ ብዙ ሰዎች አይገነዘቡም። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ዘዳ. 17:17) ሰሎሞን ከባዕድ አገሮች ባገባቸው ሚስቶቹ ተጽዕኖ ምክንያት የሐሰት አማልክትን አመለከ፣ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። . . . እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቆጣ።”—1 ነገ. 11:1–9
የትዳር ጓደኛሞች በሰላም አብረው መኖር ካልቻሉ ተለያይተው እንዲኖሩ ይፈቀዳልን?
1 ቆሮ. 7:10–16:- “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፣ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፣ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፣ እኔ ግን አላዝም ጌታ እንጂ። ሌሎችንም እኔ እላለሁ፣ ጌታም አይደለም፤ [ቁጥር 40 እንደሚያሳየው ጳውሎስ ይህን የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ነበር።] ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት፤ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፣ አትተወው። ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፣ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኩሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። አንቺ ሴት፣ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ፣ አንተ ሰው ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?” (አማኙ ወገን ችግሮችን በመታገሥ ጋብቻው ጸንቶ እንዲኖር ከልብ መጣር ያለበት ለምንድን ነው? ይህን የሚያደርገው የጋብቻን መለኮታዊ አመጣጥ በማክበርና የማያምነው ወገን ከጊዜ በኋላ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ ለመሆን ይችል ይሆናል በሚል ተስፋ ነው።)
ሌላ ለማግባት ሲባል ስለሚፈጸም ፍቺ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
ሚል. 2:15, 16:- “መንፈሳችሁን ጠብቁ፣ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጠላለሁ፣ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።”
ማቴ. 19:8, 9:- “እርሱም [ኢየሱስ]:- ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያለ ዝሙት ምክንያት [በጋብቻ ላይ የሚፈጸም የሩካቤ ሥጋ ውስልትና] ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል አላቸው።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ንጹሕ የሆነው የትዳር ጓደኛ “ዝሙት” የፈጸመውን ወገን ለመፍታት ተፈቅዶለታል፣ ሆኖም ግን የግድ መፍታት አለበት ማለት አይደለም።)
ሮሜ 7:2, 3:- “ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች። ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም።”
1 ቆሮ. 6:9–11:- “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ [ወንዶች] . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።” (ይህ መግለጫ የጉዳዩን ክብደት ያጎላል። ንስሐ የማይገቡ አመንዝሮች በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ የላቸውም። ይሁን እንጂ ቀደም ብለው ምንዝር የፈጸሙ፣ ምናልባትም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሁለተኛ ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች ከልብ ንስሐ ከገቡና ኃጢአት በሚያስተሠርየው የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ዋጋ ካመኑ የአምላክን ይቅርታ ሊያገኙና በአምላክ ዘንድ ንጹሕ አቋም ሊይዙ ይችላሉ።)
በድሮ ጊዜ በወንድምና በእህት መካከል ይደረግ የነበረውን ጋብቻ አምላክ ለምን ፈቀደ?
ቃየን ከእህቶቹ አንዷን (ዘፍ. 4:17፤ 5:4) (ወይም የወንድሙን ልጅ ሊሆን ይችላል) እንዳገባ አብርሃም ደግሞ በግማሽ እህቱ የሆነችውን እንዳገባ (ዘፍ. 20:12) መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ በሙሴ በኩል በተሰጠው ሕግ ላይ ይህን የመሰለው ጋብቻ በግልጽ ተጠቅሶ ተከልክሏል። (ዘሌ. 18:9, 11) ዛሬም በክርስቲያኖች መካከል አይፈቀድም። በቅርብ ዘመዳሞች መካከል ከሚደረግ ጋብቻ በሚወለዱ ልጆች ላይ በዘር የሚተላለፉ ጐጂ ነገሮች የመድረሳቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው።
የሰው ልጅ ታሪክ በጀመረበት ጊዜ ላይ የወንድምና እህት ጋብቻ ስህተት ያልነበረው ለምን ነበር? አምላክ አዳምንና ሔዋንን ፍጹም አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ የሰው ዘር በሙሉ ከእነርሱ እንዲገኝ አስቦ ነበር። (ዘፍ. 1:28፤ 3:20) በዚህ መሠረት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ትውልዶች ውስጥ የቅርብ ዘመዳሞች ጋብቻ እንደሚኖር ግልጽ ነው። ሰብዓዊው ዘር አዳምና ሔዋን ለነበራቸው ፍጽምና ቅርብ ስለነበር ኃጢአት ከመጣም በኋላ ቢሆን በመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ላይ ይህ ዓይነቱ ጋብቻ አካለ ጐደሎነት ለማድረስ የነበረው አደጋ እምብዛም አልነበረም። ይህም በዚያን ጊዜ ይኖሩ በነበሩት ሰዎች የዕድሜ ርዝማኔ ተረጋግጧል። (ዘፍጥረት 5:3–8፤ 25:7ን ተመልከት።) አዳም ኃጢአት ከሠራ ከ2,500 ዓመታት በኋላ ግን አምላክ የሥጋ ዘመዳሞች እንዳይጋቡ ከለከለ። ይህም በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚደረገው ጋብቻ በሚወለዱት ልጆች ላይ የሚያስከትለውን አካለ ጐደሎነት ለመከልከል ከማገልገሉም በላይ የአምላክ አገልጋዮች የፆታ ሥነ ምግባር ንጽሕና በዚያን ጊዜ አስነዋሪ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ከነበሩት በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ የተሻለ አቋም እንዲኖራቸው አስችሏል።—ዘሌዋውያን 18:2–18ን ተመልከት።
ትዳርን ለማሻሻል ምን ነገሮች ሊረዱ ይችላሉ?
(1) አዘውትሮ የአምላክን ቃል አንድ ላይ ማጥናትና ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዳቸው ወደ አምላክ መጸለይ።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵ. 4:6, 7
(2) የራስነትን ሥርዓት በደስታ መቀበል። ይህ በባል ላይ ከባድ ኃላፊነት ይጭናል። (1 ቆሮ. 11:3፤ ኤፌ. 5:25–33፤ ቆላ. 3:19) ሚስትም ከልብ ጥረት እንድታደርግ ይጠይቅባታል።—ኤፌ. 5:22–24, 33፤ ቆላ. 3:18፤ 1 ጴጥ. 3:1–6
(3) የፆታ ፍላጎትን ከትዳር ጓደኛ ጋር ብቻ ማርካት (ምሳሌ 5:15–21፤ ዕብ. 13:4) ለትዳር ጓደኛ ችግር ከልብ ማሰብ መጥፎ ለመሥራት ከሚገፋፋ ፈተና ይጠብቃል።—1 ቆሮ. 7:2–5
(4) በደግነትና በአሳቢነት እርስ በርስ መነጋገር፤ ከንዴትና ከጩኸት መራቅ፤ ንዝነዛንና የነቀፌታ ንግግርን ማስወገድ።—ኤፌ. 4:31, 32፤ ምሳሌ 15:1፤ 20:3፤ 21:9፤ 31:26, 28
(5) ታታሪ መሆን፤ ባልና ሚስት ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን መኖሪያና ልብስ እንዲሁም ለጤና የሚስማማ ምግብ በማቅረብ በኩል እምነት የሚጣልባቸው ሆነው መገኘት።—ቲቶ 2:4, 5፤ ምሳሌ 31:10–31
(6) ሌላው ወገን መሥራት የሚገባውን ሁሉ እንደሠራ ቢሰማችሁም ባይሰማችሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በትሕትና በተግባር ማዋል።—ሮሜ 14:12፤ 1 ጴጥ. 3:1, 2
(7) ትኩረት ሰጥቶ የግል መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበር።—1 ጴጥ. 3:3–6፤ ቆላ. 3:12–14፤ ገላ. 5:22, 23
(8) ልጆች ካሉ የሚያስፈልጋቸውን ፍቅር፣ ትምህርትና ማሰልጠኛ መስጠት።—ቲቶ 2:4፤ ኤፌ. 6:4፤ ምሳሌ 13:24፤ 29:15