በይሖዋ እጅ ያሉ ዘመናትና ወቅቶች
“አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም።”—ሥራ 1:7
1. ኢየሱስ ሐዋርያቱ ላቀረቡለት በጊዜ ላይ ላተኮሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?
በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እና በመላው ምድር ላይ ‘በሚሠራው ርኩሰት ሁሉ ለሚያለቅሱና ለሚተክዙ’ ሰዎች ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትና በአምላክ ጻድቅ አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ከመጠየቅ ሌላ የሚያሳስባቸው ነገር ይኖራልን? (ሕዝቅኤል 9:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊትና ከሞት ከተነሣም በኋላ ሐዋርያቱ በጊዜ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3፤ ሥራ 1:6) ይሁንና ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መልስ የሰጠው ቀናትን ለማስላት የሚችሉበትን መንገድ በመንገር አይደለም። በአንድ በኩል ጥምር የሆነ ምልክት ሲሰጣቸው በሌላ በኩል ደግሞ ‘አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ዘመናትንና ወራትን ያውቁ ዘንድ ለእነሱ እንዳልተሰጣቸው’ ነግሯቸዋል።—ሥራ 1:7
2. ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸሙትን ነገሮች በተመለከተ አባቱ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ ሁልጊዜ ያውቅ ነበር ለማለት የማይቻለው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ምንም እንኳ የይሖዋ አንድያ ልጅ ቢሆንም አባቱ ነገሮችን የሚያስፈጽምበትን የጊዜ ሰሌዳ ሁሉ ያውቅ ነበር ማለት አይደለም። ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት በተናገረው ትንቢት ላይ ኢየሱስ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ሲል በትሕትና አምኗል። (ማቴዎስ 24:36) ኢየሱስ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የጥፋት እርምጃ የሚወሰድበትን ትክክለኛ ጊዜ አባቱ እስኪነግረው ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር።a
3. ኢየሱስ ስለ አምላክ ዓላማዎች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ከሰጣቸው መልሶች ምን ልንማር እንችላለን?
3 ኢየሱስ ከአምላክ ዓላማ ፍጻሜ ጋር የተያያዙ ነገሮች የሚከሰቱበትን ጊዜ በተመለከተ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ከመለሰበት መንገድ ሁለት ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል። አንደኛ፣ ይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ እንዳለው፤ ሁለተኛ ደግሞ የጊዜ ሰሌዳውን የሚያወጣው እሱ ብቻ መሆኑንና አገልጋዮቹ ዘመናቱ ወይም ወቅቶቹ በትክክል መቼ እንደሆኑ አስቀድሞ ሊነግረን ይገባል ብለው ሊጠብቁ እንደማይችሉ መገንዘብ ይቻላል።
ይሖዋ የወሰናቸው ዘመናትና ወቅቶች
4. በሥራ 1:7 ላይ ‘ዘመናት’ እና ‘ወቅቶች’ ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት ትርጉማቸው ምንድን ነው?
4 ‘ዘመናት’ እና ‘ወቅቶች’ የሚሉት ቃላት ምን ያመለክታሉ? በሥራ 1:7 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የጊዜን ሁለት ገጽታዎች የያዙ ናቸው። ‘ዘመናት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (አጭርም ይሁን ረዥም) “የተወሰነን የጊዜ ርዝመት” ለማመልከት የገባ ነው። ‘ወቅቶች’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ደግሞ በተወሰኑ ክንውኖች ተለይቶ የሚታወቅን አንድን የተወሰነ ጊዜ ወይም አንድን የተለየ ወቅት የሚያመለክት ነው። እነዚህን ሁለት በኩረ ቃላት አስመልክተው ደብሊው ኢ ቫይን እንዲህ ብለዋል:- “በሥራ 1:7 ላይ ‘አብ በራሱ ሥልጣን’ ዘመናቱን (ክሮኖስ) ማለትም የጊዜያቱን ርዝመትና በተወሰኑ ክንውኖች ተለይተው የሚታወቁትን ወቅቶች (ካይሮስ) ርዝመት ወስኗል።”
5. ይሖዋ ያንን ብልሹ ዓለም የማጥፋት ዓላማ እንዳለው ለኖኅ የነገረው መቼ ነበር? ኖኅስ ምን ድርብ ተልእኮ አከናውኗል?
5 አምላክ ሰዎችና ሥጋ የለበሱ ዓመፀኛ መላእክት ያመጡትን ብልሹ ዓለም በውኃ ከማጥፋቱ በፊት የ120 ዓመት የጊዜ ገደብ ሰጥቶ ነበር። (ዘፍጥረት 6:1–3) የአምላክ ሰው የነበረው ኖኅ በዚህን ጊዜ ዕድሜው 480 ዓመት ነበር። (ዘፍጥረት 7:6) በዚያን ጊዜ ልጅ ያልወለደ ሲሆን በዚህ ዓይነት ሁኔታም ለሌላ 20 ዓመታት ኖሯል። (ዘፍጥረት 5:32) የኖኅ ልጆች ለአቅመ አዳም ከደረሱና ካገቡ በኋላ አምላክ ክፋትን ከምድር የማጥፋት ዓላማ እንዳለው ለኖኅ ነገረው። (ዘፍጥረት 6:9–13, 18) ኖኅ መርከብ የመሥራትና በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች የመስበክ ድርብ ተልእኮ ቢሰጠውም እንኳ ይሖዋ የጊዜ ፕሮግራሙን አልገለጠለትም።—ዘፍጥረት 6:14፤ 2 ጴጥሮስ 2:5
6. (ሀ) ኖኅ ጊዜን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በይሖዋ እጅ ላይ እንደተወ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) የኖኅን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
6 ለአሥርተ ዓመታት፣ ምናልባትም ለግማሽ ምዕተ ዓመት “[ኖኅ] እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ [አድርጓል]።” ኖኅ ይህን ያደረገው ትክክለኛውን ቀን ሳያውቅ “በእምነት” ነበር። (ዘፍጥረት 6:22፤ ዕብራውያን 11:7) ይሖዋ የጥፋት ውኃው ሊጀምር አንድ ሳምንት እስኪቀረው ድረስ ሁኔታዎቹ የሚፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜ አልነገረውም። (ዘፍጥረት 7:1–5) ኖኅ በይሖዋ ላይ የነበረው የማያወላውል ትምክህትና እምነት የጊዜ ጉዳዮችን በአምላክ እጅ እንዲተዋቸው አስችሎታል። እንዲሁም ኖኅ በጥፋት ውኃው ጊዜ የይሖዋን ጥበቃ ማግኘቱና በኋላም ከመርከቡ ወጥቶ በጸዳች ምድር ላይ ለመኖር መቻሉ ምንኛ በአመስጋኝነት መንፈስ እንዲሞላ አድርጎት ይሆን! እኛም በተመሳሳይ ከጥ ፋት ለመትረፍ ተስፋ የምናደርግ እንደመሆናችን መጠን በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት እንዳለን ልናሳይ አይገባም?
7, 8. (ሀ) ብሔራትና የዓለም ኃይላት ሕልውና ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነበር? (ለ) ይሖዋ ‘የተወሰኑትን ዘመኖችና የሚኖሩበትን ስፍራ ለሰዎች የመደበላቸው’ በምን መንገድ ነበር?
7 ከጥፋት ውኃ በኋላ አብዛኞቹ የኖኅ ዘሮች እውነተኛውን የይሖዋ አምልኮ እርግፍ አድርገው ተዉ። በአንድ ቦታ ሰፍሮ መቆየትን ዓላማ በማድረግ ለሐሰት አምልኮ የሚሆን ከተማና ግንብ መሥራት ጀመሩ። ይሖዋ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልገው ወሰነ። ቋንቋቸውን በመደባለቅ “[ከባቢሎን] በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው።” (ዘፍጥረት 11:4, 8, 9) ከጊዜ በኋላ እነዚህ በቋንቋ የተከፋፈሉ ቡድኖች የየራሳቸውን ብሔራት መሠረቱ፤ አንዳንዶቹ ሌሎች ብሔራትን በመዋጥ የአካባቢያቸውና ሌላው ቀርቶ የዓለም ኃያላን ሆኑ።—ዘፍጥረት 10:32
8 አምላክ ከዓላማው መፈጸም ጋር በሚስማማ መንገድ አንዳንድ ጊዜ ብሔራዊ ድንበሮችን የወሰነበት ጊዜ ነበር፤ እንዲሁም በጊዜ ሂደት ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ አንድ የሆነ መንግሥት የአካባቢው ወይም የዓለም ኃያል እንዲሆን አድርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 15:13, 14, 18–21፤ ዘጸአት 23:31፤ ዘዳግም 2:17–22፤ ዳንኤል 8:5–7, 20, 21) ሐዋርያው ጳውሎስ በግሪኳ አቴንስ ለሚገኙ ምሁራን እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ይሖዋ ስለወሰናቸው ስለነዚህ ዘመናትና ወቅቶች ገጽታ ገልጿል:- “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ . . . በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው።”—ሥራ 17:24, 26
9. ይሖዋ ነገሥታትን በተመለከተ ‘ዘመናትንና ወቅቶችን’ የለወጠው እንዴት ነው?
9 ይህ ማለት ግን ብሔራት ፖለቲካዊ ድል የሚያገኙትና ለውጦችን የሚያደርጉት በይሖዋ አማካኝነት ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ዓላማውን ለማስፈጸም ሲል በፈለገው ጊዜ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። በመሆኑም ባቢሎናዊው የዓለም ኃይል ሲደመሰስና በሜዶ ፋርስ ሲተካ ያየው ነቢዩ ዳንኤል ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፣ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።”—ዳንኤል 2:21፤ ኢሳይያስ 44:24—45:7
“ዘመኑ ሲቃረብ”
10, 11. (ሀ) ይሖዋ የአብርሃምን ዘሮች ከባርነት ነፃ የሚያወጣበትን ጊዜ የወሰነው ከምን ያህል ጊዜ በፊት ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ነፃ የሚወጡበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደማያውቁ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
10 ከአራት ምዕተ ዓመታት ከሚበልጡ ጊዜያት በፊት ይሖዋ የግብጹን የዓለም ኃይል የሚያጠፋበትንና የአብርሃምን ዘሮች ነፃ የሚያወጣበትን ትክክለኛ ዓመት ወስኖ ነበር። ዓላማውን ለአብርሃም በመግለጽ አምላክ እንዲህ ሲል ቃል ገባ:- “ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ።” (ዘፍጥረት 15:13, 14) እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀርቦ የእስራኤልን ታሪክ አጠር አድርጎ በገለጸበት ጊዜ ስለዚህ 400 ዓመት ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፣ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፣ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ።”—ሥራ 7:6, 17, 18
11 ይህ አዲስ ፈርዖን እስራኤላውያንን አዋርዶ ባሪያ አደረጋቸው። ይሖዋ ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ በቃል ወይም በጽሑፍ እንደተላለፈ የታወቀ ቢሆንም ሙሴ የዘፍጥረትን መጽሐፍ ገና አልጻፈም ነበር። ያም ሆኖ ግን እስራኤላውያን የነበራቸው መረጃ ከጭቆና ነፃ የሚወጡበትን ትክክለኛ ቀን ለማስላት የረዳቸው አይመስልም። አምላክ መቼ ነፃ እንደሚያወጣቸው ቢያውቅም በመከራ ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ግን ምንም የተነገራቸው ነገር አልነበረም። እንዲህ እናነባለን:- “ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፣ ጮኹም፣ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የልቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፣ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።”—ዘጸአት 2:23–25
12. ሙሴ እርምጃ የወሰደው ይሖዋ ከቀጠረው ጊዜ ቀድሞ መሆኑን እስጢፋኖስ የገለጸው እንዴት ነበር?
12 እስራኤላውያን ነፃ የሚወጡበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደማያውቁ ከእስጢፋኖስ መግለጫም መገንዘብ ይቻላል። ስለ ሙሴ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፣ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፣ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።” (ሥራ 7:23-25፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሙሴ እርምጃ ለመውሰድ የተነሣው አምላክ ከቀጠረው ጊዜ 40 ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር። እስጢፋኖስ ‘አምላክ በእጁ ለእስራኤላውያን መዳንን እስኪሰጥ’ ድረስ ሙሴ ሌላ 40 ዓመት መጠበቅ እንደነበረበት አመልክቷል።—ሥራ 7:30–36
13. እኛ ያለንበት ሁኔታ እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ ከመውጣታቸው በፊት ከነበሩበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
13 ‘ተስፋው የሚፈጸምበት ዘመን ቀርቦ’ የነበረና ይህ የሚሆንበትን ዓመት አምላክ የወሰነ ቢሆንም ሙሴም ሆነ መላው የእስራኤል ሕዝብ እምነት ማሳየት ነበረበት። ጊዜውን አስቀድመው ለማስላት ስለማይችሉ ይሖዋ የወሰነውን ጊዜ መጠበቅ ነበረባቸው። እኛም ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ነፃ የምንወጣበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን የሚያረጋግጡልን አሳማኝ ማስረጃዎች አግኝተናል። ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደምንኖር እናውቃለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) እምነታችንን ለማሳየትና ይሖዋ ለታላቅ ቀኑ የቀጠረውን ጊዜ ለመጠባበቅ ፈቃደኝነታችንን ማሳየት አይገባንምን? (2 ጴጥሮስ 3:11–13) ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን እንዳደረጉት ይሖዋን ለማወደስ ክብራማ የሆነ የነፃነት መዝሙር እንዘምራለን።—ዘጸአት 15:1–19
‘ዘመኑ በደረሰ ጊዜ’
14, 15. አምላክ ልጁ ወደ ምድር የሚመጣበትን ጊዜ ወስኖ እንደነበር እንዴት እናውቃለን? ነቢያት፣ ሌላው ቀርቶ መላእክት ጭምር በንቃት ይጠባበቁ የነበሩት ነገር ምንድን ነው?
14 ይሖዋ አንድያ ልጁ መሲሕ ሆኖ ወደ ምድር የሚመጣበትን ጊዜ ወስኖ ነበር። ጳውሎስ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 4:4) አምላክ ይህን ያደረገው አንድ ዘር ማለትም ‘ሴሎ ተብሎ የሚጠራውንና ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለትን’ ለመላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነበር።—ዘፍጥረት 3:15፤ 49:10 የ1980 ትርጉም
15 የአምላክ ነቢያት፣ ሌላው ቀርቶ መላእክት ጭምር መሲሑ በምድር ላይ የሚገለጥበትንና ለኃጢአተኛው የሰው ዘር መዳንን የሚያስገኝበትን “ወቅት” በንቃት ይከታተሉ ነበር። ጴጥሮስ እንዲህ አለ:- “ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፣ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፣ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። . . . ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።”—1 ጴጥሮስ 1:1–5, 10–12
16, 17. (ሀ) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን መሲሑን እንዲጠባበቁ የረዳቸው በየትኛው ትንቢት አማካኝነት ነበር? (ለ) የዳንኤል ትንቢት አይሁዶች መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ በተመለከተ ምን አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል?
16 ይሖዋ ጠንካራ እምነት በነበረው በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት ‘ሰባ ሱባዔን’ የሚመለከት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መምጫ መቃረቡን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አይሁዳውያን ሊያሳውቃቸው ይችል ነበር። ትንቢቱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል።” (ዳንኤል 9:24, 25) የአይሁድ፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ምሁራን እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ሱባዔ” (ሳምንታት) የዓመታት ሱባዔዎችን እንደሚያመለክቱ በአንድ ድምፅ ይስማማሉ። በዳንኤል 9:25 ላይ የተጠቀሱት 69 “ሳምንታት” (483 ዓመታት) የጀመሩት በ455 ከዘአበ ንጉሥ አርጤክስስ ለነህምያ ‘ኢየሩሳሌምን እንዲጠግንና እንዲሠራ’ ሥልጣን በሰጠው ጊዜ ነበር። (ነህምያ 2:1–8) እነዚህ ዓመታት ያበቁት ከ483 ዓመታት በኋላ በ29 እዘአ ኢየሱስ በተጠመቀና በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ መሲሕ ወይም ክርስቶስ በሆነ ጊዜ ነበር።—ማቴዎስ 3:13–17
17 የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶች እነዚህ 483 ዓመታት የጀመሩበትን ትክክለኛ ጊዜ ይወቁ አይወቁ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ “ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ:- ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር።” (ሉቃስ 3:15) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አይሁዶች መሲሑ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብለው ሊጠባበቁ የቻሉት በዳንኤል ትንቢት ምክንያት ነው ይላሉ። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ ማቲው ሄንሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሕዝቡ ዮሐንስ ያከናውን ከነበረው አገልግሎትና ጥምቀት ስለ መሲሑ ማሰብ እንደጀመሩና በቅርቡ ይመጣል ወደሚል መደምደሚያ እንዴት እንደደረሱ እየተነገረን ነው። . . . የዳንኤል ሰባ ሳምንታት እያበቁ ነበር።” በቪጉሩ፣ ባክዌ እና ብራሳክ በፈረንሳይኛ የተዘጋጀው ማኑኤል ቢብሊክ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች በዳንኤል የተወሰኑት ሰባ የዓመታት ሳምንታት እየተገባደዱ መሆናቸውን አውቀው ስለነበር ዮሐንስ መጥምቁ የአምላክ መንግሥት መቅረቡን ሲናገር የተደነቀ ሰው አልነበረም።” አይሁዳዊው ምሁር አባ ሂለል ሲልቨር እንደጻፉት በጊዜው “ታዋቂ በነበረው የዘመን አቆጣጠር” መሠረት “መሲሑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ሁለተኛ ሩብ አካባቢ ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።”
በጊዜ ስሌቶች ላይ ሳይሆን በክንውኖች ላይ ተመሥርቶ ማመን
18. አይሁዳውያን መሲሑ የሚመጣበትን ወቅት ለመረዳት የዳንኤል ትንቢት ቢረዳቸውም የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጠው ከሁሉ የሚበልጠው ማስረጃ ምን ነበር?
18 የዘመናት ስሌቱ የአይሁድ ሕዝብ መሲሑ ስለሚመጣበት ወቅት አጠቃላይ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ቢረዳቸውም ተከታታይ የሆኑ ክንውኖች እንደሚያሳዩት የዘመናት ስሌቱ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው አልቻለም። ኢየሱስ ሊሞት ከአንድ ዓመት ያነሠ ጊዜ ሲቀረው ደቀ መዛሙርቱን “ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነሱም “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም:- ኤልያስ፣ ሌሎችም:- ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ” ብለው መለሱለት። (ሉቃስ 9:18, 19) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማስረዳት ሲል ስለ ምሳሌያዊዎቹ ሳምንታት የሚናገረውን ትንቢት መጥቀሱን የሚያመለክት ምንም ዘገባ የለም። ሆኖም በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር:- “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፣ ይህ የማደርገው ሥራ፣ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።” (ዮሐንስ 5:36) በግልጽ ከተቀመጠ የዘመናት ስሌት ይልቅ የኢየሱስ ስብከት፣ ተአምራቱና በሞቱ ዙሪያ የተከናወኑ ነገሮች (ተአምራዊው ጨለማ፣ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ መቀደድና የመሬት መንቀጥቀጥ መሆኑ) በአምላክ የተላከ መሲሕ መሆኑን መስክረዋል።—ማቴዎስ 27:45, 51, 54፤ ዮሐንስ 7:31፤ ሥራ 2:22
19. (ሀ) ክርስቲያኖች የኢየሩሳሌም ጥፋት ቅርብ መሆኑን የሚያውቁት እንዴት ነበር? (ለ) የቀድሞ ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ጥለው ለመሸሽ ከፍተኛ እምነት የጠየቀባቸው ለምንድን ነው?
19 በተመሳሳይም ከኢየሱስ ሞት በኋላ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መጪውን የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ለማስላት የሚያስችላቸው ምንም ነገር አልተሰጣቸውም። እርግጥ ዳንኤል ስለ ምሳሌያዊዎቹ ሳምንታት የተናገረው ትንቢት ስለዚያ ሥርዓት መውደም ይጠቅስ ነበር። (ዳንኤል 9:26, 27) ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው ‘ሰባዎቹ ሳምንታት’ (455 ከዘአበ–36 እዘአ) ካበቁ በኋላ ነበር። በሌላ አነጋገር በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ የተጠቀሰው የዘመናት ስሌት የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ የኢየሱስ ተከታዮች ከሆኑበት ከ36 እዘአ በኋላ የሚፈጸሙ ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ ለማስላት የሚያስችላቸውን ፍንጭ ለክርስቲያኖች አይሰጥም። የአይሁድ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚያበቃ የሚያመለክታቸው የዘመናት ስሌት ሳይሆን በመፈጸም ላይ ያሉ ክንውኖች ነበሩ። የሮማ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ቦታውን ለቅቆ ሲሄድ እነዚህ በኢየሱስ የተተነበዩ ክንውኖች ከ66 እዘአ ጀምሮ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነበር። ይህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ታማኝና ንቁ ክርስቲያኖች ‘ወደ ተራሮች የሚሸሹበትን’ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 21:20–22) እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት የዘመናት ስሌት ምልክት ስላልነበራቸው የኢየሩሳሌም ጥፋት መቼ እንደሚመጣ አላወቁም። ቤታቸውን፣ እርሻቸውንና የመሥሪያ ቦታቸውን ትተው ለመውጣትና የሮማ ሠራዊት ከአራት ዓመት በኋላ በ70 እዘአ ተመልሶ እስኪመጣና የአይሁድን ሥርዓት እስኪደመስስ ድረስ ከኢየሩሳሌም ውጪ ለመቆየት እንዴት ያለ ከፍተኛ እምነት ጠይቆባቸው ይሆን!—ሉቃስ 19:41–44
20. (ሀ) ከኖኅ፣ ከሙሴና በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ከነበሩ ክርስቲያኖች ምሳሌ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንወያየው ስለ ምን ነገር ነው?
20 እንደ ኖኅ፣ ሙሴና በይሁዳ እንደነበሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እኛም ዛሬ ዘመናትንና ወቅቶችን በትምክህት በይሖዋ እጅ ላይ ልንተዋቸው እንችላለን። በመጨረሻው ዘመን እንደምንኖርና ነፃ የምንወጣበት ጊዜ መቅረቡን ማመናችን የተመካው በዘመናት ስሌት ላይ ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ በሆኑ እውነተኛ ክንውኖች ላይ ነው። ከዚህም በላይ ክርስቶስ በተገኘበት ጊዜ ብንኖርም እምነት ማሳየትና ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጹትን እጅግ አስደሳች ክንውኖች በከፍተኛ ጉጉት መጠባበቃችንን መቀጠል አለብን። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጠበቂያ ግንብ፣ ነሐሴ 1, 1996 ገጽ 30–1 ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
◻ ይሖዋ የወሰናቸውን ዘመናትና ወቅቶች በተመለከተ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ምን ብሏቸው ነበር?
◻ ኖኅ የጥፋት ውኃ የሚጀምርበትን ጊዜ ያወቀው ምን ያህል ቀደም ብሎ ነበር?
◻ ሙሴና እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ የሚወጡበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደማያውቁ የሚያሳየው ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ስለወሰናቸው ዘመናትና ወቅቶች ከሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኖኅ እምነት የጊዜ ጉዳዮችን በይሖዋ እጅ ላይ እንዲተዋቸው አስችሎታል