ውስጥህ የሚያሰማውን ድምፅ አዳምጥ
‘[የአምላክ] ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ያደርጋሉ።’—ሮሜ 2:14
1, 2. (ሀ) ብዙዎች ለሌሎች አሳቢነት ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ረገድ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች መጥቀስ እንችላለን?
የሚጥል በሽታ ያለበት አንድ የ20 ዓመት ወጣት ባቡር በመጠባበቅ ላይ እያለ ተንቀጥቅጦ ሐዲዱ ላይ ወደቀ። ይህን የተመለከተ በአቅራቢያው ያለ አንድ ሰው ሁለት ሴት ልጆቹን ጥሎ ወደ ባቡር ሐዲዱ ዘሎ ገባ። ከዚያም የወደቀውን ወጣት ጎትቶ በሐዲዶቹ መሃል ካስገባው በኋላ በላያቸው የሚያልፈው ባቡር እንዳይጎዳው እላዩ ላይ ተኛበት። አንዳንዶች ይህን ሰው ጀግና ብለው የጠሩት ቢሆንም እሱ ግን እንዲህ ብሏል:- “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል። ይህን ያደረግሁት ወጣቱ ስላሳዘነኝ እንጂ ዝና ወይም ክብር ለማግኘት አይደለም።”
2 አንተም፣ ሌሎችን ለመርዳት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ የጣለ ሰው ታውቅ ይሆናል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙ ሰዎች የማያውቋቸውን ሰዎች ቤታቸው በመሸሸግ እንዲህ አድርገዋል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስና 275 ሰዎች በሲሲሊ አቅራቢያ በምትገኘው በመላጥያ መርከባቸው በተሰበረ ጊዜ ያጋጠማቸውን ሁኔታ አስታውስ። የአካባቢው ነዋሪዎች የማያውቋቸውን ሰዎች በመርዳት “የሚያስገርም ደግነት” አሳዩአቸው። (የሐዋርያት ሥራ 27:27 እስከ 28:2) ስለ እስራኤላዊቷ ልጃገረድስ ምን ማለት ይቻላል? ሕይወቷን አደጋ ላይ ባትጥልም እንኳ በምርኮ ከወሰዷት ሶርያውያን መካከል ለአንዱ ጥልቅ አሳቢነት አሳይታለች። (2 ነገሥት 5:1-4) እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን የኢየሱስ ምሳሌ አስብ። ካህኑና ሌዋዊው በሞትና በሕይወት መካከል የነበረውን ወገናቸውን አይተው እንዳላዩ ሆነው አልፈውታል። ሳምራዊው ግን ሰውየውን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ይህ ምሳሌ በተለያዩ ዘመናት የኖሩና ልዩ ልዩ ባሕል ያላቸውን ሰዎች ልብ ነክቷል።—ሉቃስ 10:29-37
3, 4. ብዙ ሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ ያላቸው መሆኑ ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ምን ይነግረናል?
3 የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ መሆኑ እሙን ነው፤ ብዙዎች “ጨካኞች” እና “መልካም የሆነውን የማይወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) ያም ሆኖ በደግነት ተነሳስተው መልካም የሚያደርጉ ሰዎችን እንደምናውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባት እኛም የሌሎችን ደግነት በሕይወታችን ቀምሰን ይሆናል። መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ እጅግ የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶች ይህንን ድርጊት “ሰብዓዊነት” በማለት ይጠሩታል።
4 መሥዋዕትነት ቢጠይቅም እንኳ ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ የመሆን ዝንባሌ በሁሉም ዘርና ባሕል ውስጥ ይታያል። በመሆኑም ይህ ሁኔታ ሰው የሚመራው ‘በጫካ ሕግ’ ነው ወይም ማንኛውም ፍጥረት የሚጣጣረው የራሱን ሕይወት ለማቆየት ነው ከሚለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ይጋጫል። ፍራንሲስ ኮሊንስ የተባሉ የጂን ተመራማሪ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ፣ ለዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። . . . የራሳቸውን ሕይወት ለማራዘም የሚጥሩት ራስ ወዳድ የሆኑ የሰው ልጅ ጂኖች ይህ ዝንባሌ ሊኖራቸው አይችልም።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “አንዳንዶች የእነሱ ወገን ያልሆነን ወይም ምንም የሚያመሳስላቸው ነገር የሌላቸውን ሰው ለመርዳት ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። . . . የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ለዚህ ሁኔታ ማብራሪያ መስጠት የሚችል አይመስልም።”
“የሕሊና ድምፅ”
5. ብዙ ጊዜ በሰዎች ላይ ምን ዓይነት ባሕርይ ይታያል?
5 ዶክተር ኮሊንስ፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ ያለውን አንድ ገጽታ ሲገልጹ “በምላሹ የምናገኘው ጥቅም ባይኖርም እንኳ የሕሊናችን ድምፅ ሌሎችን እንድንረዳ ጥሪ ያሰማል” ብለዋል።a እኚህ ሰው “ሕሊናን” መጥቀሳቸው ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የገለጸውን ሐቅ ያስታውሰናል:- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ።”—ሮሜ 2:14, 15
6. ሁሉም ሰው በፈጣሪ ዘንድ ተጠያቂ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ሰዎች ከሚያዩአቸው ነገሮች ተነስተው የአምላክን መኖርና ባሕርያቱን መገንዘብ ስለሚችሉ በእሱ ፊት ተጠያቂዎች መሆናቸውን ገልጿል። ማስረጃዎቹ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ” ግልጽ ሆነው ሲታዩ ቆይተዋል። (ሮሜ 1:18-20፤ መዝሙር 19:1-4) ይሁን እንጂ ብዙዎች ፈጣሪያቸውን ችላ በማለት መረን የለቀቀ አኗኗር ሲከተሉ ይታያል። የአምላክ ፈቃድ ግን ሰዎች ጻድቅ መሆኑን አምነው ከክፉ ሥራቸው ንስሐ እንዲገቡ ነው። (ሮሜ 1:22 እስከ 2:6) አይሁዳውያን የአምላክ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቷቸው ስለነበር ይህን ለማድረግ የሚያነሳሳቸው ጠንካራ ምክንያት ነበራቸው። ይሁንና “የአምላክ ቅዱስ ቃል” ያልተሰጣቸው ሕዝቦችም ቢሆኑ አምላክ መኖሩን ማመን ነበረባቸው።—ሮሜ 2:8-13፤ 3:2 NW
7, 8. የፍትሕ ስሜት በሁሉም ዓይነት ሰዎች ላይ የሚታይ ባሕርይ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህስ ምን ይጠቁማል?
7 ሁሉም ሰው አምላክ መኖሩን ማመንና እሱ በሚፈልገው መንገድ መመላለስ አለበት እንድንል የሚያደርገን ሌላው አሳማኝ ማስረጃ፣ የሰው ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚያስችል ውስጣዊ ስሜት ያላቸው መሆኑ ነው። የፍትሕ ስሜት ያለን መሆኑ ማለትም ትክክል ያልሆነ ነገር ሲፈጸም የሚሰማን መሆኑ ሕሊና እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር:- የተወሰኑ ልጆች ዥዋዥዌ ለመጫወት ተሰልፈው ተራቸውን እየተጠባበቁ ነው እንበል። አንድ ልጅ ከኋላ መጥቶ ሌሎቹን ከቁብ ሳይቆጥር ከፊት ይቆማል። በዚህ ጊዜ ብዙዎቹ ልጆች ‘ልክ አይደለህም! ውጣ!’ እያሉ ይንጫጫሉ። አሁን ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ብዙ ልጆች ትክክል ያልሆነ ነገር ሲፈጸም በአንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት ሊያንጸባርቁ የቻሉት እንዴት ነው?’ እንዲህ ማድረጋቸው ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚያስችል ውስጣዊ ስሜት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ሁኔታው አልፎ አልፎ የሚፈጸም ነገር ይመስል “ካደረጉ” በማለት አልገለጸም። ከዚህ ይልቅ “ሲያደርጉ” ማለቱ ሰዎች ሁልጊዜ የሚፈጽሙት ነገር መሆኑን ያሳያል። ይህም ሰዎች ‘ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ያደርጋሉ’ ማለትም በውስጣቸው ያለው ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ በአምላክ ሕግ ውስጥ ከተጻፉት መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለሱ ይገፋፋቸዋል ማለት ነው።
8 ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ በብዙ ሕዝቦች ዘንድ ይታያል። የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ አንድ ፕሮፌሰር እንደጻፉት ባቢሎናውያን፣ ግብጻውያንና ግሪካውያን እንዲሁም የአውስትራሊያ አቦርጂኖችና የአሜሪካ ሕንዶች “ጭቆናን፣ ግድያን፣ ማታለልንና ውሸትን የሚያወግዙ ሲሆን ለአረጋውያን፣ ለልጆችና ለደካሞች እንክብካቤ ማድረግን በተመለከተም ተመሳሳይ አቋም አላቸው።” በተጨማሪም ዶክተር ኮሊንስ “መላው የሰው ዘር ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ተመሳሳይ አቋም ያለው ይመስላል” በማለት ጽፈዋል። ይህ ሐሳብ ሮሜ 2:14 ላይ ያሉትን ቃላት አያስታውስህም?
ሕሊናህ የሚሠራው እንዴት ነው?
9. ሕሊና ምንድን ነው? አንድ እርምጃ ከመውሰድህ በፊት እንዴት ሊረዳህ ይችላል?
9 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕሊና ድርጊቶችህን ለማጤንና ለመመዘን የሚያስችልህ ውስጣዊ ችሎታ እንደሆነ ይገልጻል። ይህም በውስጥህ ያለ አንድ ድምፅ፣ እየተከተልክ ያለኸው ጎዳና ትክክል መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚነግርህ ያህል ነው። ጳውሎስ በውስጡ ስላለው ስለዚህ ድምፅ ሲናገር “ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል” ብሏል። (ሮሜ 9:1) ለምሳሌ ያህል፣ ይህ ድምፅ አንድ ነገር ከማድረግህ በፊት ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን አስቀድሞ ሊነግርህ ይችላል። ሕሊናህ ልታደርግ ያሰብከውን ነገር ለመመዘን የሚረዳህ ከመሆኑም ባሻገር ድርጊቱን ከፈጸምክ በኋላ ምን ሊሰማህ እንደሚችልም ይነግርሃል።
10. ሕሊና በአብዛኛው የሚሠራው በምን መንገድ ነው?
10 ይሁንና ሕሊናህ በአብዛኛው የሚናገረው አንድ እርምጃ ከወሰድክ በኋላ ነው። ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ሸሽቶ በነበረበት ጊዜ አምላክ በቀባው ንጉሥ ላይ አክብሮት የጎደለው ድርጊት ፈጽሞ ነበር። ከዚያ በኋላ ዳዊት “ልቡ በሐዘን ተመታ።” (1 ሳሙኤል 24:1-5፤ መዝሙር 32:3, 5) እዚህ ጥቅስ ላይ “ሕሊና” የሚለው ቃል ባይጠቀስም ዳዊት እንዲህ የተሰማው ሕሊናው ስለወቀሰው ነው። በተመሳሳይም ሁላችንም ሕሊናችን የወቀሰን ጊዜ እንዳለ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ድርጊት ከፈጸምን በኋላ ባደረግነው ነገር ተጨንቀንና ተረብሸን ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ቀረጥ ባለመክፈላቸው የተነሳ ሕሊናቸው ስለረበሻቸው የነበረባቸውን ዕዳ ከፍለዋል። ሌሎች ደግሞ ምንዝር መፈጸማቸውን ለትዳር ጓደኛቸው ለመናዘዝ ተገፋፍተዋል። (ዕብራውያን 13:4) ያም ሆኖ አንድ ሰው ሕሊናው ከሚነግረው ነገር ጋር የሚስማማ እርምጃ ሲወስድ እፎይታና ሰላም ያገኛል።
11. ‘ሕሊናህ በሚመራህ ብቻ መሄድ’ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
11 ታዲያ ‘ሕሊናችን በሚመራን ብቻ መሄድ’ አለብን ማለት ነው? ሕሊናችንን ማዳመጣችን ጠቃሚ እንደሆነ ባይካድም እንዲህ ማድረጋችን አንዳንድ ጊዜ ለከባድ ችግር ሊዳርገን ይችላል። አዎን፣ “ውስጣዊው ሰውነታችን” የሚያሰማው ድምፅ ሊያሳስተን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) አንድ ምሳሌ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጸጋንና ኀይልን ስለተሞላ’ እስጢፋኖስ የተባለ ቀናተኛ የክርስቶስ ተከታይ ይናገራል። የተወሰኑ አይሁዳውያን እስጢፋኖስን ከኢየሩሳሌም ውጭ አውጥተው በድንጋይ ወግረው ገደሉት። በአቅራቢያው ቆሞ የነበረው ሳውል (በኋላ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ሆኗል) “በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር።” እነዚህ አይሁዳውያን የሚያደርጉት ነገር ትክክል እንደሆነ ስለተሰማቸው ሳይሆን አይቀርም ሕሊናቸው አልረበሻቸውም። ሳውልም ከዚያ በኋላ ‘የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ይዝት’ ስለነበር እሱም ሕሊናው እንዳልቆረቆረው ማስተዋል ይቻላል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሕሊናው ትክክለኛውን ድምፅ ወይም መልእክት አላስተላለፈለትም።—የሐዋርያት ሥራ 6:8፤ 7:57 እስከ 8:1፤ 9:1
12. በሕሊናችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው አንዱ ነገር ምንድን ነው?
12 በሳውል ሕሊና ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ምን ሊሆን ይችላል? አንዱ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የነበረው ቅርርብ ሊሆን ይችላል። ብዙዎቻችን ከአባቱ ድምፅ ጋር የሚመሳሰል ድምፅ ካለው ሰው ጋር በስልክ አውርተን እናውቅ ይሆናል። ልጁ የድምፁን ቃና ከአባቱ የወረሰ ቢሆንም የአባቱ የአነጋገር ስልትም ተጽዕኖ አድርጎበታል። በተመሳሳይም ሳውል ኢየሱስን ይጠሉና ትምህርቱን ይቃወሙ ከነበሩት አይሁዶች ጋር መቀራረቡ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 11:47-50፤ 18:14፤ የሐዋርያት ሥራ 5:27, 28, 33) አዎን፣ የሳውል ወዳጆች ከውስጡ በሚሰማው ድምፅ ማለትም በሕሊናው ላይ ተጽዕኖ አሳድረውበታል።
13. አንድ ሰው የሚኖርበት አካባቢ በሕሊናው ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
13 አካባቢያችን በአነጋገር ዘዬአችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሁሉ አንድ ሰው ያደገበት ባሕልና አካባቢ በሕሊናው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል። (ማቴዎስ 26:73) በጥንቶቹ አሦራውያን ላይ የደረሰው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሳይሆን አይቀርም። አሦራውያን በጦረኝነታቸው የታወቁ ሲሆኑ ምርኮኞቻቸውን ያሠቃዩ እንደነበር የሚያሳዩ ምስሎችም አሉ። (ናሆም 2:11, 12፤ 3:1) በዮናስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የነነዌ ሰዎች “ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ” እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። ይህም በአምላክ ዓይን ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን ለመለየት የሚያስችል ትክክለኛ መሥፈርት እንዳልነበራቸው ያመለክታል። ይህ ሁኔታ በነነዌ ባደገ ሰው ሕሊና ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገምት! (ዮናስ 3:4, 5፤ 4:11) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የአንድ ሰው ሕሊና በዙሪያው ባሉት ሰዎች ዝንባሌ ሊቀረጽ ይችላል።
ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?
14. ሕሊና ያለን መሆኑ በዘፍጥረት 1:27 ላይ ያለውን ሐቅ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ሕሊና የሰጣቸው ሲሆን እኛም ይህን ስጦታ ከእነሱ ወርሰናል። ዘፍጥረት 1:27 የሰው ልጆች በአምላክ አምሳል እንደተፈጠሩ ይናገራል። ይህ ሲባል የአምላክ ዓይነት አካል አለን ማለት አይደለም። ምክንያቱም እሱ መንፈስ ነው፤ እኛ ግን ሥጋ ነን። አምላክን የምንመስለው ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳንን ሕሊና ጨምሮ የእሱ ባሕርያት እንዲኖሩን ተደርገን ስለተፈጠርን ነው። ይህ ሐቅ፣ ሕሊናችን ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ማሠልጠን የምንችልበትን አንድ መንገድ ይጠቁመናል። ይኸውም ስለ ፈጣሪያችን ይበልጥ መማርና ወደ እሱ መቅረብ ነው።
15. አባታችንን ማወቅ ከሚያስገኝልን ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ምንድን ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሕይወት ሰጪያችን በመሆኑ የሁላችንም አባት እንደሆነ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 64:8) በሰማይም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ታማኝ ክርስቲያኖች አምላክን አባታችን ብለው ሊጠሩት ይችላሉ። (ማቴዎስ 6:9) ከመቼውም ይበልጥ ወደ አባታችን ለመቅረብ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብና የአቋም ደረጃዎች ለመማር ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። (ያዕቆብ 4:8) ብዙዎች እንዲህ የማድረግ ፍላጎት የላቸውም። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ከተናገራቸው አይሁዳውያን ጋር ይመሳሰላሉ:- “እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም።” (ዮሐንስ 5:37, 38) እኛም የአምላክን ድምፅ ቃል በቃል ሰምተን አናውቅም፤ ሆኖም ቃሉን በማንበብ አስተሳሰቡን ማወቅ እንችላለን። በዚህ መንገድ እሱን መምሰልና የእሱን ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንችላለን።
16. የዮሴፍ ታሪክ ሕሊናችንን ማሠልጠንና የሚነግረንን መስማት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 ዮሴፍ በጲጢፋራ ቤት ስላጋጠመው ሁኔታ የሚገልጸው ዘገባ የአምላክን ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር እንደምንችል ያሳያል። የጲጢፋራ ሚስት ዮሴፍን ልታሳስተው ሞክራ ነበር። ዮሴፍ በኖረበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፈ ከመሆኑም ሌላ አሥርቱ ትእዛዛትም አልተሰጡም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ለጲጢፋራ ሚስት “ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ብሏታል። (ዘፍጥረት 39:9) ዮሴፍ የሚኖረው ከቤተሰቡ ርቆ ስለነበር እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሰጠው እነሱን ለማስደሰት ብሎ አልነበረም። ይህን ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት አምላክን ማሳዘን ስላልፈለገ ነው። ዮሴፍ፣ አምላክ ያቋቋመው የጋብቻ ሥርዓት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት እንደሆነና ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ዮሴፍ፣ አቤሜሌክ ርብቃ ያገባች መሆኗን ሲረዳ ምን ያህል አዝኖ እንደነበር ሳይሰማ አይቀርም። አቤሜሌክ ርብቃን መውሰድ ትክክል እንዳልሆነና ሕዝቡን በደለኛ እንደሚያደርግ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ከአቤሜሌክና ከርብቃ ጋር የተያያዘው ሁኔታ በአግባቡ እንዲፈታ በማድረግ ለምንዝር ያለውን አመለካከት ግልጽ አድርጓል። ዮሴፍ ይህን ሁሉ ማወቁ ሕሊናውን አሠልጥኖለታል፤ ይህ ደግሞ ከጾታ ብልግና እንዲርቅ ገፋፍቶታል።—ዘፍጥረት 2:24፤ 12:17-19፤ 20:1-18፤ 26:7-14
17. አባታችንን ለመምሰል በምናደርገው ጥረት ከዮሴፍ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን የምንለው ለምንድን ነው?
17 እኛ ከዮሴፍ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ግልጽ ነው። አባታችን የሚፈቅድልንን እና የሚከለክለንን ነገሮች ጨምሮ የእሱን አስተሳሰብና ስሜት ለመማር የሚያስችለን ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባወቅን መጠን ወደ አምላክ በበለጠ መቅረብና እሱን መምሰል እንችላለን። ይህን ስናደርግ ሕሊናችን የሚያስተላልፍልን መልእክት የአባታችንን አስተሳሰብ ይበልጥ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአባታችን ፈቃድ ጋር እየተስማማ ይሄዳል።—ኤፌሶን 5:1-5
18. ያለፈው ሕይወታችን ተጽዕኖ የሚያሳድርብን መሆኑ ባይካድም ሕሊናችን ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን?
18 አካባቢያችን በሕሊናችን ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖስ ምን ማለት ይቻላል? የዘመዶቻችን አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሁም ያደግንበት ኅብረተሰብ ተጽዕኖ አድርጎብን ይሆናል። በዚህም ምክንያት ሕሊናችን የደነዘዘ ወይም የሚያስተላልፍልን መልእክት የተዛባ ሊሆን ይችላል። በሌላ አባባል ሕሊናችን በአካባቢያችን ያሉ ሰዎችን “የአነጋገር ዘዬ” የተከተለ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ያለፈውን ሕይወታችንን መለወጥ እንደማንችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በሕሊናችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል አካባቢና ወዳጅ ለመምረጥ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። ይህን ለማድረግ ቁልፉ፣ አባታቸውን ለመምሰል ሲጥሩ ከቆዩ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ስብሰባዎቹ ከመጀመራቸው በፊትና ካበቁ በኋላ ከሌሎች ጋር መጨዋወት ለዚህ ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል። የእምነት አጋሮቻችን፣ ሕሊናቸው የአምላክን አስተሳሰብና መንገዶች ሲነግራቸው ለመስማት ፈጣን እንደሆኑ፣ ብሎም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና አኗኗር እንዳላቸው ማስተዋል እንችላለን። ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ሕሊናችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንዲስማማ ስለሚረዳን የአምላክን መልክ ይበልጥ እናንጸባርቃለን። በውስጣችን ያለው ድምፅ አባታችን ካወጣቸው መመሪያዎች ጋር እንዲስማማ ስናደርግና የእምነት አጋሮቻችን በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብን ስንፈቅድ፣ ሕሊናችን አስተማማኝ ይሆናል፤ እኛም የሚያስተላልፍልንን መልእክት ለማዳመጥ ይበልጥ ፈቃደኞች እንሆናለን።—ኢሳይያስ 30:21
19. ሕሊናን በተመለከተ የትኞቹን ጉዳዮች መመርመራችን ተገቢ ነው?
19 ያም ሆኖ አንዳንዶች ሕሊናቸው የሚነግራቸውን ለማዳመጥ በየዕለቱ ትግል ያደርጋሉ። የሚቀጥለው ርዕስ ክርስቲያኖች ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ያብራራል። እነዚህን ሁኔታዎች መመርመራችን ሕሊና የሚጫወተውን ሚና በግልጽ እንድንረዳ፣ እንዲሁም የአንድ ሰው ሕሊና ከሌላው የሚለየው ለምን እንደሆነና የሕሊናችንን ድምፅ ይበልጥ መስማት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—ዕብራውያን 6:11, 12
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በተመሳሳይም የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባና የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኦወን ጂንጅሪች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ፣ እንስሳትን በማጥናት ሳይንሳዊ መልስ ሊገኝለት የማይችል ጥያቄ ያስነሳል። ለጥያቄው ይበልጥ አሳማኝ የሆነ መልስ ማግኘት የሚቻለው ከሌላ አቅጣጫ ሳይሆን አይቀርም። ይኸውም ሕሊናን ጨምሮ የሰው ልጆች ሰብዓዊ ርኅራኄ እንዲሰማቸው ከሚያደርጓቸው አምላክ ከሰጣቸው ባሕርያት ጋር የተያያዘ መሆን አለበት።”
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ሁሉም ሰው ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ ወይም ሕሊና ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?
• ሕሊናችን በሚነግረን ብቻ እንዳንመራ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?
• ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዱን አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ሕሊናው ወቅሶታል . . .
የጠርሴሱ ሳውል ግን ሕሊናው አልወቀሰውም
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕሊናችንን ማሠልጠን እንችላለን