እውነተኛውን አምላክ አሁኑኑ መፍራት ያለብን ለምንድን ነው?
“ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”—መክብብ 12:13
1, 2. ለአምላክ ትክክለኛ ፍርሃት ማሳየታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
የሰው ልጅ ለአምላክ ጤናማ የሆነና ቅድስና የተሞላበት ፍርሃት ቢኖረው ጥሩ ይሆንለታል። አዎን፣ የሰው ልጅ የሚያድሩበት ብዙዎቹ ፍርሃቶች የስሜት መረበሽ የሚያስከትሉ እንዲያውም ለሕልውና የሚያሰጉ ቢሆኑም እኛ ይሖዋ አምላክን መፍራታችን ይጠቅመናል።—መዝሙር 112:1፤ መክብብ 8:12
2 ፈጣሪ ይህን ያውቃል። የሰው ልጅ በሙሉ እንዲያመልከውና እንዲፈራው የሚያዘውም ለፍጥረቶቹ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው። እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም፦ የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።”—ራእይ 14:6, 7
3. ፈጣሪ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን አድርጎላቸው ነበር?
3 የሕይወት ምንጭ የሆነው የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ የሰው ልጆችና የዚህች ፕላኔት ባለቤት ስለሆነ ችላ ልንለው አይገባም። (መዝሙር 24:1) ይሖዋ ለታላቅ ፍቅሩ መግለጫ እንዲሆን ለምድራዊ ልጆቹ በተዋበች ገነት ውስጥ ሕይወትና ግሩም የሆነ የመኖሪያ ቦታ ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ አስደናቂ ስጦታ ለመጠቀም ማሟላት የነበረባቸው ግዴታ ነበር። በመሠረቱ ይህ ስጦታ የተሰጣቸው በአደራ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለገነታዊ መኖሪያቸው የሚገባውን እንክብካቤ እንዲያደርጉና ተባዝተው መላውን ምድር እስኪሞሉ ድረስ ይህን ገነት እንዲያስፋፉ ታዘው ነበር። ከእነሱና ከልጆቻቸው ጋር ምድርን የሚጋሩትን ሕያዋን ፍጥረታት ማለትም እንስሳትን፣ አእዋፍንና የባሕር ዓሦችን በሙሉ የመግዛት መብትና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። ለዚህ ታላቅ አደራ ተጠያቂ ይሆናሉ።
4. ሰው የአምላክን ፍጥረት ምን አድርጎታል?
4 ይህ በጣም ግሩም የሆነ ጅምር ነበር። ሆኖም የሰው ልጅ ይህችን ውብ መኖሪያ ምን ያህል እንደበከላት ተመልከት! ሰዎች አምላክ ለዚህች የተዋበች ዕንቁ ያለውን ባለቤትነት በመናቅ ምድርን በክለዋታል። ይህ ብክለት የብዙ እንስሳትን፣ አእዋፍንና ዓሦችን ዝርያዎች ሕልውና የሚፈታተንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ጻድቅና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይህ ሁኔታ ለዘላለም እንዲቀጥል አይፈቅድም። የተበላሸው የምድር ሁኔታ በምድር በካዮች ላይ እንዲፈርድባቸው ጥሪውን እያሰማ ነው። ይህ ለብዙዎች አስፈሪ ይሆንባቸዋል። በሌላ በኩል አምላክን የሚያከብሩና የሚተማመኑበት ወደፊት የሚሆነውን ነገር ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። ይሖዋ ለጥፋተኞቹ የሚገባቸውን ፍርድ ይሰጣል። ምድርም ትታደሳለች። ይህ በእርግጥም በምድር ላይ ለሚኖሩ ቅን ሰዎች በሙሉ ታላቅ የምሥራች ነው።
5, 6. ይሖዋ ሰው በፍጥረቱ ላይ ላደረሰው ጉዳት ምን ምላሽ ይሰጣል?
5 አምላክ ፍርዱን የሚያስፈጽመው እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ በተቀመጠው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። ይሖዋ በዚህ ሰማያዊ ልጅ አማካኝነት ይህን የአሁኑን ቆሻሻና ዓመፀኛ ሥርዓት ያጠፋል። (2 ተሰሎንቄ 1:6–9፤ ራእይ 19:11) በዚህ መንገድ እሱን ለሚፈሩ ሰዎች እፎይታ በማምጣት ምድራዊ መኖሪያችንን ከጥፋት ያድናታል።
6 ታዲያ ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በአርማጌዶን ጦርነት ስለሚጠናቀቀው ስለ መጪው ታላቅ መከራ ይናገራል። (ራእይ 7:14፤ 16:16) ይህ ታላቅ መከራ በዚህ ብልሹ የነገሮች ሥርዓትና በበካዮቹ ላይ አምላክ የሚፈርድበት ጊዜ ይሆናል። በዚያን ወቅት በሕይወት የሚተርፍ ሰው ይኖር ይሆን? አዎን! የሚተርፉት ለአምላክ ጤናማ ያልሆነ፣ የሚያርበደብድ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ ቅድስና የተሞላበት ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ናቸው። እነሱ ከጥፋቱ ይድናሉ።—ምሳሌ 2:21, 22
አስፈሪ የኃይል መግለጫ
7. አምላክ በሙሴ ዘመን እስራኤላውያንን ለማዳን ጣልቃ የገባው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ አምላክ ከዘመናችን አቆጣጠር ከ1,500 ዓመታት በፊት አምላኪዎቹን ለማዳን የወሰደው ታላቅ የኃይል እርምጃ ለዚህ አስደናቂ ድርጊት ትንቢታዊ ጥላ ይሆናል። ታላቅ ወታደራዊ ኃይል የነበረው የግብፅ መንግሥት ከሌላ አገር መጥተው በአገሩ የሠፈሩትን እስራኤላውን ምንደኞች በባርነት ረግጦ ከመግዛቱም በላይ ገዢው ፈርዖን ከእስራኤላውያን የሚወለዱ ወንድ ሕፃናት በሙሉ እንዲገደሉ ባዘዘ ጊዜ መላውን የእስራኤል ዘር ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። አምላክ በግብፃውያን ላይ የተቀዳጀው ድል እስራኤላውያንን ጨቋኝ ከሆነው የፖለቲካ ሥርዓትና በብዙ አማልክት አምልኮ ከተበከለው ብሔር ነፃ አውጥቷቸዋል።
8, 9. ሙሴና እስራኤላውያን ለአምላክ የማዳን እርምጃ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
8 እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ በወጡ ጊዜ ምን እንደተሰማቸው በዘጸአት ምዕራፍ 15 ላይ ተመዝግቧል። ይህን ታሪክ መመርመራችን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ከተበከለው ከዚህ ከዘመናችን ሥርዓት እንዴት ነፃ እንደሚወጡ ለመገንዘብ ያስችለናል። ዘጸአት ምዕራፍ 15ን እናውጣና ምርጫችን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን መፍራት መሆን ያለበት ለምን እንደሆነ ለማወቅ አንዳንድ ቁጥሮችን እንመርምር። በቁጥር 1 እና 2 እንጀምር፦
9 “በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፣ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፣ መድኃኒቴም ሆነልኝ።”
10. አምላክ የግብፃውያንን ሠራዊት እንዲያጠፋ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
10 በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዴት ከግብፅ ነፃ እንዳወጣቸው የሚገልጸውን ታሪክ ያውቃሉ። ፈርዖን እስራኤላውያን እንዲወጡ እስኪፈቅድ ድረስ ይሖዋ በዚህ የዓለም ኃያል መንግሥት ላይ የተለያዩ መቅሠፍቶችን አውርዶ ነበር። እስራኤላውያን ከወጡ በኋላ ግን የፈርዖን ጭፍሮች እነዚህን መከላከያ የሌላቸው ሰዎች አሳድደው በቀይ ባሕር ዳርቻ አጥምደው የያዟቸው መስሎ ነበር። የእስራኤል ልጆች አዲስ ያገኙትን ነፃነት ያጡ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ ያሰበው አንድ ነገር ነበር። በተአምር ባሕሩን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቦቹ የሚያልፉበትን መንገድ ካዘጋጀ በኋላ በሰላም እንዲሻገሩ አደረገ። ግብፃውያን ተከትለዋቸው በገቡ ጊዜ ግን የቀይ ባሕር ውኃ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረግ ፈርዖንና ወታደራዊ ጭፍሮቹን አሰጠማቸው።—ዘጸአት 14:1–31
11. አምላክ በግብፃውያን ላይ እርምጃ መውሰዱ ምን ውጤት አስገኘ?
11 ይሖዋ የግብፅን ወታደራዊ ኃይሎች በቀይ ባሕር ማጥፋቱ በአምላኪዎቹ ፊት ከፍ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ ስሙ በስፋት እንዲታወቅ አስችሏል። (ኢያሱ 2:9, 10፤ 4:23, 24) አዎን፣ ይህን አስደናቂ ተአምር በመፈጸሙ ምክንያት ስሙ አምላኪዎቻቸውን ለማዳን ሳይችሉ ከቀሩት ደካማ የግብፃውያን የሐሰት አማልክት በላይ እጅግ ከፍ ብሏል። ግብፃውያን በአማልክቶቻቸው፣ ሟች በሆነው ሰውና በወታደራዊ ኃይላቸው ላይ የነበራቸው ትምክህት መራራ ውድቀት አስከትሎባቸዋል። (መዝሙር 146:3) እስራኤላውያን ሕዝቦቹን በታላቅ ኃይል ነፃ ለሚያወጣ ሕያው አምላክ ያላቸውን ጤናማ ፍርሃት የሚያንጸባርቅ የውዳሴ መዝሙር እንዲዘምሩ መገፋፋታቸው አያስደንቅም!
12, 13. አምላክ በቀይ ባሕር ላይ ከተቀዳጀው ድል ምን መማር ይኖርብናል?
12 እኛም በተመሳሳይ ማንኛውም የዘመናችን የሐሰት አምላክ፣ ማንኛውም ኃያል መንግሥት፣ በኑክሌር መሣሪያዎች የታጠቀም ቢሆን የይሖዋን ኃይል ሊቋቋም እንደማይችል መገንዘብ ይኖርብናል። ሕዝቦቹን ለማዳን ይችላል፣ ያድናልም። “በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።” (ዳንኤል 4:35) እኛም የእነዚህን ቃላት የተሟላ ትርጉም ስንረዳ ውዳሴውን በደስታ ለመዘመር እንገፋፋለን።
13 በቀይ ባሕር የተዘመረው የድል መዝሙር “ይሖዋ ብርቱ ተዋጊ ነው፤ ስሙም ይሖዋ ነው” በማለት ይቀጥላል። ስለዚህ ይህ በማንም ድል የማይነሣው ጦረኛ የሰው ግምታዊ አስተሳሰብ የወለደው አንድ ስም የሌለው አካል አይደለም። የራሱ የሆነ ስም አለው! እሱ ‘መሆን የሚፈልገውን የሚሆን’ አምላክ ነው። ታላቅ ፈጣሪና ‘ስሙ ይሖዋ የሆነ በመላው ምድር የመጨረሻው የበላይ ነው።’ (ዘጸአት 3:14 አዓት ፤ 15:3–5 አዓት ፤ መዝሙር 83:18 አዓት) እነዚያ የጥንት ግብፃውያን ሁሉን የሚችለውን አምላክ ከማቃለል ይልቅ ምክንያታዊና አክብሮታዊ ፍርሃት ቢኖራቸው ኖሮ መልካም ይሆንላቸው እንደነበር አትስማሙምን?
14. በቀይ ባሕር አምላካዊ ፍርሃት ያለው ጠቀሜታ የታየው እንዴት ነው?
14 የባሕርና የምድር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ትላልቅ የውኃ አካላትን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። (ዘጸአት 15:8) በተጨማሪም ነፋስን ለመቆጣጠር በሚያስችለው ኃይሉ በመጠቀም ፈጽሞ የማይቻል መስሎ የሚታይ ነገር ፈጽሟል። ጥልቁን ውኃ ለሁለት ከከፈለ በኋላ በሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች ተገፍቶ እንዲቆም በማድረግ ሕዝቦቹ የሚያልፉበት መንገድ አዘጋጀ። ሁኔታው ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ፦ ከፍተኛ መጠን ያለው የባሕር ውኃ በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ ተቆለለና ለእስራኤላውያን የማምለጫ መንገድ ተከፈተ። አዎን፣ ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ጥበቃ እንዲያገኙ ተደረገ። ከዚያም ይሖዋ ውኃውን በኃይል ለቀቀውና የፈርዖን ጭፍሮች ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር እንዲሰምጡ አደረገ። ከንቱ በሆኑ አማልክትና በሰብዓዊ ወታደራዊ ኃይል ላይ የተገለጠ አስደናቂ መለኮታዊ ኃይል ነበር! በእርግጥም ሊፈራ የሚገባው ይሖዋ ነው፤ አይደለም እንዴ?—ዘጸአት 14:21, 22, 28፤ 15:8
ፈሪሃ አምላክ እንዳለን ማሳየት
15. ለአምላክ ኃይለኛ የማዳን ተግባራት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
15 ከሙሴ ጋር በሰላም ተሻግረን ቢሆን ኖሮ “አቤቱ፣ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፣ ድንቅንም የምታደርግ፣ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ብለን ለመዘመር እንደምንገፋፋ አያጠራጥርም። (ዘጸአት 15:11) ከዚያ ዘመን ጀምሮ ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ በዚህ መዝሙር የተገለጸው ስሜት ሲስተጋባ ኖሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ አንድ ታማኝ የቅቡዓን አገልጋዮች ቡድን ሲናገር “የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ” በማለት ይገልጻል። ይህ ታላቅ መዝሙር ምንድን ነው? “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?”—ራእይ 15:2–4
16, 17. በአሁኑ ጊዜ ምን አስደናቂ ሁኔታዎች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው?
16 ዛሬም ቢሆን የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ብቻ ሳይሆን የጽድቅ ትእዛዛቱን ጭምር የሚያደንቁ ነፃ የወጡ አምላኪዎች አሉ። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ስለሚገነዘቡና በሥራም ላይ ስለሚያውሉ ከዚህ ከተበከለ ዓለም ተለይተው መንፈሳዊ ነፃነት አግኝተዋል። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ብልሹ ዓለም ድነው ንጹሕና ሐቀኛ በሆነው የይሖዋ አምላኪዎች ድርጅት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። በቅርቡም እሳታማ የሆነው የአምላክ ፍርድ በሐሰት ሃይማኖትና በቀሪው ክፉ ሥርዓት ላይ ከወረደ በኋላ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ።
17 ከራእይ 14:6, 7 ጋር በሚስማማ መንገድ የሰው ልጆች የይሖዋ ምሥክሮች በመላእክት መሪነት የሚያውጁትን የፍርድ ማስጠንቀቂያ መልእክት በመስማት ላይ ናቸው። ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ምሥክሮች ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የአምላክን መንግሥት ምሥራችና የፍርድ ሰዓት በማወጅ ላይ ናቸው። እነዚህ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች ለመዳን የሚያስችላቸውን ትምህርት እንዲያገኙ ዘወትር ወደ ቤታቸው እየሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እየመሩ ነው። በየዓመቱ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በእውቀት እንዲፈሩ፣ ሕይወታቸውን ለእሱ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ የሚያበቃቸውን እውቀት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ መፍራታቸው ምንኛ ያስደስታል!—ሉቃስ 1:49–51፤ ሥራ 9:31፤ ከዕብራውያን 11:7 ጋር አወዳድር።
18. መላእክት በስብከት ሥራችን እንደሚሳተፉ የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 መላእክት በእርግጥ በዚህ የስብከት ሥራ ይሳተፋሉን? የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ የተጨነቁ፣ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት የሚቃትቱና የሚጸልዩ ሰዎችን ለማግኘት በመቻላቸው በዚህ ሥራ የመላእክት አመራር እንዳለ በግልጽ ታይቷል! ለምሳሌ ያህል በአንድ የካሪቢያን ደሴት ውስጥ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ ትንሽ ልጅ ጋር ሆነው የምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ይናገሩ ነበር። እኩለ ቀን እየቀረበ ሲሄድ ሁለቱ ሴቶች አገልግሎታቸውን አቁመው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ወሰኑ። ልጁ ግን የሚቀጥለውን ቤት እናንኳኳ እያለ ያለወትሮው ወተወታቸው። ከእሱ በዕድሜ የሚበልጡት ሴቶች ቤቱን ለማንኳኳት ፍላጎት እንደሌላቸው በተመለከተ ጊዜ ብቻውን ሄዶ አንኳኳ። አንዲት ወጣት ሴት በሩን ከፈተች። ትላልቆቹ ሴቶች ይህን ሲመለከቱ ሄደው አነጋገሯት። ሴትየዋ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸውና በሩ በተንኳኳበት ጊዜ አምላክ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲልክላትና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምሯት ትጸልይ እንደነበር ነገረቻቸው። ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ተደረገ።
19. አምላክን መፍራት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ምን ልንጠቅስ እንችላለን?
19 የአምላክን የፍርድ መልእክት በታማኝነት በምንናገርበት ጊዜ የጽድቅ ትእዛዛቱንም እናስተምራለን። ሰዎች እነዚህን ትእዛዛት በሥራ ላይ ሲያውሉ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ በረከት ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም የጾታ ርኩሰት በግልጽ ያወግዛል። (ሮሜ 1:26, 27, 32) በዛሬው ጊዜ እነዚህን የመሳሰሉት የአቋም ደረጃዎች በዓለም ውስጥ በብዛት በመጣስ ላይ ይገኛሉ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ጋብቻዎች በመፈራረስ ላይ ናቸው። ወንጀል እየበዛ ነው። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ለአካለ ጎዶሎነት የሚዳርጉና ቀሳፊ የሆኑ በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች ወረርሽኝ ተዛምቷል። ኤድስ የተባለው አስፈሪ በሽታ በአብዛኛው የሚዛመተው ከሥነ ምግባር ውጪ በሆኑ የጾታ ድርጊቶች ነው። ይሁን እንጂ እውነተኛ አምላኪዎች ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየታቸው ትልቅ ጥበቃ አልሆነላቸውምን?—2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ፊልጵስዩስ 2:12፤ በተጨማሪም ሥራ 15:28, 29ን ተመልከት።
አሁኑኑ አምላክን መፍራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
20. ሌሎች ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ስም እንዳላቸው እንደሚያውቁ የሚያሳየው ምንድን ነው?
20 አምላክን የሚፈሩና ትእዛዛቱን የሚጠብቁ ሰዎች የተትረፈረፉ በረከቶችን ያገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ ወንድማማችነት የመሠረቱ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ክርስቲያኖች መሆናቸው በሰፊው እየታወቀ መሄዱን የሚያሳይ አንድ ሁኔታ ተመለከቱ። በዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሌሎች አገሮች የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ባረፉበት አንድ ሆቴል ውስጥ በአንድ ምሽት የአገሩ ፕሬዚዳንት ንግግር የሚሰጡበት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች የሚያደርጉት አንድ ስብሰባ ተዘጋጅቶ ነበር። የጸጥታ ኃይሎች ስብሰባውን ለመክፈት በመግባት ላይ የሚገኙትን ፕሬዚዳንት እየተጣደፉ ወደ ሊፍት በሚያስገቡበት ጊዜ በሊፍቱ ውስጥ ያለውን ሰው ማንነት ያላወቀች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጥልቅ ብላ ገባች። በዚህ ሁኔታ የጸጥታ ኃይሎቹ ተደናገጡ። ምሥክሯ ያደረገችውን ነገር ስትገነዘብ ጣልቃ በመግባቷ በትሕትና ይቅርታ ጠየቀች። ከዚያም የይሖዋ ምሥክር መሆኗን የሚያሳውቀውን የስብሰባ ባጅ አሳየቻቸውና በፕሬዚዳንቱ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ የማታመጣ መሆኗን ገለጸች። ከጸጥታ ኃይሎቹ አንዱ ፈገግ ብሎ “ሁሉ ሰው እንደ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሆን ኖሮ ይህን የመሰለ ጥበቃ ማድረግ አያስፈልገንም ነበር” አላት።—ኢሳይያስ 2:2–4
21. በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ምን አካሄድ እንዲከተሉ አጋጣሚ ተሰጥቷቸዋል?
21 ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚሰበስበውና ይህን ሥርዓት ከሚያጠፋው ‘ከታላቁ መከራ’ በሕይወት ለማለፍ እንዲችሉ በማጥራት ላይ የሚገኘው እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ነው። (ራእይ 7:9, 10, 14) ከዚህ ጥፋት በአጋጣሚ መትረፍ አይቻልም። አንድ ሰው ከጥፋቱ በሕይወት ከሚተርፉት መካከል ለመሆን ከፈለገ ይሖዋን መፍራት፣ የአጽናፈ ዓለም ትክክለኛ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን መቀበልና ራሱን መወሰን አለበት። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ጥበቃ የሚያስገኝላቸውን ፍርሃት እንዳልኮተኮቱ ያለው እውነታ ያሳያል። (መዝሙር 2:1–6) ማስረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት ይሖዋ የመረጠው ገዢ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወሳኝ ዓመት ከሆነው ከ1914 ጀምሮ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ነው። ይህም ይሖዋ ግለሰቦች ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ለመኮተኮትና ለማሳየት የቀራቸው ጊዜ እያለቀ ሄዷል ማለት ነው። አሁንም ቢሆን ይሖዋ ግለሰቦች ሌላው ቀርቶ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ለሚከተለው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል፦ “አሁንም እናንት ነገሥታት፣ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፣ ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፣ ቁጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።”—መዝሙር 2:7–12
22. አሁኑኑ እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች ወደፊት ምን ያገኛሉ?
22 ፈጣሪያችን ከጠላቶቻችን እጅ አዳነን ብለው ከሚያወድሱት ሰዎች መካከል እንሁን። ሆኖም ይህ አሁኑኑ እውነተኛውን አምላክ መፍራትን ይጠይቅብናል! (ከመዝሙር 2:11፣ ከዕብራውያን 12:28 እና ከ1 ጴጥሮስ 1:17 ጋር አወዳድር።) የጽድቅ ትእዛዛቱን መማራችንንና መታዘዛችን መቀጠል አለብን። በራእይ 15:3, 4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የሙሴና የበጉ መዝሙር ይሖዋ ከምድር ላይ ክፋትን ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ አጥፍቶ የሰውን ልጅና የሰው ልጅ መኖሪያ የሆነችውን ምድር በኃጢአት በመበከል ምክንያት ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲፈወሱ ማድረግ ሲጀምር የመጨረሻውን ከፍተኛ ድምቀት ያገኛል። በዚያን ጊዜ “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከበር ማን ነው?” ብለን በሙሉ ልባችን እንዘምራለን።
ታስታውሳለህን?
◻ ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ አምላክ በቀይ ባሕር ባከናወናቸው ነገሮች የታየው ምንድን ነው?
◻ ይሖዋን በአክብሮት በመፍራታችን ምን ጥቅሞችን እናገኛለን?
◻ አሁኑኑ እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩት ሰዎች ወደፊት ምን ያገኛሉ?