አሁን ያለው ፍርሃት ለዘላለም ይወገዳል!
የአምላክ ቃል ተማሪዎች ፍርሃት ይህን ያህል መብዛቱ አያስገርማቸውም። የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው በስፋት እንዳሳወቁት የምንኖረው በሰው ልጅ ታሪክ ለየት ባለ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ይህ ዘመን ፍርሃት እየጨመረ የመጣበት ዘመን እንደሆነ ታውቃለህ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ በፊት ዘመናችንን ለይቶ አሳውቋል ወይም አመልክቷል። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ሐዋርያት ስለ መገኘቱ እና ስለዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ወይም ‘ስለ ዓለም ፍጻሜ’ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በመለሰላቸው ጊዜ ነበር።—ማቴዎስ 24:3
ኢየሱስ ከተናገረው ትንቢት ከፊሉ የሚከተለው ነው፦
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።”—ሉቃስ 21:10, 11
ኢየሱስ “የሚያስፈራም ነገር” በማለት የጠቀሰውን ሐሳብ ልብ ብለኸዋልን? ኢየሱስ ቆየት ብሎ በዚሁ መልስ ላይ ፍርሃትን በተመለከተ አንተንም ሆነ የምትወዳቸውን ሰዎች ያለጥርጥር በቀጥታ የሚነካውን ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ተናግሯል። ይሁን እንጂ ይህን ጉዳይ ከመመልከታችን በፊት በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችን በአጭሩ እንመልከት።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
ሰዎች ጦርነትን የሚፈሩበት በቂ ምክንያት አላቸው
ወታደራዊ ግጭቶች ብዙዎቹን የምድር አካባቢዎች አውድመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጂኦ መጽሔት በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ ተከስቶ በነበረው ግጭት ማብቂያ ላይ የነዳጅ ዘይት ጉድጓዶች በእሳት እንዲቀጣጠሉ በመደረጉ ምክንያት የደረሰውን ሁኔታ “በሰው ምክንያት ከደረሱት ጥፋቶች በሙሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ጥፋት” ሲል ጠርቶታል። በጦርነት ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ወይም የአካል ጉዳተኞች ሆነዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ወታደሮችና ሲቪሎች በተጨማሪ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 55 ሚልዮን ሰዎች ተገድለዋል። ኢየሱስ የዚህ ዓለም መጨረሻ መቅረቡን ከሚጠቁመው ምልክት አንዱ ክፍል በማድረግ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” እንዳለ አስታውስ።
በተጨማሪም ሰው አንዳንድ ዘሮችን ወይም ነገዶችን ፈጽሞ ለማጥፋት ያደረገውን ጥረት ችላ ብለን ልናልፈው አንችልም። በሚልዮን የሚቆጠሩ አርመናውያን፣ ካምቦዳውያን፣ አይሁዳውያን፣ ሩዋንዳውያን፣ ዩክሬናውያንና ሌሎች ሕዝቦች መጨፍጨፋቸው የሰው ልጅ በሃያኛው መቶ ዘመን የፈጸመውን ከፍተኛ የደም ማፍሰስ ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶታል። አሁንም ቢሆን ሃይማኖታዊ አክራሪዎች የዘር ጥላቻ እንዲስፋፋ በሚያበረታቱባቸው አገሮች ግድያው አላቆመም። አዎን፣ ጦርነቶች አሁንም ምድር በሰዎች ደም እንድትርስ በማድረግ ላይ ናቸው።
ዘመናዊ ጦርነቶች ውጊያው ካበቃ በኋላ እንኳን ብዙ ሰዎችን መጉዳታቸውን ወይም መግደላቸውን አላቆሙም። ለምሳሌ ያህል፣ በየቦታው የሚቀበሩት ፈንጂዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ተመልከት። ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የምርምር ድርጅት ባቀረበው ሪፖርት መሠረት “በመላው ዓለም 100 ሚልዮን የሚያክሉ የተቀበሩ ፈንጂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ናቸው።” እነዚህ ፈንጂዎች በሥራ ላይ የዋሉበት ጦርነት ካበቃ በኋላ ብዙ ቆይቶም እንኳን በንጹሐን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። በየወሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከ60 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት እንደሚሞቱ ወይም አካላቸው እንደሚቆራረጥ ተገልጿል። እነዚህ በሕይወትና በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ፈንጂዎች በሥርዓት ተጠርገው የማይወገዱት ለምንድን ነው? ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ፈንጂ ለማጽዳት በሚደረጉ ዘመቻዎች ከሚመክኑት ወይም ከሚወገዱት ፈንጂዎች በጣም የሚበልጡ ብዙ ፈንጂዎች በየቀኑ ስለሚቀበሩ በፈንጂዎች ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር በጣም እያደገ መጥቷል” ብሏል።
ይህ በ1993 በወጣ ጋዜጣ ላይ የሰፈረ ርዕስ እንደ ዘገበው የእነዚህ ፈንጂዎች ሽያጭ “በየዓመቱ 200 ሚልዮን ዶላር ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ ሆኗል።” በዚህ ንግድ የሚሳተፉ “በ48 አገሮች የሚገኙ 100 የሚያክሉ ኩባንያዎችና መንግሥታዊ ድርጅቶች” ሲኖሩ “340 ዓይነት” ፈንጂዎችን “ወደ ሌሎች አገሮች ይልካሉ።” አንዳንድ ፈንጂዎች ሕፃናት እንዲጫወቱባቸው ተብሎ አሻንጉሊት እንዲመስሉ ተደርገው መሠራታቸው ዲያብሎሳዊ ተግባር ነው! ምንም የማያውቁ ሕፃናትን ሆን ብሎ የግድያና የአካለ ስንኩልነት ዒላማ ማድረግ ምን ያህል አረመኔያዊ ድርጊት እንደሆነ አስብ! “100 ሚልዮን ፈንጂዎች” የሚል ርዕስ የተሰጠው አንድ ርዕሰ አንቀጽ እነዚህ ፈንጂዎች “ከኬሚካል፣ ከባዮሎጂካልና ከኑክሌር መሣሪያዎች ይበልጥ ለብዙ ሰዎች መገደል ወይም አካል መጉደል ምክንያት ሆነዋል” ብሏል።
ይሁን እንጂ በዓለም ገበያ የሚሸጡት የነፍስ መግደያ መሣሪያዎች ፈንጂዎች ብቻ አይደሉም። የጦር መሣሪያ የሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች በመላው ምድር ከሚያካሂዱት ንግድ ብዙ ቢልዮን ዶላር በማግበስበስ ላይ ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ መረጃ ማዕከል የሚታተመው ዘ ዲፌንስ ሞኒተር የተባለ መጽሔት እንደ ዘገበው ከሆነ “ባለፉት አሥር ዓመታት [አንድ ኃያል መንግሥት] 135 ቢልዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሣሪያ ሸጧል።” በተጨማሪም ይኸው ኃያል መንግሥት “በ142 አገሮች ውስጥ 63 ቢልዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሣሪያ ሽያጭ፣ ወታደራዊ ግንባታና ሥልጠና እንዲከናወን ፈቃድ ሰጥቷል።” በዚህ መንገድ ወደፊት ሌሎች ጦርነቶች ወደሚያስነሡና በሰው ልጅ ላይ መከራ ወደሚያስከትሉ ሁኔታዎች የሚያመሩ ነገሮች ተፈጥረዋል። ዘ ዲፌንስ ሞኒተር እንዲህ ብሏል፦ “በ1990 ብቻ 5 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ለጦርነት ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ላይ ይገኙ ነበር። ጦርነት ያስከተለው ኪሣራ 50 ቢልዮን ዶላር ሲሆን ሩብ ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች ተገድለዋል። ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።” ከዚያ ዓመት ጀምሮ ፈንድተው ፍርሃት ያስከተሉና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለእልፈት የዳረጉ በርካታ ጦርነቶች ልታስታውስ እንደምትችል አያጠራጥርም!
በምድርና በእርሷ ላይ በሚኖሩት ፍጥረታት ላይ እየደረሰ ያለው ተጨማሪ ጥፋት
ፕሮፌሰር ባሪ ኮሞነር “ይህ የምድር መበከል ልጓም ካልተበጀለት ውሎ አድሮ ይህች ፕላኔት ለሰው መኖሪያ መሆን ወደማትችልበት ደረጃ ትደርሳለች ብዬ አምናለሁ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አስተያየታቸውን በመቀጠል ችግሩ የተከሰተው ባለማወቅ ሳይሆን ሆን ተብሎ በሚደረግ ስግብግብነት ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። ጻድቅና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይህን ሁኔታ ለዘላለም ዝም ብሎ በመመልከት ብክለት እየጨመረ ይሄዳል በሚል ፍራቻ ተውጠን እንድንኖር የሚተወን ይመስልሃል? የተበላሸው የምድር ሁኔታ ምድርን በማበላሸት ላይ ላሉ ሰዎች ፍርድ እንዲሰጥና ከዚያም በኋላ ምድራችን መለኮታዊ ተሐድሶ እንድታገኝ ጥሪውን እያሰማ ነው። ይህም ኢየሱስ ‘የዓለምን ፍጻሜ’ በተመለከተ ለሐዋርያት መልስ ሲሰጣቸው ከጠቀሳቸው ነገሮች አንዱ ነው።
ይሖዋ ይህን ፍርድ እንዴት እንደሚሰጥ ከመመልከታችን በፊት የሰው ልጅ ያደረጋቸውን ነገሮች በዝርዝር እንመርምር። የሰው ልጅ ያደረሰውን ጉዳት በከፊል እንኳ ብንዘረዝር በጣም አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን። የአሲድ ዝናብ፣ ትላልቅ ደኖችን በማውደም ላይ የሚገኘው ስግብግብ ሰዎች የተያያዙት የዛፎች ጭፍጨፋ፤ የኑክሌር ዝቃጮችን፣ መርዛማ ኬሚካሎችንና ቆሻሻን ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በየቦታው መጣል፤ የዖዞን ሽፋን መመናመን እና የተባይና የአረም ማጥፊያ መድኃኒቶችን አለአግባብ መጠቀም ጥቂቶቹ ናቸው።
ምድር ትርፍ ለማግኘት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በሌሎች መንገዶች በመበከል ላይ ነች። በየቀኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ ወደ ወንዞች፣ ወደ ውቅያኖሶች፣ ወደ አየርና ወደ አፈር ይጣላል። ሳይንቲስቶች ወደ ጠፈር የላኩትን ቆሻሻ መልሰው ባለመሰብሰባቸው ምክንያት ሰማይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በመሆን ላይ ነው። ምድራችን ዙሪያዋን በሚሽከረከር የቆሻሻ ክምር በመሞላት ላይ ናት። አምላክ ምድርን ራሷን በራሷ ለማደስ የሚያስችላት ተፈጥሮያዊ ሂደት እንዲኖራት አድርጎ ባይሠራት ኖሮ ምድራዊ መኖሪያችን ሕይወት ማቆየት ይሳናት ነበር። የሰው ልጅ ከብዙ ጊዜ በፊት ራሱ በፈጠረው ቆሻሻ ራሱን መርዞ ይጨርስ ነበር።
የሰው ልጅ የራሱን ሰውነት ሳይቀር ይበክላል። ለምሳሌ ያህል፣ ትንባሆንና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን ተመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ ትንባሆ ማጨስና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ “በአገሪቱ ውስጥ በአንደኛ ደረጃ የሚታይ የጤና ችግር ሆኗል” ተብሏል። ይህ የጤና ችግር በዚህች አገር ላይ በየዓመቱ የ238 ቢልዮን ዶላር ወጪ ያስከትላል። ከዚህ ውስጥ 34 ቢልዮን ዶላር የሚውለው “አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች [ማለትም ሊወገዱ በሚችሉ ምክንያቶች ለሚመጡ በሽታዎች] መታከሚያ ነው።” አንተ በምትኖርበት አገር ውስጥ ትንባሆ ምን ያህል ገንዘብና ሕይወት የሚያጠፋ ይመስልሃል?
ብዙዎች መብታችን ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው በሚሟገቱለት ልቅና ነውረኛ አኗኗር ሳቢያ ቀሳፊ የሆኑ የአባላዘር በሽታዎች በመስፋፋታቸው ብዙ ሰዎች አለዕድሜያቸው ተቀጭተዋል። በታላላቅ ከተሞች የሚታተሙ ጋዜጦች የዜና እረፍት አምዶች ከ30 እስከ 40 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ሳሉ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ያሳያሉ። ለምን እንዲህ ሆነ? ለብዙዎች መሞት ምክንያት የሆነው ሲከተሉ የኖሩት መጥፎ ልማድ ያስከተለባቸው ጠንቅ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” ይሆናል ብሎ ስለ ነበር እንደዚህ ያሉ የአባላዘር በሽታዎች ሌሎች በሽታዎች መስፋፋታቸው ከኢየሱስ ትንቢት ጋር ይስማማል።
ይሁን እንጂ ከሁሉ የከፋው ብከላ በሰዎች አእምሮና መንፈስ ወይም ዝንባሌ ላይ የደረሰው ብከላ ነው። እስካሁን የጠቀስናቸውን የብከላ ዓይነቶች መለስ ብለህ ብትመለከት ለብዙዎቹ ብከላዎች ምክንያት የሆነው የሰዎች አእምሮ መበከሉ አይደለምን? በተጨማሪም በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ደረጃ ጤናማ ያልሆነ አእምሮ ያላቸው ሰዎች በሚፈጽሙት ግድያ፣ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል፣ ዝርፊያና በሌሎች የዓመፅ ተግባራት ሳቢያ የደረሰውን ጥፋት አስብ። ከዚህም ሌላ በየዓመቱ የሚፈጸሙትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ውርጃዎች ብዙዎች የሰዎች አእምሮና መንፈስ የተበከለ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
ይህን ብከላ በልጆች ዝንባሌ ላይ በብዛት እንመለከታለን። ልጆች ለወላጆችና ለሌሎች ባለ ሥልጣናት አክብሮት ባለማሳየታቸው ምክንያት ቤተሰቦች እየፈራረሱ ነው፣ ሕግና ሥርዓትም እየተጣሰ ነው። ይህ አምላክ ላቋቋመው ሥልጣን ጤናማ ፍርሃት ያለማሳየት ባሕርይ ወጣቶች መንፈሳዊነት የሌላቸው ከመሆናቸው ጋር ቀጥተኛ ዝምድና አለው። ስለዚህ ዝግመተ ለውጥን፣ አምላክ የለም ባይነትንና ሌሎች እምነት አጥፊ ንድፈ ሐሳቦችን የሚያስተምሩ ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ወንጀለኞች ናቸው። በተጨማሪም ዘመናዊና “ትክክለኛ” መስለው ለመታየት በሚያደርጉት ጥረት ለአምላክ ቃል ጀርባቸውን የሰጡት ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች ወንጀለኞች ናቸው። እነሱም ሆኑ በዓለም ጥበብ የተካኑ ሌሎች ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችን ያስተምራሉ።
ይህ ሁሉ ያስከተለው ውጤት በአሁኑ ጊዜ በግልጽ ይታያል። ሰዎች የሚመሩት ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ሳይሆን በስግብግብነትና በጥላቻ ነው። ያስገኙት መጥፎ ፍሬ በስፋት የተሰራጨ የሥነ ምግባር ውድቀት፣ ዓመፅና ተስፋ ቢስነት ነው። የሚያሳዝነው ይህ ሁኔታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሰው ልጅ ራሱንም ሆነ ዓለማችንን ያጠፋ ይሆናል ብለው እንዲሰጉና ሌሎች ነገሮችን እንዲፈሩ አድርጓቸዋል።
ነገሩ እየተባባሰ ይሄዳል ወይስ ይሻሻላል?
ፍርሃትን በሚመለከት በቅርቡ ምን ይፈጸማል? ፍርሃት እየጨመረ ይሄዳል ወይስ ይወገዳል? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የነገራቸውን በድጋሚ እንመልከት።
በቅርቡ ታላቅ መከራ እንደሚመጣ ገልጿል። እንዲህ አለ፦ “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።”—ማቴዎስ 24:29, 30
ስለዚህ ታላቁ መከራ በቅርቡ እንደሚጀምር ልንጠብቅ እንችላለን። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ታላቁ መከራ የሚጀምረው በመላው ዓለም በሚገኘው የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት እንደሆነ ያሳያሉ። ከዚያም ከዚህ በፊት የተገለጹት አስደንጋጭ ሁኔታዎች ይከሰታሉ። ይህም በሰማይ ላይ በሆነ መልክ የሚታይ ክስተትን ይጨምራል። ይህ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?
ኢየሱስ ለሰጠው መልስ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ትንቢታዊ ሐሳቦች የምናገኝበትን የሚከተለውን ተመሳሳይ ዘገባ ተመልከት፦
“በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ እያመነቱ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና።”—ሉቃስ 21:25, 26
ይህ ወደፊት የሚፈጸም ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች በፍርሃት ይደክማሉ። ኢየሱስ ከዚህ በተቃራኒ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ብሏል።—ሉቃስ 21:28
ኢየሱስ እነዚህን የሚያበረታቱ ቃላት የተናገረው እውነተኛ ተከታዮቹን በሚመለከት ነው። በፍርሃት ከመድከም ወይም ከመሽመድመድ ይልቅ የታላቁ መከራ ከፍተኛ ደረጃ በጣም እንደ ቀረበ ቢያውቁም እንኳ በድፍረት ራሳቸውን ቀና የሚያደርጉበት ምክንያት አላቸው። የማይፈሩት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ከጠቅላላው “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች እንደሚኖሩ ስለሚናገር ነው። (ራእይ 7:14) የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በሕይወት ከሚተርፉት ሰዎች መካከል ከሆንን ወደር የሌላቸው በረከቶች ከአምላክ እጅ እንደምንቀበል ተስፋ ይሰጣል። ኢየሱስ “እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል” የሚል ማረጋገጫ በመስጠት ይደመድማል።—ራእይ 7:16, 17
እነዚህን በረከቶች የሚያገኙት በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚያሰጓቸው ነገሮች አያስፈሯቸውም። እኛም ከእነዚህ መካከል ልንሆን እንችላለን። ሆኖም እነዚህን በረከቶች የሚያገኙ ሰዎች ምንም ዓይነት ፍርሃት አይኖራቸውም ማለት አይደለም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩና ጤናማ የሆነ ፍርሃት እንዳለ ያሳያል። በሚቀጥለው ርዕስ ይህ ፍርሃት ምን ዓይነት ፍርሃት እንደሆነና እኛን እንዴት ሊነካን እንደሚገባ እንመለከታለን።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች እየተቃረበ የመጣውን አዲስ ዓለም በደስታ ይጠባበቃሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብክለት፦ Photo: Godo-foto; ሮኬት፦ U.S Army Photo; የዛፎች ቃጠሎ፦ Richard Burregard, Smithsonian institution