የአጉረምራሚ ሰው የሕይወት ዕጣ አስደሳች የማይሆነው ለምንድን ነው?
ከጥቂት ሣምንታት በፊት በደስታ ፈንድቆ የነበረው ሕዝብ ተስፋ ወደ መቁረጥ ተመለሰ። እስራኤላውያን ከግብጻውያን ባርነት ነጻ በመውጣታቸው ምክንያት ያገኙት ደስታና ፍንደቃ እየቀነሰ ሄዶ ስለሚበሉት ምግብ ማጉረምረም ጀመሩ። ይህ አጉረምራሚ ሕዝብ ከግብጽ በወጣ በሁለተኛው ወር በምድር በዳ አስቸጋሪ ኑሮ ከመኖር የግብጽን ባርነት መረጠ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ወራትም እስራኤላውያን የነበራቸው ይህ የማጉረምረም መንፈስ ይሖዋን ለመታዘዝ የነበራቸውን ቁርጥ ውሳኔ ከማዳከሙም በላይ ያ ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ አድርጎአል። — ዘጸአት 16:1–3፤ ዘኁልቁ 14:26–30
እርግጥ አጉረምራሚነት በአንድ ትውልድ ወይም በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ስለ ሥራው፣ ስለ ምግቡ፣ ስለ አየሩ ሁኔታ፣ ስለ ልጆቹ፣ ስለ ጎረቤቶቹ ወይም ስለ ኑሮ ውድነት አልፎ አልፎ የማያጉረመርም ማን አለ? ሰብዓዊ አለፍጽምና ወደ ማጉረምረም ያዘነበለ ይመስላል። — ሮሜ 5:12፤ ያዕቆብ 3:2
ማጉረምረም የሚቀናን ለምንድን ነው? ምናልባት ተስፋ ቆርጠን፣ አዝነን ወይም ታመን ይሆናል። ማጉረምረማችን ለብስጭታችን መወጫ ሊሆን ይችላል። አለበለዚያም በተዘዋዋሪ መንገድ “እኔ የተሻለ ልሠራ እችላለሁ” ማለት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር በመጋጨት ምክንያት ማጉረምረም ሊመጣ ይችላል። በትክክል ሊያበሳጩ የሚችሉ ሁኔታዎችም ያጋጥማሉ።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ማጉረምረም ከቆየ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ቀደም ብለን የተመለከትነው የእስራኤላውያን ምሳሌ ያስረዳል። አንድ ሰው ሥር የሰደደ የማጉረምረም መንፈስ ሊኖረው ይችላል። በይሖዋ አሠራር ላይ እንኳን ሊያጉረመርም ይችላል። ይህ ሁኔታ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለማጉረምረም በቂ ምክንያት ሲኖር ሁኔታውን በተገቢ መንገድ ማስተካከል የሚቻለው እንዴት ነው?
ለማጉረምረም ትክክለኛ መሠረት ሊኖር ይችላል
የተፈጸመው ስህተት ከባድ ካልሆነ ራሳችንን መጠየቅ የሚኖርብን የመጀመሪያ ጥያቄ በፍቅር ላልፈው እችላለሁን? የሚል ነው። እርግጥ፣ በአንድ ሰው ላይ፣ የእምነት ባልደረባችንም ሊሆን ይችላል፣ የምናጉረመርምበት በቂ ምክንያት ሊኖረን ይችላል። ተገቢ ያልሆነ ወይም ደግነት የጎደለው ነገር አድርጎብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለተፈጸመብን በደል ለሌሎች ስሞታ መናገር ሁኔታውን ሊያሻሽል ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንድናደርግ ያሳስበናል? ቆላስይስ 3:13 እንዲህ ይላል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ [ይሖዋ አዓት] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” ስለዚህ ለማጉረምረም የሚያስችል ተገቢ ምክንያት ቢኖርም እንኳን አጉረምራሚ ከመሆን ይልቅ ይቅር ባይ መሆን እንደሚሻል ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳስባሉ። — ማቴዎስ 18:21, 22
ጉዳዩ በጣም ከባድ በመሆኑ ምክንያት ሊረሳ የማይችል ከሆነስ? ወቀሳ ለማሰማት የሚያበቃ ጥሩ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ይሖዋ ተገቢ የሆነ “የሰዶምና ገሞራ ጩኸት” እጅግ በበዛ ጊዜ በእነዚያ ምግባረ ብልሹ ከተሞች የነበረውን ሁኔታ ለማስወገድ እርምጃ ወስዶአል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓልም ለማጉረምረም የሚያበቃ ሌላ ተገቢ ምክንያት ተፈጥሮአል። ችግረኛ ለሆኑ መበለቶች ምግብ በሚታደልበት ጊዜ ዕብራይስጥ ተናጋሪ ለሆኑ ሴቶች አድልዎ ተደርጎ ነበር። ይህም ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑትን መበለቶች ቅር አሰኘ። በኋላም ቅሬታው ወደ ሐዋርያት ጆሮ ደረሰና ወዲያው ችግሩን እንዲያስተካክሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ተመደቡ። — ሥራ 6:1–6
ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከበድ ያሉ ጉዳዮች በሚቀርቡላቸው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘግየት አይኖርባቸውም። ምሳሌ 21:13 “የድሃውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም” ይላል። ሽማግሌዎች ምክንያታዊ የሆነ ቅሬታ ሲቀርብላቸው ችላ ከማለት ይልቅ በሐዘኔታ ማዳመጥ ይኖርባቸዋል። በሌላው በኩል ደግሞ ሁላችንም ከበድ ያሉ ቅሬታዎችን ሊሰማን ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ሁሉ ከማውራት ይልቅ ጉዳዩን ወደ ሽማግሌዎች በመውሰድ ልንተባበር እንችላለን።
ይሁን እንጂ አብዛኞቻችን በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ሳያስፈልግ የምናጉረመርምበት ጊዜ እንዳለ ለማመን እንገደዳለን። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ያሳዩትን ባሕርይ ቀረብ ብለን ብንመረምር አልፎ አልፎ በውስጥ የሚሰማው ማንጐራጐር ተባብሶ የማጉረምረም መንፈስ ሲያስከትል አደገኛ መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳናል።
አምላክ ስለ አጉረምራሚዎች ያለው አመለካከት
እስራኤላውያን ስለ ምግብ አቅርቦት ማጉምረማቸው የማጉረምረምን ሁለት አደገኛ ባሕርያት ያሳየናል። በመጀመሪያ ደረጃ ማጉረምረም ተላላፊ ነው። ታሪኩ “የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ” ይላል። (ዘጸአት 16:2) በቂ ምግብ ባለመኖሩ ማጉረምረም የጀመሩት ጥቂት ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። ብዙ ሳይቆይ ግን ሁሉ ሰው ማጉረምረም ጀመረ።
በሁለተኛ ደረጃ አጉረምራሚ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ችግሩን ያጋንናል። እስራኤላውያን ዳቦና ሥጋ እንደ ልባቸው ይበሉበት የነበረው የግብጽ ምድር ይሻላቸው እንደነበረ ተናግረዋል። ወደ ምድር በዳ የመጡት በረሐብ ለመሞት ብቻ እንደሆነ በመናገር አጉረመረሙ። — ዘጸአት 16:3
የእስራኤላውያን ሁኔታ ይህን ያህል የከፋ ነበርን? ምናልባት የያዙት ስንቅ እያለቀ መሄድ ጀምሮ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያለ ችግር እንደሚመጣ በቅድሚያ አውቆ ሥጋዊ ችግራቸውን የሚያስወግድላቸውን መና አዘጋጀላቸው። ከመጠን በላይ አጋንነው ማጉረምረማቸው በአምላክ ላይ እምነት የማይጥሉ ሰዎች መሆናቸውን አጋልጦባቸዋል። በግብጽ በነበሩበት ጊዜ ስለተጣለባቸው ጭቆና ማጉረምረማቸው ተገቢ ነበር። (ዘጸአት 2:23) ይሖዋ ከባርነት ነጻ ባወጣቸው ጊዜ ግን ስለ ምግብ ማጉረምረም ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የሚያጉረመርሙበት በቂ ምክንያት አልነበራቸውም። ሙሴም “ማንጎራጎራችሁ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም” ሲል አስጠንቅቆአቸዋል። — ዘጸአት 16:8
ይህ የእስራኤላውያን የአጉረምራሚነት መንፈስ በተደጋጋሚ ተከስቶአል። በአንድ ዓመት ውስጥ ስለ መናው ማጉረምረም ጀመሩ። (ዘኁልቁ 11:4–6) ከዚያ በኋላ ደግሞ ብዙም ሳይቆይ ከ12ቱ ሰላዮች መካከል አሥሩ የተናገሩትን ሰምተው የተስፋይቱን ምድር መያዝ ከባድ አደጋ እንደሚያመጣባቸው በማሰብ ጮሁ። “በግብጽ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ” እስከማለት ደረሱ። (ዘኁልቁ 14:2) ምንኛ ምስጋና የጎደላቸው ሰዎች ነበሩ! ይሖዋ ለሙሴ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም?” ማለቱ አያስደንቅም። (ዘኁልቁ 14:11) እነዚህ ምሥጋና ቢስ አጉረምራሚዎች ትውልዳቸው ሞቶ እስኪያልቅ ድረስ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ ተፈርዶባቸዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ምሳሌ ያሳስበናል። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን አጉረምራሚዎች በመሆናቸው ምክንያት በምድረ በዳ እንደጠፉት እስራኤላውያን እንዳይሆኑ አስጠንቅቆአል። (1 ቆሮንቶስ 10:10, 11) አለበቂ ምክንያት ቅሬታ ማሰማትና የአጉረምራሚነት መንፈስ ማንጸባረቅ እምነታችንን ሊያዳክምብንና የይሖዋን መከፋት ሊያስክትልብን ይችላል።
ቢሆንም ይሖዋ ተስፋ በሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ምክንያት አልፎ አልፎ የሚያጉረመርሙትን አገልጋዩቹን ይታገሳል። ኤልያስ ክፉ የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል ስላሳደደችው ወደ ኮሬብ ተራራ በሸሸ ጊዜ የነቢይነት ሥራው እንዳበቃ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው የሌለ መስሎት ነበር። አምላክ የኤልያስን እምነት ለማጠንከር ሲል መጀመሪያ መለኮታዊ ኃይሉን ገለጠለት። ከዚያ በኋላ በእስራኤል ምድር 7,000 የሚያክሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዳሉና ገና ብዙ መሥራት የሚኖርበት ሥራ እንዳለው ነገረው። በዚህም ምክንያት ኤልያስ ማጉረምረሙን ረስቶ በአዲስ ጉልበት ሥራውን ጀመረ። (1 ነገሥት 19:4, 10–12, 15–18) ክርስቲያን ሽማግሌዎችም አስተዋዮች በመሆን ታማኝ ክርስቲያኖችን በሚያጽናና ቃል ሊናገሩና በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ እንዲያስተውሉ ሊረዱአቸው ይችላሉ። — 1 ተሰሎንቄ 5:14
የአጉረምራሚነትን መንፈስ ማሸነፍ
የአጉረምራሚነትን መንፈስ እንዴት ማሸነፍ ይቻላል? ትንባሆ በአካል ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ማስረጃ የቀረበላቸው ሰዎች ማጨስን ለማቆም የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት ይኖራቸዋል። በተመሳሳይም የአጉረምራሚነት መንፈስ ይህን ያህል አደገኛ የሆነበትን ምክንያት መረዳት ያለብንን የአጉረምራሚነት ልማድ ለማቆም ይረዳናል።
የአጉረምራሚነትን መንፈስ የሚያሸንፉ ሰዎች ምን ጥቅም ያገኛሉ? ከማጉረምረም የሚርቁ ሰዎች ከሚያገኙአቸው ጥቅሞች አንዱ ነገሮችን በቅዱሳን ጽሑፎች ዓይንና ሚዛናዊ በሆነ አመለካከት ሊያዩ መቻላቸው ነው። አጉረምራሚ ሰው ቆም ብሎ ችግሮችን በይሖዋ አመለካከት አያይም። አጉረምራሚዎቹ እስራኤላውያን ይሖዋ አምላክ ከባርነት ነጻ እንዳወጣቸውና ቀይ ባሕርን በተአምር እንደከፈለ ዘንግተዋል። አፍራሽ አስተሳሰባቸው የአምላክን ኃይል እንዳያዩ ከማሳወሩም በላይ ደስታ አሳጥቶአቸዋል። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ላይ የነበራቸው ትምክህት በንኖ ጠፋ።
ከዚህም በተጨማሪ ችግሮቹን በሚዛናዊነት ለመመልከት የሚችል ሰው ችግር ያስከተለበት የራሱ ስህተት የሚሆንበትን ጊዜ ያስተውላል። በዚህም ምክንያት ያንን ስህተቱን አይደግምም። ኤርምያስ እስራኤላውያን ወገኖቹን ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ በደረሰባቸው መከራ እንዳያጉረመርሙ አስጠንቅቆ ነበር። መከራ የደረሰባቸው በኃጢአታቸው ምክንያት ነበር። ንስሐ እንዲገቡና ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ከተፈለገ ይህን ማስተዋል ነበረባቸው። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:39, 40) ደቀ መዝሙሩ ይሁዳም በተመሳሳይ የይሖዋን መመሪያ የማይቀበሉትንና “ስለ ዕድላቸው የሚያጉረመርሙትን” አምላክ የለሽ ሰዎች ገስጾአል። — ይሁዳ 3, 4, 16
ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን አንድ ጊዜ እንደተናገረው “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች።” (ምሳሌ 17:22) የአጉረምራሚነት መንፈስ ስሜታችንን አሟጥጦ ደስታ ያሳጣናል። ገንቢ አስተሳሰብን ሳይሆን አፍራሽ አመለካከትን ያንፀባርቃል። ‘ምሥጋና ያለበትን’ ማሰብንና መናገርን የለመዱ ግን ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው የሚያስችል ደስተኛ ልብ አላቸው። — ፊልጵስዩስ 4:8
የሰዎችን ጉድለት ሳይሆን መልካምነታቸውን ብንመለከት ሕይወታችን በደስታ በይበልጥ የበለጸገ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ስላጋጠመን እንቅፋት ከማጉረምረም ይልቅ ፈታኝ የሆኑትን ሁኔታዎች በደስታ ብንቀበል መንፈሳችን ይነቃቃል። ፈተና በሚደርስብን ጊዜ እንኳን ፈተናውን እምነታችንንና ጽናታችንን እንደሚያጠናክር ጥሩ አጋጣሚ አድርገን ብንመለከት ከፈተናው ደስታ ልናገኝ እንችላለን። — ያዕቆብ 1:2, 3
በተጨማሪም በምናጉረመርምበት ጊዜ የምንጎዳው ራሳችንን ብቻ አለመሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ሁልጊዜ ስናጉረመርም የሌሎችን እምነት እንገዘግዛለን። አሥሩ እስራኤላውያን ያመጡት መጥፎ ሪፖርት መላው ሕዝብ ተስፋይቱን ምድር መውረስ ፈጽሞ የማይሳካ ሙከራ እንደሆነ አድርጎ እንዲመለከት አድርጎአል። (ዘኁልቁ 13:25 እስከ 14:4) በሌላ ጊዜ ሙሴ በሕዝቡ የማያባራ አጉረምራሚነት ምክንያት ቅስሙ ተሰብሮ ይሖዋ ሕይወቱን እንዲወስድለት ጠይቆአል። (ዘኁልቁ 11:4, 13–15) በሌላው በኩል ደግሞ የሚያንጹ ቃላት ብንናገር የሌሎችን እምነት ልንገነባና ለደስታቸው አስተዋጽኦ ልናደርግ እንችላለን። — ሥራ 14:21, 22
ስለ ሥራ ባልደረቦቻችን፣ ስለ ወዳጆቻችን፣ ስለ ቤተሰባችን ወይም ስለ ጉባኤ ሽማግሌዎች ለማጉረምረም ልንፈተን ብንችልም ይሖዋ ሕዝቦቹ በሙሉ እርስ በርሳቸው የጋለ ፍቅር እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ይህ ዓይነቱ ፍቅር የሌሎችን ስሕተቶች ከማጉላት ይልቅ እንድንሸፍንላቸው ይገፋፋናል። (1 ጴጥሮስ 4:8) ይሖዋ አፈር መሆናችንን ስለሚያስብና ስህተታችንን ስለማይከታተል እናመሰግነዋለን። (መዝሙር 103:13, 14፤ 130:3) ሁላችንም የይሖዋን አርዓያ ለመከተል ብንሞክር የማጉረምረም መንፈሳችን በጣም እንደሚቀንስ ጥርጥር የለውም።
የሰው ልጅ እንደገና ፍጽምና ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ በሕይወቱ ስለሚያጋጥመው ዕጣ የሚያጉረመርም ሰው አይኖርም። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ስለ ሌሎችም ሆነ ስለሚያጋጠሙን ፈታኝ ሁኔታዎች ከማጉረምረም መቆጠብ ይኖርብናል። በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለንና የእምነት ባልደረቦቻችንን እንደምንወድ ለማሳየት ‘ሳናንጎራጉር ሁሉን እናድርግ።’ (ፊልጵስዩስ 2:14) ይህም ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል፣ እኛንም በጣም ይጠቅመናል። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ደህንነት ስንል የአጉረምራሚ ሰው የሕይወት ዕጣ አስደሳች አለመሆኑን እናስታውስ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ በተአምር ያስገኘላቸው መናም እንኳ ለማጉረምረም ምክንያት ሆኗል