ከግብፅ ሃብት የሚልቅ ነገር
ሙሴ በታሪክ ውስጥ ከታዩት ታላላቅ ሰዎች መካከል የሚጠቀስ ነው። ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ያሉት አራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የሚናገሩት አምላክ ሙሴን ተጠቅሞ ከእስራኤላውያን ጋር ስላደረገው ግንኙነት ነው። ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል፤ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ በመሆን አገልግሏል፤ እንዲሁም እስራኤልን እስከ ተስፋይቱ ምድር መዳረሻ መርቷል። ሙሴ በፈርኦን ቤት ውስጥ ቢያድግም ነቢይ፣ ፈራጅና በመለኮታዊ መንፈስ የሚመራ ጸሐፊ ነበር። በአምላክ ሕዝቦች ላይ የመግዛት ሥልጣን ቢኖረውም “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።”—ዘኁልቍ 12:3
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሙሴ ተጠቅሶ የምናገኘው አብዛኛው ዘገባ የሚያተኩረው ሙሴ ባሳለፋቸው የመጨረሻዎቹ 40 ዓመታት ላይ ሲሆን ይህም እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ሙሴ በ120 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ያለውን ይሸፍናል። ሙሴ ከ40 እስከ 80 ዓመቱ ድረስ በምድያም እረኛ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ዘገባ እንደገለጸው ከሆነ ምናልባትም ከውልደቱ ወደ ግብጽ እስከተሰደደበት ጊዜ ድረስ ያሉት የመጀመሪያዎቹ 40 ዓመታት “ለማወቅ የሚያጓጉ ሆኖም ብዙም ያልተባለላቸው የሕይወቱ ክፍሎች” ናቸው። ስለዚህ ጊዜ ምን ለማለት እንችላለን? የሙሴ አስተዳደግ በኋለኛው ሕይወቱ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው? ለምን ዓይነት ተጽእኖዎችስ ተጋልጦ ነበር? ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎችንስ መጋፈጥ ነበረበት? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
በግብጽ አገር በባርነት መኖር
የዘጸአት መጽሐፍ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በፍጥነት እየተባዙ በመምጣታቸው በዘመኑ ይገዛ የነበረው የግብጽ ፈርኦን ስጋት እንዳደረበት ይናገራል። ስለዚህም ቁጥራቸውን ለመቀነስ የሚያስችል “ዘዴ” እንደቀየሰ አድርጎ በማሰብ እስራኤላውያኑን ለከፋ ባርነት ዳረጋቸው። በግብፃውያን አለቆች እየተገረፉ ከባድ ሸክም መሸከም፣ ጡብ መሥራትና የየቀኑን የጡብ ኮታ አሟልተው ማቅረብ ነበረባቸው።—ዘጸአት 1:8-14 አ.መ.ት ፤ 5:6-18
ስለ ሙሴ የትውልድ አገር ማለትም ስለ ግብጽ የተሰጠው መግለጫ ከታሪካዊው ማስረጃ ጋር ይስማማል። በፓፒረስ የተዘጋጁ የጥንት ጽሑፎችና ቢያንስ በመቃብር ላይ የተቀረጸ አንድ ሥዕል በሁለተኛው ሺህ ከዘአበ ወይም ከዚያ ቀደም ብሎ ስለነበረው የጡብ አሠራር ይገልጻሉ። ጡብ እንዲያቀርቡ የተመደቡት ግለሰቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ ባሮች ካሰባሰቡ በኋላ ከ6 እስከ 18 የሚሆኑ አባላት ባሏቸው ቡድኖች ይከፋፍሏቸዋል። ከዚያም ለእያንዳንዱ ቡድን አንድ አለቃ ወይም መሪ ይመድቡለታል። ለጡብ የሚሆነው አፈር ከመሬት ተቆፍሮ መውጣት ያለበት ሲሆን ጭዱንም ወደ ጡብ መሥሪያው አካባቢ መውሰድ ያስፈልጋል። ከተለያየ አገር የመጡ ሠራተኞች ውኃ ከጉድጓድ ካወጡ በኋላ ጭቃውንና ጭዱን አንድ ላይ ያቦኩታል። ቀጥሎም በቅርጽ ማውጫ አማካኝነት የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ጡቦች ይሠራሉ። ከዚያም በፀሐይ የደረቁትን ጡቦች ጫፍና ጫፉ ላይ ሁለት መያዣ ባለው ቀንበር ተሸክመው ወደ ግንባታ ቦታዎቹ ይወስዷቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ጡቦቹን ወደ እነዚህ ቦታዎች ለማድረስ በመወጣጫ መጠቀም ያስፈልጋል። ጅራፍ የያዙ ግብፃውያን አስገባሪዎች በመካከላቸው ጎርደድ ጎርደድ እያሉ አሊያም ቁጭ ብለው ይቆጣጠሯቸዋል።
አንድ ጥንታዊ ዘገባ 602 የቀን ሠራተኞች ስለሠሯቸው 39, 118 ጡቦች ይገልጻል። ይህ ማለት አንድ ሰው በአንድ ፈረቃ ብቻ በአማካይ 65 ሸክላዎችን ሠርቷል ማለት ነው። እንዲሁም በ13ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተገኘ አንድ ዘገባ እንደሚገልጸው “ወንዶቹ . . . ለቀኑ የተመደበውን ጡብ ይሠሩ ነበር።” ይህ ሁሉ እስራኤላውያን እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸው የነበረውን ግዴታ በተመለከተ በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጸው ጋር ይስማማል።
ይሁን እንጂ ጭቆናው የዕብራውያኑን ቁጥር ከመጨመር አላገደውም። እንዲያውም “[ግብጻውያኑ] ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቁጥር በዛ፤ . . . ከዚህም የተነሣ ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው።” (ዘጸአት 1:10, 12 አ.መ.ት ) በመሆኑም ፈርኦን በመጀመሪያ ዕብራውያኑን አዋላጆች ቀጥሎም ሕዝቡን በአጠቃላይ የሚወለደውን እስራኤላዊ ወንድ ሁሉ እንዲገድሉ አዘዛቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእንበረም ሚስት ዮካብድ ሙሴ የተባለ አንድ የሚያምር ሕፃን ወለደች።—ዘጸአት 1:15-22፤ 6:20፤ ሥራ 7:20
ተደበቀ፣ ተገኘ በኋላም ለማደጎ ተሰጠ
የሙሴ ወላጆች የፈርዖንን ጭካኔ የተሞላበት ትእዛዝ በመጣስ ትንሹን ልጃቸውን ደበቁት። ወላጆቹ ይህንን ሲያደርጉ በየቤቱ እየዞሩ አዲስ የተወለዱ ሕፃናትን የሚፈልጉ ሰላዮችና ቤት ፈታሾች ነበሩን? ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ወላጆቹ ሙሴን ከሦስት ወራት በላይ ደብቀው ሊያቆዩት አልቻሉም። ስለዚህም በጭንቀት የተዋጠችው እናቱ የደንገል ቅርጫት ካመጣች በኋላ ውኃ እንዳያስገባ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው። ከዚያም ልጅዋን በውስጡ አስተኛችው። ምንም እንኳ ዮካብድ የሚወለደው ዕብራዊ ወንድ ሁሉ ወደ ወንዝ እንዲጣል ፈርዖን የሰጠውን ትእዛዝ በቀጥታ ባትፈጽምም ልጅዋን ውኃው ላይ ማስቀመጧ አልቀረም። የሙሴ ታላቅ እኅት ማርያም የሚደርስበትን ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ትከታተል ነበር።—ዘጸአት 1:22–2:4
ዮካብድ የፈርዖን ልጅ ገላዋን ለመታጠብ ስትመጣ እንድታገኘው ሆን ብላ ያደረገችው ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር ባይኖርም ንግሥቲቱ ሕፃኑን አግኝታዋለች። ሕፃኑ የዕብራውያን ልጅ እንደሆነ ገብቷታል። ምን ታደርግ ይሆን? ከአባቷ ትእዛዝ ጋር በመስማማት ታስገድለው ይሆን? በፍጹም። የሴት አንጀቷ በሕፃኑ ላይ ሊጨክን አልቻለም።
ወዲያው ማርያም ሮጣ ወደ ንግሥቲቱ መጣችና ‘ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽ?’ ስትል ጠየቀቻት። አንዳንዶች ይህንን ዘገባ ሲያነብቡ በጣም ይገረማሉ። የሙሴ እህት ያደረገችው ነገር ፈርዖን ዕብራውያንን “በዘዴ” በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ከአማካሪዎቹ ጋር የሸረበውን ሴራ የሚጻረር ነበር። እርግጥ፣ የሙሴ ደህንነት የተመካው ንግሥቲቱ በእህቱ እቅድ በመስማማቷ ላይ ነበር። የፈርኦን ልጅ ‘እንድትሄድ’ ስትነግራት ማርያም ሮጣ ሄዳ እናቷን ጠራቻት። በመጨረሻም ዮካብድ በንጉሣዊ ቤተሰብ እንክብካቤ ሥር የገዛ ልጅዋን ለማሳደግ በደመወዝ ተቀጠረች።—ዘጸአት 2:5-9
ንግሥቲቷ ያሳየችው ርኅራኄ አባቷ ካሳየው ጭካኔ ፈጽሞ ተቃራኒ ነበር። ስለ ልጁ ማንነት ሳታውቅ ቀርታ ወይም ተታልላ ያደረገችው አልነበረም። ሕፃኑ አንጀቷን ስለበላው ወስዳ ልታሳድገው ፈለገች። ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግ ዕብራዊት ሞግዚት በማምጣቱ ሐሳብ መስማማቷም አባቷ የነበረው ዓይነት መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳልነበራት ያሳያል።
አስተዳደግና ትምህርት
ዮካብድ “ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። ሕፃኑም አደገ፣ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፣ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት።” (ዘጸአት 2:9, 10) መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ ከሥጋ ወላጆቹ ጋር ለምን ያህል ጊዜ እንደኖረ አይገልጽም። አንዳንዶች ቢያንስ ጡት እስኪጥል ማለትም ሁለት ወይም ሦስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ቆይቶ መሆን አለበት በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ጊዜም ቆይቶ ሊሆን ይችላል። የዘጸአት መጽሐፍ የሚገልጸው ወላጆቹ ‘እንዳሳደጉት’ ብቻ ነው። ከዚህ አገላለጽ ደግሞ እድሜውን በትክክል መናገር አይቻልም። ያም ሆነ ይህ አንበረምና ዮካብድ ይህንን ጊዜ ሙሴን ስለ ይሖዋ ለማስተማርና ዕብራዊ መሆኑን እንዲያውቅ ለማድረግ እንደተጠቀሙበት ምንም ጥርጥር የለውም። ወላጆቹ በሙሴ ልብ ውስጥ እምነትንና የጽድቅ ፍቅርን በመትከል ረገድ ምን ያህል እንደተሳካላቸው የሚያሳየው ጊዜ ብቻ ይሆናል።
ሙሴ ወደ ፈርዖን ልጅ ከተመለሰ በኋላ “የግብፆችን ጥበብ ሁሉ” ተማረ። (ሥራ 7:22) ይህ ለመንግሥት ባለ ሥልጣንነት የሚያበቃ ሥልጠና ማግኘትንም ይጨምራል። የግብጻውያን ትምህርት ሒሳብን፣ ጂኦሜትሪን፣ የሕንጻ ጥበብን፣ ግንባታን እንዲሁም የተለያዩ የሥነ ጥበብ ዘርፎችንና ሳይንስን ያካትታል። ምናልባትም ንጉሣዊው ቤተሰብ ሙሴ የግብጽን ሃይማኖት እንዲማር ማድረግ ፈልጎም ይሆናል።
ሙሴ ይህንን ከፍተኛ ትምህርት የወሰደው ከሌሎች የንጉሣውያን ቤተሰብ ልጆች ጋር መሆን አለበት። እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ትምህርት የመማር መብት ካገኙት መካከል “‘ከሰለጠኑ’ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው” የፈርዖን ታማኝ “ሎሌዎች በመሆን እንዲያገለግሉ ወደ ግብጽ የተላኩ ወይም በምርኮኛነት የመጡ የውጪ አገር ገዢዎች ልጆች” ይገኙበታል። (በቤትሲ ኤም ብራያን የተዘጋጀው የቱትሞስ አራተኛ የግዛት ዘመን የተባለው መጽሐፍ) በንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ሥር ባሉት የሕፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ የሚያድጉት ወጣቶች የቤተ መንግሥት ባለሟሎች ሆነው ለማገልገል የሚያስችላቸውን ሥልጠና ያገኙ የነበረ ይመስላል።a መካከለኛና አዲስ በመባል በሚታወቁት የግብጽ ሥርወ መንግሥታት ዘመን በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ከፈርዖን የቅርብ ባለሟሎችና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት መካከል አብዛኞቹ ትልልቅ ሰዎች ከሆኑም በኋላ እንኳ ሳይቀር “የሕፃናት ማሳደጊያው ልጆች” በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ ነበር።
የቤተ መንግሥት ሕይወት ሃብት፣ ምቾትና ሥልጣን የሚያስገኝ በመሆኑ ሙሴን እንደሚፈትነው የታወቀ ነው። ከዚህም ሌላ ሥነ ምግባራዊ አደጋም ነበረው። ሙሴ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን? ታማኝ የሚሆነው ለማን ይሆን? ሙሴ ከይሖዋ አምላክና ከተጨቆኑት ዕብራውያን ወገኖቹ ጎን ይቆም ይሆን ወይስ አረማዊ የሆነችው ግብጽ የምታቀርብለትን ኑሮ ይመርጥ ይሆን?
ከባድ ውሳኔ
ሙሴ ሙሉ በሙሉ ግብጻዊ መሆን በሚችልበት በ40 ዓመት እድሜው ‘ወንድሞቹን ለማየት ወጣ። የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ።’ ወዲያው የወሰዳቸው እርምጃዎች እንዲሁ የማወቅ ጉጉት አድሮበት እንዳልወጣ ከዚያ ይልቅ ግን ወንድሞቹን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያሉ። አንድ ግብጻዊ አንድን ዕብራዊ ሲመታ ሲመለከት ጣልቃ ገባና ግብፃዊውን ገደለው። ይህ ድርጊት የሙሴ ልብ ከወንድሞቹ ጋር እንደነበረ አረጋግጧል። የሞተው ሰው ምናልባት ሥራውን በመፈጸም ላይ የነበረ ባለ ሥልጣን ሊሆን ይችላል። ከግብጻውያን አመለካከት አንጻር ሙሴ ለፈርዖን ታማኝ እንዲሆን የሚያስገድዱት ብዙ ምክንያቶች ነበሩት። ሆኖም ሙሴን ለተግባር ያነሳሳው ሌላው ነገር ለፍትህ የነበረው ቅንዓት ነው። በሚቀጥለው ቀን የገዛ ባልንጀራውን አላግባብ ይመታ ከነበረ አንድ ዕብራዊ ጋር በተከራከረ ጊዜ ይህ ባሕርይው ይበልጥ ተንጸባርቋል። ሙሴ ዕብራውያንን ከባርነትና ከጭቆና ነጻ ለማውጣት ፈልጎ ነበር። ሆኖም ፈርዖን ይህንን ሲሰማ ሊገድለው ስለፈለገ ወደ ምድያም ለመሸሽ ተገደደ።—ዘጸአት 2:11-15፤ ሥራ 7:23-29b
ሙሴ የአምላክን ሕዝቦች ነጻ ለማውጣት ያሰበበት ወቅት ይሖዋ ካቀደው ጊዜ ጋር የሚስማማ አልነበረም። ያም ሆኖ ድርጊቱ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ዕብራውያን 11:24-26 “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ . . . ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ” በማለት ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም “ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦ” ስለነበረ ነው። “ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና።” “ክርስቶስ” ማለትም “የተቀባ” የሚለው እንግዳ የሆነ አነጋገር ከጊዜ በኋላ በቀጥታ ከይሖዋ ልዩ ተልእኮ ለተቀበለው ለሙሴ ተስማሚ መግለጫ ነው።
እስቲ አስበው! ሙሴ ከግብጻውያን ባላባቶች ወገን የተወለደ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊያገኘው በማይችለው ሁኔታ ሥር ተቀማጥሎ አድጓል። ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራና ከቁሳዊ ነገሮች ሊገኝ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ደስታ የማግኘት አጋጣሚ ነበረው። ቢሆንም ሁሉንም ትቷቸዋል። በጨቋኙ ፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ያለውን ሕይወት ለይሖዋና ለፍትሕ ካለው ፍቅር ጋር ማስማማት አልቻለም። አምላክ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የገባላቸውን ተስፋዎች ማወቁና በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ማሰላሰሉ መለኮታዊ ሞገስን እንዲመርጥ አነሳስቶታል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ዓላማዎቹን በማስፈጸም ረገድ ታላላቅ መብቶች በመስጠት ተጠቅሞበታል።
ሁላችንም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይተን እንድንመርጥ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ምናልባት አንተም ልክ እንደ ሙሴ ከፊትህ ከባድ ውሳኔ ተደቅኖብህ ይሆናል። የቱንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅብህ አንዳንድ ልማዶችን ወይም ጥቅም የሚያስገኙ አጋጣሚዎችን ትተዋለህ? በፊትህ የተደቀነው ምርጫ ይህ ከሆነ ሙሴ ከግብጽ ሃብት ሁሉ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ከፍ አድርጎ እንደተመለከተ አስታውስ። በዚህ ምርጫው ፈጽሞ አልተቆጨም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ትምህርት ዳንኤልና ጓደኞቹ በባቢሎን የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመሆናቸው በፊት ከተሰጣቸው ትምህርት ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል። (ዳንኤል 1:3-7) የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! በሚል ርዕስ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።
b ሙሴ መጻተኛ ሆኖ ወደ ምድያም በተሰደደበት ወቅት ረዳት የሌላቸውን የሴት እረኞች ይደርስባቸው ከነበረው በደል ታድጓቸዋል። በዚህም ለፍትህ የነበረው ቅንዓት በድጋሚ ተረጋግጧል።—ዘጸአት 2:16, 17
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከሚያጠቡ ሞግዚቶች ጋር የሚደረግ ውል
አብዛኛውን ጊዜ እናቶች የገዛ ልጆቻቸውን ያጠባሉ። ሆኖም ምሁሩ ብሬቫርድ ቻይልድስ ጆርናል ኦቭ ቢብሊካል ሊትሬቸር በተባለው ጽሑፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “አንዳንድ የባላባት [በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ] ቤተሰቦች አልፎ አልፎ ጡት አጥቢ ሞግዚት ይቀጥሩ ነበር። በተጨማሪም እናቲቱ ማጥባት ሳትችል ስትቀር ወይም ማንነቷ ሳይታወቅ ሲቀር ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግ ሞግዚት ትቀጠር ነበር። ሞግዚቷ በተሰጣት የጊዜ ገደብ ውስጥ ልጁን የማጥባትና የማሳደግ ኃላፊነት ነበረባት።” እያጠቡ ከሚያሳድጉ ሞግዚቶች ጋር የተደረጉ በርካታ ውሎች የሰፈሩባቸው ጥንታዊ ፓፒረሶች በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ተገኝተዋል። እነዚህ መዛግብቶች ከሱመሪያን ዘመን አንስቶ በግብፅ ሰፍኖ የነበረው የግሪክ ባሕልና አስተሳሰብ እስከከሰመበት ዘመን ድረስ ተስፋፍቶ የነበረውን ልማድ ይጠቁማሉ። መዛግብቱ ከያዟቸው ዋና ዋና ሐሳቦች መካከል ውሉን የተዋዋሉት ሰዎች ያሰፈሯቸው ሐሳቦች፣ ውሉ የሚጸናበት ጊዜ፣ የሥራው ሁኔታ፣ ስለ አመጋገብ የተሰጡ ዝርዝር ሁኔታዎች፣ ውሉን አለማክበር ስለሚያስከትለው ቅጣት፣ ደመወዝና ደመወዙ ስለሚከፈልበት መንገድ የሚገልጹ ሐሳቦች ይገኙበታል። ቻይልድስ አብዛኛውን ጊዜ “ውሉ ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመታት ይቆይ” እንደነበረ ገልጸዋል። “ሞግዚቷ ሕፃኑን ቤቷ ወስዳ ታሳድገዋለች። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የልጁን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ወደ ባለቤቱ እንድትመልሰው ትጠየቅ ነበር።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥንታዊው ሥዕል እንደሚያሳየው በግብጽ ያለው የጡብ ሥራ በሙሴ ዘመን ከነበረው ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል
[ምንጭ]
ከላይ:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.; ከታች:- Erich Lessing/Art Resource, NY