ምዕራፍ 07
ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው?
ስለ ይሖዋ አምላክ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? እንደ ከዋክብት በጣም የሚያስደምም ሆኖም ከአንተ እጅግ የራቀ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ እንደ መብረቅ በጣም ኃይለኛ ሆኖም ምንም ስሜት የሌለው አካል እንደሆነ አድርገህ ታስባለህ? በእርግጥ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው? ይሖዋ፣ ምን ባሕርያት እንዳሉት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደሚያስብ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ገልጿል።
1. አምላክን ማየት የማንችለው ለምንድን ነው?
“አምላክ መንፈስ ነው።” (ዮሐንስ 4:24) ይሖዋ ሥጋዊ አካል የለውም። ከዚህ ይልቅ መንፈስ ነው፤ የሚኖረውም በሰማይ እኛ ልናይ በማንችለው ቦታ ነው።
2. ከይሖዋ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ በዓይን ባይታይም ግሩም ባሕርያት ያሉትና የራሱ ማንነት ያለው አካል ነው። እነዚህን ባሕርያት ስናውቅ እሱን ለመውደድ እንነሳሳለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም” ይላል። (መዝሙር 37:28) በተጨማሪም ይሖዋ “እጅግ አፍቃሪና መሐሪ” ነው፤ በተለይ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ ሰዎች ፍቅርና ምሕረት ያሳያቸዋል። (ያዕቆብ 5:11) “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል።” (መዝሙር 34:18 የግርጌ ማስታወሻ) እኛ የምናደርገው ነገር ይሖዋን ሊያስደስተው ወይም ሊያስከፋው እንደሚችልስ ታውቃለህ? አንድ ሰው መጥፎ ነገር ሲያደርግ አምላክ ያዝናል እንዲሁም ስሜቱ ይጎዳል። (መዝሙር 78:40, 41) ጥሩ ነገር ሲያደርግ ደግሞ አምላክ ይደሰታል።—ምሳሌ 27:11ን አንብብ።
3. ይሖዋ እንደሚወደን ያሳየው እንዴት ነው?
ከይሖዋ ባሕርያት መካከል ጎልቶ የሚታየው ፍቅር ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ፍቅር እንዳለው ብቻ ሳይሆን ‘አምላክ ራሱ ፍቅር እንደሆነ’ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ብቻ አይደለም፤ የፈጠራቸው ነገሮችም የእሱን ፍቅር ያሳያሉ። (የሐዋርያት ሥራ 14:17ን አንብብ።) እኛን የፈጠረበትን መንገድ እንደ ምሳሌ መውሰድ ትችላለህ። ውብ ቀለማትን የማየት፣ አስደሳች ሙዚቃ የማዳመጥና ጣፋጭ ምግቦችን የማጣጣም ችሎታ ሰጥቶናል። አምላክ ደስተኛ ሆነን እንድንኖር ይፈልጋል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ይሖዋ አስደናቂ ነገሮችን ለማከናወን ምን እንደተጠቀመ እናያለን። ከዚያም ማራኪ ባሕርያቱን የገለጠው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
4. መንፈስ ቅዱስ—አምላክ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል
የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን እጃችንን እንደምንጠቀም ሁሉ ይሖዋም ቅዱስ መንፈሱን ይጠቀማል። መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ሳይሆን አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሉቃስ 11:13ን እና የሐዋርያት ሥራ 2:17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
አምላክ፣ ቅዱስ መንፈሱን ለማግኘት በሚጠይቁት ሰዎች ላይ ይህን መንፈስ ‘ያፈስሳል።’ ታዲያ መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ነው ወይስ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አስደናቂ ነገሮችን ለማከናወን ቅዱስ መንፈሱን ይጠቀማል። መዝሙር 104:30ን እና 2 ጴጥሮስ 1:20, 21ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን የተጠቀመባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
5. ይሖዋ ማራኪ ባሕርያት አሉት
ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ሙሴ ስለ ፈጣሪው ይበልጥ ማወቅ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም አምላክን “እንዳውቅህ . . . መንገድህን አሳውቀኝ” በማለት ጠይቆታል። (ዘፀአት 33:13) በምላሹም ይሖዋ አንዳንድ ባሕርያቱን ለሙሴ ገልጦለታል። ዘፀአት 34:4-6ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ለሙሴ የትኞቹን ባሕርያቱን ገልጦለታል?
ከይሖዋ ባሕርያት መካከል አንተን ይበልጥ የሚማርኩህ የትኞቹ ናቸው?
6. ይሖዋ ለሰዎች ያስባል
የአምላክ ሕዝቦች የሆኑት ዕብራውያን በግብፅ ባሪያዎች ነበሩ። ይሖዋ የሚደርስባቸውን መከራ ሲያይ ምን ተሰማው? ኦዲዮውን ከፍታችሁ ተከታተሉ ወይም ዘፀአት 3:1-10ን አንብቡ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ከዚህ ዘገባ መረዳት እንደምንችለው ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ሲያይ ምን ይሰማዋል?—ቁጥር 7 እና 8ን ተመልከት።
ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመርዳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ታምናለህ? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
7. ፍጥረት የይሖዋን ባሕርያት ይገልጣል
ይሖዋ የፈጠራቸው ነገሮች ስለ እሱ ባሕርያት ለማወቅ ይረዱናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም ሮም 1:20ን አንብቡና በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የትኞቹ ባሕርያቱ ተንጸባርቀዋል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “አምላክ በእውን ያለ አካል ሳይሆን በየትኛውም ቦታ የሚገኝ ኃይል ነው።”
አንተ ምን ይመስልሃል?
እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ
ይሖዋ በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል ነው፤ በርካታ ማራኪ ባሕርያት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዋነኛው ፍቅር ነው።
ክለሳ
ይሖዋን ማየት የማንችለው ለምንድን ነው?
መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?
ከይሖዋ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
ምርምር አድርግ
ስለ አራቱ የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት በመማር ስለ ይሖዋ ያለህን እውቀት አሳድግ።
አምላክ በሁሉም ቦታ እንደማይገኝ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መርምር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስን የአምላክ እጅ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ለምን እንደሆነ ተመልከት።
ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አምላክ ለእሱ እንደሚያስብለት ማመን ይከብደው ነበር። አመለካከቱን እንዲለውጥ የረዳው ምን እንደሆነ አንብብ።