የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ሥልጣን ለአንድ ክርስቲያን ደም ለመስጠት ሙከራ ቢደረግ ክርስቲያኑ ምን ያህል በብርቱ ሊቃወመው ይገባል?
እያንዳንዱ ሁኔታ የተለያየ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉንም የሚጠቀልል ደንብ ማውጣት አይቻልም። ክርስቲያኖች በአክብሮት የዓለማዊ መንግሥታትን ሕጎች በመታዘዝ ‘የቄሳርን ለቄሳር’ በመስጠት በኩል የታወቁ ናቸው። ሆኖም ከሁሉ በላይ የሆነው ግዴታቸው “የአምላክን ነገሮች ለአምላክ” መስጠት፤ ይኸውም ሕጎቹን ከመጣስ መራቅ መሆኑን ያውቃሉ።—ማርቆስ 12:17
ሮሜ 13:1-7 ክርስቲያኖች ከመንግሥታዊ “የበላይ ባለሥልጣኖች” ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ይገልጻል። እነዚህ መንግሥታት ሕጎችን ለማውጣት ወይም በጠቅላላው ለሕዝቡ ደኅንነትን ለማስፈን ሲባል መመሪያዎችን ለመስጠት ሥልጣን አላቸው። በተጨማሪም መንግሥታት ሕጋቸውን ለማስፈጸምና ‘በሕጋቸው መሠረት መጥፎ በሚያደርገው ላይ ቁጣቸውን ለመግለጽ’ ‘ሰይፍ ይታጠቃሉ።’ ክርስቲያኖች ለበላይ ባለ ሥልጣኖች የሚገዙ ስለሆነ ሕጎችንና የፍርድ ቤት ድንጋጌዎችን ለመታዘዝ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ የመገዛት ሁኔታ ውስን መሆን ይኖርበታል። አንድ ክርስቲያን ከፍተኛውን የአምላክ ሕግ የሚያስጥስ ነገር እንዲፈጽም ቢጠየቅ የሚቀድመው መለኮታዊው ሕግ ነው። የአምላክ ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል።
በመሠረቱ ጥሩ የሆኑ አንዳንድ ዘመናዊ ሕጎች ለአንድ ክርስቲያን በግድ ደም እንዲሰጠው ለማዘዝ አለቦታቸው ይሠራባቸው ይሆናል። እንደዚህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደያዘው ያለ አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል፦ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥ አድርገን መታዘዝ ይኖርብናል።”—ሥራ 5:29 አዓት
ይሖዋ እስራኤላውያንን፦ “ነገር ግን ደሙ ነፍሱ ነውና፣ ነፍሱንም ከሥጋው ጋር መብላት አይገባህምና ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ” ወይም እንደ አዓት “ላለመብላት ጥብቅ ውሳኔ አድርግ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 12:23) አንድ የ1917 የአይሁዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ደም እንዳትበላ ጸንተህ ብቻ ቁም” በማለት ይህን ጥቅስ ይተረጉመዋል። አይዛክ ሊዘርም ጥቅሱን እንዲህ በማለት ይተረጉሙታል፦ “ደምን ላለመብላት ጽና።” ታዲያ ይህ የሚያስተላልፈው መልዕክት የአምላክ አገልጋዮች የአምላክ ሕግ ስለመጠበቅ ለዘብተኞች ወይም ግድ የለሾች መሆን አለባቸው የሚል ነውን?
እንግዲያው አንድ መንግሥት ተቃራኒ መመሪያ ቢሰጥም ክርስቲያኖች አምላክን ለመታዘዝ የማያወላውል ቁርጥ ሐሳብ ሊኖራቸው ይገባል። ፕሮፌሰር ሮበርት ኤል ዊል ኬልን “ክርስቲያኖች [ለሮማውያን] ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት እምቢ ከማለታቸውም ሌላ ከተሞችን ለማስተዳደር አንድ ዓይነት ሥልጣን ወይም የኃላፊነት ቦታ አይቀበሉም ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። (ክርስቲያኖች—በሮማውያን ዓይን የተባለው መጽሐፍ) እምቢ ማለታቸው ሕግ የማያከብሩ የሚል ስም ሊያሰጣቸው ወይም በሮማውያን ስታዲየሞች ከአውሬ ጋር ታግለው እንዲሞቱ ሊያስፈርድባቸው ይችል ነበር።
ዛሬም ክርስቲያኖች በአቋማቸው ጽኑ መሆን አለባቸው። ከመንግሥታት በኩል አደጋ የሚያመጣባቸው ቢሆንም መለኰታዊውን ሕግ ላለመጣስ ቁርጥ ሐሳብ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻዎቹ ከፍተኛ ሕጎች ይኸውም የአምላክ ሕጎች ክርስቲያኖች ከዝሙት እንዲርቁ እንደሚያዟቸው ሁሉ ከደምም እንዲርቁ ይዟቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን እገዳዎች “አስፈላጊ ነገሮች” ብሎ ይጠራቸዋል። (ሥራ 15:19-21, 28, 29) እንደዚህ ያለው መለኰታዊ ድል ቀለል ተደርጎ የሚታይ አይደለም። ሲያመች ብቻ ወይም ችግር የማይፈጥር ሲሆን ብቻ ሊከተሉት እንደሚገባ አድርገው ማየት የለባቸውም። የአምላክ ሕግ የግድ መከበር ይኖርበታል።
እንግዲያው በገጽ 17 ላይ የተጠቀሰችው ወጣት ክርስቲያን “ደም ቢሰጣት በሰውነትዋ ላይ ጥቃት እንደተደረገና እንዲያውም ተገድዳ ከመነወር ጋር እንደምታወዳድረው” ለፍርድ ቤቱ የተናገረችበትን ምክንያት ለመረዳት እንችላለን። ትልቅም ትሁን ትንሽ አንዲት ክርስቲያን ዝሙት እንዲፈጸምባት ሕጋዊ ትእዛዝ ቢወጣ ነገሩን በቸልተኝነት በማየት እሺ ትላለችን?
በተመሳሳይም በዚሁ ገጽ ላይ የተጠቀሰችው የ12 ዓመት ልጅ ‘ፍርድ ቤቱ ደም እንዲሰጣት ቢያዝ ባላት ኃይል ሁሉ እንደምትከላከል፤ እንደምትጮኽና እንደምትታገል፤ ክንዷ ላይ የተሰካውን መርፌ አውልቃ እንደምትጥለውና ከአልጋዋ በላይ የተንጠለጠለውን የደም ከረጢት አፈንድታ እንደምታፈሰው በማያጠራጥር መንገድ ገልጻለች።
ኢየሱስ ንጉሥ ሊያደርጉት ባሰቡ ጊዜ ቦታውን ለቆ ሄዷል። በተመሳሳይም ደም ይሰጥ የሚል የፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚመጣ መስሎ ከታየው አንድ ክርስቲያን እንደዚህ ላለው የአምላክን ሕግ ለሚያስጥስ አድራጎት ላለመጋለጥ ወደ ሌላ ዘወር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። (ማቴዎስ 10:16፤ ዮሐንስ 6:15) በዚህ ላይ ግን ክርስቲያኑ አስተዋይ በመሆን ሌላ አማራጭ ሕክምና ለማግኘት ይጥራል። ይህን ካደረገ ሕይወቱን ለማዳንና ጤንነቱን ለመመለስ ልባዊ ጥረት ያደርጋል።
አንድ ክርስቲያን ስለ ደም የሚገልጸውን የአምላክ ሕግ ላለመጣስ ኃይል የታከለበት ጥረት ቢያደርግ ባለሥልጣኖቹ ሕግ አፍርሷል በማለት ክስ ሊመሠርቱበት ይችላሉ። ክሱ ቅጣት ቢያስከትል ስለ ጽድቅ ሲባል መከራ እንደደረሰበት አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። (ከ1 ጴጥሮስ 2:18-20 ጋር አወዳድር) አብዛኛውን ጊዜ ግን ክርስቲያኖች ደም ለመውሰድ እምቢ ካሉ በኋላ ጥሩ ችሎታ ባለው ሐኪም ታክመው ድነዋል። በዚህ መንገድ ክስ አልመጣባቸውም። ከሁሉ በላይ ግን በመለኰታዊው ሕይወት ሰጪያቸውና ፈራጃቸው ፊት በንጹሕ አቋም ጸንተዋል።