ይሖዋ ባስተማራችሁ መንገድ ሂዱ
“አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] መንገድህን ምራኝ (አስተምረኝ)፣ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤን [አንድ አድርግልኝ አዓት]”—መዝሙር 86:11
1, 2. የይሖዋ ምስክሮች ደም ለመውሰድም ሆነ ለመቀበል እምቢ እንዲሉ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው?
“ምናልባት የይሖዋ ምስክሮች በደም ውጤቶች አንጠቀምም በማለታቸው ትክክል ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ምክንያቱም በሽታ የሚያመጡ በርካታ ሕዋሳት ከሌላ ሰው በተወሰደ ደም ምክንያት ሊተላለፉ ይችላሉ።”—ለ ኮቲዲየ ዱ ሜዴሳ የተባለ ዕለታዊ የፈረንሳይኛ የሕክምና መጽሔት ታህሣሥ 15, 1987
2 ይህንን አስተያየት የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች ይህን ማድረጉ ያን ያህል አደገኛ፣ እንዲያውም ሞትን ሊያስከትል የሚችል መሆኑ በሰፊው ከመታወቁ በፊት የይሖዋ ምስክሮች ደም ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው የአጋጣሚ ሁኔታ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምስክሮች ስለ ደም የያዙት አቋም በአጋጣሚ የሆነ ወይም የደምን አስተማማኝ አለመሆን በመፍራት አንድ አዲስ ሃይማኖት ከያዘው አቋም የተፈጠረ ሕግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ምስክሮች ደምን የማይወስዱበት ምክንያት በታላቁ አስተማሪያቸው በአምላክ ፊት በታዛዥነት ለመመላለስ ቁርጥ ሐሳብ ስላላቸው ነው።
3. (ሀ) ዳዊት በይሖዋ ላይ ስለ መመካት የተሰማው እንዴት ነበር? (ለ) ዳዊት በአምላክ ላይ መመካቱ ወደፊት ምን ለማግኘት እንዲጠብቅ አድርጎት ነበር?
3 ያለ አምላክ ምንም ማድረግ እንደማይችል የተሰማው ንጉሥ ዳዊት እርሱ እንዲያስተምረውና ‘በእውነቱ ለመሄድ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (መዝሙር 86:11) በአንድ ወቅት ዳዊት በአምላክ ፊት ከደም ዕዳ ቢርቅ ‘ነፍሱ በይሖዋ ዘንድ በሕይወት ከረጢት ልትታሰር እንደምትችል’ ምክር ተሰጥቶት ነበር። (1 ሳሙኤል 25:21, 22, 25, 29) ሰዎች ውድ የሆኑ ዕቃዎችን ለመጠበቅና ለማቆየት ጠቅልለው እንደሚያስቀምጧቸው ሁሉ የዳዊትም ሕይወት በአምላክ ሊጠበቅና ሊቆይ ይችል ነበር። ዳዊት ጥበብ ያለበትን ይህን ምክር ተቀበለ እንጂ በግል ጥረቱ ራሱን ለማዳን አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ሕይወቱን በሰጠው ላይ በመተማመን “የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፣ በቀኝህም የዘላለም ፍስሐ አለ” ብሏል።—መዝሙር 16:11
4. ዳዊት ይሖዋ እንዲያስተምረው የፈለገው ለምን ነበር?
4 ዳዊት ይህን ዝንባሌ በመያዝ ታዛዥ ለመሆን የትኞቹ መለኮታዊ ሕጎች ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ ወይም እንደሚያስፈልጉ በግሉ ለመምረጥ እንደሚችል ሆኖ አልተሰማውም። እርሱ የነበረው ዝንባሌ የሚከተለው ነበር፦ “አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] መንገድህን አስተምረኝ፣ . . . በቀና መንገድ ምራኝ።” “አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] መንገድህን ምራኝ፣ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህንም ለመፍራት ልቤን [አንድ አድርገው (አዓት)] አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] ሆይ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ።” (መዝሙር 27:11፤ 86:11, 12) አንዳንድ ጊዜ በአምላክ ፊት በእውነት ጐዳና መመላለሱ አስቸጋሪ ሊመስል ወይም ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ዳዊት አምላክ ትክክለኛውን መንገድ እንዲያስተምረውና በእርሱም ለመሄድ ፈልጎ ነበር።
ስለ ደም ትምህርት ማግኘት
5. ዳዊት አምላክ በደም ላይ ስለነበረው አቋም ምን ዕውቀት ኖሮት መሆን አለበት?
5 ዳዊት ከልጅነቱ ጀምሮ አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተምሮ እንደነበረ ማስተዋላችን ጠቃሚ ነው። ይህም የአምላክ አመለካከት ሃይማኖታዊ ምሥጢር አልነበረም። ሕጉ ለሕዝቡ በሚነበብበት ጊዜ ዳዊት የሚከተለውን ሰምቶ መሆን ይኖርበታል፦ “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች፦ ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፣ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ።”—ዘሌዋውያን 17:11, 12፤ ዘዳግም 4:10፤ 31:11
6. የአምላክ አገልጋዮች ስለ ደም አሁንም ትምህርት ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
6 አምላክ እስራኤልን እንደ አንድ የተሰባሰበ ሕዝብ አድርጎ እስከተጠቀመበት ድረስ እርሱን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ስለ ደም ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ልጆች በዚህ ረገድ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር። ነገር ግን አምላክ ክርስቲያኖችን እንደ ጉባኤው አድርጎ ከተቀበላቸውና ‘የአምላክ እስራኤል’ ብሎ ካደራጃቸው በኋላ እንደዚህ ያለው ትምህርት ይቀጥል ይሆንን? (ገላትያ 6:16) አዎን ቀጥሏል። አምላክ ስለ ደም ያለው አመለካከት አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) ደምን አለ አግባብ ስለ መጠቀም ያለውን አቋም የገለጸው የሕጉ ቃል ኪዳን ከመደረጉ በፊት ነው፤ ሕጉ መሥራቱን ካቆመ በኋላም ይህ አቋሙ ቀጥሏል።—ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ሥራ 15:28, 29
7. ስለ ደም አምላክ እንዲያስተምረን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
7 ለደም አክብሮት ማሳየት በክርስትና እምነት ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ ያለው ነገር ነው። አንድ ሰው ‘ይህ ማጋነን አይሆንምን?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ በክርስትና እምነት ውስጥ ማዕከላዊውን ቦታ የያዘው ነገር የኢየሱስ መስዋዕት ሌላ ምን ነገር አለ? ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በውድ ልጁም [በኢየሱስ] እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፣ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።” (ኤፌሶን 1:7) በፍራንክ ሲ ሎውባች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ደብዳቤዎች የተባለው መጽሐፍ ይህንን ጥቅስ፦ “የክርስቶስ ደም ተከፈለልን፤ አሁን እኛ የእርሱ ሆነናል” ይላል።
8. “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሕይወት ለማግኘት በደም ላይ መመካት የሚያስፈልጋቸው እንዴት ነው?
8 በመምጣት ላይ ካለው “ታላቅ መከራ” ለመትረፍና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የአምላክን በረከቶች ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ሕልውናቸው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ የተመካ ነው። ራእይ 7:9-14 ከቀድሞ ሁኔታቸው አንፃር ስለ እነርሱ የሚከተለውን መግለጫ ይሰጣል፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” እዚህ ላይ ያለውን አነጋገር ልብ በል። ኢየሱስን መቀበልና በእርሱ ላይ ማመኑ የግድ አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ጥቅሱ ከታላቁ መከራ ተርፈው በሕይወት ያለፉት ‘ኢየሱስን ተቀብለዋል’ ወይም ‘በእርሱ ላይ እምነት አድርገዋል’ አይልም። አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ “ልብሳቸውን አጥበው [በኢየሱስ] ደም አነጹ” ይላል። ይህ ሊሆን የቻለው ደሙ የቤዛነት ዋጋ ስላለው ነው።
9. ደምን በተመለከተ ይሖዋን መታዘዙ ያን ያህል ከባድ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
9 የይሖዋ ምስክሮች ለዚህ ዋጋ ያላቸው አድናቆት አንድ የሕክምና ባለሞያ በቅንነት ደም መውሰዱ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ቢነግራቸውም ደምን አላግባብ ላለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። የሕክምና ባለሞያዎች ደም ከሚያስከትላቸው የጤና ጠንቆች ይልቅ ደም መውሰዱ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንደሚያመዝኑ ያምን ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኑ ከዚህ የበለጠውን ጠንቅ ማለትም ደምን አለአግባብ ለመጠቀም በመስማማት የአምላክን ሞገስ ማጣቱን ችላ ሊለው አይችልም። አንድ ጊዜ ጳውሎስ ‘የእውነትን እውቀት ከተቀበሉ በኋላ አውቀው ኃጢአት መፈጸምን ስለገፉበት ሰዎች’ ተናግሮ ነበር። እንደዚህ ያለው ኃጢአት ይህን ያህል ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንደዚህ ያለው ሰው “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ” በመሆኑ ነው።—ዕብራውያን 9:16-24፤ 10:26-29
ሌሎች ይህን እንዲማሩ መርዳት
10. ከደም ለመራቅ ከምናደርገው ቁርጥ ውሳኔ በስተጀርባ ያለው ምንድን ነው?
10 እኛ የኢየሱስን ቤዛዊ መስዋዕት የምናደንቅ ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የደሙን ዋጋ በመናቅ ኃጢአት እየሠራን እንዳንኖር እንጠነቀቃለን። ጉዳዩን በሚገባ ካሰብንበት አምላክ ስለሰጠን ሕይወት የሚኖረን ትንሽ ምስጋና ለጥቅማችን ይኸውም ለዘለቄታው ጥቅማችን ሲባል እንደተሰጡን እርግጠኞች ሆነን የተቀበልናቸውን የጽድቅ ሕጎቹን ለማፍረስ አቋማችንን እንድናላላ የሚቀርቡልንን የሽንፈት መንገዶች እንዳንከተል ሊገፋፋን ይገባል። (ዘዳግም 6:24፤ ምሳሌ 14:27፤ መክብብ 8:12) ስለ ልጆቻችንስ ምን ሊባል ይቻላል?
11-13. አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ስለ ልጆቻቸውና ስለ ደም ምን የተሳሳተ አስተሳሰብ ይዘዋል? ለምንስ?
11 ልጆቻችን ሕፃናት ወይም በጣም ትንንሾች ሊሆኑ ቢችሉም ይሖዋ አምላክ የእኛን አምልኮ መሠረት በማድረግ እንደ ንጹሕና ተቀባይነት እንዳላቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ስለዚህ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙት ሕፃናት አምላክ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ ለመረዳትና ምርጫ ለማድረግ ገና የማይችሉ መሆናቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ እኛ ስለዚህ አስፈላጊ ስለሆነ ጉዳይ እነርሱን ለማስተማር የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ላይ ነንን? ክርስቲያን ወላጆች ይህንን አክብደው ሊያስቡበት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም አንዳንድ ወላጆች ስለ ልጆቻቸውና ስለ ደም የተሳሳተ አስተሳሰብ የያዙ ይመስላል። አንዳንዶች ትንንሽ ልጆቻቸው ደም እንዳይሰጣቸው ለማድረግ ብዙ ሥልጣን እንደሌላቸው አድርገው የሚያስቡ ይመስላሉ። እንደዚህ ያለ የተሳሳተ አስተያየት የያዙት ለምንድን ነው?
12 ብዙ አገሮች ችላ ለተባሉና አለ አግባብ በመያዛቸው ለሚሰቃዩ ልጆች የሚቆሙ ሕጎች ወይም መንግሥታዊ ተቋሞች አሏቸው። ወላጆቻቸው ለሚወዷቸው ወንድና ሴት ልጆቻቸው ደም እንዳይሰጣቸው ሲቃወሙና በምትኩ ዘመናዊ ሕክምና ሊያቀርብ በሚችለው አማራጭ የሕክምና ዘዴ እንዲታከሙላቸው ሲጠይቁ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ችላ ተባሉ ወይም አላግባብ ተያዙ ማለት አይደለም። ከሕክምናው አንጻር ስንመለከተውም እንኳ ቢሆን ደም በመስጠት የሚደረገው ሕክምና የሚያስከትለው አደጋ ከታሰበ ይህ እርምጃ ችላ ማለት ወይም አላግባብ ልጆችን ማሰቃየት አይደለም። አድራጎቱ ሊያስከትል የሚችላቸውን አደጋዎች በማመዛዘን በመብት ተጠቅሞ የሕክምና ምርጫ የማድረግ ጉዳይ ነው።a ይሁንና በአንዳንድ ሐኪሞች ያለ ፍላጎት ደም አስገድዶ ለመስጠት የሚያስችል ሥልጣን በመፈለግ አንዳንድ ሕጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።
13 አንዳንድ ወላጆች ሐኪሞች ለትንሽ ልጅ ደም ለመስጠት የፍርድ ቤት ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ነገሩ ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሆነና ወላጆች ሊያደርጉት የሚችሉት ወይም ሊያደርጉት የሚያስፈልጋቸው ምንም ነገር እንደሌለ ሊሰማቸው ይችል ይሆናል። ይህ እንዴት የተሳሳተ አመለካከት ነው!—ምሳሌ 22:3
14. ዳዊትና ጢሞቴዎስ በልጅነታቸው የተማሩት እንዴት ነው?
14 ዳዊት ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ አምላክ መንገዶች ትምህርት ተሰጥቶት እንደነበረ ተመልክተናል። ይህም ሕይወትን ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ አድርጎ እንደሚመለከትና ደም ሕይወትን የሚወክል መሆኑን እንዲያውቅ አስችሎታል። (ከ2 ሳሙኤል 23:14-17 ጋር አወዳድር) ጢሞቴዎስ ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ’ የአምላክን አስተሳሰብ ተምሮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ዳዊትና ጢሞቴዎስ ዛሬ ሕጋዊ የጉልምስና ዕድሜ ከሚባለው ዕድሜ በታች በነበሩበት ጊዜ የአምላክን ፈቃድ በተመለከተ ለሚነሱ ጉዳዮች ማስረዳት የሚችሉ ነበሩ ቢባል አትስማማምን? በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ወጣት ክርስቲያኖች ሕጋዊ ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የአምላክን መንገድ መማር ይኖርባቸዋል።
15, 16. (ሀ) በአንዳንድ ቦታዎች የልጆችን መብት በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ተፈጥሮአል? (ለ) አንድ ወጣት ደም እንዲሰጠው የተደረገው ለምን ነበር?
15 በአንዳንድ ቦታዎች የበሰሉ ልጆች የሚባሉት ወጣቶች ለትልልቆቹ ከሚሰጡት ጋር የሚመሳሰሉ መብቶች ይሰጧቸዋል። በዕድሜ ወይም በአስተሳሰብ ብስለት ወይም በሁለቱም ላይ በመመሥረት አንድ ወጣት በሕክምናው ረገድ የራሱን ውሳኔዎች ለማድረግ እንደሚችል የጎለመሰ ሰው ተደርጎ ሊታይ ይችላል። እንደዚህ ያለ ሕግ በማይኖርበት ቦታም እንኳ ዳኞች ወይም ባለ ሥልጣኖች ስለ ደም ያለውን ቁርጥ ውሳኔ በግልጽ ለማስረዳት የሚችልን የአንድን ወጣት ሐሳብ አክብደው ሊመለከቱት ይችላሉ። በሌላው በኩል ግን አንድ ወጣት እምነቱን በግልጽና በብስለት ማስረዳት ካልቻለ ፍርድ ቤቱ ልክ ለአንድ ሕፃን ልጅ እንደሚያደርገው የተሻለ መስሎ የታየውን ነገር መወሰን እንዳለበት ሆኖ ሊሰማው ይችላል።
16 አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ ዓመታት አንዴ ሲያጠና አንዴ ሲያቋርጥ ቆየ፤ ሆኖም አልተጠመቀም። “ራሱ የሕክምና ዘዴዎችን ለመቃወም የሚችልበት መብት” በሚያገኝበት ዕድሜ ላይ ለመድረስ ሰባት ሳምንታት የቀሩት ቢሆንም እንኳ ለካንሰር በሽታው ሕክምና የሚያደርግለት ሆስፒታል እርሱና ወላጆቹ ደም እንዳይሰጠው ያላቸውን ፍላጎት በመቃወም የፍርድ ቤት ድጋፍ ለማግኘት ፈለገ። ጠንቃቃ የሆነው ዳኛ ስለ ደም አንዳንድ ጥያቄዎችን አቀረበለት፣ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስሞች ምንድን ናቸው? እንደሚሉት ያሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ጠየቀው። ወጣቱ የመጻሕፍቱን ስም ለመናገር አልቻለም ወይም ደም የማይወስድበትን ምክንያት የተረዳ ለመሆኑ የሚያሳምን ምስክርነት ለመስጠት አልቻለም። ያሳዝናል፣ ዳኛው የሚከተለውን አስተያየት በመስጠት ደም እንዲሰጠው ወሰነ፦ “(እከሌ) ደም እንዳይሰጠው የተቃወመው ሃይማኖታዊ እምነቶቹን በብስለት በመረዳት ላይ ተመስርቶ አይደለም።”
17. አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ደምን ስለ መውሰድ ምን ዓይነት አቋም ወሰደች? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?
17 የአምላክን መንገዶች በደንብ በተማሩና በእውነት ጐዳና ላይ በትጋት በሚመላለሱ ትንንሽ ወጣቶች ላይ ሁኔታው የተለየ መልክ ሊኖረው ይችላል። አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንደዚሁ ለየት ያለ ካንሰር ያዛት። ልጅቱና ወላጆችዋ ነገሩን ካወቁ በኋላ በአንድ ታዋቂ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ ልዩ ሐኪም የሚሰጠውን የኬሞቴራፒ ሕክምና ተቀበሉ። ይህም ሆኖ ነገሩ ወደ ፍርድ ቤት ቀረበ። ዳኛው እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ዲ.ፒ. ደም እንዳይሰጣት በምትችለው መንገድ ሁሉ እንደምትቃወም የምስክርነት ቃልዋን ሰጥታለች። ደም ቢሰጣት በሰውነትዋ ላይ ጥቃት እንደተደረገና እንዲያውም ተገድዳ ከመነወር ጋር እንደምታወዳድረው ገለጸች። ፍርድ ቤቱ ምርጫዋን እንዲያከብርላትና ደም በግድ እንድትወስድ ፍርድ ቤቱ ሳያዝ በ[ሆስፒታሉ] ውስጥ ሕክምናዋን እንድትቀጥል እንዲፈቀድላት ጠየቀች።” ቀደም ሲል የተሰጣት ክርስቲያናዊ ትምህርት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ረዳት።—ሳጥኑን ተመልከት።
18. (ሀ) አንዲት በበሽታ የተጠቃች ልጃገረድ ደምን በተመለከተ ምን ዓይነት ጥብቅ አቋም ወሰደች? (ለ) ስለ ሕክምናዋስ ዳኛው ምን ዓይነት ውሳኔ ሰጠ?
18 አንዲት የ12 ዓመት ልጃገረድ ለደም ካንሰር በሽታ ሕክምና ይሰጣት ነበር። የልጆች ደኅንነት የሚከታተል ድርጅት ደም በግድ እንዲሰጣት ለማድረግ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው። ዳኛው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጡ፦ “ኤል. በግድ ደም ሊሰጣት ሙከራ ቢደረግ በሚኖራት አቅም ሁሉ ይህን የደም መስጠት ሙከራ እንደምትታገለው ለፍርድ ቤቱ በግልጽና በተጨባጭ መንገድ ተናግራለች። እርስዋም እንደተናገረችውና እኔም ታደርገዋለች ብዬ እንደማምነው እየጮኸች ትታገላለች፤ በዚህም መርፌውን ከእጅዋ ላይ በመንቀል ከአልጋዋ በላይ በሚገኘው ከረጢት ውስጥ ያለውን ደም ለማፍሰስ ሙከራ ታደርጋለች። ይህችን ልጅ በእንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ የሚያደርጋትን ትዕዛዝ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም። . . . ይህችን በሽተኛ በተመለከተ ሆስፒታሉ ያቀደው ሕክምና በሽታዋን ማከም የሚችለው በአካላዊ ሁኔታ ብቻ ነው። ስሜታዊ ፍላጎቶችዋንና ሃይማኖታዊ እምነቶችዋን ለማሟላት ሳይችል ቀርቷል።”
ወላጆች—በደንብ አስተምሩ
19. ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ምን ልዩ ግዴታ መወጣት ይኖርባቸዋል?
19 እነዚህ ተሞክሮዎች ቤተሰባቸው በሙሉ አምላክ ስለ ደም ካወጣው ሕግ ጋር የሚስማማ ተግባር እየሠሩ እንዲኖሩ ለሚፈልጉ ወላጆች ኃይለኛ መልዕክት ይዘዋል። አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ሊባል የቻለበት አንዱ ምክንያት ይህ የቤተሰብ መሪ የሆነ አባት “ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ [የይሖዋን (አዓት)] መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን” እንደሚያዛቸው ያውቅ ስለነበር ነው። (ዘፍጥረት 18:19) ዛሬስ ክርስቲያን ልክ እንደዚህ ማድረግ አይገባቸውምን? ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ ‘ስለ ተስፋቸው ለሚጠይቋቸው ሁሉ በየዋህነትና በጥልቅ አክብሮት መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ እንዲሆኑ’ ውድ ልጆችህን በይሖዋ መንገድ እንዲሄዱ ታስተምራቸዋለህን?—1 ጴጥሮስ 3:15
20. ልጆቻችን ስለ ደም ከሁሉ በፊት ምንን እንዲያውቁና እንዲያምኑ መፈለግ ይኖርብናል? (ዳንኤል 1:3-14)
20 ልጆቻችን ደም መውሰድ ስላሉት የበሽታ ጠንቆችና ሌሎች አደጋዎች እንዲያውቁ ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም አምላክ ደምን በተመለከተ ስለሰጠው ፍጹም ሕግ ልጆቻችንን ማስተማር አለብን ሲባል ከሁሉ በላይ የደምን ፍርሃት በውስጣቸው ለማሳደር መሞከር ማለት አይደለም። ለምሳሌ አንዲት ልጃገረድ ለምን ደም መውሰድ እንደማትፈልግ አንድ ዳኛ ቢጠይቃት መልስዋ ደም በጣም አደገኛ ወይም አስፈሪ ስለሆነ ነው የሚል ቢሆን ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ዳኛው ገና እንዳልበሰለችና ከሚገባው በላይ እንደፈራች አድርጎ ሊደመድም ይችላል። ይህም ልክ ወላጆችዋ ለእርስዋ የተሻለ እንደሆነ እየተሰማቸው እርስዋ በመፍራትዋ የትርፍ አንጀት ቀዶ ጥገና እንዳይደረግላት እያለቀሰች ከምትቃወም ልጃገረድ ጋር ሊያመሳስላት ይችላል። ከዚህም ሌላ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ክርስቲያኖች ደም መውሰድን የሚቃወሙበት ዋናው ምክንያት ደሙ የተበከለ ሊሆን ስለሚችል ሳይሆን ለአምላካችንና ለሕይወት ሰጪአችን ውድ ነገር ስለሆነ ነው። ልጆቻችንም ይህንን ማወቅ አለባቸው፤ እንዲሁም ደም የሚያስከትላቸው የሕክምና ጠንቆች ለሃይማኖታዊ አቋማችን ክብደት እንደሚጨምሩለት ማወቅ ይኖርባቸዋል።
21. (ሀ) ወላጆች ስለ ልጆቻቸውና መጽሐፍ ቅዱስ ለደም ስላለው አመለካከት ምንን ነገር መማር ይኖርባቸዋል? (ለ) ወላጆች ከደም ጋር በተያያዘ ልጆቻቸውን እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?
21 ልጆች ካሉህ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሌላውን ደም ስለ መውሰድ ባለው አቋም እንደሚስማሙና ስለዚሁ አቋም በደንብ ማስረዳት እንደሚችሉ እርግጠኛ ነህን? ይህ አቋም የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ በእርግጥ ያምናሉን? የአምላክን ሕግ ማፍረስ በጣም ከባድ ነገር በመሆኑ አንድ ክርስቲያን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚኖረውን ተስፋ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል እርግጠኞች ሆነው ያምናሉን? አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ትንንሾችም ሆኑ ጐልማሳ ወደመሆን የተጠጉ ስለ እነዚህ ነገሮች ከእነርሱ ጋር ይወያያሉ። ወላጆች ምናልባት እያንዳንዱ ወጣት በአንድ ዳኛ ወይም የሆስፒታል ባለ ሥልጣን ሊቀርቡ የሚችሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚዘጋጅባቸውን የልምምድ ፕሮግራሞች ሊያዘጋጁ ይችላሉ። የዚህ ልምምድ ዓላማ አንድ ወጣት የተመረጡ ማስረጃዎችን ወይም መልሶችን ሸምድዶ በማስታወስ ብቻ እንዲደግማቸው ለማድረግ አይደለም። ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው በነገሩ እነርሱ የሚያምኑበት መሆኑን ለምን እንደሚያምኑበት ማወቃቸው ነው። እርግጥ ነው፣ በፍርድ ቤት ችሎት ላይ ወላጆች ወይም ሌሎች ሰዎች ደም ስለሚያመጣቸው ጠንቆችና ሌሎች አማራጭ ሕክምናዎች ስለመኖራቸው ሐሳብ ሊያቀርቡ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ዳኛው ወይም ባለ ሥልጣኑ ከልጆቻችን ጋር በመነጋገር ለማወቅ የሚፈልገው ስለ ሁኔታቸውና ስላሉት አማራጮች በብስለት የተረዱ መሆናቸውን እንዲሁም የራሳቸው የሆኑ የነገሮች መመዘኛዎችና ጥብቅ እምነቶች ያሏቸው መሆኑን ነው።—ከ2 ነገሥት 5:1-4 ጋር አወዳድር
22. ስለ ደም ከአምላክ የተማርን መሆናችን የሚያስገኘው ዘላቂ ውጤት ምን ሊሆን ይችላል?
22 ሁላችንም አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ማወቅና አጥብቀን መያዝ ያስፈልገናል። ራእይ 1:5 ክርስቶስ ‘የሚወደንና ኃጢአታችንንም በደሙ ያጠበልን’ መሆኑን ይገልጻል። ለኃጢአታችን ሙሉና ዘላቂ ይቅርታ ማግኘት የምንችለው የኢየሱስን ደም ዋጋ በመቀበል ብቻ ነው። ሮሜ 5:9 በግልጽ “ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቁጣው እንድናለን” ይላል። እንግዲያው ስለዚህ ጉዳይ በይሖዋ የተማርን መሆናችንና ለዘላለም በመንገዱ ለመሄድ መቁረጣችን ለእኛና ለልጆቻችን ምንኛ ጥበብ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የታተመውን ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተባለ ብሮሹር ገጽ 21-22, 28-31 ተመልከት
ቁልፍ የሆኑ ማስተማሪያ ነጥቦች
◻ ከይሖዋ ስለመማር ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
◻ አምላክ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ ማክበሩ ይህን ያህል አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
◻ ወጣቶች ስለ ደም ያላቸውን እምነትና አቋም በግልጽና በቁርጠኝነት ማስረዳት መቻላቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
◻ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ በደንብ እንዲማሩ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍርድ ቤቱ ተደነቀ
በአንቀጽ 17 ላይ የተጠቀሰችውን ዲ.ፒን በተመለከተ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምን ይል ነበር?
“ፍርድ ቤቱ ይህች የ14 ዓመት ተኩል ወጣት ባላት የማሰብ ችሎታ፣ መረጋጋት፣ የሚያስከብር ሁኔታና ኃይለኛ አቋም ምክንያት በጣም ተደንቋል። ገዳይ የሆነ የካንሰር ዓይነት እንዳለባት ስታውቅ በጣም ተክዛ ሊሆን ይችላል። . . . ሆኖም ወደ ፍርድ ቤቱ ቃልዋን ለመስጠት የመጣችው አንዲት የበሰለች ወጣት ነበረች። ከፊት ለፊትዋ በተጋረጠው አስቸጋሪ ሥራ ላይ በግልጽ ትኩረትዋን ያደረገች ትመስላለች። በሁሉም የምክር ክፍለ ጊዜዎች ላይ ተገኝታለች፣ ሕክምና እንዲደረግላት ተስማምታለች፣ እንዲሁም እንደ አንድ ሰው በመሆን እንደዚህ ዓይነቱን ተፈታታኝ የሕክምና ዘዴ እንዴት እንደምትጋፈጠው አንድ ዓይነት የተጣራ ፍልስፍና አዳብራለች፣ ወደ ፍርድ ቤቱ ይዛው የመጣችው ስሜትን የሚነካ ጥያቄም፦ ውሳኔዬን አክብሩልኝ የሚል ነው። . . .
“ከብስለቷም በተጨማሪ ዲ.ፒ. ውሳኔዋን ፍርድ ቤቱ እንዲያከብርላት የሚያደርጉ በቂ የሆኑ መሠረቶችን ገልጻለች። ደም መውሰድን የሚጨምረው የሕክምና ዕቅድ በመንፈሳዊ፣ በስነ ልቦና፣ በሞራል የሚጎዳት ነው። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ የመረጠችውን የሕክምና ዘዴ ያከብርላታል።”
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ዳኛ ወይም የሆስፒታል አስተዳዳሪ አንድ ክርስቲያን ወጣት ምን እንደሚያምንና ይህንንም ለምን እንደሚያምን ለማወቅ ይፈልግ ይሆናል