የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች፣ ጥር-የካቲት 2021
ከጥር 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 18-19
“ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ጠብቁ”
ከሰይጣን ወጥመድ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት
ይሖዋ፣ በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት ስለሚፈጽሙት አስጸያፊ ድርጊት ለእስራኤላውያን ሲናገር እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እኔ በማስገባችሁ በከነአን ምድር ያሉ ሰዎች [እንደሚያደርጉት] አታድርጉ። . . . ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ።” ቅዱስ የሆነው የእስራኤል አምላክ፣ የከነአናውያን አኗኗር እጅግ የረከሰ ከመሆኑ የተነሳ ይኖሩባት የነበረችው ምድርም እንደረከሰችና እንደተበከለች ተሰምቶት ነበር።—ዘሌ. 18:3, 25
ይሖዋ ሕዝቡን ይመራል
13 ታማኝ የሆኑት ነገሥታት፣ በሰብዓዊ ጥበብ እና ዕቅድ ከሚመሩ ማስተዋል የጎደላቸው የሌሎች ሕዝቦች ነገሥታት ምንኛ የተለዩ ነበሩ! ከነዓናውያን መሪዎችና ሕዝቦቻቸው በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ከእንስሳ ጋር የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን፣ ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን እንዲሁም ጣዖት አምልኮን የመሳሰሉ አስጸያፊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። (ዘሌ. 18:6, 21-25) በተጨማሪም ባቢሎናውያንና ግብፃውያን መሪዎች፣ አምላክ ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ጠቃሚ መመሪያዎች አይከተሉም ነበር። (ዘኁ. 19:13) ከዚህ በተቃራኒ ታማኝ የሆኑት የእስራኤል መሪዎች ሕዝቡ መንፈሳዊ፣ አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን እንዲጠብቅ ያበረታቱ ነበር። ታማኞቹን መሪዎች የሚመራቸው ይሖዋ እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ክፋትን ለማስወገድ አምላክ ምን እርምጃ ይወስዳል?
የክፋት ጎዳናቸውን ለመለወጥ እምቢተኛ በመሆን መጥፎ ነገሮችን ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ” የሚለውን በግልጽ የተቀመጠ ተስፋ ልብ በል። (ምሳሌ 2:21, 22) ክፉ ሰዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከዚያ በኋላ አይኖርም። እንዲህ ባለው ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከወረሱት ኃጢአት ቀስ በቀስ ነፃ ይወጣሉ።—ሮም 6:17, 18፤ 8:21
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”
11 በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው የሙሴ ሕግ ክፍል ደግሞ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው የመቃረም መብት ነው፤ ይህ መብት አምላክ ለሕዝቡ ደኅንነት አሳቢ እንደሆነ ያሳያል። ይሖዋ፣ አንድ እስራኤላዊ ገበሬ ምርቱን በሚሰበስብበት ጊዜ አጫጆች ትተውት ያለፉትን ችግረኞች እንዲሰበስቡ እንዲፈቀድላቸው አዝዞ ነበር። ገበሬዎች የእርሻቸውን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርገው ማጨድ እንዲሁም ትተውት ያለፉትን የወይን ወይም የወይራ ፍሬ ለመልቀም መመለስ አይፈቀድላቸውም ነበር። በተጨማሪም ሳያውቁት ሜዳ ላይ ጥለውት የሄዱትን ክምር ተመልሰው መውሰድ አይችሉም ነበር። ይህ ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው፣ ለመጻተኞች፣ ወላጅ ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች የተደረገ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። ሥራው ለሚቃርሙት ሰዎች ትጋት የሚጠይቅባቸው መሆኑ ባያጠራጥርም ለልመና እንዳይዳረጉ ይረዳቸዋል።—ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19-22፤ መዝሙር 37:25
ከጥር 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 20-21
“ይሖዋ ሕዝቡ ከሌሎች የተለዩ እንዲሆኑ ይፈልጋል”
በገነት ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ ምክንያት አለህ?
12 ያም ሆኖ ልብ ልንለው የሚገባን አንድ ነገር አለ። አምላክ እስራኤላውያንን “ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 11:8) ይህች ምድር በዘሌዋውያን 20:22, 24 ላይም ተገልጻለች፦ “እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም። . . . እናንተ ግን፣ ‘ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ’ አልኋችሁ።” አዎን፣ ተስፋ የተገባላቸውን ምድር ማግኘታቸው ከይሖዋ አምላክ ጋር በሚኖራቸው መልካም ግንኙነት ላይ የተመካ ነበር። አምላክ፣ ባቢሎናውያን እስራኤላውያንን ድል አድርገው ከምድራቸው እንዲያፈናቅሏቸው የፈቀደው ሳይታዘዙት በመቅረታቸው ነበር።
it-1 1199
ውርስ
አንድ ባለንብረት ሲሞት ለወራሹ ወይም የወራሽነት መብት ላላቸው ሰዎች የሚተላለፍ ማንኛውም ንብረት፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ማንኛውም ነገር። በዋነኝነት የሚሠራበት የዕብራይስጥ ግስ ናካል (ስም፣ ናካላ) ነው። ቃሉ ውርስ ወይም ርስት መስጠትን ወይም መቀበልን ያመለክታል፤ ብዙውን እንዲህ ያለው ውርስ የሚተላለፈው ከትውልድ ወደ ትውልድ ነው። (ዘኁ 26:55፤ ሕዝ 46:18) ያራሽ የሚለው ግስ አንዳንድ ጊዜ “ወራሽ መሆንን” ለማመልከት ይሠራበታል፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ግን በዘር ያልተላለፈ “ውርስን” ለማመልከት ነው። (ዘፍ 15:3፤ ዘሌ 20:24) በተጨማሪም በወታደራዊ እርምጃ አማካኝነት “ማስለቀቅ፣ ማባረር” የሚል ትርጉም አለው። (ዘዳ 2:12፤ 31:3) ውርስን ለማመልከት የሚሠራባቸው የግሪክኛ ቃላት ክሌሮስ ከሚለው ቃል ጋር ይዛመዳሉ፤ ይህ ቃል ዋነኛ ትርጉሙ “ዕጣ” የሚል ቢሆንም ከጊዜ በኋላ “ድርሻ” ውሎ አድሮም “ርስት” የሚል ፍቺ ኖረው።—ማቴ 27:35፤ ሥራ 8:21፤ 26:18
it-1 317 አን. 2
ወፎች
ከጥፋት ውኃው በኋላ ኖኅ ‘ንጹሕ የሆኑ የሚበርሩ ፍጥረታትን’ እና ሌሎች እንስሳትን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። (ዘፍ 8:18-20) ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዎች ወፎችን እንዲበሉ አምላክ ፈቅዶላቸዋል፤ ደሙን መብላት ግን ተከልክለው ነበር። (ዘፍ 9:1-4፤ ከዘሌ 7:26፤ 17:13 ጋር አወዳድር።) በወቅቱ አንዳንድ ወፎች ‘ንጹሕ’ ተደርገው የተቆጠሩት መሥዋዕት ሆነው ለመቅረብ ተቀባይነት እንዳላቸው አምላክ በመጠቆሙ ምክንያት መሆን አለበት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው የሙሴ ሕግ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ከምግብነት አንጻር “ርኩስ” ተደርጎ የሚቆጠር ወፍ አልነበረም። (ዘሌ 11:13-19, 46, 47፤ 20:25፤ ዘዳ 14:11-20) በሕጉ ውስጥ አንዳንድ ወፎች “ርኩስ” ተደርገው የተቆጠሩት ከምን አንጻር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። “ርኩስ” እንደሆኑ የተገለጹት አብዛኞቹ ወፎች፣ አዳኝ ወፎች ወይም ጥንብ የሚበሉ ወፎች ቢሆኑም ሁሉም ግን አልነበሩም። (ጅንጅላቴ የሚለውን ተመልከት።) አዲሱ ቃል ኪዳን ከተቋቋመ በኋላ ይህ ገደብ ተነስቷል፤ አምላክ በራእይ አማካኝነት ለጴጥሮስ ይህን ግልጽ አድርጎለታል።—ሥራ 10:9-15
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 563
መተልተል
የአምላክ ሕግ ለሞተ ሰው ሲባል ሰውነትን መተልተልን በግልጽ ይከለክል ነበር። (ዘሌ 19:28፤ 21:5፤ ዘዳ 14:1) ይህ የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብና ልዩ ንብረቱ ስለነበሩ ነው። (ዘዳ 14:2) በዚህም የተነሳ እስራኤላውያን ከጣዖት አምልኮ ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ልማድ መራቅ ነበረባቸው። በተጨማሪም ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚያውቁ ሰዎች፣ የገዛ አካላቸውን እንደመተልተል ያለ የተጋነነ የሐዘን መግለጫ ማሳየታቸው ተገቢ አይሆንም። (ዳን 12:13፤ ዕብ 11:19) ከዚህም ሌላ እስራኤላውያን አካላቸውን እንዳይተለትሉ መከልከላቸው፣ የአምላክ ፍጥረት ለሆነው ለሰውነታቸው ተገቢው አክብሮት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስታውሳቸዋል።
ከጥር 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 22-23
“በየወቅቱ ይከበሩ ከነበሩት በዓላት የምናገኘው ትምህርት”
it-1 826-827
የቂጣ በዓል
የቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም ሰንበት ነበር። በሁለተኛው ቀን ማለትም ኒሳን 16 እስራኤላውያን ከአዝመራቸው መጀመሪያ የደረሰውን ገብስ ነዶ (በፓለስቲና መጀመሪያ የሚደርሰው ሰብል ገብስ ነው) ለካህኑ ማምጣት ነበረባቸው። ከዚህ በዓል በፊት ከአዲሱ አዝመራ ምንም ዓይነት እሸት፣ ዳቦም ሆነ ቆሎ መብላት አልነበረባቸውም። ካህኑ እንዲህ ያለውን የፍሬ በኩራት የሚያቀርበው በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ በመወዝወዝ ነበር፤ በተጨማሪም አንድ ዓመት ገደማ የሆነው እንከን የሌለበት ጠቦት በዘይት ከተለወሰ የእህል መባ ጋር የሚቃጠል መባ ሆኖ ይቀርባል፤ የመጠጥ መባም አብሮ ይቀርብ ነበር። (ዘሌ 23:6-14) ከጊዜ በኋላ ካህናቱ የፍሬ በኩራቱን እሸት ወይም ዱቄት በመሠዊያው ላይ ማቃጠል የጀመሩ ቢሆንም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያዝ መመሪያ አልነበረም። በብሔር ደረጃ ከሚቀርበው የፍሬ በኩራት በተጨማሪ እያንዳንዱ ቤተሰብ እንዲሁም እስራኤል ውስጥ ርስት ያለው እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህ የደስታ ወቅት የምስጋና መሥዋዕት እንዲያቀርብ ዝግጅት ተደርጎ ነበር።—ዘፀ 23:19፤ ዘዳ 26:1, 2፤ በኩራት የሚለውን ተመልከት።
ትርጉሙ። እስራኤላውያን በዚህ ወቅት ቂጣ መብላታቸው በዘፀአት 12:14-20 ላይ ከሚገኘው ይሖዋ ለሙሴ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር የሚስማማ ነው፤ ይህ ትእዛዝ በቁጥር 19 ላይ የሚገኘውን “ለሰባት ቀናት እርሾ የሚባል ነገር በቤታችሁ ውስጥ አይገኝ” የሚል ጥብቅ ማሳሰቢያ ያካትታል። ቂጣው በዘዳግም 16:3 ላይ “የመከራ ቂጣ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን አይሁዳውያኑ ከግብፅ ተጣድፈው የወጡበትን ጊዜ በየዓመቱ ያስታውሳቸዋል (በወቅቱ ሊጡ እስኪቦካ ለመጠበቅ ጊዜ አልነበራቸውም [ዘፀ 12:34])። በመሆኑም እስራኤላውያን ከምን ዓይነት የመከራና የባርነት ሕይወት ነፃ እንደወጡ ያስታውሳሉ፤ ይሖዋ ራሱ “ይህን የምታደርገው ከግብፅ ምድር የወጣህበትን ዕለት በሕይወት ዘመንህ ሁሉ እንድታስታውስ ነው” ብሏቸዋል። እስራኤላውያን ከሦስቱ ዓመታዊ በዓላት የመጀመሪያው የሆነውን ይህን በዓል ሲያከብሩ በብሔር ደረጃ ያገኙትን ነፃነት ማስታወሳቸውና ይሖዋ አዳኛቸው እንደሆነ መቀበላቸው ለበዓሉ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።—ዘዳ 16:16
it-2 598 አን. 2
ጴንጤቆስጤ
በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን የስንዴ አዝመራ በኩራት ለይሖዋ ይቀርብ ነበር። ሆኖም የስንዴ በኩራት የሚቀርብበት መንገድ የገብስ በኩራት ከሚቀርብበት መንገድ ይለያል። ሁለት አሥረኛ ኢፍ (4.4 ሊትር) የላመ የስንዴ ዱቄት እርሾ ገብቶበት ሁለት ቂጣ ይጋገራል። እስራኤላውያን ቂጣዎቹን ‘ከሚኖሩባቸው ቦታዎች’ እንዲያመጡ ታዘዋል፤ ይህም ቂጣዎቹን፣ ለአምልኮ በሚያዘጋጁበት መንገድ ሳይሆን ለዕለት ምግባቸው በሚያዘጋጁበት መንገድ መጋገር እንዳለባቸው ያመለክታል። (ዘሌ 23:17) ከቂጣዎቹ ጋር የሚቃጠል መባና የኃጢአት መባ መቅረብ ነበረበት፤ እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መቅረብ ነበረባቸው። ካህኑ ቂጣዎቹንና የበግ ጠቦቶቹን በእጁ ላይ አድርጎ ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም መባው ለይሖዋ መቅረቡን ያመለክታል። ቂጣዎቹና ጠቦቶቹ በይሖዋ ፊት ከቀረቡ በኋላ ካህኑ በኅብረት መሥዋዕት መልክ ይበላቸዋል።—ዘሌ 23:18-20
ከይሖዋ ድርጅት ጋር ወደፊት እየተጓዝክ ነው?
11 የይሖዋ ድርጅት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ትኩረት እንድንሰጥ የሚያሳስበን ለእኛው ጥቅም ሲል ነው፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።” (ዕብ. 10:24, 25) እስራኤላውያን የሚያከብሯቸው ዓመታዊ በዓላትም ሆኑ ለአምልኮ የሚያደርጓቸው ሌሎች ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ያጠናክሯቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በነህምያ ዘመን እንደተከበረው ልዩ የዳስ በዓል ያሉት ወቅቶች አስደሳች ነበሩ። (ዘፀ. 23:15, 16፤ ነህ. 8:9-18) እኛም ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎች ተመሳሳይ ጥቅም እናገኛለን። እንግዲያው ደስተኞችና በመንፈሳዊ ጤናሞች እንድንሆን ተብለው ከሚደረጉት ከእነዚህ ዝግጅቶች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እናድርግ።—ቲቶ 2:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ንጹሕ አቋማችሁን ጠብቁ!
3 ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ይሖዋን እንደ እውን አካል በማየት እሱን በሙሉ ልብ መውደድንና ምንጊዜም ለእሱ ማደርን ያመለክታል፤ ይህም በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የአምላክን ፈቃድ እንድናስቀድም ያነሳሳናል። እስቲ ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት። ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከሚያስተላልፋቸው መሠረታዊ ትርጉሞች መካከል አንዱ ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን እንስሳትን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ሕጉ እንስሳው እንከን የሌለበት እንዲሆን ያዛል። (ዘሌ. 22:21, 22) የአምላክ ሕዝቦች እግሩ፣ ጆሮው ወይም ዓይኑ ላይ ችግር ያለበት አሊያም በበሽታ የተጠቃ እንስሳ እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሖዋ እንስሳው ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። (ሚል. 1:6-9) ይሖዋ የሚቀርብለት መሥዋዕት እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን የሚፈልገው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ የበሰበሰ ፍራፍሬ፣ ገጾቹ ያልተሟሉ መጽሐፍ ወይም የሆነ ዕቃ የጎደለው መሣሪያ መግዛት አንፈልግም። የምንገዛው ነገር ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሖዋም ለእሱ ከምናሳየው ፍቅርና ታማኝነት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ይጠብቃል። ፍቅራችንና ታማኝነታችን ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ይኖርበታል።
ከጥር 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 24-25
“የኢዮቤልዩ ዓመት እና ወደፊት የምናገኘው ነፃነት”
it-1 871
ነፃነት
የነፃነት አምላክ። ይሖዋ የነፃነት አምላክ ነው። የእስራኤልን ብሔር ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷል። እንዲሁም እስራኤላውያን እሱ የሰጣቸውን ትእዛዛት እስከጠበቁ ድረስ ድህነት ከሚያስከትለው ችግር ነፃ ሆነው እንደሚኖሩ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳ 15:4, 5) ዳዊት ደግሞ በኢየሩሳሌም የመከላከያ ግንቦች ውስጥ “ከስጋት ነፃ” ሆኖ ስለመኖር ተናግሯል። (መዝ 122:6, 7) ይሁን እንጂ ሕጉ፣ አንድ ሰው ከደኸየ ለራሱና ለቤተሰቡ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ሲል ራሱን ለባርነት ሊሸጥ እንደሚችል ገልጾ ነበር። ሆኖም ራሱን ለባርነት የሸጠው ዕብራዊ በሰባተኛው ዓመት ነፃ እንዲወጣ ሕጉ ይደነግጋል። (ዘፀ 21:2) በየ50 ዓመቱ በሚከበረው ኢዮቤልዩ ወቅት በምድሪቱ ላይ ለሁሉም ነዋሪዎች ነፃነት ይታወጅ ነበር። ዕብራዊ የሆኑ ባሪያዎች በሙሉ ነፃ ይወጡ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ ነበር።—ዘሌ 25:10-19
it-1 1200 አን. 2
ውርስ
መሬት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚቆይ ንብረት ስለሆነ ለዘለቄታው ሊሸጥ አይችልም ነበር። በመሆኑም መሬት ተሸጠ ሲባል ለተወሰነ ጊዜ መከራየቱን የሚያመለክት ነበር፤ ዋጋው የሚተመነው መሬቱ እስከ ቀጣዩ ኢዮቤልዩ ድረስ ባሉት ዓመታት የሚያስገኘውን ሰብል ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፤ ባለርስቱ መሬቱን ከኢዮቤልዩ በፊት መልሶ ካልገዛው ወይም ካልዋጀው በኢዮቤልዩ ወቅት ሁሉም መሬት ወደ ባለርስቱ ይመለሳል። (ዘሌ 25:13, 15, 23, 24) ይህ መመሪያ፣ ቅጥር በሌላቸው ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ይጨምራል፤ ምክንያቱም ቤቶቹ የእርሻ መሬት ክፍል እንደሆኑ ይቆጠራሉ። አንድ ሰው በቅጥር በታጠረ ከተማ ውስጥ የሚገኝን መኖሪያ ቤት ቢሸጥ የመዋጀት መብቱ እንደተጠበቀ የሚቆየው ቤቱን ከሸጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ ቤቱ ለዘለቄታው የገዢው ንብረት ይሆናል። በሌዋውያን ከተሞች ውስጥ ያሉትን የሌዋውያን ቤቶች በተመለከተ ግን ሌዋውያኑ እነዚህን ቤቶች የመዋጀት መብታቸው ምንጊዜም የተጠበቀ ነው፤ ምክንያቱም ሌዋውያን ርስት የላቸውም።—ዘሌ 25:29-34
it-2 122-123
ኢዮቤልዩ
እስራኤላውያን የኢዮቤልዩን ሕግ ማክበራቸው በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ በሚታየው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ከመውደቅ ይጠብቃቸዋል፤ በሌላ አባባል በጣም ሀብታምና በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎች የሞሉበት ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር ያደርጋል። ይህ ዝግጅት ለግለሰቦች የሚያስገኘው ጥቅም ብሔሩንም ያጠናክረዋል፤ ምክንያቱም ማንም ሰው በኢኮኖሚ ችግር ተደቁሶ ሥራ ፈት አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው አቅሙንና ችሎታውን አስተባብሮ ብሔሩን መገንባት ይችላል። እስራኤላውያን ታዛዥ በሚሆኑበት ጊዜ ይሖዋ እርሻቸውን ስለሚባርከውና ግሩም ትምህርት ስለሚሰጣቸው እውነተኛ ቲኦክራሲ ብቻ ሊያስገኝ የሚችለውን ፍጹም አስተዳደርና ብልጽግና ማጣጣም ይችሉ ነበር።—ኢሳ 33:22
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሰዎች ሲያናድዱህ
አንድ እስራኤላዊ የባልንጀራውን ዓይን ቢያጠፋ ሕጉ ተገቢው ቅጣት እንዲበየንበት ያዛል። ይሁንና ጉዳት ባደረሰው ግለሰብም ሆነ በቤተሰቡ አባላት ላይ የቅጣት እርምጃውን የሚወስደው በደል የተፈጸመበት ሰው አይደለም። ሕጉ በደል የተፈጸመበት ግለሰብ ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት ጉዳዩን ሥልጣን በተሰጣቸው ሰዎች ማለትም በተሾሙ ዳኞች ፊት እንዲያቀርብ ያዛል። ሆነ ብሎ ወንጀል የሚፈጽም ሰው እሱ የፈጸመው ድርጊት በራሱ ላይ የሚፈጸምበት መሆኑ ሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳይፈጽሙ ለማስጠንቀቅ ያገለግል ነበር። ይሁንና ሕጉ ከዚህም ያለፈ ጥቅም ነበረው።
ከየካቲት 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 26-27
“የይሖዋን በረከት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?”
‘ከከንቱ ነገሮች’ ራቁ
8 “ገንዘብ” አምላክ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በጥንቷ እስራኤል የሚገኝን አንድ ድንጋይ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ድንጋዩ፣ ቤት ለመሥራት ወይም ግንብ ለመገንባት ሊያገለግል ይችላል። በሌላ በኩል ግን “የማምለኪያ ዐምድ” ወይም “የተቀረጸ ድንጋይ” ተደርጎ ከተበጀ ለይሖዋ ሕዝቦች ማሰናከያ ይሆናል። (ዘሌ. 26:1) በተመሳሳይም ገንዘብ አስፈላጊ ሲሆን በተገቢው መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ገንዘብ፣ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚያስፈልገን ከመሆኑም በላይ በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ልናውለው እንችላለን። (መክ. 7:12፤ ሉቃስ 16:9) ሆኖም ገንዘብን ከክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ካስበለጥነው አምላካችን ሆነ ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) ሀብት ማካበት ከፍ ተደርጎ በሚታይበት ዓለም ውስጥ በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል።—1 ጢሞ. 6:17-19
it-1 223 አን. 3
አክብሮታዊ ፍርሃት
ይሖዋ ሙሴን የተጠቀመበት መንገድና ከእሱ ጋር የነበረው ግንኙነት ሙሴ በአምላክ ሕዝቦች ዘንድ የተከበረና የተፈራ (ዕብ. ሞህራ) እንዲሆን አድርጎታል። (ዘዳ 34:10, 12፤ ዘፀ 19:9) እምነት ያላቸው ሰዎች ለሙሴ ሥልጣን ተገቢ ፍርሃት ነበራቸው። አምላክ የሚናገረው በእሱ አማካኝነት እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። እስራኤላውያን ለይሖዋ መቅደስም አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ነበረባቸው። (ዘሌ 19:30፤ 26:2) ይህም ሲባል በመቅደሱ ውስጥ ይሖዋ ባዘዘው መንገድ አምልኳቸውን በማከናወንና ምግባራቸው ከሁሉም የአምላክ ትእዛዛት ጋር የሚስማማ እንዲሆን በማድረግ ለመቅደሱ አክብሮት እንዳላቸው ሊያሳዩ ይገባ ነበር ማለት ነው።
w91 3/1 17 አን. 10
“የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ
10 ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ ነግሮት ነበር፦ “በሥርዓቴ ብትሄዱ፣ ትዕዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፣ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ። ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ። ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ። ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” (ዘሌዋውያን 26:3, 4, 6, 12) እሥራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ጥበቃ ስለሚያገኙ በሚያስፈልጋቸው ሥጋዊ ነገሮች ረገድም መትረፍረፍና ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ስለሚኖራቸው ሰላምን ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከይሖዋ ሕግ ጋር በመጣበቃቸው ላይ የተመካ ነበር።—መዝሙር 119:165
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 617
ቸነፈር
የአምላክን ሕግ ችላ በማለት ምክንያት የሚመጣ። እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ካፈረሱ አምላክ ‘በመካከላቸው በሽታ እንደሚልክባቸው’ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘሌ 26:14-16, 23-25፤ ዘዳ 28:15, 21, 22) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነት ከአምላክ በረከት ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል (ዘዳ 7:12, 15፤ መዝ 103:1-3፤ ምሳሌ 3:1, 2, 7, 8፤ 4:21, 22፤ ራእይ 21:1-4)፤ በሽታ ደግሞ ከኃጢአትና ከአለፍጽምና ጋር ተያይዟል። (ዘፀ 15:26፤ ዘዳ 28:58-61፤ ኢሳ 53:4, 5፤ ማቴ 9:2-6, 12፤ ዮሐ 5:14) ይሖዋ አምላክ ራሱ በሰዎች ላይ ድንገተኛ ሕመም ያመጣበት ጊዜ እንዳለ አይካድም፤ ለምሳሌ ሚርያምን፣ ዖዝያንና ግያዝን በሥጋ ደዌ መቷቸዋል (ዘኁ 12:10፤ 2ዜና 26:16-21፤ 2ነገ 5:25-27)፤ ብዙውን ጊዜ ግን ሕመምና ቸነፈር፣ ግለሰቦች ወይም ብሔራት የተከተሉት የኃጢአት ጎዳና ያመጣው መዘዝ ነው። እነዚህ ሰዎች የታመሙት የዘሩትን ስላጨዱ ነው፤ አካላዊ ሥቃይ የደረሰባቸው የስህተት ጎዳና በመከተላቸው ነው። (ገላ 6:7, 8) ሐዋርያው ጳውሎስ አስጸያፊ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን በተመለከተ ሲናገር “አምላክ . . . የገዛ ራሳቸውን አካል እንዲያስነውሩ ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው። . . . እነሱ ራሳቸውም ለጥፋታቸው የሚገባውን ቅጣት እየተቀበሉ ነው” ብሏል።—ሮም 1:24-27
ከየካቲት 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 1-2
“ይሖዋ ሕዝቡን ያደራጃል”
የይሖዋ አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ቦታ
4 በምድረ በዳ ሠፍረው የነበሩትን እስራኤላውያን ከላይ ሆነህ ወደታች ለመመልከት አጋጣሚ አግኝተህ ቢሆን ኖሮ ምን ታይ ነበር? በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ በሦስት በሦስት ነገድ የተከፋፈለውን ሦስት ሚልዮን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን ሕዝብ የያዙ በጣም ብዙ ነገር ግን ሥርዓታማ በሆነ መንገድ በረድፍ በረድፍ የተተከሉ ድንኳኖችን ታይ ነበር። ቀረብ ብለህ ስትመለከት ደግሞ ወደ ሠፈሩ መሐል አካባቢ ሌሎች በቡድን በቡድን የተከፋፈሉ ድንኳኖችን ታያለህ። እነዚህ በአራት ተከፍለው በትንሽ በትንሹ አንድ ላይ እጅብ ብለው የተተከሉ ድንኳኖች የሌዊ ነገድ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸው ናቸው። በሠፈሩ መሐል በጨርቅ በተጋረደው ቦታ ላይ አንድ ለየት ያለ ቅርፅ ያለው ነገር ይታያል። ይህም የእስራኤል ‘ጥበበኞች’ ይሖዋ በሰጣቸው ፕላን መሠረት የሠሩት “የመገናኛው ድንኳን” ወይም የማደሪያው ድንኳን ነው።—ዘኁልቁ 1:52, 53፤ 2:3, 10, 17, 18, 25፤ ዘጸአት 35:10
it-1 397 አን. 4
ሰፈር
የእስራኤላውያን ሰፈር በጣም ሰፊ ነበር። ከላይ እንደተገለጸው ተዋጊ የሆኑ ወንዶች ቁጥር 603,550 ነበር፤ ይህ ቁጥር ሴቶችንና ልጆችን፣ አረጋውያንንና የአካል ጉዳተኞችን፣ 22,000 ሌዋውያንን እንዲሁም “እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” የተባሉትን የባዕድ አገር ሰዎች አይጨምርም፤ በእስራኤላውያን ሰፈር የነበረው ሕዝብ በድምሩ 3,000,000 ወይም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል። (ዘፀ 12:38, 44፤ ዘኁ 3:21-34, 39) እነዚህን ሁሉ ሰዎች የያዘው ሰፈር ምን ያህል ሰፊ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፤ በዚህ ረገድ የሚሰነዘሩት ግምቶች በጣም የተለያዩ ናቸው። ሕዝቡ በኢያሪኮ ማዶ በሚገኘው በሞዓብ ሜዳ ላይ በሰፈሩበት ወቅት ሰፈራቸው “ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሺቲም” እንደሚደርስ ተገልጿል።—ዘኁ 33:49
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 764
ምዝገባ
ብዙውን ጊዜ ምዝገባ የሚካሄደው ነገድንና ቤተሰብን መሠረት በማድረግ ሲሆን የእያንዳንዱ ሰው ስምና የዘር ሐረግ ይመዘገባል። እንዲህ ያለው ምዝገባ ከሕዝብ ቆጠራ የተለየ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ብሔራዊ ምዝገባዎች የተለያየ ዓላማ ነበራቸው፤ ለምሳሌ ከቀረጥና ከውትድርና አገልግሎት፣ ለሌዋውያን ደግሞ በመቅደሱ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ውለዋል።
ከየካቲት 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 3-4
“ሌዋውያን የሚያከናውኑት አገልግሎት”
it-2 683 አን. 3
ካህን
በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር። እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች በነበሩበት ወቅት ይሖዋ የግብፅን በኩሮች በአሥረኛው መቅሰፍት አጥፍቶ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤላውያንን በኩር ወንዶች በሙሉ ለራሱ ቀድሷቸዋል። (ዘፀ 12:29፤ ዘኁ 3:13) እነዚህ በኩሮች ለይሖዋ ለሚቀርብ ልዩ አገልግሎት የተለዩ የእሱ ንብረቶች ነበሩ። በመሆኑም ይሖዋ ሁሉንም እስራኤላውያን በኩሮች ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉና መቅደሱን እንዲንከባከቡ ሊመድባቸው ይችል ነበር። ሆኖም ይሖዋ የሌዊ ነገድ አባላት የሆኑ ወንዶችን ለዚህ አገልግሎት ለመጠቀም መርጧል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ በሌሎቹ 12 ነገዶች (የዮሴፍ ልጆች የሆኑት የኤፍሬምና የምናሴ ዘሮች እንደ ሁለት ነገድ ተቆጥረዋል) ውስጥ ባሉ በኩር ወንዶች ምትክ ሌዋውያን ወንዶች እንዲለዩ ፈቀደ። ቆጠራ በተደረገበት ወቅት አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሌዋዊ ያልሆኑ በኩሮች ቁጥር ከሌዋውያን ወንዶች ቁጥር በ273 እንደሚበልጥ ታወቀ፤ በመሆኑም አምላክ 273ቱን ሰዎች ለመዋጀት ለእያንዳንዱ ግለሰብ አምስት ሰቅል እንዲከፈል አዘዘ፤ ገንዘቡም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ተሰጠ። (ዘኁ 3:11-16, 40-51) ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ይሖዋ ከሌዊ ነገድ የአሮንን ቤተሰብ ወንዶች ለእስራኤል ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ መርጦ ነበር።—ዘኁ 1:1፤ 3:6-10
it-2 241
ሌዋውያን
የሥራ ድርሻ። ሌዋውያን ከሦስት ቤተሰቦች ይኸውም ጌድሶን (ጌርሳም)፣ ቀአት እና ሜራሪ ከተባሉት የሌዊ ወንዶች ልጆች የተገኙ ነበሩ። (ዘፍ 46:11፤ 1ዜና 6:1, 16) እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት ሦስቱም ቤተሰቦች በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ የሚሰፍሩበት ቦታ ተመድቦላቸው ነበር። የቀአት ዘር የሆኑት የአሮን ቤተሰቦች በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በማደሪያ ድንኳኑ ፊት ይሰፍሩ ነበር። ሌሎቹ ቀአታውያን በስተ ደቡብ፣ ጌድሶናውያን በስተ ምዕራብ፣ ሜራራውያን ደግሞ በስተ ሰሜን ይሰፍሩ ነበር። (ዘኁ 3:23, 29, 35, 38) የማደሪያ ድንኳኑን መትከል፣ መንቀልና መሸከም የሌዋውያኑ ሥራ ነበር። ሰፈሩ በሚነሳበት ጊዜ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየውን መጋረጃ ያወርዱታል፤ ከዚያም የምሥክሩን ታቦት፣ መሠዊያዎቹን እንዲሁም ሌሎቹን የተቀደሱ ዕቃዎች ይሸፍኗቸዋል። ቀጥሎም ቀአታውያን እነዚህን ቁሳቁሶች ይሸከማሉ። ጌድሶናውያን የድንኳኑን ጨርቆች፣ መደረቢያዎቹን፣ መከለያዎቹን፣ የግቢውን መጋረጃዎች እንዲሁም የድንኳኑን ገመዶች (የማደሪያ ድንኳኑ ገመዶች ሳይሆኑ አይቀሩም) ይሸከማሉ፤ ሜራራውያን ደግሞ ቋሚዎቹን፣ ዓምዶቹን፣ መሰኪያዎቹን፣ የድንኳን ካስማዎቹንና ገመዶቹን (በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ ያለው ግቢ የድንኳን ገመዶች) ይሸከማሉ።—ዘኁ 1:50, 51፤ 3:25, 26, 30, 31, 36, 37፤ 4:4-33፤ 7:5-9
it-2 241
ሌዋውያን
በሙሴ ዘመን ሌዋውያን አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ ማከናወን የሚጀምሩት (ለምሳሌ የማደሪያ ድንኳኑ በሚጓጓዝበት ጊዜ ድንኳኑንና ቁሳቁሶቹን የሚሸከሙት) በ30 ዓመታቸው ነበር። (ዘኁ 4:46-49) እርግጥ አንዳንዶቹን ሥራዎች ከ25 ዓመታቸው ጀምሮ ማከናወን ይችሉ ነበር፤ ሆኖም የማደሪያ ድንኳኑን እንደማጓጓዝ ያሉ ከባድ ሥራዎችን አያከናውኑም። (ዘኁ 8:24) በንጉሥ ዳዊት ዘመን ሌዋውያኑ አገልግሎታቸውን ማከናወን የሚጀምሩበት ዕድሜ ወደ 20 ዓመት ዝቅ ተደርጓል። ዳዊት፣ ይህን ያደረገው የማደሪያ ድንኳኑ (በቤተ መቅደሱ ስለሚተካ) ከቦታ ቦታ መጓጓዝ ስለማያስፈልገው እንደሆነ ገልጿል። ሌዋውያኑ 50 ዓመት ከሞላቸው በኋላ በቤተ መቅደሱ ማገልገል አይጠበቅባቸውም። (ዘኁ 8:25, 26፤ 1ዜና 23:24-26፤ ዕድሜ የሚለውን ተመልከት።) ሌዋውያን ሕጉን ጠንቅቀው ማወቅ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሕጉን በሰዎች ፊት ማንበብና ለተራው ሕዝብ ማስተማር ነበረባቸው።—1ዜና 15:27፤ 2ዜና 5:12፤ 17:7-9፤ ነህ 8:7-9
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
አምላክን በመፍራት ጠቢብ ሁን!
13 ዳዊት፣ በችግር ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት የይሖዋን እርዳታ ማግኘቱ ለአምላክ የጠለቀ ፍርሃት እንዲያድርበት ከማድረጉም በላይ የመተማመን መንፈሱን አጠንክሮለታል። (መዝሙር 31:22-24) ሆኖም፣ ዳዊት በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ለአምላክ የነበረው ፍርሃት በመቀነሱ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርጎ ነበር። የመጀመሪያው፣ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ካደረገው ዝግጅት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ጊዜ ታቦቱ የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት በሌዋውያን ትከሻ ላይ ሆኖ ከመጓዝ ይልቅ በሠረገላ ተጭኖ ነበር። ሠረገላውን ይነዳ የነበረው ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ አስቦ በፈጸመው ‘የድፍረት’ ድርጊት ወዲያውኑ ተቀሠፈ። ዖዛ ትልቅ ኃጢአት የፈጸመ ቢሆንም እንኳ ዳዊት ለአምላክ ሕግ ተገቢውን አክብሮት ሳይሰጥ መቅረቱ ለዚህ አሳዛኝ ክስተት አስተዋጽኦ አድርጓል። አምላክን መፍራት ማለት እርሱ ያዘዛቸውን ነገሮች በእርሱ መንገድ መፈጸም ማለት ነው።—2 ሳሙኤል 6:2-9፤ ዘኍልቍ 4:15፤ 7:9
ከየካቲት 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 5-6
“ናዝራውያንን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?”
it-2 477
ናዝራዊ
የናዝራዊነት ስእለት በሚሳሉ ሰዎች ላይ የሚጣሉት ሦስት ዋና ዋና ገደቦች የሚከተሉት ነበሩ፦ (1) የሚያሰክር መጠጥ መጠጣት አይፈቀድላቸውም፤ እንዲሁም ከወይን ተክል የተዘጋጀን ማንኛውንም ነገር ይኸውም ያልበሰለም ሆነ የበሰለ የወይን ፍሬ እንዲሁም ዘቢብ መብላት አይችሉም፤ በተጨማሪም ከወይን ፍሬ የተዘጋጀን ማንኛውንም መጠጥ ይኸውም የወይን ጭማቂ፣ የወይን ጠጅ ወይም ኮምጣጤ መጠጣት አይችሉም ነበር። (2) የራስ ፀጉራቸውን መቆረጥ አልነበረባቸውም። (3) በድን መንካት አይችሉም ነበር፤ ይህም እንደ አባት፣ እናት፣ ወንድምና እህት ያሉ የቅርብ ዘመዶቻቸውን አስከሬንም ይጨምራል።—ዘኁ 6:1-7
ልዩ ስእለት። አንድ ሰው ይህን ልዩ ስእለት የሚሳለው ‘ለይሖዋ ናዝራዊ [ማለትም ለአንድ ነገር የተወሰነ፤ ለአንድ ዓላማ የተለየ] ሆኖ ለመኖር’ እንጂ የባሕታዊ ሕይወት በመምራት ሌሎችን ለማስደመም አይደለም። ግለሰቡ “ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል።”—ዘኁ 6:2, 8
ከናዝራውያን የሚጠበቀው ብቃት በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ልዩ ትርጉም አለው። ሊቀ ካህናቱ ቅዱስ ኃላፊነት ስለተሰጠው የቅርብ ዘመዶቹን ጨምሮ የማንንም አስከሬን መንካት እንደማይፈቀድለት ሁሉ ናዝራዊውም ይህን ማድረግ አይፈቀድለትም ነበር። ሊቀ ካህናቱና ሌሎቹ ካህናት ከባድ ኃላፊነት ስለተጣለባቸው በይሖዋ ፊት ቅዱስ አገልግሎት በሚያቀርቡበት ወቅት የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ መጠጣት አይፈቀድላቸውም።—ዘሌ 10:8-11፤ 21:10, 11
በተጨማሪም አንድ ናዝራዊ (ዕብ. ናዚር) “የራስ ፀጉሩን በማሳደግ ቅዱስ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል”፤ ራሱ ላይ ያለው ይህ ምልክት ቅዱስ የሆነውን የናዝራዊነት ስእለት እንደተሳለ ለሚያየው ሁሉ ለማሳወቅ ያስችላል። (ዘኁ. 6:5) ናዚር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፣ ቅዱስ በሆነው የሰንበት ዓመትና በኢዮቤልዩ ወቅት ከሚኖረው “ያልተገረዘ” ወይን ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። (ዘሌ 25:5, 11) በሊቀ ካህናቱ ጥምጥም ላይ የሚገኘውና “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ በላዩ ላይ የተቀረጸበት ጠፍጣፋ ወርቅ ‘ለአምላክ የተወሰኑ [ዕብ. ኔዜር፣ ናዚር ከሚለው ሥርወ ቃል የመጣ] መሆንን የሚያሳየው ቅዱስ ምልክት’ ተብሎ የተጠራ መሆኑም ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘፀ 39:30, 31) በተመሳሳይም የእስራኤል የተቀቡ ነገሥታት የሚያጠልቁት ንጉሣዊ ዘውድ ወይም አክሊል ኔዜር ተብሎ ይጠራ ነበር። (2ሳሙ 1:10፤ 2ነገ 11:12፤ አክሊል፤ መወሰን የሚሉትን ተመልከት።) ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሴት ረጅም ፀጉር የተሰጣት በራስ መሸፈኛ ምትክ እንደሆነ ገልጿል። ይህም ከወንድ የተለየ ቦታ እንዳላት የሚጠቁም ተፈጥሯዊ ማስታወሻ ነው፤ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያላትን የተገዢነት ቦታ ማስታወስ ይኖርባታል። ስለዚህ ለአምላክ የተወሰነው ናዝራዊ ፀጉሩን እንዲያስረዝም (ለወንድ ተፈጥሯዊ ያልሆነ)፣ ከወይን ጠጅ ጨርሶ እንዲርቅ እንዲሁም ንጹሕ እንዲሆንና እንዳይረክስ የተሰጠው መመሪያ ራሱን መካድና ለይሖዋ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መገዛት እንዳለበት ያስታውሰዋል።—1ቆሮ 11:2-16፤ ፀጉር፤ የፀጉር መሸፈኛ፤ ተፈጥሮ የሚሉትን ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
የሳምሶን ናዝራዊነት ግን ለየት ያለ ነበር። ከመወለዱ በፊት አንድ የይሖዋ መልአክ ለእናቲቱ “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል” ብሏት ነበር። (መሳፍንት 13:5) ሳምሶን ናዝራዊ ለመሆን አልተሳለም ነበር። ዕድሜ ልኩን ናዝራዊ እንዲሆን የሾመው አምላክ ራሱ ነው። የሳምሶን ዓይነት ናዝራዊነት በድን መንካትን የሚከለክል ደንብ ሊያካትት አይችልም። ይህ ሕግ በሳምሶን ላይ የሚሠራ ቢሆንና ድንገት አስከሬን ቢነካ፣ ሲወለድ የጀመረውን የዕድሜ ልክ ናዝራዊነት እንዴት እንደገና ሊጀምር ይችላል? ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ዕድሜ ልካቸውን ናዝራዊ ከሚሆኑ ሰዎችና በገዛ ፈቃዳቸው ናዝራዊ ከሆኑ ሰዎች የሚጠበቀው ብቃት በአንዳንድ መንገዶች ይለያያል።