የመጽሐፍ ቅዱስን ምንነት እንዳለ አምኖ መቀበል
“ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፣ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።”—1 ተሰሎንቄ 2:13
1. መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ የሚያደርገው በውስጡ የያዘው የትኛው እውቀት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ በብዛት የተተረጎመና በሰፊው የተሰራጨ መጽሐፍ ነው። ከታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አንዱ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ከዚህ ይበልጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የየትኛውም ዘርና ብሔር አባል የሆኑ ሰዎች ሥራቸውም ሆነ የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ባስቸኳይ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን መመሪያ ይሰጣል። (ራእይ 14:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ ልብንና አእምሮን በሚያረካ መንገድ እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ የሰው ልጅ ሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? (ዘፍጥረት 1:28፤ ራእይ 4:11) ሰብዓዊ መንግሥታት ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ያልቻሉት ለምንድን ነው? (ኤርምያስ 10:23፤ ራእይ 13:1, 2) ሰዎች ለምን ይሞታሉ? (ዘፍጥረት 2:15–17፤ 3:1–6፤ ሮሜ 5:12) በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? (መዝሙር 119:105፤ ምሳሌ 3:5, 6) የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል?—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:3–5
2. መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቻችን ፍጹም ተኣማኒነት ያለው መልስ የሚሰጠን ለምንድን ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች ተኣማኒነት ባለው መንገድ መልስ የሚሰጠው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል ስለሆነ ነው። አምላክ መጽሐፉን ለማጻፍ በሰዎች ቢጠቀምም በ2 ጢሞቴዎስ 3:16 [አዓት] ላይ በማያሻማ መንገድ እንደተገለጸው “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ነው።” የሰው ልጅ ያከናወናቸውን ነገሮች አስመልክቶ ሰዎች በግል የሰጧቸው ትንታኔዎች ውጤት አይደለም። “ትንቢት [ወደፊት ስለሚከሰቱ ሁኔታዎች የተነገሩት ነገሮች፣ መለኰታዊ ትእዛዛት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደረጃ] ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:21
3. (ሀ) በተለያዩ አገሮች ያሉ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ከፍተኛ ግምት እንደሰጡት የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (ለ) ግለሰቦች ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማንበብ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ለመጣል ፈቃደኛ የነበሩት ለምንድን ነው?
3 ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቀሜታ ተገንዝበው መጽሐፍ ቅዱስን ለማግኘትና ለማንበብ ሲሉ እስከ መታሰርና እስከ መሞት ድረስ እንኳ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። ቀሳውስቱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ካነበቡ የእኛ ተሰሚነት ይቀንሳል የሚል ፍራቻ ባደረባቸው በካቶሊካዊቷ አገር በስፔይን ውስጥ ባለፉት ዘመናት የሆነው ይህ ነበር፤ አምላክ የለም ብሎ የሚያምነው መንግሥት የሁሉንም ሃይማኖት ተጽዕኖ ጨርሶ ለማጥፋት ከባድ እርምጃ በወሰደበት በአልባኒያ ውስጥ የተፈጸመውም ሁኔታ ይህ ነበር። ሆኖም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች የቅዱሳን ጽሑፎችን ቅጂዎች እንደ ውድ ሀብት አድርገው ይይዟቸው፣ ያነብቧቸውና በጋራ ይጠቀሙባቸው ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዛክሰንሐውዘን የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ (የተከለከለ ቢሆንም እንኳ) ካንድ የማጎሪያ ክፍል ወደሌላ የማጎሪያ ክፍል በዘዴ ይዘዋወር ነበር፤ መጽሐፉን ያገኙትም ለሌሎች ለማካፈል እንዲችሉ የተወሰኑ ክፍሎችን በቃላቸው ያጠኑ ነበር። በ1950ዎቹ በወቅቱ ኮሙኒስት በነበረችው ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በእምነታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ማታ ማታ ለማንበብ እንዲችሉ አንዱ እስረኛ ለሌላው እስረኛ አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያቀብል የነበረው ከተያዘ የእስራቱ ጊዜ ተራዝሞ ለረጅም ጊዜ በእስር ቤቱ ውስጥ እንደሚቆይ እያወቀ ነበር። ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ስለተገነዘቡና “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት” እንደማይኖር ስለሚያውቁ ነው። (ዘዳግም 8:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት እነዚህ ቃላት ምሥክሮቹ ለማመን የሚያስቸግር ግፍ ቢፈጸምባቸውም እንኳ በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው እንዲቆዩ አስችለዋቸዋል።
4. መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው ይገባል?
4 መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ ለማየት ያህል በመጽሐፍ መደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ አሊያም አማኞች ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ወቅት ብቻ የሚጠቀሙበት መጽሐፍ አይደለም። የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች በቀላሉ ለማስተዋል እንዲያስችለንና የምንሄድበትን ትክክለኛ መንገድ እንዲጠቁመን በየቀኑ ልንጠቀምበት ይገባል።—መዝሙር 25:4, 5
እንድናነበውና እንድንረዳው ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ ነው
5. (ሀ) በተቻለ መጠን ሁላችንም ምን ሊኖረን ይገባል? (ለ) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነበሩ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉ የሚያውቁት እንዴት ነበር? (ሐ) መዝሙር 19:7–11 መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማንበብ ያለህን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?
5 በዘመናችን በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንደ ልብ ይገኛሉ፤ እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ አንባቢም የራሱ ቅጂ እንዲኖረው እናበረታታዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የማተሚያ መሣሪያዎች አልነበሩም። ሰዎች በአጠቃላይ የግል ቅጂዎች አልነበሯቸውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ የተጻፈ ቃሉን እንዲያዳምጡ ለአገልጋዮቹ ዝግጅት አድርጎላቸው ነበር። ስለዚህ ዘጸአት 24:7 ሙሴ ይሖዋ እንዲጽፍ ያዘዘውን ከጻፈ በኋላ “የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው” በማለት ይናገራል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በሲና ተራራ ላይ የታየውን መለኮታዊ መግለጫ ስለተመለከቱ ሙሴ የሚያነብላቸው መልእክት ከአምላክ እንደመጣና ይህን መልእክት ማወቅ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል። (ዘጸአት 19:9, 16–19፤ 20:22) እኛም ብንሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ ማወቅ ያስፈልገናል።—መዝሙር 19:7–11
6. (ሀ) የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት ሙሴ ምን አደረገ? (ለ) የሙሴን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
6 የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ያሳለፉትን የዘላንነት ኑሮ ወደ ኋላ ትተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ሊሻገሩ በዝግጅት ላይ ሳሉ የይሖዋን ሕግና እሱ ከእነሱ ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች መከለሳቸው ተገቢ ነበር። ሙሴ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ሕጉን ከለሰላቸው። የሕጉን ዝርዝር ሐሳቦች አስታወሳቸው እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚነኩትን ከሕጉ በስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶችና እነሱ ሊኖራቸው የሚገባውን አቋም አጎላ። (ዘዳግም 4:9, 35፤ 7:7, 8፤ 8:10–14፤ 10:12, 13) ዛሬ እኛም አዲስ ሥራዎች ሲሰጡን ወይም በሕይወታችን ውስጥ አዲስ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡት ምክር የምናደርገውን ነገር እንዴት ሊነካው እንደሚገባ ብንመረምር ጥሩ ነው።
7. እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የይሖዋን ሕግ በአእምሯቸውና በልባቸው ለመቅረጽ ምን ተደረገ?
7 እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ከተሻገሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያስተላለፈላቸውን ትእዛዞች ለመከለስ እንደገና ተሰበሰቡ። ሕዝቡ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተሰበሰቡ። ግማሾቹ ነገዶች በጌባል ተራራ ግማሾቹ ደግሞ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ። እዚያም ኢያሱ “የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ።” በዚህ ሁኔታ መጻተኞችን ጨምሮ ወንዶቹ፣ ሴቶቹና ሕፃናቱ በይሖዋ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት የሚያሳጣቸውን ነገርና ይሖዋን ከታዘዙ ደግሞ የሚያገኟቸውን በረከቶች የሚመለከቱትን ወቅታዊ የሆኑ ሥነ ምግባራዊ ሕጎች እንደገና ሲነበቡ አዳመጡ። (ኢያሱ 8:34, 35) በይሖዋ ፊት ጥሩና መጥፎ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ ሁላችን ልናደርገው እንደሚገባ ሁሉ እነርሱም ለመልካም ነገር ፍቅር፣ ለመጥፎ ነገር ደግሞ ጥላቻ በልባቸው ውስጥ እንዲሰረጽ ማድረግ ነበረባቸው።—መዝሙር 97:10፤ 119:103, 104፤ አሞጽ 5:15
8. በእስራኤል ውስጥ በተለያዩ ብሔራዊ ስብሰባዎች ወቅት የአምላክ ቃል በየጊዜው መነበቡ ምን ጥቅም ነበረው?
8 በእነዚህ ታሪካዊ ወቅቶች ሕጉ ከመነበቡም በተጨማሪ በዘዳግም 31:10–12 ላይ እንደተገለጸው የአምላክ ቃል ዘወትር እንዲነበብ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በየሰባት ዓመቱ መላው ሕዝብ የአምላክ ቃል ሲነበብ ለማዳመጥ ይሰበሰብ ነበር። ይህ ዝግጅት የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ያስችላቸው ነበር። ይህ ንባብ ስለ ዘሩ የተሰጡት ተስፋዎች በአእምሯቸውና በልባቸው ሕያው እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ታማኝ ሰዎች በመሲሕ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ አገልግሏል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ የተደረገላቸው ዝግጅት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ አልተቋረጠም። (1 ቆሮንቶስ 10:3, 4) እንዲያውም አምላክ ለነቢያት የገለጠላቸው ተጨማሪ ነገሮች ሲታከሉበት የአምላክ ቃል ይበልጥ በለጸገ።
9. (ሀ) እስራኤላውያን ቅዱሳን ጽሑፎችን ያነቡ የነበሩት ብዙ ሆነው ሲሰበሰቡ ብቻ ነበርን? አብራራ። (ለ) የቅዱሳን ጽሑፎች ትምህርት በቤተሰብ ውስጥ ይሰጥ የነበረው እንዴት ነው? የትምህርቱ ዓላማስ ምን ነበር?
9 የአምላክ ቃል የሚሰጠው ምክር የሚከለሰው ሰዎች ብዙ ሆነው በሚሰበሰቡባቸው በእነዚህ ጊዜያት ብቻ አልነበረም። የተወሰኑ የአምላክ ቃል ክፍሎችና በውስጡ የታቀፉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በየቀኑ ውይይት ይደረግባቸው ነበር። (ዘዳግም 6:4–9) በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ ቦታዎች ወጣቶች የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ሊያገኙ ይችላሉ፤ የራሳቸው ቅጂ እንዲኖራቸው ማድረጋቸው በጣም ይጠቅማቸዋል። ይሁን እንጂ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነበረው ሁኔታ እንደዚህ አልነበረም። በዚያን ወቅት ወላጆች ከአምላክ ቃል ለልጆቻቸው ትምህርት ሲሰጡ በቃላቸው ባጠኗቸው፣ በልባቸው ውስጥ እንደ ውድ ሀብት አድርገው በጠበቋቸው እውነቶችና በግላቸው በጻፏቸው ጥቂት ምንባቦች መጠቀም ነበረባቸው። ቃሎቹን በተደጋጋሚ በመንገር ልጆቻቸው ለይሖዋና ለመንገዶቹ ፍቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥሩ ነበር። ዓላማው አእምሯቸውን በእውቀት መሙላት ሳይሆን እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለይሖዋና ለቃሉ ፍቅር እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲኖር መርዳት ነበር።—ዘዳግም 11:18, 19, 22, 23
በምኩራብ ይደረግ የነበረው የቅዱሳን ጽሑፎች ንባብ
10, 11. በምኩራቦች ምን የቅዱሳን ጽሑፎች ንባብ ፕሮግራም ይደረግ ነበር? ኢየሱስስ እነዚህን ጊዜያት እንዴት ተመለከታቸው?
10 አይሁዶች ለምርኮ ወደ ባቢሎን ከተወሰዱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለአምልኮ ቦታ እንዲሆኑ ተብለው ምኩራቦች ተቋቋሙ። በእነዚህ የመሰብሰቢያ ቦታዎች የአምላክ ቃል እንዲነበብና ውይይት እንዲደረግበት ተጨማሪ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ተዘጋጁ። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎችን የያዙ ወደ 6,000 ገደማ የሚደርሱ በእጅ የተጻፉ የጥንት ቅጂዎች እንዲተርፉ ያደረገው ይህ ነበር።
11 በምኩራብ ውስጥ ከሚሰጠው በጣም አስፈላጊ አገልግሎት አንዱ በዘመናዊዎቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ካሉት ከመጀመሪያዎቹ አምስት መጻሕፍት ጋር የሚመሳሰለው ቶራህ መነበቡ ነበር። ሥራ 15:21 በመጀመሪያ መቶ ዘመን እዘአ እንደዚህ ዓይነቱ ንባብ በሰንበት ቀን ይደረግ እንደነበረ ሲናገር ሚሽናህ ደግሞ በሁለተኛው መቶ ዘመን የሳምንቱ ሁለተኛና አምስተኛ ቀናትም ቶራህ የሚነበብባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ያሳያል። የተለያዩ ሰዎች የተመደቡትን ክፍሎች ተራ በተራ ያነቡ ነበር። በባቢሎን ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች ቶራህን በየዓመቱ ከዳር እስከ ዳር የማንበብ ልማድ የነበራቸው ሲሆን በጳለስጢና የነበሩት ደግሞ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንዴ ያነቡት ነበር። በተጨማሪም ከነቢያት መጽሐፍ የተወሰደ አንድ ክፍል ተነቦ ይብራራ ነበር። ኢየሱስ ይኖርበት በነበረው ቦታ በሚደረጉ የሰንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራሞች ላይ የመገኘት ልማድ ነበረው።—ሉቃስ 4:16–21
በግል ምላሽ መስጠትና የተማሩትን በሥራ ላይ ማዋል
12. (ሀ) ሙሴ ሕጉን ለሕዝቡ ሲያነብላቸው ሕዝቡ የተጠቀሙት እንዴት ነው? (ለ) ሕዝቡ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
12 በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉት የቅዱሳን ጽሑፎች ንባብ ለወጉ ያህል የሚደረግ ነገር አልነበረም። የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት ለማርካት ብቻ ተብሎ የሚደረግ አልነበረም። ሙሴ በሲና ተራራ ፊት ለፊት ባለው ሜዳ ‘የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ’ ያነበበው በአምላክ ዘንድ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲያውቁና ይህን ኃላፊነት እንዲፈጽሙት ብሎ ነበር። ታዲያ እንደዚያ አደረጉን? ንባቡ ምላሽ ይጠይቅ ነበር። ሕዝቡም ይህን ተገንዝበው “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም” አሉ።—ዘጸአት 24:7፤ ከዘጸአት 19:8ና ከ24:3 ጋር አወዳድር።
13. ኢያሱ አለመታዘዝ ስለሚያስከትለው እርግማን ሲያነብ ሕዝቡ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ምን ዓላማ ይዘው?
13 ቆየት ብሎ ኢያሱ ለሕዝቡ ቃል የተገባላቸውን በረከቶችና መርገሞች ሲያነብላቸው ከሕዝቡ ምላሽ ይጠበቅ ነበር። እያንዳንዱ እርግማን ከተነበበ በኋላ “ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ” የሚል መመሪያ ተሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 27:4–26) በዚህ ሁኔታ እያንዳንዱ ነጥብ አንድ በአንድ ሲጠቀስ ይሖዋ እነዚህን መጥፎ ነገሮች በማውገዙ መስማማታቸውን ገለጹ። ጠቅላላው ሕዝብ መስማማቱን የሚገልጽ ድምፅ ሲያስተጋባ ምንኛ የሚያስደስት ሁኔታ ነበር!
14. በነህምያ ዘመን ሕጉ ለሕዝቡ መነበቡ ልዩ ጥቅም ያስገኘው እንዴት ነው?
14 በነህምያ ዘመን ሕዝቡ በሙሉ ሕጉን ለመስማት ወደ ኢየሩሳሌም በተሰበሰቡበት ወቅት በሕጉ ውስጥ የሰፈሩትን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ እንዳልፈጸሟቸው ተገነዘቡ። በዚያን ወቅት የተማሩትን ወዲያውኑ በተግባር ላይ አዋሉት። ውጤቱስ ምን ነበር? “እጅግም ታላቅ ደስታ” ሆኖ ነበር። (ነህምያ 8:13–17) በበዓሉ ወቅት ለአንድ ሳምንት በየዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ካደረጉ በኋላ ሌሎች የሚፈለጉባቸው ነገሮች እንዳሉ ተገነዘቡ። ይሖዋ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ ከሕዝቡ ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች የሚዳስሱትን ታሪኮች በጸሎት ከለሱ። ይህ ሁሉ ሕጉ ከሚጠይቅባቸው ብቃቶች ጋር ለመስማማት፣ ከባዕዳን ሕዝቦች ጋር ከመጋባት ለመቆጠብና ቤተ መቅደሱንና የቤተ መቅደሱን አገልግሎት በተመለከተ ያለባቸውን ግዴታዎች ለመፈጸም በመሃላ እንዲያረጋግጡ ገፋፋቸው።—ነህምያ ከምዕራፍ 8–10
15. በዘዳግም 6:6–9 ላይ ያሉት መመሪያዎች በቤተሰብ ውስጥ የሚሰጠው የአምላክ ቃል ትምህርት ለወጉ ያህል የሚደረግ መሆን እንደሌለበት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
15 በተመሳሳይም በቤተሰብ ውስጥ የሚሰጠው የቅዱሳን ጽሑፎች ትምህርትም ለወጉ ያህል የሚሰጥ አልነበረም። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በዘዳግም 6:6–9 ላይ በምሳሌያዊ አገላለጽ ሕዝቡ ‘የአምላክን ቃሎች በእጆቻቸው ላይ እንደ ምልክት አድርገው እንዲያስሯቸው’ ይኸውም ምሳሌ በመሆንና በድርጊት ለይሖዋ መንገዶች ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ ታዘው ነበር። በተጨማሪም የአምላክን ቃሎች ‘በዓይኖቻቸው መካከል እንደ ክታብ ማድረግ ነበረባቸው፤’ በዚህ መንገድ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የታቀፉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ዘወትር በማስታወስ በየቀኑ ለሚያደርጓቸው ውሳኔዎች መሠረት አድርገው ይጠቀሙባቸዋል። (ዘጸአት 13:9, 14–16 ላይ ካለው አነጋገር ጋር አወዳድር።) ‘የአምላክን ቃሎች በቤታቸው መቃኖችና በደጃፋቸው በሮች ላይ መጻፍ ነበረባቸው፤’ በዚህ መንገድ ቤታቸውንና ማኅበረሰባቸውን የአምላክ ቃል የሚከበርባቸውና የሚተገበርባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ለይተው ያሳውቃሉ። በሌላ አባባል አኗኗራቸው የይሖዋን የጽድቅ ትእዛዛት እንደሚወዷቸውና እንደሚተገብሯቸው በግልጽ ማሳየት ነበረበት ማለት ነው። ይህ ምንኛ ጠቃሚ ይሆን ነበር! ቤተሰባችን በዕለታዊ ኑሮው ለአምላክ ቃል እንደዚህ ያለ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋልን? አይሁዶች ክታብ ይመስል ጥቅሶችን የያዙ ማህደሮች በማሰር ይህን ሁሉ የአምልኮ ዝግጅት እንደ ወግ መቁጠራቸው ያሳዝናል። አምልኳቸው ከልብ የመነጨ መሆኑ ቀረና በይሖዋ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት አጡ።—ኢሳይያስ 29:13, 14፤ ማቴዎስ 15:7–9
በበላይ ተመልካችነት ቦታ ያሉ ያላቸው ኃላፊነት
16. ኢያሱ ዘወትር ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበቡ ጠቃሚ የነበረው ለምንድን ነው?
16 ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ ረገድ የሕዝቡ የበላይ ተመልካቾች በነበሩት ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ ነበር። ይሖዋ ኢያሱን ‘ሕጉን ሁሉ ጠብቅ’ ብሎት ነበር። እንዲፈጽመው የተሰጠውን ኃላፊነት በተመለከተ “የሕጉን መጽሐፍ ቀንና ሌሊት አንብበው፣ . . . የዚያን ጊዜም መንገድህ ይሳካልሃል በጥበብም ትመላለሳለህ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር። (ኢያሱ 1:7, 8 አዓት) ዛሬ እንዳሉት ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሁሉ ኢያሱም ዘወትር ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበቡ ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጣቸውን ትእዛዞች ግልጽ በሆነ መንገድ በአእምሮው እንዲይዝ ይረዳዋል። በተጨማሪም ኢያሱ ይሖዋ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ሕዝቡን እንዴት እንደያዛቸው ማስተዋል ያስፈልገው ነበር። ስለ አምላክ ዓላማ የሚናገሩ ሐሳቦችን ሲያነብ ከዚያ ዓላማ ጋር በተያያዘ መልኩ ያለበትን ኃላፊነት ማሰቡ በጣም አስፈላጊ ነበር።
17. (ሀ) ነገሥታት ቅዱሳን ጽሑፎችን ይሖዋ በገለጸው መንገድ በማንበብ እንዲጠቀሙ ከተፈለገ ከንባባቸው በተጨማሪ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? (ለ) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸውና ማሰላሰላቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ የሕዝቡ ንጉሥ ሆኖ የሚያገለግለው እያንዳንዱ ንጉሥ በንግሥናው መጀመሪያ ላይ በካህናት እጅ ባለው ቅጂ ላይ የተመሠረተ የአምላክ ሕግ ቅጂ እንዲያስገለብጥ አዝዞ ነበር። ከዚያ በኋላ ‘ዕድሜውን ሁሉ ማንበብ’ ነበረበት። የዚህ ዓላማ ፍሬ ሐሳቦቹን በሙሉ በቃሉ ማጥናት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዓላማው ‘እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማር’ እና ‘ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ’ ነበር። (ዘዳግም 17:18–20) ይህም በሚያነበው ነገር ላይ በጥልቅ ማሰላሰልን ይጠይቅበት ነበር። አንዳንድ ነገሥታት የአስተዳደር ሥራ ስለሚበዛብን ይህን ለማድረግ አንችልም ብለው እንዳሰቡ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል፤ በቸልተኝነታቸው ሳቢያም ጠቅላላው ሕዝብ ተጎድቷል። የጉባኤ ሽማግሌዎች ሥራ ከነገሥታቱ የሥራ ድርሻ ጋር አንድ ዓይነት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም እንደ ነገሥታቱ ሁሉ ሽማግሌዎችም የአምላክን ቃል ማንበባቸውና ማሰላሰላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረጋቸው በእነሱ ጥበቃ ሥር ላሉት ዘወትር ተገቢ አመለካከት እንዲይዙ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም የአስተማሪነት ኃላፊነታቸውን አምላክን በሚያስከብርና እንደነሱ ክርስቲያን የሆኑትን በመንፈሳዊ በሚያንጽ መንገድ እንዲወጡ ያስችላቸዋል።—ቲቶ 1:9፤ ከዮሐንስ 7:16–18 ጋር አወዳድር፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 1:6, 7 ጋር አነጻጽር።
18. ሐዋርያው ጳውሎስ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
18 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉትን ቅዱሳን ጽሑፎች በደንብ ያውቃቸው ነበር። በጥንቷ ተሰሎንቄ ለነበሩ ሰዎች ሲመሰክርላቸው ከቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሶ እያመራመረ ውጤታማ በሆነ መንገድ ምክንያቱን በማስረዳት ትርጉሙን እንዲያስተውሉ ሊረዳቸው ችሎ ነበር። (ሥራ 17:1–4) ከልብ ያዳምጡት የነበሩትን ሰዎች ልብ ነክቶ ነበር። ስለዚህ ይሰሙት ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ አማኞች ሆኑ። (1 ተሰሎንቄ 2:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ፕሮግራምህ ምክንያት ከቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሰህ ውጤታማ በሆነ መንገድ እያመራመርክ ማስረዳት ችለሃልን? የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በሕይወትህ ውስጥ የያዘው ቦታና መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበት ዘዴ የአምላክ ቃል በእጅህ መኖሩ ምን ትርጉም እንዳለው በእርግጥ እንደተገነዘብክ ያሳያልን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ፕሮግራማቸው በጣም የተጣበበባቸውም እንኳ ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ሲሉ ሕይወታቸውንና ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ለመጣል ፈቃደኛ የነበሩት ለምንድን ነው?
◻ የጥንት እስራኤላውያን የአምላክን ቃል እንዲሰሙ የተደረገላቸውን ዝግጅቶች በመከለሳችን የተጠቀምነው እንዴት ነው?
◻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብነውን ነገር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
◻ በተለይ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ኢያሱን ‘የሕጉን መጽሐፍ ቀንና ሌሊት አንብበው’ ሲል አዝዞት ነበር