የአንባብያን ጥያቄዎች
የዜና ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት አንዳንድ ሆስፒታሎች አንድ ሕፃን ከተወለደ በኋላ የእንግዴ ልጁንና እትብቱን ወስደው ያስቀምጡና በውስጣቸው ከሚገኘው ደም አንዳንድ ነገሮችን ያወጣሉ። ይህ አንድን ክርስቲያን ሊያሳስበው ይገባልን?
በአብዛኞቹ ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ስለሌለ ጉዳዩ ክርስቲያኖችን ሊያሳስባቸው አይገባም። አንዲት ክርስቲያን በምትወልድበት ሆስፒታል እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደሚፈጸም ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ካላት ግን እንግዴ ልጁና እትብቱ መወገድ እንጂ በማንኛውም መልኩ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለባቸው ለዶክተሩ መግለጹ ተገቢ ይሆናል።
ሕይወት ካላቸው ነገሮች ማለትም ከእንስሳትም ሆነ ከሰዎች መድኃኒትነት ያላቸው ልዩ ልዩ ተዋጽኦዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ከእርጉዝ ፈረሶች ሽንት አንዳንድ ሆርሞኖች ይወጣሉ። የፈረስ ደም የመንጋጋ ቆልፍ መከላከያ መድኃኒት ምንጭ የነበረ ሲሆን በሽታን ለመከላከል የሚያገለግለው ጋማ ግሎብሊን የተባለው መድኃኒት ደግሞ ለረጅም ጊዜያት (ከወሊድ በኋላ) ከሰው እንግዴ ልጅ ከሚወሰደው ደም ሲመረት ቆይቷል። አንዳንድ ሆስፒታሎች እንግዴ ልጁን አስቀርተው በማቀዝቀዣ ውስጥ ካስቀመጡት በኋላ እንግዴ ልጁን መድኃኒት ወደሚቀመምበት ቤተ ሙከራ ይልኩና ብዙ የፀረ ባዕድ አካል (የአንቲቦዲ) ክምችት ካለው ከዚህ ደም በቤተ ሙከራ ውስጥ ጋማ ግሎብሊንን የማጣራት ሂደት ያካሂዳሉ።
በቅርቡ ተመራማሪዎች ከእንግዴ ልጅ የሚገኘውን ደም ተጠቅመው አንዱን ዓይነት ሉኪሚያ (የደም ካንሰር) በማከም የተሳካ ውጤት እንዳገኙ ተናግረዋል። ይህ ከእንግዴ ልጅ የሚገኝ ደም የሰውነት መድን መቃወስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለማከም ሊረዳ ወይም በአጥንት ውስጥ ያለውን መቅኔ በመቀየር የሚደረገውን ሕክምና ሊተካ ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል። በዚህ ምክንያት ወላጆች ከእንግዴ ልጅ የሚወሰደው ደም ወደፊት ልጃቸውን ለማከም የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ለመጠቀም እንዲቻል ረግቶ በጥንቃቄ እንዲቀመጥላቸው እንዳደረጉ አልፎ አልፎ በመገናኛ ብዙሃን ሲነገር ይሰማል።
እንዲህ ያለው በእንግዴ ልጅ ደም የሚካሄድ ንግድ ፍጹም በሆነው በአምላክ ሕግ ለሚመሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ፈተና አይሆንባቸውም። ፈጣሪያችን ደምን እንደ ቅዱስና አምላክ የሰጠውን ሕይወት እንደሚወክል ነገር አድርጎ ይመለከተዋል። ደምን ሰዎች እንዲጠቀሙበት የፈቀደው በመሠዊያ ላይ መሥዋዕቶች በማቅረብ ብቻ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:10-12፤ ከሮሜ 3:25፤ 5:8 እና ኤፌሶን 1:7 ጋር አወዳድር።) ከዚህ በተረፈ ከአንድ ፍጥረት የሚወጣ ደም መሬት ላይ መፍሰስ በሌላ አባባል መወገድ ይኖርበታል።— ዘሌዋውያን 17:13፤ ዘዳግም 12:15, 16
ክርስቲያኖች አንድን እንስሳ አድነው ሲበሉ ወይም ዶሮ ወይም አሳማ ሲያርዱ ደሙ በደንብ እንዲፈስ በማድረግ ያስወግዱታል። ዋናው ተፈላጊ ነገር ደሙን ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ ማስወገድ ስለሆነ ደሙን ቃል በቃል መሬት ላይ ማፍሰስ አያስፈልጋቸውም።
ሆስፒታል የገቡ ክርስቲያኖች ከሰውነታቸው የሚወጡ ቆሻሻዎችም ይሁኑ በበሽታ ከተለከፈው የአካል ክፍላቸው ተቆርጦ የሚወሰድ ነገር ወይም ከአካላቸው የሚወጣ ደም በመጨረሻ ይወገዳል ብለው ያስባሉ። አንድ ዶክተር በመጀመሪያ የሽንት ምርመራ፣ ዕጢ ካለበት የአካል ክፍል በጥቂቱ ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ ወይም የደም ምርመራ የመሳሰሉ ምርመራዎች እንዲደረጉ ይፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ በአገሩ ሕግ መሠረት እነዚህ ነገሮች ይጣላሉ። እነዚህን ነገሮች ማስወገድ ምክንያታዊና በሕክምና ረገድ ለጥንቃቄ ሲባል የሚደረግ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የሆስፒታሉ ታካሚ ስለዚህ ጉዳይ ልዩ ጥያቄ ማቅረብ አያስፈልገውም። ታካሚው እንዲህ ዓይነቱ ልማድ አይሠራበት ይሆናል ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ካለው እሱ ወይም እሷ እነዚህ ነገሮች እንዲወገዱ የሚፈልጉባቸውን ሃይማኖታዊ ምክንያቶቹን በመጥቀስ ለሚመለከተው ሐኪም ሁኔታውን መግለጽ ይችላሉ።
ሆኖም ከላይ እንደተገለጸው በብዙ ቦታዎች እንዲህ ዓይነቱ እንግዴ ልጅን ወይም ሌሎች ከሰውነት የሚወጡ ነገሮችን እንደገና መጠቀም ጭራሽኑ የማይታሰብ ወይም ደግሞ ያልተለመደ በመሆኑ ለአብዛኞቹ ታካሚዎች እምብዛም አሳሳቢ አይደለም።
በጥር 1, 1997 “መጠበቂያ ግንብ” ላይ “መጥፎ የሆነውን ነገር እንጸየፍ” በሚል ርዕስ የወጣው ትምህርት በሕፃናት ላይ በሚሰነዘረው የጾታ ጥቃት ላይ ልዩ ትኩረት የሚያደርግ ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህ ድርጊት ምንድን ነው?
ዌብስተር ናይንዝ ኒው ኮልጂየት ዲክሽነሪ ሕፃናትን በጾታ ማስነወርን (“pedophilia”) “በሕፃናት ላይ የሚደረግ የጾታ ብልግና” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። የዚህ ድርጊት አንዳንድ ገጽታዎች በዘዳግም 23:17, 18 ላይ ተወግዘዋል። እዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ በቤተ መቅደስ ውስጥ የግልሙትና ተግባር መፈጸምን (“ወይም የጾታ ብልግና የሚፈጸምበት ልጅ መኖሩን፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) አውግዟል። በተጨማሪም በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “የውሻ” (“በተለይ ከወንድ ልጅ ጋር በፊንጢጣ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት የሚፈጽም ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ዋጋ “ወደ እግዚአብሔር ቤት” እንዳይገባ ተከልክሏል። እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑና ሃይማኖታዊ ካልሆኑ ምንጮች የተገኙ ማስረጃዎች መጠበቂያ ግንቡ መዳራትን ጨምሮ አንድ አዋቂ ሰው በአንድ ልጅ ላይ የሚፈጽመውን የጾታ ማስነወር ድርጊት ለመግለጽ እንደፈለገ ልንረዳ እንችላለን።