ምዕራፍ አሥር
“ተብሎ ተጽፏል”
1-3. ኢየሱስ የናዝሬት ሰዎች ምን መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ፈልጎ ነበር? ምን ማስረጃስ አቀረበ?
ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደጀመረ አካባቢ ነው። ወዳደገባት ወደ ናዝሬት ተመልሶ መጥቷል። ዓላማው የከተማው ሕዝብ አንድ ወሳኝ እውነታ እንዲገነዘብ መርዳት ነው፤ ይኸውም ከረጅም ጊዜ በፊት በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እሱ መሆኑን ማሳወቅ! ታዲያ ኢየሱስ ምን ማስረጃ ያቀርብላቸው ይሆን?
2 ብዙዎች ተአምር እናያለን ብለው ሳይጠብቁ አልቀሩም። ኢየሱስ ስላከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ሲወራ ሰምተዋል። ኢየሱስ ግን ምንም ተአምር አላሳያቸውም። ከዚህ ይልቅ እንደ ልማዱ ወደ ምኩራብ ገባ። ሊያነብ ሲነሳም የኢሳይያስ መጽሐፍ ጥቅልል ተሰጠው። ኢየሱስ ረጅሙን ጥቅልል ከአንዱ ዘንግ ወደ ሌላኛው በመጠቅለል የሚፈልገውን ሐሳብ አወጣ። ከዚያም በአሁኑ ጊዜ በኢሳይያስ 61:1-3 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ።—ሉቃስ 4:16-19
3 አድማጮቹ ይህን ሐሳብ እንደሚያውቁት ግልጽ ነው። ጥቅሱ ስለ መሲሑ የሚናገር ትንቢት ይዟል። በምኩራቡ የተገኙት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ትኩር ብለው እየተመለከቱት ነው፤ ምኩራቡ ውስጥ ጸጥታ ሰፍኗል። ኢየሱስ “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” በማለት ተናገረ፤ ከዚያም ዝርዝር ማብራሪያ መስጠቱን የቀጠለ ይመስላል። አድማጮቹ ከአፉ በሚወጡት ማራኪ ቃላት ተደንቀዋል፤ ይሁንና ብዙዎቹ አሁንም ተአምራዊ ምልክት ማየት እንደሚፈልጉ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ግን ተአምር አልፈጸመም፤ እንዲያውም እምነት የለሽ መሆናቸውን የሚያጋልጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ በድፍረት ጠቀሰላቸው። ብዙም ሳይቆይ የናዝሬት ሰዎች ሊገድሉት ተነሱ።—ሉቃስ 4:20-30
4. ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ ምን ሊኮረጅ የሚገባው አካሄድ ተከትሏል? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
4 ኢየሱስ በዚህ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ አገልግሎቱን ሲያከናውን የተከተለው ይህ አካሄድ ሊኮረጅ የሚገባው ነው። ለአገልግሎቱ መሠረት አድርጎ የተጠቀመው በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ነው። እርግጥ ነው፣ የፈጸማቸው ተአምራት የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ እንደሚሠራ በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሰጠው ለቅዱሳን መጻሕፍት ነው። በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ጌታችን ከአምላክ ቃል የጠቀሰው፣ ለአምላክ ቃል ጥብቅና የቆመውና የአምላክን ቃል ያብራራው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ከአምላክ ቃል መጥቀስ
5. ኢየሱስ አድማጮቹ ምን እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር? የተናገረው እውነት መሆኑን ያሳየውስ እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ የሚናገረው መልእክት ምንጭ ማን እንደሆነ ሰዎች እንዲያውቁ ይፈልግ ነበር። “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) በሌላ ጊዜ ደግሞ “በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር [አላደርግም]፤ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ [ነው]” ብሏል። (ዮሐንስ 8:28) በተጨማሪም “የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም፤ ሆኖም ሥራውን እየሠራ ያለው ከእኔ ጋር አንድነት ያለው አብ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:10) ኢየሱስ ከላይ የተናገራቸውን ሐሳቦች እውነተኝነት ያሳየበት አንዱ መንገድ በጽሑፍ ከሰፈረው የአምላክ ቃል በተደጋጋሚ መጥቀስ ነው።
6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ያህል ጠቅሷል? ይህስ የሚያስደንቀው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ትምህርት ከጸሐፍት የሚለየው እንዴት ነው?
6 በጽሑፍ የሰፈረውን የኢየሱስ ንግግር በጥልቀት ስንመረምር፣ ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ አሊያም በተዘዋዋሪ እንደጠቀሰ እንረዳለን። ‘ታዲያ ይህ ምን ያስገርማል? ኢየሱስ ሲያስተምርና ሲሰብክ በቆየበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ከነበሩት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት በሙሉ መጥቀስ አይችልም ነበር?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እውነቱን ለመናገር፣ እንደዚያ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች መካከል በጽሑፍ የሰፈሩት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን አትዘንጋ። (ዮሐንስ 21:25) እንዲያውም በጽሑፍ የሰፈሩትን የኢየሱስ ሐሳቦች አንብበህ ለመጨረስ ከጥቂት ሰዓታት ያለፈ ጊዜ አይወስድብህ ይሆናል። ሆኖም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ እያብራራህ ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥቀስ ብትባልስ? ይህ ቀላል አይሆንም! ደግሞም ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ ጥቅልሎቹን በቅርብ ማግኘት አይችልም ነበር። የታወቀውን የተራራ ስብከቱን ባቀረበበት ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ብዙ ጊዜ ጠቅሷል፤ ሁሉንም የጠቀሰው በአእምሮው ከሚያስታውሰው ነው!
7 ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት መጥቀሱ ለአምላክ ቃል ጥልቅ አክብሮት እንደነበረው ያሳያል። “ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [ተደንቀዋል]”፤ ምክንያቱም የሚያስተምራቸው “እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን” ነበር። (ማርቆስ 1:22) ጸሐፍት በሚያስተምሩበት ጊዜ የቃል ሕግ በመባል የሚታወቀውን ይኸውም ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩ የተማሩ ረቢዎችን ሐሳብ መጥቀስ ይወዱ ነበር። ኢየሱስ ግን የቃል ሕጉንም ሆነ የረቢዎችን ሐሳብ እንደ ማስረጃ አድርጎ ጠቅሶ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ዋና ማስረጃ አድርጎ የሚጠቅሰው የአምላክን ቃል ነበር። ኢየሱስ “ተብሎ ተጽፏል” በማለት በተደጋጋሚ ተናግሯል። ተከታዮቹን በሚያስተምርበትም ሆነ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በሚያርምበት ጊዜ ይህን ወይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አገላለጾችን ደጋግሞ ይጠቀም ነበር።
8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ባጸዳበት ጊዜ የአምላክን ቃል እንደ ባለሥልጣን አድርጎ የጠቀሰው እንዴት ነው? (ለ) በቤተ መቅደሱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ንቀት ያሳዩት በምን መንገድ ነው?
8 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ባጸዳበት ጊዜ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አድርጋችሁታል” ብሏል። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ ኢሳይያስ 56:7፤ ኤርምያስ 7:11) ከዚያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በዚያ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን ፈጽሞ ነበር። በስፍራው የነበሩት ልጆች ባደረገው ነገር ተደንቀው አወደሱት። የሃይማኖት መሪዎቹ በዚህ በጣም በመቆጣት ‘ልጆቹ የሚሉትን ትሰማለህ?’ አሉት። እሱም “አዎ እሰማለሁ። ‘ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” ሲል መለሰላቸው። (ማቴዎስ 21:16፤ መዝሙር 8:2) ልጆቹ ያደረጉትን ነገር የአምላክ ቃል እንደሚደግፈው የሃይማኖት መሪዎቹ እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር።
9 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሃይማኖት መሪዎቹ አንድ ላይ ተሰብስበው ወደ ኢየሱስ በመምጣት “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። (ማቴዎስ 21:23) ኢየሱስ ሥልጣኑን ያገኘው ከየት እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ደጋግሞ ተናግሯል። የሚያስተምረው ከራሱ ያመነጫቸውን አዳዲስ ሐሳቦች አልነበረም። ይልቁንም ያብራራ የነበረው በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በአባቱ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ነው። በመሆኑም እነዚያ ካህናትና ጸሐፍት ከፍተኛ ንቀት እያሳዩ ያሉት ለይሖዋና ለቃሉ ነው። በእርግጥም ኢየሱስ የልባቸውን ክፋት በማጋለጥ እነሱን ማውገዙ ተገቢ ነበር።—ማቴዎስ 21:23-46
10. የአምላክን ቃል በመጠቀም ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ያልነበሩት ምን መርጃ መሣሪያዎች አሉን?
10 እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ እንደ ዋነኛ ማስረጃ የሚጠቅሱት የአምላክን ቃል ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በቅንዓት ለሌሎች በማካፈላቸው ነው። ጽሑፎቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተወሰዱ ጥቅሶች የተሞሉ ናቸው። በአገልግሎታችን ላይም ሰዎችን በምናነጋግርበት ጊዜ ሁሉ ጥቅሶችን አውጥተን ለማንበብ ጥረት እናደርጋለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን እንድናነብለት እንዲሁም የአምላክን ቃል እንድናብራራለትና ጠቀሜታውን እንድናስረዳው ፈቃደኛ ሲሆን እጅግ እንደሰታለን! እውነት ነው፣ እንደ ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ የለንም፤ ያም ሆኖ ኢየሱስ ያልነበሩት በርካታ መሣሪያዎች አሉን። ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝባቸው ቋንቋዎች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ በተጨማሪም የምንፈልገውን ማንኛውንም ጥቅስ ለማግኘት የሚያስችሉን መርጃ መሣሪያዎች አሉን። በመሆኑም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመጥቀስና ለማንበብ እንጣር!
ለአምላክ ቃል ጥብቅና መቆም
11. ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜ ለአምላክ ቃል ጥብቅና መቆም ያስፈለገው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ በአምላክ ቃል ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥቃት ሲሰነዘር ተመልክቷል፤ ሆኖም ይህ አላስገረመውም። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) እንዲሁም “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን “ውሸታምና የውሸት አባት” መሆኑን በሚገባ ያውቃል። (ዮሐንስ 8:44፤ 14:30) ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ፈተና ምላሽ ሲሰጥ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሦስት ጊዜ ጠቅሷል። ሰይጣን ከመዝሙር መጽሐፍ ላይ አንድ ጥቅስ በመጥቀስ ከአውዱ በወጣ መንገድ ሊጠቀምበት ሞክሮ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ጥቅሱ የተጠቀሰበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን የሚያሳይ ምላሽ በመስጠት ለአምላክ ቃል ጥብቅና ቆሟል።—ማቴዎስ 4:6, 7
12-14. (ሀ) የሃይማኖት መሪዎቹ ለሙሴ ሕግ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳዩት በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ ለአምላክ ቃል ጥብቅና የቆመው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍት ያለቦታቸው ሲጠቀሱ፣ የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጣቸውና ከአውዱ በራቀ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውሉ ለአምላክ ቃል ጥብቅና ይቆም ነበር። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት አስተማሪዎች የአምላክን ቃል በተሳሳተ መንገድ ይጠቀሙ ነበር። በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዝርዝር ነገሮች ለመጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፤ ሆኖም ሕጉ የተመሠረተባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አይሰማቸውም። በመሆኑም እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ለመሳሰሉ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለታይታ የሚደረግ የአምልኮ ሥርዓትን ያበረታቱ ነበር። (ማቴዎስ 23:23) ኢየሱስ ለአምላክ ሕግ ጥብቅና የቆመው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ከሙሴ ሕግ በሚጠቅስበት ጊዜ “እንደተባለ ሰምታችኋል” የሚለውን አገላለጽ በተደጋጋሚ ተጠቅሟል። ከዚያም “እኔ ግን እላችኋለሁ” በማለት ከሕጉ በስተ ጀርባ ያለውን አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት ያብራራ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ይህን ሲያደርግ ሕጉን እየተቃወመ ነበር? በፍጹም! እንዲያውም ለሕጉ ጥብቅና መቆሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ “አትግደል” የሚለውን ሕግ ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰውን መጥላት በራሱ ከዚህ ሕግ መንፈስ ጋር እንደሚጋጭ ነገራቸው። በተመሳሳይም የትዳር ጓደኛው ላልሆነ ሰው የፍትወት ስሜት ያለው ሰው ምንዝርን ከሚከለክለው የአምላክ ሕግ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ጥሷል።—ማቴዎስ 5:17, 18, 21, 22, 27-39
14 በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘ባልንጀራህን ውደድ፣ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ።” (ማቴዎስ 5:43, 44) ለመሆኑ “ጠላትህን ጥላ” የሚለው ትእዛዝ ከአምላክ ቃል የተወሰደ ነው? በጭራሽ! የሃይማኖት መሪዎቹ ከራሳቸው አመንጭተው ያስተማሩት ነው። እነዚህ ሰዎች ፍጹም የሆነውን የአምላክ ሕግ በሰብዓዊ አስተሳሰብ በርዘውት ነበር። ኢየሱስ የአምላክ ቃል፣ የሰው ወግ በሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዳይበከል ሲል ለቃሉ በድፍረት ጥብቅና ቆሟል።—ማርቆስ 7:9-13
15. ኢየሱስ፣ የአምላክን ሕግ ከልክ በላይ ጥብቅ እንዲሁም ጨቋኝ ለማስመሰል የተደረጉ ጥረቶችን በመቃወም ለሕጉ ጥብቅና የቆመው እንዴት ነው?
15 የሃይማኖት መሪዎቹ የአምላክን ሕግ በሌላም መንገድ አቃልለዋል፤ ሕጉ ከልክ በላይ ጥብቅ ይባስ ብሎም ጨቋኝ እንዲመስል አድርገዋል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በእርሻ መካከል ሲያልፉ ጥቂት እሸት በመቅጠፋቸው የሰንበትን ሕግ እንደተላለፉ አንዳንድ ፈሪሳውያን ተናግረው ነበር። ኢየሱስ ይህን የተዛባ አመለካከት የሚያርም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ በመጥቀስ ለአምላክ ቃል ጥብቅና ቆሟል። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሲራቡ የቤተ መቅደሱን ገጸ ኅብስት እንደበሉ የሚናገረውን ታሪክ ጠቀሰላቸው፤ ገጸ ኅብስቱ ከቅድስቱ ውጭ ጥቅም ላይ እንደዋለ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተገለጸው እዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያኑ የይሖዋን ምሕረትና ርኅራኄ መረዳት ተስኗቸው እንደነበረ አሳይቷል።—ማርቆስ 2:23-27
16. የሃይማኖት መሪዎቹ ሙሴ ፍቺን በተመለከተ የሰጠውን ትእዛዝ እንዴት ይጠቀሙበት ነበር? ኢየሱስስ ምን ምላሽ ሰጠ?
16 የሃይማኖት መሪዎቹ በአምላክ ሕግ ውስጥ የሚገኙ ትእዛዞችን የሚያለዝቡ ማምለጫ ቀዳዳዎችም ይፈጥሩ ነበር። ለምሳሌ ሕጉ አንድ ሰው በሚስቱ ላይ “ነውር የሆነ ነገር” ካገኘባት ሊፈታት እንደሚችል ይገልጻል፤ ነውር የተባለው ነገር በቤተሰቡ ላይ ውርደት የሚያስከትል ከባድ ችግር እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 24:1) ይሁን እንጂ በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ለመፍቀድ ይህን ሕግ ሰበብ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር፤ ለምሳሌ አንድ ባል ራቱን ስላሳረረችበት ሚስቱን ሊፈታት እንደሚችል ይናገሩ ነበር!a ኢየሱስ፣ እነዚህ ሰዎች ሙሴ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን ይህን ሐሳብ ፍጹም በተሳሳተ መንገድ እንደሚጠቅሱ ገልጿል። ከዚያም ይሖዋ ለጋብቻ መጀመሪያ ያወጣውን መሥፈርት በግልጽ አስቀምጧል፤ ይኸውም አንድ ወንድ ማግባት ያለበት አንዲትን ሴት ብቻ እንደሆነ፣ ለመፋታት የሚያበቃው ብቸኛ ምክንያት ደግሞ የፆታ ብልግና መሆኑን ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:3-12
17. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል ጥብቅና በመቆም ረገድ ኢየሱስን የሚመስሉት እንዴት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮችም ቅዱሳን መጻሕፍትን ከጥቃት የመከላከል ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። የሃይማኖት መሪዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ አድርገው ሲያስተምሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ነው። በተጨማሪም ሃይማኖቶች፣ የሚያስተምሩትን የሐሰት ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ አድርገው ሲናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው። እኛ ግን ንጹሕ ለሆነው የእውነት ቃል ጥብቅና መቆም ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማናል፤ ለምሳሌ አምላክ ሥላሴ አለመሆኑን ስናስረዳ ለአምላክ ቃል ጥብቅና መቆማችን ነው። (ዘዳግም 4:39) ይሁንና ይህን የምናደርገው በፍጹም ገርነትና በጥልቅ አክብሮት ነው።—1 ጴጥሮስ 3:15
የአምላክን ቃል ማብራራት
18, 19. ኢየሱስ የአምላክን ቃል የማብራራት ግሩም ችሎታ እንዳለው የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?
18 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተጻፉበት ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ነበር። ወደ ምድር መጥቶ የአምላክን ቃል ለሌሎች የማብራራት አጋጣሚ በማግኘቱ ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! ለምሳሌ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ከነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር የተገናኘበትን ያንን የማይረሳ ዕለት አስብ። ደቀ መዛሙርቱ መጀመሪያ ላይ ማንነቱን አልለዩትም ነበር፤ ስለሆነም የሚወዱት ጌታቸው በመሞቱ ምን ያህል እንዳዘኑና ግራ እንደተጋቡ ነገሩት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አላቸው? “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ አብራራላቸው።” እነሱስ ምን ተሰማቸው? በኋላ ላይ እርስ በርሳቸው “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ሲገልጥልን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ።—ሉቃስ 24:15-32
19 በኋላም በዚያኑ ዕለት ኢየሱስ ከሐዋርያቱና ከሌሎች ደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገናኘ። በዚህ ጊዜ ምን እንዳደረገላቸው ልብ በል፦ “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:45) ይህ አስደሳች አጋጣሚ ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ለእነሱም ሆነ ያዳምጡት ለነበሩ ሁሉ በተደጋጋሚ ያደረገውን ተመሳሳይ ነገር ሳያስታውሳቸው አልቀረም። ብዙ ጊዜ ኢየሱስ የተለመዱ ጥቅሶችን ከጠቀሰ በኋላ ብትንትን አድርጎ ያብራራላቸዋል፤ በውጤቱም አድማጮቹ ስለ አምላክ ቃል አዲስ ግንዛቤና ጥልቅ ማስተዋል በማግኘታቸው ይደነቁ ነበር።
20, 21. ይሖዋ በሚነደው ቁጥቋጦ አጠገብ ለሙሴ የነገረውን ሐሳብ ኢየሱስ ያብራራው እንዴት ነው?
20 ኢየሱስ በአንድ ወቅት ከሰዱቃውያን ጋር ሲነጋገር እንዲሁ አድርጎ ነበር። ሰዱቃውያን ከአይሁድ ካህናት ጋር ቅርበት ያላቸው የአይሁዳውያን ሃይማኖት መሪዎች ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች በትንሣኤ አያምኑም ነበር። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ አምላክ እንዲህ ሲል ለእናንተ የተናገረውን አላነበባችሁም? ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ብሏል። እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” (ማቴዎስ 22:31, 32) ኢየሱስ የጠቀሰው በሚገባ የሚያውቁትን ጥቅስ ነው፤ ሰዱቃውያን እጅግ የሚያከብሩት ሙሴ የጻፈው ሐሳብ ነው። ማብራሪያው ግን ምን ያህል ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አስተዋልክ?
21 ሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ አጠገብ ከይሖዋ ጋር የተነጋገረው በ1514 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር። (ዘፀአት 3:2, 6) በዚያ ወቅት አብርሃም ከሞተ 329 ዓመታት፣ ይስሐቅ ከሞተ 224 ዓመታት፣ ያዕቆብ ከሞተ ደግሞ 197 ዓመታት አልፈዋል። ሆኖም ይሖዋ በዚህ ጊዜም እንኳ የእነሱ አምላክ “ነኝ” በማለት ተናግሯል። ሰዱቃውያኑ ይሖዋ፣ በሙታን ዓለም ላይ ይገዛል ተብሎ እንደሚታመን የአረማውያን የሙታን አምላክ አለመሆኑን ያውቃሉ። አዎ፣ ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው ይሖዋ “የሕያዋን” አምላክ ነው። ታዲያ ይህ ወደ ምን መደምደሚያ ያደርሳል? ኢየሱስ አሳማኝ የመደምደሚያ ሐሳብ አቀረበ፤ “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው” አለ። (ሉቃስ 20:38) ይሖዋ ገደብ የለሽ የማስታወስ ችሎታ ስላለው የሚወዳቸውን በሞት ያንቀላፉ አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይረሳቸውም። እነሱን ለማስነሳት ያለው ዓላማ የተረጋገጠ ከመሆኑ የተነሳ ሕያው እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። (ሮም 4:16, 17) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ያብራራበት መንገድ በእርግጥ አስደናቂ አይደለም? ‘ሕዝቡ በትምህርቱ መደነቃቸው’ ምንም አያስገርምም!—ማቴዎስ 22:33
22, 23. (ሀ) የአምላክን ቃል በማብራራት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?
22 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እንደ ኢየሱስ የአምላክን ቃል የማብራራት መብት ተሰጥቷቸዋል። በእርግጥ ፍጹም አእምሮ እንደሌለን የታወቀ ነው። ያም ሆኖ ሰዎችን ስናነጋግር በሚገባ የሚያውቁትን ጥቅስ፣ ፈጽሞ ካላስተዋሉት አቅጣጫ ልናብራራላቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች “ስምህ ይቀደስ” እና “መንግሥትህ ትምጣ” የሚሉትን ልመናዎች ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲደግሙ ኖረዋል፤ ሆኖም የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ወይም የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ አያውቁም። (ማቴዎስ 6:9, 10 የ1954 ትርጉም) ሰሚ ጆሮ አግኝተን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ ማብራራት እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!
23 ከአምላክ ቃል መጥቀስ፣ ለቃሉ ጥብቅና መቆምና ቃሉን ማብራራት እውነትን ለሌሎች በማካፈል ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችልባቸው ቁልፍ መንገዶች ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የአድማጮቹን ልብ በሚነካ መንገድ ለማቅረብ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ ውጤታማ ዘዴዎች እንመረምራለን።
a የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ (እሱ ራሱ ከሚስቱ የተፋታ ፈሪሳዊ ነው) “በማንኛውም ምክንያት” መፋታት እንደሚቻል ተናግሯል፤ ደግሞም “ወንዶች ሚስቶቻቸውን ለመፍታት ብዙ ምክንያት” እንደሚያነሱ ጠቁሟል።