በረከት ወይም መርገም—ምርጫ ቀርቦላችኋል!
‘በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን አስቀምጫለሁ፤ . . . በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ። ’—ዘዳግም 30:19
1. ሰዎች ምን ችሎታ ተለግሷቸዋል?
ይሖዋ አምላክ የማሰብ ችሎታ ያለንን ሰብዓዊ ፍጥረቶቹን የሠራን ነፃ የሥነ ምግባር ምርጫ እንዲኖረን አድርጎ ነው። እኛ የተፈጠርነው በደመ ነፍስ እንድንቀሳቀስ ወይም እንደ ሮቦቶች ሆነን እንድንሠራ ሳይሆን የመምረጥ መብትና ኃላፊነት ተሰጥቶን ነው። (መዝሙር 100:3) የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን የፈለጉትን አካሄድ ለመምረጥ ነፃነት ነበራቸው፤ በተጨማሪም ለሚያደርጉት ነገር በአምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች ነበሩ።
2. አዳም ምን ምርጫ አደረገ? ያደረገውስ ምርጫ ምን ውጤት አስከተለበት?
2 ፈጣሪ በምድራዊ ገነት ውስጥ ለሰብዓዊ ሕይወት የሚሆን ዘላለማዊ በረከት አትረፍርፎ ሰጥቶ ነበር። ይህ ዓላማ እስካሁን ድረስ ከዳር ሳይደርስ የቀረው ለምንድን ነው? አዳም መጥፎ ምርጫ በመምረጡ ምክንያት ነው። ይሖዋ “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” በማለት ሰውዬውን አዞት ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳም ለመታዘዝ መርጦ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ይባረኩ ነበር። አለመታዘዝ ሞት አመጣ። (ዘፍጥረት 3:6, 18, 19) ስለሆነም ኃጢአትና ሞት ለአዳም ዘሮች በሙሉ ተላለፈ።—ሮሜ 5:12
በረከት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
3. አምላክ ለሰው ዘር ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም ዋስትና የሰጠው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን ለመባረክ ያለው ዓላማ ከጊዜ በኋላ የሚፈጸምበትን ዝግጅት አደረገ። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” በማለት እርሱ ራሱ ስለ አንድ ዘር በዔደን ውስጥ ትንቢት ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:15) ከጊዜ በኋላ ለታዛዥ ሰዎች በረከት የሚመጣው በዚህ የአብርሃም ተወላጅ በሆነ ዘር አማካኝነት መሆኑን አምላክ ተስፋ ሰጠ።—ዘፍጥረት 22:15-18
4. ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመባረክ ያደረገው ዝግጅት ምንድን ነው?
4 ይህ ተስፋ የተሰጠበት በረከት የሚያመጣ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተገኘ። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ የሰው ልጆችን ለመባረክ ይሖዋ ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ኢየሱስ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ሲጽፍ “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ብሏል። (ሮሜ 5:8) ከኃጢአተኛው የሰው ዘር መካከል አምላክን የሚታዘዙትና የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ካለው ዋጋ ተጠቃሚ ለመሆን ራሳቸውን የሚያቀርቡ ሁሉ በረከቶችን ያገኛሉ። (ሥራ 4:12) ታዛዥነትንና በረከትን ትመርጣለህን? አለመታዘዝ ከዚህ በጣም የተለየ ነገር ያመጣል።
ስለ መርገም ምን ለማለት ይቻላል?
5. “መርገም” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
5 የበረከት ተቃራኒ መርገም ነው። “መርገም” ማለት በአንድ ሰው ላይ ክፉ ነገር መናገር ወይም መጥፎ ነገር እንዲደርስበት መፈለግን መግለጽ ማለት ነው። ቀላላህ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘው ቀላል ከተባለው የዕብራይስጥ ግሥ ሲሆን ይህ ግሥ ቃል በቃል ሲተረጎም “ቀላል መሆን” የሚል ፍቺ አለው። ሆኖም በምሳሌያዊ መንገድ ሲሠራበት ‘ክፉ ነገር እንዲደርስ መለመን’ ወይም ‘በንቀት ዓይን ማየት’ የሚል ትርጉም አለው።—ዘሌዋውያን 20:9፤ 2 ሳሙኤል 19:43
6. በጥንቷ ቤቴል አቅራቢያ ኤልሳዕ ምን አጋጥሞት ነበር?
6 እርግማንን በተመለከተ ወዲያውኑ እርምጃ የተወሰደበትን አንድ አስደናቂ ሁኔታ ተመልከቱ። ይህ የተከሰተው የአምላክ ነቢይ የነበረው ኤልሳዕ ከኢያሪኮ ወደ ቤቴል በመሄድ ላይ ሳለ ነበር። ታሪኩ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው፦ አንተ መላጣ፣ ውጣ፤ አንተ መላጣ፣ ውጣ፤ ብለው አፌዙበት። ዘወርም ብሎ አያቸው፣ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች መጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።” (2 ነገሥት 2:23, 24) ኤልሳዕ ሲያፌዙበት የነበሩትን ልጆች ምን ብሎ እንደረገማቸው በትክክል አይታወቅም። ሆኖም ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ የሚኖር የአምላክ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን በይሖዋ ስም የተናገረው ነገር ውጤት አስገኝቷል።
7. ኤልሳዕን የሰደቡት ልጆች ምን ደረሰባቸው? ለምን?
7 ልጆቹ ያፌዙበት ዋነኛ ምክንያት ኤልያስ ብቻ ይለብሰው የነበረውን ልብስ ኤልሳዕ በመልበሱና ኤልያስን የሚተካ ነቢይ በመካከላቸው እንዲኖር ባለመፈለጋቸው ነበር። (2 ነገሥት 2:13) ኤልሳዕ የኤልያስ ተተኪ በመሆን ረገድ ለመጣበት ግድድር ምላሽ ለመስጠትና እነዚህ ወጣቶችና የእነርሱ ወላጆች ለይሖዋ ነቢይ ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ ለማድረግ ሲያፌዙበት በነበሩት ባለጌ ልጆች ላይ ክፉ ነገር እንዲደርስ በኤልያስ አምላክ ስም ለመነ። ይሖዋ ሁለት ሴት ድቦች መጥተው ያሾፉበት ከነበሩት መካከል አርባ ሁለቱን ቦጫጭቀው እንዲጥሏቸው በማድረግ ኤልሳዕን እንደ ነቢዩ አድርጎ እንደተቀበለው አሳየ። ይሖዋ ይህን ኃይለኛ እርምጃ የወሰደው በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሐሳብ መገናኛ መሥመር አድርጎ ይጠቀምበት ለነበረው አካል አክብሮት ባለማሳየታቸው ምክንያት ነው።
8. የእስራኤል ሕዝብ ምን ለማድረግ ተስማሙ? ይህን ማድረጋቸውስ ምን በረከቶችን አስገኝቶላቸዋል?
8 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እስራኤላውያን ለአምላክ ዝግጅቶች አክብሮት የማጣት ተመሳሳይ ዝንባሌ አሳይተው ነበር። ነገሩ እንዲህ ነበር፦ በ1513 ከዘአበ ይሖዋ ‘በንስር ክንፍ’ የተሸከማቸው ያህል ከግብፅ ባርነት በማዳን ለእስራኤል ሕዝብ ሞገስ አሳየ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አምላክን ለመታዘዝ ቃል ገቡ። ታዛዥነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ጋር ፈጽሞ እንደማይነጣጠል ልብ በሉ። ይሖዋ “ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ” በማለት በሙሴ አማካኝነት ነግሯቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። (ዘጸአት 19:4, 5, 8፤ 24:3) እስራኤላውያን ይሖዋን እንደሚወዱ ተናገሩ፣ ራሳቸውን ለእርሱ ወሰኑ፣ በተጨማሪም ለቃሉ እንደሚታዘዙ ማሉ። ለይሖዋ መታዘዛቸው ታላላቅ በረከቶች ያስገኝላቸዋል።
9, 10. ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በነበረበት ወቅት እስራኤላውያን ምን አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስከተለባቸው?
9 ስምምነቱን የሚገልጹት መሠረታዊ ሕጎች ‘በእግዚአብሔር ጣት’ በድንጋይ ላይ ከመጻፋቸው በፊት መለኮታዊ መርገም ማምጣት የግድ አስፈላጊ ሆነ። (ዘጸአት 31:18) እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ አስፈላጊ የሆነው ለምን ነበር? እስራኤላውያን አምላክ ያዘዛቸውን በሙሉ ለመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው አልነበረምን? አዎን፣ በቃል በረከቶችን ቢፈልጉም በድርጊቶቻቸው መርገም የሚያመጣ አካሄድ ለመከተል መረጡ።
10 ሙሴ አሥርቱን ቃላት ለመቀበል በሲና ተራራ ላይ ባሳለፋቸው 40 ቀናት ወቅት እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቀደም ሲል የገቡትን ቃል ኪዳን አፈረሱ። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፦ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት።” (ዘጸአት 32:1) ይሖዋ በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ለመምራት ለሚጠቀምበት ሰብዓዊ ወኪል አክብሮት ያልታየበት ሌላው ምሳሌ ይህ ነው። እስራኤላውያን የግብፅን ጣዖት አምልኮ በመኮረጃቸው ከመካከላቸው በአንድ ቀን 3,000 የሚያህሉ ሰዎች በሰይፍ በመገደላቸው መጥፎ ውጤቶችን አጭደዋል።—ዘጸአት 32:2-6, 25-29
የበረከትና የመርገም መግለጫ
11. በረከቶችንና መርገሞችን በተመለከተ ኢያሱ የተከተለው መመሪያ ምን ነበር?
11 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ያደረጉትን የ40 ዓመት ጉዞ ሊያጠናቅቁ በተቃረቡበት ወቅት ሙሴ አምላክን ለመታዘዝ ከመረጡ የሚያገኟቸውን በረከቶች በዝርዝር ገለጸላቸው። በተጨማሪም እስራኤላውያን ይሖዋን ላለመታዘዝ ከመረጡ የሚደርስባቸውን መርገሞች አንድ በአንድ ነገራቸው። (ዘዳግም 27:11 እስከ 28:10) እስራኤላውያን ወዲያው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደገቡ ኢያሱ እነዚህን በረከቶችና መርገሞች በሚመለከት ሙሴ የሰጠውን መመሪያዎች ፈጸመ። ስድስት የእስራኤል ነገዶች በጌባል ተራራ ግርጌ ሲቆሙ ሌሎቹ ስድስት ነገዶች ደግሞ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ያዙ። ሌዋውያን በመካከላቸው በሚገኘው ሸለቆ ቆሙ። በጌባል ተራራ ፊት ለፊት የቆሙት ነገዶች እርግማኖቹ በቀጥታ ለእነርሱ ሲነበቡላቸው “አሜን!” ሳይሉ አልቀረም። ሌዋውያን ፊታቸውን ወደ እነርሱ አዙረው በረከቶቹን ሲያነቡ ሌሎቹ በገሪዛን ተራራ ግርጌ ሆነው ምላሽ ሰጡ።—ኢያሱ 8:30-35
12. ሌዋውያን ከተናገሯቸው መርገሞች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
12 ሌዋውያን እንዲህ በማለት ሲናገሩ እየሰማችሁ እንዳለ አድርጋችሁ አስቡ፦ “በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፣ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን። . . . አባትና እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን። . . . የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን። . . . ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን። . . . በመጻተኛ በድሀ አደጉም በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን። . . . ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ልብስ ገልጦአልና ርጉም ይሁን። . . . ከማናቸይቱም እንስሳ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን። . . . ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን። . . . ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን። . . . ባልንጀራውን በስውር የሚመታ ርጉም ይሁን። . . . የንጹሕን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን። . . . የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማይጸና ርጉም ይሁን።” ከእያንዳንዱ መርገም በኋላ በጌባል ተራራ ፊት ለፊት የቆሙት ነገዶች “አሜን” ይላሉ።—ዘዳግም 27:15-26
13. ሌዋውያን የተናገሯቸውን አንዳንድ በረከቶች በራስህ አባባል የምትገልጻቸው እንዴት ነው?
13 አሁን ደግሞ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት የቆሙት ነገዶች ሌዋውያን እያንዳንዱን በረከት ሲያነቡላቸው ከፍ ባለ ድምፅ መልስ ሲሰጡ እየሰማህ እንዳለህ አድርገህ አስብ፤ እንዲህ አሉ፦ “አንተ በከተማ ብሩክ ትሆናለህ፣ በእርሻም ብሩክ ትሆናለህ። የሆድህ ፍሬ፣ የምድርህም ፍሬ፣ የከብትህም ፍሬ፣ የላምህም ርቢ፣ የበግህም ርቢ ብሩክ ይሆናል። እንቅብህና ቡሃቃህ ብሩክ ይሆናል። አንተም በመግባትህ ብሩክ ትሆናለህ፣ በመውጣትህም ብሩክ ትሆናለህ።”—ዘዳግም 28:3-6
14. እስራኤላውያን በረከት ማግኘት ይችሉ የነበሩት ምን ቢያደርጉ ነበር?
14 እነዚህን በረከቶች ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፣ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል።” (ዘዳግም 28:1, 2) አዎን፣ መለኮታዊ በረከትን ለማግኘት ቁልፉ ለአምላክ መታዘዝ ነበር። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ስለምንገኘው ምን ለማለት ይቻላል? እያንዳንዳችን በረከትንና ሕይወትን መርጠን ‘የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዛችንን’ እንቀጥል ይሆን?—ዘዳግም 30:19, 20
ጉዳዩን አንድ በአንድ መመርመር
15. በዘዳግም 28:3 ላይ በሚገኘው በረከት ላይ የተገለጸው ነጥብ ምንድን ነው? እኛስ ከእርሱ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
15 አንድ እስራኤላዊ ለይሖዋ ታዛዥ ሲሆን ሊያገኛቸው የሚችላቸውን አንዳንድ በረከቶች እስቲ እንመልከት። ለምሳሌ ያህል ዘዳግም 28:3 “አንተ በከተማ ብሩክ ትሆናለህ፣ በእርሻም ብሩክ ትሆናለህ” ይላል። በአምላክ መባረክ በቦታ ወይም በተሰጠን ሥራ ላይ የተመካ አይደለም። ምናልባት አንዳንዶች ቁሳዊ ነገር እንደልብ በማይገኝበት አካባቢ ወይም በጦርነት በሚታመስ አገር ስለሚኖሩ አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንደወደቁ ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሌላ ቦታ ሄደው ይሖዋን ማገልገል ይናፍቁ ይሆናል። አንዳንድ ክርስቲያን ወንዶች የጉባኤ አገልጋዮች ወይም ሽማግሌዎች ሆነው ስላልተሾሙ ተስፋ ቆርጠው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን ሴቶች አቅኚዎች ወይም ሚስዮናውያን ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሠማራት የሚያስችል ሁኔታ ስለሌላቸው ቅስማቸው ይሰበራል። ሆኖም ‘የይሖዋን ቃል የሚያዳምጥና እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በጥንቃቄ የሚፈጽም’ ማንኛውም ግለሰብ አሁንም ሆነ ለዘላለም የተባረከ ነው።
16. በዘዳግም 28:4 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
16 ዘዳግም 28:4 “የሆድህ ፍሬ፣ የምድርህም ፍሬ፣ የከብትህም ፍሬ፣ የላምህም ርቢ፣ የበግህም ርቢ ብሩክ ይሆናል” ይላል። እዚህ ላይ ‘አንተ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ነጠላ ተውላጠ ስም መግባቱ ይህ እያንዳንዱ ታዛዥ የሆነ እስራኤላዊ በግሉ የሚያጋጥመው ነገር እንደሆነ ያሳያል። በዛሬው ጊዜ ስላሉት ታዛዥ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ለማለት ይቻላል? በይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ውስጥ በመላው ዓለም የሚታየው ጭማሪና መስፋፋት አምላክ ከ5,000,000 በላይ የሆኑት የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች ያደረጓቸውን ልባዊ ጥረቶች በመባረኩ የተገኘ ነው። (ማርቆስ 13:10) በተጨማሪም በ1995 በተከበረው የጌታ እራት በዓል ላይ ከ13,000,000 በላይ የሆኑ ሰዎች መገኘታቸው ተጨማሪ እድገት ሊገኝ እንደሚችል ያሳያል። አንተስ የመንግሥቱን በረከቶች በማግኘት ላይ ነህን?
የእስራኤል ምርጫ ለውጥ አምጥቷል
17. በረከቶችን ማግኘት ወይም መርገሞችን መቀበል የተመካው በምን ላይ ነው?
17 ታዛዥ የሆነውን እስራኤላዊ በረከቶች ይከተሉት ነበር። “እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል” የሚል ተስፋ ተሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 28:2) በተመሳሳይም መርገሞቹን በተመለከተ “እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል” ተብሎ ነበር። (ዘዳግም 28:15) በጥንት ዘመን የነበርክ እስራኤላዊ ብትሆን ኖሮ በረከቶቹ ‘ይመጡልህ’ ነበር ወይስ መርገሞቹ ‘ይመጡብህ’ ነበር? ይህ የተመካው አምላክን በመታዘዝህ ወይም ባለመታዘዝህ ላይ ነው።
18. እስራኤላውያን መርገሞች እንዳይደርሱባቸው መከላከል ይችሉ የነበሩት እንዴት ነው?
18 በዘዳግም 28:15-68 ላይ አለመታዘዝ የሚያመጣቸው አስከፊ ውጤቶች እንደ መርገሞች ሆነው ተዘርዝረዋል። አንዳንዶቹ መርገሞች በዘዳግም 28:3-14 ላይ ከተዘረዘሩት በረከቶች ተቃራኒ ናቸው። የእስራኤል ሕዝብ በሐሰት አምልኮ ይሳተፉ ስለ ነበር ብዙውን ጊዜ ከባድ መርገሞች መጥተውባቸዋል። (ዕዝራ 9:7፤ ኤርምያስ 6:6-8፤ 44:2-6) እንዴት የሚያሳዛን ነው! ትክክለኛ ምርጫ አድርገው መልካምና ክፉውን ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያስቀምጡትን የይሖዋ ጤናማ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ታዝዘው ቢሆን ኖሮ እነዚህ ነገሮች አይደርሱባቸውም ነበር። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የሐሰት ሃይማኖት በመያዝ፣ የጾታ ብልግና በመፈጸም፣ የተከለከሉ አደንዛዥ መድኃኒቶችን አለአግባብ በመጠቀም፣ የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ በመጠጣትና የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራት በመፈጸም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ። በጥንት እስራኤልና ይሁዳ ውስጥ እንደዚህ ያሉትን ምርጫዎች ማድረጉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ከማሳጣቱም በተጨማሪ ከባድ የልብ ሐዘን ያስከትላል።—ኢሳይያስ 65:12-14
19. ይሁዳና እስራኤል ይሖዋን ለማገልገል በመረጡበት ወቅት የነበሩባቸውን ሁኔታዎች ግለጹ።
19 እስራኤላውያን የተትረፈረፉ በረከቶችንና ሰላም ያገኙ የነበረው ይሖዋን ሲታዘዙ ብቻ ነበር። ለምሳሌ ያህል የንጉሥ ሰሎሞንን ዘመን በተመለከተ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። . . . በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።” (1 ነገሥት 4:20-25) ሕዝቡ ከአምላክ ጠላቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ባጋጠመው በንጉሥ ዳዊት ዘመን እንኳ የእውነትን አምላክ ለመታዘዝ ሲመርጡ የይሖዋን እርዳታና በረከት አግኝተው ነበር።—2 ሳሙኤል 7:28, 29፤ 8:1-15
20. አምላክ ሰዎችን በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነው?
20 ለአምላክ ትታዘዛለህ ወይስ አትታዘዝም? እስራኤላውያን ምርጫ ነበራቸው። ምንም እንኳ ሁላችንም ከአዳም የኃጢአት ዝንባሌ የወረስን ቢሆንም ነፃ ምርጫ ተሰጥቶናል። ሰይጣን፣ ይህ ክፉ ዓለምና አለፍጽምና ቢያስቸግሩንም ትክክለኛ ምርጫ ልናደርግ እንችላለን። ከዚህም በላይ ፈጣሪያችን ምንም እንኳ ብዙ ፈተናዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ጭምር ትክክለኛ ምርጫ የሚያደርጉ ሰዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8-10) አንተ ከእነርሱ መካከል ትሆናለህን?
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በጥንት ምሳሌዎች ተጠቅመን ዝንባሌዎቻችንና ድርጊቶቻችንን በጥንቃቄ ለመመርመር እንችላለን። እያንዳንዳችን ‘በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን አስቀምጫለሁ፤ . . . በሕይወት ትኖር ዘንድ ሕይወትን ምረጥ’ በማለት አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለተናገራቸው ቃላት በአመስጋኝነት ስሜት አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ።—ዘዳግም 30:19
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ ኃጢአተኛ ሰዎች በረከቶች የሚያገኙበትን መንገድ የከፈተላቸው እንዴት ነው?
◻ መርገሞች ምንድን ናቸው?
◻ እስራኤላውያን ከመርገሞች ይልቅ በረከቶችን ሊያገኙ ይችሉ የነበሩት እንዴት ነው?
◻ እስራኤላውያን አምላክን ሲታዘዙ ምን በረከቶችን ያገኙ ነበር?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን በጌባልና በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ተሰብስበው
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.