መታመኛችን ይሖዋ ሊሆን ይገባል
“እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናል።”—ምሳሌ 3:26
1. ብዙ ሰዎች በአምላክ እንደሚታመኑ ቢናገሩም ሁልጊዜ እንደዚያ እንደማያደርጉ የሚያሳየው ምንድን ነው?
በዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ላይ “በአምላክ እንታመናለን” የሚል መፈክር ተጽፎ እናገኛለን። ይሁን እንጂ በዚህ አገርም ሆነ በሌላ ቦታ በገንዘቡ የሚገበያዩ ሰዎች ሁሉ በአምላክ ይታመናሉ ማለት ነው? ወይስ ይበልጥ የሚታመኑት በራሱ በገንዘቡ ነው? በዚህ አገርም ሆነ በየትኛውም ሌላ አገር ገንዘብ መታመን ሁሉን ቻይ በሆነው አፍቃሪ አምላክ ከመታመን ጋር ምንም አይገናኝም። እርሱ ኃይሉን አላግባብ አይጠቀምም ምንም ስስትም የለበትም። እንዲያውም ስስትን አጥብቆ ያወግዛል።—ኤፌሶን 5:5
2. እውነተኛ ክርስቲያኖች ሀብት ስላለው ኃይል ምን ዓይነት ዝንባሌ አላቸው?
2 እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚታመኑት በአምላክ እንጂ ‘የማታለል ኃይል’ ባለው በሀብት አይደለም። (ማቴዎስ 13:22) ገንዘብ ደስተኛ ማድረግም ሆነ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ያለው አቅም እጅግ ውስን መሆኑን ይገነዘባሉ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ያለው ኃይል ግን እንዲህ አይደለም። (ሶፎንያስ 1:18) እንግዲያውስ “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” የሚለው ማሳሰቢያ ምንኛ ጥበብ የሞላበት ነው!—ዕብራውያን 13:5
3.የዘዳግም 31:6 ጥቅስ ጠቅላላ ይዘት ጳውሎስ ጥቅሱን የጠቀሰበትን ምክንያት ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገው እንዴት ነው?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከላይ ያሉትን ቃላት ሲጽፍ ሙሴ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለእስራኤላውያን የሰጠውን መመሪያ መጥቀሱ ነበር:- “ጽኑ፣ አይዞአችሁ፣ አትፍሩ፣ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፣ አይተውህም።” (ዘዳግም 31:6) ይሖዋ ቁሳዊ ፍላጎቶቻቸውን እንደሚያሟላላቸው መተማመን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ነገር ረገድ ሙሉ ትምክህት እንዲኖራቸው ሙሴ እስራኤላውያንን እያበረታታ እንደነበረ ከጥቅሱ ጠቅላላ ይዘት ለመረዳት ይቻላል። ግን እንዴት?
4. አምላክ ሊታመን የሚችል መሆኑን ለእስራኤላውያን ያረጋገጠው እንዴት ነበር?
4 እስራኤላውያን በምድረ በዳ በተንከራተቱባቸው 40 ዓመታት አምላክ አንድም ሳያጓድል ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አቅርቦላቸዋል። (ዘዳግም 2:7፤ 29:5) አመራርም እንዲያገኙ አድርጓል። ይህን ያደረገበት አንዱ መንገድ ቀን በደመና፣ ሌሊት ደግሞ በእሳት አማካኝነት “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር” በመምራት ነበር። (ዘጸአት 3:8፤ 40:36-38) ተስፋይቱን ምድር ሊወርሱ ሲቃረቡ ይሖዋ የሙሴ ተተኪ እንዲሆን ኢያሱን መረጠ። የምድሪቱ ነዋሪዎች በቀላሉ እጃቸውን እንደማይሰጡ የታወቀ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ለአሥርተ ዓመታት ሲጓዝ ስለነበር አሁን ምንም የሚያስፈራ ነገር አልነበረም። እስራኤላውያን ይሖዋ ሊታመን የሚችል አምላክ መሆኑን እርግጠኛ የሚሆኑባቸው ብዙ ማስረጃዎች ነበሯቸው!
5. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁኔታ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ከነበራቸው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
5 ዛሬም ክርስቲያኖች ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት በዚህ ክፉ ዓለም ምድረ በዳ ውስጥ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ይህን ጎዳና ከጀመሩ ከ40 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። አሁን በአምላክ አዲስ ዓለም ድንበር ላይ ቆመዋል። ሆኖም ወተትና ማር ታፈስ ከነበረችው ከጥንቷ ምድር ይበልጥ ክብራማ ወደሆነውና እንደ ተስፋይቱ ምድር ወደሚመሰለው ስፍራ ማንም እንዳይገባ ለማደናቀፍ ጠላቶች ቆመዋል። እንግዲያውስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” የሚሉት ጳውሎስ በድጋሚ የተናገራቸው የሙሴ ቃላት ምንኛ ተስማሚ ናቸው! ጠንካሮችና ደፋሮች እንዲሁም በእምነት የተሞሉ ሆነው ይሖዋን መታመኛቸው በማድረግ የሚቀጥሉ ሁሉ ያለ ምንም ጥርጥር ሽልማቱን ያገኛሉ።
በእውቀትና በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ትምክህት
6, 7. (ሀ) አብርሃም በይሖዋ ላይ የነበረውን የእርግጠኝነት ስሜት ፈተና ላይ የጣለው ነገር ምን ነበር? (ለ) አብርሃም ይስሐቅን ወደሚሠዋበት ቦታ እየተጓዘ ሳለ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል?
6 የእስራኤላውያን አባት የነበረው አብርሃም በአንድ ወቅት ልጁን ይስሐቅን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ታዝዞ ነበር። (ዘፍጥረት 22:2) ይህ አፍቃሪ አባት ያለማንገራገር ለመታዘዝ እስኪችል ድረስ በይሖዋ ላይ ጠንካራ ትምክህት እንዲኖረው ያስቻለው ምንድን ነው? ዕብራውያን 11:17-19 መልሱን ይሰጠናል:- “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፣ የተስፋንም ቃል የተቀበለው:- በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፣ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው።”
7 አብርሃምና ይስሐቅ መሥዋዕቱ ወደሚቀርብበት ስፍራ ለመድረስ ሦስት ቀን እንደፈጀባቸው ልብ በል። (ዘፍጥረት 22:4) አብርሃም እንዲያደርግ ስለተጠየቀው ነገር የሚያሰላስልበት በቂ ጊዜ ነበረው። ምን ተሰምቶት እንደነበረ መገመት እንችላለን? የይስሐቅ መወለድ ያልተጠበቀ ደስታ ፈጥሮ ነበር። ይህ መለኮታዊ እርዳታ አብርሃምና ቀደም ሲል መካን የነበረችው ሚስቱ ሣራ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ቅርርብ ይበልጥ የሚያጠናክር ነበር። ከዚያ በኋላ ይስሐቅና ዘሮቹ ስለሚኖራቸው የወደፊት ሕይወት ማሰብ እንደጀመሩ የተረጋገጠ ነው። ታዲያ አምላክ ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት ምኞታቸው እውን ሳይሆን መቅረቱ ይሆን?
8. አብርሃም በአምላክ ላይ የነበረው እምነት አምላክ ለይስሐቅ ትንሣኤ እንደሚሰጠው ከማመንም አልፎ የሄደው እንዴት ነበር?
8 በጣም የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ካላቸው ትውውቅ አንጻር እርስ በርስ እንደሚተማመኑ ሁሉ አብርሃምም በይሖዋ ላይ ተመሳሳይ ትምክህት ነበረው። አብርሃም “የእግዚአብሔር ወዳጅ” እንደመሆኑ መጠን “እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።” (ያዕቆብ 2:23) አብርሃም በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት አምላክ ይስሐቅን ትንሣኤ ሊሰጠው እንደሚችል በማመን ብቻ የተወሰነ አልነበረም። አብርሃም ሙሉ በሙሉ ገብቶት ነበር ማለት ባይሆንም ይሖዋ የጠየቀው ነገር ትክክል መሆኑን አምኖ ነበር። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ስላቀረበለት የይሖዋን ጽድቅ የሚጠራጠርበት ምክንያት አልነበረውም። ከዚያም ይስሐቅ ቃል በቃል መሥዋዕት ሆኖ እንዳይሞት ለመከላከል የይሖዋ መልአክ ጣልቃ በገባ ጊዜ የአብርሃም እምነት ይበልጥ ተጠናክሯል።—ዘፍጥረት 22:9-14
9, 10. (ሀ) አብርሃም ቀደም ሲል በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው መቼ ነበር? (ለ) ከአብርሃም ምን ጠቃሚ ትምህርት ልንማር እንችላለን?
9 አብርሃም ከ25 ዓመታት ቀደም ብሎም በይሖዋ ጽድቅ ላይ እንደሚታመን አሳይቶ ነበር። ሰዶምና ገሞራ እንደሚጠፉ አውቆ ስለነበር የወንድሙን ልጅ ሎጥን ጨምሮ በዚያ የሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች ደኅንነት አሳስቦት ነበር። አብርሃም እንደሚከተለው በማለት አምላክን ተማጽኗል:- “ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፣ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፣ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?”—ዘፍጥረት 18:25
10 የዕብራውያን አባት የነበረው አብርሃም ይሖዋ ፈጽሞ ጽድቅ የጎደለው ነገር እንደማያደርግ ተገንዝቦ ነበር። ከጊዜ በኋላ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር [“ታማኝ፣” NW] ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 145:17) ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘የይሖዋን ጽድቅ ሳልጠራጠር እንዲደርስብኝ የሚፈቅደውን ነገር እቀበላለሁን? እሱ እንዲሆን የሚፈቅደው ነገር ሁሉ ለራሴና ለሌሎች ጥቅም እንደሚያመጣ አምናለሁን? ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎን የሚል ምላሽ መስጠት ከቻልን ከአብርሃም በጣም ጠቃሚ ትምህርት አግኝተናል ማለት ነው።
በይሖዋ ምርጫ እንደምንተማመን ማሳየት
11, 12. (ሀ) ለአምላክ አገልጋዮች አስፈላጊ የሆነው የትኛው የእምነት ገጽታ ነው? (ለ) አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል?
11 ይሖዋን መታመኛቸው ያደረጉ ሁሉ ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም በሚጠቀምባቸው ሰዎች ላይም እንደሚተማመኑ ያሳያሉ። ይህም እስራኤላውያን በመጀመሪያ በሙሴና በኋላም እሱን በተካው በኢያሱ እንዲተማመኑ የሚጠይቅባቸው ነበር። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በሐዋርያትና በኢየሩሳሌም ጉባኤ በነበሩት ሽማግሌዎች መተማመን ነበረባቸው። ዛሬ ደግሞ እኛ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ እንዲሰጠን በተሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም ከዚህ ባሪያ የተውጣጡ ሰዎች በሚገኙበት የአስተዳደር አካል መተማመንን ይጠይቅብናል።—ማቴዎስ 24:45
12 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቀዳሚ ሆነው እንዲያገለግሉ በተሾሙት ወንዶች መተማመናችን ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለራሳችን ነው። “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ” ተብሎ ተነግሮናል።—ዕብራውያን 13:17
በይሖዋ ምርጫ ላይ አሉታዊ አመለካከት ከመያዝ ተቆጠቡ
13. ቀዳሚ ሆነው እንዲያገለግሉ በተሾሙት ላይ እንድንታመን የሚያደርጉን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
13 መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቀዳሚ ሆነው በሚያገለግሉት ወንዶች ላይ የምንተማመነው ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ እንዲሆን ይረዳናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ሙሴ ስህተት ሠርቶ ያውቃልን? ሐዋርያት ሁልጊዜ ኢየሱስ እንደሚፈልግባቸው የእሱን ዓይነት ባሕርይ ያሳዩ ነበርን?’ መልሱ የታወቀ ነው። ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመሩ የመረጣቸው ሰዎች ፍጹም ባይሆኑም ታማኝና ለእሱ ያደሩ ናቸው። በተመሳሳይም ዛሬ ሽማግሌዎች ፍጹም ባይሆኑም ‘የአምላክን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ የበላይ ተመልካቾች ሆነው በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ መሆናቸውን’ አምነን ልንቀበል ይገባል። ልንደግፋቸውና ልናከብራቸው ይገባል።—ሥራ 20:28
14. ይሖዋ ከአሮን ወይም ከሚሪያም ይልቅ ሙሴን መሪ እንዲሆን መምረጡ ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
14 አሮን ሙሴን በሦስት ዓመት ይበልጠው የነበረ ቢሆንም እህታቸው ሚሪያም ግን የሁለቱም ታላቅ ነበረች። (ዘጸአት 2:3, 4፤ 7:7) አሮን ደግሞ ከሙሴ ይልቅ አንደበተ ርቱዕ ስለነበር የወንድሙ ቃል አቀባይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሹሞ ነበር። (ዘጸአት 6:29–7:2) ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመምራት የሁሉም ታላቅ የነበረችውን ሚሪያምን ወይም አንደበተ ርቱዕ የነበረውን አሮንን አልመረጠም። የይሖዋ ምርጫ ሙሴ መሆኑ ሁሉንም እውነታዎች እንዲሁም በጊዜው አስፈላጊ የነበሩትን ነገሮች ያገናዘበ ነበር። አሮንና ሚሪያም በአንድ ወቅት ይህን ማስተዋል ስለተሳናቸው እንዲህ ሲሉ አማረው ነበር:- “በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” ነገሩን የቆሰቆሰችው እሷ ሳትሆን ስለማትቀር ሚሪያም የይሖዋን ምርጫ አክብሮት በጎደለው መንገድ በመመልከቷ ተቀጥታለች። እሷም ሆነች አሮን ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” መሆኑን መገንዘብ ነበረባቸው።—ዘኁልቁ 12:1-3, 9-15
15, 16. ካሌብ በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነበር?
15 የተስፋይቱን ምድር ለመሰለል ከተላኩት 12 ሰላዮች ውስጥ አሥሩ ክፉ ወሬ ይዘው መጡ። በከንዓን ምድር ስለሚኖሩ “ረጃጅም ሰዎች” በመናገር በእስራኤላውያን ልብ ውስጥ ፍርሃት አሳደሩ። ከዚህ የተነሣ እስራኤላውያን ‘በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ።’ ይሁን እንጂ በሙሴና በይሖዋ እንደማይታመኑ ያሳዩት ሁሉም ሰላዮች አልነበሩም። እንዲህ እናነባለን:- “ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና:- ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ፣ እንውረሰው አለ።” (ዘኁልቁ 13:2, 25-33፤ 14:2) ኢያሱም የካሌብን የመሰለ ጽኑ አቋም አሳይቷል። እንደሚከተለው ብለው በተናገሩ ጊዜ ይሖዋን መታመኛቸው አድርገው እንደነበር አሳይተዋል:- “እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። . . . የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ . . . እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው።” (ዘኁልቁ 14:6-9) በይሖዋ ላይ በመታመናቸውም ተክሰዋል። በዚያን ጊዜ በሕይወት ከነበረው ጎልማሳ ትውልድ መካከል ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብት ያገኙት ካሌብ፣ ኢያሱና ጥቂት ሌዋውያን ብቻ ነበሩ።
16 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ካሌብ እንዲህ አለ:- “እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ። . . . አሁንም፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፣ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፣ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፣ እነሆ፣ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፣ ዛሬ ጉልበታም ነኝ ጉልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፣ እንዲሁ ዛሬ . . . ጉልበቴ ያው ነው።” (ኢያሱ 14:6-11) ካሌብ የነበረውን አዎንታዊ አመለካከት፣ ታማኝነቱንና አካላዊ ጥንካሬውን ተመልከቱ። ሆኖም ይሖዋ ሙሴን እንዲተካ ካሌብን አልመረጠም። ይህ መብት የተሰጠው ለኢያሱ ነበር። ይሖዋ ላደረገው ምርጫ ምክንያቶች እንደነበሩት ልንተማመን እንችላለን፤ ደግሞም ከሁሉ የተሻለ ምርጫ ነበር።
17. ጴጥሮስ ለኃላፊነት አይበቃም ተብሎ እንዲታሰብ የሚያደርጉ ምን ነገሮች ነበሩ?
17 ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ ክዷል። በተጨማሪም የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ በመቁረጥ የችኮላ እርምጃ ወስዷል። (ማቴዎስ 26:47-55, 69-75፤ ዮሐንስ 18:10, 11) አንዳንዶች ጴጥሮስ ፈሪ፣ ሚዛኑን የሳተና ለልዩ መብቶች የማይበቃ ሰው ነው ይሉ ይሆናል። ይሁንና የመንግሥቱን ቁልፎች በመቀበል ለሦስት ቡድኖች የሰማያዊውን ጥሪ መንገድ የመክፈት መብት የተሰጠው ለማን ነበር? ለጴጥሮስ ነበር።—ሥራ 2:1-41፤ 8:14-17፤ 10:1-48
18. ይሁዳ የጠቀሰውን የትኛውን ስህተት ከመሥራት ለመራቅ እንፈልጋለን?
18 ውጫዊ ገጽታዎችን ተመልክቶ ፍርድ በመስጠት በኩል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን እነዚህ ምሳሌዎች ያሳያሉ። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ እርሱ በሚያደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ጥርጣሬ አይገባንም። በምድር ያቋቋመው ጉባኤ የተዋቀረው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ቢሆንም ይሖዋ በእነዚህ ሰዎች በእጅጉ እየተጠቀመ ነው። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ስህተት አንፈጽምም አይሉም። የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ‘ጌትነትን የሚንቁና ሥልጣን ያላቸውን የሚሳደቡ’ ግለሰቦችን አስጠንቅቋል። (ይሁዳ 8-10) ፈጽሞ እንደ እነሱ ልንሆን አይገባም።
19. በይሖዋ ምርጫ ላይ አሉታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚያበቃን ምንም ምክንያት የሌለን ለምንድን ነው?
19 ይሖዋ በተወሰነ ወቅት ላይ ሕዝቦቹን እሱ በሚፈልገው መንገድ በመምራት ረገድ በጊዜው ተፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ያላቸውን ግለሰቦች እንደሚመርጥ የታወቀ ነው። አምላክ አገልጋዮችን በሚመርጥበት ጊዜ አሉታዊ አመለካከት ከመሰንዘር ይልቅ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ባስቀመጠን በየትኛውም ቦታ ትሑት ሆነን በማገልገል ራሳችንን ዝቅ አድርገን በፈቃደኝነት በማቅረብ ይህንን ሃቅ ለመቀበል ጥረት ማድረግ ይገባናል። በዚህ መንገድ ይሖዋን መታመኛችን እንዳደረግነው እናሳያለን።—ኤፌሶን 4:11-16፤ ፊልጵስዩስ 2:3
በይሖዋ ጽድቅ እንደምንታመን ማሳየት
20, 21. አምላክ ከሙሴ ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን?
20 አንዳንድ ጊዜ በይሖዋ ላይ ከመታመን ይልቅ በራሳችን ላይ ከመጠን በላይ የመታመን ዝንባሌ ካደረብን ከሙሴ እንማር። አርባ ዓመት ሲሞላው እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ ለማውጣት በግሉ መንቀሳቀስ ጀመረ። ከቅን ልቦና ተነሳስቶ ይህን እንዳደረገ አያጠራጥርም፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች እስራኤላውያንን ለመታደግም ሆነ የራሱን ሁኔታ ለማሻሻል አላስቻሉትም። እንዲያውም ለመሸሽ ተገዶ ነበር። ቀደም ሲል ለማድረግ ይፈልግ የነበረውን ነገር ለማድረግ ብቃቱን ያገኘው ለ40 ዓመታት ያህል በባዕድ አገር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ ሥልጠና ካገኘ በኋላ ነበር። አሁን ነገሮች የሚከናወኑት በይሖዋ መንገድና ከራሱ የጊዜ ሰሌዳ ጋር ተስማሚ በሆነ ጊዜ ውስጥ ስለሚሆን የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው ሊተማመን ይችላል።—ዘጸአት 2:11–3:10
21 እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘አንዳንድ ጊዜ ከይሖዋና በጉባኤ ውስጥ ከተሾሙ ሽማግሌዎች ቀድሜ በመሄድ ነገሮችን ይበልጥ ለማፋጠን ወይም በራሴ መንገድ ለመሥራት እሞክራለሁን? አንዳንድ መብቶችን ባለማግኘቴ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝን? በእርግጥ ከሙሴ ጠቃሚ ትምህርት አግኝተናል?
22. ሙሴ ትልቅ መብት ቢያጣም ስለ ይሖዋ እንዴት ተሰምቶት ነበር?
22 ከዚህም በላይ ከሙሴ ሌላ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ዘኁልቁ 20:7-13 ሙሴ የፈጸመውን ስህተትና ያስከተለበትን ከፍተኛ ጉዳት ይነግረናል። እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ የማስገባት መብቱን አጣ። ታዲያ በዚህ ምክንያት ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ትክክል አይደለም ብሎ ተከራክሯል? አምላክ እንዴት እንዲህ ያደርግብኛል ብሎ በማኩረፍ ራሱን አግልሏልን? ሙሴ፣ ይሖዋ ጻድቅ ስለመሆኑ የነበረውን የእርግጠኝነት መንፈስ አጥቶ ይሆን? ሙሴ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለእስራኤላውያን ከተናገራቸው ቃላት መልሶቹን ለማግኘት እንችላለን። ሙሴ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሥራው ፍጹም ነው፣ መንገዱም ሁሉ ፍትሕ ያለበት ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ፍትሕ የማያጓድል፣ እርሱ ጻድቅና ቅን ነው።” (ዘዳግም 32:4 NW) በእርግጥም ሙሴ በይሖዋ ላይ የነበረውን የመተማመን መንፈስ እስከ መጨረሻው አጽንቶ ይዟል። እኛስ? በግለሰብ ደረጃ በይሖዋና በጽድቁ ላይ ያለንን የመተማመን መንፈስ ለማጠንከር እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነንን? እንዲህ ልናደርግ የምንችለውስ እንዴት ነው? ቀጥለን እንመልከት።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ እስራኤላውያን በይሖዋ ለመታመን የሚያበቋቸው ምን ምክንያቶች ነበሯቸው?
◻ ይሖዋን መታመኛ ማድረግን በተመለከተ ከአብርሃም ምን ለመማር ይቻላል?
◻ ይሖዋ በመረጣቸው ሰዎች ላይ አሉታዊ አመለካከት ከመያዝ መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ መታመን በጉባኤ ውስጥ ቀዳሚ ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙትን ማክበርን ይጨምራል