“የቀድሞዎቹን ቀኖች አስታውሱ” ለምን?
“የቀድሞዎቹን ቀኖች አስታውሱ።” በ61 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ይህ ምክር በይሁዳ ለሚገኙ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈ ነበር። (ዕብራውያን 10:32 የ1980 ትርጉም) ይህን ምክር ለመስጠት ያነሳሳው ምንድን ነው? የመጀመሪያው መቶ ዘመን የይሖዋ አምላኪዎች ያለፉትን ጊዜያት ማስታወስ አስፈልጓቸው የነበረው ለምንድን ነው? እኛ በዛሬው ጊዜ ይህን የመሰለ ምክር ብንከተል እንጠቀማለንን?
ባለፉት መቶ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስላለፈው ጊዜ ግዴለሽ ወይም ቸልተኛ መሆን ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። የቀድሞዎቹ ዘመናትና ክንውኖች በአእምሮ ውስጥ መቀመጥና መታወስ አለባቸው። እንዲያውም ይሖዋ ራሱ “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም” ብሏል። (ኢሳይያስ 46:9) ይህን ምክር ሰምተን ተግባራዊ የምናደርግበትን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች እስቲ እንመርምር።
ማነቃቂያና ማበረታቻ
አንደኛ፣ ትልቅ የማነቃቂያና የማበረታቻ ምንጭ ሊሆንልን ይችላል። ጳውሎስ ደብዳቤውን ለዕብራውያን ጉባኤ ሲጽፍ ከአይሁዳውያን በሚደርስባቸው ተቃውሞ የተነሳ እምነታቸው በየቀኑ ለሚፈተነው ክርስቲያን ጓደኞቹ መጻፉ ነበር። ጽናትን ማዳበር እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ ብዙ መከራ ተቀብላችሁ የታገሣችሁባቸውን እነዚያን የቀድሞዎቹን ቀኖች አስታውሱ።” (ዕብራውያን 10:32 የ1980 ትርጉም) በመንፈሳዊ ውጊያ ከዚህ ቀደም የወሰዱትን የታማኝነት እርምጃ ማስታወሳቸው የጀመሩትን ሩጫ ለመጨረስ የሚያስፈልገውን ድፍረት ይሰጣቸዋል። ነቢዩ ኢሳይያስም በተመሳሳይ “እናንተ ሰዎች ድፍረት እንድታገኙ ይህን አስቡ” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 46:8 አዓት) ኢየሱስ ክርስቶስ ተመሳሳይ የሆነ መልካም ውጤት በአእምሮው ይዞ ነው “እንግዲህ ከወዴት [ከቀድሞው ፍቅርህ] እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ” ሲል በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ ምክር የሰጠው።—ራእይ 2:4, 5
“የዱሮውን ዘመን አስብ፣ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል” የሚለው ጥብቅ ምክር ሕዝቡ ለይሖዋ ፍርሃት የለሽ ታማኝነት እንዲያሳይ ለማደፋፈር ሙሴ ለእስራኤላውያን ባደረገው ንግግር ላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ሐሳብ ነው። (ዘዳግም 32:7) በዘዳግም 7:18 ላይ የተመዘገቡትን ሙሴ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል፦ “[ከነዓናውያንን] ከቶም አትፍሩአቸው፤ ይልቅስ አምላካችሁ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡ ላይ ያደረገውን ሁሉ አስታውሱ።” (የ1980 ትርጉም) ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሲል የወሰደውን የማዳን እርምጃ መለስ ብሎ ማስታወሱ የይሖዋን ሕግጋት በታማኝነት የሙጥኝ ብለው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ማበረታቻ ይሆንላቸው ነበር።—ዘዳግም 5:15፤ 15:15
የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ የመርሳት ኃጢአት ይፈጽሙ ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ተመለሱ፣ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፣ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱም እጁን አላሰቡም፣ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን።” (መዝሙር 78:41, 42) በመጨረሻም የይሖዋን ትእዛዛት መዘንጋታቸው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል።—ማቴዎስ 21:42, 43
“ያህ ያደረጋቸውን ነገሮች አስታውሳለሁ፤ ከረጅም ጊዜ በፊት ያከናወንካቸውን አስደናቂ ሥራዎች አስታውሳለሁ። ባደረግሃቸው ነገሮች ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ፣ እንዲሁም ድርጊቶችህን አስብባቸዋለሁ” ሲል የጻፈው መዝሙራዊ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። (መዝሙር 77:11, 12 አዓት) ያለፈውን የታማኝነት አገልግሎትና የይሖዋን ፍቅራዊ ተግባራት በማሰላሰል ማስታወስ አስፈላጊውን ማነቃቂያና ማበረታቻ እንድናገኝ እንዲሁም አድናቆታችን እንዲጨምር ያደርጋል። በተጨማሪም ‘የቀድሞዎቹን ቀኖች ማስታወስ’ ድካምን ለማስወገድ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ በታማኝነት ለመጽናት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ሊቀሰቅሰን ይችላል።
ካለፉ ስህተቶች መማር
ሁለተኛ ደግሞ የቀድሞዎቹን ቀኖች አለመርሳት ካለፉ ስህተቶችና ካስከተሉት መዘዝ ትምህርት የሚገኝበት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል። ሙሴ ይህን በአእምሮው ይዞ እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል መከራቸው፦ “አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዳስቆጣኸው፤ ከግብፅ አገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ አስብ፣ አትርሳ።” (ዘዳግም 9:7) እስራኤላውያን ባሳዩት ዓመፀኝነት የተነሳ ‘አምላካቸው ይሖዋ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ እንዳደረጋቸው’ ሙሴ ገልጿል። ይህን እንዲያስታውሱ የተበረታቱት ለምንድን ነው? ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉና ‘በመንገዱ በመሄድና እርሱን በመፍራት የአምላካቸውን የይሖዋን ትእዛዛት ለመጠበቅ’ የዓመፀኝነት መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለማድረግ ነው። (ዘዳግም 8:2-6) ከዚህ በፊት የሠሯቸውን ስህተቶች እንዳይደግሙ አድርገው መማር ነበረባቸው።
አንድ ደራሲ “ብልጥ ሰው በራሱ ላይ ከደረሰው ነገር ይማራል፤ ጥበበኛ የሆነ ሰው ደግሞ በሌሎች ላይ ከደረሰው ነገር ይማራል” ሲሉ ተናግረዋል። ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ ስህተቶቻቸውን በማስታወስ እንዲማሩ የመከረ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ሌሎችን ማለትም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የቆሮንቶስ ጉባኤ እግረመንገዱንም እኛን ጭምር ከዚሁ ታሪክ ትምህርት እንድናገኝ አጥብቆ መክሯል። ጳውሎስ “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:11 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ አንድ ሌላ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክና ከዚህ ታሪክ የመማርን አስፈላጊነት በአእምሮው ይዞ “የሎጥን ሚስት አስቡአት” አለ። (ሉቃስ 17:32፤ ዘፍጥረት 19:1-26) እንግሊዛዊው ባለቅኔና ፈላስፋ ሳሙኤል ቴይለር ኮለሪጅ “ሰዎች ከታሪክ መማር ቢችሉ ኖሮ ምን ያህል አዋቂዎች በሆንን ነበር!” ሲሉ ጽፈዋል።
ትሕትናና አመስጋኝነት
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የቀድሞዎቹን ቀኖች ማስታወስ አምላክ የሚወዳቸው የትሕትናና የአመስጋኝነት ባሕርያት በውስጣችን እንዲያድጉ ያደርጋል። በምንኖርበት ዓለም አቀፋዊ የሆነ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የምንደሰትባቸው ብዙ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ለዚህ መሠረት የሆኑ ነገሮች እንዳሉም ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከአሥርተ ዓመታት በፊት በብዙ አገሮች ውስጥ ሥራውን ለመጀመር መንገድ ጠራጊ ሆነው ያገለገሉት ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሳዩአቸው እንደ ታማኝነት፣ ፍቅር፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ፣ መከራን በልበ ሙሉነት መጋፈጥ፣ ጽናት፣ ትዕግሥትና እምነት የመሳሰሉት ባሕርያት ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የ1995 የዓመት መጽሐፍ በሜክሲኮ የሚገኙትን ዘመናዊ የአምላክ ሕዝቦች ታሪክ በሚመለከት ያቀረበውን ሪፖርት ሲያጠቃልል እንደሚከተለው ብሏል፦ “በቅርብ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ የጀመሩ ሰዎች በሜክሲኮ ሥራው እንዲጀመር በማድረጉ ሥራ የተካፈሉ ወንድሞች አጋጥመዋቸው ስለ ነበሩት ፈተናዎች ሲሰሙ በጣም ሊያስገርማቸው ይችላል። እነሱ ያሉት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ባለበት፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አምላክን የሚፈሩ ወንድሞችና እህቶች ባሉበትና ለአምላክ የሚቀርበው አገልግሎት በሚገባ በተደራጀ ሁኔታ በሚከናወንበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው።”
እነዚህ ግንባር ቀደም ሆነው ሥራውን የጀመሩ ወንድሞች በአብዛኛው ብቻቸውን ወይም ደግሞ ራቅ ብለው ባሉ ገለልተኛ ክልሎች በሚገኙ አነስተኛ ቡድኖች አገልግለዋል። ብቸኝነት፣ የምግብ ዕጦትና ፍጹም አቋምን የሚፈታተኑ ሌሎች ከባድ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። ምንም እንኳን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ቢሆንም ይሖዋ ያከናወኑትን የታማኝነት አገልግሎት እንደሚያስታውስ ማወቅ እንዴት የሚያስደስት ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” ብሎ በመጻፍ ይህን አረጋግጧል። (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ እንዲህ በአድናቆት የሚያስታውስ ከሆነ እኛም በተመሳሳይ በአመስጋኝነት መንፈስ ማስታወስ አይኖርብንምን?
በቅርቡ ወደ እውነት የመጡ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች—የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች (የእንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የቀድሞ ታሪክ ሊያውቁ ይችላሉ።a ከዚህም በተጨማሪ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ በእድሜ የገፉ ወንድሞች ወይም እኅቶች ባሉበት ቤተሰብ አሊያም ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምትገኙ ከሆነ “የዱሮውን ዘመን አስብ፣ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፣ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፣ ይነግሩህማል” የሚለውን የዘዳግም 32:7 መንፈስ እንድታንጸባርቁ እናበረታታችኋለን።
አዎን፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር በማሳየት የተከናወኑ ድርጊቶችን መለስ ብሎ ማስታወስ በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን በደስታ መጽናታችንን እንድንቀጥል ሊያነቃቃን ይችላል። በተጨማሪም ታሪክ ልናውቃቸው የሚገቡ ትምህርቶችን ይዟል። እንዲሁም አምላክ እየባረከው ስላለው መንፈሳዊ ገነታችን ማሰላሰል እንደ ትህትናና አመስጋኝነት ያሉትን ጥሩ ባሕርያት እንድናፈራ ያደርገናል። እውነትም “የቀድሞቹን ቀኖች አስታውሱ።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።