ናዖድ—የእምነትና የድፍረት ሰው
እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተስፋይቱን ምድር ከረገጡ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። ሙሴና ተተኪው ኢያሱ ከሞቱ ቆይተዋል። እንደነሱ ያሉ የእምነት ሰዎች ባለመኖራቸው እስራኤላውያን ለንጹሕ አምልኮ ያላቸው አድናቆት እጅግ ቀንሷል። እንዲያውም እስራኤላውያን በኣልንና የተቀደሱ አምዶቹን ማምለክ ጀምረዋል።a በዚህ ምክንያት ይሖዋ ሕዝቦቹን ለስምንት ዓመታት በሶርያውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ ጮኹ። ልመናቸውን በመስማት ምሕረት አሳያቸው። ይሖዋ ሕዝቡን እንዲያድን ጎቶንያል የተባለ መስፍን አስነሣ።—መሳፍንት 3:7-11
እስራኤላውያን ከእነዚህ ሁኔታዎች አንድ መሠረታዊ እውነት ሊማሩ ይገባ ነበር:- ለይሖዋ መታዘዝ በረከቶችን የሚያመጣ ሲሆን አለመታዘዝ ግን መርገሞችን ያመጣል። (ዘዳግም 11:26-28) ሆኖም የእስራኤል ሕዝቦች ይህን ትምህርት ሳያገኙ ቀሩ። ለ40 ዓመት ያህል ሰላም ከሰፈነ በኋላ እንደገና ንጹሑን አምልኮ ተዉ።— መሳፍንት 3:12
በሞዓብ ተወረረች
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡ በሞዓብ ንጉሥ በዔግሎም እጅ እንዲወድቅ ፈቀደ። መጽሐፍ ቅዱስ ዔግሎምን “እጅግ ወፍራም ሰው” በማለት ይገልጸዋል። ዔግሎም በአሞንና በአማሌቅ እየታገዘ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ቤተ መንግሥቱን ‘ዘንባባ ባለባት’ በኢያሪኮ ከተማ አደረገ። እስራኤል ድል አድርጋ የያዘቻት የመጀመሪያዋ የከነዓናውያን ከተማ ካሞሽ የተባለውን ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎች የአስተዳደር ማዕከል ሆነች!b— መሳፍንት 3:12, 13, 17
ዔግሎም ለቀጣዮቹ 18 ዓመታት እስራኤላውያንን ረግጦ ገዝቷቸዋል፤ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ከባድ ቀረጥ ጭኖባቸው ነበር። ሞዓብ በየጊዜው ግብር እንዲከፈል በማዘዝ የራሱን ኢኮኖሚ ሲያበለጽግ የእስራኤል የተፈጥሮ ሀብት ግን እየተመናመነ ሄዶ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች እፎይታ ለማግኘት ለምን እንደጮኹ ሊገባን ይችላል፤ አሁንም እንደገና ይሖዋ ሰማቸው። ሌላ አዳኝ አስነሣላቸው። በዚህ ጊዜ ያስነሣው ቢንያማዊውን ናዖድን ነበር። የዔግሎምን የጭቆና አገዛዝ ለመገርሰስ ናዖድ በሚቀጥለው ጊዜ ግብር በሚሰበሰብበት ቀን እርምጃ ለመውሰድ አቀደ።— መሳፍንት 3:14, 15
ናዖድ ለሚወስደው የድፍረት እርምጃ ዝግጅት ሲያደርግ አንድ ክንድ ርዝመት ያለው በሁለቱም በኩል ስለታም የሆነ ሰይፍ ሠራ። መሣሪያው አጭር ክንድ ከሆነ 38 ሴንቲ ሜትር ያህል ርዝመት ይኖረዋል። አንዳንዶች ጩቤ ነው ብለው ያምናሉ። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በስለቱና በእጀታው መካከል መግቻ አልነበረውም። ስለዚህ ናዖድ ትንሹን ሰይፍ ከልብሱ ሥር ሊደብቀው ችሏል። ከዚህም በላይ ናዖድ ግራኝ ስለ ነበር ሰይፉን በቀኝ ጭኑ በኩል ሊታጠቅ ይችላል፤ ይህ ደግሞ መሣሪያ የሚያዝበት የተለመደ ቦታ አልነበረም።— መሳፍንት 3:15, 16
ናዖድ ያቀደው ዘዴ አደጋ ሊያስከትልበት ይችል ነበር። ለምሳሌ ያህል የንጉሡ ጠባቂዎች ናዖድ መሣሪያ መያዙን ለማረጋገጥ ፍተሻ ቢያደርጉ ኖሮ ምን ሊሆን ይችል ነበር? ባይፈትሹትም እንኳ ንጉሣቸውን ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ብቻውን ጥለውት እንደማይሄዱ የተረጋገጠ ነው! ይሁን እንጂ ናዖድ ብቻውን አግኝቶት ዔግሎምን ለመግደል ቢችል እንኳን እንዴት ሊያመልጥ ይችላል? የዔግሎም ጠባቂዎች የተፈጸመውን ሁኔታ ከማወቃቸው በፊት ምን ያህል ርቀት ሊሸሽ ይችላል?
ናዖድ እነዚህን በመሳሰሉ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ አስቦባቸው ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ምናልባትም ሊፈጠሩ የሚችሉ ብዙ አደጋዎች እንዳሉ ሳያስብ አልቀረም። ሆኖም ድፍረት በማሳየትና በይሖዋ ላይ እምነት በመጣል እቅዱን ዳር ለማድረስ ተነሣ።
ናዖድ ዔግሎምን አገኘው
በቀጣዩ ዓመት ግብር የሚገበርበት ቀን ደረሰ። ናዖድና ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ገቡ። ብዙም ሳይቆይ በንጉሥ ዔግሎም ፊት ቀረቡ። ሆኖም ናዖድ ጥቃት የሚሰነዝርበት ጊዜ አልደረሰም ነበር። ግብር ካቀረቡ በኋላ ናዖድ ግብሩን የተሸከሙትን ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ነገራቸው።— መሳፍንት 3:17, 18
ናዖድ ዔግሎምን ቶሎ ያልገደለው ለምን ነበር? ፈርቶ ይሆን? በጭራሽ! ናዖድ እቅዱን ለመፈጸም ንጉሡን በግል ማነጋገር ነበረበት። ይህ ደግሞ በመጀመሪያ ጉብኝቱ አላመቸውም ነበር። ከዚህም በላይ ናዖድ ቶሎ የሚያመልጥበትን መንገድ መፈለግ ነበረበት። ግብር ይዞ የመጣው ጠቅላላው ቡድን ለማምለጥ ከሚሞክር ይልቅ አንድ ግለሰብ ለማምለጥ ቢሞክር ይቀል ነበር። ስለዚህ ናዖድ አመቺ አጋጣሚ ጠበቀ። ዔግሎምን ለአጭር ጊዜ ባነጋገረበት ወቅት የቤተ መቅደሱን አቀማመጥ ለማወቅና ለንጉሡ የሚደረግለት ጥበቃ ምን ያህል የጠበቀ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችሎ ነበር።
ናዖድ ‘በጌልገላ በነበሩት ትክል ድንጋዮች’ አጠገብ ሲደርስ ከእሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች አሰናበታቸውና ተመልሶ ወደ ዔግሎም ቤተ መንግሥት ሄደ። ሁለት ኪሎ ሜትር የሚያህለው ይህ የእግር ጉዞ ናዖድ ስለ ተልእኮው እንዲያስብና የይሖዋን በረከት ለማግኘት እንዲጸልይ ጥቂት ጊዜ እንዲያገኝ አስችሎታል።— መሳፍንት 3:19
ናዖድ ተመለሰ
ናዖድ ሲመለስ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ጥሩ አቀባበል የተደረገለት ይመስላል። ምናልባት ቀደም ሲል ያቀረበው ብዙ ግብር ዔግሎምን ሳያስደስተው አይቀርም። ምንም እንኳ የመጀመሪያው ጉብኝት አጭር ቢሆንም ናዖድ በንጉሡ ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለታል። ምንም ይሁን ምን ናዖድ ወደ ዔግሎም ተመልሷል።
“ንጉሥ ሆይ፣ የምሥጢር ነገር አለኝ” አለ ናዖድ። እዚህ ድረስ መምጣቱ ራሱ ይሖዋ እየመራው እንዳለ የሚጠቁም ነበር። ሆኖም አንድ ችግር ነበር። ናዖድ ይዞት የመጣው “የምሥጢር ነገር” በንጉሡ ጠባቂዎች ፊት የሚነገር አልነበረም። ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ከተፈለገ ናዖድ እርዳታ የሚያስፈልገው አሁን ነው። “ዝም በል” ሲል ንጉሡ አዘዘው። ዔግሎም ይህን “የምሥጢር ነገር” እንዳይሰሙት ስለ ፈለገ ጠባቂዎቹን ከክፍሉ አስወጣቸው። ናዖድ ምን ያህል እፎይታ እንደተሰማው ገምት!— መሳፍንት 3:19
ናዖድ ወደ እሱ ቀርቦ ‘የምነግርህ የአምላክ መልእክት አለኝ’ ሲለው ዔግሎም በሰገነቱ ቤት ተቀምጦ ነበር። ናዖድ “አምላክ” ሲል ካሞሽን መጥቀሱ ነበርን? ዔግሎም እንደዚያ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ዔግሎም ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ጓጉቶ ከዙፋኑ ተነሣ። ንጉሡ ጥቃት ይሰነዝርብኛል የሚል ጥርጣሬ እንዳያድርበት ናዖድ በጥንቃቄ እየተራመደ ሳይሆን አይቀርም ወደ እሱ ቀረበ። ከዚያም ፈጠን አለና “ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፣ ሆዱንም ወጋው፤ የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፣ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።”— መሳፍንት 3:20-22
በአቅራቢያው የሚገኙት የንጉሡ ጠባቂዎች ንቅንቅ አላሉም። ሆኖም ናዖድ አሁንም በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው። በሆነ ሰዓት የዔግሎም አገልጋዮች ወደ ክፍሉ ሊገቡና የወደቀውን የንጉሣቸውን ሬሳ ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ናዖድ ፈጥኖ መሸሽ ያስፈልገው ነበር! በሩን ከቆለፈ በኋላ በሰገነቱ ቤት አየር ማስገቢያ በኩል ወጥቶ ሸሸ።— መሳፍንት 3:23, 24
የጉዳዩ መታወቅና ሽንፈታቸው
ወዲያውኑ የዔግሎም አገልጋዮች ነገሩ እንግዳ ሆነባቸው። ሆኖም በግሉ የሚያደርገውን ውይይት አቋርጠው የንጉሡን ቁጣ ለመጋፈጥ አልደፈሩም። ከዚያም የሰገነቱ ቤት በር እንደተቆለፈ ተገነዘቡ። “ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል” ብለው አሰቡ። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ነገሩ እንግዳ ከመሆን ይልቅ አስጊ ሆነባቸው። የዔግሎም ጠባቂዎች ከዚህ በላይ ብዙ መታገሥ አልቻሉም። “መክፈቻውን ወስደው [የሰገነቱን ቤት በር] ከፈቱ፣ እነሆም፣ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት።”— መሳፍንት 3:24, 25
በዚህ መካከል ናዖድ ሸሽቶ አመለጠ። በጌልገላ የሚገኙትን ትክል ድንጋዮች አልፎ በተራራማው የኤፍሬም አገር በሚገኘው ሴይሮታም የተባለ ቦታ ደረሰ። ናዖድ የእስራኤልን ሰዎች አንድ ላይ ከሰበሰበ በኋላ በእሱ መሪነት የተባበረ ክንዳቸውን በሞዓባውያን ላይ አነሡ። ዘገባው “ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፣ ጎልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፣ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም” ይላል። ሞዓብ ከተሸነፈ በኋላ የእስራኤል ምድር ለ80 ዓመታት ያህል ጸጥታ ሰፈነባት።— መሳፍንት 3:26-30
ከናዖድ ምሳሌ መማር
ናዖድን እንዲህ እንዲያደርግ የገፋፋው በአምላክ ላይ የነበረው እምነት ነው። ዕብራውያን ምዕራፍ 11 “በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፣ . . . በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፣ የባዕድ አገር ጭፍሮችን አባረሩ” ሲል እሱን በቀጥታ አይጠቅሰውም። (ዕብራውያን 11:33, 34) ሆኖም ናዖድ በእምነት እርምጃ ሲወስድና እስራኤልን ከንጉሥ ዔግሎም የጭቆና ቀንበር ሲያላቅቅ ይሖዋ ረድቶታል።
ናዖድ ካሳያቸው መልካም ባሕርያት መካከል አንዱ ድፍረት ነበር። በሰይፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ድፍረት ያስፈልገው ነበር። በዚህ ዘመን የምንገኝ የአምላክ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን በእንዲህ ዓይነት ሰይፍ አንጠቀምም። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52) ሆኖም “የመንፈስ ሰይፍ” በሆነው የአምላክ ቃል እንጠቀማለን። (ኤፌሶን 6:17) ናዖድ በሰይፍ አጠቃቀም ረገድ የተካነ ነበር። እኛም ብንሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች በምንሰብክበት ወቅት የአምላክን ቃል በጥሩ ችሎታ መጠቀም ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:14) የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት፣ በአገልግሎት በቅንዓት መሳተፍ እንዲሁም በሰማያዊው አባታችን ላይ በጸሎት መደገፋችን በእርግጥም ደፋርና የእምነት ሰው የነበረው ናዖድ ያሳያቸውን መልካም ባሕርያት ለመኮረጅ እንድንችል ይረዳናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የተቀደሱ አምዶች የተባሉት የወንድ ብልት ምልክቶች ሳይሆኑ አይቀርም። ልቅ ከሆነ ከባድ የጾታ ብልግና ጋር የሚዛመዱ ነበሩ።— 1 ነገሥት 14:22-24
b ካሞሽ የሞዓባውያን ዋነኛ አምላክ ነው። (ዘኁልቁ 21:29፤ ኤርምያስ 48:46) ቢያንስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለዚህ ርኩስ የሆነ የሐሰት አምላክ ሕፃናት መሥዋዕት ሆነው ሳይቀርቡ አይቀርም።— 2 ነገሥት 3:26, 27
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናዖድና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ለንጉሥ ዔግሎም ሲገብሩ
[ምንጭ]
ምንጭ:- Illustrirte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s