ማዳን የይሖዋ ነው
“አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው።”—መዝሙር 68:20
1, 2. (ሀ) ይሖዋ የመዳን ምንጭ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ምሳሌ 21:31ን እንዴት ታብራራለህ?
ይሖዋ የሚወዱትን ሰዎች የሚያድን አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 43:11) ታዋቂው የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት በራሱ የግል ተሞክሮ ይህን አይቷል፤ ስለሆነም “ማዳን የእግዚአብሔር ነው” ሲል ከልቡ ዘምሯል። (መዝሙር 3:8) ነቢዩ ዮናስ በትልቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ባቀረበው ልባዊ ጸሎት ላይ እነዚሁኑ ቃላት ተጠቅሟል።—ዮናስ 2:10
2 የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም ማዳን የይሖዋ መሆኑን ያውቅ ስለነበረ እንዲህ ብሎ ተናግሯል:- “ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል [“ማዳን፣” NW] ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።” (ምሳሌ 21:31) ጥንት በመካከለኛው ምሥራቅ በሬ ለእርሻ፣ አህያ ለጭነት፣ በቅሎ ለኮርቻ፣ ፈረስ ደግሞ ለጦርነት ያገለግሉ ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ወደፊት አምላክ ንጉሣቸው የሚሆነው ሰው ‘ፈረሶችን ማብዛት’ እንደሌለበት አዝዞ ነበር። (ዘዳግም 17:16) ይሖዋ ሕዝቡን ስለሚያድን የጦር ፈረሶች አያስፈልጉም።
3. ልንመረምራቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
3 የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ ይሖዋ “የሚያድን አምላክ” ነው። (መዝሙር 68:20 የ1980 ትርጉም) ይህ እንዴት የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! ሆኖም ይሖዋ ምን ‘የማዳን እርምጃዎች’ ወስዷል? ያዳነውስ እነማንን ነው?
ይሖዋ ቅኖችን ያድናል
4. ይሖዋ የሚያመልኩትን ሰዎች እንደሚያድን እንዴት እናውቃለን?
4 ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች በመሆን ትክክለኛ አካሄድ የሚከተሉ ሁሉ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ማጽናኛ ሊያገኙ ይችላሉ:- “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።” ጴጥሮስ ለዚህ ነጥብ ማስረጃ ሲያቀርብ አምላክ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ [ማውረዱን]” ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 2:5, 9
5. ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ ያገለገለው በምን ሁኔታዎች ሥር ነበር?
5 ራሳችሁን በኖኅ ዘመን በነበረው ሁኔታ ውስጥ እንዳላችሁ አድርጋችሁ አስቡ። ሥጋዊ አካል የለበሱ አጋንንት በምድር ላይ ይገኛሉ። ከዓመፀኞቹ መላእክት የተወለዱት ልጆች ሰዎችን በጭካኔ ያሠቃያሉ፤ ‘ምድርም በግፍ ተሞልታለች።’ (ዘፍጥረት 6:1–12) ይሁን እንጂ ኖኅ በፍርሃት ተውጦ ከይሖዋ አገልግሎት ወደኋላ አላለም። ከዚህ ይልቅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆነ። እሱና ቤተሰቡ በዚያን ጊዜ የነበረው ክፋት በእነሱ የሕይወት ዘመን ተጠራርጎ እንደሚጠፋ እርግጠኞች በመሆን መርከብ ሠርተዋል። የኖኅ እምነት ያንን ዓለም ኮንኗል። (ዕብራውያን 11:7) በጊዜያችን ያሉት ሁኔታዎች በኖኅ ዘመን ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉ ሲሆኑ የዚህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ለይተው የሚያሳውቁ ናቸው። (ማቴዎስ 24:37–39፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ኖኅ ያኔ እንዳደረገው የይሖዋን ማዳን እየተጠባበቃችሁ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመተባበር የታመናችሁ የጽድቅ ሰባኪዎች መሆናችሁን ታረጋግጣላችሁን?
6. ሁለተኛ ጴጥሮስ 2:7, 8 ይሖዋ ቅኖችን እንደሚያድን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ቅኖችን እንደሚያድን ጴጥሮስ ተጨማሪ ማስረጃ ያቀርባል። ሐዋርያው “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ [እንደ] ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ [አምላክ እንዳዳነው]” ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 2:7, 8፤ ዘፍጥረት 19:1–29) በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ለሚኖሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጾታ ብልግና የሕይወታቸው ክፍል እየሆነ መጥቷል። ልክ እንደ ሎጥ በዛሬው ጊዜ በሚገኙ በብዙ ሰዎች ‘ሴሰኛ ኑሮ እጅግ ታዝናለህን?’ የምታዝንና ጽድቅን የምታደርግ ከሆነ ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ ይሖዋ ከሚያድናቸው መካከል ትሆናለህ።
ይሖዋ ሕዝቡን ከጨቋኞች እጅ ያድናል
7. ይሖዋ በግብጽ ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ሕዝቡን ከጭቆና ነፃ እንደሚያወጣ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
7 ይህ ክፉ ሥርዓት እስካለ ድረስ የይሖዋ አገልጋዮች ይሰደዳሉ እንዲሁም በጠላቶቻቸው ይጨቆናሉ። ሆኖም ይሖዋ ጥንት በጭቆና ቀንበር ሥር የነበሩትን ሕዝቦቹን እንዳዳነ ሁሉ እነሱንም ነፃ እንደሚያወጣቸው ሊተማመኑ ይችላሉ። በሙሴ ዘመን በነበሩት ግብጻውያን የጭቆና ቀንበር እየተሰቃየህ ያለህ እስራኤላዊ ነህ እንበል። (ዘጸአት 1:1–14፤ 6:8) አምላክ በግብጻውያን ላይ ተከታታይ መቅሰፍቶችን አወረደ። (ዘጸአት 8:5—10:29) ገዳይ የነበረው አሥረኛው መቅሰፍት የግብጻውያንን የበኩር ልጆች ሕይወት በቀጠፈ ጊዜ ፈርዖን እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው እንዲወጡ ቢፈቅድም በኋላ ላይ ግን ሠራዊቱን በማንቀሳቀስ እስራኤላውያንን ማሳደዱን ተያያዘው። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ እሱና ግብረ አበሮቹ በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ጠፉ። (ዘጸአት 14:23–28) ከሙሴና ከመላው እስራኤል ጋር የሚከተለውን መዝሙር አብረህ ትዘምራለህ:- “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፣ ስሙ እግዚአብሔር ነው፣ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ።” (ዘጸአት 15:3–5) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የአምላክን ሕዝብ የሚጨቁኑ ሁሉ ተመሳሳይ የሆነ ጥፋት ይጠብቃቸዋል።
8, 9. ይሖዋ ሕዝቡን ከጨቋኞች እጅ እንደሚያድን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ከመሳፍንት መጽሐፍ ተናገር።
8 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላም ቢሆን ለብዙ ዓመታት መሳፍንት በመካከላቸው ሆነው ፍትሕ ያስፈጽሙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡ ከባዕድ አገር በሚመጡ ጨቋኞች ይሠቃይ የነበረ ቢሆንም አምላክ እነሱን ለማዳን የታመኑ መሳፍንትን ተጠቅሟል። እኛም በተመሳሳይ ‘በሚጨቁኑንና በሚያንገላቱን ሰዎች ምክንያት እንጮኽ ይሆናል፤’ ሆኖም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዳዳነ ሁሉ እኛንም ያድነናል። (መሳፍንት 2:16–18፤ 3:9, 15) እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱሱ የመሳፍንት መጽሐፍ ስለዚህና አምላክ በሾመው መስፍን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ስለሚወስደው ታላቅ የማዳን እርምጃ ማረጋገጫ ይሰጠናል።
9 እስቲ ወደ መስፍኑ ባርቅ ዘመን መለስ እንበል። እስራኤላውያን በሐሰት አምልኮ በመዘፈቃቸውና መለኮታዊ ተቀባይነት በማጣታቸው ምክንያት በከነዓናዊው ንጉሥ በኢያቢስ አስከፊ ቀንበር ሥር ለ20 ዓመታት ሲሠቃዩ ኖረዋል። ሲሣራ የታላቁ የከነዓናውያን ወታደራዊ ኃይል አለቃ ነበር። ይሁን እንጂ የእስራኤል ብሔር ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጋ ቢሆንም ‘በአርባ ሺህ እስራኤላውያን ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።’ (መሳፍንት 5:6–8) እስራኤላውያን ንስሐ በመግባት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ባርቅ በነቢይቱ ዲቦራ አማካኝነት በአምላክ እየተመራ 10,000 የሚሆኑ ሰዎችን በታቦር ተራራ ላይ አሰባሰበ፤ ይሖዋ ደግሞ በግዙፉ የታቦር ተራራ ግርጌ በሚገኘው ሸለቆ የጠላት ሠራዊት እንዲሰበሰብ አደረገ። የሲሣራ ሠራዊትና 900 የጦር ሰረገሎቹ ሜዳውንና ደረቁን የቂሶንን ወንዝ ዳርቻ አቋርጠው እያስገመገሙ መጡ። ሆኖም ኃይለኛ ዶፍ ዝናብ በመዝነቡ የቂሶን ወንዝ ሞላ። ባርቅና ሰዎቹ ኃይለኛ ዝናቡን ከለላ በማድረግ ከታቦር ተራራ ወረዱ፤ የይሖዋ ቁጣ ያስከተለውን ከፍተኛ ጥፋትም ተመለከቱ። ተደናግጠው በመሸሽ ላይ የነበሩትን ከነዓናውያን የባርቅ ሰዎች አንድ በአንድ ለቅመው ስለገደሏቸው ማንም ያመለጠ አልነበረም። ከአምላክ ጋር ውጊያ ለመግጠም ለሚዳዳቸው ጨቋኞቻችን ይህ እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው!—መሳፍንት 4:3–16፤ 5:19–22
10. አምላክ በዚህ ዘመን የሚገኙ አገልጋዮቹን ከጨቋኞቻቸው እንደሚያድናቸው እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
10 ይሖዋ፣ አምላካዊ ፍርሃት የነበራቸውን እስራኤላውያንን በአደጋ ጊዜ እንዳዳናቸው ሁሉ በዚህ ዘመን የሚገኙትንም አገልጋዮቹን ከሁሉም ጨቋኝ ጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸዋል። (ኢሳይያስ 43:3፤ ኤርምያስ 14:8) አምላክ ዳዊትን “ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ” አድኖታል። (2 ሳሙኤል 22:1–3) ስለዚህ የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን ጭቆና ወይም ስደት ቢደርስብንም መሲሐዊው ንጉሥ ከጭቆና ነፃ ስለሚያወጣን ደፋሮች እንሁን። አዎን፣ “የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል።” (መዝሙር 72:13, 14) ይህ ደኅንነት በቅርቡ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው።
አምላክ በእርሱ የሚታመኑትን ያድናል
11. ወጣቱ ዳዊት በይሖዋ በመታመን ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
11 የይሖዋን ማዳን ለማየት ከፈለግን ደፋሮች በመሆን በእርሱ መታመን ይኖርብናል። ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን ለመግጠም በወጣበት ወቅት ደፋር በመሆን በአምላክ እንደሚታመን አሳይቷል። ዳዊት በዚያ ረዥምና ግዙፍ ሰው ፊት ቆሞ እንዲህ ብሎ ሲናገር በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ:- “አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፣ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና።” ጎልያድ ወዲያውኑ ሞተ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከፍተኛ ሽንፈት ገጠማቸው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ሕዝቡን አድኗል።—1 ሳሙኤል 17:45-54
12. የዳዊትን ኃያል ሰው አልዓዛርን ማስታወሱ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
12 በአሳዳጆቻችን ፊት ስንቆም ‘ደፋሮች መሆንና’ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን ያስፈልገን ይሆናል። (ኢሳይያስ 46:8-13፤ ምሳሌ 3:5, 6) ፈስደሚም በሚባል ቦታ የተከሰተውን ይህን ነገር ልብ በል። እስራኤላውያን የፍልስጥኤም ኃይሎችን በመፍራት ወደ ኋላቸው አፈግፍገው ነበር። ይሁን እንጂ ከሦስቱ የዳዊት ኃያላን መካከል አንዱ የነበረው አልዓዛር ፍርሃት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ አላደረገውም። በአንድ የገብስ ማሳ ውስጥ የያዘውን ቦታ ሳይለቅ ፍልስጥኤማውያንን ለብቻው በሰይፍ መታቸው። በዚህ መንገድ ‘ይሖዋ እስራኤልን በታላቅ ማዳን አዳናቸው።’ (1 ዜና መዋዕል 11:12-14፤ 2 ሳሙኤል 23:9, 10) አንድን ወታደራዊ ኃይል ለብቻችን ወግተን እንድናሸንፍ ማንም አይጠብቅብንም። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ብቻችንን ልንሆንና ከጠላት ተጽእኖ ሊገጥመን ይችላል። አዳኝ በሆነው አምላክ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንተማመናለንን? የእምነት አጋሮቻችንን ለአሳዳጆቻችን አሳልፈን እንዳንሰጥ የእሱን እርዳታ ለማግኘት እንጥራለንን?
ይሖዋ ንጹሕ አቋም ጠባቂዎችን ያድናል
13. በአሥሩ የእስራኤል ነገድ መንግሥት ውስጥ ለአምላክ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?
13 የይሖዋን ማዳን ለማየት ከፈለግን በማንኛውም ሁኔታ ሥር ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አለብን። በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች የተለያዩ መከራዎች ደርሰውባቸዋል። በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ብትኖር ኖሮ ምን ሁኔታዎችን መጋፈጥ ይኖርብህ እንደነበር አስብ። ሮብዓም ይፈጽመው የነበረው ክፋት አሥሩ ነገዶች ከእርሱ እንዲነጠሉና ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ለማቋቋም እንዲነሳሱ አድርጓል። (2 ዜና መዋዕል 10:16, 17፤ 11:13, 14) ለንግሥና ከበቁት ከብዙዎቹ ነገሥታት መካከል ኢዩ ከሁሉ የተሻለ ነበረ፤ ሆኖም እሱም እንኳ ‘በፍጹም ልቡ በይሖዋ ሕግ አልተመላለሰም።’ (2 ነገሥት 10:30, 31) ያም ሆኖ ግን በአሥሩ ነገድ መንግሥትም ውስጥ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ ነበሩ። (1 ነገሥት 19:18) በአምላክ ያምኑ ነበር፤ አምላክም ከእነሱ ጋር መሆኑን አረጋግጧል። እምነታችሁ ፈተና ቢደርስበትም ለይሖዋ ያላችሁን ንጹሕ አቋም ትጠብቃላችሁ?
14. በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ይሖዋ ምን የማዳን እርምጃ ወስዷል? ይሁዳ በባቢሎን ለመወረር ያበቃትስ ምን ነበር?
14 ለአምላክ ሕግ ግዴለሽነት መስፋፋቱ የእስራኤልን መንግሥት ለከባድ ችግር ዳርጎታል። አሦራውያን በ740 ከዘአበ የእስራኤልን መንግሥት በተቆጣጠሩ ጊዜ በአሥሩ ነገዶች ሥር የሚገኙ ግለሰቦች ይሖዋን በመቅደሱ ሊያመልኩ ወደሚችሉበት ወደ ሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት እንደሸሹ አያጠራጥርም። በዳዊት መስመር ከነገሡት 19 ነገሥታት መካከል አራቱ ማለትም አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ ከሌሎቹ የላቁ ነበሩ። ንጹሕ አቋም ጠባቂ በነበረው በሕዝቅያስ ዘመን አሦራውያን ይሁዳን ለመውጋት ከፍተኛ ጦር ይዘው መጡ። አምላክ ለሕዝቅያስ ልመና ምላሽ በመስጠት አንድ መልአክ ብቻ ተጠቅሞ በአንድ ሌሊት 185,000 አሦራውያን እንዲገደሉ በማድረግ አምላኪዎቹን አድኗል! (ኢሳይያስ 37:36–38) ከጊዜ በኋላ ሕዝቡ ሕጉን ሳይጠብቁና የአምላክ ነቢያት የሚሰጧቸውን ማስጠንቀቂያዎች ሳይከተሉ መቅረታቸው ለይሁዳ በባቢሎን መወረር እንዲሁም በ607 ከዘአበ ለዋና ከተማዋ ለኢየሩሳሌምና ለቤተ መቅደሱ መጥፋት ምክንያት ሆኗል።
15. በባቢሎን የሚገኙ አይሁድ ግዞተኞች መጽናት ያስፈለጋቸው ለምን ነበር? በመጨረሻስ ይሖዋ መዳንን የሰጣቸው እንዴት ነበር?
15 አይሁዳውያን ግዞተኞች በባቢሎን በምርኮ በቆዩባቸው 70 አሰቃቂ ዓመታት ለአምላክ ያላቸውን ንጹሕ አቋም ጠብቀው ለመቆየት መጽናት አስፈልጓቸው ነበር። (መዝሙር 137:1-6) ከእነዚህ ንጹሕ አቋም ጠባቂዎች መካከል ነቢዩ ዳንኤል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። (ዳንኤል 1:1-7፤ 9:1-3) አይሁዳውያን ወደ ይሁዳ ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ የሚፈቅደው የፋርሱ ንጉሥ የቂሮስ ድንጋጌ በ537 ከዘአበ ተግባራዊ ሲሆን ሲመለከት ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን አስብ! (ዕዝራ 1:1-4) ዳንኤልና ሌሎችም ለብዙ ዓመታት ጸንተው ኖረዋል፤ በመጨረሻ ግን ባቢሎን ስትገለበጥና የይሖዋ ሕዝቦች ከመከራ ነፃ ሲወጡ ተመልክተዋል። እኛም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” የምትጠፋበትን ጊዜ በጽናት ለመጠባበቅ ይህ ሊረዳን ይገባል።—ራእይ 18:1–5
ይሖዋ ምንጊዜም ሕዝቦቹን ያድናል
16. አምላክ በንግሥት አስቴር ዘመን ምን የማዳን እርምጃ ወስዷል?
16 ይሖዋ ሕዝቦቹ ለስሙ የታመኑ እስከሆኑ ድረስ ምንጊዜም ያድናቸዋል። (1 ሳሙኤል 12:22፤ ኢሳይያስ 43:10–12) ንግሥት አስቴር ትኖርበት ስለነበረው ስለ አምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ እስቲ አስቡ። ንጉሥ አሕሻዊሮስ (አርጤክስስ ቀዳማዊ) ሐማን ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሾሞት ነበር። ሐማ አይሁዳዊው መርዶክዮስ ሊሰግድለት ፈቃደኛ ስላልሆነ በመናደዱ እሱንና በፋርስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ አይሁዳውያንን በሙሉ ለማጥፋት የሚያስችል ተንኮል ሸረበ። ሕግ ተላላፊዎች እንደሆኑ አድርጎ በመግለጽና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳለው በመናገር አይሁዳውያን እንዲጠፉ የሚደነግገውን ሰነድ በንጉሡ ቀለበት እንዲያትም ተፈቀደለት። አስቴር ደፋር በመሆን አይሁዳዊ ዝርያ ያላት መሆኗን ለንጉሡ ተናገረች፤ እንዲሁም የሐማን የግድያ ሴራ አጋለጠች። ሐማ ለመርዶክዮስ መሰቀያ አዘጋጅቶት በነበረው ግንድ ላይ ራሱ ተሰቀለ። መርዶክዮስ አይሁዳውያን ራሳቸውን እንዲከላከሉ የመፍቀድ ሥልጣን ጭምር ተሰጥቶት ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ተሾመ። በጠላቶቻቸው ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጁ። (አስቴር 3:1—9:19) ይህ ክንውን ይሖዋ በዚህ ዘመን ለሚገኙ ታዛዥ አገልጋዮቹ የማዳን እርምጃ እንደሚወስድ ያለንን እምነት ሊያጠነክርልን ይገባል።
17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ታዛዥነት በሕይወት ከመትረፋቸው ጋር ምን ግንኙነት ነበረው?
17 አምላክ ሕዝቡን የሚያድንበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እሱንና ልጁን ስለሚታዘዙ ነው። እስቲ አይሁዳውያን በሆኑት የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቦታ ራስህን አስቀምጥ። “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ” በማለት ነገራቸው። (ሉቃስ 21:20–22) ዓመታት እያለፉ በሄዱ ቁጥር ታዲያ እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው እያልክ ማሰብህ አይቀርም። ከዚያም በ66 እዘአ የአይሁዳውያን ዓመፅ ተቀሰቀሰ። በሴስቲየስ ጋለስ የሚመሩት ሮማውያን ኃይሎች ኢየሩሳሌምን ከብበው ወደ ቤተ መቅደሱ ግንቦች ተጠጉ። በድንገትና ባልታወቀ ምክንያት ሮማውያኑ ከበባቸውን ትተው ሄዱ። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ምን ያደርጉ ይሆን? ዩሴቢየስ ኤክለሲያስቲካል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፉ ላይ (3ኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 5 ገጽ 3) ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ሸሽተው መውጣታቸውን ተናግሯል። የኢየሱስን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ በመታዘዛቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል። ኢየሱስ “ባለው” ሁሉ ላይ በሾመው “ታማኝና ልባም መጋቢ” በኩል የሚቀርበውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ለመከተል ፈጣኖች ናችሁ?—ሉቃስ 12:42–44
የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መዳን
18, 19. (ሀ) የኢየሱስ ሞት የትኛውን መዳን እውን እንዲሆን አድርጓል? ለማንስ? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ለማድረግ ቆርጦ ተነስቶ ነበር?
18 የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሰምቶ መከተሉ በይሁዳ የነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ሕይወት አድኗል። ሆኖም የኢየሱስ ሞት ‘ሰዎች ሁሉ’ ድነው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አስችሏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:10) የሰው ዘር ቤዛ ያስፈለገው አዳም ኃጢአት ሠርቶ የራሱን ሕይወት ባጣበትና ዘሮቹን በሙሉ ለኃጢአትና ለሞት ባርነት በሸጠበት ጊዜ ነው። (ሮሜ 5:12–19) በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳ መሥዋዕቶች እንዲያው ለስሙ ያህል የሚቀርቡ የኃጢአት መሸፈኛዎች ነበሩ። (ዕብራውያን 10:1–4) ኢየሱስ ሰብዓዊ አባት ስለሌለውና ማርያም ከጸነሰችበት ጊዜ አንስቶ እርሱ እስከ ተወለደበት ጊዜ ድረስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በላይዋ ላይ መሆኑ እርግጠኛ ስለነበር ኢየሱስ ከውርስ ኃጢአት ወይም ከአለፍጽምና ነፃ ሆኖ ተወልዷል። (ሉቃስ 1:35፤ ዮሐንስ 1:29፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ኢየሱስ ፍጹም አቋም ጠባቂ ሆኖ ሲሞት የሰው ልጆችን መልሶ ለመግዛትና ከኃጢአት ነፃ ለማውጣት ፍጹም ሕይወቱን አቅርቧል። (ዕብራውያን 2:14, 15) በዚህ መንገድ ክርስቶስ “ራሱንም ለሁሉ [“ተመጣጣኝ፣” NW] ቤዛ [አድርጎ ሰጥቷል]።” (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) ከዚህ የመዳን ዝግጅት ተጠቃሚዎች የሚሆኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም፤ ይሁን እንጂ አምላክ ዝግጅቱን በእምነት የሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ ቤዛው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ተካፋዮች እንዲሆኑ ያደርጋል።
19 ክርስቶስ በሰማይ ለሚገኘው አምላክ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ በማቅረብ የአዳምን ዘሮች እንደገና ገዝቷቸዋል። (ዕብራውያን 9:24) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለሰማያዊ ሕይወት በተነሱ 144,000 የተቀቡ ተከታዮቹ የተገነባች ሙሽራ አግኝቷል። (ኤፌሶን 5:25–27፤ ራእይ 14:3, 4፤ 21:9) በተጨማሪም መሥዋዕቱን ለሚቀበሉና በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለሚያገኙ ሰዎች ሁሉ “የዘላለም አባት” ሆኗል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው! የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደሚያሳየው ጳውሎስ ለዚህ ዝግጅት የነበረው አድናቆት በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሣሽነት በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ በግልጽ የሚታይ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ለአስደናቂው የይሖዋ የመዳን ዝግጅት ሰዎች ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ከመርዳት ምንም ነገር እንዲያግደው ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ አምላክ የእሱን ቅን ሰዎች እንደሚያድን የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
◻ ይሖዋ በእርሱ የሚታመኑትንና ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁትን እንደሚያድን እንዴት እናውቃለን?
◻ አምላክ ድነን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ምን ዝግጅቶች አድርጓል?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ‘አዳኝ’ በሆነው በይሖዋ ታምኖ ነበር። አንተስ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በንግሥት አስቴር ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ይሖዋ ምንጊዜም ሕዝቡን ያድናል