ሸክማችሁን ምን ጊዜም በይሖዋ ላይ ጣሉ
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ሸክሞች እንደተጫኗቸው ይሰማቸዋል። የኢኮኖሚ ችግሮች፣ አስጨናቂ የቤተሰብ ችግሮች፣ የጤና ችግሮች በጭቆናና በአምባገነን አገዛዝ ሳቢያ የሚደርስ ሥቃይና መከራ እንዲሁም ሌሎች መከራዎች በአንገታቸው ላይ እንደታሰረ የወፍጮ ድንጋይ ሆነውባቸዋል። አንዳንዶች ከእነዚህ ውጪያዊ ችግሮች በተጨማሪ በራሳቸው ጉድለቶች ምክንያት ምንም እንደማይረቡና የሚገባቸውን ያህል እንዳላደረጉ ይሰማቸዋል። ብዙዎች ትግሉን ከነአካቴው ለማቋረጥ ይፈተናሉ። ልንሸከማቸው የማንችላቸው የሚመስሉ ሸክሞችን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
በአንድ ወቅት ንጉሥ ዳዊት የደረሰበት ችግር ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ያህል ተሰምቶት ነበር። በመዝሙር 55 ላይ እንደምናነበው ጠላቶቹ ባደረሱበት ችግርና ለእርሱ በነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት በጭንቀት እንደተዋጠ ይነግረናል። እጅግ ተጨንቆና በፍርሃት ተውጦ ነበር። በደረሰበት ሐዘን ምክንያት ይቃትት ነበር። (መዝሙር 55:2, 5, 17) ሆኖም ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ይህን መከራ መቋቋም የሚችልበት መንገድ አግኝቷል። እንዴት? አምላኩ እንዲረዳው በመጠየቅ ነው። እርሱ የተሰማው ዓይነት ስሜት ለሚሰማቸው ሰዎች የሰጠው ምክር ‘ሸክምህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል’ የሚል ነው።—መዝሙር 55:22
ዳዊት ‘ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? እንዲህ ሲባል ወደ ይሖዋ በጸሎት ቀርበን ጭንቀታችንን መግለጻችን ብቻ በቂ ነው ማለት ነውን? ወይስ ችግሩን ለማስወገድ እኛ ራሳችን ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራል? ወደ ይሖዋ ፈጽሞ መቅረብ እንደማይገባን ከተሰማን ምን ማድረግ እንችላለን? ዳዊት እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት ቁልጭ ብለው የሚታወሱትን አንዳንድ ተሞክሮዎች በመመልከት ምን ለማለት እንደፈለገ ለመረዳት እንችላለን።
ነገሮችን በይሖዋ ኃይል አከናውኑ
ጎልያድ የእስራኤል ወታደሮችን ልብ እንዴት በፍርሃት እንዳቀለጠ ታስታውሳለህን? ከ2.7 ሜትር በላይ ቁመት የነበረው ይህ ግዙፍ ሰው አስፈራራቸው። (1 ሳሙኤል 17:4-11, 24) ዳዊት ግን አልፈራም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ዳዊት ጎልያድን በራሱ ኃይል ለመቋቋም አልሞከረም። የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንዲሆን ከተቀባበት ጊዜ ጀምሮ የአምላክ መንፈስ በሚያደርገው ሁሉ እንዲመራውና እንዲያጠነክረው ፈቅዶ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:13) ስለዚህ ጎልያድን “እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” አዓት] ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል” አለው። (1 ሳሙኤል 17:45, 46) ዳዊት ወንጭፍ የመወንጨፍ ችሎታ ቢኖረውም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደመራውና ወደ ጎልያድ የወረወረው ድንጋይ ጎልያድን እንዲገድለው እንዳደረገ ምንም አያጠራጥርም።—1 ሳሙኤል 17:48-51
ዳዊት ይህን ታላቅ ፈተና ተቋቁሞ ድል የተጎናጸፈው አምላክ እንደሚረዳውና እንደሚያጠነክረው ስለተማመነ ነው። ከአምላክ ጋር ጥሩና አስተማማኝ የሆነ ዝምድና መሥርቶ ነበር። ይሖዋ ቀደም ሲል እርሱን ያዳነበት ሁኔታ ይህን ዝምድና እንዳጠናከረለት አያጠራጥርም። (1 ሳሙኤል 17:34-37) አንተም እንደ ዳዊት ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ልታጠናክርና በማናቸውም ሁኔታ ሥር አንተን ለማበርታትና ለመርዳት ችሎታ እንዳለውና ፈቃደኛ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ልትተማመን ትችላለህ።—መዝሙር 34:7, 8
ችግሩን ለመፍታት የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ
እንደዚህ ሲባል ግን ከመዝሙር 55 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ከባድ ሥቃይና ጭንቀት አልፎ ተርፎም ፍርሃት ጨርሶ አያጋጥምም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ዳዊት በይሖዋ ላይ በመመካት ይህን ድፍረት ካሳየ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በጠላቶቹ ፊት በጣም ፈርቶ ነበር። በንጉሥ ሳኦል ፊት ሞገስ ስላላገኘ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ለመሸሽ ተገደደ። ይህ ሁኔታ በዳዊት ላይ ያስከተለበትን የስሜት መቃወስና ስለ አምላክ ዓላማዎች አፈጻጸም በአእምሮው ውስጥ የተነሡትን ጥያቄዎች እስቲ ገምት። የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባ ቢሆንም እንደ አውሬ እየታደነ ስለ ነበረ ሕይወቱን ለማትረፍ ወደ በረሃ መሸሽ ነበረበት። የጎልያድ የትወልድ ከተማ በነበረችው በጌት ውስጥ በስደተኝነት ለመኖር ሲሞክር ማንነቱ ታወቀ። ሁኔታው ምን ውጤት አስከተለበት? ታሪኩ “እጅግ ፈራ” ይላል።—1 ሳሙኤል 21:10-12
ሆኖም ፍርሃቱና ስጋቱ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ከማለት አላገደውም። በመዝሙር 34 ላይ (መዝሙሩ የተጻፈው ይህ ሁኔታ ካጋጠመው በኋላ ነው) ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፣ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። ይህ ችግረኛ ጮኸ፣ እግዚአብሔርም ሰማው፣ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።”—መዝሙር 34:4, 6
እርግጥ ይሖዋ ረድቶታል። ሆኖም ዳዊት እጁን አጣጥፎ ቁጭ ብሎ ይሖዋ እንዲያድነው እንዳልጠበቀ አስተውል። ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመዳን የሚችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። እርሱን በማዳን ረገድ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ቢያምንም የጌት ንጉሥ እንዳይገድለው ያበደ በማስመሰል የራሱን እርምጃ ወስዷል። (1 ሳሙኤል 21:14–22:1) እኛም ሸክሞቻችንን ለመቋቋም የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንጂ እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን ይሖዋ እንዲያድነን መጠበቅ አይገባንም።—ያዕቆብ 1:5, 6፤ 2:26
በሸክሞቻችሁ ላይ ሸክም አትጨምሩ
ዳዊት በኋለኛው ሕይወቱ ሌላ ከባድ ትምህርት አግኝቷል። ይህ ትምህርት ምን ነበር? አንዳንድ ጊዜ በራሳችን ሸክሞች ላይ ተጨማሪ ሸክም እንደምንጭን ተምሯል። ዳዊት በፍልስጤማውያን ላይ ድል ከተቀዳጀ በኋላ የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ በወሰነበት ወቅት አንድ ስሕተት ፈጸመ። ታሪካዊው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው . . . የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፣ . . . የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር።”—2 ሳሙኤል 6:2, 3
ታቦቱን ለማጓጓዝ በሰረገላ መጠቀማቸው ይሖዋ የታቦቱን አያያዝ በተመለከተ የሰጣቸውን መመሪያዎች ያስጥስ ነበር። ታቦቱን የመሸከም ሥልጣን የተሰጣቸው ከቀዓት ልጆች የሆኑ ሌዋውያን ብቻ እንደሆኑና በታቦቱ ላይ በሚገኙት ቀለበቶች ውስጥ እንጨቶችን በማስገባት ታቦቱን በትከሻቸው መሸከም እንደሚኖርባቸው በግልጽ ተነግሮ ነበር። (ዘጸአት 25:13, 14፤ ዘኁልቁ 4:15, 19፤ 7:7-9) እነዚህን መመሪያዎች ችላ ማለታቸው ከባድ ጉዳት አስከተለባቸው። ሰረገላውን የሚስበው ከብት ታቦቱን ሊጥለው ሲል ሌዋዊ ቢሆንም እንኳ ካህን ያልነበረው ዖዛ ታቦቱን ለመያዝ እጁን በመዘርጋቱ ምክንያት አክብሮት ባለማሳየቱ ይሖዋ ቀሠፈው።—2 ሳሙኤል 6:6, 7
ዳዊት፣ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ ተጠያቂ ነበር። እርሱ ያሳየው ስሜት ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ያላቸው ሰዎችም እንኳ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት አልፎ አልፎ መጥፎ ነገር ሊሠሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል። በመጀመሪያ ዳዊት በጣም ተናደደ። ከዚያም ፈራ። (2 ሳሙኤል 6:8, 9) ከይሖዋ ጋር የነበረው አስተማማኝ ግንኙነት ክፉኛ ተፈተነ። በዚህ ወቅት የይሖዋን ትእዛዛት ስላላከበረ ሸክሙን በይሖዋ ላይ አልጣለም ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ይደርስብን ይሆን? የእርሱን መመሪያዎች ሳንከተል በመቅረታችን በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ይሖዋን እንወቅሰዋለንን?—ምሳሌ 19:3
የጥፋተኝነት ስሜት የሚያስከትለውን ሸክም መቋቋም
ከዚህ በኋላ ዳዊት የይሖዋን የሥነ ምግባር ደረጃዎች በመጣስ ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ ትልቅ የጥፋተኝነት ስሜት ሸክም በራሱ ላይ ጫነ። በዚህ ወቅት ዳዊት የጦር መሪነት ኃላፊነቱን ትቶ ነበር። ወታደሮቹ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እርሱ በኢየሩሳሌም ቀረ። ይህም ከባድ ችግር አስከተለበት።—2 ሳሙኤል 11:1
ንጉሥ ዳዊት ውብ የነበረችው ቤርሳቤህ ገላዋን ስትታጠብ አየ። ከእርሷ ጋር የጾታ ብልግና ፈጸመና አረገዘችበት። (2 ሳሙኤል 11:2-5) የፈጸመውን ጥፋት ለመሸፋፈን በመሞከር ባሏ ኦርዮ ከጦር ሜዳ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስ አደረገ። ኦርዮ እስራኤላውያን በጦርነት ላይ ሳሉ ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም አልፈለገም። (2 ሳሙኤል 11:6-11) በዚህ ወቅት ዳዊት ኃጢአቱን ለመሸፋፈን መጥፎና መሠሪ የሆነ መንገድ ተጠቀመ። ከኦርዮ ጋር ያሉት ወታደሮች እርሱ እንዲገደል በአደገኛ ቦታ ትተውት እንዲያፈገፍጉ ትእዛዝ አስተላለፈ። ይህ በጣም አሠቃቂ የሆነ ከባድ ኃጢአት ነበር!—2 ሳሙኤል 11:12-17
ከጊዜ በኋላ ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት ተጠያቂ ከመሆኑም በተጨማሪ እንዲጋለጥ ተደረገ። (2 ሳሙኤል 12:7-12) ዳዊት በጾታ ስሜት ተነሳስቶ የፈጸመው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘብ የተሰማውን ከባድ ሐዘንና የጥፋተኝነት ስሜት እስቲ ገምት። በተለይ ዳዊት በቀላሉ የሚሰማውና የሚያዝን ሰው ስለ ነበር በፈጸመው ስሕተት በጣም ተረብሾ ሳይሆን አይቀርም። ፈጽሞ እንደማይረባ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል!
ሆኖም ዳዊት “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ለነቢዩ ናታን ተናግሮ ስሕተቱን ወዲያውኑ አመነ። (2 ሳሙኤል 12:13) መዝሙር 51 እንዴት እንደተሰማውና ከኃጢአቱ እንዲያነጻውና ይቅር እንዲለው ወደ ይሖዋ አምላክ ምልጃ እንዳቀረበ ይነግረናል። “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 51:2, 3) ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ምክንያት ከይሖዋ ጋር ያለውን ጠንካራና የተቀራረበ ዝምድና መልሶ ለመገንባት ችሏል። ዳዊት በጸጸትና ምንም ዋጋ የለኝም በሚል ስሜት አልተዋጠም። ራሱን ዝቅ አድርጎ ስሕተቱን በማመን፣ ልባዊ ንስሐ በማሳየትና ይሖዋ ይቅር እንዲለው የጋለ ጸሎት በማቅረብ ሸክሙን በይሖዋ ላይ ጥሏል። በዚህም ምክንያት የአምላክን ሞገስ መልሶ አግኝቷል።—መዝሙር 51:7-12, 15-19
የቅርብ ወዳጅ ሲከዳ የሚፈጠረውን ችግር መቋቋም
ይህም ዳዊት መዝሙር 55ን እንዲጽፍ ወደገፋፋው ድርጊት ይወስደናል። በዚህ ወቅት በከፍተኛ የስሜት ውጥረት ውስጥ ነበር። “ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፣ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 55:4) ይህን ሥቃይ ያስከተለበት ምንድን ነው? የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ንግሥናውን ከዳዊት ለመንጠቅ አሢሮ ነበር። (2 ሳሙኤል 15:1-6) ይህ የልጁ ክህደት ሳያንስ ይባስ ብሎ የዳዊት ታማኝ አማካሪ የነበረው አኪጦፌል በዳዊት ላይ በተጠነሰሰው ሤራ ተባባሪ ሆነ። ዳዊት በመዝሙር 55:12-14 ላይ የተናገረው ስለ አኪጦፌል ነው። ዳዊት በዚህ ሤራና ክህደት ምክንያት ከኢየሩሳሌም ለመሸሽ ተገደደ። (2 ሳሙኤል 15:13, 14) ይህ ሁኔታ እንዴት ያለ ጭንቀት አስከትሎበት መሆን አለበት!
ሆኖም ዳዊት በዚህ ከባድ ጭንቀትና ሐዘን ምክንያት በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲቀንስ አልፈቀደም። የሤረኞቹን እቅዶች እንዲያጨናግፍ ወደ ይሖዋ ጸሎት አቀረበ። (2 ሳሙኤል 15:30, 31) እዚህም ላይ ቢሆን ዳዊት እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንዲያደርግለት እንዳልጠበቀ እንገነዘባለን። አጋጣሚውን እንዳገኘ በእርሱ ላይ የተጠነሰሰበትን ሤራ ለማክሸፍ የሚችለውን ሁሉ አደረገ። ከአማካሪዎቹ አንዱ የሆነውን ኩሲን ወደ ኢየሩሳሌም ላከውና ከሤረኞቹ ጋር ያበረ መስሎ ሤራውን እንዲያከሽፍ አዘዘው። (2 ሳሙኤል 15:32-34) በይሖዋ እርዳታ ይህ እቅድ ተሳካ። ኩሲ አቤሴሎምን ስላዘናጋው ዳዊት ተከታዮቹን በአዲስ መልክ ለማሰባሰብና ራሱን ለመከላከል የሚያስችል ሠራዊት ለማደራጀት ጊዜ አገኘ።—2 ሳሙኤል 17:14
ዳዊት ዕድሜውን ሙሉ የይሖዋን ጥበቃ ከማግኘቱም በላይ ትዕግሥቱንና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን በመመልከቱ ምንኛ በአድናቆት ተሞልቶ መሆን አለበት! (መዝሙር 34:18, 19፤ 51:17) በመከራችን ወቅት እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር እንድንልና በልበ ሙሉነት ‘ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እንድንጥል’ ዳዊት ያበረታታን በዚህ ምክንያት ነው።—ከ1 ጴጥሮስ 5:6, 7 ጋር አወዳድር።
ከይሖዋ ጋር ጠንካራና አስተማማኝ ዝምድና መሥርቶ መኖር
ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረው ዓይነት ዝምድና ማለትም በከባድ ፈተናና መከራ ወቅት ደግፎ ያቆመውን ዓይነት ዝምድና መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትጉ ተማሪዎች በመሆን ይህን ዝምድና መገንባት እንችላለን። እርሱ ስለ ሕጎቹ፣ ስለ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና ስለ ባሕርይው እንዲያስተምረን እንፍቀድለት። (መዝሙር 19:7-11) በአምላክ ቃል ላይ በይበልጥ ባሰላሰልን መጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ እርሱ መቅረብና ያለ አንዳች ጥርጣሬ በእርሱ መተማመንን እንማራለን። (መዝሙር 143:1-5) ከይሖዋ ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት አብረውን ከሚያመልኩት ጋር ከተሰበሰብን ይህን ዝምድናችንን በይበልጥ እናጠናክራለን። (መዝሙር 122:1-4) ወደ ይሖዋ በምናቀርበው ልባዊ ጸሎት አማካኝነት ዝምድናችንን እናጎለብታለን።—መዝሙር 55:1
እርግጥ ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረው ዝምድና ጠንካራ መሆን የነበረበትን ያህል ጠንካራ ሳይሆን ሲቀር እንደ እኛ ጭንቀቶች አጋጥመውታል። ጭቆና ‘በጣም ሊያበሳጨን’ ይችላል። (መክብብ 7:7) ይሁን እንጂ ይሖዋ እየደረሰብን ያለውን ነገር ይመለከታል፤ በልባችን ውስጥ ያለውንም ያውቃል። (መክብብ 4:1፤ 5:8) ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና መሥርተን ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ማንኛውም ዓይነት ሸክም ቢኖርብን ከጭንቀታችን እፎይታ ለማግኘት ወይም ያለንበትን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን በይሖዋ ልንተማመን እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ይህን ለማግኘት ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖር ያስፈልጋል። ዳዊት ከይሖዋ ጋር ሲቀራረብ ፍጹም ተረጋግቶ ይኖር ነበር።
ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ዳዊት ምን ጊዜም ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል ይልሃል። እንዲህ ካደረግን “እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚለው ተስፋ ሲፈጸም እንመለከታለን።—መዝሙር 55:22