በእናንተ ላይ ሥልጣን የተሰጣቸውን አክብሩ
“ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17
1, 2. በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለሥልጣን ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ለምንስ?
“መብቱ ሁሉ የተሰጠው ለልጆች ነው። ወላጆች አይከበሩም” ስትል አንዲት እናት ምሬቷን ገልጻለች። በመኪና ላይ በሚለጠፍ አንድ ወረቀት ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ደግሞ “በሥልጣን ላይ ዓምፁ” ይላል። እነዚህ በዛሬው ጊዜ በእጅጉ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሁኔታ የሚያስገነዝቡ ሁለት ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። በዓለም ዙሪያ ብዙዎች ለወላጆች፣ ለአስተማሪዎች፣ ለአሠሪዎችና ለመንግሥት ባለ ሥልጣኖች አክብሮት የላቸውም።
2 አንዳንዶች ትከሻቸውን በመነቅነቅ ‘በሥልጣን ላይ ያሉት እኮ አክብሮት የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም’ ይሉ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ይህን አባባል ማስተባበል አይቻል ይሆናል። በሙስና ተግባር ስለተዘፈቁ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች፣ ስለ ስግብግብ አሠሪዎች፣ ብቃት ስለጎደላቸው አስተማሪዎችና በደል ስለሚፈጽሙ ወላጆች የሚገልጹ ዜናዎች ዘወትር እንሰማለን። ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ በሥልጣን ቦታ ላይ የሚገኙትን በዚህ መንገድ የሚመለከቱ አለመሆናቸው የሚያስደስት ነው።—ማቴዎስ 24:45-47
3, 4. ክርስቲያኖች በሥልጣን ቦታ ላይ ላሉት አክብሮት ማሳየት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
3 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን እንድናከብር ‘የሚያስገድድ ምክንያት’ አለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች [ተገዙ]። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” ሲል አጥብቆ መክሯቸዋል። (ሮሜ 13:1, 2, 5፤ 1 ጴጥሮስ 2:13-15) በተጨማሪም ጳውሎስ በቤተሰብ ውስጥ ሥልጣን ያላቸውን እንድናከብር የሚገፋፋ አጥጋቢ ምክንያት ጠቅሷል:- “ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላስይስ 3:18, 20) የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘የአምላክን መንጋ እንዲጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ የሾማቸው’ በመሆኑ ልናከብራቸው ይገባል። (ሥራ 20:28) ሰብዓዊ ባለ ሥልጣኖችን የምናከብረው ለይሖዋ አክብሮት ስላለን ነው። ለይሖዋ ሥልጣን ያለን አክብሮት ምንጊዜም በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያውን እንደሚይዝ የታወቀ ነው።—ሥራ 5:29
4 ይሖዋ ያለውን ከሁሉ የላቀ ሥልጣን በአእምሯችን በመያዝ በሥልጣን ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ያከበሩትንና ያላከበሩትን አንዳንድ ሰዎች ምሳሌ እንመልከት።
አክብሮት አለማሳየት ተቀባይነት ያሳጣል
5. ሜልኮል ለዳዊት ምን ዓይነት ንቀት አሳይታለች? ይህስ ምን አስከተለ?
5 የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ በመመልከት ይሖዋ ሥልጣን የሰጣቸውን የሚንቁ ሰዎችን እንዴት እንደሚመለከታቸው ማስተዋል እንችላለን። ዳዊት የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ ባደረገበት ጊዜ ሚስቱ ሜልኮል “ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው።” ሜልኮል ዳዊት የቤተሰቡ ራስ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ንጉሥ መሆኑንም መገንዘብ ነበረባት። ይሁን እንጂ እንዲህ ስትል ስሜቷን በአሽሙር ገለጸች:- “ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቆነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው!” በዚህ ሳቢያ ሜልኮል መካን ሆና ቀርታለች።—2 ሳሙኤል 6:14-23
6. ይሖዋ እሱ በቀባው ሰው ላይ ቆሬ ያሳየውን ንቀት የተመለከተው እንዴት ነበር?
6 አምላክ ያቋቋመውን ቲኦክራሲያዊ አመራር ባለማክበር እጅግ መጥፎ ምሳሌ የሚሆነው ቆሬ ነው። ከቀዓት ወገን እንደመሆኑ መጠን ይሖዋን በመገናኛው ድንኳን የማገልገል ልዩ መብት አግኝቶ ነበር! ሆኖም አምላክ የእስራኤል መሪዎች አድርጎ በቀባቸው በሙሴና በአሮን ላይ ስህተት ይለቃቅም ነበር። ቆሬ ከሌሎች የእስራኤል አለቆች ጋር ኅብረት በመፍጠር ዓይን ባወጣ ድፍረት ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው:- “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና . . . በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” ይሖዋ የቆሬንና የግብረ አበሮቹን አመለካከት እንዴት ተመለከተው? አምላክ በዚህ ድርጊታቸው ራሱን ይሖዋን እንዳቃለሉ አድርጎ ነበር የተመለከተው። ከእነሱ ጎን ቆመው የነበሩትን ሁሉ ምድር አፍዋን ከፍታ ስትውጣቸው ከተመለከቱ በኋላ ቆሬና 250ዎቹ አለቆች ይሖዋ ባወረደው እሳት ጠፉ።—ዘኁልቁ 16:1-3, 28-35
7. “ዋነኞቹ ሐዋርያት” ጳውሎስን ሊተቹ የሚችሉበት ምክንያት ነበራቸውን?
7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለቲኦክራሲያዊ ሥልጣን ንቀት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩት “ዋነኞቹ ሐዋርያት” ለጳውሎስ አክብሮት አልነበራቸውም። “ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” በማለት የንግግር ችሎታውን ተችተዋል። (2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:5) ጳውሎስ የተዋጣለት ተናጋሪም ሆነ አልሆነ ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን አክብሮት ሊሰጠው ይገባ ነበር። ይሁንና በእርግጥ የጳውሎስ ንግግር የሚናቅ ነበርን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት በሕዝብ ፊት የሰጣቸው ንግግሮች ምን ያህል አሳማኝ ተናጋሪ እንደነበር በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ጳውሎስ ‘የአይሁድን ክርክር ጠንቅቆ ከሚያውቀው’ ከዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ጋር ባደረገው አጭር ውይይት እንኳ ንጉሡ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው! [የ1980 ትርጉም ]” እንዲል አድርጎታል። (ሥራ 13:15-43፤ 17:22-34፤ 26:1-28) ሆኖም በቆሮንቶስ የነበሩት ዋነኞቹ ሐዋርያት ንግግሩ የተናቀ ነው ሲሉ ከሰውታል! ይሖዋ ይህን አስተሳሰባቸውን የተመለከተው እንዴት ነበር? ኢየሱስ ክርስቶስ ለኤፌሶን ጉባኤ የበላይ ተመልካቾች በላከው መልእክት ላይ ‘ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን በሚሉት’ ለመወሰድ ፈቃደኞች ሳይሆኑ የቀሩትን ሰዎች በማድነቅ ተናግሯል።—ራእይ 2:2
አለፍጽምና ቢኖርባቸውም አክብሮት ማሳየት
8. ይሖዋ ለሳኦል ለሰጠው ሥልጣን ዳዊት አክብሮት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?
8 መጽሐፍ ቅዱስ በሥልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች ሥልጣናቸውን አላግባብ በተጠቀሙበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር አክብሮት ስላሳዩ ሰዎች የሚገልጹ ብዙ ምሳሌዎች ይዟል። ዳዊት ለዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው። ዳዊት የበታች ሆኖ ያገለግለው የነበረው ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊት ባከናወናቸው ነገሮች በመቅናቱ ሊገድለው ፈልጎ ነበር። (1 ሳሙኤል 18:8-12፤ 19:9-11፤ 23:26) ያም ሆኖ ዳዊት ሳኦልን መግደል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አግኝቶ የነበረ ቢሆንም “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው” ብሏል። (1 ሳሙኤል 24:3-6፤ 26:7-13) ሳኦል ስህተት እየሠራ መሆኑን ዳዊት ያውቅ የነበረ ቢሆንም ፍርዱን ለይሖዋ ትቶታል። (1 ሳሙኤል 24:12, 15፤ 26:22-24) ሳኦልን ፊት ለፊትም ሆነ ከበስተኋላው አልተቸውም።
9. (ሀ) ሳኦል በደል ይፈጽምበት በነበረበት ወቅት ዳዊት የተሰማው ስሜት ምን ነበር? (ለ) ዳዊት ለሳኦል ከልብ የመነጨ አክብሮት ነበረው ብለን እንድንናገር የሚያደርገን ምንድን ነው?
9 ዳዊት እንግልት በደረሰበት ወቅት ተጨንቆ ነበርን? “ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታል” ሲል ወደ ይሖዋ ጮዃል። (መዝሙር 54:3) እንዲህ በማለት የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል:- “አምላኬ ሆይ፣ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ . . . ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ፤ አቤቱ፣ በበደሌም አይደለም፣ በኃጢአቴም አይደለም። ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፣ ተቀበለኝ፣ እይም።” (መዝሙር 59:1-4) አንተም ልክ እንደዚሁ በሥልጣን ላይ ያለ ሰው ባደረሰብህ መከራ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ዳዊት ለሳኦል የነበረው አክብሮት አልቀነሰም። ሳኦል በሞተበት ወቅት ዳዊት በደስታ ከመፈንጠዝ ይልቅ የሚከተለውን ሙሾ አውጥቷል:- “ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ . . . ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ፣ . . . ለሳኦል አልቅሱለት።” (2 ሳሙኤል 1:23, 24) ዳዊት ምንም እንኳ ሳኦል አግባብ ያልሆነ ድርጊት የፈጸመበት ቢሆንም ይሖዋ ለቀባው ሰው ልባዊ አክብሮት በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ትቷል!
10. ጳውሎስ አምላክ ለአስተዳደር አካሉ የሰጠውን ሥልጣን በማክበር ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? ይህስ ምን አስከትሏል?
10 በክርስትናም ዘመን አምላክ ለሾማቸው አክብሮት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የተዉ ሰዎች አሉ። ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል ላሳለፋቸው ውሳኔዎች አክብሮት አሳይቷል። ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በነበረበት ወቅት ለሙሴ ሕግ ምንም ዓይነት ጥላቻ እንደሌለው ለሌሎች ለማሳየት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ራሱን እንዲያነጻ የአስተዳደር አካሉ ምክር ሰጥቶት ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር:- ‘ቀደም ሲል እነዚህ ወንድሞች ሕይወቴ አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ኢየሩሳሌምን ለቅቄ እንድሄድ ነግረውኝ እንዳልነበር አሁን ደግሞ ለሙሴ ሕግ አክብሮት እንዳለኝ በሕዝብ ፊት እንዳሳይ ይፈልጋሉ። ቀደም ሲል ለገላትያ ሰዎች በጻፍኩላቸው ደብዳቤ ላይ ሕጉን መጠበቅ እንደሌለባቸው የሚገልጽ ምክር ሰጥቻቸዋለሁ። ወደ ቤተ መቅደሱ ብሄድ ሌሎች የማደርገውን ነገር በተሳሳተ መንገድ በመረዳት አቋሜን አላልቼ ከተገረዙት ወገን ጋር እንዳበርኩ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።’ ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንደዚያ ብሎ እንዳላሰበ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህ ሁኔታ የትኛውንም ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓት የሚያስጥስ ባለመሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአስተዳደር አካል የሰጠውን ምክር በማክበር የተባለውን አድርጓል። በዚህም ሳቢያ ጳውሎስ በወቅቱ አይሁዶች ባስነሱት ረብሻ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቆ የነበረ ከመሆኑም በላይ ለሁለት ዓመት እስር ተዳርጓል። ውሎ አድሮ ግን የአምላክ ፈቃድ ሊፈጸም ችሏል። ጳውሎስ በቂሣርያ በከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ፊት ምስክርነት ከመስጠቱም በተጨማሪ በመንግሥት ወጪ ወደ ሮም ተወስዶ በቄሣር ፊትም መስክሯል።—ሥራ 9:26-30፤ 21:20-26፤ 23:11፤ 24:27፤ ገላትያ 2:12፤ 4:9, 10
አክብሮት ታሳያለህን?
11. ለዓለማዊ ሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 በሥልጣን ላይ ላሉት ተገቢውን አክብሮት ታሳያለህን? ክርስቲያኖች ‘ለሁሉ የሚገባውን እንዲያስረክቡና ክብር ለሚገባው ክብርን እንዲሰጡ’ ታዝዘዋል። በእርግጥም “በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች” የምንገዛው ግብር በመክፈል ብቻ ሳይሆን በምግባራችንና በአነጋገራችን ለባለ ሥልጣናት አክብሮት በማሳየት ጭምር ነው። (ሮሜ 13:1-7) ኃይለኛ የሆኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በሚገጥሙን ጊዜ ምን ምላሽ እንሰጣለን? በሜክሲኮ ቺያፓስ ግዛት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ባለ ሥልጣናት በተወሰኑ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ አይካፈሉም በሚል የ57 የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ንብረት የሆኑ የእርሻ ቦታዎችን ወሰዱ። ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ይካሄዱ በነበሩት ስብሰባዎች ላይ ምሥክሮቹ ንጹሕና ሥርዓታማ ልብስ በመልበስ ዘወትር በአክብሮት ይናገሩ ነበር። ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በላይ የሚሆን ጊዜ ካለፈ በኋላ የምሥክሮቹ አቋም ተቀባይነት እንዳለው የሚያሳይ ውሳኔ ተላለፈ። አንዳንድ ታዛቢዎች የምሥክሮቹን አመለካከት እጅግ ከማድነቃቸው የተነሳ እነሱም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እስከመነሳሳት ደርሰዋል!
12. ለማያምን ባል “ጥልቅ አክብሮት” ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 አምላክ በቤተሰብ ውስጥ ለሰጠው ሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ መከራ በመቀበል የተወውን ምሳሌ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን [“ጥልቅ አክብሮት የሚንጸባረቅበትን፣” NW ] ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:1, 2፤ ኤፌሶን 5:22-24) ጴጥሮስ ምንም እንኳ አንዳንድ ባሎች አክብሮት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ነገር የማያደርጉ ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ አንዲት ሚስት ለባሏ “ጥልቅ አክብሮት” በማሳየት የመገዛቷን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። አንዲት ሚስት የምታሳየው አክብሮት የተሞላበት አመለካከት የማያምነውን ባሏን ልብ ሊያሸንፈው ይችላል።
13. ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር የሚችሉት እንዴት ነው?
13 ከዚህ ጥቅስ በታች ጴጥሮስ የሰጠው ሐሳብ ግሩም የእምነት ምሳሌ የሆነው የአብርሃም ሚስት ሣራ በተወችው ምሳሌ ላይ እንድናተኩር የሚያደርግ ነው። (ሮሜ 4:16, 17፤ ገላትያ 3:6-9፤ 1 ጴጥሮስ 3:6) አማኝ የሆኑ ባሎች ያሏቸው ሚስቶች ለባሎቻቸው የሚያሳዩት አክብሮት አማኝ ያልሆኑ ባሎች ያሏቸው ሚስቶች ከሚያሳዩት አክብሮት ያነሰ መሆን ይኖርበታልን? በአንድ ጉዳይ ላይ ከባሎቻችሁ ጋር ባትስማሙስ? ኢየሱስ ጠቅለል ባለ መልኩ እዚህም ላይ ሊሠራ የሚችል አንድ ምክር ሰጥቷል:- “ማንም [“በሥልጣን ላይ ያለ፣” NW ] ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ።” (ማቴዎስ 5:41) ከባሎቻችሁ ፍላጎት ጋር በመስማማት አክብሮታችሁን ታሳያላችሁን? ይህን ማድረጉ አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በጉዳዩ ላይ ያላችሁን ስሜት ለባሎቻችሁ አካፍሉ። ምን እንደሚሰማኝ ያውቃል ብላችሁ አታስቡ። ሆኖም ፍላጎታችሁን ለባሎቻችሁ የምታሳውቁት አክብሮት በተሞላበት መንገድ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን” ሲል አጥብቆ ይመክረናል።—ቆላስይስ 4:6
14. ለወላጆች አክብሮት ማሳየት ምን ማድረግ ይጠይቃል?
14 ልጆች የሆናችሁትስ? የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ያዝዛችኋል:- “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። . . . አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” (ኤፌሶን 6:1-3) ለወላጆቻችሁ መታዘዝ ‘አባታችሁንና እናታችሁን ከማክበር’ ጋር አንድ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹን ልብ በሉ። “ማክበር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ከፍ አድርጎ መመልከት” ወይም “ትልቅ ግምት መስጠት” የሚል ትርጉም ያዘለ ነው። ስለዚህ ታዛዥ መሆን ምክንያታዊ መስለው ያልታዩአችሁን የወላጆቻችሁን መመሪያዎች ቅር እያላችሁ ከመታዘዝ የበለጠ ነገርን የሚጠይቅ ነው። አምላክ ወላጆቻችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድትመለከቱና የሚሰጧችሁን አመራር ዋጋማነት እንድታደንቁ ይፈልግባችኋል።—ምሳሌ 15:5
15. ልጆች ወላጆቻቸው ስህተት እንደሠሩ ቢሰማቸው እንኳ ለእነርሱ ያላቸው አክብሮት እንዳይቀንስ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ወላጆቻችሁ ለእነሱ ያላችሁን አክብሮት ዝቅ ሊያደርግ የሚችል ነገር ቢፈጽሙ ምን ታደርጋላችሁ? ያሉትን ሁኔታዎች ከእነሱ አመለካከት አንጻር ለመመልከት ሞክሩ። ‘የወለዷችሁና’ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች የሚያሟሉላችሁ እነሱ አይደሉምን? (ምሳሌ 23:22) ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉላችሁ በፍቅር ተገፋፍተው አይደለምን? (ዕብራውያን 12:7-11) የሚሰማችሁን ነገር በየዋህነት መንፈስ በመግለጽ ወላጆቻችሁን በአክብሮት አነጋግሯቸው። እናንተ ደስ በማትሰኙበት መንገድ ቢመልሱላችሁ እንኳ አክብሮት በጎደለው መንገድ ከመናገር መቆጠብ ይኖርባችኋል። (ምሳሌ 24:29) ዳዊት ንጉሥ ሳኦል የአምላክን ምክር ከመከተል ፈቀቅ ባለበት ጊዜ እንኳ ለእሱ የነበረው አክብሮት ቀንሶ እንዳልነበር አስታውሱ። ስሜታችሁን መቆጣጠር ትችሉ ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳችሁ ጠይቁት። “ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ” ሲል ዳዊት ተናግሯል። “እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።”—መዝሙር 62:8፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:25-27
ግንባር ቀደም ሆነው የሚሠሩትን አክብሯቸው
16. ከሐሰተኛ አስተማሪዎቹና ከመላእክት ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
16 የጉባኤ ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ቢሆኑም ፍጹም ካለመሆናቸውም በላይ ስህተት ይሠራሉ። (መዝሙር 130:3፤ መክብብ 7:20፤ ሥራ 20:28፤ ያዕቆብ 3:2) በዚህም የተነሳ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በሽማግሌዎች ቅር ሊሰኙ ይችላሉ። በጉባኤ ውስጥ አንድ ጉዳይ ትክክለኛ በሆነ መንገድ እንዳልተከናወነ ሆኖ ቢሰማን ወይም ቢያንስ ቢያንስ እንደዚያ ሆኖ ቢታየን ምን ዓይነት ምላሽ ማሳየት ይኖርብናል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና በመላእክት መካከል የነበረውን ልዩነት ልብ በሉ:- “[ሐሰተኛ አስተማሪዎች] ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት [“ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ፣” NW ] በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም።” (2 ጴጥሮስ 2:9-13) ሐሰተኞቹ አስተማሪዎች “ሥልጣን ያላቸውን” ማለትም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩትን ሽማግሌዎች ሲሳደቡ መላእክት ግን በወንድሞች መካከል መከፋፈልን እየፈጠሩ የነበሩትን ሐሰተኛ አስተማሪዎች አልሰደቡም። መላእክት ከሰዎች በላቀ ቦታ ላይ የሚገኙና ከሰዎች የበለጠ የፍትሕ ስሜት ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን በጉባኤው ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ያውቁ ነበር። ሆኖም “ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ” ፍርዱን ለአምላክ ትተውታል።—ዕብራውያን 2:6, 7፤ ይሁዳ 9
17. ሽማግሌዎች ስህተት እንደሠሩ ሆኖ እንዲሰማህ የሚያደርግ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ እምነትህ ትልቅ ሚና የሚጫወተው እንዴት ነው?
17 አንድ ሁኔታ መያዝ ባለበት መንገድ ሳይያዝ ቢቀር እንኳ የክርስቲያን ጉባኤ ሕያው ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ሊኖረን አይገባምን? በራሱ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ አያውቅምን? ሁኔታውን የሚይዝበትን መንገድ ማክበርና ጉዳዮችን የመቆጣጠር ችሎታ እንዳለው አምነን መቀበል አይኖርብንምን? ‘በሌላው ግን የምንፈርድ እኛ ማን ነን?’ (ያዕቆብ 4:12፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ቆላስይስ 1:18) የሚያሳስቡህን ነገሮች ለምን በጸሎት ወደ ይሖዋ አታቀርብም?
18, 19. አንድ ሽማግሌ ስህተት እንደሠራ ሆኖ ከተሰማህ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
18 በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት አንዳንድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሽማግሌ ስህተት ሊሠራና ይህም አንዳንዶችን ሊረብሽ ይችላል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ተቻኩለን የምንወስደው እርምጃ ችግሩን ያባብሰው እንደሆነ እንጂ ሁኔታውን አይለውጠውም። መንፈሳዊ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ይሖዋ በራሱ ጊዜና መንገድ ሁኔታውን እስኪያስተካክለውና አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ተግሳጽ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ዕብራውያን 12:7-11
19 ሰላም የነሳህ አንድ ጉዳይ ተፈጥሮ ከሆነስ? ጉዳዩን በጉባኤው ውስጥ ካሉት ከሌሎች ጋር ከማውራት ይልቅ ሽማግሌዎቹ እንዲረዱህ ለምን በአክብሮት ቀርበህ አታነጋግራቸውም? ከተቺነት መንፈስ በመራቅ ስሜትህ እንዴት እንደተጎዳ ግለጽላቸው። ዘወትር ‘ራስህን በእነሱ ቦታ አድርገህ አስብ።’ በተጨማሪም ወደ እነሱ ቀርበህ ችግርህን ስትነግራቸው አክብሮት ልታሳያቸው ይገባል። (1 ጴጥሮስ 3:8 የ1980 ትርጉም ) ወደ ሽሙጥ ከማምራት ይልቅ ባላቸው ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ እምነት ይኑርህ። በደግነት መንፈስ የሚሰጡህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ በአመስጋኝነት ተቀበል። በተጨማሪም ሌሎች መወሰድ ያለባቸው የእርምት እርምጃዎች እንዳሉ ሆኖ የሚታይም ከሆነ ይሖዋ ሽማግሌዎቹ ጥሩና ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ እንደሚመራቸው እርግጠኛ ሁን።—ገላትያ 6:10፤ 2 ተሰሎንቄ 3:13
20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመረምረው ነገር ምንድን ነው?
20 ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ ያሉትን ከፍ አድርጎ ከመመልከትና ከማክበር ጋር በተያያዘ ሊጤን የሚገባው ሌላም ገጽታ አለ። በሥልጣን ላይ ያሉት በአደራ የተሰጧቸውን ማክበር አይገባቸውምን? ይህን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሥልጣን ያላቸውን እንድናከብር የሚገፋፋ ምን ጥሩ ምክንያት አለን?
• ይሖዋና ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ሥልጣን የማያከብሩ ሰዎችን የሚመለከቱት እንዴት ነው?
• ሥልጣን የተሰጣቸውን በማክበር ረገድ እነማን ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል?
• በእኛ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው ስህተት እንደሠራ ሆኖ ከታየን ምን ልናደርግ እንችላለን?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሣራ የአብርሃምን ሥልጣን በጥልቅ ታከብር የነበረ ሲሆን ደስተኛም ነበረች
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሜልኮል፣ ዳዊት የነበረውን የቤተሰብ ራስነትና የንግሥና ሥልጣን ሳታከብር ቀርታለች
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው !”
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሚያሳስቡህን ነገሮች ለምን በጸሎት ወደ ይሖዋ አታቀርብም ?