ይሖዋ የቃል ኪዳን አምላክ ነው
“ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል።” —ኤርምያስ 31:31
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ምሽት ላይ ያቋቋመው በዓል ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሞቱ ጋር አያይዞ የጠቀሰው ስለ የትኛው ቃል ኪዳን ነው?
ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ምሽት ላይ ከ12 ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የማለፍን በዓል አክብሯል። ኢየሱስ ይህ ከእነርሱ ጋር በማዕድ የሚቀመጥበት የመጨረሻ አጋጣሚ እንደሆነና ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጠላቶቹ እጅ እንደሚገደል ስለተገነዘበ ይህን ወቅት ለቅርብ ደቀ መዛሙርቱ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ለማስረዳት ተጠቅሞበታል።—ዮሐንስ 13:1–17:26
2 ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ካስወጣ በኋላ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ያከብሩት ዘንድ የታዘዙትን ብቸኛ ሃይማኖታዊ በዓል ማለትም የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያቋቋመው በዚህ ጊዜ ነበር። በጽሑፍ የሰፈረው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና:- እንካችሁ፣ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴዎስ 26:26-28) የኢየሱስ ተከታዮች የእርሱን ሞት ቀለል ባለና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሊያስቡት ይገባ ነበር። ኢየሱስ ከሞቱ ጋር በማያያዝ ስለ አንድ ቃል ኪዳን ተናግሯል። በሉቃስ ዘገባ ውስጥ “አዲስ ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል።—ሉቃስ 22:20
3. አዲሱን ቃል ኪዳን በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ተነስተዋል?
3 ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ምንድን ነው? አዲስ ቃል ኪዳን ነው ከተባለ አሮጌ ቃል ኪዳን ነበር ማለት ነው? ከዚህ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ቃል ኪዳኖችስ አሉ? ኢየሱስ የቃል ኪዳን ደሙ “ለኃጢአት ይቅርታ” የሚፈስ መሆኑን ስለተናገረ እነዚህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። እንዲህ ያለውን ይቅርታ ማግኘት ለሁላችን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።—ሮሜ 3:23
ከአብርሃም ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን
4. ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ለመረዳት የሚያስችለን ጥንት የተነገረ የትኛው ተስፋ ነው?
4 ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ለመረዳት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካከናወነበት ጊዜ 2,000 ዓመታት ገደማ ወደኋላ ተመልሰን አብራም (በኋላ አብርሃም ተብሏል) እና የአብራም ሚስት ሦራን (በኋላ ሣራ ተብላለች) ጨምሮ ታራንና ቤተሰቡ ከበለጸገችው የከለዳውያን ዑር ከተማ ወጥተው በሰሜን ሜሶጶጣሚያ ወደምትገኘው ወደ ካራን ስላቀኑበት ጊዜ መዳሰስ ያስፈልገናል። ታራ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ከዚያም የ75 ዓመቱ አብርሃም የአምላክን ትእዛዝ በመቀበል በድንኳን ውስጥ የዘላኖች ዓይነት ኑሮ ለመኖር የኤፍራጥስን ወንዝ አቋርጦ በደቡብ ምዕራብ በኩል ወደ ከነዓን ምድር ተጓዘ። (ዘፍጥረት 11:31–12:1, 4, 5፤ ሥራ 7:2-5) ይህ የሆነው 1943 ከዘአበ ነበር። አብርሃም ገና በካራን ሳለ ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” አብርሃም ወደ ከነዓን ከገባ በኋላም ይሖዋ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” ሲል ጨምሮ ነግሮታል።—ዘፍጥረት 12:2, 3, 7
5. ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ከየትኛው ታሪካዊ ትንቢት ጋር የሚዛመድ ነው?
5 ለአብርሃም የተገባለት ቃል ይሖዋ ከሰጣቸው ሌሎች ተስፋዎች ጋር የሚዛመድ ነበር። በእርግጥም ይህ የተስፋ ቃል አብርሃምን የትንቢቶች ሁሉ መጀመሪያ ከሆነው ትንቢት ጋር የሚያዛምደው ስለነበር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት አድርጎታል። አዳምና ሔዋን በኤደን የአትክልት ሥፍራ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ በሁለቱም ላይ ብያኔውን ያሳለፈ ሲሆን ሔዋንን ያሳሳታትን ሰይጣንን በዚያው ጊዜ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ሲል ተናግሮታል። (ዘፍጥረት 3:15) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን የሰይጣንን ሥራ የሚያፈርሰው ዘር በዚህ የእምነት አባት የዘር መስመር እንደሚመጣ የሚጠቁም ነበር።
6. (ሀ) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው በማን በኩል ነው? (ለ) የአብርሃም ቃል ኪዳን ምንድን ነው?
6 ይሖዋ የሰጠው የተስፋ ቃል ከዘር ጋር ተዛምዶ ያለው ስለነበር አብርሃም ይህን ዘር ለማስገኘት እንዲችል ልጅ ሊኖረው ያስፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ እርሱና ሣራ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ልጅም አልነበራቸውም። ሆኖም የኋላ ኋላ ይሖዋ የመራቢያ ኃይላቸው በተዓምራዊ ሁኔታ እንዲታደስና ሣራ ለአብርሃም፣ ይስሐቅ የሚባል ወንድ ልጅ እንድትወልድለት በማድረግ ስለባረካቸው አንድ ዘር እንደሚመጣ የገባው የተስፋ ቃል ሕያው እንዲሆን አድርጓል። (ዘፍጥረት 17:15-17፤ 21:1-7) በጣም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ እስከመጠየቅ ድረስ የአብርሃምን እምነት ከፈተነው በኋላ ይሖዋ ከብዙ ዓመታት በፊት የገባውን ቃል እንደሚከተለው በማለት በድጋሚ አረጋገጠለት:- “በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችህን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ፣” NW]፣ ቃሌን ሰምተሃልና።” (ዘፍጥረት 22:15-18) ይህ ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ተስፋ አብዛኛውን ጊዜ የአብርሃም ቃል ኪዳን በመባል የሚጠራ ሲሆን የኋለኛው አዲስ ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር በቅርብ የሚዛመድ ይሆናል።
7. የአብርሃም ዘር በቁጥር እየጨመረ መሄድ የጀመረው እንዴት ነው? በግብጽ ነዋሪዎች ለመሆን ያበቋቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
7 ከጊዜ በኋላ ይስሐቅ ሁለት መንትያ ወንዶች ልጆች ማለትም ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ይሖዋ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ቅድመ አያት እንዲሆን የመረጠው ያዕቆብን ነበር። (ዘፍጥረት 28:10-15፤ ሮሜ 9:10-13) ያዕቆብ 12 ልጆች ነበሩት። ከዚህ በኋላ የአብርሃም ዘር በቁጥር እያደገ እንደሚሄድ ግልጽ ነበር። የያዕቆብ ልጆች ለአካለ መጠን ደርሰው በነበረበትና ብዙዎቹም የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው መኖር በጀመሩበት ጊዜ በረሃብ ምክንያት ሁሉም ወደ ግብጽ ለመሰደድ ተገደዱ። በዚያም የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በመለኮታዊ ድጋፍ መንገዱን አመቻችቶ ነበር። (ዘፍጥረት 45:5-13፤ 46:26, 27) ከጥቂት ዓመታት በኋላ በከነዓን የነበረው ረሃብ አቆመ። ይሁን እንጂ የያዕቆብ ቤተሰብ መጀመሪያ በእንግድነት ከዚያም በባርነት ግብጽ ውስጥ ቆየ። ሙሴ የያዕቆብን ዝርያዎች ከግብጽ እየመራ ነፃ ያወጣቸው በ1513 ከዘአበ ማለትም አብርሃም የኤፍራጥስን ወንዝ ከተሻገረ ከ430 ዓመታት በኋላ ነበር። (ዘጸአት 1:8-14፤ 12:40, 41፤ ገላትያ 3:16, 17) ከዚህ በኋላ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።—ዘጸአት 2:24፤ 6:2-5
‘አሮጌው ቃል ኪዳን’
8. ይሖዋ በሲና ከያዕቆብ ዝርያዎች ጋር የተጋባው ቃል ምንድን ነው? ይህስ ከአብርሃም ቃል ኪዳን ጋር ምን ዝምድና አለው?
8 ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ሲገቡ አንድ ትልቅ ቤተሰብ የነበሩ ቢሆንም ልጆቻቸው ግብጽን ለቅቀው ሲወጡ ግን ብዙ ሕዝብ ያቀፉ ነገዶች ሆነው ነበር። (ዘጸአት 1:5-7፤ 12:37, 38) ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ከነዓን ከማስገባቱ በፊት በአረቢያ ምድር ወደሚገኘው የኮሬብ (ወይም ሲና) ተራራ ግርጌ በደቡብ በኩል መራቸው። በዚያም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ይህ ቃል ኪዳን ‘ከአዲሱ ቃል ኪዳን’ አንጻር “ብሉይ [አሮጌ] ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 3:14) ይሖዋ በአሮጌው ቃል ኪዳን አማካኝነት ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።
9. (ሀ) ይሖዋ በአብርሃም ቃል ኪዳን አማካኝነት እንደሚያከናውናቸው ቃል የገባቸው አራት ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ይሖዋ ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ምን ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ከፍቷል? ይህ የሚሆነውስ ምን ቅድመ ሁኔታ ከተሟላ ነው?
9 ይሖዋ የዚህን ቃል ኪዳን ስምምነት ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” (ዘጸአት 19:5, 6) ይሖዋ የአብርሃም ዘር (1) ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን፣ (2) በጠላቶቹ ላይ ድል እንደሚቀዳጅ፣ (3) የከነዓንን ምድር እንደሚወርስ እንዲሁም (4) አሕዛብ የሚባረኩበት መስመር እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር። አሁን ደግሞ እስራኤላውያን ትእዛዛቱን የሚጠብቁ ከሆነ የእርሱ ልዩ ሕዝብ ማለትም “የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ” ሆነው እነርሱ ራሳቸው እነዚህን በረከቶች እንደሚወርሱ ገለጸላቸው። እስራኤላውያን በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ለመግባት ተስማምተው ነበርን? እንደ አንድ ሰው ሆነው “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መልሰዋል።—ዘጸአት 19:8
10. ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር መልክ ያደራጃቸው እንዴት ነው? ምን እንዲያደርጉስ ይጠብቅባቸው ነበር?
10 ከዚህ በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ አደራጃቸው። አምልኮአቸውንም ሆነ ማኅበራዊ ኑሯቸውን የሚመሩበት ሕግ ሰጣቸው። በተጨማሪም የመገናኛ ድንኳንና (በኋላም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ) በውስጡ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የክህነት አገልግሎት አዘጋጀላቸው። ቃል ኪዳኑን መጠበቅ ማለት የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ በተለይም ደግሞ እርሱን ብቻ ማምለክ ማለት ነበር። ለእነዚያ ሕጎች አስኳል የሆነውና ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል መጀመሪያ የተጠቀሰው ሕግ የሚከተለው ነበር:- “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ።”—ዘጸአት 20:2, 3
በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት የሚገኙ በረከቶች
11, 12. በአሮጌው ቃል ኪዳን ውስጥ የተሰጡት ተስፋዎች ለእስራኤላውያን የተፈጸሙላቸው በምን መንገዶች ነው?
11 በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠባቸው ነገሮች ለእስራኤላውያን ተፈጽመውላቸዋልን? እስራኤል “የተቀደሰ ሕዝብ” ሆኗልን? እስራኤላውያን የአዳም ልጆች እንደመሆናቸው መጠን ኃጢአተኞች ነበሩ። (ሮሜ 5:12) ሆኖም በሕጉ ሥር ኃጢአታቸውን ለመሸፈን መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። በዓመታዊው የስርየት ቀን የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች በሚመለከት ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተሰሪያ ይሆንላችኋልና . . . በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።” (ዘሌዋውያን 16:30) በመሆኑም እስራኤላውያን የታመኑ ሆነው ሲገኙ ለይሖዋ አገልግሎት የጸዱ ቅዱስ ሕዝብ ይሆኑ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ንጽሕናቸው የተመካው ሕጉን በመታዘዛቸውና መሥዋዕቶችን ማቅረባቸውን በመቀጠላቸው ላይ ነበር።
12 የእስራኤል ብሔር “የካህናት መንግሥት” ሆኖ ነበርን? ገና ከጅምሩ አንስቶ ይሖዋ ሰማያዊ ንጉሡ የሆነለት መንግሥት ነበር። (ኢሳይያስ 33:22) ከዚህም በተጨማሪ የሕጉ ቃል ኪዳን ሰብዓዊ ነገሥታት መግዛት የሚችሉበትንም ዝግጅት ያቀፈ ነበር፤ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ መቀመጫቸውን ኢየሩሳሌም ያደረጉ ነገሥታት ይሖዋን በመወከል አስተዳድረዋል። (ዘዳግም 17:14-18) ይሁን እንጂ የእስራኤል ብሔር የካህናት መንግሥት ነበርን? በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የሚቀርብበት የክህነት ሥርዓት ነበር። የመገናኛው ድንኳን (በኋላም ቤተ መቅደሱ) ለእስራኤላውያኑም ሆነ እስራኤላዊ ላልሆኑት ሰዎች የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። እንዲሁም ብሔሩ ለሰው ዘር የተገለጠው እውነት የሚተላለፍበት ብቸኛ መስመር ነበር። (2 ዜና መዋዕል 6:32, 33፤ ሮሜ 3:1, 2) ሌዋውያን ካህናቱ ብቻ ሳይሆኑ የታመኑት እስራኤላውያን በሙሉ የይሖዋ ‘ምሥክሮች’ ነበሩ። የእስራኤል ብሔር ‘ምስጋናውን እንዲነግር’ የተቋቋመ የይሖዋ “ባሪያ” ነበር። (ኢሳይያስ 43:10, 21) አንዳንድ ትሑት መጻተኞች ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል ያደረገውን የኃይል መግለጫ በማስተዋል ወደ ንጹሕ አምልኮው ተስበዋል። ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል። (ኢያሱ 2:9-13) ይሁን እንጂ ቅቡዓን ካህናት ሆነው ያገለግሉ የነበሩት የአንድ ነገድ አባላት ብቻ ነበሩ።
በእስራኤላውያን መካከል የነበሩ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች
13, 14. (ሀ) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች የሕጉ ቃል ኪዳን ተካፋዮች አልነበሩም ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች ከሕጉ ቃል ኪዳን በታች የነበሩት እንዴት ነው?
13 ወደ ይሁዲነት የተለወጡት እነዚህ ሰዎች ምን ቦታ ነበራቸው? ይሖዋ ቃል ኪዳኑን ያደረገው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ብቻ ነበር፤ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በቦታው የተገኘ ቢሆንም የቃል ኪዳኑ ተካፋይ ተደርጎ አልተጠቀሰም። (ዘጸአት 12:38፤ 19:3, 7, 8) የእስራኤል በኩሮች የቤዛነት ዋጋ ሲሰላ የእነርሱ በኩሮች አልተቆጠሩም። (ዘኁልቁ 3:44-51) ከአሥርተ ዓመታት በኋላም የከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን ነገዶች ሲከፋፈል እስራኤላዊ ላልሆኑት አማኞች የተሰጠ ርስት አልነበረም። (ዘፍጥረት 12:7፤ ኢያሱ 13:1-14) ለምን? ምክንያቱም የሕጉ ቃል ኪዳን የተደረገው ወደ ይሁዲነት ከተለወጡት ሰዎች ጋር አልነበረም። ይሁን እንጂ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ወንዶች ሕጉን በመታዘዝ ይገረዙ ነበር። የሕጉን መመሪያዎች ይታዘዙና ከዝግጅቶቹ ይጠቀሙ ነበር። ወደ ይሁዲነት የተለወጡትም ሆኑ እስራኤላውያኑ ከሕጉ ቃል ኪዳን በታች ነበሩ።—ዘጸአት 12:48, 49፤ ዘኁልቁ 15:14-16፤ ሮሜ 3:19
14 ለምሳሌ ያህል ወደ ይሁዲነት የተለወጠ አንድ ሰው ድንገት ሰው ቢገድል እንደ ሌላው እስራኤላዊ ሁሉ እርሱም ወደ አንደኛው የመማጸኛ ከተማ መሸሽ ይችል ነበር። (ዘኁልቁ 35:15, 22-25፤ ኢያሱ 20:9) በስርየት ቀን “ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ” አንድ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች የጉባኤው አባል እንደመሆናቸው መጠን በሥርዓቱ ይካፈሉና የመሥዋዕቱም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:7-10, 15, 17, 29፤ ዘዳግም 23:7, 8) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች በሕጉ ሥር ከእስራኤላውያን ጋር በቅርብ የተሳሰሩ በመሆናቸው በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት እስራኤላውያን በመጀመሪያው ‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ’ በተከፈተላቸው ጊዜ ወደ ይሁዲነት የተለወጡትም ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ መሠረት ‘ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረው የአንጾኪያው ኒቆላዎስ’ ክርስቲያን ከመሆኑም ሌላ የኢየሩሳሌምን ጉባኤ ጉዳይ እንዲከታተሉ ከተሾሙት ‘በመልካም የተመሠከረላቸው ሰባት ወንዶች መካከል’ ሊሆን ችሏል።—ማቴዎስ 16:19፤ ሥራ 2:5-10፤ 6:3-6፤ 8:26-39
ይሖዋ የአብርሃምን ዘር ባረከ
15, 16. ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
15 ይሖዋ የእምነት አባት ለሆነው ለአብርሃም በገባው ቃል መሠረት በሕጉ ሥር በብሔር መልክ የተደራጁትን የአብርሃም ዝርያዎች ባርኳቸዋል። በ1473 ከዘአበ በሙሴ እግር በተተካው በኢያሱ መሪነት እስራኤላውያኑ ወደ ከነዓን ምድር ገብተዋል። ከዚያ በኋላ የተከናወነው ምድሪቱን በየነገዱ የመከፋፈሉ ሥራ ይሖዋ ምድሪቱን ለአብርሃም ዘር እንደሚሰጥ የገባውን ቃል ያስፈጸመ ነበር። የእስራኤል ብሔር የታመነ ሆኖ ሲገኝ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ የገባላቸውን ቃል ይጠብቅ ነበር። ይህ በተለይ በንጉሥ ዳዊት የግዛት ዘመን በተግባር ታይቷል። በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ዘመን ደግሞ የአብርሃም ቃል ኪዳን ሦስተኛ ዘርፍ ፍጻሜውን አግኝቷል። “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሏቸው ነበር።”—1 ነገሥት 4:20
16 ይሁንና አሕዛብ የአብርሃም ዘር በሆነው በእስራኤል ብሔር አማካኝነት ራሳቸውን የሚባርኩት እንዴት ነው? ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የእስራኤል ብሔር በሌሎች አሕዛብ መካከል ይሖዋን የሚወክል የእርሱ ልዩ ሕዝብ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ “እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 32:43) ብዙ መጻተኞች ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እስራኤላውያንን ተከትለው ከግብጽ ከመውጣታቸውም ሌላ ይሖዋ በምድረ በዳ ኃይሉን ሲያሳይ የዓይን ምሥክር ነበሩ፤ እንዲሁም ሙሴ ያቀረበውን ደስ ይበላችሁ የሚለውን ጥሪ ሰምተዋል። (ዘጸአት 12:37, 38) ከጊዜ በኋላ ሞዓባዊቷ ሩት እስራኤላዊውን ቦዔዝን አግብታ የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን ችላለች። (ሩት 4:13-22) በትውልድ አይሁዳዊ የሆኑ ብዙዎች የታመኑ ሳይሆኑ በቀሩበት ጊዜ ቄናዊው ኢዮናዳብና ልጆቹ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ከትክክለኛው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ተጣብቀው የሚመላለሱ ሰዎች መሆናቸውን አሳይተዋል። (2 ነገሥት 10:15-17፤ ኤርምያስ 35:1-19፤ 38:7-13) በፋርስ ግዛት ሥር የነበሩ ብዙ መጻተኞች ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሲሆን ከእስራኤል ጋር ወግነው ጠላቶቻቸውን ተዋግተውላቸዋል።—አስቴር 8:17 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
አዲስ ቃል ኪዳን አስፈለገ
17. (ሀ) ይሖዋ የእስራኤልን ሰሜናዊና ደቡባዊ መንግሥታት የተዋቸው ለምንድን ነው? (ለ) አይሁዳውያን ጨርሶ እንዲተዉ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
17 ይህም ሆኖ አምላክ የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም የአምላክ ልዩ ብሔር የታመነ ሆኖ መገኘት ያስፈልገው ነበር። ሆኖም የታመነ ሆኖ አልተገኘም። እርግጥ ነው ድንቅ እምነት ያሳዩ እስራኤላውያን ነበሩ። (ዕብራውያን 11:32–12:1) ይሁን እንጂ ብሔሩ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወደ አረማዊ አማልክት ፊቱን ያዞረባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። (ኤርምያስ 34:8-16፤ 44:15-18) ግለሰቦች ሕጉን አላግባብ ተጠቅመውበታል አለዚያም ቸል ብለውታል። (ነህምያ 5:1-5፤ ኢሳይያስ 59:2-8፤ ሚልክያስ 1:12-14) ከሰሎሞን ሞት በኋላ እስራኤል በሰሜኑና በደቡቡ መንግሥት ለሁለት ተከፈለች። የሰሜኑ መንግሥት ጨርሶ ዓመፀኛ በሆነ ጊዜ ይሖዋ “አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ” ሲል ተናግሯል። (ሆሴዕ 4:6) የደቡቡም መንግሥት ቃል ኪዳኑን ሳያከብር በመቅረቱ ከባድ ቅጣት ደርሶበታል። (ኤርምያስ 5:29-31) አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉ ጊዜ እርሱም እንዲሁ ትቷቸዋል። (ሥራ 3:13-15፤ ሮሜ 9:31–10:4) በመጨረሻ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አዲስ ዝግጅት አደረገ።—ሮሜ 3:20
18, 19. ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ሲል ምን አዲስ ዝግጅት አድርጓል?
18 ይህ አዲስ ዝግጅት አዲሱ ቃል ኪዳን ነው። ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ስለዚህ ቃል ኪዳን ትንቢት መናገሩ ነበር:- “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ . . . ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።”—ኤርምያስ 31:31-33
19 ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ቀን የጠቀሰው አዲስ ቃል ኪዳን ይህ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህ ተስፋ የተሰጠበት ቃል ኪዳን በኢየሱስ መካከለኛነት በደቀ መዛሙርቱና በይሖዋ መካከል የሚደረግ መሆኑን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 11:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5፤ ዕብራውያን 12:24) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንደምናየው በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ይበልጥ ክብራማ የሆነና ዘላቂ ፍጻሜውን ያገኛል።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ምን ቃል ገብቷል?
◻ ይሖዋ የአብርሃም ቃል ኪዳን በሥጋዊ እስራኤላውያን ላይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?
◻ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ከአሮጌው ቃል ኪዳን የተጠቀሙት እንዴት ነው?
◻ አዲስ ቃል ኪዳን ያስፈለገው ለምን ነበር?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት የአብርሃም ቃል ኪዳን የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል