ምዕራፍ 24
“ከአምላክ ፍቅር ሊለየን” የሚችል ነገር የለም
1. አንዳንድ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት አፍራሽ ስሜት ይሰማቸዋል?
ይሖዋ አንተን እንደሚወድህ ይሰማሃል? አንዳንዶች ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው አምላክ በጥቅሉ የሰውን ዘር እንደሚወድ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ‘አምላክ እኔን በግለሰብ ደረጃ ሊወደኝ አይችልም’ ብለው ያስባሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንኳ አልፎ አልፎ እንዲህ ያለ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረበት አንድ ሰው “አምላክ ስለ እኔ ያስባል ብዬ ማመን ይከብደኛል” ሲል ተናግሯል። አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት ይሰማሃል?
2, 3. ‘ይሖዋ አይወደኝም ወይም ከቁብ አይቆጥረኝም’ ብለን እንድናስብ የሚፈልገው ማን ነው? እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ መዋጋት የምንችለውስ እንዴት ነው?
2 ሰይጣን ‘ይሖዋ አይወደኝም ወይም ከቁብ አይቆጥረኝም’ ብለን እንድናስብ ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የትዕቢትና የኩራት መንፈስ እንዲያድርባቸው በማድረግ እንደሚያስት የታወቀ ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ይሁን እንጂ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡና የከንቱነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግም ያስደስተዋል። (ዮሐንስ 7:47-49፤ 8:13, 44) በተለይ ደግሞ ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ይህን ዘዴ በእጅጉ እየተጠቀመበት ይገኛል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ያደጉት ‘ፍቅር በሌለበት’ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ሌሎች ደግሞ የዕለት ተዕለት ውሏቸው ጨካኝ፣ ራስ ወዳድና ግትር ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አንዳንዶች ለብዙ ዓመታት ሲደርስባቸው የኖረው ግፍ፣ የዘር መድልዎ ወይም ጥላቻ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው አሊያም ደግሞ የሚወዳቸው እንደሌለ ሆኖ እንዲሰማቸው አድርጓቸው ሊሆን ይችላል።
3 እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ። ብዙዎቻችን አንዳንድ ጊዜ አላግባብ ራሳችንን እንኮንናለን። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል “ነገሮችን ለማቅናት” እና “ምሽግን ለመደርመስ” ማለትም ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ለማስወገድ እንደሚረዳ አስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4) መጽሐፍ ቅዱስ “[ልባችን] በፊቱ እንዲረጋጋ እናደርጋለን፤ ይህን የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ልባችን እንዲረጋጋ’ ማለትም ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርጉ አራት አሳማኝ ነጥቦችን ይጠቅሱልናል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።
በይሖዋ ፊት ውድ ነህ
4, 5. ኢየሱስ ድንቢጦችን አስመልክቶ የተናገረው ምሳሌ በይሖዋ ፊት ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?
4 በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።” (ማቴዎስ 10:29-31) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን ትርጉም እንደነበራቸው ተመልከት።
5 ‘አንድ ሰው ድንቢጥ የሚገዛበት ምን ምክንያት አለ?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። በኢየሱስ ዘመን ለምግብነት ይሸጡ ከነበሩት ወፎች ሁሉ በጣም ርካሿ ድንቢጥ ነበረች። አንድ ሰው በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ባላት አንድ ሳንቲም ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል እንደነበረ ልብ በል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በኋላ እንደገለጸው አንድ ሰው ሁለት ሳንቲሞች ከከፈለ አራት ሳይሆን አምስት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር። አምስተኛዋ ወፍ ምንም ዋጋ እንደሌለው ነገር በምርቃት መልክ የምትሰጥ ናት። እነዚህ ፍጥረታት በሰዎች ፊት ዋጋ አይኖራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ፈጣሪ ለእነዚህ ፍጥረታት ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ኢየሱስ “አንዷም እንኳ [በምርቃት መልክ የምትሰጠው እንኳ ሳትቀር] በአምላክ ዘንድ አትረሳም” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 12:6, 7) ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ምን ማለት እንደፈለገ መረዳት እንችላለን። ይሖዋ ለአንዲት ድንቢጥ እንኳ ይህን ያህል ዋጋ የሚሰጥ ከሆነ ሰውንማ ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት መገመት አያዳግትም! ኢየሱስ እንደገለጸው ይሖዋ ስለ እኛ እያንዳንዷን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። የራሳችን ፀጉር እንኳ ሳይቀር የተቆጠረ ነው!
6. ኢየሱስ የራሳችን ፀጉር እንኳ የተቆጠረ እንደሆነ ሲናገር ማጋነኑ እንዳልነበር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
6 ፀጉር ደግሞ ይቆጠራል እንዴ? አንዳንዶች እዚህ ላይ ኢየሱስ በጣም እንዳጋነነ አድርገው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ ስለ ትንሣኤ ተስፋ አስብ። ይሖዋ እኛን መልሶ የሚፈጥረን ምን ያህል ቢያውቀን ነው! በእሱ ፊት ውድ በመሆናችን ጀነቲካዊ ንድፋችንን እንዲሁም የብዙ ዓመት ትዝታዎቻችንንና በሕይወታችን ውስጥ የተከናወኑ ነገሮችን ጨምሮ እያንዳንዷን ነገር በሚገባ ያስታውሳል።a ከዚህ አንጻር ሲታይ በአማካይ 100,000 ገደማ የሚሆነውን ፀጉራችንን መቁጠር በጣም ቀላል ነገር ነው።
ይሖዋ እኛን ሲመረምር የሚያተኩረው በምን ላይ ነው?
7, 8. (ሀ) ይሖዋ የሰዎችን ልብ በሚመረምርበት ጊዜ የሚደሰተው የትኞቹን ባሕርያት ሲመለከት ነው? (ለ) ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
7 በሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አገልጋዮቹን በሚመረምርበት ጊዜ ትኩረት የሚያደርገው በምን ነገር ላይ እንደሆነ ይገልጻል። በአጭር አነጋገር ይሖዋ መልካም ባሕርያችንንና የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ልጁን ሰለሞንን “ይሖዋ ልብን ሁሉ ይመረምራልና፤ ሐሳብንና ውስጣዊ ዝንባሌን ሁሉ ይረዳል” ብሎታል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) አምላክ ዓመፀኛ በሆነውና በጥላቻ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ በሚመረምርበት ጊዜ ሰላምን፣ እውነትንና ጽድቅን የሚወድ ልብ ሲያገኝ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ይሖዋ እሱን የሚወድ እንዲሁም ስለ እሱ ለመማርና እንዲህ ያለውን እውቀት ለሌሎች ማካፈል የሚፈልግ ልብ ሲያገኝ ምን ያደርጋል? ይሖዋ ስለ እሱ ለሌሎች የሚናገሩ ሰዎችን በትኩረት እንደሚመለከት ተናግሯል። እንዲያውም እሱን “ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ” ሰዎች ያዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” አለው። (ሚልክያስ 3:16) እንዲህ ያሉት ባሕርያት በይሖዋ ፊት የተወደዱ ናቸው።
8 ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ መልካም ሥራዎች ምንድን ናቸው? ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥሮስ 2:21) አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው አንዱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ነው። ሮም 10:15 “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” ይላል። እርግጥ ብዙ ጊዜ እግሮቻችን “ያማሩ” ወይም ውብ እንደሆኑ አድርገን አናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሱት እግሮች የሚያመለክቱት የይሖዋ አገልጋዮች ምሥራቹን ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ነው። እንዲህ ያለው ጥረት በይሖዋ ፊት ያማረና የተወደደ ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
9, 10. (ሀ) ይሖዋ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት ለመቋቋም የምናደርገውን ጥረት እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በተመለከተ ምን ዓይነት አፍራሽ አመለካከት የለውም?
9 ይሖዋ የምናሳየውን ጽናትም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ማቴዎስ 24:13) ሰይጣን ይሖዋን ማምለክህን እንድትተው እንደሚፈልግ አስታውስ። እያንዳንዱን ቀን ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ የምታሳልፍ ከሆነ ይሖዋን ለሚነቅፈው ለሰይጣን መልስ በመስጠት ረገድ የበኩልህን አስተዋጽኦ ታደርጋለህ። (ምሳሌ 27:11) ይሁንና ጸንቶ መኖር ቀላል አይደለም። የጤና እክል፣ የኑሮ ውድነት፣ ጭንቀትና ሌሎች ችግሮች እያንዳንዱን ቀን ፈታኝ ሊያደርጉብን ይችላሉ። በተጨማሪም የጠበቅነው ነገር እንዳሰብነው ቶሎ አለመፈጸሙ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። (ምሳሌ 13:12) እንዲህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ስንጸና ይሖዋ እጅግ ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን “እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም” በማለት የጠየቀው ለዚህ ነው። አክሎም “ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?” ሲል በእርግጠኝነት ተናግሯል። (መዝሙር 56:8) አዎን፣ ይሖዋ ከእሱ ጎን በታማኝነት ለመቆም ስንል የምናፈስሰውን እንባና የሚደርስብንን ሥቃይ ፈጽሞ አይረሳም። እንዲህ ያለውን መከራና ሥቃይ በጽናት ለመቋቋም የምናደርገው ጥረት በይሖዋ ዘንድ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል።
የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም የምናሳየውን ጽናት ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
10 ይሁንና ራሱን የሚኮንን ልብ በአምላክ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆንን የሚያሳየውን ይህን ማስረጃ ላይቀበል ይችላል። ‘ከእኔ ይበልጥ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ አገልጋዮች አሉ። ይሖዋ እኔን ከእነሱ ጋር ሲያነጻጽረኝ ምንኛ ያዝንብኝ ይሆን!’ እያለ ራሱን ሊኮንን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ አንዱን ከሌላው አያወዳድርም፤ በተጨማሪም ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። (ገላትያ 6:4) ልባችንን ጠልቆ የመመርመር ችሎታ ያለው ሲሆን ያለንን ማንኛውም መልካም ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከታል።
ይሖዋ መልካም ጎናችንን አበጥሮ ያወጣዋል
11. ይሖዋ ለአቢያህ ካደረገው ነገር ምን ልንማር እንችላለን?
11 በሦስተኛ ደረጃ ይሖዋ ልባችንን በሚመረምርበት ጊዜ መልካም ጎናችንን አበጥሮ ያወጣዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሃዲ የሆነው የንጉሥ ኢዮርብዓም ሥርወ መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ በወሰነ ጊዜ ከንጉሡ ልጆች አንዱ የሆነው አቢያህ በወግ በማዕረግ መቀበር እንዳለበት ተናግሮ ነበር። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ . . . አንድ መልካም ነገር [አግኝቶበታል]” ይላል። (1 ነገሥት 14:1, 10-13) ይሖዋ የአቢያህን ልብ በመመርመር ያለውን “መልካም ነገር” አበጥሮ አውጥቶታል። በአቢያህ ልብ ውስጥ የተገኘው መልካም ነገር ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ይሖዋ ከፍ አድርጎ ስለተመለከተው በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። አልፎ ተርፎም የዚያ ከሃዲ ቤተሰብ አባል ለነበረው ለዚህ ልጅ ተገቢውን ምሕረት በማሳየት ክሶታል።
12, 13. (ሀ) ይሖዋ ለንጉሥ ኢዮሳፍጥ ያደረገው ነገር ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜም እንኳ መልካም ጎናችንን እንደሚመለከት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ለመልካም ባሕርያችንና ሥራዎቻችን ምን አመለካከት አለው?
12 ይሖዋ ጥሩ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮሳፍጥ ያደረገው ነገር በዚህ ረገድ የተሻለ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ ማስተዋል የጎደለው ድርጊት በፈጸመ ጊዜ የይሖዋ ነቢይ “በዚህ ምክንያት ይሖዋ በአንተ ላይ ተቆጥቷል” ብሎታል። ይህ እንዴት የሚያስደነግጥ አነጋገር ነው! ይሁን እንጂ ይሖዋ በነቢዩ በኩል ያስተላለፈው መልእክት በዚህ አላበቃም። “ይሁንና . . . መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (2 ዜና መዋዕል 19:1-3) በመሆኑም ይሖዋ የጽድቅ ቁጣው የኢዮሳፍጥን መልካም ነገር እንዳያይ አላገደውም። ይሖዋ ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች ምንኛ የተለየ ነው! ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሲያበሳጩን መልካም ጎናቸው አይታየንም። ራሳችንም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሚሰማን ሐዘን፣ ኀፍረትና የጥፋተኝነት ስሜት መልካም ጎናችን እንዳይታየን ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ንስሐ ከገባንና የሠራነውን ኃጢአት ላለመድገም ጥረት ካደረግን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን አስታውስ።
13 አንድ የወርቅ ማዕድን የሚፈልግ ሰው ወርቁን ብቻ እየለየ በማስቀረት አላስፈላጊ የሆነውን ኮረት እንደሚያስወግድ ሁሉ ይሖዋም ልብህን በሚመረምርበት ጊዜ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶችን እየለየ ያስወግዳል። መልካም ባሕርያትህንና ሥራዎችህንስ ምን ያደርጋል? እነዚህን እንደ “ተፈላጊ ማዕድናት” ለይቶ ያስቀራቸዋል! አፍቃሪ የሆኑ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በሕፃንነታቸው የሣሏቸውን ሥዕሎች ወይም የሠሯቸውን የእጅ ሥራዎች እንደ ማስታወሻ አድርገው ለረጅም ዓመታት እንደሚያስቀምጡ አስተውለሃል? ምናልባትም ልጆቹ እነዚህን ነገሮች ረስተዋቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ደግሞ ከሁሉ ይበልጥ አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ነው። ከእሱ ጎን በታማኝነት እስከቆምን ድረስ መልካም ሥራዎቻችንንና ባሕርያታችንን ፈጽሞ አይረሳም። እንዲያውም እንዲህ ያሉ ነገሮችን መርሳት በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ እንደማዛባት ይቆጠራል፤ እሱ ደግሞ ፍትሕ አያዛባም። (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ መልካም ጎናችንን አበጥሮ የሚያወጣበት ሌላም መንገድ አለ።
14, 15. (ሀ) ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ይሖዋ መልካም ጎናችንን እንዳያይ ሊያግደው የማይችለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ይሖዋ መልካም ባሕርያችን ምን እንዲሆን ያደርጋል? ታማኝ አገልጋዮቹን የሚመለከታቸውስ እንዴት ነው?
14 ይሖዋ ካለብን አለፍጽምና ባሻገር ይመለከታል፤ ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንችል ያስተውላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሥዕሎች ወይም ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በለንደን ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ባለው 30 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚያወጣ የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ሥዕል ላይ ተኩሶ ጉዳት አድርሶ ነበር፤ ይሁንና ይህ ሥዕል ጉዳት ስለደረሰበት መጣል አለበት ያለ ሰው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ወደ 500 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያስቆጠረውን ይህን ድንቅ የጥበብ ሥራ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ወዲያውኑ ጥረት ማድረግ ተጀመረ። ለምን? ምክንያቱም በሥነ ጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ በጣም ውድ ስለሆነ ነው። ታዲያ አንተ በእርሳስ ከተሳለ ሥዕል እጅግ አትበልጥም? በወረስከው አለፍጽምና ምክንያት እንከን ቢኖርብህም እንኳ በአምላክ ፊት የላቀ ዋጋ እንዳለህ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 72:12-14) የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ጥበበኛው አምላክ ይሖዋ፣ ለፍቅራዊ እንክብካቤው ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ወደ ፍጽምና ደረጃ ለመመለስ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አይልም።—የሐዋርያት ሥራ 3:21፤ ሮም 8:20-22
15 አዎን፣ ይሖዋ እኛ ራሳችን እንኳ ሳናስተውለው የምንቀረውን መልካም ጎናችንን ይመለከታል። በተጨማሪም እሱን በታማኝነት ማገልገላችንን ከቀጠልን ፍጽምና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ መልካም ባሕርያችን እየዳበረ እንዲሄድ ያደርጋል። የሰይጣን ዓለም ለእኛ ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደከበሩ ነገሮች አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ሐጌ 2:7
ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር ያሳያል
16. ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ምንድን ነው? ይህስ ለእያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ስጦታ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
16 በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ብዙ ነገር አድርጓል። ሰይጣን፣ ‘ይሖዋ አይወዳችሁም’ ወይም ‘በአምላክ ፊት ዋጋ የላችሁም’ እያለ ለሚያስፋፋው ውሸት የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አጥጋቢ መልስ ይሆናል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት የደረሰበት ሥቃይም ሆነ ይሖዋ የሚወደው ልጁ ሲሞት ዝም ብሎ ማየቱ ያስከተለበት ከዚያ የባሰ ሥቃይ ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚወዱን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች ይህ መሥዋዕት ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ማመን ይከብዳቸዋል። ይህ ፈጽሞ እንደማይገባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ እንደነበረ አስታውስ። ሆኖም ‘የአምላክ ልጅ ወድዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ በማለት ተናግሯል።—ገላትያ 1:13፤ 2:20
17. ይሖዋ ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበን እንዴት ነው?
17 ይሖዋ ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚዎች እንድንሆን በግለሰብ ደረጃ በመርዳት ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) አዎን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ወደ ልጁና ወደ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ይስበናል። እንዴት? በግለሰብ ደረጃ ምሥክርነቱ እንዲደርሰን አድርጓል፤ እንዲሁም የአቅም ገደብና አለፍጽምና ቢኖርብንም እንኳ መንፈሳዊ እውነቶችን ማስተዋልና ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል በቅዱስ መንፈሱ ይረዳናል። ይሖዋ እስራኤልን በተመለከተ “በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ። ከዚህም የተነሳ በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ” ሲል እንደተናገረ ሁሉ ለእኛም እንዲሁ ሊናገር ይችላል።—ኤርምያስ 31:3
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ልናይ የምንችልበት ትልቁ መንገድ ምንድን ነው? ይህን ጉዳይ የሚከታተለው ራሱ እንደሆነ የሚያሳየውስ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ቃል ይሖዋ ችግራችንን እንደ ራሱ አድርጎ በማየት ጸሎታችንን እንደሚያዳምጥ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?
18 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚወደን ልናይ የምንችልበት ትልቁ መንገድ የጸሎት መብት ነው ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ እያንዳንዳችንን ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማል። እንዲያውም “ጸሎት ሰሚ” ተብሏል። (መዝሙር 65:2) ይህን ሥልጣን ለማንም፣ ሌላው ቀርቶ ለልጁ እንኳ አልሰጠም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስበው፤ የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው አምላክ ሳንሸማቀቅ የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው እየጋበዘን ነው። ጸሎታችንን የሚሰማውስ እንዴት ነው? በግድየለሽነትና በቀዘቀዘ ስሜት ነው? በፍጹም።
19 ይሖዋ የሌሎችን ችግር እንደ ራሱ አድርጎ የሚያይ አምላክ ነው። አንድ በዕድሜ የገፉ ታማኝ ክርስቲያን ይህን ባሕርይ ሲገልጹት “በአንተ ሥቃይ የእኔም ልብ ይታመማል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሖዋ የእኛ ሥቃይ ይሰማዋል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቡ በእስራኤላውያን ላይ የደረሰውን ሥቃይ ሲመለከት ምን እንደተሰማው ሲገልጽ “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” ይላል። (ኢሳይያስ 63:9) ይሖዋ እንዲሁ ችግራቸውን መመልከት ብቻ ሳይሆን እሱም አብሮ ተሠቃይቷል። “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” በማለት ለአገልጋዮቹ የተናገረው ቃል ሥቃያቸው ምን ያህል እንደሚሰማው በግልጽ የሚያሳይ ነው።b (ዘካርያስ 2:8) የዓይን ብሌን ሲነካ ምን ያህል እንደሚያምም መገመት አያዳግትም! አዎን፣ ይሖዋ ስሜታችንን ይረዳል። ስንሠቃይ እሱም አብሮ ይሠቃያል።
20. በሮም 12:3 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የትኛውን ሚዛናዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ማስወገድ ያስፈልገናል?
20 አንድ የበሰለ ክርስቲያን አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት የሚያሳየውን ይህን ማስረጃ ሰበብ አድርጎ በመጠቀም ለመኩራራት ወይም ራሱን ከፍ አድርጎ ለመመልከት አይዳዳውም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።” (ሮም 12:3) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ” ሲል ይገልጻል። (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ስለዚህ ሰማያዊ አባታችን እንዲህ የሚወደን መሆኑ የሚያስደስተን ቢሆንም የአምላክ ፍቅር ይገባናል የምንለው እንዳልሆነ በማስታወስ ሚዛናችንን መጠበቅ ይኖርብናል።—ሉቃስ 17:10
21. ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን የትኞቹን ውሸቶች መቀበል የለብንም? ልባችን ይሖዋ የሰጠንን የትኛውን ማረጋገጫ እንዲቀበል ማድረግ ይኖርብናል?
21 ‘ይሖዋ አይወዳችሁም’ ወይም ‘በአምላክ ፊት ዋጋ የላችሁም’ የሚለውን ውሸት ጨምሮ ሰይጣን የሚያስፋፋው ማንኛውም ውሸት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ። በሕይወትህ ውስጥ ያሳለፍከው ነገር፣ አምላክ የቱንም ያህል ታላቅ ፍቅር ያለው ቢሆን አንተን ሊወድህ እንደማይችል ሆኖ እንዲሰማህ አድርጎሃል? ወይም ያከናወንከው መልካም ሥራ፣ ሁሉን ማየት የሚችለው የአምላክ ዓይን እንኳ ሊያስተውለው የማይችል ኢምንት ነገር እንደሆነ ይሰማሃል? አሊያም ደግሞ የሠራኸውን ኃጢአት የአምላክ ውድ ልጅ የከፈለው መሥዋዕት እንኳ ሊሸፍነው እንደማይችል አድርገህ ታስባለህ? ከሆነ በጣም ተሳስተሃል። ሰይጣን የሚያስፋፋውን እንዲህ ያለ ውሸት ፈጽሞ መቀበል የለብህም! ልባችን ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐቅ አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ይኖርብናል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።”—ሮም 8:38, 39
a መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት የትንሣኤ ተስፋን ከይሖዋ የማስታወስ ችሎታ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። ታማኙ የአምላክ አገልጋይ ኢዮብ ይሖዋን ‘ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ ባስታወስከኝ!’ ብሎታል። (ኢዮብ 14:13) ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተናግሯል። ይሖዋ ከሞት ሊያስነሳቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች በሚገባ የሚያስታውሳቸው በመሆኑ ይህ አነጋገር ተገቢ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ ሲተረጉሙ የአምላክን ሕዝብ የሚነካ የአምላክን ሳይሆን የራሱን ዓይን ወይም የእስራኤልን ሕዝብ ዓይን እንደሚነካ አድርገው ገልጸውታል። ይህ ስህተት የተፈጠረው በጥቅሱ ላይ የሰፈረው ሐሳብ አክብሮት የጎደለው እንደሆነ የተሰማቸው አንዳንድ ጸሐፊዎች ጥቅሱን በራሳቸው መንገድ ለማስተካከል በመሞከራቸው ነው። የወሰዱት የተሳሳተ እርምጃ የይሖዋ ጥልቅ የርኅራኄ ስሜት እንዲሰወር አድርጓል።