ለኢዮብ የተከፈለው ወሮታ የተስፋ ምንጭ ነው
“እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ።”—ኢዮብ 42:12
1. ይሖዋ ሕዝቡ በፈተናዎች እጅግ በሚዳከሙበት ጊዜም እንኳ ምን ያደርግላቸዋል?
ይሖዋ በቅንነት ‘ለሚፈልጉት ዋጋ ይሰጣል።’ (ዕብራውያን 11:6) በተጨማሪም ራሳቸውን ለእሱ የወሰኑ ሕዝቡ ፈተናዎች የሞቱ ሰዎችን ያህል ቢያዳክሟቸውም እንኳ በድፍረት እንዲመሠክሩ ያነሳሳቸዋል። (ኢዮብ 26:5፤ ራእይ 11:3, 7, 11) ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ሥቃይ በደረሰበት በኢዮብ ላይ ተረጋግጧል። በሦስት ሐሰተኛ አጽናኞች ትክክል ያልሆነ ነቀፋ ቢሰነዘርበትም ሰዎችን በመፍራት ከመናገር አልተቆጠበም። ከዚህ ይልቅ ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት ሰጥቷል።
2. የይሖዋ ምሥክሮች ስደትና መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ የሚደርሱባቸውን ፈተናዎች የሚቋቋሙት እንዴት ነው?
2 በዘመናችን ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ሞት አፋፍ እስኪደርሱ ድረስ ይህን የመሰሉ ከባድ ስደቶችና መከራዎች ተቀብለዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:23) ይሁን እንጂ ልክ እንደ ኢዮብ ለአምላክ ፍቅር አሳይተዋል፤ ጽድቅንም በሥራ አውለዋል። (ሕዝቅኤል 14:14, 20) ይሖዋን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ፣ ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት ለመስጠት ራሳቸውን በማጠንከርና እውነተኛ ተስፋን በመያዝ የደረሱባቸውን ፈተናዎች ጸንተው ተቋቁመዋል።
ኢዮብ በድፍረት ምሥክርነት ሰጠ
3. ኢዮብ በመጨረሻ ንግግሩ ላይ ምን ዓይነት ምሥክርነት ሰጥቷል?
3 ኢዮብ በመጨረሻው ንግግሩ ላይ ቀደም ሲል ሰጥቶት ከነበረው የላቀ ምሥክርነት ሰጥቷል። የሐሰት አጽናኞቹን ዝም አሰኛቸው። በሚዋጋ አሽሙር “ኃይል የሌለውን ክንድ ምንኛ ረዳኸው!” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 26:2) ኢዮብ የምድራችንን ሉል በጠፈር ውስጥ በባዶ ቦታ ላይ ያቆመና ውኃ ያዘሉ ደመናዎችን ከምድር በላይ ያንጠለጠለ ኃይል ያለውን ይሖዋን አወድሶታል። (ኢዮብ 26:7–9) ሆኖም ኢዮብ እንዲህ ያሉት ድንቆች ‘የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ናቸው’ ብሏል።—ኢዮብ 26:14
4. ኢዮብ የጸና አቋም መጠበቅን አስመልክቶ ምን አለ? ራሱን በዚያ መንገድ ሊገልጽ የቻለውስ ለምንድን ነው?
4 ኢዮብ ከበደል ነፃ ነኝ የሚል ሙሉ እምነት ስለነበረው “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም” ብሏል። (ኢዮብ 27:5) የኢዮብ ሁኔታ ከተሰነዘሩበት የሐሰት ክሶች ተቃራኒ ነበር። ለዛ ሁሉ መከራ የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም። ኢዮብ ይሖዋ የከሃዲዎችን ጸሎት እንደማይሰማ ከዚህ ይልቅ ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ከእርሱ ጋር ተጣብቀው የሚኖሩ ሰዎችን ወሮታ እንደሚከፍላቸው ያውቅ ነበር። ይህም በቅርቡ የአርማጌዶን ዐውሎ ነፋስ ክፉዎችን ከተቆናጠጡት ቦታ እንደሚጠራርጋቸውና ዒላማውን ከማይስተው የአምላክ እጅ እንደማያመልጡ ሊያስታውሰን ይችላል። እስከዚያው ድረስ የይሖዋ ሕዝብ ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ይመላለሳሉ።—ኢዮብ 27:11–23
5. ኢዮብ ለእውነተኛ ጥበብ ፍቺ የሰጠው እንዴት ነው?
5 እስቲ አስበው፤ ሦስቱ ዓለማዊ ጥበብ ያካበቱ ሰዎች ሰው ወርቅ፣ ብርና ሌሎች ውድ ማዕድናትን በመሬትና በባሕር ውስጥ ለማግኘት ችሎታውን እንደተጠቀመበት ኢዮብ ሲገልጽ ይሰሙ ነበር። ይሁንና ኢዮብ “የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ይበልጣል” ሲል ተናገረ። (ኢዮብ 28:18) የኢዮብ ሐሰተኛ አጽናኞች እውነተኛ ጥበብን መግዛት አልቻሉም ነበር። የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ የነፋስ፣ የዝናብ፣ የመብረቅና የነጎድጓድ ፈጣሪ ነው። እውነትም ለይሖዋ ‘አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው።’—ኢዮብ 28:28
6. ኢዮብ ስለ ቀድሞ ሕይወቱ የተናገረው ለምንድን ነው?
6 ኢዮብ የተለያዩ መከራዎች ቢደርሱበትም ይሖዋን ማገልገሉን አልተወም። ከልዑሉ አምላክ ዘወር አላለም፤ ከዚህ ይልቅ የጸና አቋሙን የጠበቀው ይህ ሰው ቀደም ሲል “ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና” መልሶ ለማግኘት ጓጉቷል። (ኢዮብ 29:4 አዓት) ኢዮብ ‘ችግረኛውን እንዴት እንዳዳነ፣ ጽድቅን እንዴት እንደለበሰና ለድሀው እንዴት አባት እንደነበረ’ ሲናገር ጉራውን መንዛቱ አልነበረም። (ኢዮብ 29:12–16) ከዚህ ይልቅ የታመነ የይሖዋ አገልጋይ ሆኖ ያሳለፈውን ሕይወት እውነታዎች መጥቀሱ ነበር። እንዲህ ያለ ጥሩ ስም አትርፈሃልን? እርግጥ ኢዮብ ሦስቱ ሃይማኖታዊ አስመሳዮች የሰነዘሯቸው ክሶች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ማጋለጡም ነበር።
7. ኢዮብ ምን ዓይነት ሰው ነበር?
7 ኢዮብ ‘አባቶቻቸውን ከመንጋው ውሾች ጋር ለማኖር የናቃቸው’ በዕድሜ ከእሱ የሚያንሱ ሰዎች ተሳለቁበት። ሰዎች ተጸይፈውት ምራቃቸውን በፊቱ ጢቅ ይሉ ነበር። ኢዮብ ከፍተኛ አበሳ የደረሰበት ቢሆንም ዞር ብሎ የተመለከተው አልነበረም። (ኢዮብ 30:1, 10, 30) ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ ሰው ስለነበር ንጹሕ ሕሊና ነበረው፤ በዚህም ምክንያት “በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፣ እግዚአብሔርም ቅንነቴን [የያዝኩትን የጸና አቋም አዓት] ይወቅ” ብሎ ለመናገር ችሎ ነበር። (ኢዮብ 31:6) ኢዮብ አመንዝራ ወይም ተንኮል የሚሸርብ ሰው አልነበረም። ችግረኞችንም ከመርዳት የታቀበ ሰው አልነበረም። ባለጠጋ የነበረ ቢሆንም በቁሳዊ ሀብት አልታመነም። ከዚህም በላይ ኢዮብ ጨረቃን የመሳሰሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮችን በማምለክ የጣዖት አምልኮ አልፈጸመም። (ኢዮብ 31:26–28) በአምላክ በመታመን አቋምን ሳያጎድፉ ከእርሱ ጋር ተጣብቆ የመኖርን ምሳሌ ትቷል። ያ ሁሉ ፈተና ቢደርስበትና በአጠገቡ የሐሰት አጽናኞች የነበሩ ቢሆንም እንኳ ኢዮብ ግሩም መከላከያ አቅርቧል፤ እንዲሁም የተዋጣለት ምሥክርነት ሰጥቷል። አምላክን እንደ ፈራጁና እንደ ወሮታ ከፋዩ አድርጎ በመመልከት ንግግሩን አጠቃሏል።—ኢዮብ 31:35–40
ኤሊሁ ተናገረ
8. ኤሊሁ ማን ነበር? አክብሮትንም ሆነ ድፍረትን ያሳየውስ እንዴት ነው?
8 በአቅራቢያቸው የናኮር ልጅ የቡዝ ዝርያ የሆነው ወጣቱ ኤሊሁ ይገኝ ነበር። በመሆኑም ኤሊሁ የይሖዋ ወዳጅ የሆነው የአብርሃም የሩቅ ዘመድ ነው። (ኢሳይያስ 41:8) ኤሊሁ ከሁለቱም ወገኖች የሚሰነዘሩትን እሰጥ አገባዎች ዝም ብሎ በማዳመጥ በዕድሜ ለሚበልጡት ሰዎች ያለውን አክብሮት አሳይቷል። ሆኖም የተሳሳቱባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በድፍረት ተናግሯቸዋል። ለምሳሌ ያህል “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና” ኢዮብን ተቆጥቶታል። የኤሊሁ ቁጣ በተለይ በሐሰተኛ አጽናኞቹ ላይ ያነጣጠረ ነበር። ንግግራቸው አምላክን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይመስል ነበር፤ ይሁን እንጂ በተነሣው ውዝግብ ከሰይጣን ጎን በመቆም አምላክን የሚነቅፍ ቃል ተናግረው ነበር። ‘ቃልን የተሞላውና’ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሳው ኤሊሁ የማያዳላ የይሖዋ ምሥክር ነበር።—ኢዮብ 32:2, 18, 21
9. ኤሊሁ ኢዮብ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደሚመለስ የጠቆመው እንዴት ነው?
9 ኢዮብ ይበልጥ አሳስቦት የነበረው የአምላክ ሳይሆን የራሱ ስም ከክስ ነፃ የመሆኑ ጉዳይ ነበር። እንዲያውም ከአምላክ ጋር ተሟግቶ ነበር። ይሁን እንጂ የኢዮብ ነፍስ ሞት አፋፍ ስትደርስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንደሚመለስ የሚጠቁም ነገር መጣ። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ ኢዮብን የሚከተለው መልእክት እንዲደርሰው በማድረግ ሞገሱን እንዳሳየው ለመናገር ኤሊሁ ተገፋፍቶ ነበር፦ “ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጉድጓድ እንዳይወርድ አድነው . . . ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጉብዝናውም ዘመን ይመለሳል።”—ኢዮብ 33:24, 25
10. ኢዮብ እስከ ምን ድረስ ሊፈተን ይችል ነበር? ይሁን እንጂ 1 ቆሮንቶስ 10:13 በሚለው መሠረት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
10 ኢዮብ የጸና አቋምን ሳያጎድፉ በአምላክ መደሰት የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም በማለቱ ኤሊሁ አርሞታል። ኤሊሁ እንዲህ አለ፦ “ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር፣ በደልንም ይሠራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ። ለሰው ሥራውን ይመልስለታል።” ኢዮብ የራሱን ጽድቅ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ተቻኩሏል፤ ይህን ያደረገው ግን ያለ በቂ እውቀትና ማስተዋል ነበር። ኤሊሁ “ኢዮብ እስከ ፍጻሜ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ! እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ኢዮብ 34:10, 11, 35, 36) በተመሳሳይም እምነታችንና የጸና አቋማችን ሙሉ በሙሉ ሊረጋገጥ የሚችለው በሆነ መንገድ ‘እስከ ፍጻሜ ድረስ ከተፈተን’ ብቻ ነው። ያም ሆነ ይህ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይተወንም።—1 ቆሮንቶስ 10:13
11. ከባድ ፈተና ሲደርስብን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
11 ኤሊሁ መናገሩን በመቀጠል፣ ኢዮብ የራሱን ጽድቅ ከሚገባው በላይ ጎላ አድርጎ እንዳቀረበ በድጋሚ ገልጿል። ትኩረት ሊደረግ የሚገባው በታላቁ ፈጣሪያችን ላይ መሆን አለበት። (ኢዮብ 35:2, 6, 10) አምላክ “የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤ ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል” ሲል ኤሊሁ ተናግሯል። (ኢዮብ 36:6) የአምላክን መንገድ ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ትክክል አልሠራም ሊለው የሚችል ማንም የለም። እኛ ልናውቀው ከምንችለው በላይ ከፍ ከፍ ያለ ነው። ዘመኑም ሊመረመር የማይችል፣ ወሰን የሌለው ነው። (ኢዮብ 36:22–26) ከባድ ፈተና ሲደርስባችሁ ዘላለማዊው አምላካችን ጻድቅ መሆኑንና እርሱን ለሚያስመሰግኑት የታማኝነት ሥራዎቻችን ወሮታ እንደሚከፍለን አስታውሱ።
12. ኤሊሁ ንግግሩን ሲያጠቃልል የተጠቀመበት አገላለጽ አምላክ በክፉዎች ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ምን ያስረዳል?
12 ኤሊሁ እየተናገረ ሳለ ዐውሎ ነፋስ እየተመመ ይመጣ ነበር። እየቀረበ ሲመጣ የኤሊሁ ልብ መሸበርና ድው ድው ማለት ጀመረ። ኤሊሁ ይሖዋ ስላከናወናቸው ታላላቅ ነገሮች ተናገረና እንዲህ አለ፦ “ኢዮብ ሆይ፣ ይህን ስማ፤ ቁም፣ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።” ልክ እንደ ኢዮብ እኛም የአምላክን ድንቅ ሥራዎችና አስፈሪ ክብሩን ልብ ልንል ይገባል። “ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፤ በኃይል ታላቅ ነው፤ በፍርድና በጽድቅም አያስጨንቅም። ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል” በማለት ኤሊሁ ተናግሯል። (ኢዮብ 37:1, 14, 23, 24) ኤሊሁ ንግግሩን ሲያጠቃልል የተጠቀመበት አገላለጽ አምላክ በቅርቡ በክፉዎች ላይ ፍርዱን ሲያስፈጽም ፍትሕንና ጽድቅን ገሸሽ እንደማያደርግና የሚፈሩትን ሰዎች አክብሮታዊ ፍርሃት እንደሚያሳዩት አምላኪዎቹ አድርጎ በማየት እንደሚጠብቃቸው ያስታውሰናል። ይሖዋን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ አድርገው ከተቀበሉና የጸና አቋማቸውን አጥብቀው ከያዙት ከእነዚህ ሰዎች መካከል መሆን እንዴት ያለ መብት ነው! ልክ እንደ ኢዮብ ጽና፤ በእነዚህ ደስተኛ ሕዝብ መካከል ካለህ የተባረከ ቦታ ዲያብሎስ እንዲያፈናቅልህ ፈጽሞ አትፍቀድለት።
ይሖዋ ለኢዮብ መልስ ሰጠው
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ኢዮብን መጠየቅ የጀመረው ምንን በተመለከተ ነበር? (ለ) አምላክ ለኢዮብ ካቀረባቸው ሌሎች ጥያቄዎች ምን ነጥቦችን መቅሰም ይቻላል?
13 ይሖዋ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ሲያነጋግረው ኢዮብ ምንኛ ተደንቆ ይሆን! ይህ ዐውሎ ነፋስ አምላክ ያመጣው ነበር። ሰይጣን ቤቱን ለመደርመስና የኢዮብን ልጆች ለመግደል ከተጠቀመበት ኃይለኛ ንፋስ የተለየ ነበር። አምላክ እንዲህ ብሎ በጠየቀው ጊዜ ኢዮብ መናገር ተስኖት ነበር፦ “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? . . . አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፣ የእግዚአብሔርም ልጆች እልል ሲሉ፣ . . . የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?” (ኢዮብ 38:4, 6, 7) ይሖዋ ስለ ባሕር፣ ምድርን ስለሚያለብሰው ደመና፣ ስለ ንጋት ብርሃን፣ ስለ ሞት ደጆች፣ ስለ ብርሃንና ስለ ጨለማ እንዲሁም በቡድን በቡድን ስለተከማቹ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት በመጠየቅ በኢዮብ ላይ የጥያቄ ናዳ አወረደበት። ኢዮብ “የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን?” ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው ነገር አልነበረውም።— ኢዮብ 38:33
14 ሌሎቹ ጥያቄዎች ሰው ከመፈጠሩ በፊትና ዓሣን፣ አዕዋፍን፣ አራዊትንና በሆዳቸው የሚሳቡ ነፍሳትን የመግዛት መብት ለሰው ልጅ ከመሰጠቱ በፊት አምላክ ያላንዳች ሰብዓዊ እርዳታ ወይም ምክር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይሰጣቸው እንደነበር ይጠቁማሉ። ይሖዋ ቀጥሎ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ጎሽን፣ ሰጎንንና ፈረስን የመሰሉ ፍጥረታትን የሚጠቅሱ ናቸው። ኢዮብ “በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን?” ተብሎ ተጠይቋል። (ኢዮብ 39:27) እንዴት ሆኖ! አምላክ “በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ የኢዮብ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው። ኢዮብ “እነሆ፣ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ” ብሎ መናገሩ አያስደንቅም። (ኢዮብ 40:2, 4) ይሖዋ ምን ጊዜም ትክክል ስለሆነ በእሱ ላይ እንድናጉረመርም ብንፈተን ‘እጃችንን በአፋችን ላይ መጫን’ አለብን። በፍጥረቱ ላይ እንደታየው አምላክ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የበላይነቱን፣ ክብሩንና ብርታቱንም ጎላ አድርገው የሚያንጸባርቁ ናቸው።
ብሄሞትና ሌዋታን
15. ብሄሞት የትኛው እንስሳ እንደሆነ ይታመናል? አንዳንድ ጠባዮቹስ ምንድን ናቸው?
15 ይሖዋ ቀጥሎ የጠቀሰው ጉማሬ መሆን አለበት ተብሎ የሚታመነውን ብሄሞትን ነው። (ኢዮብ 40:15–24 የ1980 ትርጉም) በግዙፍነቱ፣ ባለው ከፍተኛ ክብደትና በጠንካራ ቆዳው የተደነቀው ይህ እንስሳ ‘የሚመገበው ሣር ነው።’ ኃይሉና ጉልበቱ የሚመነጨው ከወገቡና ከሆዱ ጅማቶች ነው። የእግሮቹ አጥንቶች “እንደ ነሐስ በትር” በጣም ጠንካራ ናቸው። ብሄሞት በፈረሰኛ ውኃ አይሸበርም፤ ከዚህ ይልቅ ውኃው እየጋለበ ወደሚመጣበት አቅጣጫ ያለምንም ችግር ይዋኛል።
16. (ሀ) ስለ ሌዋታን የተሰጠው መግለጫ ከየትኛው ፍጡር ሁኔታ ጋር ይስማማል? ይህን ፍጡር በተመለከተ ያሉት አንዳንድ እውነታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) የብሄሞትና የሌዋታን ኃይል በይሖዋ አገልግሎት የተሰጡንን አንዳንድ ሥራዎች ማሟላትን በተመለከተ ምን ሐሳብ ሊጠቁመን ይችላል?
16 አምላክ ኢዮብን “ሌዋታን ተብሎ የሚጠራውን የባሕር አውሬ ዓሣ በሚጠመድበት መንጠቆ ልትይዘው ወይም ምላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህን?” የሚል ጥያቄም አቅርቦለት ነበር። ስለ ሌዋታን የተሰጠው መግለጫ ለአዞ የሚስማማ ነው። (ኢዮብ 41:1–34 የ1980 ትርጉም) ከማንም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አይገባም። ማንኛውም አስተዋይ ሰው ይህን ደመ ቀዝቃዛ እንስሳ ከተኛበት ለመቀስቀስ አይደፍርም። ቀስቶች አያሸሹትም፤ “ጦር ሲወረውሩበት በማፌዝ ይስቃል።” ቁጣው የገነፈለ ሌዋታን በባሕር ወለል ላይ ያለውን ውኃ በማሰሮ ውስጥ እንደሚፈላ ዘይት ያንተከትከዋል። ኢዮብ ሌዋታንና ቤሄሞት ከእሱ እጅግ የላቀ ኃይል ያላቸው መሆኑ ትሑት እንዲሆን ረድቶቷል። እኛም በራሳችን ኃያል እንዳልሆንን በትሕትና አምነን መቀበል አለብን። ከእባቡ ከሰይጣን ንክሻ ለማምለጥና በይሖዋ አገልግሎት እንድናከናውናቸው የተሰጡንን ሥራዎች እንድንፈጽም አምላክ የሚሰጠው ጥበብና ጥንካሬ ያስፈልገናል።—ፊልጵስዩስ 4:13፤ ራእይ 12:9
17. (ሀ) ኢዮብ ‘አምላክን ያየው’ እንዴት ነው? (ለ) ኢዮብ ሊመልሳቸው ባልቻላቸው ጥያቄዎች የተረጋገጠው ነገር ምንድን ነው? ይህስ እኛን የሚረዳን እንዴት ነው?
17 ኢዮብ ሙሉ በሙሉ ራሱን አዋርዷል። የተሳሳተ አመለካከት ይዞ እንደነበረና ያለ እውቀት እንደተናገረ አምኗል። ሆኖም ‘አምላክን እንደሚያይ’ ያለውን እምነት ገልጿል። (ኢዮብ 19:25–27) ማንም ሰው ይሖዋን አይቶ መኖር ስለማይችል ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? (ዘጸአት 33:20) ኢዮብ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫን አይቷል፣ የአምላክን ቃል ሰምቷል፣ እንዲሁም ስለ ይሖዋ እውነቱ ምን እንደሆነ ማየት እንዲችል የማስተዋል ዓይኑ ተከፍቷል። በዚህም ምክንያት ኢዮብ ‘አፍሯል፤ በዐመድና በትቢያ ላይ ተቀምጦም ንስሐ ገብቷል።’ (ኢዮብ 42:1–6 የ1980 ትርጉም) ቀርበውለት የነበሩት ሊመልሳቸው ያልቻላቸው ብዙ ጥያቄዎች አምላክ ታላቅ መሆኑን አረጋግጠዋል፤ እንዲሁም ሰው እንደ ኢዮብ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ያደረ ቢሆንም እንኳ ከቁጥር የማይገባ መሆኑን አሳይተዋል። ይህም የእኛን ፍላጎቶች ከይሖዋ ስም መቀደስና ከሉዓላዊነቱ መከበር አስበልጠን መመልከት እንደማይገባ እንድንገነዘብ ይረዳናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ዋነኛው ትኩረታችን የጸና አቋማችንን ሳናጎድፍ ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን መኖርና ስሙን ማክበር መሆን ይኖርበታል።
18. የኢዮብ ሐሰተኛ አጽናኞች ምን ማድረግ አስፈልጓቸዋል?
18 ራሳቸውን ያመጻድቁ የነበሩት ሐሰተኛ አጽናኞችስ? ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር እንደ ኢዮብ ስለ እርሱ እውነት የሆነውን ነገር ባለመናገራቸው ይሖዋ ሊገድላቸው ይችል ነበር። “ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፣ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል” በማለት አምላክ ተናግሯል። ሦስቱ ሰዎች የተባሉትን ለማድረግ ራሳቸውን ዝቅ ማድረግ ነበረባቸው። የሚጸልይላቸው አቋሙን ያላጎደፈው ኢዮብ ነበር። ይሖዋም ጸሎቱን ተቀባይነት ያለው ሆኖ አግኝቶታል። (ኢዮብ 42:7–9) ይሁን እንጂ አምላክን እንዲሰድብና እንዲሞት የወተወተችው የኢዮብ ሚስትስ? በአምላክ ምሕረት ምክንያት ከኢዮብ ጋር ዕርቅ የፈጠረች ይመስላል።
አምላክ ቃል የገባልን ወሮታዎች ተስፋ ይሰጡናል
19. ከኢዮብ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ይሖዋ በዲያብሎስ ላይ ያለውን የበላይነት ያሳየው እንዴት ነው?
19 ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ ማሰቡን እንዳቆመና በአምላክ አገልግሎት መነቃቃት እንደ ጀመረ ወዲያው ይሖዋ ሁኔታዎቹን ለወጠለት። ኢዮብ ለሦስቱ ሰዎች ከጸለየ በኋላ አምላክ “ምርኮውን መለሰለት . . . ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ” ሰጠው። ሰይጣን በበሽታ የሚበክለውን እጁን እንዲሰበስብ በማድረግና ኢዮብን በተአምራዊ መንገድ በመፈወስ ይሖዋ በዲያብሎስ ላይ ያለውን የበላይነት አሳይቷል። በተጨማሪም አምላክ መላእክቱ በዙሪያው ሠፍረው እንደገና ኢዮብን እንዲጠብቁ በማድረግ የአጋንንትን ጭፍሮች ወደ ኋላ መልሶ ዳግም ዝር እንዳይሉ አድርጓቸዋል።—ኢዮብ 42:10፤ መዝሙር 34:7
20. ይሖዋ ኢዮብን ወሮታ የከፈለውና የባረከው በምን መንገዶች ነው?
20 የኢዮብ ወንድሞች፣ እኅቶችና ቀደም ሲል ያውቁት የነበሩ ሰዎች ከእርሱ ጋር ለመብላት፣ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽና ይሖዋ እንዲደርስበት ከፈቀደው መከራ ለማጽናናት ወደ ቤቱ ይመጡ ነበር። እያንዳንዳቸው ለኢዮብ ገንዘብና የወርቅ ቀለበት ሰጡት። ይሖዋ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ስለባረከለት 14,000 በጎች፣ 6,000 ግመሎች 1,000 ጥማድ በሬዎችና 1,000 እንስት አህዮች አገኘ። በተጨማሪም ኢዮብ ልክ እንደ መጀመሪያው ሰባት ወንዶች ልጆችና ሦስት ሴቶች ልጆች ወለደ። ይሚማ፣ ቃስያና አማልቶያስ ቂራስ የተባሉት ሴቶች ልጆቹ በአገሩ ከነበሩት ሴቶች ሁሉ በቁንጅናቸው የላቁ ነበሩ። ኢዮብም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጥቷቸዋል። (ኢዮብ 42:11–15) ከዚህም በላይ ኢዮብ ሌላ 140 ዓመት በመኖር ዘሩን እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። ዘገባው “ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ” ሲል ታሪኩን ይቋጫል። (ኢዮብ 42:16, 17) የሕይወቱ መራዘም የይሖዋ አምላክ ተአምራዊ ሥራ ነበር።
21. ስለ ኢዮብ በሚተርከው ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባ የምንጠቀመው እንዴት ነው? ምን ለማድረግስ መቁረጥ ይኖርብናል?
21 ስለ ኢዮብ የሚተርከው ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ይበልጥ እንድናውቅ ያደርገናል፤ እንዲሁም ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ሰው ለአምላክ የሚያሳየውን የጸና አቋም ሳያጎድፍ ከመቀጠሉ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ መገንዘብ እንድንችል ረድቶናል። ልክ እንደ ኢዮብ አምላክን የሚያፈቅሩ ሁሉ ፈተና ይደርስባቸዋል። ይሁን እንጂ እኛም እንደሱ መጽናት እንችላለን። ኢዮብ የደረሱበትን ፈተናዎች በእምነትና በተስፋ ተወጥቷቸዋል፤ ለዚህም ከፍተኛ ወሮታ ተከፍሎታል። በዛሬው ጊዜ የምንኖር የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን እውነተኛ እምነትና ተስፋ አለን። ታላቁ ወሮታ ከፋይ ደግሞ በእያንዳንዳችን ፊት የዘረጋው ተስፋ ምንኛ ታላቅ ነው! ቅቡዓኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን በአእምሮአቸው መያዛቸው በተቀረው ምድራዊ ሕይወታቸው አምላክን በታማኝነት ከጎኑ ቆመው እንዲያገለግሉት ይረዳቸዋል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ብዙዎች እስከናካቴው ሞትን ሳይቀምሱ ይኖራሉ፤ በሞት የሚጠለፉት ግን ከኢዮብ ጋር በገነቲቱ ምድር ላይ የመነሣት ወሮታ ያገኛሉ። አምላክን የምናፈቅር ሁሉ ይህን የመሰለ እውነተኛ ተስፋ በልባችንና በአእምሮአችን ይዘን አቋማችንን የማናጎድፍና ያለማወላወል ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን የምንደግፍ ሆነን ከይሖዋ ጎን ጸንተን በመቆም ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እናረጋግጥ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ኢዮብ ለሐሰተኛ አጽናኞቹ መጨረሻ ላይ በሰጠው መልስ ከተናገራቸው ነጥቦች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
◻ ኤሊሁ የማያዳላ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው?
◻ አምላክ ለኢዮብ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ምን ውጤትስ ነበራቸው?
◻ ስለ ኢዮብ ከሚተርከው ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባ ጥቅም ያገኘኸው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ስለ ብሄሞትና ሌዋታን የተናገራቸው ነገሮች ኢዮብ ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ ረድተውታል