አስደናቂ የሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ይሖዋን ያወድሳሉ
ይሖዋ ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች ከሚያስቡት በላይ ከፍ ያለ አምላክ ነው። በሰማይና በምድር ያሉት የፍጥረት ሥራዎቹ ለእርሱ ምስጋና ከማምጣታቸውም ሌላ እኛም በአድናቆት እንድንሞላ ያደርጉናል።—መዝሙር 19:1-4
ይሖዋ ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለሙ ልዑል እንደመሆኑ መጠን እርሱ ሲናገር ልናዳምጠው ይገባል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በዚህ ምድር ላይ የምንኖረውን ተራ ሰዎች በቀጥታ ቢያናግረን ኖሮ ምንኛ ያስደንቀን ነበር! እርሱ ራሱ ምናልባትም በመልአክ ተጠቅሞ ቢያናግርህ በትኩረት እንደምታዳምጠው የተረጋገጠ ነው። ቅን የነበረው ኢዮብ ከ3,500 ዓመታት በፊት አምላክ ባናገረው ወቅት በትኩረት አዳምጧል። አምላክ ሰማይና ምድርን አስመልክቶ ለኢዮብ ከተናገረው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
ምድርን የመሠረተ፣ ባሕርንስ የሚቆጣጠር ማን ነው?
አምላክ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ ስለ ምድርና ስለ ባሕር ጥያቄ አቀረበለት። (ኢዮብ 38:1-11) የምድር መጠን ይህን ያህል ይሁን ብሎ የወሰነ ወይም አምላክ በሚፈጥርበት ወቅት የረዳው አንድም መሐንዲስ የለም። አምላክ ምድርን ከአንድ ሕንፃ ጋር በማወዳደር ኢዮብን “የማእዘን ድንጋይዋንስ ማን አቆመ?” በማለት ጠይቆታል። የትኛውም የሰው ዘር ይህን አላደረገም! ይሖዋ ይህችን ፕላኔት በፈጠረበት ወቅት ልጆቹ የሆኑት መላእክት ደስታቸውን በእልልታ ገልጸዋል።
የባሕር ዕድሜ፣ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ልብስ እንዳለበሰው ተደርጎ ከተገለጸው ከአምላክ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። “ባሕር ከማሕፀን በወጣ ጊዜ፣ በር የዘጋበት ማን ነው?” አምላክ ባሕርን በመዝጊያና በመወርወሪያ የመከለል ያህል ድንበር አበጅቶለታል። ማዕበልን ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ የስበት ኃይል አማካኝነት ያንቀሳቅሰዋል።
ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል:- “አብዛኛውን ጊዜ ከባሕር ላይ የሚነሳው ነፋስ፣ ትናንሽ ሞገድም ሆነ ባሕሩን በጣም የሚያናውጠውና 30 ሜትር ያህል ወደ ላይ ከፍታ የሚኖረው ከባድ ማዕበል እንዲፈጠር ያደርጋል። . . . ነፋሱ ካቆመ በኋላም ሞገዱ መንቀሳቀሱን የሚቀጥል ሲሆን በባሕሩ ወለል ላይ ረጅም ርቀት ሊጓዝ ይችላል። ይህ ሞገድ ሰከን ያለና ሰፊ ቦታን የሚሸፍን ይሆናል። በመጨረሻም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲደርስ ይዳከምና አረፋ መሰል ማዕበል ይፈጥራል።” ባሕር “እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ፤ ማለፍ ግን አትችልም፤ የዕቡይ ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው” ብሎ ያለውን አምላክ ይታዘዛል።
ጎህ እንዲቀድ የሚያደርግ ማን ነው?
አምላክ ቀጥሎም ኢዮብን ብርሃንና ሌሎች የፈጠራቸው ነገሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ውጤት ጠይቆታል። (ኢዮብ 38:12-18) የትኛውም የሰው ዘር ቢሆን የቀንና የሌሊትን መፈራረቅ ሊቆጣጠር አይችልም። ምሳሌያዊ በሆነ አነጋገር የንጋት ብርሃን የምድርን ዳርቻ ይዞ ክፉዎችን ከላይዋ ያራግፋል። ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች “ድንግዝግዝታን” ተገን አድርገው ክፉ ድርጊት ይፈጽማሉ። (ኢዮብ 24:15, 16) ይሁን እንጂ ጎህ ሲቀድ አብዛኞቹ ክፉ አድራጊዎች ሁሉን ጥለው ይሸሻሉ።
የንጋት ብርሃን ልክ በአምላክ እጅ እንዳለ ማህተም ምድር የሚያምር ቅርጽ ይዛ እንድትወጣ ያደርጋታል። የፀሐይ ብርሃን ምድር ላይ በሚያርፍበት ጊዜ በርካታ ቀለማት እንዲታዩ ስለሚያደርግ ምድርን በውብ ልብስ ያሸበረቀች ያስመስላታል። ኢዮብ ግን በዚህ ሥራ ውስጥ ያበረከተው አንዳች ነገር የለም፤ እንዲሁም ወደ ባሕር ጥልቅ ገብቶ በውስጡ ያለውን ሀብት አልተመለከተም። ሌላው ቀርቶ በዛሬው ጊዜ ምርምር የሚያካሂዱ ሰዎች እንኳ በውቅያኖስ ውስጥ ስላለው ሕይወት ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ነው!
የበረዶ መጋዘን ያለው ማን ነው?
ብርሃንን ወይም ጨለማን ወደ ቤታቸው የሚሸኛቸው ወይም አምላክ “ለጦርነትና ለውጊያ ቀን” ወዳስቀመጠው ወደ በረዶው መጋዘን የገባ ማንም ሰው የለም። (ኢዮብ 38:19-23) ይሖዋ ጠላቶቹን በገባዖን ላይ በበረዶ ድንጋይ በመታበት ወቅት “በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው” ተገኝተዋል። (ኢያሱ 10:11) ይሖዋ በጎግ ወይም በሰይጣን የሚመሩትን ክፉ የሰው ዘሮች ለማጥፋት መጠናቸው ያልተገለጸ የበረዶ ድንጋዮችን ይጠቀም ይሆናል።—ሕዝቅኤል 38:18, 22
በቻይና፣ በማዕከላዊ ሔናን ግዛት ውስጥ ሐምሌ 2002 እንቁላል የሚያካክሉ የበረዶ ድንጋዮች በመዝነባቸው 25 ሰዎች ሲሞቱ 200 በሚያህሉት ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል። ጣሊያናዊው የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ቤንቬኑቶ ቼሊኒ በ1545 የዘነበውን የበረዶ ድንጋይ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ሰማዩ ኃይለኛ ነጎድጓድ በማሰማት ሲያስገመግም . . . ከሊዮን የአንድ ቀን መንገድ ርቀት ላይ ነበርን። . . . ከነጎድጓዱ በኋላ ሰማዩ በጣም ኃይለኛና አስደንጋጭ ድምጽ ሲያሰማ የመጨረሻው ቀን እንደመጣ አሰብኩ፤ የፈረሴን ልጓም ለጥቂት ጊዜያት ሳብ አድርጌ ቆም አልኩ፤ ወዲያውኑ ምንም የዝናብ ጠብታ የሌለበት የበረዶ ድንጋይ ይወርድ ጀመር። . . . የበረዶው ድንጋይ ትልቅ ሎሚ ያክል ነበር። . . . በረዶው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከጣለ በኋላ ጋብ አለ . . . እኛም ሰውነታችንን ስንመለከት ተቦጫጭሮና ሰንበር አውጥቶ ነበር፤ 1.5 ኪሎ ሜትሮች ገደማ እንደሄድን ግን እኛ ከደረሰብን የከፋና በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር እልቂት አየን። ሁሉም ዛፎች ቅጠላቸው ረግፏል እንዲሁም ተገነጣጥለዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ በሜዳ ላይ የሚገኙ እንስሳትና አብዛኞቹ እረኞች ሞተው ነበር። በሁለት እጅ ለማንሳት የማይቻሉ በርካታ የበረዶ ድንጋዮችም ተመለከትን።”—አውቶባዮግራፊ (መጽሐፍ 2, 50)፣ ሃርቫርድ ክላሲክስ፣ ጥራዝ 31፣ ገጽ 352-353
ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የበረዶውንና የዐመዳዩን መጋዘን በሚከፍትበት ጊዜ ምን ይከሰት ይሆን? ፈቃዱን ለማስፈጸም የበረዶውን ድንጋይ በሚጠቀምበት ወቅት ጠላቶቹ ሊቋቋሙት ፈጽመው አይችሉም።
ዝናብ፣ ጤዛ፣ ዐመዳይና በረዶ የማን እጅ ሥራ ናቸው?
ይሖዋ በመቀጠልም ኢዮብን ስለ ዝናብ፣ ጤዛ፣ ዐመዳይና በረዶ ጠየቀው። (ኢዮብ 38:24-30) ዝናብን የፈጠረው ይሖዋ ሲሆን ‘ሰው የሌለበት ምድረ በዳ’ እንኳ ዝናብ ያገኛል። ዝናብ፣ ዐመዳይና በረዶ ሰብዓዊ ፈጣሪ ወይም አባት የላቸውም።
ኔቸር ቡሌቲን የተባለው መጽሔት እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “[የበረዶ] አስገራሚው ምናልባትም በጣም አስፈላጊው ገጽታ ውኃ ወደ በረዶነት ሲቀየር የሚስፋፋ መሆኑ ነው። . . . በክረምት ወራት በኩሬ ላይ የሚፈጠረውና ከላይ የሚንሳፈፈው የበረዶ ግግር ከታች ባለው ውኃ ውስጥ የሚገኙት የባሕር ውስጥ እፅዋትና እንስሳት (ዓሣና የመሳሰሉት) መኖር እንዲችሉ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። . . . ውኃ ወደ ጠጣርነት ሲለወጥ የሚኮማተር ቢሆን ኖሮ በረዶ ከውኃ ይበልጥ ክብደት ስለሚኖረው ወደታች ይዘቅጥ ነበር። ስለዚህም ኩሬው በሙሉ በረዶ ይሆን ነበር። . . . እንዲህ ቢሆን ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ በሆኑት የዓለም ክፍሎች የሚገኙት ወንዞች፣ ኩሬዎች፣ ሐይቆችና ውቅያኖሶች ሳይቀር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ በረዶነት ይቀየሩ ነበር።”
የውኃ አካላት ቀዝቅዘው በረዶ አለመሆናቸው እንዴት የሚያስደስት ነው! የይሖዋ የእጅ ሥራ የሆኑት ዝናብና ጤዛ የምድራችን እፅዋት እንዲያፈሩ ስለሚያደርጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን።
የሰማይን ሥርዓት ያስቀመጠ ማን ነው?
አምላክ፣ ኢዮብን ሰማያትን አስመልክቶም ጥያቄ አቅርቦለታል። (ኢዮብ 38:31-33) ካይማ የተባለው ኅብረ ኮከብ አብዛኛውን ጊዜ ፕልያዲስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከፀሐይ በ380 የብርሃን ዓመት ርቀት ላይ የሚገኙትን ሰባት ትላልቅና በርካታ ትናንሽ ከዋክብት ያካትታል። የሰው ልጅ “ፕልያዲስ የተባሉትን ውብ ከዋክብት” መለጎም ወይም አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ማድረግ አይችልም። የትኛውም የሰው ዘር “የኦርዮንን ማሰሪያ” ለመፍታት አይችልም። ይሖዋ የትኞቹን ኅብረ ከዋክብት ማዛሮት ወይም ድብ ብሎ እንደጠራቸው እርግጠኛ ባንሆንም እንኳ እነርሱን ለመቆጣጠርና ለመምራት የሚችል ማንም ሰብዓዊ ፍጡር እንደሌለ ግን እናውቃለን። ሰዎች “የሰማያትን ሥርዓት” ማለትም አጽናፈ ዓለሙን የሚመሩትን ሕግጋት መለወጥ አይችሉም።
በምድር የአየር ንብረት፣ የባሕር ሞገድና ከባቢ አየር እንዲሁም በፕላኔቷ ላይ በሚገኝ ሕይወት ሕልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉት የሰማይ አካላት የሚመሩበትን ሕግ ያወጣው አምላክ ነው። ፀሐይን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና (የ1996 እትም) እንዲህ ይላል:- “የፀሐይ ጨረር ለምድር ሙቀትና ብርሃን ከመስጠቱ በተጨማሪ ተክሎች እንዲያድጉ፣ ከውቅያኖሶችና ከሌሎች የውኃ አካላት ላይ ውኃ እንዲተንን እንዲሁም ነፋስ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ በምድር ላይ ላለው ሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን በማከናወን ረገድም የራሱ የሆነ ሚና ይጫወታል።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በፀሐይ ብርሃን ውስጥ ያለው ኃይል ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ለመረዳት ነፋስ፣ ግድቦችና ወንዞች ያላቸው ኃይል እንዲሁም እንደ እንጨት፣ ከሰልና የነዳጅ ዘይት በመሳሰሉት የተፈጥሮ የነዳጅ ምንጮች ውስጥ የሚገኘው ኃይል በሙሉ አንዲት ትንሽ ፕላኔት [ምድር] ከእርሷ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ከፀሐይ የወሰደችው እንደሆነ ማሰቡ ብቻ በቂ ነው።”
በደመናት ውስጥ ጥበብን ያኖረ ማን ነው?
ይሖዋ ደመናትን አስተውሎ እንዲመለከትም ለኢዮብ ነግሮታል። (ኢዮብ 38:34-38) ሰው ዝናብ ያዘለ ደመና በውስጡ የያዘውን ውኃ እንዲለቅ ማዘዝ አይችልም። ሆኖም የሰው ልጅ ፈጣሪ ያዘጋጀው የውኃ ዑደት በጣም ያስፈልገዋል።
የውኃ ዑደት ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይናገራል:- “የውኃ ዑደት አራት የተለያዩ ክፍሎች አሉት፤ እነርሱም የውኃ መከማቸት፣ ትነት፣ ዝናብና ፍሰት ናቸው። ውኃ ከምድር በታች፣ በውቅያኖስ፣ በሐይቅና በወንዝ ውስጥ እንዲሁም በዋልታዎች ላይ በሚገኙ በረዷማ ቦታዎችና በግግር በረዶ መልክ ለተወሰነ ጊዜ ሊከማች ይችላል። ይህ ውኃ ከምድር ገጽ ላይ በመትነን ደመና ይሠራል። ከዚያም በዝናብ ወይም በበረዶ መልክ ወደ ምድር ይወርድና ወይ ወደ ባሕር ይፈሳል አሊያም ተንኖ ወደ ከባቢ አየር ይጓዛል። በምድር ላይ ያለው ውኃ ሁሉ ማለት ይቻላል ለቁጥር ለሚታክቱ ጊዜያት በዚህ ዑደት ውስጥ አልፏል።”—ማይክሮሶፍት ኢንካርታ ሪፈረንስ ላይብራሪ 2005
ዝናብ አዘል ደመናዎች በሰማይ እንዳሉ የውኃ መያዣ ገንቦዎች ናቸው። ይሖዋ እነርሱን ዘምበል ሲያደርግ የያዙትን ውኃ ይለቁታል። በዚህም ምክንያት አቧራው ወደ ጭቃነት ይለወጣል፤ እንዲሁም አፈሩ ጓል ይሆናል። አምላክ ዝናብን ለማዝነብም ሆነ እንዳይዘንብ ለማድረግ ኃይል አለው።—ያዕቆብ 5:17, 18
አብዛኛውን ጊዜ ዝናብ ሲጥል መብረቅ ይኖራል። ይሁን እንጂ ሰው ፈቃዱን ለማስፈጸም በመብረቅ መጠቀም አይችልም። መብረቆች ለአምላክ “እነሆ፤ እዚህ አለን” ብለው እንደሚታዘዙት ተደርገው ተገልጸዋል። የኮምፕተን ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል:- “መብረቅ በከባቢ አየር ውስጥ ጠቃሚ የሆነ ኬሚካላዊ ለውጥ እንዲካሄድ ያደርጋል። መብረቅ በአየር ውስጥ በሚጓዝበት ወቅት ከፍተኛ ሙቀት የሚያመነጭ ሲሆን ይህም ናይትሮጅንና ኦክስጅን እንዲዋሃዱ በማድረግ ናይትሬትና ሌሎች ውሕዶችን ያስገኛል። እነዚህ ውሕዶች ከዝናብ ጋር ወደ ምድር ይወርዳሉ። በዚህ መንገድ ከባቢ አየር ለተክሎች እድገት አስፈላጊ የሆኑትን በአፈር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች አለማቋረጥ ያቀርባል።” አሁንም ቢሆን የሰው ዘር መብረቅን አስመልክቶ ያለው እውቀት ውስን ሲሆን ለአምላክ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው።
አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች ለአምላክ ውዳሴ ያመጣሉ
እውነትም ፍጥረታት የሁሉ ነገር ፈጣሪ ለሆነው አምላክ ውዳሴ ያመጣሉ። (ራእይ 4:11) ይሖዋ ምድርንና በሰማይ ያሉ አካላትን አስመልክቶ የተናገረው ነገር ኢዮብን ምንኛ አስደንቆት ይሆን!
አስደናቂ የሆኑትን የፍጥረት ሥራዎች አስመልክቶ ለኢዮብ ከቀረቡለት ጥያቄዎችና ከተሰጡት መግለጫዎች መካከል እስካሁን የተመለከትነው የተወሰኑትን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህም እንኳ ቢሆኑ “እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአእምሯችን በላይ ታላቅ ነው” እንድንል ያደርጉናል።—ኢዮብ 36:26
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የበረዶ ቅንጣት:- snowcrystals.net
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ፕልያዲስ:- NASA, ESA and AURA/Caltech; ዓሣ:- U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./William W. Hartley