የሕይወትህ ዓላማ ምንድን ነው?
‘የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ . . . የሚሠሩት መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስካይ ድረስ ልቤን በጥበብ መራሁት።’— መክብብ 2:3
1, 2. ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለ ራሳችን ማሰባችን ስህተት የማይሆነው ለምንድን ነው?
ስለ ራስህ ታስባለህ፤ አይደለም እንዴ? ይህ ተፈጥሮአዊ ስሜት ነው። በመሆኑም በየዕለቱ እንመገባለን፣ ሲደክመን እንተኛለን፣ ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍም ያስደስተናል። አንዳንድ ጊዜ እንጫወታለን፣ እንዋኛለን ወይም የሚያስደስቱንን ሌሎች ነገሮች እናደርጋለን፤ ይህም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለ ራሳችን እንደምናስብ ያሳያል።
2 በዚህ መንገድ ስለ ራሳችን የምናስብ መሆኑ አምላክ ሰሎሞንን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት በድካሙም ነፍሱን ደስ ከማሰኘት ይበልጥ የሚሻል ነገር የለም” በማለት እንዲጽፍ ካነሳሳው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው። ሰሎሞን ከራሱ ተሞክሮ በመነሣት እንዲህ ሲል ጨምሮ ተናግሯል:- “ይህም ደግሞ ከአምላክ እጅ እንደተሰጠ እኔ ራሴ አይቻለሁ። ከእኔ ይበልጥ የበላና የጠጣስ ማን አለ?”— መክብብ 2:24, 25 NW
3. አብዛኞቹ ሰዎች መልስ ያላገኙላቸው ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
3 ይሁንና ሕይወት ማለት መብላት፣ መጠጣት መተኛትና አንዳንድ መልካም ነገሮችን ማከናወን ማለት ብቻ እንዳልሆነ ታውቃለህ። ሕመም፣ ያልተጠበቁ አሳዛኝ ሁኔታዎችና የሚያስጨንቁ ነገሮች ይገጥሙናል። ስለ ሕይወታችን ትርጉም ቆም ብለን ለማሰብ ጊዜ ያጣን ይመስላል። ያንተ ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነውን? ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው መጽሔት አዘጋጅ የነበሩት ቨርመንት ሮይስተር የሰው ልጅ የደረሰበትን ከፍተኛ እውቀትና ጥበብ ከገለጹ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር አለ። ስለ ራሱ ስለ ሰው ልጅ፣ ግራ ስለሚያጋቡ ጥያቄዎቹና ሰው በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ስላለው ቦታ ስናስብ በፍጥረት መጀመሪያ ከነበረው ነገር የተሻለ አላወቅንም። እኛ ማን ነን? የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? እና መጨረሻችንስ ምን ይሆን? ለሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም ቢሆን መልስ አላገኘንም።”
4. እኛን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች እያንዳንዳችን መልስ ማግኘት መቻል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
4 እኛ ማን ነን? የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? እና መጨረሻችንስ ምን ይሆን? ለሚሉት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ? ሚስተር ሮይስተር ባለፈው ሐምሌ አርፈዋል። ከመሞታቸው በፊት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያገኙ ይመስልሃል? የእርሳቸውን እንተወውና አንተስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የምታገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? ይህስ ይበልጥ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
ማስተዋል የሚገኝበት ዋነኛ ምንጭ
5. ስለ ሕይወት ትርጉም የሚነሱትን ጥያቄዎች በሚመለከት ማስተዋል ለማግኘት ወደ አምላክ ዘወር ማለት የሚገባን ለምንድን ነው?
5 የሕይወታችን ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ መፈለጉ ለእያንዳንዳችን የተተወ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ትምህርትና ተሞክሮ አግኝተዋል እንደሚባሉት ብዙ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ የእኛም ጥረት የሚያስገኘው ውጤት በጣም ውስን አለዚያም ጭራሹኑ ፍሬ አልባ ሊሆን ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ እንድናደርግ ብቻችንን አልተተውንም። ፈጣሪያችን እርዳታ አዘጋጅቶልናል። እንዲያው ስታስበው “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖርና ስለ አጽናፈ ዓለምም ሆነ ስለ ታሪክ የተሟላ እውቀት ያለው የመጨረሻው የማስተዋልና የጥበብ ምንጭ እርሱ አይደለምን? (መዝሙር 90:1, 2) ሰዎችን ከመፍጠሩም ሌላ የሰው ልጅ ያሳለፋቸውን ነገሮች ሁሉ ከመጀመሪያ አንስቶ ሲመለከት ቆይቷል፤ ስለዚህ ማስተዋል ለማግኘት ፊታችንን ማዞር የሚገባን እውቀታቸውና የማስተዋል ችሎታቸው ውስን ወደ ሆነው ወደ ሰው ልጆች ሳይሆን ወደ እርሱ ነው።— መዝሙር 14:1-3፤ ሮሜ 3:10-12
6. (ሀ) ፈጣሪ አስፈላጊውን ማስተዋል የሚሰጠን በምን አማካኝነት ነው? (ለ) ሰሎሞን በዚህ በኩል ምን ድርሻ አበርክቷል?
6 ምንም እንኳ ፈጣሪ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ በግል ይነግረናል ብለን መጠበቅ ባንችልም ማስተዋል የምናገኝበትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ቃሉን ሰጥቶናል። (መዝሙር 32:8፤ 111:10) በተለይ የመክብብ መጽሐፍ በዚህ ረገድ በጣም ጠቃሚ ነው። አምላክ ለመጽሐፉ ጸሐፊ መንፈሱን ስለ ሰጠው ‘የሰሎሞን ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በልጦ ተገኝቷል።’ (1 ነገሥት 3:6-12፤ 4:30-34) ልትጎበኘው የመጣች አንዲት ንግሥት ‘በሰሎሞን ጥበብ’ በጣም በመገረሟ ስለ እርሱ ጥበብ የነገሯት እኩሌታውን ብቻ እንደነበረና የእርሱን ጥበብ የሚሰሙ ደስተኞች እንደሆኑ ተናግራለች።a (1 ነገሥት 10:4-8) እኛም ብንሆን ፈጣሪያችን በሰሎሞን አማካኝነት ካስተላለፈው መለኮታዊ ጥበብ ጥልቅ ማስተዋልና ደስታ ልናገኝ እንችላለን።
7. (ሀ) ሰሎሞን ከፀሐይ በታች ስለሚከናወኑት አብዛኞቹ ነገሮች ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? (ለ) ሰሎሞን ተጨባጭ ግምገማ እንዳቀረበ የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 የመክብብ መጽሐፍ የሰሎሞንን ልብና አእምሮ የለወጠው አምላካዊ ጥበብ የተንጸባረቀበት መጽሐፍ ነው። ሰሎሞን ጊዜ፣ ብዙ ሀብትና ጥልቅ ማስተዋል ስለነበረው “ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ” መርምሯል። አብዛኛው ነገር “ከንቱ . . . ነፋስንም እንደ መከተል” እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፤ ይህ አባባሉ ስለ ሕይወታችን ዓላማ ስናስብ ልናስታውሰው የሚገባ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረ ቃል ነው። (መክብብ 1:13, 14, 16) ሰሎሞን በግልጽነት ሐቁን ሳይሸሽግ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል እስቲ በመክብብ 1:15 እና 18 ላይ ስለተናገራቸው ቃላት ረጋ ብለህ አስብ። ላለፉት በርካታ መቶ ዘመናት ሰዎች የተለያዩ ዓይነት መስተዳድሮችን እንደሞከሩ ታውቃለህ፤ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ለሰዎች ችግር እልባት ለመስጠትና የሕዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል በቅንነት የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ማንኛቸውስ ቢሆኑ በዚህ ፍጽምና የሌለው ሥርዓት ውስጥ ያሉትን “ጠማማ” ነገሮች ሁሉ ሊያስተካክሉ ችለዋልን? አንድ ሰው እውቀቱ ይበልጥ እየሰፋ በሄደ መጠን የዚያኑ ያክል በአጭሯ የሕይወት ዘመኑ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ማስተካከል የማይሞከር ነገር እንደሆነ እየተገነዘበ እንደሚመጣ አንተም አስተውለህ ይሆናል። ብዙዎች ይህን መገንዘባቸው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል፤ እኛ ግን እንደዚህ ላይሰማን ይችላል።
8. ከጥንት ጀምሮ የነበሩት ዑደቶች የትኞቹ ናቸው?
8 ሌላው የምንመለከተው ነገር ደግሞ እንደ ፀሐይ መውጣትና መጥለቅ ወይም የነፋስና የውኃ እንቅስቃሴ የመሳሰሉትን በዙሪያችን ያሉ ተደጋጋሚ ዑደቶች ነው። እነዚህ ዑደቶች በሙሴ፣ በሰሎሞን፣ በናፖሊዮንና በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ሁሉ ነበሩ። አሁንም አሉ። በተመሳሳይም “ትውልድ ይሄዳል፣ ትውልድም ይመጣል።” (መክብብ 1:4-7) በሰው ዓይን ሲታይ ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። የጥንቶቹም ሆኑ ዛሬ ያሉት ሰዎች፣ የሚሠሩት ሥራ፣ ተስፋቸው፣ ምኞታቸው እና ያገኙት ውጤት ሁሉ ይመሳሰላል። ትልቅ ስም ያተረፉ ወይም በውበታቸው አለዚያም በችሎታቸው የተወደሱ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። አሁን እነዚህ ሰዎች የት አሉ? አልፈዋል፤ ምናልባትም ተረስተዋል። ይህንን ስንል ግን አፍራሽ አስተሳሰብ መያዛችን አይደለም። አብዛኞቹ ሰዎች ቅድመ አያቶቻቸው እነማን እንደሆኑ ወይም የት እንደተወለዱና የት እንደተቀበሩ እንኳ አያውቁም። ሰሎሞን የሰው ልጅ ድካምና ጥረት ሁሉ ከንቱ ነው በማለት የደመደመው ለምን እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም።— መክብብ 1:9-11
9. ስለ ሰው ልጅ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ጥልቅ ማስተዋል ማግኘታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
9 ስለ ሰው ልጅ መሠረታዊ ሁኔታ ይህን አምላካዊ ማስተዋል ማግኘታችን ተስፋ አያስቆርጠንም፤ ከዚህ ይልቅ ቶሎ ለሚጠፉና ለሚረሱ ግቦች የተሳሳተ ግምት ከማሳደር እንድንቆጠብ ስለሚገፋፋን ሊጠቅመን ይችላል። ከሕይወት ምን እያገኘን እንደሆነና በሕይወታችን ምን ነገር ለማከናወን እየጣርን እንዳለን እንድንገመግም ሊረዳን ይገባል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ራሳቸውን ጨቁነው እንደሚኖሩት መናኞች ከመሆን ይልቅ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በመብላትና በመጠጣት ደስታ ልናገኝ እንችላለን። (መክብብ 2:24) ቀጥሎ እንደምንመለከተው ሰሎሞን ፍጹም አዎንታዊና ብሩህ የሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ባጭሩ የደረሰበት መደምደሚያ ደስታ የሰፈነበትና ዘላለማዊ ዓላማ ያለው የወደፊት ተስፋ ሊሰጠን ከሚችለው ፈጣሪያችን ጋር ያለንን ዝምድና ከልብ ልናደንቀው ይገባል የሚል ነው። ሰሎሞን እንደሚከተለው በማለት ጉዳዩን ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው [“ሁለንተናዊ ግዴታው፣” NW] ነውና እግዚአብሔርን ፍራ ትእዛዛቱንም ጠብቅ።”— መክብብ 12:13
የሕይወት ዑደቶች ስለ ሕይወት ዓላማ ምን ያስገነዝቡናል?
10. ሰሎሞን እንስሳትንና ሰዎችን ያወዳደረው በምን መንገድ ነው?
10 ከዚህ በተጨማሪ በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የተንጸባረቀው መለኮታዊ ጥበብ የሕይወታችንን ዓላማ እንድመረምር ይረዳናል። እንዴት? ሰሎሞን እምብዛም የማናስብባቸውን ሌሎች እውነቶችም በሐቀኝነት ተመልክቷል። አንዱ በሰዎችና በእንስሳት መካከል ያለው ተመሳሳይነት ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን ከበጎች ጋር አመሳስሏቸዋል፤ ይሁንና ሰዎች ባጠቃላይ ከእንስሳት ጋር ሲወዳደሩ ደስ አይላቸውም። (ዮሐንስ 10:11-16) ሆኖም ሰሎሞን አንዳንድ የማይታበሉ ሐቆችን ተናግሯል:- “እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር [የሰው ልጆችን] ይፈትናቸዋል አልሁ። የሰው ልጆችና የእንስሳ ዕድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላው እንዲሁ ይሞታል፤ . . . ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። . . . ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።”— መክብብ 3:18-20
11. (ሀ) የአንድ እንስሳ የሕይወት ዑደት እንዴት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል? (ለ) እንዲህ ስላለው ግምገማስ ምን ይሰማሃል?
11 እስቲ ስለሚያስደስትህ አንድ እንስሳ አስብ፤ እንስሳው ሽኮኮ ወይም ጥንቸል ሊሆን ይችላል። (ዘዳግም 14:7፤ መዝሙር 104:18፤ ምሳሌ 30:26) ወይም ስለ ሙጭጭላ (አላጅ) ልታስብ ትችላለህ፤ በምድር ዙሪያ ከ300 የሚበልጥ ዓይነት ያላቸው የሙጭጭላ ዝርያዎች አሉ። የዚህ እንስሳ የሕይወት ዑደት ምን ይመስላል? ከተወለደ በኋላ እናቱ ለጥቂት ሳምንታት ትንከባከበዋለች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰውነቱ ጠጉር ስለሚያበቅል ወጣ ወጣ ማለት ይጀምራል። ምግብ መፈላለግን ለመማር ወዲያና ወዲህ ሲሮጥ ታየው ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እንዲሁ ሲጫወትና ሲቦርቅ ይታያል። አንድ ዓመት ገደማ ከቆየ በኋላ ተጓዳኝ መፈለግ ይጀምራል። ከዚያም ልጆቹን የሚያሳድግበት ጎጆ ወይም ጎሬ መሥራት ይኖርበታል። የሙጭጭላው ቤተሰብ ፍራፍሬ፣ ለውዝ እና ጥራጥሬ እንደ ልብ ካገኘ እያደገ ስለሚሄድ ቤታቸውን ማስፋት ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንስሳው ያረጅና ለአደጋና ለበሽታ ይበልጥ የተጋለጠ ይሆናል። አሥር ዓመት ገደማ ከኖረ በኋላ ይሞታል። በሙጭጭላ ዝርያዎች መካከል ጥቂት ልዩነት ቢኖርም ባጠቃላይ የሕይወት ዑደቱ ከዚህ የተለየ አይደለም።
12. (ሀ) በሐቅ ሲታይ የብዙ ሰዎች የሕይወት ዑደት ከእንስሳት ጋር ተመሳሳይ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአእምሮህ የያዝከውን አንድ እንስሳ ሌላ ጊዜ ስታይ ስለ ምን ነገር ልታስብ ትችላለህ?
12 አብዛኞቹ ሰዎች የአንድ እንስሳ የሕይወት ዑደት ይህን ይመስላል የሚለውን ሐሳብ አይቃወሙም፤ ደግሞም ሙጭጭላ የሕይወት ዓላማ ኖሮት ሕይወቱን ከዚህ በተሻለ መንገድ በማስተዋል ይመራል ብለው አያስቡም። ይሁን እንጂ የብዙ ሰዎች ሕይወት ከዚህ እምብዛም አይለይም፤ አይደለም እንዴ? ከተወለዱ በኋላ በሕፃንነታቸው እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። ይበላሉ፣ ያድጋሉ፣ በልጅነታቸው ይጫወታሉ። ብዙም ሳይቆይ ነፍስ ያውቁና የትዳር ጓደኛ ይፈልጋሉ፤ መኖሪያ ቦታና የዕለት ጉርስ ለማግኘት ይጣጣራሉ። ከተሳካላቸው ይወልዳሉ ልጆቻቸውንም ለማሳደግ ቤታቸውን (ጎጆአቸውን) ያሰፋሉ። ይሁን እንጂ እነዚያ አሥርተ ዓመታት በቅጽበት ያልፉና ያረጃሉ። “በመከራና በሐዘን” ከተሞሉ 70 ወይም 80 ዓመታት በኋላ ይሞታሉ፤ ለዚያውም ሞት ካልቀደማቸው። (መዝሙር 90:9, 10, 12 የ1980 ትርጉም) ሌላ ጊዜ ሙጭጭላ (ወይም በአእምሮህ የያዝከውን እንስሳ) ስታይ እነዚህን እውነታዎች በቁም ነገር ልታስብባቸው ትችላለህ።
13. እንስሳትም ሆኑ ሰዎች በመጨረሻ ምን ይሆናሉ?
13 ሰሎሞን የሰዎችን ሕይወት ከእንስሳ ሕይወት ጋር ያወዳደረበትን ምክንያት ማስተዋል ትችላለህ። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለሁሉ ዘመን አለው፣ . . . ለመወለድ ጊዜ አለው፣ ለመሞትም ጊዜ አለው።” የኋለኛው የሰውና የእንስሳት ዕጣ ፋንታ አንድ ዓይነት ነው “አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል።” አክሎም “ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈርም ይመለሳል” ሲል ተናግሯል።— መክብብ 3:1, 2, 19, 20
14. አንዳንድ ሰዎች የተለመደውን የሕይወት ዑደት ለመለወጥ የሚሞክሩት እንዴት ነው? ይሁን እንጂ ውጤቱ ምንድን ነው?
14 ይህ በሐቀኝነት የተደረገ ግምገማ አሉታዊ አስተሳሰብ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይገባንም። አንዳንዶች ተጨማሪ ሥራዎችን ሠርተው ከወላጆቻቸው የሚበልጥ ቁሳዊ ሀብት በማካበት ሁኔታውን ለመለወጥ እንደሚሞክሩ አይካድም። ስለ ሕይወት ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋትና የተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማግኘት ሲሉ የብዙ ዓመታት ትምህርት ይከታተሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ የተሻለ ጤና ለማግኘትና ረጅም ዕድሜ ለመኖር ሲሉ የአካል እንቅስቃሴ ያደርጉ ወይም የአመጋገብ ስልታቸውን ይለውጡ ይሆናል። እነዚህ ጥረቶች አንዳንድ ጥቅሞችን ያስገኙላቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥረቶች የተሳካ ውጤት ያስገኛሉ ብሎ እርግጠኛ ሊሆን የሚችል ማን አለ? የተሳካ ውጤት ቢያስገኙ እንኳ ጠቀሜታቸው ምን ያህል ዘላቂ ይሆናል?
15. ስለ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሕይወት በግልጽ የተነገረው የትኛው አባባል እውነትነት አለው?
15 ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? ሰው በከንቱ ወራቱ ቁጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው . . . ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?” (መክብብ 6:11, 12) ሰው የሚያደርገው ጥረት በሞት ምክንያት የሚጨናገፍ ከሆነ ብዙ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ ወይም ብዙ ንብረት ለማካበት የብዙ ዓመታት ትምህርት መከታተሉ እርባናው ምኑ ላይ ነው? ብዙ ሰዎች ሕይወት በጣም አጭርና እንደ ጥላ አላፊ በመሆኑ ያወጡት ሰብዓዊ ግብ እንደማይሰምርላቸው ሲረዱ ሌላ ግብ ለመቀየስ በቂ ጊዜ እንደማይኖራቸው ተገንዝበዋል። እንዲሁም አንድ ሰው “ከእርሱ በኋላ” ልጆቹ ምን እንደሚገጥማቸው ማወቅ አይችልም።
መልካም ስም ለማትረፍ ጊዜው አሁን ነው
16. (ሀ) እንስሳት ሊያደርጉት የማይችሉት እኛ ግን ልናደርገው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? (ለ) በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚገባው ሌላው እውነት የትኛው ነው?
16 እኛ ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ ‘በሕይወት የመኖሬ ዓላማ ምንድን ነው? ከተወሰነው የመወለድና የመሞት ዑደት በስተቀር ሌላ ነገር የለም ማለት ነው?’ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰብ እንችላለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰሎሞን ስለ ሰውና እንስሳት በተናገራቸው ቃላት ውስጥ ያለውን እውነት አስታውስ:- “ሁሉ ወደ አፈር ይመለሳሉ።” ታዲያ ይህ ማለት ሞት የአንድ ሰው ሕልውና መጨረሻ ነው ማለት ነውን? እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከሞት በኋላ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ አላቸው ብሎ አይናገርም። ሰዎች ነፍሳት ናቸው፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ ደግሞ ትሞታለች። (ሕዝቅኤል 18:4, 20) ሰሎሞን እንዲህ ሲል አብራርቶታል:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፣ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”— መክብብ 9:5, 10
17. መክብብ 7:1, 2 ስለ ምን ነገር እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል?
17 ከዚህ ሊታበል የማይችል ሐቅ አንጻር እስቲ የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት:- “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፣ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።” (መክብብ 7:1, 2) ሞት “የሰው ሁሉ ፍጻሜ” መሆኑን አንክድም። ዕድሜ የሚያራዝም መድኃኒት በመጠጣት፣ ቫይታሚኖች በመውሰድ፣ የአመጋገብ ስልት በመቀየስ ወይም በአንድ ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ በመካፈል ለዘላለም መኖር የቻለ አንድም ሰው የለም። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘መታሰቢያው ሁሉ ይረሳል።’ ታዲያ “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” የተባለው ለምንድን ነው?
18. ሰሎሞን በትንሣኤ ያምን እንደ ነበር እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
18 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሰሎሞን የተናገረው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ነው። በፈጣሪያችን ዘንድ መልካም ስም አትርፈው ስለነበሩት የቀድሞ አባቶቹ ስለ አብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆብ ያውቃል። ይሖዋ አምላክ ከአብርሃም ጋር በሚገባ ይተዋወቅ ስለነበር እርሱንና ዘሩን ለመባረክ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 18:18, 19፤ 22:17) አዎን፣ አብርሃም በአምላክ ዘንድ መልካም ስም በማትረፉ ወዳጁ ሆኗል። (2 ዜና መዋዕል 20:7፤ ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23) አብርሃም የእርሱም ሆነ የልጁ ሕይወት ማቆሚያ የሌለው የመወለድና የመሞት ሂደት ክፍል እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ሕይወት ከዚህ የተሻለ ዓላማ እንዳለው አያጠራጥርም። እንደገና የመኖር አስተማማኝ ተስፋ ነበራቸው። ይህ የሆነው የማይሞት ነፍስ ስላላቸው ሳይሆን ትንሣኤ ስለሚያገኙ ነው። አብርሃም “እግዚአብሔር [ይስሐቅን] ከሙታን እንኳ ሊያነሣው እንዲቻለው” አጥብቆ ያምን ነበር።— ዕብራውያን 11:17-19
19. የመክብብ 7:1ን ትርጉም በሚመለከት ከኢዮብ መጽሐፍ ምን ማስተዋል ማግኘት እንችላለን?
19 “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ከመወለድም ቀን የሞት ቀን” ይሻላል የሚለውን ቃል ለመረዳት ቁልፉ ይኸው ነው። ሰሎሞን ከእርሱ በፊት ይኖር እንደነበረው እንደ ኢዮብ የሰዎችን ሕይወት የፈጠረው አምላክ ሙታንን መልሶ ሕያው ማድረግ እንደማያቅተው አጥብቆ ያምን ነበር። የሞቱትን ሰዎች ማስነሳት ይችላል። (ኢዮብ 14:7-14) የታመነው ኢዮብ እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜ አንተ ትጠራኛለህ፤ እኔም ‘አቤት’ አልሃለሁ፤ ፍጡርህ የሆንኩትን እኔን ለማየት ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:15 የ1980 ትርጉም) እስቲ ቆም ብለህ አስብ! ፈጣሪያችን የሞቱትን ታማኝ አገልጋዮቹን ‘ይናፍቃል።’ (ዘ ጀሩሳሌም ባይብል “የእጅህን ሥራ እንደገና ለማየት በጓጓህ ነበር” ይላል።) ፈጣሪ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት ተጠቅሞ ሰዎችን ከሞት ሊያስነሣ ይችላል። (ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 24:15) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሰዎች ሟች ከሆኑት እንስሳት የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ።
20. (ሀ) ከመወለድ ቀን የሞት ቀን የተሻለ ሆኖ የሚገኘው መቼ ነው? (ለ) የአልዓዛር ትንሣኤ ብዙዎችን እንዴት ነክቷቸው መሆን አለበት?
20 በዚህ መሠረት አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ በሞት ያንቀላፉትን የታመኑ ሰዎች ሊያስነሣ በሚችለው በይሖዋ ዘንድ ጥሩ ስም አትርፎ ከሆነ ከተወለደበት ቀን የሞተበት ቀን የተሻለ ሊሆን ይችላል። ታላቁ ሰሎሞን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አረጋግጧል። ለምሳሌ ያህል የታመነውን አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። (ሉቃስ 11:31፤ ዮሐንስ 11:1-44) አልዓዛር ከሞት መነሣቱን ያዩ ብዙ ሰዎች በጣም በመነካታቸው በአምላክ ልጅ ላይ ምን ያህል እምነት እንዳሳደሩ ልትገምት ትችላለህ። (ዮሐንስ 11:45) ማንነታቸውንና የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘላቸው የማያውቁ፣ ሕይወት ዓላማ እንደሌለው የሚሰማቸው ሰዎች ይመስሉሃል? በፍጹም አልነበሩም፤ ተወልደው ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ በመጨረሻ እንደሚሞቱ እንስሳት መሆን እንደሌለባቸው መገንዘብ ችለው ነበር። የሕይወታቸው ዓላማ የኢየሱስን አባት ከማወቃቸውና ፈቃዱን ከማድረጋቸው ጋር በቀጥታና በጥብቅ የተሳሰረ ነበር። አንተስ? ይህ ትምህርት ሕይወትህ እውነተኛ ዓላማ እንዴት ሊኖረው እንደሚችልና እንደሚገባው እንድታስተውል ወይም ደግሞ የነበረህን ማስተዋል እንድታሳድግ ረድቶሃልን?
21. ትርጉም ያለው ሕይወት በማግኘት ረገድ ወደፊት ልንመረምረው የምንፈልገው ጉዳይ ምንድን ነው?
21 ይሁንና እውነተኛና ትርጉም ያለው የሕይወት ዓላማ መጨበጥ ማለት ስለሞትና ከዚያ በኋለ እንደገና ስለመኖር ማሰብ ማለት ብቻ አይደለም። በዕለታዊ ሕይወታችን የምናከናውነውንም ነገር የሚጨምር ነው። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ሰሎሞን ይህንን ጉዳይ በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ አብራርቷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የሳባ ንግሥት ታሪክ የሰሎሞንን ጥበብ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ሲሆን ብዙውን ጊዜ አፈ ታሪክ እንደሆነ ይነገራል (1 ነገ. 10:1-13)። ይሁን እንጂ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ሰሎሞን ዘንድ በመሄድ ያደረገችው ጉብኝት ከንግድ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ የማይመስል ነገር አይደለም፤ ታሪካዊ ሐቅነቱ ምንም ሊያጠራጥር አይገባም።”— ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፔድያ (1988) ጥራዝ 4 ገጽ 567
ታስታውሳለህን?
◻ እንስሳትና ሰዎች የሚነጻጸሩባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ሞት አብዛኛው የሰው ልጅ ጥረትና እንቅስቃሴ ከንቱ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳየው እንዴት ነው?
◻ ከመወለድ ቀን የሞት ቀን የተሻለ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ለሕይወታችን ትርጉም ያለው ዓላማ ማግኘታችን በየትኛው ዝምድና ላይ የተመካ ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሕይወትህ ከእንስሳት ሕይወት የሚለይበት ዓቢይ ነገር ምንድን ነው?