በይሖዋ ቃል ታመኑ
“በቃልህ ታምኛለሁ።”—መዝሙር 119:42
1. የመዝሙር 119ን ጸሐፊ ማንነትና ባሕርይ በተመለከተ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
የመዝሙር 119 አቀናባሪ ለይሖዋ ቃል ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ጸሐፊው የይሁዳ መስፍን የነበረው ሕዝቅያስ እንደሆነ ይገመታል። በዚህ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈ መዝሙር ውስጥ የተንጸባረቀው ስሜት የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ወቅት ‘ከእግዚአብሔር ጋር እንደተጣበቀ’ የተነገረለት ሕዝቅያስ ካሳየው ባሕርይ ጋር ይጣጣማል። (2 ነገሥት 18:3-7) ያም ሆነ ይህ አንድ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር አለ:- የመዝሙሩ አቀናባሪ ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር።—ማቴዎስ 5:3
2. የመዝሙር 119 ጭብጥ ምንድን ነው? መዝሙሩ የተቀናበረውስ እንዴት ነው?
2 በመዝሙር 119 ላይ የጎላው ነጥብ የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ያለው ጠቀሜታ ነው።a ጸሐፊው መዝሙሩን ያሠፈረው በፊደል ቅደም ተከተል ሲሆን ይህም ለማስታወስ እንዲረዳው ብሎ ያደረገው ይሆናል። አንድ መቶ ሰባ ስድስት ጥቅሶችን የያዘው ይህ መዝሙር በዕብራይስጥ ሆሄ ቅደም ተከተል መሠረት የተጻፈ ነው። መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ በመዝሙሩ ውስጥ የሚገኙት 22 አንቀጾች በተመሳሳይ ፊደል የሚጀምሩ 8 መስመሮች ነበሯቸው። መዝሙሩ ስለ አምላክ ቃል፣ ሕግ፣ ምስክርነት (ማሳሰቢያዎች)፣ መንገዶች፣ ደንቦች፣ ሥርዓቶች፣ ትእዛዛት፣ ፍርዶች፣ ቃሎችና ድንጋጌዎች ይናገራል። በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መዝሙር 119 በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ትርጉም መሠረት ይብራራል። ጥንት የነበሩና በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ባሳለፉት ሕይወት ላይ ማሰላሰላችን በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው ለዚህ መዝሙር ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፋልን ከመሆኑም ሌላ በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ማለትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለንን አመስጋኝነት ያሳድግልናል።
የአምላክን ቃል በመታዘዝ ደስተኞች ሁኑ
3. ነቀፋ የለብንም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
3 እውነተኛ ደስታ ማግኘታችን የተመካው በአምላክ ሕግ በመመራታችን ላይ ነው። (መዝሙር 119:1-8) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ‘በመንገዳችን ነቀፋ የሌለብን’ እንደሆንን አድርጎ ይቆጥረናል። (መዝሙር 119:1) ነቀፋ የለብንም ሲባል ፍጹማን ነን ማለት ሳይሆን የይሖዋ አምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው። ኖኅ ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ’ “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ . . . ከበደል የራቀ ሰው ነበር።” ይህ ታማኝ የእምነት አባትና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ ሊተርፉ የቻሉት ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት በመኖሩ ነው። (ዘፍጥረት 6:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:20) በተመሳሳይ የዚህን ዓለም ፍጻሜ በሕይወት ማለፋችን የተመካው የአምላክን ‘ሥርዐት ጠንቅቀን በመጠበቃችን’ ይኸውም ፈቃዱን በመፈጸማችን ላይ ነው።—መዝሙር 119:4
4. ደስተኛና ስኬታማ መሆናችን በምን ላይ የተመካ ነው?
4 ይሖዋ ‘በቅን ልብ ምስጋና የምናቀርብለትና ሥርዐቱን የምንጠብቅ’ ከሆነ ፈጽሞ አይተወንም። (መዝሙር 119:7, 8) እስራኤላዊው መሪ ኢያሱ ‘በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ መፈጸም እንዲችል መጽሐፉን ቀንም ሆነ ሌሊት’ እንዲያነበው የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረጉ የአምላክ ድጋፍ አልተለየውም። እንዲህ ማድረጉ ስኬታማ እንዲሆንና የጥበብ እርምጃ እንዲወስድ አስችሎታል። (ኢያሱ 1:8) ኢያሱ የሕይወቱ ማብቂያ በተቃረበበት ወቅትም አምላክን ማመስገኑን የቀጠለ ከመሆኑም ሌላ እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) እንደ ኢያሱና እንደ መዝሙር 119 ጸሐፊ ሁሉ እኛም ይሖዋን በማወደስና በቃሉ በመታመን ደስታና ስኬት ማግኘት እንችላለን።
የይሖዋ ቃል ንጹሕ እንድንሆን ያስችለናል
5. (ሀ) በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆኖ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (ለ) ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ወጣት ምን እርዳታ ሊያገኝ ይችላል?
5 የአምላክ ቃል የሚናገረውን አክብረን ከኖርን በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን እንችላለን። (መዝሙር 119:9-16) ወላጆቻችን ጥሩ ምሳሌ ባይሆኑን እንኳ እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። ምንም እንኳ አባቱ ጣዖት አምላኪ የነበረ ቢሆንም ሕዝቅያስ ‘መንገዱን አንጽቶ’ ነበር፤ እንዲህ የተባለው ከአረማውያን ተጽዕኖ በመራቁ ሊሆን ይችላል። በዛሬው ጊዜ አምላክን የሚያገለግል አንድ ወጣት ከባድ ኃጢአት ፈጸመ እንበል። ንስሐ መግባት፣ ጸሎት፣ ከወላጆቹ የሚያገኘው እርዳታና ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጡት ፍቅራዊ ድጋፍ ሕዝቅያስን እንዲመስል እንዲሁም ‘መንገዱን እንዲያነጻና በቃሉ መሠረት እንዲኖር’ ሊረዳው ይችላል።—ያዕቆብ 5:13-15
6. ‘መንገዳቸውን ያነጹትና በአምላክ ቃል መሠረት የኖሩት’ ሴቶች እነማን ናቸው?
6 ረዓብና ሩት የኖሩት መዝሙር 119 ከመቀናበሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም እንኳ ‘መንገዳቸውን አንጽተው’ ነበር። ረዓብ ከነዓናዊት ጋለሞታ ነበረች፤ ሆኖም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበራት የምትታወቀው የእርሱ አምላኪ በመሆኗ ነው። (ዕብራውያን 11:30, 31) ሞዓባዊቷ ሩት አማልክቶቿን ትታ ይሖዋን ማገልገል የጀመረች ከመሆኑም ሌላ ለእስራኤላውያን የተሰጣቸውን ሕግ አክብራ ኖራለች። (ሩት 1:14-17፤ 4:9-13) እነዚህ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሁለት ሴቶች ‘በአምላክ ቃል መሠረት የኖሩ’ ከመሆኑም በተጨማሪ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያቶች የመሆን ግሩም መብት አግኝተዋል።—ማቴዎስ 1:1, 4-6
7. መንፈሳዊ ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ ዳንኤልና ሌሎች ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ የተዉት እንዴት ነው?
7 “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም” ወጣቶች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ እንኳ ንጹሕ መንገድ መከተል ይችላሉ። (ዘፍጥረት 8:21፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ዳንኤልና ሌሎች ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ባቢሎን ውስጥ በስደት እያሉ ‘በአምላክ ቃል መሠረት ኖረዋል።’ ለምሳሌ ያህል፣ ‘በንጉሡ ምግብ’ ላለመርከስ ጥንቃቄ አድርገዋል። (ዳንኤል 1:6-10) ባቢሎናውያን የሙሴ ሕግ የሚከለክላቸውን ርኩስ እንስሳት ይበሉ ነበር። (ዘሌዋውያን 11:1-31፤ 20:24-26) እንዲሁም እንስሳ ካረዱ በኋላ ደሙን የማፍሰስ ልማድ አልነበራቸውም፤ ሥጋውን ከነደሙ መብላት ደግሞ አምላክ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ መጣስ ይሆናል። (ዘፍጥረት 9:3, 4) አራቱ ዕብራውያን የንጉሡን ምግብ መብላት አለመፈለጋቸው ምንም አያስገርምም! እነዚህ አምላክን የሚፈሩ ወጣቶች መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን በመጠበቅ ግሩም ምሳሌ ትተዋል።
የአምላክ ቃል ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል
8. የአምላክን ሕግ ለመረዳትና በሥራ ለማዋል ምን ዓይነት ዝንባሌና እውቀት ያስፈልገናል?
8 ለአምላክ ቃል ፍቅር ማሳደር ለይሖዋ ታማኝ እንድንሆን በማስቻል ረገድ ወሳኝ ነገር ነው። (መዝሙር 119:17-24) በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን መዝሙራዊ የምንመስል ከሆነ የአምላክን ሕግ ‘ድንቅ ነገር’ ለመረዳት ጉጉት ይኖረናል። ‘ዘወትር ደንቡን የምንናፍቅ’ ከመሆኑም በተጨማሪ ‘በምስክርነቱ ደስ እንሰኛለን።’ (መዝሙር 119:18, 20, 24) ታዲያ ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም እንኳ ‘ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት መመኘት’ ጀምረናል? (1 ጴጥሮስ 2:1, 2) የአምላክን ሕግ መረዳትና በሥራ ማዋል እንድንችል መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማወቅ ይኖርብናል።
9. በአምላክ ሕግና በሰዎች ትእዛዝ መካከል ቅራኔ ቢፈጠር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
9 የአምላክን ምስክርነት ማለትም ማሳሰቢያ የምንወድ ቢሆንም “ገዦች” በሆነ ምክንያት ቢዶልቱብንስ? (መዝሙር 119:23, 24) በዘመናችን፣ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ከአምላክ ሕግ ይልቅ የሰውን ሕግ እንድናስቀድም ለማስገደድ ብዙ ጊዜ ይሞክራሉ። በሰዎች ትእዛዝና በአምላክ ሕግ መካከል ቅራኔ ቢፈጠር ምን እናደርጋለን? ለአምላክ ቃል ያለን ፍቅር ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። ስደት ደርሶባቸው እንደነበሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ሁሉ እኛም “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” እንላለን።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
10, 11. በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ለይሖዋ ታማኝ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
10 በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንችላለን። (መዝሙር 119:25-32) ለአምላክ ታማኝ ሆኖ በመኖር ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን ለመማር ፈቃደኞች መሆንና ይሖዋ እንዲያስተምረን ከልብ መጸለይ ይኖርብናል። እንዲሁም “የእውነትን [“የታማኝነትን፣” NW] መንገድ” መምረጥ ይኖርብናል።—መዝሙር 119:26, 30
11 መዝሙር 119ን እንደጻፈ የሚታሰበው ሕዝቅያስ ‘የታማኝነትን መንገድ’ መርጧል። በሐሰት አምላኪዎች ተከብቦና የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ያሾፉበት የነበረ ቢሆንም ከመንገዱ አልወጣም። ከነበረበት ሁኔታ አንጻር ‘ነፍሱ በሐዘን እንቅልፍ አጥታ’ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 119:28 NW) ሆኖም ሕዝቅያስ በአምላክ የሚታመን ጥሩ ንጉሥ ነበር፤ ደግሞም “በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር” አድርጓል። (2 ነገሥት 18:1-5) እኛም በአምላክ በመታመን ፈተናዎችን በጽናት ማለፍና ለአምላክ ታማኝ ሆነን መኖር እንችላለን።—ያዕቆብ 1:5-8
የይሖዋ ቃል ድፍረት ይሰጣል
12. መዝሙር 119:36, 37ን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
12 የአምላክ ቃል የያዘውን መመሪያ መከተል በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን መከራዎች የምንቋቋምበት ድፍረት ይሰጠናል። (መዝሙር 119:33-40) ሕጉን ‘በፍጹም ልባችን’ መታዘዝ እንድንችል የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት በትሕትና እንጣጣራለን። (መዝሙር 119:33, 34) ተገቢ ያልሆነን ጥቅም በተመለከተ እኛም እንደ መዝሙራዊው “ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል” ብለን አምላክን እንለምናለን። (መዝሙር 119:36) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም “በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር” እንጥራለን። (ዕብራውያን 13:18) አሠሪያችን ሐቀኝነት የጎደለው ነገር እንድናደርግ ቢጠይቀን በድፍረት የአምላክን መመሪያ እንከተላለን። ይሖዋ ምንጊዜም እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ይባርካል። እንዲያውም መጥፎ ምኞቶቻችንን ሁሉ መቆጣጠር እንድንችል ይረዳናል። ስለዚህ “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” ብለን እንጸልይ። (መዝሙር 119:37) አምላክ የሚጠላውን ከንቱ ነገር ጠቃሚ እንደሆነ አድርገን ማየት አንፈልግም። (መዝሙር 97:10) እንዲህ ብለን መጸለያችን ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ወሲባዊ ሥዕሎችንና መናፍስታዊ ተግባሮችን እንድንርቅ ያነሳሳናል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8
13. ስደት ይደርስባቸው የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያለፍርሃት ለመመሥከር የሚያስችላቸውን ድፍረት ያገኙት እንዴት ነው?
13 የአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት በድፍረት እንድንመሠክር ልበ ሙሉ ያደርገናል። (መዝሙር 119:41-48) ደግሞም ‘ለሚሰድቡን መልስ ለመስጠት’ ድፍረት ያስፈልገናል። (መዝሙር 119:42) አንዳንድ ጊዜ፣ ስደት ሲደርስባቸው “ጌታ ሆይ፤ . . . ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው” ብለው እንደጸለዩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልንሆን እንችላለን። ለጸሎታቸው ያገኙት መልስ ምን ነበር? “ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።” በተመሳሳይ ለእኛም ልዑል ጌታ ቃሉን ሳንፈራ እንድንናገር የሚያስችል ድፍረት ይሰጠናል።—የሐዋርያት ሥራ 4:24-31
14. ጳውሎስ እንዳደረገው በድፍረት እንድንመሠክር የሚረዳን ምንድን ነው?
14 “የእውነትን ቃል” በአድናቆት የምንመለከትና ‘የአምላክን ሕግ ዘወትር የምንጠብቅ’ ከሆነ ምንም ሳናፍር እንድንመሠክር የሚያስችል ድፍረት ይኖረናል። (መዝሙር 119:43, 44) በጽሑፍ የሠፈረውን የአምላክ ቃል በትጋት ማጥናታችን ‘ምስክርነቱን በነገሥታት ፊት እንድንናገር’ ያስታጥቀናል። (መዝሙር 119:46) ከዚህ በተጨማሪ ጸሎትና የይሖዋ መንፈስ ትክክለኛውን ነገር በተገቢው መንገድ እንድንናገር ይረዱናል። (ማቴዎስ 10:16–20፤ ቈላስይስ 4:6) ጳውሎስ የአምላክን ማሳሰቢያዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ገዥዎች በድፍረት ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ለሮማዊው ገዥ ለፊልክስ የመሠከረ ሲሆን እርሱም ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳምጦታል።’ (የሐዋርያት ሥራ 24:24, 25) ከዚህ በተጨማሪ ጳውሎስ በአገረ ገዥው ፊስጦስና በንጉሥ አግሪጳ ፊት ምሥክርነት ሰጥቷል። (የሐዋርያት ሥራ 25:22 እስከ 26:32) እኛም በይሖዋ እርዳታ ‘በወንጌል ሳናፍር’ በድፍረት መመሥከር እንችላለን።—ሮሜ 1:16
የአምላክ ቃል መጽናኛ ይሰጠናል
15. ሌሎች ሲሳለቁብን የአምላክ ቃል መጽናኛ ሊሰጠን የሚችለው እንዴት ነው?
15 የይሖዋ ቃል አስተማማኝ መጽናኛ ይዟል። (መዝሙር 119:49-56) መጽናኛ ለማግኘት በጣም የምንፈልግበት ጊዜ ይኖራል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በድፍረት የምንናገር ቢሆንም “እብሪተኞች” ማለትም አምላክን የሚዳፈሩ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ‘እጅግ ይሣለቁብናል።’ (መዝሙር 119:51) ይሁን እንጂ በምንጸልይበት ወቅት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ ገንቢ ነገሮችን ልናስታውስና ‘መጽናኛ’ ልናገኝ እንችላለን። (መዝሙር 119:52) ምልጃ እያቀረብን ባለበት ወቅት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት ልናስታውስና ከጭንቀታችን ልንጽናና ወይም ድፍረት ልናገኝ እንችላለን።
16. የአምላክ አገልጋዮች ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ ምን አላደረጉም?
16 በመዝሙራዊው ላይ የተሳለቁበት እብሪተኞች ለአምላክ የተወሰነ ብሔር አባላት የነበሩ እስራኤላውያን ናቸው። እንዲህ ማድረጋቸው እጅግ አሳፋሪ ነው! እኛ ግን ከእነርሱ በተቃራኒ ከአምላክ ሕግ ንቅንቅ ላለማለት ቁጥር ውሳኔ እናድርግ። (መዝሙር 119:51) በሺዎች የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች ናዚ ካደረሰባቸው ስደት በተጨማሪ ለበርካታ ዓመታት ተመሳሳይ እንግልት ቢያጋጥማቸውም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመጣስ ፈቃደኛ አልሆኑም። (ዮሐንስ 15:18-21) ደግሞም የይሖዋ ሥርዓት መንፈስ እንደሚያድስ መዝሙር ስለሆነ እርሱን መታዘዝ ሸክም አይደለም።—መዝሙር 119:54፤ 1 ዮሐንስ 5:3
ለይሖዋ ቃል አመስጋኝ ሁኑ
17. ለአምላክ ቃል ያለን አድናቆት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
17 የአምላክን ቃል በመታዘዝ ለቃሉ አመስጋኝ መሆናችንን እናሳያለን። (መዝሙር 119:57-64) መዝሙራዊው ‘የይሖዋን ቃል ለመታዘዝ ቈርጧል፤’ ከዚህም ሌላ ‘ስለ ጻድቅ ሥርዓቱ በእኩለ ሌሊት አምላክን ለማመስገን ተነስቷል።’ ሌሊት ላይ ከእንቅልፋችን ብንነቃ ይህ በጸሎት አምላክን ለማመስገን የሚያስችለን ግሩም አጋጣሚ ነው! (መዝሙር 119:57, 62) ለአምላክ ቃል ያለን አድናቆት መለኮታዊ ትምህርት ለማግኘት እንድንጣጣር የሚያነሳሳን ከመሆኑም ሌላ ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት ለሚያሳዩ ሰዎች ማለትም ‘ይሖዋን ለሚፈሩት ባልንጀራ’ እንድንሆን ያስችለናል። (መዝሙር 119:63, 64) በምድር ላይ ከዚህ የተሻለ ባልንጀርነት ማን ሊያገኝ ይችላል?
18. ይሖዋ ‘የክፉዎች ገመድ ሲተበተብብን’ ለምናቀርበው ጸሎት መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?
18 በሙሉ ልባችን መጸለያችንና ይሖዋ እንዲያስተምረን በትሕትና መጠየቃችን ሞገሱን ለማግኘት ‘ፊቱን እንደምንፈልግ’ ያሳያል። በተለይ ‘የክፉዎች ገመድ ሲተበተብብን’ መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:58, 61) ይሖዋ ጠላት እኛን ለማሠር የሚጠቀምበትን ገመድ በጥሶ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንቀጥል ነጻ ሊያደርገን ይችላል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይህ ሁኔታ ሥራችን ታግዶ በነበረባቸው አገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል።
በአምላክ ቃል ላይ እምነት ይኑራችሁ
19, 20. በመከራ ውስጥ ማለፍ መልካም የሚሆንልን እንዴት ነው?
19 በአምላክና በቃሉ ላይ ያለን እምነት መከራን ችለን እንድናሳልፍና ፈቃዱን እንድናደርግ ይረዳናል። (መዝሙር 119:65-72) ምንም እንኳ እብሪተኞች ‘ስሙን በሐሰት ቢያጠፉም’ መዝሙራዊው “በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:66, 69, 71) ለአንድ የይሖዋ አገልጋይ መከራ መልካም ነገር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
20 መከራ ሲደርስብን ወደ ይሖዋ አጥብቀን እንደምንጸልይ የታወቀ ነው፤ ይህ ደግሞ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ያስችለናል። በጽሑፍ የሠፈረውን የአምላክን ቃል በማጥናት ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ ልናሳልፍና በሥራ ለማዋል የበለጠ ጥረት ልናደርግ እንችል ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ሕይወታችንን ይበልጥ አስደሳች ያደርግልናል። ሆኖም መከራ ሲደርስብን የምንሰጠው ምላሽ እንደ ትዕግሥት ማጣትና ኩራት የመሳሰሉ መጥፎ ባሕርያት እንዳሉብን ቢያሳይስ? ልባዊ ጸሎት በማቅረብ እንዲሁም ከአምላክ ቃልና መንፈስ በምናገኘው እርዳታ እንዲህ ዓይነት ድክመቶችን ማሸነፍና ይበልጥ በተሟላ መልኩ ‘አዲሱን ሰው መልበስ’ እንችላለን። (ቈላስይስ 3:9-14) ከዚህ በተጨማሪ የሚደርስብንን መከራ ችለን ስናሳልፍ እምነታችን ይጠናከራል። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) ጳውሎስ የደረሰበት መከራ ይበልጥ በይሖዋ እንዲታመን ስላስቻለው ጥቅም አግኝቶበታል። (2 ቆሮንቶስ 1:8-10) እኛስ መከራ በሕይወታችን ውስጥ በጎ ውጤት እንዲያመጣ እንፈቅዳለን?
ምንጊዜም በይሖዋ ታመኑ
21. አምላክ እብሪተኞችን ለእፍረት ሲዳርጋቸው ምን ይፈጸማል?
21 የአምላክ ቃል በይሖዋ እንድንታመን የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ይሰጠናል። (መዝሙር 119:73-80) በእርግጥ በፈጣሪያችን የምንታመን ከሆነ የምናፍርበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ይሁንና ሌሎች ከሚያደርጉት ነገር የተነሳ መጽናኛ ሊያስፈልገንና “እብሪተኞች . . . ይፈሩ” ብለን ለመጸለይ እንገፋፋ ይሆናል። (መዝሙር 119:76-78) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ለእፍረት ሲዳርጋቸው ክፉ መንገዳቸው ይጋለጣል፤ ቅዱስ ስሙም ይባረካል። የአምላክን ሕዝቦች የሚያሳድዱ ሰዎች ፈጽሞ እንደማይሳካላቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በፍጹም ልባቸው በአምላክ የሚታመኑትን የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ በፊት ማጥፋት አልቻሉም፤ ወደፊትም አያጠፉም።—ምሳሌ 3:5, 6
22. መዝሙራዊው ‘ጢስ የጠጣ የወይን አቊማዳ የመሰለው’ በምን መንገድ ነው?
22 ስደት ሲደርስብን የአምላክ ቃል በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። (መዝሙር 119:81-88) መዝሙራዊው እብሪተኞች ያሳድዱት ስለነበረ ‘ጢስ የጠጣ የወይን አቊማዳ እንደመሰለ’ ተሰምቶት ነበር። (መዝሙር 119:83, 86) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የእንስሳት ቆዳ በመጠቀም ውኃ፣ ወይንና ሌሎች ፈሳሾች ለማስቀመጥ የሚያገለግል አቁማዳ ይሠራ ነበር። ምንም ነገር ያልያዘ አቁማዳ ጭስ ማውጫ በሌለበት ክፍል ውስጥ እሳት አጠገብ ከተንጠለጠለ ኩርምት ሊል ይችላል። ከደረሰባችሁ መከራ ወይም ስደት የተነሳ ‘ጢስ የጠጣ የወይን አቊማዳ’ እንደሆናችሁ የተሰማችሁ ወቅት አለ? እንዲህ ዓይነት ነገር ካጋጠማችሁ በይሖዋ ታመኑ እንዲሁም “እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ” ብላችሁ ጸልዩ።—መዝሙር 119:88
23. በመዝሙር 119:1-88 ላይ ባደረግነው ጥናት ምን ተመልክተናል? መዝሙር 119:89-176ን ከማጥናታችን በፊት ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?
23 በመዝሙር 119 የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል ላይ የተመለከትናቸው ነገሮች አገልጋዮቹ በቃሉ ስለሚታመኑ እንዲሁም ሥርዓቶቹን፣ ማሳሰቢያዎቹን፣ ትእዛዛቱንና ሕግጋቱን ስለሚወድዱ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያሳያቸው ይገልጻሉ። (መዝሙር 119:16, 47, 64, 70, 77, 88) ለእርሱ ያደሩ አገልጋዮቹ በቃሉ መሠረት ስለሚኖሩ ይደሰታል። (መዝሙር 119:9, 17, 41, 42) የዚህን ግሩም መዝሙር ቀሪ ክፍል ለማጥናት በጉጉት ስትጠባበቅ ‘የይሖዋ ቃል በእርግጥ ለመንገዴ ብርሃን እንዲሆን ፈቃደኛ ነኝ?’ ብለህ መጠየቅህ ተገቢ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአምላክ ቃል የሆነው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የይሖዋ መልእክት ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• እውነተኛ ደስታ በምን ላይ የተመካ ነው?
• የይሖዋ ቃል በመንፈሳዊ ንጹሕ እንድንሆን የሚያስችለን እንዴት ነው?
• የአምላክ ቃል ድፍረትና መጽናኛ የሚሰጠን በምን መንገዶች ነው?
• በይሖዋና በቃሉ ላይ እምነት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት፣ ረዓብና ባቢሎን ውስጥ በስደት የነበሩት ዕብራውያን ‘በአምላክ ቃል መሠረት ኖረዋል’
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ ‘ስለ አምላክ ምስክርነት በነገሥታት ፊት’ በድፍረት ተናግሯል